ረቡዕ 2 ሴፕቴምበር 2020

ዘጠና ቀናት በአዲስ አበባ፣ ተጻፈ በመዘምር ግርማ

 ዘጠና ቀናት በአዲስ አበባ

ተጻፈ በመዘምር ግርማ

ከሰኔ 1፣  2012 እስከ ነሐሴ 30፣ 2012 በአዲስ አበባ ስላደረኩት ቆይታ አንዳንድ ነገሮች

ሀ. ሰኔ 1፣ 2012 ዓ.ም. ከደብረ ብርሃን ከሞቀ ቤቴ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ አነስተኛ የመኖሪያ ቤት ተከራይቼ ሁቱትሲን አሳትሜ ማከፋፈል ጀመርኩ።

ለ. ሁቱትሲ የሩዋንዳዊቷ የኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ የዘር ማጥፋት ወቅት ማስታወሻ የ Left to Tell የአማርኛ ትርጉም ነች። 

ሐ. በ2008 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዕትሟን ሳወጣ 62,000 ብር ለማተሚያ ቤት ከፍዬ ነበር። መጽሐፉ ተከፋፍሎ ገንዘቡ በወቅቱ ስላልተሰበሰበ ደግሜ ለማሳተም የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት አራት ዓመታት ፈጅቶብኛል።

መ. ይህም የሆነው ከመጽሐፉ ሕትመት በኋላ በደብረብርሃን የከፈትኩት ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ወጪ ስለሚያስወጣኝ ነው።

ሠ. እንደ መምህርነቴ ከመጋቢት መጀመሪያ እስከ ግንቦት መጨረሻ በኮቪድ ምክንያት እረፍት ላይ ስለነበርኩ በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት በአስነባቢነት ሰርቻለሁ። ይህም የሆነው አስነባቢዎቹ በበሽታው ምክንያት ከስራቸው ስለለቀቁና ገጠር ስለገቡ ነው። ከሰኔ እስከአሁን አዲስ አስነባቢ ስላገኘሁ በሷ መኖር ምክንያት ነው አዲስ አበባ ልቀመጥ መቻሌ።

ረ. በጥቅሉ መጽሐፏ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ዕትም 20,000 ኮፒ የተሸጠች ሲሆን፤ ይህም በቀን በአማካይ 222 መጽሐፍ እንደተሸጠ ያሳያል።

ሰ. መጀመሪያውኑ በክረምትና በኮቪድን መምጣት ምክንያት አንባቢያን መጽሐፏን ይፈልጋሉ የሚል ሐሳብ ስለመጣልኝ ወደ ህትመቱ ሥራ ገብቻለሁ። 

ሸ. ሥራው ብዙ ውጣውረድ ያለው ሲሆን ወደ ተስፋ ማስቆረጥ ደጅም አድርሶ ይመልሳል። ቢሆንም የመጻሕፍት ማሳተምና ማከፋፈልን ሥራ ከታች በመጀመር ላውቅበት ችያለሁ። በአሁኑ ወቅት ሁለት የሌሎች ደራሲያንን ሥራዎች በአሳታሚነት ወደ ማተሚያ ቤት አስገብቻለሁ። ይህም እነዚህ ሦስት ወራት የሥራ ፈጠራ ሕይወቴን እንዴት እንደቀየሩት ለማየት ይቻላል።

ቀ. ማህበራዊ ሚዲያ፣ ዋናው ሚዲያና ብዙ ወዳጆቼ ለመጽሐፏ መሰራጨት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ከነዚህም ውስጥ አማራ ቴሌቪዥን፣ ሠይፉ በኢቢኤስ፣ አልዐይን አማርኛ፣ ፀደይ ኤፍኤም 102.9፣ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ፣ Meet EBC (ተፈራ ገዳሙ) እና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው።

በ. አሁን የሚቀረን በመጽሐፉ ላይ መወያየትና ለሃገራችን የዘር ተኮር ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ መሞከር ነው።

ተ. ከመጽሐፉ ሽያጭ ከተገኘው ትርፍ ባለፈው ወር ለሦስት የሰኔ 2012 የዘርና የኃይማኖት ጥቃት ሰለባዎች 30,000 ብር ድጋፍ ተደርጓል። ከሰሞኑም ለአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ትምህርት ቢሮዎች በስራቸው ለሚገኙ አብያተ መጻሕፍት የ60,000 ብር የሁቱትሲ መጻሕፍት ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። 

ቸ. ከሚያዝያ 27፣ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቀን አንድ ጊዜ (ጠዋት ብቻ) ተመጋቢ በመሆኔ በረሃብ አንጀቴ እንደምሰራ ሊታሰብም ይችላል። ክብደቴ አስር ኪሎግራም ያህል ቀንሷል። 

እስኪ የጋራ ጉዟችንን እንወያይበት።

ሁላችሁንም አመሠግናለሁ።

አንዲት ነገር ይፈቀድልኝ።

ደብረብርሃንን በጣም እንደምወዳት ስርቃት ገባኝ። እናም ከመስከረም 2013 ጀምሮ ወደ ደብረብርሃኑ ቤቴ በመመለስ የማሳተምና የማከፋፈል ሥራውን ከዚያ እየተመላለስኩ ወይም ሥራ አስኪያጅ ቀጥሬ እሠራለሁ/አሰራለሁ።

ሌላ ዋና ነገር

ሞትን ንቄው እንደከረምኩ ይሰማኛል። አዲስ አበባን ሲዞር የዋለ ብር ከየመጻሕፍት አዟሪውና መደብሩ እኔ ጋ ቢመጣም ለኮቪድ የነበረኝ ጥንቃቄ ዜሮ ነበር። ሰኔ አንድ የገዛሁት ሳኒታይዘር አሁንም አለ። ይህ ከኔ የሚጠበቅ ነገር ባይሆንም መጠንቀቁ ስለሰለቸኝ ነው።  በማናቸውም ደቂቃ ልወድቅና በዚያው ልቀር እንደምንችል ወይም በተኛሁበት ላሸልብ እንደምችል እየተሰማኝ ሦስት ወር ቆየሁ። ዘጠና ቀናት በሩዋንዳ የነገሰው ሞት በአዲስ አበባም በኮሮና ወረርሽኝ መልክ ማንዣበቡን እሰማለሁ። ይሁን እንጂ ሳይነካኝ ወደ ደብረብርሃን ልመለስ እንደሆነ ይመስለኛል።

አምስተኛው ዕትምስ?

አይ ቆይ፣ ለማተሚያ ቤት ልጆችም እናስብ! ዓመት በዓሉን አረፍ ይበሉና ከበዓል በኋላ ያትሙታል። እስከዚያው መጽሐፉን የገዛን ሰዎች እየተዋዋስን እናንብብ።

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...