ዓርብ 24 ጁን 2022

ዓለም ወደፊት እኛ ግን ወደኋላ

 



ከመቼውም ጊዜ በላይ በዚህ ክፍለዘመን ዓለም በቴክኖሎጂ ውጤቶችና በስልጣኔ አስተሳሰብ እየተሳሰረችና አንድ መንደር እየሆነች ነው፡፡ የሰዎች ተንቀሳቅሶ የመስራትና የመኖር ዕድል እየሰፋ ነው፡፡ ምን ይህ ብቻ! ባሉበትም ሆኖ ከሌላው የዓለም ክፍል ጋር ትስስር ማድረግና እቤትዎም ቁጭ ብለው በሌላው ዓለም ለሚገኝ ድርጅት የመስራት ዕድልዎ ሰፍቷል፡፡ ራሱን ከዓለም አጥሮና ዜጎቹን ዕድል ነፍጎ ለአስርት ዓመታት ለኖረ አገር ይህ በደንብ ባይገባውም፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ኢትዮጵያ ካለ የትስስርና የእንቅስቃሴ ዕድሎች ከተቆላለፉበት አገርም የሚወጣው ከሚገመተው በላይ ነው፡፡ የማያስገባ ቢሆንም ጥሶ የሚወጣበት ብዙ ነው፡፡

በእርግጥ ይህን ጉዳይ ልናይ የሚገባን ከአንዱ የዓለም ክፍል ወደ ሌላው ያለው ልዩነትና አንድነት ምን ይመስላል የሚለውን በማጤን ነው፡፡ አሁን ሰዎች ከምንጊዜውም በላይ የዓለም ዜጎች ነን ብለው ስለሚያምኑ እራሳቸውን በአንድ ኃይማኖት፣ ብሔር ወይም የሙያ ማህበር የመግለጣቸውና በዚያም የመመካት ዕድላቸው እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በስብስቦች የመርካትና የመመካት ዕድል ቀንሷል፡፡ በአሜሪካ የሚታየው ይህ ነው፡፡ በ1999 እ.ኤ.አ. 70 በመቶ አሜሪካውያን የኃይማኖት ተቋም አባል ነን ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ይህ አሐዝ  ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በ2018 ወደ 50 በመቶ ወርዷል፡፡ ይባስ ብሎ በ2020 ወደ 47 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡ ዛሬ ከሁለት ዓመት በኋላ ይህ ቁጥር የት ደርሶ ይሆን? የሙያ ማህበራትን የማደግ ሁኔታ ባጠና አንድ ጥናት እንደታየውም 68 በመቶ ድርጅቶች የማደግ ዕድል አጥተናል ብለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 11 በመቶዎቹ ከነጭራሹ ጠፍተዋል፡፡ 25 በመቶዎቹ ደግሞ አላደጉም፡፡ 32 በመቶዎቹ ደግሞ 1-5 በመቶ ብቻ ነው ለማደግ የቻሉት፡፡ በማንነት ላይ የተመሰረቱ ማህበራትም ቢሆኑ የአባልነታቸው ሁኔታ ተቀዛቅዟል፡፡ በአጠቃላይ በማናቸውም ዓይነት ስብስብ ወይም ማህበር ባለፉት የተወሰኑ አስርት ዓመታት አባልነት በአማካይ ከሩብ በላይ ቀንሷል፡፡ በአንዳንድ ልዩ ሁኔታዎችና ለማንነት ትልቅ ግምት በሚሰጥባቸው ከመካከለኛው ዘመን ፈቅ ባላለ አስተሳሰብ ላይ ባሉ አገራትና ዝግ ማህበረሰቦች ግን የዚህ ተቃራኒው ይስተዋላል፡፡ በተለይ አውሮፓ በዘር የመከፋፈል ባህሉን ወደ አፍሪካ በማራገፍ ራሱ መሆን ባለበት ጎዳና እየሄደ ነው፡፡ ከእነዚህ ሰለባዎች አንዷ የኛዋ ኢትዮጵያ ለመሆኗ ጥርጥር የለውም፡፡ ለዚህም ቀጥሎ የተመለከተውን አብነት እንይ፡፡

ዓለም ራሱን በስልጣኔ ጎዳና እየመራ ነው፡፡ በዚህ ዘመን መደረስ የሚቻልበትን እያሳየን ነው፡፡ ይህን የሰውነት ደረጃና የመሰባሰብን ጣጣ የመተው ልክ ያመጣው የስልጣኔ ትሩፋት ለእኛም ደርሷል፡፡ በአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም በሌሎች አህጉራት ያለው የቴክኖሎጂ ውጤት በማግስቱ እኛም ጋ በሚገባበት በዚህ ዘመን እኛ የምንሸርበው ሕይወታችንን የሚያቀል ሳይሆን ችግርን የሚያባብስ ነገር ነው፡፡ በችግር ላይ ችግር የሚደራርቡ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃን፣ ነጋዴዎች፣ ምሁራን ወዘተ በየቀኑ እየፈሉ አገሪቱ ከድጡ ወደማጡ እያመራች ትገኛለች፡፡ የእኛ አገርና አህጉር  ከመቼውም በዘለለ በዘረኝነት አባዜ ተጠምዷል፡፡ በኢትዮጵያ የዘር ጥቃትን፣ ግድያንና ዘርተኮር እንቅስቃሴዎችን መስማት ዋል አደር ብሏል፡፡ በሰላምም ሆነ በችግር ጊዜ የሚታሰበው በዘር ነው፡፡ አገሪቱን ሰቅዞ የያዘው አሰቃቂ የግድያ ዜናና ዘመቻ ወሬ ለአንድ ሳምንት አልለቀቀንም፡፡ በዚህ ዝቅጠት ውስጥ ሆነንም አሁንም የዘር አባዜ አይለቀንም፡፡ በዚያው ላይ ኃይማኖት እንጨምርበታለን፡፡ አካባቢያዊነትም አለ፡፡ የመከፋፈያ መንገዱ የትየለሌ ነው፡፡ እንደ አገር ይህን ለማስቆምና የተሻለና በሰውነት የምንንቀሳቀስበትን ዕድል ለመፍጠር አንፈልግም፡፡ ከ1500 በላይ አማሮች በወለጋ በግፍ በተጨፈጨፉበት በዚህ ሳምንትም ከዚህ አባዜ ለመውጣት የምትፈልግ ሳይሆን የዘር አዙሪቷ ውስጥ የምትባትል አገር ውስጥ ነን፡፡ በአጠቃላይ የኋሊት ጉዞውን ተያይዘነዋል፡፡ መድረሻችን አይታወቅም፡፡ መፍትሔ ያለው ዜጋ ካለ አሁኑኑ ያንን መፍትሔ ቢሻ ውድመቱን በተወሰነ መጠን ሊቀንሰው ይችላል፡፡ እንጂማ የታቀደልንን የጥፋት መጠን መገንዘብ ያዳግታል፡፡ በሌላው ዓለም እየቀነሰ የመጣው በቡድን ማሰብና መንቀሳቀስ እዚህ አደገኛ አቅጣጫ የያዘው ለምን ይሆን? አገራዊ፣ ቀጣናዊ ዓለምአቀፋዊ እጆቹ የእማን ይሆኑ?

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...