ጥቁር አሜሪካዊቷ ዲሻንታል ለዓመታት ‹‹ትምህርት ቤቴን አየህልኝ ወይ?›› በማለት ስትጠይቀኝ ከቆየች በኋላ ከፌስቡክ ጠፍታ ላገኛት አልቻልኩም ነበር፡፡ ይህን ደብዳቤ ልልክላት የቻልኩት እንዴት ላገኛት እችላለሁ ከሚል ብዙ ሃሳብ በኋላ የሆት ሜይል ኢሜሏን አሁን ብዙም ከማልጠቀመው ከያሁ አካውንቴ ማግኘት እንደምችል አስቤ እዚያ ገብቼ አግኝቼው ነው፡፡
‹‹ወደ ጠባሴ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ስላደረኩት ጉዞና ስለበጎፈቃድ ስራሽ ቀጣይነት
ውድ ዲሻንታል፣
ይህ ዓመት እንዴት ይዞሻል? ትምህርት ቤትሽን ከሰባት ዓመታት በኋላ ጎብኝቼዋለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ጊዜ እዚያ አለመሄዴ ፀፅቶኛል፡፡ ትምህርት ቤቱ ጋ እንደደረስኩ በቀጥታ ወደ ትምህርት ማዕከልሽ ነበር ያቀናሁት፡፡ ያ ሲያዩትም ሆነ ውስጡ ሆኖ ሲያጠኑበት በጣም የሚያምረው ማዕከልሽ አሁን እቃዎች እንደነገሩ እዚህም እዚያም የተጣሉበት መጋዘን ሆኗል፡፡ ዝግ ነበር፡፡ ሁለት ዓመት ሙሉ ያን ያህል እንዳለፋሽ! ምን ይህል ሰነፎች እንደሆንን ልገልጽልሽ አልችልም! ከበለጸገው ዓለም ለመማር አእምሯችን ይህን ያህል ዝግ የሆነበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ወደ ትምህርት ቤቱ የሄድኩት የራሴን የሠላም ጓድ - የአማራ የሠላም ጓድ ልጀምር ስላሰብኩ ነው፡፡ እስካሁን የሠላም ጓዶች ተመድበው ይሰሩ የነበሩባቸውን የተወሰኑ ጣቢያዎችን ጎብኝቻለሁ፡፡ ትምህርት ቤትሽን ከጎበኘሁ በኋላ ከፕሮጀክቶችሽ አንዱን መልሼ አነቃቅቼዋለሁ፡፡ ከስድስተኛና ሰባተኛ ክፍሎች ስድስት ሴክሽኖች ከእያንዳንዳቸው በእንግሊዝኛ ዝቅተኛ ውጤት ያላቸውን አምስት አምስት ተማሪዎች መምህራን መርጠውልኝ የእንግሊዝኛ ሥልጠና እየሰጠኋቸው ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ የማይክንም ፕሮጀክት ‹ማይክ ምገባ›ን አነቃችቼው ተማሪዎቹን ሳስተምር እየመገብኳቸው ነው፡፡ ትምህርቱ ለሃያ ሰዓታት ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አድርጌያለሁ፡፡ (በነገራችን ላይ ሥልጠናው ትናንት አስረኛ ሰዓቱን ይዟል፤ ልጆቹም እንግሊዝኛን እየወደዱ ሲሆን፤ አብዛኞቹም በማጠቃለያ ፈተናውም ውጤታቸው መሻሻሉን በነበረን ግምገማ ተናግረዋል፡፡) በትምህርት ቤቱ ያገኘኋቸው የሚያውቁሽ ሁሉ ላንቺ ሰላምታና ምስጋናቸውን እንዳደርስላቸው ጠይቀውኛል! ስለአገልግሎትሽ በእጅጉ እናመሰግናለን፡፡ ከዚህ በታች ከጉብኝቱ በኋላ ጽፌ በብሎጌ የለጠፍኩት ጉብኝቱንና የፕሮጀክትሽን ቀጣይነት ጉዳይ የተመለከተ ጽሑፍ የሚገኝበት አድራሻ አለ፡፡ በአማርኛ ስለሆነ በጉግል ተርጉመሽ እንደምታነቢው ተስፋ አደርጋሁ፡፡
ከሰላምታ ጋር፣
ተጨማሪ፣
እስኪ እባክሽ በደብረብርሃን የነበሩሽን ፕሮጀክቶች መግለጫና በሠላም ጓድ ሦስት ወር የሰለጠንሽበትን ሰነድ ላኪልኝ፡፡ ምንም ነገር ቢሆን ይጠቅመኛል፡፡››
ጁን 19፣ 2022
‹‹ሰላም መዘምር!
ካንተ ይህ መልዕክት ስለደረሰኝ በጣም ደስ ብሎኛል! እኔ በጣም ደህና ነኝ፡፡ በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ነገር ተቀይሯል፡፡ አግብቼ ከዘጠኝ ወር በፊት ሴት ልጅ ተገላግያለሁ፡፡ በጣም የምታምርና በሕይወቴ ከተከሰቱት መልካም ነገሮች ሁሉ የመጀመሪያዋ ነች፡፡ (ይህን ሳነብ የተሰማኝ - ‹አይ ጭምት! የታገሰ ሰው መጨረሻው ማማሩ አይቀርም! እንደተመኘሽው ናይጀሪያዊ ባል አግኝተሸ ይሆናል፡፡ በሰላሳዎቹ ዕድሜሽ መጨረሻ ልጅ መውለድሽ ሰዓትሽን በትክክል ለመጠቀም መወሰንሽን ያሳያል፡፡ ይህን ደስታ ቀድሜ ባጣጥመው ብለሽ ተቆጭተሽም ይሆናል፡፡) እንዲያው እንዴት ነህ? በብሎግህ ያወጣኸውን ጽሑፍ አነበብኩት፡፡ በጠባሴ መድኃኔዓለም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሰራሁት ስራ ለሰጠኸኝ እውቅና አድናቆት አለኝ፡፡ ፕሮጀክቱን አለማስቀጠላቸውን መስማቱ ያማል፤ ይሁን እንጂ አንተ በውጥኔ ላይ መልሰህ ሕይወት ለመዝራትና ከዓለምአቀፍ ድርጅቶች ነጻ የሆነና ራሱን የቻለ መርሐግብር ለመቅረጽ መወሰንህ ባያሌው የሚደነቅ ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ማዕከሉ መክሰሙ አልደነቀኝም፡፡ ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ልባዊ አቀባበል ፈጽሞ አግኝቼበት አላውቅም፤ መምህራንንና ተማሪዎችን ማዕከሉን እንዲጠቀሙ መሳብ ከባድ ነበር፤ ስመለስም የአገልግሎት ጊዜዬን ጨራርሼ ወደ አገሬ በመመለስ ጉዳይ ላይ አተኩሬ ስለነበር ኃላፊነቱን አስተማማኝ ለሆነ ሰው በአግባቡ ለማስተላለፍ አልተቻለኝም፡፡ ለጥረትህ እገዛ የሚያደርጉልህን ሰነዶች ከቆዩ የሠላም ጓድ ክምችቶቼ እፈላልጋለሁ፡፡ በዱሮ ትምህርት ቤቴና ከሱም ዉጪ ላሉና የአሜሪካዊት ወዳጃቸውን ቆይታ ይወዱ ለነበሩት ሁሉ ልባዊ ሰላምታዬን አድርስልኝ፡፡ መልካሙን ሁሉ እመኝልሃለሁ፣ ጓደኛዬ፤ በቅርቡ ደግሞ የሰራኸውን ሁሉ ለማየት እንደምጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ዲሻንታል ኮልስ፣
ጁላይ 1፣ 2022
(ትንሽ ማስታወሻ - የአባቷን ስም በባሏ ስም ቀይራለች፡፡ ይህን መልዕክት በማግኘቴ በእጅጉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለበለጠ ስራም ተነቃቅቻለሁ፡፡ )››
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ