ቅዳሜ 20 ኦገስት 2022

የአካባቢ ተወላጆችን እርዱን የሚሉ ተቋማት ሲመጡ

 የአካባቢ ተወላጆችን እርዱን የሚሉ ተቋማት ሲመጡ


በቅርብ ዓመታት ከሣሢት የመንግሥት ተቋማት የእርዳታ ጥሪ አስተላልፈውልኝ ነበር። እናንተም ከተወላችሁበት አካባቢ ወይም ከምትኖሩበት አካባቢ ተመሳሳይ ጥሪዎች ቀርበውላችሁ ያውቁ ይሆናል። በእኔ በኩል ኮቪድ በገባ ጊዜ የሙቀት መለኪያ እንድገዛ፣ ትምህርት ቤቶችን በየወቅቱ እንዳግዝ፣ የወረዳ ተቋማትን እንድደግፍ ወዘተ ጥሪ ቀርቦልኛል። በተቻለኝ መጠን ያገዝኳቸው ወይም ሌሎች እንዲያግዟቸው የጠየኩላቸው ይኖራሉ። ያላገዝኳቸውም እንዲሁ። 

ይህ በዚህ እንዳለ ከሣሢት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2012 የቀረበልኝ ጥሪ ነበር። ለዚህ ጥሪ ምላሽ የተሰጠ አልመሰለኝም። በወቅቱም ሰዎች እንዲያግዟቸው ጠይቄ ነበር፤ አልተሳካም እንጂ። 

ርዕሰመምህሩ ደብረብርሃን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት መጥተው ነበር ደብዳቤውን የሰጡኝ። የመጻሕፍትን እጥረት በተወላጆች ተሳትፎ ለመፍታት መሞከራቸው ጥሩ ነው። የአካባቢውን አቅም አሟጠው መጠቀምም ያለባቸው ይመስለኛል። በወቅቱ ስለትምህርት ቤቱ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ጠይቄያቸው መረጃ ሰጥተውኛል። እነሱም ራሱን የቻለ የቤተመጻሕፍት ሠራተኛ የለም። ቤተመጻሕፍቱ እስከ ሕዳር ዝግ ነበር። ፕላዝማ በመብራት ምክንያት አይሰራም። ኮምፒውተር ሁለት ላብ ቢያስፈልግም አንድ ብቻ ነው ያለው። በብሔራዊ ፈተና ከ400 ተማሪዎች 10ኛ ወደ 11ኛ ያለፉት 100 ብቻ ናቸው። 

ለነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሁሉንም ወገን ጥረት ይጠይቃል። በወቅቱ የተነጋገርናቸው የመፍትሔ ሃሳቦች ቢኖሩም የተወሰነ መጨመር ይቻላል። ለምሳሌ የመብራቱ ጉዳይ አንገብጋቢ በመሆኑ መፍትሔ እንዲያገኝ አስተዳደራዊ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል። ያለዚያ ፕላዝማውም ሆነ ኮምፒውተር ላቡ ጥቅም አይሰጥም ማለት ነው። የቤተመጻሕፍቱ ጉዳይ ሰራተኛ ካልተገኘ በበጎፈቃደኞች ሊሰራ ይገባዋል። ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሰራተኞችና ከተማሪዎች የሰው ኃይል ፍላጎቱን ማሟላት አስፈላጊ ነው። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የሚያልፈውን ተማሪ ቁጥር ለመጨመርና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ያግዛል። ተመሳሳይ ሁኔታዎች በክልሉ ባሉ ሌሎች አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ የሁላችንም ክትትልና እገዛ ያስፈልጋል። አግዙን ብለው ለሚመጡትም ሆነ ሄደን አይተን ክፍተቱን ለይተን ለምናግዛቸው ተቋማት እገዛው ግድ የገንዘብና የቁሳቁስ ሳይሆን የዕውቀት፣ የክህሎት፣ የጊዜና የምክር ሊሆን ይችላል። እስኪ ምን ታዘባችሁ? የአማራ የሠላም ጓድስ ምን ይስራ?



ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...