ተጻፈ ሰኞ 9/1/2015 ዓ.ም. ማለዳ
(ተሳታፊዎች መልሰው ካነበቡት በኋላ የተስተካከለው ቅጂ)
መዘምር ግርማ፣ ደብረብርሃን
ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በአይኦዋ ዩኒቨርሲቲ የአስር ሳምንታት ቆይታ ለማድረግ ወደ አሜሪካ መሄዱን ከማህበራዊ ሚዲያ አንብበናል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ ደራስያንን ከመላው ዓለም አወዳድሮና መርጦ መርሐግብር የማሰናዳት ልምድ አለው፡፡ እንዳለጌታ ከበደ በኢምባሲው በኩል ከአገር ውስጥ እንዲሁም ከዚያ በኋላ በውጪ በተደረገ ውድድር አሸንፎ ነው ወደዚያ ያቀናው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ደራሲው በቴሌግራም መልዕክት ላከልኝ፡፡
በመልዕክቱም ‹‹መዘምር ከቻልክ ተሳተፍ፡፡ በተለይ ስለ ቡክ ባንካችን ›› በማለት የዙም ሊንኩን አያይዞ ነበር፡፡
‹‹በደስታ›› በማለት መለስኩ፡፡
ሰዓቱን 6:00 PM PST የሚለውን ወደ ኢትዮጵያ ሠዓት ስቀይረው ሌሊት 10፡00 ይላል፡፡ እሱም ሌሊት ላይ መሆኑን አላወቀም ነበርና ደንግጦ ‹‹እንቅልፍህን አጥተህ›› ሲል መለሰልኝ፡፡
‹‹ችግር የለውም፡፡ ብዙ ጊዜ ማላጅ ነኝ›› በማለት አስከተልኩ፡፡
‹‹ዛጎል የመጻሕፍት ባንክን ይደግፋሉና ታስፈልገናለህ፡፡ መጻሕፍት የሚሰጠን እያጣን ነው፡፡›› የሚል ሃሳብ ጨመረ፡፡
ዛጎል ቡክ ባንክ ከተመሰረተ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የሆነው ሲሆን ከበጎ አድራጊዎች የሚያገኛቸውን መጻሕፍት የንባብ ባህል ይስፋፋ ዘንድ ለማገዝ በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ አብያተመጻሕፍት ያከፋፍላል፡፡ እስካሁንም ከ35 ሺህ በላይ መጻሕፍትን አዳርሷል፡፡ የተሻለ እንዲሰራ ከተፈለገ የሌሎችም ድጋፍ ስለሚያስፈለገው በባንኩ ዓላማ አፍቃሪዎች የተዘጋጀውን ይህን ዝግጅት ለመታደም በመጋበዜ ዕድለኝነት ተሰማኝ፡፡
ከዚህ ምልልስና ሌሎች ስራዎች በኋላ ስተኛ ከሌሊቱ 7፡00 አልፎ ነበር፡፡ አላርም ሞልቼ የነበረ ቢሆንም ቢጠራም አጥፍቼው ሳይሆን አይቀርም አንድ ሰዓት አሳልፌ 11፡00 ላይ ነቃሁ፡፡ ወዲያውኑ በቁጭት እስኪ ካላለቀ በማለት ወደ ዙም ስብሰባው ገባሁ፡፡ ደግነቱ አላለቀም ነበር፡፡ ተሳታፊዎቹ ውይይቱን አጧጡፈውታል፡፡ አንባብያን መሆናቸው ያስታውቃል፡፡ በዕውቀት ኃይል የሚያምኑና አንዳንዶቹም የጽሑፍ ዝንባሌ ያላቸው ናቸው፡፡ ለወገን አሳቢዎችና ትሁቶች መሆናቸውን ታዘብኩ፡፡ የተነጋገርነው ብዙና ሰፊ ጉዳይ ላይ ቢሆንም ዋና ዋናውን በአጭሩ ታነቡት፣ እንደሁም ለዛጎል ቡክ ባንክም ሆነ ለሌላ የመጻሕፍት ፍላጎት ላለው አካል እገዛ ለማድረግ ትነሳሱበት ዘንድ ከያዝኩት ማስታወሻ በዚህ መልኩ አስፍሬያለሁ፡፡ መልካም የንባብና የማሰላሰል ቆይታ!
የዙም ስብሰባው መሪ ያሬድ ልሣነወርቅ ናቸው፡፡ በልጅነታቸው መንዝ እንደተማሩ በጨዋታ በጨዋታ ነግረውናል፡፡ የደራሲ ከበደ ሚካኤልን ግጥሞች ደጋግመው በማንሳት ለንግግሮቻቸው ማሳመሪያ ይጠቀማሉ፡፡ ከመጽሐፍ እየጠቀሰ የሚያወራ ሰው መስማት መታደል ነው መቼስ! የሰሩት ንባብና ዕውቀት ተኮር ስራ በእርሳቸውም ሆነ በሌሎች ተገልጧል፡፡ በሚኖሩበት ካውንቲ የአፍሪካ መጽሐፍ የለም፡፡ የአሜሪካ ብቻ ነው፡፡ እንዲኖር የሚመለከታቸውን አናግረዋል፡፡ ፊርማም ስለማሰባሰብ አስበዋል፡፡ በኢትዮጵያም መሰራት ስላለበት ስራ ሁሉ አገርቤት ያለነውን ‹‹ምሩን፣ መንገዱን አሳዩን›› ሲሉ ተማጽነዋል፡፡ እኛ ለብቻችን የምናደርገው መፍጨርጨርም ሰፋ እንዲል በማሰብ ‹‹አንድን መሪ ትልቁ ሊያደርገው የሚችለው ሊተካው የሚችለው ሰው ሲኖር ነው›› በማለት ተተኪ እንድናፈራ አበረታተውናል፡፡ የዘላቂነት ጥያቄ ለአሁኑ ዘመን አዳዲስ ሃሳብ ተግባሪዎች!
የበጎ አድራጎት ስራ አስተባበሪው ያሬድ አሜሪካ ቢሩም ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ጠብቀው ኖረዋል፡፡ ለዚህም የሚጠቅሱት በልጅነታቸው ያነበቡትንና የተማሩትን ነው፡፡ እኔ ከደብረብርሃን መሆኔን ሲያውቁ የአገር ሰዎችን እነ ፊታውራሪ ቅጣው አዘነና ልጆቻቸውን መዓዛ ቅጣውንና ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣውን ጠቅሰውልኛል፡፡
‹‹ኃይለማርያም ማሞ የጦሩ ገበሬ፣
ፈረሱን እንደሰው አስታጠቀው ሱሬ››
የሚለውን ግጥምም በመጥቀስ የዛሬው ትውልድም እንደነ ልጅ ኃይለማርያም ማሞ ሁሉ በነገው ተተኪ ትውልድ የሚወሳ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው አበረታተውናል፡፡ ብዙ የቤት ስራ አለብን አትሉልኝም!
‹‹‹ዱቢን ሃቡልቱ›› - ይደር ይቆይ - ይላል ያገሬ ኦሮሞ ሲተርት›› የሚሉት አቶ ያሬድ አጋፋሪነት ለወደፊቱም ተስፋ የሰነቀ ነው፡፡ ይህ ውይይት በየስቴቱ መሆን እንዳለበት ሃሳብ ተነስቷል፡፡ እውነት ነው፡፡ የአንድ ስቴት ሐበሻ በአንድ የኢትዮጵያ ዞን ውስጥ ያሉ አብያተመጻሕፍትን በመጻሕፍት ሊሞላ ይችላል፡፡ መጻሕፍትን ከአሜሪካም በጥንቃቄ መርጦ የማምጣት ስራ ከተሰራ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ‹‹ጎፈሬ የሚኖረው የራስ ቅል ሲኖር ነው››ን በመሰሉ አባባሎች በመጠቀም መሰረቱ መረሳት እንደሌለበት የሚያስታውሱት አቶ ያሬድ እስከዛሬም በዛጎል ቡክ ክለብ በኩል መደርደሪያ በመግዛት፣ ለታዋቂው ደራሲ ሣህለሥላሴ ድጋፍ በማድረግ ማገዛቸውን ደራሲ እንዳለጌታ መስክሯል፡፡ እዚህ ላይ ሣህለሥላሴን የመሰለ ታዋቂ ደራሲና ተርጓሚ፣ በአፍሪካን ራይተርስ ሲሪስ ሳይቀር ያሳተሙ፣ የተማሩ ሰው የሚታገዙበት መንገድ አለመዘርጋታችን እንደ አገር ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ አሁንም ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ አንድ ድርጅትን ቢያማክሩ፣ ዕውቅና ቢሰጣቸው፣ ወይም በሆነ መንገድ ማበረታቻ ቢያገኙ መልካም ነው፡፡ የሚቀርብንና የምናፍረው እኛው የዛሬ ትውልድ አባላትና መሪዎች ነን!
ደርሰህ የተባሉ ተሳታፊ እንዲህ አሉን፡፡ ‹‹አባቴ የጳውሎስ ኞኞን ‹አንድ ጥያቄ አለኝ› በዚያ እልም ባለ ገጠር እያስነበቡ ከእርሳቸው የተሻለ ኑሮ እንድኖር አስችለውኛል፡፡ እኔም ለልጆቼ የተቻለኝን አድርጌያለሁ፡፡ አገራችን ይህ ሁሉ ችግር የሚደርስባት በማቴሪያል ላይ እንጂ በዕውቀት ላይ ስላልተሰራ ነው፡፡ ይህ ጅምር ትልቅ ተስፋ ነው፡፡››
ዶክተር እንዳለጌታ ከበደና ሌሎቹም ተሳታፊዎች እኔ ከመግባቴ በፊት የተናገሩት እንዳለ ሆኖ እንዳለጌታ ስለ ቡክ ባንኩ፣ ስለ ንባብ፣ ስለ ትውልዱ ሃሳቡን አጋርቶናል፡፡
‹‹ለዕውቀት ለሥራ ግሎ ለመነሣት
ቆስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደ እሳት፣›› የሚል የደራሲ ከበደ ሚካኤልን ግጥም ጠቅሶ ለስራ መትጋት እንዳለብን አውስቷል፡፡ ንግግሩ ሁሉ ትህትና የተሞላበትና አነቃቂ ነው፡፡ በቀናነቱ የማይስማማ የለም፡፡ እስኪ ከዚህ ትህትናውና ከበጎ አድራጎት ስራው ለመማር የማይፈልግ ማነው? ደራሲው ስለ አድራጎታችን ማሰብ እንዳለብን አውስቷል፡፡ አገሩ ሁሉ የማይረባ ነገር ይጽፋል የምንለው እኛ እያነበብንላቸው መሆኑን እንዳንዘነጋ አውስቶ መርጦ ማንበብም አስፈላጊ ነው ብሏል፡፡ ከስራችንም ውስጥ ምን ይቅደም ብለን ማሰብ እንዳለብን ጠቅሶ እንደግለሰብም ሆነ እንደአገር መቅደም ካለባቸው አንዱ ንባብ መሆኑን አስታውሷል፡፡
እንዳለጌታ ዛጎል ቡክ ባንክ በደራሲ ዮርዳኖስ አልማዝ ሠይፉ በኩል በደቡብ አፍሪካ ላሉና የአገራቸውን መጻሕፍት ለማያገኙ ልጆች መጻሕፍት መርዳቱን ነግሮናል፡፡ ውጪ ያሉ ልጆች እንዲያነቡ አገር ውስጥ ባሉ ደራስያን የተጻፉትን እንደ አትሌቱ ያሉ መጻሕፍትን ማቅረብ እንደሚቻልና መተጋገዝ እንደሚኖርብን ገልጧል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ መጽሐፍ በማጣት ጨለማ ውስጥ የሚኖር አይኖርም የሚል እምነት አለው፡፡ ለዛጎል ቡክ ባንክ እገዛ ድርጉልኝ ወይም ስጡኝ ማለት እንደማይፈልግና የፈለገ ይምጣና ይስጠን የሚል ሃሳብ እንዳለው ገልጾ ይህ ሃሳቡ መቀየር እንዳለበት ከጓደኞቹ ጋር በሚያደርገው ምክክርና እሱም በተለመከተው መሰረት እያመነ መምጣቱን ነግሮናል፡፡
በአዲስ አበባ በዛጎል ቡክ ባንክ የሚሰራውን ስራ የዛሬው የዙም ስብሰባው ተሳታፊዎች ያውቃሉ፡፡ ለማወቃቸውን የዩቱብ ቻነላቸው ምክንያት እንደሆናቸው ብዙዎች ተናግረዋል፡፡ አሜሪካ ሆነውም አገራቸው እንዳሉ እንዲሰማቸው አድርጓቿል- እንደ ገለጻቸው፡፡
ደራሲ ዓለማየሁ ማሞ 29 መጻሕፍት የደረሱ መሆናቸው ተገልጾ እንዲናገሩ ተጋበዙ፡፡ እርሳቸውም ከባህር ኃይል ጀምሮ የነበራቸውን የንባብ ልምድ አጋሩን፡፡ የመጻፍና የማሳተም ስራቸውን አስቃኙን፡፡ ሌሎች ሰዎች እንዲጽፉ የሚያደርጉትን ድጋፍም እንዲሁ፡፡ ከዛጎልም ጋር የሚያያይዛቸው አንድ ሁነኛ ጉዳይ አለ፡፡ ዛጎል ለአብያተመጻሕፍት ለመተዋወቂያ ከሚሰጠው 200 መጽሐፍ በኋላ ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡት 981 መጻሕፍትን ይጨምራል፡፡ ይህም ቁጥር እንግሊዞች ከአፄ ቴዎድሮስ ከመቅደላ የዘፏቸው መጻሕፍት ቁጥር ነው፡፡ እናም ደራሲ ዓለማየሁ ማሞ የሚረዱኝና የሚረዱኝ (ረ ይጠብቃል) ከሚሏቸው ጥቂትና ሁነኛ ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በአንድ ዓመት ጊዜ አገር ቤት የመታተም ዕድል ካገኙት መጻሕፍታቸው 2062 የሚደርሱትን ለዛጎል አበርክተዋል፡፡ ከሰጡት ወደፊት የሚሰጡት እንደሚበዛ ስለነገሩን እናመሰግናለን!
ፋሲል ስዩም ገሠሠ ከፀሐይ አሳታሚ ጋር በመሆን በአሜሪካ የመጻሕፍት ውይይት ክበቦችን አቋቁሟል፡፡ ልጆችም ሆኑ ትልልቆች በየዕድሜያቸው እያነበቡ እንዲወያዩ ያደርጋል፡፡ በተግባር የሰራቸውንና ያገኛቸውን ልምዶች አጋርቶናል፡፡ እንደ ፋሲል ሁሉ ተሰብሳቢዎቹ በየሙያቸው፣ በገንዘባቸውና በጊዜያቸው አገራቸውን ለማገልገል የሚተጉ ናቸው፡፡
የኦንላይን ፒዲኤፍ ንባብን አስመልክቶም የተናገሩ አሉ፡፡ አንዳንድ መጽሐፍ በኢሜል ስለመላክ ተነጋግረናል፡፡ አንድ ተሳታፊ 117 ሚሊየን ብንሆንም ኢትዮጵያን የሚያሻግሯት ጥቂት እንደሆኑ በመግለጽ የግለሰቦችን ሚና ጠቀሜታ ያዩበትን መንገድ አስረድተውናል፡፡ ከአራቱ መጻሕፍቷ ከእያንዳንዳቸው 100 ቅጂ ቃል የገባችው ደራሲት እመቤት መንግስቱም ተሳታፊ ነበረች፡፡ ደራስያን በአመዛኙ በድርሰት ላይ እንጂ በአካዳሚው ዘርፍ በመማርና በማደግ ላይ በማያተኩሩበት ጊዜ እስከ ፒኤችዲ ድረስ መሄዱን ጠቅሰው ዶክተር እንዳለን ያደነቁ ተሳታፊም ነበሩ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማይጠቅም መጽሐፍ እንዳናመጣና መጽሐፍ ስንመርጥ እንድንጠነቀቅ መክረውናል ያሉም እንዲሁ፡፡ ያላነበብነውን መጽሐፍ አንሰጥም የሚለው የእንዳለጌታና የዛጎል ቡክ ባንክ ሃሰብ ሲታከልበት የመጽሐፍ ምርጫ ጉዳይ ትልቅ ቦታ እንዳለው እንገነዘባለን፡፡
እኔም በተሰጠኝ ዕድል ንግግር አድርጌያለሁ፡፡ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደን በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል የጥበብ ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተዋወኩት፣ ከዚያም ለሌላ ጥናታዊ ጉባኤ ወደ ከተማችን እንደመጣ ተገናኝተን ቤተመጻሕፍቴን (ራስ አበበ አረጋይን) አይቶ እንደተወያየንና እንዳበረታታኝ ገለጽኩ፡፡ በ2013 ዓ.ም. በዛጎል ቡክ ባንክ 200 መጻሕፍት እንደተበረከተልንና የስጦታውን ሁኔታም በሦስተኛው መጽሐፌ ‹‹ብዕረኛው የሞጃ ልጅ›› ጽፌ ማካተቴን፣ ያንንም ጽሑፍ በዋልያ መጻሕፍት መደብር የቅዳሜ ዝግጅት ላይ ተገኝቼ እንዳነብ እንዳደረገኝ ገለጽኩ፡፡ ከዚያ ካቀረብኩት ጽሑፍም ሃሳቦችን በመዋስ ከተናገርኩት አንዱ የሚከተለው ነው፡፡ በቤተመጻሕፍታችን አንዲት መጽሐፍ እንኳን ትውልድን በማስተማር ረገድ ያላትን ጥቅም በቤተመጻሕፍታችን በምትገኝ በአንዲት የ11ኛና 12ኛ ክፍል የሒሳብ አጋዥ መጽሐፍ ለሰባት ዓመታት በየቀኑ በሚባል ሁኔታ መነበብና የብዙዎችን ሕይወት የመቀየር ሚና አስረዳሁ፡፡ ያለብንን የመጽሐፍ እጥረት፣ ካሉን መጻሕፍት 20 በመቶው ማለትም 600 መጻሕፍት ብቻ በሦስት አገር በቀል ድርጅቶች ድጋፍ መገኘታቸውን፣ ሌሎቹ እኔ ከመጻሕፍቴ ሽያጭና ከራሴ ገንዘብ ያሟላኋቸው መሆናቸውን፣ የአገር ውስጥ መጽሐፍ ካልሆነ እንደማይነበብ ጨምሬ ዋና ዋና ሃሳቦችን አቀረብኩ፡፡ እነዚህም የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍትን የሰባት ዓመታት ጉዞና የግል ቤተመጻሕፍት አሰራርና ይዞታ የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ስለመጻሕፍት ፍላጎታችንን ከተናገርኩ በኋላ በአፍመፍቻ ቋንቋ ስለመማር ሃሳብ ያቀረቡ ተሳታፊም ነበሩ፡፡ እርሳቸውም እነ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በደርግ ጊዜ ይህን ሃሳብ ሲያቀርቡ እንደተሳቀባቸው ገልጸው የዓለም አገሮች ግን አብዛኞቹ በቋንቋቸው እንደሚማሩ ተናግረዋል፡፡ በራሱ ቋንቋ ያልተማረ አያድግም፡፡ እንኳን ማደግ መሰረታዊ ፍላጎቱንም አያሟላም፡፡ መፈልሰፍና ማወቅ የሚቻለው በራሳችን ቋንቋ ስንማር ነው ብለውናል፡፡
ዶክተር እንዳለጌታ ከበደም ስለስራዎቼ በመናገር አስተዋውቆኛል፡፡ በዘር ማጥፋት ላይ የሚያተኩረውን ሌፍተ ቱ ቴል የተባለውን የኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛን መጽሐፍ ሁቱትሲ በሚል ርዕስ መተርጎሜንና ማሳተሜን ገለጸላቸው፡፡ በዚህ ሳልወሰን ወደ ኦሮምኛ አስተርጉሜ ማሳተሜንም በማመስገን አስተዋወቀኝ፡፡ የዚህን ስለ ይቅርታና መቻቻል የሚያስተምር ግለታሪክ መተርጎምና መታተም አስተዋጽኦ፣ የቤተመጻሕፍቴን ስራ፣ በአካዳሚው ዘርፍ ለመማርና ለማደግ ያለኝን ዕድል ገትቼ ስራዎቹን መስራቴን ገልጾ አመሰገነኝ፡፡
በዝግጅቱ ደራሲ ይታገሱ ጌትነት ተሳትፏል፡፡ የቀድመ ማስታወቂያ ሚኒስትር ግርማ ይልማም ስምና ተግባር ሲጠራ ሰምቻለሁ፡፡ ከአገር ውስጥ እኔና ይታገሱ ስንሆን በአጠቃላይ 25 ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ዶክተር እንዳለ የአሜሪካ ዕድል በማግኘቱና አሜሪካ ያሉ ወገኖች በእርሱ በኩል አገራቸውንና ወገናቸውን ለመርዳት በመፈለጋቸው ነው፡፡ አሜሪካ የዕድሎች አገር ነው የሚባለውን እውነትነት ያሳየ ስብሰባ ነበር፡፡ የአስተባባሪው ማበረታቻና ምርቃት በየመሃሉ ያጀበው ውይይታችን እየደበዘዘ የሚመስለውን ኢትዮጵያዊነታችንን የሚያነቃቃና ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ካለባቸው የጊዜ እጥረትና የኑሮ ጫና ዛሬ የሦስት ሰዓታት ጊዜያቸውን ስለሰጡን ማመስገን ይገባናል፡፡ ያልጻፍኩትን ብዙ ቁምነገር ያስጨበጡን ብዙዎች ናቸው! ከሁሉም በላይ ለዛጎል ቡክ ባንክ የገንዘብ መዋጮ ማድረጋቸው አገርቤት በየቤተመጻሕፍቱ የሚደርስ ስራ ነውና ድንቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በአቶ አመኃ አስፋው ምርቃት ይዘጋ የተባለውን እርሳቸው ለደራሲ እንዳለ እድሉን ሰጥተው ተዘጋ፡፡
‹‹በትን ያሻራህን ዘር
ይዘኸው እንዳተቀበር›› በሚል የደበበ ሠይፉ ግጥም ደራሲው ሲዘጋ ሌላ ተሳታፊ ‹‹አዲስ አበባ ነግቷል›› ሲሉ ወደ መስኮት ሳይ ወገግ ብሏል፡፡ ሠዓቴን ከጠዋቱ 1፡00 ይላል፡፡ ደብረብርሃንም ነግቷል፡፡ በእውነቱ እውነተኛ የጥበብ፣ የእውቀት፣ የፍቅር፣ የመልካም ነገር ሁሉ ንጋት እንዲመጣልን እመኛለሁ፡፡ ለዚህም የሁላችንም ጥረትና ቀናነት ያስፈልጋል፡፡
ይህ ልጥፍ በጸኃፊው አስተዳዳሪው ተወግዷል።
ምላሽ ይስጡሰርዝድንቅ ዘገባ ነው። ያንተም መገኘት ትልቅ ውክልና ነበረውና ለምሽቱ ድምቀት ነበርክ። በጀመርከው በጎነት ቀጥል። ምናልባት ከመግባትህ በፊት ይሆናል...ጥቂት ያነሣኋቸው ነጥቦች ነበሩና እነሆ። የሚረዱኝና የሚረዱኝ (አንዱ ይጠብቃል) ጥቂትና ሁነኛ ወዳጆች እንዳሉኝ. ከነርሱ ጋር በማበርም በአንድ ዓመት ጊዜ አገር ቤት የመታተም ዕድል ካገኙት መጽሐፎቼ 2062 የሚደርሱትን ለዛጎል ማበርከታችንን አንሥቻለሁ። ከሰጠነው ይልቅ ወደፊት የምንሰጠው እንደሚበዛም በምካት ፎክሬአለሁ። ከዛጎል ጋር የምንሠራውን በጎ ሥራ እንቀጥላለን ወይም እንቀጥላለን ብያለሁ።
ምላሽ ይስጡሰርዝአመሰግናለሁ፡፡ ይህ የመጀመሪያ ቅጂ ነበር፡፡ አሁን የእርስዎን ሃሳብ ጨመርኩበት፡፡ ምክንያቱም ሌሎች ሰጪዎችን ስለሚያበረታታልን፤ ማመስገንም ስላለብን፡፡
ሰርዝይበል። ተጨማሪው ነጥብ አንድም ሌሎችን እንደሚያነሣሣ አልያም አጋሮቼን እንደሚያበረታ ጥርጥር የለኝም።
ሰርዝበትክክል! እናመሰግናለን!
ሰርዝበጣም ደስ ይላል። መምህር መዘምር እየሰራህ ላለኸው ትልቅ ስራ ልትመሰገን ይገባል። ዶ/ር እንዳለጌታ ከበደ እና ሌሎች ሀገር ወዳዶችም ኢሄን ጠቃሚ ሀሳብ አንስተው በመወያየታተቸው እና አንተን የመሰለ ለትውልድ የሚሰራ ሰው በመጋበዛቸው ምስጋናዬ ይድረሳቸው። ውይይታቹ እንደሚቀጥል እና ለውጥ እንደሚያመጣ ባለሙሉ ተስፋ አለኝ።
ምላሽ ይስጡሰርዝ