ሳሲት በዕውቀት ጎዳና
የጉዞ ማስታወሻ
በመዘምር ግርማ
ጥቅምት 2፣ 2015 ዓ.ም.
ቅዳሜ መስከረም 28፣ 2015 ዓ.ም. ከደብረ ብርሃን ተነሳሁ፤ ወደ ሳሲትም ለመሄድ ወደ መናኸሪያ አቀናሁ፡፡ ‹የሕይወቴ ፈርጦች፣ እንደ መርከበኛ በባሕር፣ እንደ ጋዜጠኛ በምድር› የሚል ርዕስ ያለውን የዓለማየሁ ማሞን መጽሐፍ መኪና ውስጥ እያነበበብኩ ነው፡፡ ከሁለት ወራት በፊት መጽሐፍ እያነበበ እንዲሄድ ሃሳብ ያቀረብኩለትና መጽሐፍ ሰጥቼ የላክሁት ግሩም አስናቀ በሞላና በተጨናነቀ መኪና ውስጥ ስለተሳፈረ አለመቻሉን ስለነበረኝ ሰግቼ ነበር፡፡ የጃፓንን ምቹ የመንገደኞች ባቡሮች ሁኔታ አይቼም በእኛ ሁኔታ ተበሳጭቼ ነበር፡፡ ቀለል ባለው የተሳፋሪ ቁጥር ምክንያት ሳነብ የነበረበትን ሁኔታ በሚከተለው መልኩ ለፌስቡክ ህብረተሰብ አስተላለፍኩ፡፡ ‹‹የሁለት አንባቢያን ወግ - እኔ የአማርኛ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ስከፍት እርሳቸው የግእዝ የፀሎት መጽሐፍ መዝሙረ-ዳዊት አወጡ፡፡ ጮክ ብለው እያነበቡ ነው፡፡ በፀጥታ አነባለሁ፡፡ ዘግይተው ምን እያነበብኩ እንደሆነ ጠየቁኝ፡፡ ስነግራቸው ‹እያንዳንዱ ሰው የሕይወት ታሪክ አለው› በማለት ጀመሩ፡፡ ለማናቸውም በሠላድንጋዩ መኪና ውስጥ እየተነበበ ነው፡፡ የዓለማየሁ ማሞ መጽሐፍ እጄ ከገባ ስምንት ዓመት ቢሆነውም በቅርቡ ደራሲውን ስለተዋወቅሁ አንስቼ ለማንበብ ቻልኩ፡፡›› መነኩሴው በጻድቃኔ ማርያም የሚኖሩ ሲሆኑ፤ ስለቤተክርስቲያን ህንጻና አስተዳደር ሁኔታ ብዙ አጫወቱኝ፡፡ እኔም ስለስራዬ ነገርኳቸው፡፡ በወለጋ መኖራቸውንና እዚያ ስላሉት ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሁኔታም አውግተዋል፡፡
ሠላድንጋይ ከተማ ደርሼ ያየሁትን የልማት ጅማሮም ለወዳጆቼ በፎቶ አጅቤ አጋራሁ፡፡ እንዲህ በማለት ‹‹የሠላድንጋይ የልማት እርምጃ - ዛሬ በሞጃ ቆይታዬ ከሰዓት በፊት በዘመድ ጥየቃና የከተማዋን ለውጥ በማገናዘብ ቆይቻለሁ፡፡ በከተማዋ ያሉት ባንኮች ሰባት እየደረሱ ነው፡፡ የሞጃ ህዝብ ትጋት እየጨመረ መሆኑ በግልጽ ይታያል፡፡ በሰብዓዊ መብት፣ በጦርነት ትውስታ፣ በኪነጥበብና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂጃለሁ፡፡››
ከአፍታ ቆይታ በኋላ የሞጃ ዘነበወርቅ ባህል ቡድን አባል የሆነው ይበል ወርቁ ወደ ቤቱ ይዞኝ ሄደ፡፡ በዚያም ያገኘኋቸውን ግለሰብ ጉዳይ እንደሚከተለው በማስታወሻዬ ያዝኩ፡፡ ‹‹የፍትሕ ያለህ- ወይዘሮ አዛለች ይባላሉ፡፡ በሀሰት ሰው መግደል ወንጀል ተፈረደባቸው፡፡ ሞተች የተባለችውና በሀሰት የተመሰከረላት ጠፍታ ቆይታ ስለመጣች በይቅርታ ተፈቱ፡፡ ሲፈቱ ሀብት ንብረታቸው በሃራጅ ተሸጦ አገኙት፡፡ የአገራችን ፍትሕ ከምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ማሳያ ናቸው፡፡ በሠላድንጋይ ከተማ አግኝቻቸዋለሁ፡፡ በቤታቸው ስደርስ ያገኘኋቸው ስልክ ሲደዋወሉ ነበር፡፡ የሚያወሩትም የሚኖሩበት የቀበሌ ቤት ኪራይ ስለመጨመሩና መክፈል እንደማይችሉ ነበር፡፡ ከእማወራነት ወደ ጉልበት ሰራተኛነት እንዳወረዷቸው ነገሩኝ፡፡ ሕዝቡ በሰልፍ ወጥቶ ትገደል ሲል እንዳልነበር አሁን ንፁህ ሲሆኑ ምንም አላላቸውም፡፡ ያሳዝኗችኋል፡፡ ያላናገራቸው ሚዲያ የለም፡፡ ያገኙት ነገር ያለመኖሩን ግን ነገሩኝ፡፡ እንዳናግራቸው ለጠቆመችኝ አንዲት ወጣት ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ መፍትሔ ብንፈልግላቸው ጥሩ ነው፡፡ በተለይ የሕግ ባለሙያዎች፡፡››
ከወይዘሮ አዛለችና ከጌጤ ቤተሰብ ጋር ባለፈው ዓመት ስላሳለፉት የጦርነት ጊዜ ሁኔታም አውግተናል፡፡ እኔ ደብረብርሃን ሆኜ የጦርነት ስጋት ቢኖርብኝም እንደነሱ ለቀናት የመድፍ ጥይት ስላልተተኮሰብኝ የነሱን ታሪክ ፀጥ ብዬ ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ ሠላድንጋይ ማርቆስ አካባቢ ከሚገኘው ከእርሳቸው ቤት ወጥቼ ወደ ከተማዋ ስወርድ አንድ ባለ ግርማ ሞገስ አባት አየሁ፡፡ ይህንንም ጻፍኩ፡፡ ‹‹የሞጃው መስፍን - ሠላድንጋይ ማርቆስ አካባቢ ጌጤን ጠይቄ ወደ ከተማው ስወርድ እኝህን አዛውንት አየሁ፡፡ በራቸው ላይ ተቀምጠው ሲያስቡ ሳይ ባላባት መሰሉኝ፡፡ ይህን ገልጬ ስለፎቶ ሳወራ ይበል አስፈቀደልኝ፡፡ የተሰማኝን ነገርኳቸው፡፡
‹ጃንሆይ እኮ ዘመዴ ናቸው› አሉኝ፡፡
ጃንሆይ አጤ ምኒልክ?› ስል ጠየኳቸው፡፡
‹አጤ ኃይለሥላሴ› በማለት መለሱ፡፡
ተገረምኩ፡፡ ያቺን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳያቸው የነበሩባትን ቅጽበት መልሰን ባናገኝም ፎቶ አነሣናቸው፡፡ የታሪክ ዕውቀታቸውን ያካፍሉን ያዙ፡፡ ያነበቡት ብዙ መሆኑን ነገሩን፡፡ ከእርሳቸው በዕድሜ የሚበልጡም መኖራቸውን ነገሩን፡፡ እርሳቸውንም ሌሎቹንም የመጠየቁንና የመጻፉን ሥራ አብረውኝ ለሚዞሩት የሞጀ ዘነበወርቅ የባህል ቡድን ሰጥቼ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡››
የሞጃና ወደራ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆነችውን ሙሉጌጥ ጎርፉን ከቤቷ ጠርተን በእረፍት ቀኗ ቅዳሜ ቢሮ ገባችልን፡፡ በቢሮዋም ስለጀመሩት የማስነበብ ስራና ወደፊት በመስሪያቤቱ ግቢ ለመክፈት ስለታሰበው አነስተኛ የንባብ ቦታ ነገረችን፡፡ የባህል ቡድኑ ተጠናክሮ የሚቀጥልበትንም ሁኔታ እንደሚነጋገሩ አሳወቁኝ፡፡ የባህል ቡድኑ አባላት ድጋፍ እንደሚፈልጉ፣ የአባላት መመናመን እንዳለባቸውና የቦታ እጥረት እንዳስቸገራቸው ነግረውኛል፡፡ የሥልጠናና ድጋፍ ዕድል ቢያገኙ እንደሚሹና አቅም ከተገኘ የባህል ቤት መክፈት እንደሚፈልጉ አጫውተውኛል፡፡ በቅርቡ ወረዳው በዞን ደረጃ የተከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን እንዳስተናገደ አስታውሰው በወቅቱ የሸለሙኝንና መገኘት ባለመቻሌ ያልወሰድኩትን ጋቢ አበረከተችልኝ፡፡ ከምስጋናና ውለታ በዛብኝ ከሚል አስተያየት ጋር ተቀበልኩ፡፡
ወደ ሳሲት ከሰዓት አቀናሁ፡፡ ወዳጅ ዘመድን ጠያየቅሁ፡፡ ቅዳሜ ስለሆነ ደማምቃለች፡፡ የገበያ ቀን ከሌሎቹ በላይ የደመቀ ነው፡፡ በየቦታው የሚወራው ገንዘብ መሆኑ የመጀመሪያው ምልከታዬ ነበር፡፡ በየቤቱ እየዞሩ መጋበዝ (ጋ ይጠብቃል)፣ ቡና፣ አረቄና ቢራ መጋበዝ (ጋ ይጠብቃል) ስራዬ ሆኗል፡፡ እሁድ ጠዋት ቀበሌው ከወረዳ የመጡ ኃላፊዎች የሚሳተፉበት ስብሰባ መኖሩን በማሳወቁ ለከሰዓት ያሰብነው ስብሰባ ምን ያህል ሰው እንደሚመጣበት መጨነቃችን አልቀረም፡፡ ጋቢውን ለእናቴ አሳይቻት መቋጨት እንዳለበት ነገረችኝ፡፡ በእውቅ የተሰራ እንደሚመስልና ቆንጆ መሆኑን ነገረችኝ፡፡ ተቋጭቶ ወፍ እግር እንደሚሰፋ ስትነግረኝ እኔ እስከዛሬ ጋቢ ውሰድ ስባል ስለማልወስድ ነገሩ ብዙም አልገባኝም፡፡ ጋቢ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ስትነግረኝ አንድ ሰው ሲሞት አራት ጋቢ እንደሚያስፈልገው በማስረዳት ነው፡፡ ሁለቱ አስከሬኑ የሚሸፈንበት ሲሆን ሁለቱ የሚጋረድ ነው፡፡ በአሁኑ የገበያ ዋጋ አንድ ሰው ሲሞት አራት ጋቢ ማለትም የ6000 ብር ሀብት ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡
እሁድ ጠዋት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የሞጃና ወደራ አባላት ወርሃዊ ስብሰባቸውን በህብረት ሱቁ ደጅ ተቀምጠው ሲያካሂዱ አየኋቸው፡፡ ሰላምታ አቀረብኩላቸው፡፡ ንግግርም እንዳደርግ ጋብዘውኝ ተናገርኩ፡፡ ያለ ሥራ የተቀመጠውን የቀበሌውን አዳራሽ ተንከባክበው ለመያዝና ለስብሰባና ስራቸው ለማዋል ጥያቄ እየጠየቁ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ አዳራሹንም ጎበኘሁት፡፡ በጣም ቆሽሿል፡፡ እኔም ምናልባት ለነሱ ቢሰጥ ለኛ የመጻሕፍት ውይይት ክበብም መወያያ ይፈቅዱልናል ብዬ አሰብኩ፡፡ በኋላ እንደተረዳሁት ግን ቀበሌው ራሱ የስብሰባ አዳራሽ ስለሌለው ይህንኑ መንከባከብ ይኖርበታል፡፡
ለከሰዓቱ ስብሰባ ሰዎችን በአካል፣ በፌስቡክ፣ በስልክና በመልዕክት ስናስታውስ ቆየን፡፡ ሰዓቱም ሲደርስ እንደተሰጋው የቀበሌው ስብሰባ ስለነበር ሰዎች አልወጡም ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ሄደን ተማሪዎች ስለመጡ ስራ ከመፍታት በማለት ‹ከገንዘብና ከዕውቀት› በሚል ርዕስ ክርክር አደረጉ፡፡ ይህን ርዕስ እኔም ያሰብኩት ሲሆን ተማሪዎች ሳልጠይቃቸው እሱኑ መምረጣቸው አስደስቶኛል፡፡ ስለ ሳሲት ቡክ ክለብ ሁለት ጊዜ በፌስቡክ ላይቭ ቃለመጠይቅ ያደረኩለት ዮርዳኖስ ግሩም በክርክሩ ተሳትፏል፡፡
መምህራንና ተጋባዥ እንግዶች በአጠቃላይ 22 ሰዎች ተገኝተው ውይይቱ ተጀመረ፡፡ በመጀመሪያ ስለ መጻሕፍት ውይይት ክበብ ምንነትና አሰራር የሳሲት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ-መምህር ፀጋ ገለጻ አደረጉ፡፡ በመቀጠል ግሩም አስናቀ ስለ ሳሲት ቡክ ክለብ አጀማመር ሃሳቡን አቀረበ፡፡ በሁለቱም ሃሳቦች ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡ ቀጥሎ ለዕለቱ መወያያ በተመረጠው ‹ብዕረኛው የሞጃ ልጅ› በተባለው የኔ መጽሐፍ ላይ ተወያያን፡፡ ለውይይቱ መነሻ ሃሳብ ያቀረበው ክብሩ ማሞ ሲሆን እርሱም ከንባቡ ያቀረበውን ከማጋራት በዘለለ ከእኔ ጋር በጥያቄና መልስ መልኩ ውይይት አድርጓል፡፡ ከዚያም ለቤቱ ክፍት ተደርጎ ተወያይተናል፡፡ በመቀጠል በዝግጅቱ ተሳታፊ የሆኑት አብዛኞቹ ተማሪዎች በቅርቡ የደብተር እገዛ ያገኙት በመሆናቸው ከሠው ለሠው በጎ አድራጎት ክበብ ተጠሪ መምህር አበበ ሃሳብ ቀርቦ ለወደፊቱ ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የሚሰሩበትንና ራሳቸውን የሚደግፉበትን መንገድ እንዲሁም በትምህርታቸው ጎበዞች የሚሆኑበትን ጉዳይ ተነጋግረናል፡፡ ዕድሎች ውሱን በሆኑባቸው እንደ ሳሲት ያሉ ቦታዎች ተስፋ ያላቸው ልጆች መኖራቸውን ከተረዳሁባቸው ሁኔታዎች አንዱ በዕለቱ ተሳታፊ የነበረው ተማሪ ቶማስ ብርቅነህ በፈጠራ ስራ ከዞን አንደኛ፣ ከክልል ሦስተኛ ወጥቷል መባሉ ነው፡፡ የዕለቱ ዝግጅትም በአጠቃላይ አስደሳች በሆነ መልኩ የተጠናቀቀ ነበር፡፡
በማግስቱ ሰኞ ጠዋት ወደ ሳሲት ሙሉ ሳይክል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄጄ ከአስተዳደሩና ከቋንቋ መምህራን ጋር እንግሊዝኛ ክበብ እንዲጀመር ሃሳብ አቅርቤ መተጋገዝ በምንችልባቸው ሁኔታዎች ላይ ተነጋግረናል፡፡ የተማርኩበትን ትምህርት ቤት መጎብኘቱ፣ ተማሪዎችን ማየቱ፣ ስለትምህርት ቤቱ አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ ማየቱ ለኔ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱም በመሄድ ተመሳሳይ ውይይት ከእንግሊዝኛ መምህር ጋር አድርጌያለሁ፡፡
ሰኞ ከሰዓት ብዙ ሰዎች ወደ ለቅሶ የሄዱበት ስለነበር ከተማው ለተወሰነ ጊዜ ጭር ብሎ ነበር፡፡ ሲመለሱ በዘመዶቼና ወዳጆቼ ጋር ስለምሰራቸው የበጎፈቃደኝነት ስራዎች በግል ለመወያየትና ሃሳብ ለመቀያየር ችያለሁ፡፡ ማክሰኞ ወደ ደብረብርሃን ተመለስኩ፡፡ የሳሲት ቡክ ክለብ ውይይት በየወሩ መጨረሻ እሁድ ስለሚቀጥል እገኛለሁ፡፡
በአማራ ክልል ከተሞች ንባብን፣ ዕውቀትንና የበጎፈቃደኝነትን የማስፋፋት ሙከራችን ላይ የሞጃ/ሳሲት የሦስት ቀናት ቆይታዬን አስመልክቼ የጻፍኩት ይህ ጽሑፍ ዋና ዋና ነጥቦችን የሚነካካ እንጂ ሁሉንም የሳሲት ትዝብቶቼን የያዘ አይደለም፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ