2022 ዲሴምበር 24, ቅዳሜ

ኃይለሥላሴ፣ አፍሪካዊው ንጉሥ ሲታወሱ

 

ኃይለሥላሴ፣ አፍሪካዊው ንጉሥ ሲታወሱ

በዶክተር ጥበበ እሸቴ ተጽፎ

በዳግማዊ ውቤ የተተረጎመ

 

የአስደሳችና አናዳጅ ሃሳቦች ማስታወሻ - በመዘምር ግርማ

 

ለዚህ መጽሐፍ የተሰጡት አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት በአፄ ኃይለሥላሴ ላይ ሚዛናዊነታቸው የሚያጠራጥር መጻሕፍት በዝተዋል፡፡ ደራሲው በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን እንደኖረ፣ እንደተማረና እንዲያውም እንደተቃወማቸው ሰው ያሳዩትን ተቃውሞ ቆም ብለው የገመገሙና የኃይለሥላሴን አስተዋጽኦ ዘግይተው እንደተገነዘቡ ሆነው ቀርበዋል፤ በግላቸውም ሆነ በአስተያየት ሰጪዎቹ ዕይታ፡፡

ልጅነታቸውና እድገታቸው በእናት ሞት፣ በሞግዚቶችና በውጪ መምህራን በማደግ፣ በኋላም በአባታቸው ሞት ከባድ የነበረ ሲሆን፤ በልዩ ልዩ ምልክቶች ኢትዮጵያን የመምራቱ ኃላፊነት እጃቸው አንደሚገባ ቀድሞውኑ ያውቁ ነበር ስለሚባል በለጋ ዕድሜያቸው ከተሰየሙባቸው የሥልጣን ቦታዎችም ሆነ ከምኒልክ እልፍኝ የአስተዳደር ትምህርት ቀስመዋል፡፡

ስብዕናቸው፣ የሕይወት ዘዬአቸውና እምነታቸው በልዩ ልዩ የታቀደባቸውም ሆነ ያልታቀደባቸው አጋጣሚዎች የተሳሉ ነበሩ፡፡ በልጅነታቸውና ወጣትነታቸው ከነበሩት ሰዎች ቀድመው አገራቸውን በዘመናዊነት ጎዳና ለመምራት ጥረዋል፡፡ አንባቢ፣ ፋሽን ተከታይ፣ እንስሳትን ወዳጅ፣ ዓለም አቀፉን የፖለቲካ ስዕል ተመልካች ናቸው፡፡  

‹‹ኢትዮጵያን ወደ ታላቅ መዳረሻዋ ለመምራት በሚያስችል የተልዕኮ ስሜት ራሳቸውን ብቁ በማድረግ፣ ኢትዮጵያን ለምዕራቡ ዓለም አስተሳሰቦች በማስተዋወቅ፣ ከሞዴሎቹን መካከል የተመረጡን ብቻ በመቀበልና ሌላ ቀጥተኛ እርምጃ በመውሰድ፣ ዕድገትን ለማምጣት ፈልገው ነበር›› ይሏቸዋል ደራሲው መሪው በወጣትነታቸው የወሰዷቸውን እርምጃዎች በማሳየት፡፡ የአውሮፓ ጉዞን፣ የሕገመንግሥት አዋጅን፣ የትምህርት መስፋፋትን፣ አስተዳደሩን ማዘመንንና የሊግ ኦፍ ኔሽንስ መስራች አባል መሆናቸውን የመሳሰሉትን እርምጃዎችም ጠቃቅሰዋል፡፡

በዘውድ በዓል በዓለሲመት ንግሥተነገሥታት ዘውዲቱን ዘወር በማድረግ የንጉሠ ነገሥትነቱን መንበር የጨበጡት ተፈሪ ከዘልማዳዊው የአስተደደር ተከታዮችና አራማጆች ፈተናዎች ቢገጥሟቸውም በጥበብ አልፈዋቸዋል፤ የልጅ ኢያሱን መንበር በዘዴ እንዳፈረሱት ሁሉ፡፡ የኢጣሊያ ወረራ በስልጣኔ ጎዳናቸው ላይ የተጋረጠ መሰናክል ነበር፡፡ ውድመትን፣ ስደትንና እንግልትን ያስከተለው ይህ ወረራ ንጉሠነገሥቱን በእጅጉ የፈተነ ነበር፡፡ የጄኔቭ ንግግራቸውና የአንግሊዝ የችግር ኑሯቸው ተጠቃሽ ትውስታዎች ናቸው፡፡ የዓለም የፖለቲካ አካሄድ መለወጥና በኋላ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሳት ምክንያት የአላይድ አገሮች ድጋፍ ከአርበኞቻቸው ጋር አገራቸውን ነጻ እንዲያወጡ ለመዝመት አስችሏቸዋል፡፡ በጣሊያን እግር የገባውን እንግሊዝን ማስወጣትና ወደ አሜሪካ መጠጋት ቀጣዩ እርምጃቸው ነበር፡፡

ዘመናዊ ትምህርትን በጥንቃቄ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አስፋፍተዋል፡፡ በትምህርት አስተዳደር መሪነትና መምህርነት የመጡት የዉጪ ዜጎች በጥንቃቄ እንዲሰሩ ማሳሰቢያዎች ቢሰጧቸውም ትምህርቱ ፖለቲካዊ ሃሳቦችን የማያስተናግድ በመሆኑ፣ ከአገርበቀል ዕውቀት ጋር ባለመያያዙና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተቃውሞ ሃሳቦች ስር እየሰደዱ ሄዱ፡፡ ክርስትናና ምዕራባውያን ሚሲዮናውያንን ንጉሡነገሥቱ የያዙበት መንፈስ የመስቀሉ ኃይማኖቶች በሚል እያባበሉ የመጠቀምና አገሪቱን የማልማት ሃሳብ የራሱ የሆነ ጦስ አስከትሏል፡፡ ፈረንጆቹ የተገኘችዋን አጋጣሚ ሁሉ የአገሩቱን መሰረት ለመነቅነቅ ተጠቅመዋል፡፡ የሚገዳደራቸው የተደራጀ አገርበቀል ፍልስፍናም አልነበረም፡፡

የንጉሠነገሥቱን ዓለማቀፋዊ ተሰሚነት አስልክቶ መጽሐፉ ጥሩ ሽፋን የሰጠው ሲሆን፤ የአውሮፓ፣ የአሜሪካ፣ የእስያና የካሪቢያን ጉዞዎቻቸውና ያላቸው ጠቀሜታ ተጠቅሷል፡፡ የራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴ፣ የጥቁር ህዝቦች አንድነት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ፣ የዲፕሎማሲና የሽምግልና ስራዎች፣ የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ያላቸው ሚና ተነስቷል፡፡

ዘመናዊ ትምህርትና ዘመናዊነትን የሚደግፉት ንጉሠነገሥቱ በዚሁ ዘመናዊነትን መያዝና መምራት ባለመቻላቸው የገቡበት የመጨረሻው መጀመሪያ ምዕራፍ አሳዛኝ ፍጻሜዎች ነበሩት፡፡ ማህበራዊ ባህል በሚቀያየርበት ሁኔታ ተገቢውን ምላሽ በተገቢው ጊዜ አላቀረቡም፡፡ ሥልጣናቸውን መጠበቅ፣ የአማካሪዎችን ምክር አለመቀበል፣ ለውጦን ለማንበብ አለመቻልና ለኢትዮጵያ የእርሳቸው መፍትሔ ብቻ እንደሚጠቅም ማሰባቸው ችግሮችን አባብሷል፡፡ በ1953ቱ የታህሳስ ግርግር የጀመረው የቁልቁለት ጉዞ በ1966 ፍጻሜውን ሲያደርግ ይህ ነው የሚባል እርምጃ አለመውሰዳቸው ለእርሳቸው፣ ለዘውዳዊ ስርዓቱም ሆነ ለሚመኛት ዓይነት ኢትዮጵያ ፍጻሜ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአጭሩ የቀረበ፣ ሰፊ ዋቢ መጻሕፍትን ያካተተና ወደ ንጉሠነገሥቱ ሰፊ ታሪክ ጥሩ መግቢያ ሊባል የሚችለውን ይህን መጽሐፍ እንዳገኘሁት ግማሽ ድረስ አንቤው ነበር፡፡ በኋላ በተረጋጋ ሁኔታ ላንብበው ብዬ ተመልሼ አነበበብኩት፡፡ ድብልቅልቅ ስሜት አምጥቶብኛል፡፡ እንደማንኛውም የታሪክ መጽሐፍ ሊሆን ቢችልም በአያያዝ ጉድለት አገሪቱ ላይ የተከሰተውን ነገር ስላስታወሰኝ መጨረሻ ላይ የትካዜ ስሜት ተሰምቶኛል፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...