2022 ዲሴምበር 30, ዓርብ

ሀሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር

 

ሀሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር

ከብ/ጄ ውበቱ ፀጋዬ

 


አንዳንድ ቃንቄ ነጥቦች - በመዘምር ግርማ

707 ገጹን በ797 ቃላት

 

ከ1970 ሐምሌ ወር እስከ 1983 ዓ. ም. የተነፈገ ድል፣ ዝክረ ሠራዊት ኢትዮጵያ የሚል ንዑስ ርዕስን በውስጠኛው ሽፋኑ የያዘው መጽሐፍ በ425 ብር ከደራሲው ጥቅምት 19፣ 2015 ተፈርሞ የተሸጠልኝን ሲሆን በሁለት ወሩ ታህሳስ 22፣ 2015 ዓ.ም. ይህችን ማስታወሻ ልጽፍለት በቃሁ፡፡ ከፌስቡከ ሱስ በተረፈችኝ ጊዜ ስለማነብ ዘገየሁባችሁ፡፡ በ707 ገጽ የተሰናዳውን ይህን በዓይን እማኝነት ላይ የተመሰረተ ታሪክ በማነብበት ወቅት ‹‹አንድም የሚወድቅ ቃል የሌለው የታሪክ ማስታወሻ›› ስል ነበር፡፡

ለ30 ዓመታት በሰሜን ጦር ግንባር ደሙን ያፈሰሰውንና አጥንቱን የከሰከሰውን 300 000 ሰራዊት ታሪክ በብርጌዲየር ጄኔራል ውበቱ ብዕር ተከትቦልን በአድናቆትና በቁጭት እናነባለን፡፡ ዘመናዊ ትምህርታቸውን አቋርጠው በፍላጎታቸው ወደ አገር መከላከያ የገቡት ብርጌዲየር ጀነራሉ የመጀመሪያ ግዳጃቸው አንድ የመቶ ጦር ይዘው የዘመቱበት የኮንጎ ዛየር ዘመቻ ሲሆን፤ አውሮፕላናቸው ዛየር ለማረፍ ሲያንዣብብ የጠላት ቤልጂየም አውሮፕላን መስሏቸው ኮንጓውያኑ በጸረ-አውሮፕላን ለመምታት ደጋግመው ቢተኩሱበትም ስላልመቱት አርፎ ባለታሪኩ በአየር ማረፊያው የነበረውንና ለእርምጃ የተዘጋጀውን የኮንጎ ጦር በፈረንሳይኛ አናግረው የኢትዮጵያ የሠላም አስከባሪ መሆናቸውን በማስረዳት ጦሩን ከሞት ታድገውታል፡፡ በኮንጎ ከቅጥረኛ ሰራዊት ጋር ጭምር ልዩ ልዩ አስቸጋሪ ግዳጆችን ተወጥተዋል፡፡ ፓትሪስ ሉሙምባን ከማግኘት ጀምሮ ብዙ ትምህርት ያገኙበትን የኮንጎ ዘመቻ በድል አጠናቀው ሜዳይ ተሸልመው አገራቸው ገብተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከተመሰገነችባቸው ሁለት ዘመቻዎች የኮሪያን ጨምሮ አንዱ የሆነው ይህ ዘመቻ ኢትዮጵያውያን እስከ አዛዥነት የደረሱበትና ከማንኛውም አዛዥ በላይ አስደማሚ የጦርሜዳ ጀብዱዎች በመፈጸም የተመሰገኑበት ነበር፡፡

በባሌና ሲዳሞ ክፍለሃገራት የዘመቻ መኮንንና የሻምበል አዛዣ በመሆን በሰሩባቸው ጊዜያት በሶማሊያ ከሚደገፉት አመፀኞች ጋር የነበራቸውን ፍልሚያ እናያለን፡፡ የክፍለሃገራቱም ሰላም ዋቆ ጉቱ በይቅርታ ለመንግሥት እጃቸውን እስከሰጡበትና የመጨረሻውን ዘመቻ በድል የመሩት ሌ/ጂኔራል ጃገማ ኬሎ በአስተዳዳሪነት እስከተሾሙበት ድረስ ሲናጋ ቆይቷል፡፡ የሁለቱ ክፍለሃገራት ብቻ ሳይሆን የመላው አገሪቱ ፀጥታ በየዘመኑ ምን ያህል እየተናጋ የሚሄድ፣ ለልማት ስራ የሚያደናቅፍና የመንግሥትን ትኩረት እንደሚፈልግ መገንዘብ ይቻላል፡፡

በሆለታ ገነት ቀ.ኃ.ሥ. ጦር ትምህርት ቤት ተመድበው ካገለገሉ በኋላ ከመንግሥት ለውጡ በኋላ በ1968 ወደ ራዛ ዘመቻ አቅንተዋል፡፡ የነበልባል ክፍለጦር ዘመቻ ትምህርትና መረጃ መኮንን ቀጣዩ ማዕረጋቸው ሲሆን በሰሜንና በሰሜን ምዕራብ ከተገንጣዮችና ከኢዲዩ ፈታኝ ችግር በነበረበትና ደርግም ከንጉሠነገሥቱ የተረከበውን ሥልጣን ባላረጋጋበት ጊዜ የነበሩ የዘመቻና የሥልጠና ተግባራትን የፈጸሙባቸው ዝርዝር ማብራሪያዎች ተካተዋል፡፡ ያልታሰበው የመንግሥት ለውጥ አገሪቱን ለቀጣይ ሁለት አስርት ዓመታት ባልተጠና ሁኔታ በአንድ ሰው የስልጣን ጥማትና ስሜት እንድትመራና ወደኋላ እንድትጓዝ እንዳደረገ ከዚህ መጽሐፍ ዘመቻዎችና የድል መቀልበስ መረዳት እንችላለን፡፡

የከፍተኛ እግረኛ መኮንን ትምህርት በአሜሪካ አገር የተከታተሉት ባለታሪካችን ከብዙ አገራት ሰልጣኞችና ከሥልጠና ተቋሙ ጠቃሚ ልምድ ቀስመዋል፡፡ የምድር ጦር ምክትል ዘመቻ መኮንን ፣ የ28ኛ ብርጌድ ዋና አዛዥ፣ የሰሜን ዕዝ ትምህርትና ዘመቻ መኮንን፣ ወደ ደቡብ የመን የሄደው የወታደራዊ ዴሊጌሽን አባል፣ በዘመቻ፣ በመረጃና በትምህርት የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት ምክትል አዛዥ፣ የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት አዛዥ፣ ወታደራዊ አማካሪ በፕሬዚዳንቱ ቢሮ፣ በብሔራዊ ውትድርና ሲቪል መከላከል ዋና መምሪያ ኃላፊ የሚሉት የረጅሙ የሕይወት ጉዟቸውን የሚገልጹት የሥራ መደቦች ከወጣትነት ዘመናቸው ጀምሮ ለአገራቸው የተፋለሙና የሰሩባቸውን ቦታዎችና ጊዜያት ስፋት ያሳያሉ፡፡

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተደረገው ሦስት አስርት ዓመታት የፈጀ ጦርነት ከመንግሥትም ሆነ ከተገንጣይ ወገን ብዙ ጦር ያለቀበት፣ የተጎዳበትና የተሳተፈበት ነው፡፡ በውስጥ አስተዳደር ችግር፣ በዉጪ ኃይሎች ድጋፍና በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሰሜኑ ጦርነት አሁን የማንፈልገው ውጤት ሊኖረው ማለትም አጋችንን ለሁለት ሊከፍልና የባህር በር ሊያሳጣን ችሏል፡፡ መጽሐፉን በመድረክ ባስተዋወቁበት ወቅት ኤርትራ ወደ እናት አገሯ እንደምትመለስ ያላቸውን ተስፋ የገለጹልን ባለታሪኩ የኤርትራ ህዝብ ለኢትዮጵያዊ አንድነቱ የወጣ የወረደበትን ለአስርት ዓመታት ስላዩ ነው፡፡ ይህንንም በመጽሐፋቸው በጥልቀት አስነብበውናል፡፡ በርካታ የመስዋዕትነት፣ የድል፣ የሽንፈት፣ የተስፋመቁረጥና የጀግንነት ታሪኮቻቸውንም አጋርተውናል፡፡ የሁለተኛው አብዮታዊ ሰራዊት አዛዥ ሆነው በሻዕቢያ ተከበው ሊማረኩ በተቃረቡበት ወቅት የራሳቸውን እርምጃ በመውሰድ ራሳቸውን ሰውረው ወደኋላ የሁለት ቀን የእግር መንገድ ርቀው በመሄድ ሌላ ረጅም መንገድ ያለ ምግብና ውኃ ይጀምራሉ፡፡ ቋሚ የሰውነት ጉዳት እያሰቃያቸው በሞትና ሕይወት ካከል ሆነው ሲጓዙ እርሳቸው ሳያውቁት በቅርብ ርቀት እየተከታተለ ያገዛቸውን የትግራይ ተወላጅ፣ በኋላም ያገኙትን የባሌ ተወላጅ፣ ከዚህም ተከትሎ አግኝተዋቸው ያጀቧቸውን ሰባት ወታደሮች ስናይ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ጊዜ ሳይቀር ምን ያህል የቋንቋና የብሔር ጉዳይ ሳያግዳቸው ለአንድ ዓላማ እንደተሰማሩ እናያለን፡፡ የናቅፋን፣ የቀይባህርን፣ የአፋቤትን፣ የከረንን፣ የአስመራን፣ የመሳህሌትንና የበርካታ ቦታዎችን የሰላምና የጦርነት ጊዜ ማስወሻዎችና የአውደውጊያ ዘገባዎች ሲያነቡ ፊልም የሚያዩ እንጂ መጽሐፍ የሚያነቡ አይመስልዎትም፡፡ በየአውደውጊያዎቹም ሆነ በአጠቃላይ በሰሜኑ የጦር ግንባር የተሸነፍንባቸውን ምክንያቶች ከአንድ መሪ ሲረዱ በወታደራዊ ሳይንስ የተደገፈውን ውሳኔ፣ የዘመቻ ሁኔታና ትንታኔ ማወቁ እንደ ዜጋ አስተማሪ ከመሆኑ በዘለለ ለወደፊቱም ጠቃሚነቱ የጎላ ነው፡፡ አንድ ጀግና ሕዝብ በሁለት ጎራ ተከፍሎ ሲዋጋ የሚኖረውን እልቂት መታዘብ ይችላለ፡፡

በ1981 መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት የታሰሩት ባለታሪኩ አብዮታዊ እርምጃ የተወሰደባቸውን አገሪቱ መልሳ መተካት የማትችላቸውን አዛዦች ሁኔታም ያስቃኙናል፡፡ በእርግጥ  የብ/ጄኔራል ታሪኩ ዓይኔንም ፍጻሜ በቅርበት ስለሚያውቁ መረጃውን ከአባሪ ጋር አስነብበውናል፡፡ በጨረሻም የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የወደቁትን ጀግኖች ከራስ አሉላ በመጀመር አብረዋቸው እስከተፋለሙት ድረስ ታሪካቸውን በአጭሩ አንድ ክፍል መድበው አስነብበውናል፡፡ ይህም የጀግኖቹን ታሪክ ከማውሳት በዘለለ ምንም ያልተጻፈላቸውን ጀግኖች ታሪክ እንድናውቅ ያግዘናል፡፡ የራስ አበበ አረጋይንም ታሪክ አካተዋል፡፡ ቦታና ቋንቋ ሳይገድባቸው የሁሉንም የኢትዮጵያ ጀግኖች ታሪክ አካተዋል፡፡ የሳሲቱን ተወላጅ የናቅፋውን ጀግና የሌ/ኮሎኔል ማሞ ተምትሜን ታሪክ አካተው ማግኘቴም በፊት ከሰማሁት በላይ አንዳንድ ነጥቦችን ጨምሮልኛል፡፡ በትውልድ ቦታ ብቻ ሳይሆን አሁን ይህን ማስታወሻ ከምጽፍበት በጠባሴ የባህር ኃይል ግቢ መታሰቢያ ሐውልታቸው ስለሚገኝ የእርሳቸውን ታሪክ ለማወቅ እፈልግ ነበር፡፡ ብዙ የተማርኩበትና የገረመኝ መጽሐፍ ነው፡፡ የሻዕብያ ከንቱ ጽናት፣ የኤርትራ ህዝብ ለሻዕቢያ ያሳየው ወገንተኝነት፣ የኢትዮጵያ ሰራዊት አገሬ ብሎ በጽናትና ተስፋ ባለመቁረጥ ሕይወቱን የገበረበት ርቀት፣ ሻዕቢያ ሳይቀር የሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች ጀግንነት! የሻዕቢያ መሪዎች በአረብ አገር እየተዝናኑ ህዝቡን ማስጨረሳቸው፣ ከኋላ በመትረየስ እየተነዳና አእምሮው በሃሰት ፕሮፓጋንዳ አየታጠበ በግዳጅ የእሳት እራት የሆነው የሻዕቢያ ታጋይ፣ አገርን ለማፍረስ የተከፈለው ከንቱ መስዋዕትነትና አሁን ኤርትራም ሆነች ኢትዮጵያ ያሉበት ድህነት! ለማንኛውም መነበብ ያለበት መጽሐፍ ነው!     

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...