2022 ዲሴምበር 23, ዓርብ

ከማስታወሻ ደብተሬ

መዘምር ግርማ

ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ ስንሄድ ጎን ለጎን ተቀምጠናል፡፡ ሰንዳፋ ላይ በድንገት ንግግር ጀመርን፡፡

‹‹እንዴት ይፈጥናል በእናትሽ!››

‹‹በጣም! አነሳሳችንም በጠዋት ነው፡፡››

‹‹እያነበብክ ስለነበረ እንዳልረብሽህ ብዬ ነው እስካሁን ያላወወራሁህ፡፡››

ዋና ዋናዎቹ ስንተዋወቅ የነገረችኝ መረጃዎች እነዚህ ናቸው፡፡

የመጣችው - ሲያትል፣ ዋሽንግተን፡፡

የኖረችው - ለሁለት አስርት ዓመታት፡፡

አጠቃላይ ሕይወቷ ላይ ያላት ዕይታ - አስደሳች የሚባል ይመስላት ነበር፡፡

ስራ - ነርስ፡፡

በኢትዮጵያ የነበራት ስራ - ሜዲካል ዶክተር፡፡

‹‹ከዶክተር ወደ ነርስ ግን ትንሽ አይከብድም?››

‹‹አይ አንተ! ሰው እኮ ለመለወጥ የማይገባበት የለም፡፡››

እዚያ በነርስነት ስትሰራ ጥሩ ገቢ ታገኝ ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ ሆስፒታላቸው የመጡ ታካሚ የሚያነቡትን መጽሐፍ አይታ ስለምን ይሆን ብላ ጓጉታ ጉግል አደረገች፡፡ እንደ አንዳንድ የየዛሬ ሽማግሌ የኢህአፓ ዘመን ወጣት አንባብያን ልማድ በጋዜጣ ቢሸፍኑት ኖሮ ርዕሱን ማየት አትችልም ነበር፡፡ እንኳንም አልሸፈኑት! ርዕሱ ‹‹The 7 Habits of Highly Effective People›› ነው፡፡ ጨርሳ አነበበችው፡፡ በሕይወት ሀዲድ ቆም እንድትል አስገደዳት፡፡

‹‹የሕይወቴን ዓላማ እንድከልስ አስቻለኝ፡፡ ይሁን እንጂ ደግሜ ማንበብ እንዳለብኝ ገባኝ፡፡ ደግሜ ሳነበው ጉግል ሳደርግ ወርክ ቡክም እንደነበረው ተረዳሁ፡፡ ያንን ገዝቼ እየጻፍኩበት አነበብኩት፡፡ ወደ ውስጤ ማስገባት ቻልኩ፡፡  በጣም ስለተመቸኝ ስልጠናውንም እወስዳለሁ ብዬ ነበር፡፡ ሃሳቡ ገብቶኛል ብዬ ስላሰብኩ ግን ተውኩት፡፡ በነገራችን ላይ እስካሁን ካላነበብከው ብታነበው ጥሩ ነው፡፡››

‹‹አንብቤዋለሁ፤ ቀጥይ፡፡››

‹‹ውይ እንኳንም አነበብከው! ከሆነ ትረዳኛለህ፡፡ ያንተን አረዳድ ቆየት ብለህ ትነግረኛለህ፡፡››

‹‹ከሰባቱ ልማዶች ሁለተኛው በእርግጥ ስሜቴን ነካው፡፡ ከመጨረሻው ጀምሪ ይላል ምክሩ፡፡››

‹‹Begin with the end in mind››

‹‹እዚያ ውስጥ አንድ የሚያስደነግጥ ነገር አለ፡፡ ፍጻሜሽን ለማየት ብሎ የሚያሰራው ነገር አለው፡፡ የቀብር ልምምድ አድርጊ ይላል፡፡››

‹‹Funeral experiment?››

‹‹እግዜር ይስጥህ! ቤተክርስቲያን ሄደሽ የቀብር ሥነሥርዓት ላይ እየተሳፍሽ ነው ይላል፡፡ ያ ቀብር ከመፈጸሙ በፊት ተሰናበቱ ተብሎ በባለመስታወቱ የአስከሬኑ ሳጥን ውስጥ የተቀመጠውን ሬሳ ስታዪ ራስሽ ነሽ ብሎ አስደነገጠኝ፡፡ በዚህ ሳያበቃ ከጓደኞች፣ ከሥራ ባልደረቦች፣ ከቤተክርስቲያን ሰዎችና ከቤተሰብ አንድ አንድ ሰው ስላንቺ መሞት ምን የሚያስቡ ይመስልሻል አለኝ፡፡ እኔም ጓደኞቼ እንደሰው ቶሎ ቶሎ አገሯ ሳትሄድና ዘመድ ሳታይ ሞተች እንደሚሉ፣ የሥራ ባልደረቦቼ ከሰው እንደራቀች አንድ ቀን ሳተጫውተን ሞተች እንደሚሉ፣ የቤተክርስቲያን ሰዎች በኃይማኖቷ ጉዳይ አስተዋጽሳታደርግ ንስሐ ሳትገባ ሞተች እንደሚሉ፣ ከሁሉም በላይ ቤተሰቦቼ ግን ከልብ የማይወጣ ሐዘን እንደሚያድርባቸውና ለእነሱ ኑሮ መለወጥ ምክንያት ብሆንም ልጅ ባለመውለዴ እንደሚያዝኑ ታየኝ፡፡››

‹‹አደጋ ላይ ኖረሻል በእውነት! ቤተሰብሽ ግን ገንዘብሽ ስለሚጥማቸው ልጅ አመውለድሽ ላይደንቃቸው ይችላል፡፡››

‹‹እንዴ ተው እንጂ! ለማንኛውም ይህንን ሃሳብ ካስተናገድኩ በኋላ ‹‹በይ ሕይወትሽ በዚህ ፍጻሜ አላገኘም፤ አልሞትሽም፡፡ ሦስት ዓመት ልስጥሽና በነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ያልተስተካከለውን አስተካክዪ አለኝ፡፡››

‹‹ወደ መስመር መግቢያውን መንገድ አገኘሻ በአንዲት መጽሐፍ!››

‹‹ኧረ ተወኝ ወንድሜ!››

‹‹አንጀቴን አራሰው አንቺ! ደግ አድርጓል ኮቬይ፡፡››

‹‹ምክንያት ሆነኝ በእውነት፡፡ እንጂማ ስንት ፊልም ያየሁ፣ ስንት ትልልቅ ሰው ጋር የተገናኘሁ፣ ስንት ልምድ ያለኝ ነኝ እንደ አቅሚቲ፡፡››

አንቺ ስላት ግን ትንሽ ቅር እያለኝ ነው፡፡ ሽበት ጀማምሯታል፤ ቆዳዋም ማሸብሸብ ጀምሯል፡፡

ጊዜያችሁን እንዳልሻማባችሁ ባጭር ባጭሩ ልንገራችሁ እስኪ፡፡ አንድ አርጀት ያለና ሚስቱ የሞተችበት የበፊት የትምህርት ቤት ጓደኛዋን አግኝታ አግብታለች፡፡ የሱን ልጆች እንደልጆቿ ታያለች፡፡ ማሚ ይሏታል፡፡ መውለድ አትችልም፡፡ ተላልፏታል፡፡ በበጎ አድራጎት ላይ ትሳተፋለች፡፡ ለጓደኞቿ ጊዜ ትሰጣለች፡፡ የቤተክርስቲያን ተሳትፎዋ ቀላል አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ላይ የግል ስራ ጀምራለች፡፡ ስራውም ለየት ያለ ስለሆነ ደህና እየሄደላት ነው፡፡ ሥራው በተፈጥሮው ከውጪም የተያያዘ ስለሆነ በኢንተርኔት ከአሜሪካ ድርጅቶች ጋር ትሰራለች፡፡ በቢዝነሱ ስኬታማ ነች፡፡ ሥራዋን የማስፋፋትንና ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ የመሥራትን ሃሳብ ሲታስብ ከጸጥታም አንጻር ደብረብርሃን መጣችላት፡፡ ቦታ ተቀብላ ሥራ መጀመሯን ነገረችኝ፡፡ ቤት የገዛችው ጣፎ ላይ ስለሆነ ተሰናብታኝ ወረደች፡፡ መኪናዋ ገራዥ ስለገባች በህዝብ ትራንስፖርት መሳፈሯን ነገረችኝ፡፡ እኔም ይህን ለመስማት የቻልኩት በሚኒባስ በመሳፈሯ መሆኑን አስቤ መኪናዋ የተበላሸው በምክንያት መሆኑ ገባኝ፡፡ ለቤተመጽሐፌ መጽሐፍም እንደምትለግሰኝ ገልጻ አድራሻዬን ወሰደች፡፡ የሰውን የግል መረጃ ማጋራት ባይኖርብኝም ታሪኩ አስተማሪ ስለሆነ አጋራኋችሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...