ኢትዮጵያን ለማዋለድ እነማን እንደከሰሙ የሚማሩበት መጽሐፍ
‹‹ሰሎሞናውያን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ (1261-1521)፣ በደረሰ አየናቸው (ዶ/ር)››
ማስታወሻዎች - በመዘምር ግርማ
መስከረም 2016 ዓ.ም
በአዜባዊነት ተምኔታዊ ርዕዮት ብሔረ-ኢትዮጵያን ያዋለደው ዘመን ታሪክ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ እንዳይጠና ጫና እንደተደረገበት በመግለጽ የሚጀምረው ይህ መጽሐፍ ሰሎሞናውያን እንዴት ገናና መንግሥት መመስረት እንደቻሉ፣ ኢትዮጵያን ከእስልምና እንደጠበቁ፣ ምን ዓይነት የግዛት ማስፋፋትና የአስተዳደር ሥርዓት ሂደት እንደተከተሉ እንዲሁም ሰፊውን የአፍሪካ ቀንድ እንዴት ማስተባበር እንደቻሉ የሚያትት ሰፊ የምርምር ሥራ ነው፡፡ የዳኣማት ሳባውያን (963-142 ዓ.ዓ.)፣ የአክሱም (60-632 ዓ.ም.)፣ የድኅረ አክሱም (632- 1127 ዓ.ም)፣ የዛጉዌ (1127-1262 ዓ.ም.) ታሪክ በአጭሩ የቀረበበት ሲሆን የዳኣማትን እስከ የመን የዘለቀ ግዛት፣ የአክሱምን ሥልጣኔ፣ የድህረ አክሱምን ልዩ ልዩ ውጣውረዶች ብሎም የዛጉዌን ተከታይ ዘመን ከነመሪዎቹ፣ ከነዘመኑ ቀለማትና ጉልህ ክስተቶች በአጭሩ ያነሣሣል፡፡
ከመጽሐፉ የወሰድኳቸውን አንዳንድ ሃሳቦች የታሪኩን ሂደት ከተከተለ ማስታወሻ ጋር የማቀርብበት ይህ ጽሑፍ ዳሰሳ እንዳይባል የታሪክ ባለሙያ ስላልሆንኩና ዕውቀቱ ስለሚያጥረኝ እዚህም እዚያም ቢረግጥ እንዳትደናገጡ፡፡ ‹‹…በ7ኛው ክፍለዘመን የሕጻና ዳንኤል ከወልቃይት ሰዎች እጅ አክሱምን ለማዳን ያደረገው ትግል›› ሲልና በሌላም ቦታ በአይሁዶች መኖሪያነት ወልቃይትን ሲጠቅሳት የአሁኗ አነጋጋሪ ቦታና ጎረቤቶቿ ያኔም እንዲሁ አነጋጋሪ ነበረች እንዴ አስብሎኛል፡፡ የእርሻ መሳሪዎች አምራች ቤተእስራኤሎች ርስት የተከለከሉ ናቸው፡፡ ይህንን ቤተእስራኤል በሚል በቅርቡ በወጣ መጽሐፍም በዝርዝር አንብቤያለሁ፡፡ ‹‹ዳኛዣንም 150 ካህናትንና 60 ታቦታትን ወደ አምሓራ በማምጣቱ ክርስትናን እንዳስፋፋ ይተርካል፡፡… በአምሓራ በሐይቅ …›› ሲል የአሁኑንና የያኔውን አማራ ሁኔታ ለማገናዘብ መነሻ የሚሆን ጠቃሚ ሰነድ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ሌሎቹንም ቦታዎችና ህዝቦችበም ሁኔታ እንዳነሣቸው እንመጣበታለን፡፡
በ12ኛውና 13ኛው ክፍለ ዘመን የእስልምና እድገት ዘመን የዛጉዌ ስርወ መንግሥት መገልበጥንና የእስላም ስርወመንግሥታትን መገለባበጥ እንመለከታለን፡፡ ሰሎሞናውያን ሲነሡ ሰሜናዊ ቅንጅታቸውን ልብ እንላለን፡፡ ይኩኖ አምላክ በመንግሥቴ ውስጥ ሙስሊም ወታደሮች አሉ ብሎ ከግብጽ ጳጳስ ለማግኘት የላከውን የሐሰት ደብዳቤ እንታዘባለን፡፡ የዚህን ሐሰትነት የጻፈው ልጁ ውድምአርድ ደግሞ ከሐይቅ እስጢፋኖስ ጋር ችግር ውስጥ ገብቶ ጉልታቸውን ነጥቋቸው ነበር፤ ዳሩ አምደጽዮን መለሰላቸው እንጂ፡፡ የግዛት መስፋፋት መሐንዲሱ አምደ ጽዮን ወደ ምጽዋ ሲገባ ዝሆን ጋልቦ ሳነብ ይህ 99 ነገሥታትን ያስገበረ ንጉሥ ብዙ አዲስ ነገር አለው ብዬ እንዳነባብብ አነሣሥቶኛል፡፡ ሰበረዲን እስላማዊ መንግሥት ለመመስረት በማሰብ አምደ ጽዮንን ከነንግሥቲቱ ለማስለም እንዳሰበው ሁሉ ሌሎችም ተቀናቃኞች ክርስቲያኖቹን ነገሥታት ለማስለም አስበው አልተሳካላቸውም፡፡ በእርግጥ ንጉሡ አምደ ጽዮን የክርስቲያኑም የእስላሙም ንጉሥ መሆኑን ተናግሯል፡፡ አሕዝብ ሲያምጽ የሁለት ወር መንገድ ወስደው ያሰፍሩታል ማለትን አስደንጋጭ አድራጎት ብያለሁ፤ ታንዛኒያ እንዳይሆን ብቻ፡፡ ለመጽሐፉ በዋቢነት ያገለገሉት የአረብ ጸሐፍት መጻሕፍት የተጻፉት ኢትዮጵያውያን ሐጃጆች ወደ መካ ሲሄዱ እዚያ አግኝተው በሚጠይቋቸው የታሪክ ጸሐፊያን መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ቀደምት ፀሐፍት የአገላለጻቸው ትክክለኛነት የሚያስገርመው አንድ ቦታ ያለበትን ስፍራ ወይም የግዛቱን ልክ ሲገልጹ ‹‹የአበሻ ግዛት ከቀይ ባህር እስከ ዘይላ›› ዓይነት አገላለጽ ስለሚጠቀሙ ነው፡፡ የያኔዋን መንግሥታችንን ስፋት (ያውም የየመኑ ጠቦ) ያሳያል፡፡ ከሁሉ የሚያስገርመውና ለአሁን ዘመን የአስተዳደር ችግር እንደ ትምህርት ልንወስድለት የሚገባን የስልጣን ሽኩቻን ማርገቢያ ዘዴ ይኩኖ አምላክ የተጠቀመውን ዓይነቱ ሲሆን፤ ይኸውም አምስቱን ልጆቹን በየተራ በየዓመቱ የመሪነት ሥልጣን የሚያስይዝበት ነው፡፡ እንዳለ እንተግብረው ባይሆንም ለትምህርት ይሆነናል፡፡
ነገረ ኦሮሞ በሰፊው የተዳሰሰ ሲሆን የትመጣቸውም ሆነ መችመጣቸው ከልዩልዩ ጥናቶች ተጠናቅሮ ቀርቧል፡፡ የኦሮሞን ታሪክ በፖለቲካ ቅኝት ለማቅረብ ብዙዎች መጣራቸውን ከመጽሐፉ ስንረዳ የጉዳዩን የሰርክ አወዛጋቢነት እንገነዘባለን፡፡ በ16ኛው ክፍለዘመን ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ መጥተው ቦታዎችን መሰየማቸውን መጽሐፉ ገልጾ እነዚህን የቦታዎች ስያሜዎች በመጠቀም ከዚያም በፊት ነበርን የሚል የታሪክ ቅርምት ውስጥ በኦሮሞ የታሪክ ሊቃውንት መገባቱን ያስገነዝበናል፡፡ በመንዝ የተገኙ ከ9ኛው - 14ኛው ክፍለዘመን የተሠሩ ክምር ድንጋዮች የነዋሪዎቹን መገልገያዎችና ጨሌዎችን ይዘዋል፡፡ የነባር እምነት አማኞች መሆናቸውን የጅምላ ቀብሩም ያሳያል፡፡ ጨሌ ያላቸው ሁሉ ኦሮሞዎች ናቸው በሚል የቀረበውን መላምት ተችተውታል፡፡ በ1830ዎቹ የኦሮሞን ታሪክ አስመልክቶ የጻፈው አንቶን ዲ አባዲ ስያሜያቸው ኦሮሞ መሆኑን ጽፏል፡፡ በጦርነት ጊዜ ከሚያሰማው ፉካሮ የተነሳ ሌሎች ሌላ ስም ሰጡት ቢባልም የኬኒያ ኦሮሞ በዚያው ስም እንደሚጠራ ያስገነዝበናል፡፡ ይህንን የኬኒያውን በእርግጥ ቀድሜም አንብቤ ነበር፡፡ ሁለቱ የወቅቱን የመረጃ ምንጮች ማለትም የፖርቱጋሉን የአልቫሬዝንና የአረቡን ፋቂህን ዝንባሌ ሲጽፍ የመጀመሪያው የክርስቲያን መንግሥት ማግኘቱንና ኃያልነቱን አጉልቶ ሲጽፍ፤ ሁለተኛው ክርስቲያኑን አንኳሶ እስላማዊ መንግሥት ስለመመስረት ማለሙን አስጨብጦናል፡፡
የታሪኩ ይዞታ የሴምና ኩሽ ሃሳብን እስካሁን በምናውቀው መልኩ ማቅረቡ በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ከተነሳው ሃሳብ በተለየ ያንጸባረቀ ሥራ ነው፡፡ በአንደኛ መደብ ብዙ ቁጥር የተጻፈው የዶክተር ደረሰ የባለሙያ ድርሰት በልዩ ልዩ ማስረጃዎች የበለጸገ ነው፡፡
የጨዋ ሰራዊት የዘርአያዕቆብ ልዩ የግዛት መቆጣጠሪያ መንገዱ ነበር፡፡የተዘዋዋሪና መናገሻ ከተማ አልባ መንግሥትን ጅማሮ ስናይ ደግሞ ከተማ ንጉሥ የሚለውን ሃሳብ እናገኛለን፡፡ ይኸውም ንጉሡ በሚዘዋወርበት ጊዜ የሚሰፍርበት ከተማ ነው፡፡ ከ30 ሺህ እስከ 40 ሺ ሰው ንጉሠነገሥቱን ተከትሎ ይሄድ ነበር፡፡ ከ100 000 በላይ የጭነት ከብቶች ያሉት የንጉሥ ከተማ በአንድ ግብር ላይ ከ34000 በላይ ሰው ለአንድ ሳምንት ይገባበታል፤ ይጋበዛል፡፡ ንጉሥ ዘርአያዕቆብ አፄ-ፀላ የሚባል መጠጥ ያዛል፡፡ 12 መግቢያዎች ያሉት ከተማ ንጉሥ ሁለተኛው አጥሩ ጀጎል ይባላል፡፡ ባልተፈቀደልዎት መግቢያ መግባት ያስቀስፋል - በቀስት! በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደብረብርሃን፣ የረር፣ ዝቋላ የነገሥታቱ ከፊል ቋሚ መቀመጫዎች ሆኑ፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት አንድ መናገሻ እንዲኖር ስላስፈለገ የእስራኤልን ትውፊት ተከትለው ጀምረውታል፡፡
ቤተክርስቲያን ተከፍላ መንግሥቱም ተከትሏት እንዳይከፈል ነገሥታት ስለሚሰጉ አስተምህሮውን በጥንቃቄ ይከታላሉ፡፡ ቤተክርስቲያንን መቆጣጠር ስልጣንን መቆጣጠር ተደርጎ ተወሰደ፡፡ የሰንበት ጉዳይንም ያስወሰኑት አከራክረው ነበር፡፡ ከዓለም በተለየ ቅዳሜና እሁድን ሰንበት አድርገዋል፡፡ በተለይ አፄ ዘርዓያዕቆብ ቤተክርስቲያን ላይ ባመጡት ለውጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሰሎሞናውያን ኃይማኖታዊ ብሔረተኝነት ተስፋፍቷል፡፡ ዘርዓያዕቆብ ነባር እምነቶችን የበለጠ ማጥፋት ሥራቸው አድርገው ያዙ፡፡ በእርግጥ ሦስት ሚስቶችን ማግባት የነባር እምነቶች ልማድ ነበር፡፡ ዘርዓያዕቆብን ጨምሮ ነገሥታት ለፖለቲካ ዓላማ ፈጽመውታል፡፡ ሀድያ በዓለምአቀፍ የሲራራ ንግድ መስመር ሆኖ ንጉሡ ግን በማስቸገሩ በፖለቲካዊ ጋብቻ ልጁን እሌኒ መሐመድን ዘርዓያዕቆብ በሁለተኛ ሚስትነት ያዟት፡፡ በፖለቲካዊ ጋብቻ ያልሆነውን ደግሞ በጦር ይወጉታል፡፡
የኃይማኖት ክፍፍልን ሁኔታ ስንቃኝ ደግሞ ደቂቀ እስጢፋኖሶች ተገደሉ፤ ተጋዙ፡፡ አባ እስጢፋኖስ እንደ ማህተማ ጋንዲ ሁሉ መነኮሳት በራሳቸው እጅ ሠርተው መተዳደር ይገባቸዋል የሚሉ ነበሩ፡፡ ደስክን በመሳሰለው ነባር እምነት ላይም ተጽዕኖ ተጣለ፡፡ የክርስትና መምጣት አምልኮ ጣዖትን ሙሉ በሙሉ አላስቆመውም፡፡ በማዕቀቡም ምክንያት ነባር እምነቶች በህቡዕ አምልኮነት ተወሰኑ፡፡ በዚህም ውህድ እምነት ቀጠለ፡፡ በበዓል የማይሰሩ ስራዎች ተደነገጉ፡፡ እነዚህ ሥራዎችም ዋና ዋና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሰረት የሆኑ ሥራዎች ሲሆኑ የመስኖ ሥራን ይጨምራል፡፡ ሰራተኞች መምታትንም እንደ ሥራ ወስደው ከዝርዝሩ ከተውታል፡፡ ህዝቡ በነዚህ ቀናት ቤተክርስቲያን ስብከት እንዲሰማም ታወጀ፡፡ የታቦት ነገር በግብጽም ሆነ ሌሎች አብያተክርስቲየናት አይታወቅም የሚል ሃሳብም በመጽሐፉ አለ፡፡ የመካከለኛው ዘመን ሲቪል አስተዳደርን አስመልክቶ የመጽሐፍ ማደራጃ መኖሩ የዘርአያዕቆብንና የዘመኑን ጥረት ያንፀባርቃል፡፡ ባለማዕረግ ዐቃቤ ሰዓትም (አማካሪ) ነበር፡፡ የፍርድ ሂደትን ስናይ አከራክሮ የሚወስንና ይግባኝ የሌለው የመጨረሻው ንጉሡ ነበር፡፡ ሹማምንት ግብር መክፈል ብቻ ሳይሆን ስግደት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመስቀል በዓል የቀድሞ የአደባባይ የጣዖት አምልኮዎችን የተካ መሆኑም ተገልጧል፡፡ በተያያዘ ሞተለሚ የዳሞት ማዕረግ ስያሜ መሆኑን እኔ ባደኩበት ስፍራ ያለውን የሞተለሚን ጅረት ስያሜ በመላ ምት ለሚያጨናንቁ ጥሩ ትምህርት ነው፡፡ የዳሞቱ ሞተለሚ በአቡነ ተክለሃይማኖት ክርስቲያን ሆኗል ይላችኋል፡፡
በ16ኛው ክፍለ ዘመን ፈጠጋር ለጤፍ ምርት አመቺ ነበር ሲል ቡልጋ፣ ምንጃር፣ ሸንኮራም የንጉሥ ምግብ ይባል የነበረውን ጤፍን ያመርቱ ነበር ሲል አሁንም ይህ ልማድ አለመጥፋቱን ልብ ይሏል፡፡ የዘርአያዕቆብ ልጅ የተገደለው በስልጣን ሽኩቻ እንጂ በሰፊው እንደሚወራው በሌላ እንዳልሆነ በራሳቸው በአባትዬው መጽሐፍ መገለጡን አንብቤያለሁ፡፡
በ1521 ኢማም አህመድ ልብነድንግልን በሽምብራኩሬ ሲያሸንፍ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በመካከለኛው ዘመነ መንግስት የሙስሊም አስተዳደር ተመስርቶ ነበር፡፡ የክርስቲያኖችንና እስላሞችን ፉክክርና ትስስር ስናይ ጉዳዩ ረቂቅ ይሆንብናል፡፡ አማራና አርጎባ ክርስትናና እስልምናን የተቀበለ አንድ ህዝብ ሳይሆን አይቀርም ማለትን አሁን ተማርኩ፡፡ በእርግጥ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ብዙ ጉዳዮች በመጽሐፉ ተካተዋል፡፡ ይህም የሰነዶችን አዝማሚያ በማየት ይመስላል፡፡ እንትርታ፣ ትግራይ፣ ባህረ ነጋሽ የአዜባዊነት ርዕዮት የሚለው እይታ የአምሓራን ሲጨምር ሰሜናውያን ያላቸውን ትስስርና የታሪክ ሂደት ያስገነዝባል፡፡ የመካከለኛው ዘመን እምነቶችና ፖለቲካዊ ሚናቸው በሚለው ክፍል በተያያዥ እንደተገለጠው በአክሱም የነበሩ አምልኮ ጣዖታት አገር በቀልም የዉጪም ነበሩ፡፡ በክርስትና አገባብ ጊዜና ሁኔታ ላይ ያሉ ክርክሮች ተዳሰዋል፡፡ የአይሁድ እምነት በ1000 ዓዓ በቀዳማዊ ምኒልክ የገባ ነው፡፡ ከዘጠኙ ቅዱሳን በ5ኛው ክፍለዘመን መምጣትና የምንኩስናና የገዳማት መጀመር እስከ ሐይቅና የደብረሊባኖስ ገዳማት የጎላ ፖለቲካዊ ሚና እንዲሁም ስለደብረ ዳሞ ሰፊ ማብራሪያዎች አሉ፡፡ በ16ኛው ክፍለዘመን ለገዳማቱ ሲሶ ተጀመሮላቸዋል፡፡
በነገሥታት ደግመው የሚታሙና የሚተረጎሙ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ዓላማ የምንረዳው መጻሕፍቱ ለማህበራዊና ፖለቲካ ዓላማ ጥቅም ላይ ሲውሉና መቼና በማን ታተሙ ተብሎ በታሪክ ባለሙያዎች ክርክር ሲቀርብባቸው ነው፡፡ ከፍ ያለ ሚና ያላቸው የነገሥታት አብያተክርስቲያናት የሚባሉም ነበሩ፡፡ በግራኝ የተዘረፈው መካነሥላሴ ገዳምም ሰፋ ያለ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡
እስልምና በምስራቅና በደቡብ ግዛቶች የሚለው ክፍል እስልምና በጎሳ መከፋፈሉና አንድ አለመሆኑ ክርስትናን መገዳደር እንዳልተቻለው ሲያስረዳን፤ ሙስሊሞች ከክርስቲያኑ ጋር እየተባበሩ የሙስሊሙን ኃይል ከፋፈሉ የሚልም ሃሳብ ቀርቦበታል፡፡ እንደ ክርስትናው ሁሉ ከባዕድ አምልኮ ጋር የተሳሰረ እስልምናም ነበር ነበር፡፡ በእርግጥ የሱፊ እምነት ከባህላዊ ጋር ይሄዳል፡፡ በኢትዮጵያ ሰባቱን የእስልምና ተከታይ ግዛቶች አንድ የሚያደርግ መሪ አልተገኘም፡፡ እስልምናና ክርስትና በአደባባይ ይመለካሉ፤ በቤት ውስጥ ነባር እምነቶ አሉ፡፡
የኢኮኖሚ ስርዓትና አስተዳደራዊ ጠቀሜታዎች በሚለው ክፍል የመሬትና የንግድ ግብር ጉልህነት ይታያል፡፡ በኢት መካከለኛው ዘመን መሬት የአራሹ ነበር፡፡ ምጣኔሀብቱ ፊውዳል የተባለ የመንግሥት ስርዓትን አያንጸባርቅም፡፡ የግብር ጫና ገበሬውን አደከመው፤ ከባለ ቴክኖሎጂው የዕደጥበብ ሰራተኛ ጋር የተሳሰረ ዕድገት የለምም ይላል፡፡ በመካከለኛው ዘመን መሳፍንትና መኳንንት መልከኞች የንጉሠነገሥቱን ፈቃድ የሚፈጽሙ ደሞዝተኞች ነበሩ፡፡ ንጉሠነገሥቱም የርስት ሁሉ ባለአደራ ጠባቂ ነው፡፡ ህዝቡን በየብሔሩ ልሳኖች ይጨፍራሉ የሚለውን ሳነብ የነበረውን የቋንቋ ነፃነት ተረዳሁ፡፡ እምነታቸውንም ግብር እስከከፈሉ ድረስ እውቅና የሰጡ ነገሥታት ናቸው፡፡
1267-1967 የቆየው የመካከለኛው ዘመን ግማሹ ክፍል የሆነው ይህ መጽሐፍ በታሪካችን ያሉትን ጉልህ ክስተቶች በቋንቋችን ያቀረበ ሲሆን፤ ዶክተር ደረሰ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከፍተውት የተዘጋው የዘርአያዕቆብ የመካከለኛው ዘመን ጥናት ተቋም ተከታይ ፕሮጀክታቸው ይመስላል፡፡ ሰሎሞናውያን በእንትርታ (ትግራይ)፣ አምሓራና በዛግዌ የነበራቸውን ተጽዕኖ የሚያትተው መጽሐፉ የአማራ ነገሥታትን ብዝሃብሔር ሲላቸው የራሳቸውን ማንነት አክስመው ኢትዮጵያ የሚለውን መጠሪያ ወሰዱ ሲል ይሞግታል፡፡ ‹‹የአረብ ፋቂህ ብዙዎች የሙስሊም ትውልዶች ክርስቲያን ሆነው የኢምም አህመድን ጦር መዋጋታቸውን እየተራገመ ጽፏል›› ሲልም የአረብ ምንጮቹን ይጠቀማል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ