ሰኞ 16 ሴፕቴምበር 2024

ማዕበሉ የማይወስዳቸው ጥቂቶች

 

ማዕበሉ የማይወስዳቸው ጥቂቶች

መዘምር ግርማ

መስከረም 7፣ 2017 ዓ.ም.

ደብረብርሃን

 

ልመና

ዛሬ አንድ አረጋዊ ቤተመጻሕፍት መጥተው በር ላይ ቆሙ፡፡ እኔም እንደተለመደው ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልን›› አልኳቸው፡፡ እርሳቸው ግን ‹‹ሎሚ ትገዛላችሁ?›› የሚል ጥያቄ አስከተሉ፡፡ ከየት የመጣ ሎሚ እንደሆነ ስጠይቃቸው ከእነዋሪ መሆኑን ነገሩኝ፡፡ ትልልቅ ሎሚ ሲሆን፤ ዋጋው ደግሞ ሦስቱ አስር ብር ነው፡፡ ገዛኋቸው፡፡ ዋጋው በከተማችን ከሚሸጥበት በሦስት እጥፍ የተሻለ ነው፡፡ በጣም የሚበረታታ ስራ መሆኑን ገለጽኩላቸው፡፡ ስለ እርሳቸው ስጠይቃቸው ከወሊሶ አካባቢ ተፈናቅለው የመጡና የእነዋሪ አካባቢ ተወላጅ መሆናቸውን ገለጹልኝ፡፡ በአካባቢያቸው የሚገኘውንና የሚያውቁትን ምርት ይዘው መምጣታቸው መልካም ተግባር ነው፡፡ እኔም ይህን ገልጬ አመሰገንኳቸው፡፡ ሌላ ቀንም እንዲመጡ አሳሰብኳቸው፡፡ ወደ ጎረቤት ሄጄ ሎሚ እንደገዙ ስጠይቅ መግዛታቸውንና መጀመሪያ ሲያዩዋቸው እንደኔው  ‹‹እግዚአብሔር ይስጥልን›› ማለታቸውን ገለጹልኝ፡፡ከሎሚውም መግዛታቸውን ነገሩኝ፡፡ እኝህ አዛውንት አንድ ሰው አቅመ-ደካማ እና ተፈናቃይ ከሆነ ምጽዋት መጠየቅ አለበት የሚለውን አስተሳሰብ የሰበሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ እንደ እርሳቸው ያሉ ሰርተው መኖር የሚፈልጉ፣ ያንን የመስራት ዕድል ግን ያጡ በርካቶች ይኖራሉ፡፡ የሚሰሩትን ስራ አለማወቅ፣ ለአካባቢው እንግዳ መሆን፣ መነሻ ገንዘብ አለማግኘት ወዘተ ከስራ አርቋቸው ይሆናል፡፡ እኝህ አዛውንት ግን በእኛም ዘንድ ያለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ አጋልጠዋል፡፡ ይቅርታ ሳልላቸው ስለሄዱብኝም አዝናለሁ፡፡

 

ጨለምተኝነት

ጥናት ባናደርግም ብዙዎች በዚህ ወቅት የሚያስቡት ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች ጎጂ የሆኑ ሃሳቦችን ነው፡፡ በየስፍራው ስንሄድ የምናገኘው እሱ መስራት ስለሚችለው ሳይሆን ሌሎች መስራት ኖሮባቸው ስላልሰሩት ጉዳይ ነው፡፡ ስራ ከያዝኩ ወዲህ ባሉት ዓመታ ይህን በሰፊው አይቻለሁ፡፡ እኔ በመስሪያ ቤት፣ በከተማ፣ በኢንተርኔት ወዘተ የማገኛቸው ሰዎች በአመዛኙ ጨለምተኛ ነገር እንጂ ተስፋ የሚሰጥ ነገር አይናገሩም፡፡ ወይንም የገጠሙኝ ሰዎች እንዲህ ዓይነቶቹ ይበዛሉ፡፡ ይህን መንገድ ትተው መስራት ስለሚችሉት፣ ማሰብ ስለሚችሉት፣ መፍጠር ስለሚችሉት ወዘተ የሚያስቡ፣ የሚመክሩና የሚጠይቁ ውሱን ሰዎችንም ግን አይቻለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ብዙኃኑ እንዳደረገው ሁሉ የሚያደርጉ ሳይሆኑ እኔስ ምን ላድርግ የሚሉ ናቸው፡፡ ለአገርም ሆነ ለራሳቸው የሚጠቅመው ይህ ይመስለኛል፡፡ እርስዎ ብዙኃኑን ከወሰደው ማዕበል ያልተወሰዱ ሰዎችን አይተዋል? በምን ሁኔታ ውስጥ?  

 

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...