ቀጣዩ ትውልድ በምን ሊግባባ ነው?
"Akkam olte haadha Ababaa?
እግዚአብሄር ይመስገን። ደህና አደሩ እትዬ መገርቱ?
Nagaadhaa. Ijjollee akkam?
ሁሉም ደህና ናቸው።"
ይህን መሰል ንግግር እሱ ባደገበት ቦታ በሁለት እናቶች መካከል የሚደረግ መሆኑን አንድ ጓደኛዬ ነግሮኝ ነበር። ሁለቱም የሚናገሩት በየቋንቋቸው ቢሆንም ይግባባሉ። ምላሽም ይሰጣጣሉ። አሁን በአገራችን እየተተገበረ ያለው እያንዳንዱ ክልል የየራሱን ቋንቋ ይማር የሚለው እነዚህን እናቶች ዓይነት ትውልድ ለማፍራት ይሆን? በአሁኑ አካሄድ እንደነዚህ እናቶች እንኳን ሌላውን ቋንቋ ባይናገሩት እንኳን ሰምቶ በራስ ቋንቋ መመለስ አይቻልም። ይህን ችግር በዩኒቨርስቲዎች አይተናል። ከራሳቸውን ቋንቋ ዉጪ የማይናገሩ ተማሪዎች ብዙ ናቸው። እንግሊዝኛም አይታሰብም። በሱ መግባባት አይቻልም። አብዛኞቹ አይችሉም። ከክልላቸው ዉጪ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ቢማሩም የሚግባቡትና አብረው የሚውሉት ከክልላቸው ተማሪዎች ጋር ስለሆነ በቋንቋ ረገድ ለውጥ አያመጡም። ይህ ችግር አገራዊ መፍትሔ ይጠይቃል። የቋንቋ ባለሙያዎችን ብትጠይቁ አንድ አገራዊ የመግባቢያ ቋንቋ እንዲኖር የሚመክሩ ይመስለኛል። ያ ቋንቋ እንዳይኖር ተጽዕኖ ያለ ይመስላል። ይህ ፍላጎት ካለ መውጫ መንገዳችን ምንድነው? በሌላ የአገር ውስጥ ቋንቋ መተካት? የዉጪ ቋንቋ መጠቀም? የምልክት ቋንቋ መጠቀም? ሊታሰብበትና በፖሊሲ ሊደገፍ ይገባዋል። ባለፈው በፓርላማ የነበረውን ክርክር የምታስታውሱት ይመስለኛል።