አንድ ክህሎት ወይም ትምህርት ሲገባችሁ የተለየ ስሜት አለው። አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አብሮኝ የተማረ ጓደኛዬ እንግሊዝኛ አራተኛ ክፍል ሆኖ እንደገባው ነግሮኝ ነበር። ገባኝ የሚለውም ልክ እንደ አማርኛ መነጋገሪያ መሆኑ ስለገባኝ መነጋገር ጀመርኩ አለ። በትምህርት ቤታችንም ብቸኛው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ተማሪ ነበር ለማለት እደፍራለሁ። አስራአንደኛ ክፍል ሆኖ ደግሞ ኢኮኖሚክስ አንድ ምሽት እንደተገለጠለት ነግሮኛል። የተገለጠለትም ሌሊቱን መጽሐፉን በማንበብ ነው። መምህር ጓደኛዬ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ከአካባቢው ካሉ ሁነቶችና የፋብሪካ ምርቶች አንፃር በማገናዘብ እንደተረዳቸው አውግቶልኛል። ሌላው መምህር ደግሞ ሥነጽሑፍ የገባው በመጀመሪያ ልቦለዶችን እንደ እውነተኛ ታሪክ አንብቦ ለጓደኞቹ በመተረክ እንደነበር ነግሮኛል። ስምንተኛ ክፍል ሲደርስ አብዛኞቹን ታዋቂ የአማርኛ ድርሰቶች አንብቧል።
እናንተም አንድ ነገር የገባችሁን ጊዜ አስታውሱ። ይህን ያህል ውስብስብ አንደለም። ቴኒስን ለመቻል ዓይንህን ከኳሷ ላይ ሳትነቅል ተጫወት እንደተባለው ነው። ከአንድ ፊልም እንዳየሁት። ባያያዝኩት የልጆች መጽሐፍ የሽፋን ገጽ የሚታየውም ልጅ ተቀራራቢ ታሪክ አለው። ለመጀመሪያ ጊዜ ማንበብ ችሎ ወደ ቤት ይመለሳል። ማንበብ መቻሉን ለቤተሰቦቹ ለማሳየት ሲሞክር ስራ ይዘዋል። ስለሆነም ለራሱ ማንበብ ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይጮህ ማንበብ የቻለው ሰው ከሺዎች ዓመታት በፊት በአንድ ቦታ መሆኑን ከአንድ መጽሐፍ አንብቤያለሁ። የመጀመሪያው መገለጥ ነው። ድምፁን ለሰው ባያሰማም በጉሮሮው በውስጡ እያነበበ ነበር። በጉሮሮ ወይም በድምፅ ማውጫ ክሮች (vocal cords) ምንም ድምፅ ሳያሰሙ በፍጥነት ማንበብን በርካቶች ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝተነዋል ቢሉም ከመጀመሪያዎቹ አንዷ ኤቨሊን ውድ ነች። እኔም ያገኘሁት ወይም በፍፁም ፀጥታ ማንበብ የቻልኩ ጊዜ እንደ ትልቅ ግኝት ነበር ያየሁት። በእውነትም ነው። ዕድሜ ዘመናችንን ስናነብ የኖርን ሰዎች ምን አዲስ ነገር ልታስተምረን ነው ለሚሉ ምላሼ ትናንት ያጋራሁት ፕሮፌሰሮች ማንበብ እየተማሩ መሆኑን የሚያሳየው ዜና ነው። ልክ እንደ ተች ታይፒንግ ሁሉም ሊለማመደው የሚችለው ክህሎት ነው። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዓመታት ከምንማረው ሌላ ይህ ነው የሚባልና ተጨባጭ ልዩነት የሚያመጣ የንባብ ትምህርት እንዳልተማርን ጥናቶች ያሳያሉ። ታዲያ እንደዚህ ከሆነ ለምን በሰፊው በሥርዓተትምህርቱ ውስጥ አልተካተተም የሚልም አይጠፋም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጆርጅ ስታንክሊፍ ጽፏል። እናንተን የፍጥነት ወይም የፀጥታ ንባብ ካስተማሯችሁ ከምታመጡት አዲስ ፍጥነት እኩል ሄደው ማስተማር አይችሉም የሚለውን ጨምሮ ሃሳቦችን ሰንዝሯል። በጉዳዩ ላይ በርካታ መጻሕፍት አሉ። ድረገፆችም ሆኑ መተግበሪያዎች አሉ። የሥልጠና መርሐግብሮችም እንዲሁ። እኛም አገር መተዋወቅ ይኖርበታል በማለት በአካባቢዬ ባሉ ትምህርት ቤቶችና አብያተመጻሕፍት ሥልጠናውን እየሰጠሁ ነው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህን መንገድ ለሌሎች ለማሳየት በመጣር ላይ ነኝ። ኑ! በፍጥነትና በፍፁም ፀጥታ እናንብብ። በዚህ የቴሌግራም ቡድን እንገናኝ።
https://t.me/+YzM4zraPzGcyYTM0

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ