እሑድ 30 ኦገስት 2026

ደቡብ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ

 


 





 




 




















  



ደቡብ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ

ሰኞ ነሐሴ 25፣ 2018

ደብረብርሃን

 

ደብረብርሃን

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 19

ባለፉት ሁለት ወራት ወደ ጅማና ምስራቅ ኢትዮጵያ ስሄድ የደህንነት ስጋት ይኖራል በሚል እንዳልሄድ ያሳሰቡኝ ወዳጅ ዘመዶቼ አሁንም ወደ ደቡቡ የአገራችን ክፍል ልሂድ ስል ተመሳሳይ ማሳሰቢያ አድርሰውኛል፡፡ እኔም በማህበራዊ ሚዲያና በተገኙት አማራጮች ሁሉ የማየውና የምሰማው ዜና መጥፎ ቢሆንም አንድ ቦታ ያለምንም ጉብኝት ለዓመታት መቀመጥን ስላልመረጥኩ ለመንቀሳቀስ ወስኜ ለደቡብ ጉዞዬ ተዘገጃጀሁ፡፡ እንደተለመደው ከሰዎች፣ ከማህበራዊ ሚዲያ፣ ከጉግልና ከዩቱብ የጉዞ ምክር ሰብስቤያለሁ፡፡ ክረምት በመሆኑም ጥላ ያዝ ያለኝን የጉግልን ምክር ሳይቀር ተቀብያለሁ፤ ምንም እንኳን ዝናብ ሳይኖር ቀርቶ ሳልጠቀምበት ብመለስም፡፡

ማለዳ ተነስቼ ደብረብርሃን ጅሩ መስመር ከ30 ደቂቃዎች በላይ መኪና ብጠብቅም አላገኘሁም፡፡ የሚመጡትም ቦታ የላቸውም፡፡ መውሊድ በመሆኑ ምክንያት አዲስ አበባ ስለሚዘጋጋ ይሆን ብዬም አሰብኩ፡፡ ለማንኛውም በባጃጅ ወደ ከተማ ሄጄ ተሳፈርኩ፡፡ 15 ሰዎች የመጫን ልክ እንዳለው የሚገልጽ ጽሑፍ የሰቀለ ከፍተኛ ጣራ ያለው መኪና 17 ጭኗል፡፡ ደብረብርሃን መውጫ ላይ ያለው ኬላ ላይ ተፈተሽን፡፡ አላስወረዱንም፡፡ ሌሎችን ሳይጠይቅ ከኋላ የተቀመጥነውን ብቻ መታወቂያ ጠየቀን፡፡ ከጎኔ ያለው ወጣት ተሳፋሪ ፋይዳ መታወቂያ ሲያሳይ የሚሰራበትን መስሪያቤትና የመስሪያቤት መታወቂያ ተጠየቀ፡፡ የግል ስራ እንደሚሰራ ገልጾና የስራ መታወቂያውን አሳይቶ አለፍን፡፡ አዲስ አበባ እስከምንደርስ በየመንገዱ ሾፌሩ ትራፊክ ፖሊስ ባየ ቁጥር እየወረደ በሩጫ ይሄድና የሆነች ነገር በወረቀት ጠቅልሎ በመስጠት መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ምን ይጫን ማንን ይጫን ሳይታይበት በገንዘብ ኃይል አለፈ ማለት ነው፡፡ የታየው ጥፋቱ ትርፍ መጫኑ እንጂ ምንና ማንን መጫኑ አልነበረም፡፡ ላምበረት መናኸሪያ በሰላም ደርሰን ወርጄ እዚያው ግቢ ሌላ አውቶቡስ ያዝኩ፡፡  

 

አዲስ አበባ

አብዛኞቹ ከንግግራቸው አማርኛ ሁለተኛ ቋንቋቸው መሆኑ የሚያስታውቅ ተሳፋሪዎች በአዋሽ ባስ ተሳፍረዋል፡፡ የመኪናው ስያሜ አዋሽ የሚለውን የፀጋየ ገብረመድህን ግጥም አስታወሰኝ፡፡ እሱን እያሰብኩ ወደ ምስራቅ አፍሪካው ትልቁ ስምጥ ሸለቆ እወርዳለሁ፡፡

‹‹እስከመቼ ይሆን አዋሽ

አዋሽ የመጫ ስር ፍሳሽ …

ሕመምክስ አንተስ ምንድነህ?...

የምድርን ማኅፀን ቦርቡረህ …››

እስከዚያው የመፍረስና የመገንባት ማዕበል እያለፈች የምትገኘውን አዲስ አበባ ከተማን እያየሁ አለፍኩ፡፡  በከተማዋ ውስጥ የት እንዳለሁ የሚጠቁም ምልክት ብዙም አላየሁም፡፡ ምናልባት ግንባታዎቹ ሲያልቁ ምልክቶቹን ያቆሙ ይሆናል፡፡

በ30 ደቂቃ ውስጥ የደረስነው በሸገር ከተማ የኮዬ ፈጬ ክፍለከተማ ኮንዶሚኒየም ግቢ መሆኑን ከአንድ ጽሑፍ ተረዳሁ፡፡ የተንጣለለውን ኮንዶኒየም ግቢ አልፈን የሪል ኢስቴቶችን ግቢም አገኘን፡፡ ቱሉ ዲምቱ የፍጥነት መንገድ የክፍያ ጣቢያ በደረስን ጊዜ አንድ የትራፊክ ፖሊስ የአውቶቡሱን በር ከፍቶ በአፋን ኦሮሞ ሰላምታ አቀረበልን፡፡ ሁሉም ዝም ሲል እኔ ‹‹ነጉማ›› አልኩ፡፡ ቲኬት መታደሉን በአማርኛ ጠየቀ፡፡ ታድሏል ተባለ፡፡ መልካም መንገድ ተመኝቶልንም ወረደ፡፡

በግራና ቀኝ አገርበቀል ዛፎችን፣ ማሳዎችን፣ እንዲሁም ቆቃንና ዝዋይን የመሳሰሉ ሐይቆችን እያየን መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ ወደ አዳማ መግቢያውም ላይ ምልክት የሚሆኑት የነፋስ ኃይል ማመንጫዎች ከሩቁ ታዩኝ፡፡ በ1999 ዓ.ም. ተመራቂ ሆኜ ከክፍል ጓደኞቼ ጋር ወደ ላንጋኖ ስለሄድኩ እስከ ላንጋኖ ላለው መንገድ አዲስ አይደለሁም፡፡  አዳማም ተመላልሻለሁ፡፡ አዳማና ደብረሲና ለጽሑፍ አርትዖት የምመርጣቸው የነበሩ ቢሆንም በጦርነቶችና ግጭቶች ምክንያት ግን ቀርቻለሁ፡፡

መኪናው ዝዋይ ላይ ለአፍታ ሲያቆም ቆሎ ሻጮች፣ ወይን አዟሪዎችና ሎሎችም ለገበያ ወደ መኪናው ገቡ፡፡ ታዳጊ ወንዶች ልጆችም መንገደኛውን ምግብና ዉኃ  ስጡን በሚል መጠየቃቸውን ተያያዙት፡፡ ከመኪው ውጪ ደግሞ የዕቃ ጋሪዎች ሴቶችንና የዉኃ ጀሪካኖችን ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ስናልፍ መንገድ ላይ አትክልትና ፍራፍሬ የሚሸጥባቸውን በርካታ ዳሶች አየን፡፡ የአበባ እርሻዎችም አሉ፡፡

አርሲ ነጌሌ፣ በዝዋይና በሻሸመኔ መካከል ያለች ታዳጊ ከተማ ስትሆን ከ ከሻሸመኔ 22 ኪሎሜትር ትርቃለች፡፡ እዚያ የሚኖር ወዳጄ አደራ እንድትጠይቀኝ ቢለኝም በስልክ ሰላም ብዬው አለፍኩ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የኤሊኞ አደጋ እያጠቃትና ሰብል እየደረቀ መሆኑን ስረዳ አዝኛለሁ፡፡

 

ሻሸመኔ

ኩየራን ተሻግሬ ሻሸመኔ መግባቴን ስረዳ ለረዳቱ ኖክ ጋ እንዲያወርደኝ ነገርኩትና አወረደኝ፡፡ ከአንድ መንገድ ዳር ካለ ጀበና ቡና ተቀምጬ ቡና አዘዝኩ፡፡ ‹‹ጥቁር ቡና፣ ወይስ በወተት›› ስትለኝ በወተት አዘዝኩ፡፡ እየጠጣሁ ሳለ ወዳጄ መጣልኝና ወደታሰበው ቦታ ሄድን፡፡

የራስ ተፈሪያውያን ቤተመቅደስ እዚያው ኖክ ሰፈር ይገኛል፡፡ በዙሪያው በሚገኙ ሱቆች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሏቸው የራስ ተፈሪያውያን ልብሶች ተሰቅለዋል፡፡ ያንን ልብስ ገዝቼ በመንገድ ላይ በራሴ ላይ አደጋ እንዳልደቅን በማለት አልጠየኩም፡፡

በቤተመቅደሱ ደጅ የተሰባሰቡ ወጣቶች ቦርሳ ማዘላችንንና ለጉብኝት መምጣታችንን አይተው ቀርበው አናገሩን፡፡ የማስጎብኛና የመግቢያ ዋጋ ክርክር ገጥመን የተሻለ የምንለው ዋጋ ላይ ስንደርስ ተስማምተን ወደ በሩ አቀናን፡፡ አረጋዊውን ጥቁር ካናገራቸው በኋላ የመግቢያውን ክፍያ ከፍለን ገባን፡፡ ሲጋራ የሚያጨስ ባለ ሹሩባ ከትሪንዳድና ቶቤጎ የመጣ ራስተፈሪያን ከወጣቱ ጋር ይዞን ገብቶ አስጎበኘን፡፡ በሻሸመኔ የሚኖሩት ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ ጥቁሮች ራስ ተፈሪያውያን በከተማዋ ውስጥ ቤተመቅደሶችና ሌሎችም ግቢዎች አሏቸው፡፡ እኔ አንዱን ከጎበኘሁ ይበቃል በማለት ሌሎቹን ለሌላ ጊዜ አሸጋግሬ እዚህ ተገኝቻለሁ፡፡ ከትሪንዳድና ቶቤጎ የመጣው ጋንጃ ልጋብዛችሁ ሲለን በአክብሮት እንደማንፈልግ ነገርነው፡፡ 12 ወራትን በማስመልከት የተሳለ ባለ12 ቀለማት ሰንጠረዥ መሰል የግድግዳ ስዕል አስጎበኙን፡፡ 12ቱን የያዕቆብ ልጆች መሰረት ያደረገ መሆኑንም አስረዱን፡፡ ወራቱ የየራሳቸው ስያሜ ሲኖራቸው፤ 13ኛ ወርም አለች፡፡ የተወለድንበትን ወር ጠይቆን ስንነግረው ዕጣፈንታችንን ነገረን፡፡ በግቢው የአፄ ኃይለሥላሴና የዘርማንዘሮቻቸው ሥዕሎች በትልቁ በግድግዳዎች ላይ ተስለዋል፡፡ ለራስ ተፈሪያኑ በደብረብርሃን በራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ከልዑል ኤርምያስ ሳህለሥላሴ ጋር የተነሳሁትን ፎቶ ከሞባይሌ አውጥቼ ሳሳያቸው ተደሰቱ፡፡ የዘውድ ምክር ቤቱ የወቅቱ ሊቀመንበር መሆናቸውንም አስታወሱኝ፡፡ የፓን አፍሪካን ንባቤም አቀራረበን፡፡

ራስ ተፈሪ ናዝሬት ቤተመጻሕፍት አሁንም ካለ እየው ያሉኝ ሰው ቢኖሩም አላየሁትም፤ አልጎበኘሁትም፡፡ የተለያዩ የራስታዎች ድርጅቶች እንዳሉ ብረዳም ሻይ ቡና ካልንና ከተማዋን በእግር ከጎበኘን በኋላ ተሳፈርኩ፡፡ ከተማዋ በኮሪደር ልማት ይሁን በሌላ ምክንያት ፈራርሳ እየተሰራች ነው፡፡ አዋሳ መሽቶብኝ ደረስኩ፡፡ ዝነኛዋን ጥቁር ውሃንም በጨለማው ምክንያት ሳላያት ቀረሁ፡፡ ስሄድ በመኪና ውስጥ የሰማሁት ቋንቋ ሲዳምኛ ይሁን ኦሮምኛ ግር አለኝ፡፡ በደንብ ስሰማው ሲዳምኛ የሚመስል ኦሮምኛም ነው ብዬ ደመደምኩ፡፡ በእርግጥ ሲዳምኛን ብዙም ሰምቼው ወይም ሲዳምኛ ተናጋሪ ሰው ብዙም አግኝቼ አላውቅም፡፡   

 

አዋሳ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 20

መኪና ውስጥ አልጋ የት ሰፈር እንደሚገኝ በጠየቅሁት መሰረት ከመናኸሪያ ታክሲ ይዤ ሄጄ ፒያሳ አገኘሁ፡፡ ፋይዳ የተባለውን ዲጂታል መታወቂያ አስይዤ፣ ባለቤቱም መዝግቦና ወደሚመለከተው ክፍል አስተላልፎ አልጋውን ያዝኩ፡፡ እንደ ድሬዳዋ ፖሊስ ሁሉ የአዋሳውም የትኛው እንግዳ የት እንደሚያድር ሳያውቅ አይቀርም፡፡

በማግስቱ ጠዋት ሰውነቴን ታጥቤ በግራር እሾህ አሻሸሁት፡፡ ከግነቱ ስንመለስ እንግዳ ማረፊያው ያዘጋጃት ፎጣ ከማርጀቷ የተነሳ ሰውነትን ሲያሻሹባት በጣም ትሻክራለች ማለቴ ነው፡፡ 

በከተማው የምትገኝን አንዲትን የንባብ አፍቃሪና የኔንም ስራዎች አድናቂ ጠርቼ ከተማውን እንድታስጎበኘኝ ጠየቅኋት፡፡ ከፒያሳ ወደ ፍቅር ሐይቅ በእግር ሄድን፡፡ የከተማዋን ሰፈሮች ስም እየጠራች ነገረችኝ፡፡ ሐይቅ ዳር የሚጠበስ ዓሳም በላን፡፡ ወደ ውስጥ ገብተን ጎበኘን፡፡ በጀልባ የሚዝናኑ ሰዎችን ቁጭ ብለን አየን፡፡ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጉሬዛም ከዛፍ እዛፍ ሲዘዋወሩ አየን፡፡ በትልቁ ግቢ ውስጥም ሆነ በሐይቁ ዳር ፎቶ እናንሳችሁ የሚሉን በዚህ የሚተዳደሩ ሰዎች ቢኖሩም ቦታው ፍቅር ሐይቅ ቢሆንም አልተፋቀርንም ብለን እሷ እኔን በስልኬ እያነሳችኝ ቆይተን ወጣን፡፡ ከዚያም ዛንዚባር በተባለ ሬስቶራንት ቡና ጠጥተን ወደ ስራዋ ሄደች፡፡

ከተማዋ ትልቅ ነች፡፡ የክልል ከተማ መሆኗን ልብ ይሏል፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው ሐውልት የኮባ የውስጡን ክፍል ምልክት አድርጎ እንደተሰራ ሰማሁ፡፡ ከሱ ወደ ፒያሳ ሲል የተሰራው የሲዳማ ባህል አዳራሽ ፊትለፊት ያሉ ሐውልቶችም አሉ፡፡ የሲዳማ ጀግኖች ሐውልቶች መሆናቸው ነው፡፡ ፈረስ ላይ ተቀምጠው፣ ጦር መሳሪያ ይዘው ወዘተ ይታያሉ፡፡ ‹‹የምኒልክን ወረራ፣ የነፍጠኛን መስፋፋት የተቋቋመ ጀግና›› የሚል ከፋፋይ ትርክት የተጻፈባቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ያስረከቡንን ነገሥታት ሰድቦ ለጦርነትና ግጭት በር መክፈት ያልተገባ ነው፡፡ በሰኔ ወር የጎበኘሁትና በጅግጅጋ አዲስ በተሰራው የሰይድ መሐመድ አብዱል ሐሰን ሐውልት ስር የተጻፈው የኢጣልያ፣ የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ኃይሎችን የተዋጋ የሚለውን አስታወሰኝ፡፡ ተመሳሳይ ትርክት በሐውልት መልክ በየቦታው እየተቀረፀ ሲሆን፤ የራስ መኮንንን ዓይነት ሐውልቶች ግን እንዲፈርሱ ተደርጓል፡፡ 

የሲዳማ ሰዎችን መልክ መለየት አልችልም፡፡ ቢሆንም ግን አንድ ለየት ያለ ገጽታ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ጠይምና ረዘም ያሉ ይመስሉኛል፡፡ እንደ ሩዋንዳውያን ያሉም ይመስሉኛል፡፡ እንደ ጋምቢያውያንም ይመስሉኛል፡፡ ከተማዋ የአየር ሁኔዋ ሞቃት ነው፡፡ ሴት ሞተረኞችን ማየቴ ደንገጥ አስብሎኛል፡፡ የፕሮቴስታንት ስብከት በድምጽ ማጉያ በመንገድ ዳር ይሰበካል፡፡ ሁለት ትላልቅ የኦርቶዶክስ ክርስትና አብያተክርስቲያናትንም አይቻለሁ፡፡

መጓዜን በማህበራዊ ሚዲያ ቀድሜ ስላወጅኩና በየሄድኩበትም የማየውን ወዲያው ስለምለጥፍ ሰዎች ወንዶገነትን እየው፤ ዲላን ሳታይ እንዳትመጣ ወዘተ ብለው ቢያተጉኝም ቀድሜ በያዝኩት መርሐግብር መሰረት መጓዜን ይዣለሁ፡፡  አዋሳ ራሱ በሁለት ቀን ለማየት የማይቻል ነው፡፡ ይህም ከከተማው ስፋትና ለተጓዥ ከሚሰማው የድካም ስሜት አንጻር ነው፡፡ ስፍራው ከደብረብርሃን አንጻር ያለው ለውጥ የሰላም ስሜት መሰማቱ ነው፡፡ ያለምንም የሰዓት ገደብ እንቀሳቀሳለሁ፡፡

በቀጣዩ ቀን ስለምሄድበት ከተማ ማለትም ስለ አርባምንጭ ወይም ስለ ወላይታ ሶዶ ለማማረጥ ጉግልን ስጠይቀው አሳሳተኝ፡፡ ጥያቄዬ ‹‹ወላይታ ሶዶ ወደ አርባምንጭ መስመር ነው?›› የሚል ሲሆን የጉግል ኤአይ ግን አይደለም አለኝ፡፡ ‹‹ነው›› ቢለኝ ኖሮ የማገኘው አብሮአደግ ዘመዴ ስላለ አግኝቼ ለማለፍ ነበር፡፡

አዋሳ ላይ ሁለት ፈረንጆች ዘና ብለው ሲጎበኙ ወይም ሲንቀሳቀሱ አይቻለሁ፡፡ በሰላም ከመንቀሳቀስ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ የነሱን ሩቡን ያህል ነጻነት የለኝም፡፡ መንስኤውም ብልሹ አስተዳደርና ስሁቱ የብሔር ፖለቲካ ነው፡፡

 

አርባምንጭ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 21

በጠዋት አዋሳን ለቅቄ ወደ አርባምንጭ ስወጣ ተራሮችን እያየሁ ነበር፡፡ መኪኖቹም ታታ እንጂ አዋሽ ባስን የመሳሰሉት አልነበሩም፡፡  

በመንገዴ ላይ የሚያወጉኝ አንድ የጨንቻ ሰው ስላገኘሁ ስለ አሰፋ ጫቦም ሆነ ስለ ሌሎች ጉዳዮች አነሳስተናል፡፡ ስለ ጨንቻም ነግረውኛል፡፡ በመንገዳችን ላይ ሶዶ ከተማን አገኘናት፡፡ አርፈን አለፍን፡፡ ቁርስ ስላልበላሁ ምሳ በልቼ መንገድ ቀጠልን፡፡ 

መንገድ ላይ በማሳዎች ላይ ሳይደርስ የደረቀ በቆሎ አየን፡፡  ከአጠገቤ ላሉት ሰው ስነግራቸው ‹‹ሰማዩ ህዳርና ታህሳስ እንጂ ነሐሴ አይመስልም፡፡ በፊት ዝናቡ በዚህ ሰዓት ወደ ዉጪ እንኳን አያስወጣም ነበር፡፡ ብቻ ፈጣሪ ይሁነን›› ብለውኛል፡፡ በአርሲ ነጌሌም ተመሳሳይ መሆኑን እዚያ ያለው ወሳጄ ነግሮኛል፡፡ የካሪቢያን አገሮች ድርቁን አስመልክተው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸውን ከአዲስ ስታንዳርድ አንብቤያለሁ፡፡ በአገራችን ሰሜን ማለትም በጎንደር እንስሳትና ሰዎች ከመሞታቸው አንጻር ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ያለዚያ በ1880ዎቹ እንስሳትንና አንድ ሦስተኛውን ሕዝባችንን እንደጨረሰብን እንደ ክፉ ቀን ያለ ችግር እንዳይመጣ ያሰጋል፡፡

ወደ አርባምንጭ ስንቃረብ ሐይቁን ለረጅም ርቀት ስናይ አለፍን፡፡ ሰፊ ሐይቅ መሆኑንና አልፎ አልፎ ሲሞላ ወደ አስፋልቱ ስለሚሄድ አማራጭ የጥርጊያ መንገድ መሰራቱን አየሁ፡፡ መግቢያው ላይ የወታደር ካምፕና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲን አየሁ፡፡

በተራሮች መካከል የምትገኘው አርባምንጭ ከአዋሳ በላይ የምትሞቅ ከተማ ነች፡፡ አብረውኝ የተሳፈሩት መልካም ሰው ጥሩ የእንግዳ ማረፊያ አሳይተውኝ ያዝኩ፡፡ ወዲያውኑም ወደ አርባምንጭ ከተማ የሕዝብ ቤተመጻሕፍት ሄጄ የቤተመጻሕፍት ሰራተኞቹን አገኘሁ፡፡ በሞቃታማ አየር ሲያነቡና ኮምፒውተር ሲጠቀሙ ከተገጠመው ማቀዝቀዣ በተጨማሪ በወረቀት እያራገቡ ነበር፡፡ ንቁ የቤተመጻሕፍት ሰራተኞችም አሏቸው፡፡ እኔም አንደኛው ሰራተኛ እስኪመጣልኝ ‹የሌለውን ፈላስፋ ፍለጋ› ከሚለው መጽሐፍ የመጨረሻውን ምዕራፍ አነበብኩ፡፡ ዘርዓያዕቆብ የሚባል ፈላስፋ አለ የሚለው የማያሳምን መሆኑን ያትታል፡፡ በሻሸመኔም ያገኘሁት ወዳጄ ስለሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ቤተመጻሕፍት ነግሮኝ ነበር፡፡  

በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኙትን አርባ ምንጮችንና የነጭ ሳርን ብሔራዊ ፓርክን ለማየት ጥሩ መኪና እንደሚያስፈልግና የሰላሙም ሁኔታ እንደማያስተማምን ከጀበና ቡና እመቤት እስከ ሌሎችም ሰዎች ነገሩኝ፡፡ የአርባምንጭ ተወላጅ የሆነው ጓደኛዬ ስልክ አላነሳ አለኝ፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ወዳለው የአርባምንጭ አዞ እርባታ በኮንትራት ባጃጅ ሄድኩ፡፡

የጋሞ ልማት ማህበር የሚያስተዳድረው ይህ የአዞ እርባታ ጣቢያ በተፈጥሮ ደን ውስጥ ያለ ነው፡፡ በ200 ብር የመግቢያ ቲኬት ቆርጬ አንድ ቤተሰብን የሚያስጎበኘውን የፓርኩን ሰራተኛ ተከተልኩት፡፡ ይህ ለርቢና ለጉብኝት የሚጠቅም ግቢ መሆን ገልጾ ስለሌሎች ስራዎቸውም ነገረን፡፡ የፓርኩ ሬንጀሮች አዞ እንቁላል የጣለበትን ወንዝ ዳር ሄደው በማየት እንቁላሉን ወስደው ለሦስት ወራት በመንከባከብ እንደሚያስፈለፍሉ አስረዳን፡፡ የ35 እና 37 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወንድና ሴት ትልልቅ አዞዎችን አሳየን፡፡ አንደኛው ውኃ ውስጥ ሌላዋ ውጪ ሆነው ነበር፡፡ ሌሎቹ በዓመታት የተለዩ የስምንት፣ የዘጠኝና የአስር ዓመትና በመቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በአጥር ውስጥ ሲሆኑ ተንከባካቢያቸው ከመካከላቸው ገብቶ ውኃ እየረጫቸውና እያንቀሳቀሳቸው አሳየን፡፡ ከአሁን በፊት አንደኛውን ተንከባካቢ ማጥቃታቸውን ከሚዲያ የሰማሁትን ስጠይቅ አስጎብኛችነ አረጋገጠልኝ፡፡ ከዋናው ክፍል ወጣ ብለን በአንዲት አነስተኛ ከብረት የተሰራች ማስቀመጫ ውስጥ የተቀመጡና አፋቸው የታሰረ ሁለት አዞዎችን አየን፡፡ 50 ብር እየከፈልን ፎቶ እንድንነሳ ሲደረግ ከህጻን እስከ አዋቂ የጎብኚው ቤተሰብ አባላት ተነሱ፡፡ እኔ አልተነሳሁም፡፡ 

በመቀጠልም ዘንዶዎች ወደሚገኙበት በወንፊታማ ብረት የተሰራ ቤት ሄድን፡፡ አንድ ትልቅና አምስት ትንንሽ ዝንዶዎችን አይቻለሁ፡፡ በአማርኛ ‹‹እንኳን ሰው ወፍ አለምዳለሁ›› የሚለውን ‹‹እንኳን ሰው ዘንዶና አዞ እናለምዳለን›› በሚል አሻሽዬ አሰብኩ፡፡

ወደ መሃል ከተማ ተመልሼ ሆቴል ስፈልግ በኮሪደሩ ምክንያት ይመስለኛል ፊት ለፊት መንገድ ዳር የተሰሩት ቤቶች ትንንሽ ሱቆች እንጂ ምግብ ቤቶችና ሆቴሎችን የያዙ አልነበሩም፡፡ በአንዱ መተላለፊያ ገብቼ ስፈልግ ሆቴል አገኘሁ፡፡ ሁለት ቢራ ጠጥቼ ከተማውን እየተዟዟርኩ ለመጎብኘት ሞከርኩ፡፡ ሰላማዊና የተረጋጋ ከተማ ነው፡፡  

ለመተኛት ስሞክር ምሽት ላይ እንደ አዋሳው ሁሉ ቢምቢ እየነከሰ አስቸገረኝ፡፡ የወባ ትንኝ እንዳትሆን በመስጋት አጎበሩን ዘረጋሁት፡፡ ቢሆንም መናከሳቸው አልቀረም፡፡ ቢሆንም ሰላማዊ ምሽት ነበር፡፡

በማግስቱ ጠዋት ተነስቼ ቢምቢ የነከሰኝን እያሻሸሁ ታጥቤ ቁርስ የሚገኝባቸውን ቦታዎች ፈለግሁ፡፡ አንድ ጀበና ቡና ጋ ቁጭ አልኩ፡፡ ሰዎቹ የሚያወሩትን መስማት ጀመርኩ፡፡ ሁለት አርቴፊሻል ፀጉር ያደረጉ፣ ስስ ቲሸርቶች የለበሱና እጆቻቸውን የተነቀሱ ወጣት ሴቶች በአጠገባችን ሲያልፉ አንዱ የኮንሶ ተወላጅ መሆኑን የተረዳሁት ሰው ‹‹ቲፕ ለእንደዚህ ዓይነት ሴት አልሰጥም፡፡ እየተነቀሱ ደም አይለግሱም›› በማለት እንዳልወደዳቸው ተናገረ፡፡ 

አንደኛው ቀጥሎ ‹‹የይሖዋ ምስክር የሆነች ዘመዴ ደም ልገሳ አልቀበልም ብላ በወሊድ ጊዜ ሞተች›› አለ፡፡ ይህን አስመልክቶ የይሖዋ ምስክሮች ደም ልገሳ እንደማይቀበሉ አውቃለሁ፡፡ እንዲያውም አንድ ጊዜ ልጃቸው የታመመችባቸው ወላጆች በዚህ ጉዳይ ተከፋፍለው አባት ‹‹ደም ልገሳ አትቀበልም›› ሲል እናት ‹‹ትቀበላለች፤ ባይሆን ኃይማኖቱ ይቅርብኝ›› ማለቷንና ተቀብላ መዳኗን ከዶክመንታሪ ማየቴን አስታውሳለሁ፡፡  በራሽያ ይህ ኃይማኖት አክራሪ ተብሎ መፈረጁንም ነገርኳቸው፡፡ ዋነኛው ምክንያትም ለአገር አለመዝመታቸው ይመስለኛል፡፡ 

አንድ ኮፍያ የለበሱና በኮፍያቸው ዙሪያ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ያሰሩ አባት መጥተው ቡና አዝዘው መጠጣት ጀመሩ፡፡ የጋሞን ህዝብ ጥሩ ኢትዮጵያዊነት በአካል አየሁ፤ ‹‹ጋሞነቴና ኢትዮጵያዊነቴ ተጣልተውብኝ ለማስታረቅ ተቀምጬ አላውቅም›› ያለውን ፖለቲከኛና ደራሲ አሰፋ ጫቦንም አስታወስኩ፡፡

አጠገቤ የተቀመጠውን ወጣት ‹‹የኮንሶንና የጋሞን ሰው በዕይታ መለየት ይቻላል?›› ስል ጠየኩት፡፡ እንደሚለያዩ አረጋገጠልኝ፡፡ ሲዳማን ግን በቋንቋው እንደሚለየው ነገረኝ፡፡ የኔን ብሔር እንዲገምት ጠየኩት፡፡ እስከዛሬ በሄድኩበት ሰምቼ የማላውቀውን ነገር ነገረኝ፡፡ ‹‹አማራ ትመስላለህ›› አለኝ፡፡ ኤዥያን አሜሪካኗና ሰው ሁሉ ቻይና የሚላት የሰላም ጓድ ኤሪካ አንድ ቀን አንዱ ሞቅ ያለው ሰው ‹‹አሜሪካዊት ነሽ›› ሲላት ያሳየችውን ዓይነት ደስታ ባይሰማኝም የኔ ብሄር ለመገመት መክበዱ አስገርሞኛል፡፡

የኮንሶው ልጅ አጠገቡ ላለውና ሻይና ብስኩት ለጋበዘው ሰው አንድ ጥያቄ አስከተለ

‹‹ሴዶ ተቀጠቀጠ አይደል››

‹‹ማነው ሴዶ››

‹‹ስልክህ ምን ዓይነት ነው››

‹‹ጠቅ ጠቅ ነች››

‹‹ተወው በቃ››

በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም በቲክቶክ መነጋገሪያ የሆነውን የሚክስት ማርሻል አርት ተጋጣሚ ሽንፈት አስመልክቶ ሊያወጋለት ነበር፡፡

ትንሽ ቆየት አለና አንድ ሲኖትራክ ወጣቶችን ጭኖ አጠገባችን ቆመ፡፡

‹‹እልም አለ ባቡሩ

እልም አለ ባቡሩ

ወጣት ይዞ በሙሉ፡፡››

የሚለውስ አያሰብኩ አጠገቤ ያለውን ወጣት ስለማንነታው ጠየኩት፡፡ በአንጻሩ ወደ ገበታ ለሃገር የሚሄዱ የቀን ሰራተኞች መሆናቸውን ነገረኝ፡፡  

ሌላ ቦታ ሄጄ ቁርስ በልቼና ቡና ጠጥቼ ወደ ጋሞ ባይራ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የኮንትራት ባጃጅ ያዝኩ፡፡ ሾፌሩን ቦታውን ያውቀው መሆኑን ስጠይቀው ‹‹ባይራ፣ ጎበዝ ተማሪ የሚገቡበት፤ ግባ፤ አውቀዋለሁ›› አለኝ፡፡ ‹‹ከዉጪ ይደገፋል?›› የሚል ጥያቄም አስከተለልኝ፡፡ እንደማላውቅ ነገርኩት፡፡ በ400 ብር የወሰደኝ መንገድ ደብረብርሃን መቶ ብርም አይፈጅ፡፡ በመንገዳችን ላይ በሐረር እንዳየሁት ሁሉ እዚህም በጅምር ያለ ዓለምአቀፍ ስቴዲየም አየሁ፡፡ ያልቅና ስፖርትን ያነቃቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መንገድ ላይ ስለ ዝናብ አለመኖርና ስለ ሰማዩ ባዶ መሆን አወጋን፡፡ ጎርፍም እንደሚያሰጋ፣ እየሄድንበት ያለው ሰፈር ተጋላጭ ስለሆነ በመጪ የዝናብ ወቅት አደጋ ሊኖር እንደሚችል ነገረኝ፡፡ ኤሊኞ ድርቅና ጎርፍ ስለሚያፈራርቅ አስጊ ነው፡፡

በአዳሪ ትምህርት ቤቱ አጠገብ ያገኘኋት ባለ ጀበና ቡና ‹‹ሐይቅ ሄድክ?›› ስትል ጠየቀችኝ፡፡ አለመሄዴን ነገርኳት፡፡ ብቻዬን እንዳልሄድ መከረችኝ፡፡ ‹‹አሳ በላህ?›› የሚልም ጥያቄ አስከተለች፡፡ አለመብላቴን ስነግራት የሚገኘው ሐይቆቹ ጋ መሆኑን ነገረችኝ፡፡ አዋሳ ስለበላሁ ግድም የለኝ፡፡ ‹ባይራ› ማለት ምን ማለት እንደሆነ ስጠይቃት በጋሞኛ ‹ትልቅ› ማለት መሆኑን ነገረችኝ፡፡   

ጋሞ ባይራ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት በጋሞ ህዝብ የሚደገፍ ትምህርት ቤት ሲሆን ከዞኑ ወረዳዎች የተመረጡ ጎበዝ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተናግዳል፡፡ ከ9-12 የሚያስተምር ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ማትሪክ ባለፈው ዓመት አስፈትኖ 100 ፐርሰንት አሳልፏል፡፡ በዚህ ሰሞን የደስታ ስሜት ውስጥ ናቸው፡፡ ውስጡ የተደራጀ ነው፡፡ አዟዙረው አስጎበኙኝ፡፡ የራሱ እርሻ አለው፡፡ የአስተዳደር ሰራተኞች መኖሪያ አለው፡፡ ጂምናዝየም፣ የስፖርት ቦታ፣ ቤተመጻሕፍት፣ ቤተሙከራዎች፣ አሉት፡፡ የበጀትና የልዩ ልዩ ግብዓት ድጋፍም ያስፈልገዋል፡፡ እስካሁን የደገፈው አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የራሱን አዳሪ ትምህርት ቤት ሊከፍት ስለሆነ ድጋፉ ይቀራል፡፡

አርባምንጭ በሰላም ያለ ስጋት መንቀሳቀስ የቻልኩበት ከተማ ነው፡፡ የሰላም መናጋትን የተመለከተ ነገር አልሰማሁበትም፡፡ ሐውልቶቹም ሰላማዊ ናቸው፡፡ ጨንቻ ብርድ እንዳለውና ከአሁኑ ወቅት ይልቅ ለመስቀል ቢጎበኝ ይሻላል የሚል ሰማሁ፡፡ የጨንቻ ጉዞዬን ለሌላ ጊዜ አራዘምኩት፡፡ ወደ ጂንካም መኪኖች ይጠሩ ነበር፡፡ እሱንም ለሌላ ጊዜ ብዬ ዝም አልኩ፡፡

በዋዜማው በአፕሊኬሽንና በቴሌብር ቲኬት ቆርጬና ኦንላይ ቼክ ኢን አድርጌ ስለነበር የመልስ ጉዞዬን ለማድረግ መዘገጃጀት ጀመርኩ፡፡ ወደ አየር ማረፊያም ኮንትራት ባጃጅ ያዝኩ፡፡ የአርባምንጭ አየር ማረፊያ ሰፊ ነው፡፡ በቀን ሦስትና ከዚያ በላይ በረራዎች አሉት፡፡ በፊት እንደዚህ እንዳልነበር ቀድመው የሚያውቁት ሰው ነግረውኛል፡፡ በአርባምንጭ በአንጻራዊነት መሰረተ ልማት ተሟልቶ የግል ኢንቬስትመንት ግን እምብዛም መሆኑን አስተያየት የሰጡኝ ሌላ ሰው አሉ፡፡ ስንመለስ አውሮፕላን ውስጥ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ከተቃዋሚ ፓርቲ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ሰው ጋር ተሳፈርን፡፡ መንገዱ ከፊል ውሃማ መንገድ ስለሆነ የመንሳፈፊያ ቁሳቁስ አጠቃቀም ጥንቃቄውን በደንብ እንድንሰማ ፓይለቱ አሳሰበን፡፡ በእርግጥም በመንገዳችን ሐይቆች ይበዛሉ፡፡  

ለተጓዥ ዕቃ ተሸክሞ መዞር ያደክማል፡፡ አዲስ አበባ ሰንብቶ ሰው ለመጠየቅ ስላልፈለግሁ አንድ ቀን አዲስ አበባ አድሬ ወደ ደብረብሃን አቀናሁ፡፡ በራስ መኪና ለመሄድ ለሚያስብም በየመንገዱ ስጋት አለ፡፡ ደቡብ ሳለሁ መተሃራ አካባቢ ተኩስ መኖሩን ሰምቼ ነበር፡፡ በመኪና ብመለስ አንድ ቦታ የሚነሳ ችግር ሊኖር ስለሚችል የአየሩ አማራጭ ጥሩ ነው፡፡ ዋጋው በየጊዜው እየጨመረ የሚቀመስ ባይሆንም፡፡ 

ከአገራችን ክልሎች አፋር፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉልና ጋምቤላ ይቀሩኛል፡፡ ኤርትራን የመጎብኘት ዕድልም በለውጡ ጊዜ አምልጦኛል፡፡ ጓደኞቼ ግን ጎብኝተዋል፡፡ አገራችን ፍቅርና ሰላም አጣች እንጂ ልንጎበኛትና ልናውቃት ይገባል፡፡ በዚህ በሰለጠነ ዘመን ኢትዮጵያም ትጠበናለች፡፡ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የድንበር ውዝግብ በየቦታው አለ፡፡ ይህ ተረጋግቶ በሰላም የምንንቀሳቀስበትን ጊዜ እናፍቃለሁ፡፡    

ቅዳሜ ጠዋት ወደ ደብረብርሃን ለመመለስ መንገድ ጀመርኩ፡፡ ሰንዳፋ ላይ ሯጮች በረፋዱ ፀሐይ ከመኪና ጋር እየተጋፉ ሲሮጡ አየሁ፤ አንድ ፈረንጅ ሯጭም አብሯቸው ነበር፡፡ የፍጥነት መቀነሻ በየቦታው ስለተሰራ ስንንገጫገጭ ቆይተን ደብረብርሃን ደረስን፡፡ ተማሪ አዲሱ ጌታቸው ከቤተመጻሕፍት ጉዞዎቻችን በኋላ እንደሚለው ‹‹ጉዞ መሄድ ደስ ይላል፤ መመለሱ ነው የሚያስጠላው›› ያላልኩበት ጉዞ ነው፡፡ እንኳንም በሰላም ለቤቴ በቃሁ፡፡ 25 000 ብር ወጪ የተደረገበት ጉዞዬ እንደ ምስራቅ ኢትዮጵያው ጉዞዬ ሁሉ ወጪ ቆጣቢ ነበር፡፡ 


ደቡብ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ

            ደቡብ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰኞ ነሐሴ 25፣ 2018 ደብረብርሃን   ደብረብርሃን ማክሰኞ፣ ነሐሴ 19 ባለፉት ሁለት ወራት ወደ ጅማና ምስራቅ ኢትዮጵያ ስሄድ የደህንነት ...