ከሰሞኑ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን የሚያስታውሱኝ
አንዳንድ ነገሮችን አየሁ፡፡ በትምህርት ቤት ግንባታ እያደረገ ያለውን ጉልህ ሚና ሁላችንም እያደነቅነው ነው፡፡ አንድ ቆየት ያለ
የአማርኛ ጋዜጣ ከአንዲት ኢትዮጵያ ውስጥ ከቆየች የቢቢሲ ዘጋቢ ጋር ባደረገው ቆይታ ዘጋቢዋ ከኢትዮጵያውያን ኃይሌን በአርዓያት
እንድንጠቀምበት ጠይቃለች፡፡ ባለፉት ጥቂት ቀናት በተለያዩ ቦታዎች በተዘዋወርኩበት ጊዜ ሁለት የኃይሌ ሳይሆኑ የማይቀሩ የእጅ ጽሑፎችን
ለማየት ችያለሁ፡፡ እነዚህም አንደኛው ኃይሌ ሪዞርት የሚለው ጽሁፍ ላይ ያለው የእንግሊዝኛ ጽሑፍ፣ ይኸውም ኃይሌ (Haile) የሚለው
ነው፡፡ ሌላውና ቆየት ያለው ይቻላል የሚለው ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤትም ሳይጠቀምበት አይቀርም፡፡
የሆነው ሆኖ፣ ይቻላል ምን ማለት ነው ብዬ ራሴን
ጠየቅሁ፡፡ በትምህርት ቤትም ይቻላል ይባላል፡፡ ታላቅም ታናሹን ሲያበረታታ ይቻላል ይላል፡፡ መምህርም ተማሪውን እንዲሁ፡፡ ሻለቃ
ኃይሌ እየተጠቀሰ እሱ እንዳለው እየተባለ ይቻላል ይባላል፡፡ ይህ
ብቻ አይደለም - አሉ ብቻ አንዳንድ አገላለጾች - ዘወትር የምንሰማቸው፣ ግን ምን ማለት ናቸው የሚለውን የማናውቀቸው ወይንም ያላሰላሰልናቸው፡፡
‹‹አርስቶትል ‹እኔ የማውቀው አለማወቄን ነው› አለ›› ይባላል፡፡ ምን ማለቱ ነው የሚለው ብዙም አይብራራም፡፡ ወይም አውዱ ለማብራራት
የመያመች የጨዋታ ማድመቂያ ይሆናል፡፡
ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ብዙ
ተብሎለታል፡፡ የኃይሌ ማሸነፍ ዜና አይደለም እንዲል ደምሴ ዳምጤ፡፡ ሃያ ሰባት የዓለም ሪኮርዶችን በጣጥሷል፡፡ በዓይናችን እያየነው
ከስኬት ማማ የወጣ፣ ቀን በቀን እየጠነከረ የመጣ፣ ትልቅ አርአያ ነው፡፡ ስለ ኃይሌ ለእርስዎ መንገር ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆን
ወደ ዋናው ጉዳዬ ልግባ፡፡
ይቻላል ምንድነው?
ለእኔ ይቻላል ዝም ብሎ ቃል አይደለም፡፡ በተለይ
ኃይሌ ይህን ቃል ሲጠቀምበት ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ለስኬታችን ቀን ከቀን ያለማሰለስ ከሰራን ያን ድል መቀዳጀት ይቻለናል ማለቱ
ነው፡፡ ስኬት ለኃይሌ የዓለም ሪኮርዶችን መሰባበርና በተሰማራበት ሙያ ትልቁ ሰው መሆን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አድርጎታል፤ ሆኗል፡፡
አንድ ወቅት ላይ የደረሰኝ የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው ሪከርድ የሚሰብሩ ወይም በዓለም ላይ ካሉ አትሌቶች ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙ
ከአይኪዋቸው ብዙ ተጠቅመዋል፡፡ አዎን! በዓለም ላይ ሚሊየን ዶላሮችን የማይፈልግ የለም፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ፡፡ ከዚህ
የዓለም ህዝብ ነጥሮ መውጣት አእምሮን በትክክል መጠቀምን ይጠይቃል፡፡ አካልንና አእምሮን አጣምሮ ከስኬት ማማ የደረሰውና ዓለም
ያጨበጨበለት ኃይሌ ‹‹ፕሬዚዳንት ልሁን›› አለ ተብሎ የተቀለደው እዚህ ጋ ፉርሽ ይሆናል፡፡ ኃይሌ በአካልም በአእምሮም የበለጸገ
ስለሆነ!
ኃይሌ ስለ ዕለት ውሎው ብዙ ተናግሯል፡፡ ልምምዶችን ያለማሰለስ ያደርጋል፡፡
ሃሳቡ ከውድድሮቹና ከዓላማው ላይ ነው፡፡ የአንዲት ቀን ልምምድ መታጎል ቀጣዩን ድል ያሳጣዋል፡፡ ስለሆነም ይተጋል፡፡ በዚህም ምክንያት
ይተጋል፡፡ ስለሚተጋም ይቻላል፡፡ በተሰማራበት ዘርፍ የተቻለውን ጥረት አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ስፖርት ብዙ ይቻላል የሚያስብሉ ገጠመኞችን
አሳይቶናል፡፡ ይድነቃቸው ተሰማ፣ አበበ ቢቂላ፣ ፍቅሩ ኪዳኔ እንደሚቻል ያሳዩ ናቸው፡፡ ፍቅሩ ኪዳኔ ብዙ ስላልተነገረለት እንጥቀሰው፡፡
ከሃረር መምህራን ማሰልጠኛ በስፖርት መምህረነት በሰርተፊኬት የተመረቀ ነው፡፡ የእርሱ ፍላጎት ወደ ጋዜጠኝነት የመዝ ነበረና የቅዱስ
ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ዘጋቢ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የስፖርተ ጋዜጠኛ ሆነ፡፡ እነ ክቡር አቶ ይድነቃቸውን እየተከተለ
ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም መድረክ መወከል ጀመረ፡፡ አሁን ፊፋን፣
አይኤኤኤፍንና ሌሎችንም የስፖርት ተቋማት ያማክራል፡፡ በዘርፉ ብቸኛው ጥቁር እስከመሆን መድረሱን ከሳቢው የህይወት ታሪኩ ከፒያሳ
ልጅ መማር እንችላለን፡፡ አንዲትን ዘርፍ መርጠን ከተሰማራንና ከበረታን እንደሚቻል ከኢትዮጵያ ስፖርት ብዙ መማር እንችላለን፡፡
ይቻላል! አዎ ይቻላል! የሚቻለው ግን በትጋት፣ በጽናት፣ ጊዜን በመጠቀም ነው፡፡