እሑድ 8 ፌብሩዋሪ 2026

የትምህርት አቅጣጫ ወዴት ነው?

 የትምህርት አቅጣጫ ወዴት ነው?


ትምህርት አጉል አቅጣጫ እየሄደች ይመስላል። ለዚህ ማሳያ የተወሰኑ ክስተቶችን ላንሳ። ከሰሞኑ አንዲት መምህር እያስተማረች የነበረበት ክፍል ለፈተና ተፈልጎ እንድትወጣ ስትጠየቅ በጥያቄው ተስማምታ ስትወጣ አየኋት። አንዱ ተማሪ ዲቫይደሯን፣ ሌላኛው ፕሮጀክተሯን ይዘውላት  ይሄዳሉ። አንዳቸውም ደብተር አልያዙም። የያዙትን ለመገመት አትቸገሩም - ስማርት ስልኮችን ነው። ከሁለት ዓመታት በፊት የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነጽሑፍ ተማሪዎች ነበሩን። ሳስተምር ሰሌዳውን ፎቶ ያነሱታል። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሆነ ሰነድ ምናልባት የክፍለጊዜ ድልድል ሊያሳዩኝ ስልኮቻቸውን ሲከፍቱ የምናስተምራቸው መምህራን ሰሌዳው አጠገብ ቆመን ያነሱን ፎቶዎች አሉ። እኔ ማክሰኞና ሐሙስ ክፍለጊዜ ቢኖረኝ የአንዱን ሳምንት ጽሑፌን ከሌላው እንዴት እንደሚለዩት ግራ ይገባኛል። ከኔ በፊት ወይም በኋላ ያስተማሯቸውንስ? ነገሩ ግራ ይገባል። በፕሮጀክተር የሚያስተምሩ መምህራንን ፓወርፖይንት በስልካችን ይዘናል ብለው ደብተር የማይዙት የሌሎች ትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችም ሆኑ እኛ የሥነጽሑፍ ተማሪዎች ደብተር አለመያዛቸው ምንም ምክንያታዊ ሆኖ አይታየኝም። መጻፍ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው። መምህራን ከፓወርፖይንት ዉጪ የሚያስተምሩት ነገር አለ። መጻፍ የመማር አካል ነው። አንዱን ትምህርት ከሌላው ለይተን ማስታወሻ መያዝ ይገባናል። ትምህርት ምን ዓይነት አጉል አቅጣጫ እየሄደ ነው? የትምህርት ዓላማ አእምሮን ማልማትና ችግርፈቺ ዜጎችን ማፍራት ነው። ሰናይ ተግባር የሚሰሩ ወጣቶችንም መፍጠር አለበት። ለዚህ ደግሞ ትኩረት ሰጥቶ ምንም ሳይሰስቱ መማር ተገቢ ነው። ዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ በአሳይመንት፣ በንባብ፣ በፈተና፣ በምርምርና በሌሎችም የትምህርት ጉዳዮች እያመጣ ያለውን ችግር ትገምታላችሁ ብዬ አልነካካሁትም። ፈተናው እውነት ሀሰትና ምርጫ ሆኖስ ተማሪዎች ምን ያህል ለማሰብና ቤተመጻሕፍት ገብተው ከፓወርፖይንት በላይ ለማንበብ ይነሳሳሉ?

በማካካሻ (remedial) ፕሮግራም የሚባክነው የአገር ሀብት ሌላው ነው። ተሻለሎ ለማይሻሻል ክህሎት የተማሪዎች ዕድሜና የአገር ሀብት ይባክናል። በትምህርት ዘርፍ ማየት ያለብን በርካታ ጉዳዮች አሉ። 

የከተማ ልጆች በኮምፒውተር እየነተፈኑ የገጠሩ በወረቀት መፈተኑ ያመጣው ኢፍትሃዊነት ዘንድሮ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት ባስጠላቸው የከተማ ወጣቶች ለመሞላታቸው ምክንያት አልሆነ ይሆን?  ኮምፒውተሩ ፈተና የሚሰሩ ሶፍትዌሮች እንዳሉት የተፈተነ ተማሪ ነግሮኛል። እንወያይበት።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የትምህርት አቅጣጫ ወዴት ነው?

 የትምህርት አቅጣጫ ወዴት ነው? ትምህርት አጉል አቅጣጫ እየሄደች ይመስላል። ለዚህ ማሳያ የተወሰኑ ክስተቶችን ላንሳ። ከሰሞኑ አንዲት መምህር እያስተማረች የነበረበት ክፍል ለፈተና ተፈልጎ እንድትወጣ ስትጠየቅ በጥያቄው ተስ...