ረቡዕ 3 ማርች 2021

የራስ አበበ አረጋይ ማስታወሻ ስያሜ ሽሚያዎችን አስመልክቶ የቤተመጻሕፍታችን አቋም

 

የራስ አበበ አረጋይ ማስታወሻ ስያሜ ሽሚያዎችን አስመልክቶ የቤተመጻሕፍታችን አቋም

 

በሁለተኛው የኢጣሊያና ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ከነበሩ ፈርጦች ግንባር ቀደሙ ራስ አበበ አረጋይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጦር በስኬት በመምራት በዱር በገደል ለአምስት ዓመታት ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ፍልሚያ አድርገው የሃገራቸውን ነጻነት አረጋግጠዋል፡፡  በዚያ አስቸጋሪ ወቅት የኢትዮጵያን ባንዲራ ካውለበለቡ ጥቂቶች የጦር መሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ የኢጣሊያ ፋሽስት መሪዎች የኢትዮጵያን ህዝብ በብሔርና በቋንቋ ከፋፍለው ለመግዛት ይጥሩ በነበረበት በዚያ ወቅት ራስ አበበ አረጋይ በአንጻሩ በሸዋ የአማራና የኦሮሞ ህዝብን አስተባብረው የተራዘመውን ጦርነት በመምራት ለድል የበቁ ናቸው፡፡

ራስ አበበ አረጋይ በ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት በአረንጓዴው ሳሎን ግድያ ሕይወታቸውን ያጡት ኢትዮጵያን ከሚወዱትና ለምዕራባውያን ከማይመቹት መሪዎች አንዱ በመሆናቸው ነበር፡፡ በ1950ዎቹ ታቅዶ የነበረው ጭሰኝነትን ከኢትዮጵያ የሚነቅል የተባለለት ሰፊ ፕሮጀክትም ሰይፈጸም ቀርቷል፡፡ ከዚያ ወዲህም ሃገሪቱ ወደባሱ ዘርፈብዙ አዘቅቶች በመግባት እድገቷ ቁልቁል እየወረደ መሆኑ ይታወቃል፡፡       

ታሪክን ለማስታወስ እነሆ ዘመኑ ደርሶ ራስ አበበ አረጋይም ሆነ ሌሎች የሃገር ባለውለታዎች በትውልድ እየታወሱ ይገኛሉ፡፡ እኔ በግሌ በታሪክ ትምህርት ስለጀግናው ራስ አበበ አረጋይ ተምሬ አልፌያለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም በመጀመሪያ ዲግሪ ስመረቅ የመመረቂያ ጽሑፌንም በአርበኞች ተጋድሎ ላይ በተጻፈ ታሪካዊ ልቦለድ ላይ ስሰራ ከዚሁ ፍላጎቴ ይመነጫል፡፡ ከምረቃ በኋላም ታሪካዊ ጉዞዎችን በማድረግ በማስተባበርና የጉዞ ማስታወሻዎችን ጽፌ በማስነበብ አርበኞቻችንና ታሪካችን እንዲታወሱ ጥሬያለሁ፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከተርጓሚ፣ ደራሲና የትያትር ሰው አሊሹ ሙሜ ጋር ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን ስንመጣ አካባባውንና ታሪኩን እያነሳን መንገድ መንገዱን ስናወራ አንድ ሃሳብ ተነሳ፡፡ ይኸውም አሊሹ ከዚህ ሁሉ ነገር የሚቆጨው ራስ አበበ አረጋይ ለዚህች ሃገር ይህን ሁሉ ውለታ ውለው አለመታወሳቸው መሆኑን ነገረኝ፡፡ በነገራችን ላይ አሊሹ የሃገራችንና የጥቁር ሕዝብ ትግል የሚስበው በማልከም ኤክስንና የማርከስ ጋርቪን ስራዎች የተረጎመ የጥበብ ሰው ነው፡፡ እኔም በጉዳዩ በመስማማት ደብረ ብርሃንም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱን በእርሳቸው ለመሰየም ተፈልጎ መንግሥት ስለተቀቃወመ መቅረቱን ነገርኩት፡፡ የሆነው ሆኖ ቀድሞ በነበረኝ ፍላጎትና ቁጭት በ2008 ዓ.ም በደብረ ብርሃን ከተማ የግል ቤተመጻሕፍት ስከፍት ስያሜውን በራስ አበበ አረጋይ ለማድረግ ወሰንኩ፡፡ ይህም ቤተመጻሕፍት ህብረተሰቡን በነጻ እያስነበበ አምስተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት (ወመዘክር) በደብረ ብርሃን ከተማ ባደረገው የንባብ ሳምንት ወቅት እውቅና ሰጥቶናል፡፡ የግል ቤተመጻሕፍት በፖሊሲ በማይደገፍበተ ሃገር በንባብ ላይ የሚሰራው ቤተመጻሕፍታችን በአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ማህበር ንቁ ተሳታፊና በዋና ዋና መርሐግብሮች ኢትዮጵያን የወከለ ነው፡፡ የአሜሪካ ቤተመጻሕፍት ማህበርም በመጽሔቱ ስለቤተመጻሕፍታችን ጸፏል፡፡ ይህ እውቅናና አብሮ የመስራት ፍላጎት ከደቡብ አፍሪካው የርቀት ትምህርት ተቋምና ከሕንዱ ስቶሪ ዊቨርም መጥቶ አብረን እንሰራለን፡፡ በንባብ ላይ ባሳረፍነው አሻራም ምክንያት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን (ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ዩቱብ ቻነሎችና ጋዜጦች) በቤተመጻሕፍታችን ላይ ዝግጅቶችን በማቅረብ የንባብ ባህልና የቤተመጻሕፍት አገልግሎት እንዲስፋፋ ሰርተዋል፡፡ የቤተመጻሕፍቱ አገልግሎትና ስራ ሰፊ ቢሆንም በዚህ ልቋጨው፡፡

ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አዲስ በተሰራው የሕክምና ካምፓስ ውስጥ የሚገኘውን ቤተመጻሕፍት በራስ አበበ አረጋይ ስም ለመሰየም መወሰኑን ይህ ውሳኔ በተላለፈበት ወቅት የነበሩ ግለሰቦች ነገሩኝ፡፡ ይህም ውሳኔ ራስ አበበ አረጋይን ለማስታወስ በማሰብ የተደረገ በመሆኑ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ በፊት አስታዋሽ አጥተው የነበሩትን የሃገር ባለውለታ ዩኒቨርሲቲው ማስታወሱ የሚደነቅ ቢሆንም የራሱ አሉታዊ ጎኖች አሉት፡፡ይኸውም በከተማው ውስጥ በጀግናው የተሰየመ ቤተመጻሕፍት እያለ ሌላ ተጨማሪ መሰየሙ ግርታን የሚፈጥርና አንባቢያንንና ህብረተሰቡን የሚያሳስት ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ቤተመጻሕፍታችንም ምንም እንኳን በአነስተኛ ቦታ የተወሰነ ቢሆንም የራሱን አሻራ እያስቀመጠና በግል ቤተመጻሕፍት ዘርፍ ያለውን ክፍተት በማሳየት በትንሽ ገንዘብ፣ የሰው ሃይልና በውሱን አቅም ትልቅ ስራ መሰራት እንደሚችል እየሳየ ያለ ነው፡፡ መጻሕፍትን በማሳተምና በማከፋፈልም በመላ ሃገሪቱ የንባብና የዕውቀት ትሩፋት እንዲደርስ እየጣረ ያለ ነው፡፡ በመሆኑም ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ይህንን ውሳኔውን እንዲያጤነው ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ከተቻለም ቤተመጻሕፍቱ በሌሎች ታዋቂ ደራሲያን፣ ምሁራንና የአገር ባለውለታዎች (ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ወዘተረፈ) እንዲሰየም ሊደረግ ይችላል፡፡ ራስ አበበ አረጋይ በብዙ መልኩ እንዲታወሱ ማደረግ ይቻላል፡፡ ግርታን በማይፈጥር መልኩም እስካሁን የታወሱበትንና የተወሰኑ ፍላጎቶችን እናሳይ፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በደብረ ብርሃን በግል ቤተመጻሕፍት አስታውሰናቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ በስማቸው መንገድና ትምህርት ቤት አለ፡፡ እነዋሪ ላይ ሆቴል ተሰይሟል፡፡ የባንክ ቅርንጫፍም አለ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሰየም ፍላጎት እንዳለም ሰምቻለሁ፡፡ ወደፊት ዩኒቨርሲቲያችን ባለው ተጽዕኖና የሥራ ግንኙነት መሠረት  በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በሌሎች ክልሎችም ሆነ በፌደራል ደረጃ ለራስ አበበ አረጋይ ውለታ የሚመጥን ወታደራዊ አካዳሚ ቢሰየም ከእርሳቸው ትክክለኛ ወታደራዊ ጀብዱ ጋር የሚስተካከል ማስታወሻ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌሎችም ጀግናውን የሚያስታውሱ ስራዎች ቢሰሩ ለውለታቸው ሲያንስ አንጂ አይበዘባቸውም፡፡

 

መዘምር ግርማ

የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ሥራ አስኪያጅ

ሰኞ የካቲት 22፣ 2013 ዓ.ም.

ደብረብርሃን 



 

 

እሑድ 28 ፌብሩዋሪ 2021

የመጽሐፍ ዳሰሳ

 የመጽሐፍ ዳሰሳ

(በዚህ ገጽ የተከፈለበት)



የመጽሐፉ ርዕስ - Marcus GARVEY፣ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ

 ደራሲ - ማርከስ ጋርቪ

 የመጽሐፉ ተርጓሚ - አሊሹ ሙሜ

 ዘውግ - ግጥሞች 

 የገጽ ብዛት - 142

ዋጋ - 69

የታተመበት ጊዜ - 2007 ዓ.ም.

ዳሰሳ ጸሃፊ - ሃይማኖት ክንፈ

የተከበራችሁ ውድ የመጽሐፍ አፍቃሪያን እንደምን ሰንብታችኋል?ሰላም እና ጤና እንዲሁም  ፍቅር ከሁላችሁ ጋር እንዲሆን እየተመኘሁ! ወደ መጸሐፍ ዳሰሳዉ ስገባ:-

ማርከስ ጋርቪ ይባላል የመጽሐፉ ደራሲ ሲሆን በትውልድ የጃማይካዊ ነው። ጋርቪ የጥቁር ዘር መሪ፣ጋዜጠኛ፣ተነግሮ አሳማኝ እንዲሁም ርእዮተ አለማዊ ሰው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ማርከስ ጋርቪ ገጣሚ ሲሆን የደቡብ እና የመካከለኛውን አሜሪካ ግዛቶች ተንቀሳቅሶ ከጎበኘ በኹዋላ በ1912 ወደ እንግሊዝ ሀገር ተጓዘ።በእንግሊዝ ሎንደን ከተማ ሳለ ለአፍሪካ ታሪክ እና ባህል ልዩ ትኩረትን ሰጥቶ የግል ጥናቱን አከናወነ።

 አንደበተ ርቱእ የሆነው ማርከስ ጋርቪ በአሜሪካ የሚኖሩ ጥቁሮችን "በዝርያችሁ ኩሩ፤"ብሎም "ወደ አያት ቅድመ አያቶቻችሁ ምድር ወደ ቅድስት አፍሪካ ተመልከቱ!"እያለ መስበኩን ቀጠለ።

በፓን አፍሪካኒዝም እንዲሁም በፈረንሳይ ሀገር የአፍሪካውያን "ኔግሪቱድ"ንቅናቄና የለንደኑ የምእራብ አፍሪካ ተማሪዎች ህብረት እና ሌሎችም የጥቁር ነፃነት ትግሎች በተነሱ ቁጥር ከነ ኤድዋርድ ዊልመንት፣ክዋሜ ንክሩማ፣ጁሙ ኬንያታ፣ማልኮም ኤክስ እና ሌሎችም ስሞች ጋር ማርከስ ጋርቪ መወሳቱ አይቀሬ ነው።

 ማርከስ ጋርቪ ገና የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ባልተላቀቁበት ጊዜ እንኳን "ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ "የሚለውን መሪ ህልም ከአእምሮው አመንጭቶ ታግሎ ያታገለ ጀግና ነው። ጋርቪ የአፍሪካ ዝርያዎችን ወደ አፍሪካ እንዲመለሱ ሆኖ የበለፀገች በራሷ ህዝብ የምትተዳደር ጠንካራና ነፃ የሆነች አንዲት አዲስ አፍሪካን መፍጠር ነበር አላማው።

 በጥሞናዊ የስነግጥም ስራዎቹ ውስጥ የመጀመሪያውን የኢንፔሪያሊስቶች ሽንፈት ከዋኝ የሆኑትን የአድዋ መሪ የሆኑትን አጤ ሚኒሊክ፣ከዚህ ሽንፈት በኹላም በኦጋዴን በኩል የጣሊያን ወረራ ያርበደበዱትን ራስ ነሲቡ ዛማኔልን እና ለኢትዮጵያ የተዋጋው ቱርካዊ ውሂብ ፓሻ አንዲሁም የደቡብ ክንፍ ተዋጊ የነበሩትና ቡታጅራ የተሰውትን ራስ ደስታ ዳምጠዉ የመሳሰሉትን የነፃነት ታጋዮች በስም ለመጥቀስ የመታሰቢያ ግጥሞችን አበርክቶላቸዋል።



 በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዘመናዊው ባርነት እየተገዛን ላለነው አፍሪካውያን ራሳችንን እንድንመለከት ያደርገናል። እንዴት? ብትሉ ዛሬም በዲቪ ሰበብ እነሱ የናቁትን የስራ አይነት ወይም ምርጫ በማጣት ሳቢያ ዛሬም በአውሮፕላን ተሳፍሮ፣በመኪና ተሽከርክሮ፣በመርከብ፣በታንኳ፣በጀልባ፣በበቅሎ፣በግመል እንዲያም ሲል በእግሩ ኳትኖ እዚያዉ ስፍራው ድረስ በመሄድ የሁነቱ ሰለባ መሆን እጅግ የሚያሳዝን እውነታ ነው።ይህ መጸሐፍ አይናችንን ገልጠን እውነታውን እንድናይ አመላካች ሲሆን እንደ እንደ አፍሪካዊ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን በግጥሞቹ እያነሳሳ ፣እየመከረ እና እየኮረኮመም ያስተምረናል።

 ይህን መፅሃፍ ማን ሊያነበው ይገባል? ይህ የማርከሰ ጋርቪ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ መፅሐፍ በታሪክም ሆነ በምርምር ተግባር ለተሰማሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ተቆርቋሪና ታጋይ ዜጋ እንዲሆኑ ከማገዝም ባሻገር ለአንባብያን የንባብ ፍጆ ወይም የዚያን ዘመን ከዚህኛው ጋር በማጣቀስ ምርምር ማድረግ ለሚሹ ሁሉ የጠብታንም ያህል አስተዋፅኦ ያደርጋል።


ሐሙስ 21 ጃንዋሪ 2021

የግል ቤተመጻሕፍት ለመክፈትና ለማንቀሳቀስ ስላደረኴቸው ነገሮች

 


(ፍላጎቱ ያላቸው እንዲጀምሩት በማሰብ የተጻፈ)

1.       መጻሕፍት በሽያጭ የማገኝባቸውን ቦታዎች አወቅሁ፡፡ እነዚህ ቦታዎች በአዲስ አበባ ያሉ የመጻሕፍት ማከፋፈያ መደብሮች ናቸው፡፡ መጀመሪያ ላይ ያገለገሉ መጻሕፍትንም እገዛ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሻጩ ከየት አምጥቶ እንደሚሸጥልኝ ስለማላውቅ ትቻለሁ፡፡ ግለሰቦች ሲለግሱም እቀበላለሁ፡፡

2.       ሰፋ ያለ ቤት ተከራየሁ፡፡ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ መደርደሪያና መጻሕፍት አሟላሁ፡፡

3.       ሰራተኛ ቀጠርኩ፡፡ እኔም እሰራለሁ፡፡

4.       ንግድ ፈቃድ ‹‹የጽሕፈት መሳሪያና መጻሕፍት ችርቻሮ ንግድ›› በሚል ዘርፍ አወጣሁ፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በንግድ ሕጉ ቤተመጻሕፍት የሚል ስለሌለ ይህን ዘርፍ መምረጥ ግድ ይላል፡፡ ግብር የሚተምኑ ሰዎች ሲመጡ የምሰራውን ስራ አይተው ግብር መተመን እንጂ ሌላ ይህን አትስራ የሚሉት ነገር የለም፡፡

5.       ስለቤተመጻሕፍት አሰራር ለማንበብ ሞከርኩ፡፡ በአማርኛ በዚህ ዘርፍ የተጻፈ ነገር ያለው ኮድ ኢትዮጵያ ያዘጋጀው ያልታተመ ሞጁል ነው፡፡

6.       ለቤተመጻሕፍቱ መጀመሪያ ሥራ ማስኬጃ የተወሰኑ አስርት ሺዎች ብር ተጠቅሜያለሁ፡፡ 

7.       የተለያዩ የቤተመጻሕፍት መርሃግብሮችን ጀምሬያለሁ፡፡ ለምሳሌ የውይይትና ሥነጽሑፍ ምሽት፣ የጉዞ መርሐግብር፣ ሥልጠና ወዘተ፡፡

8.       ሥራውን ልጀምር አካባቢ የጠየኳቸው ሰዎች ቢዝነስ ፕላን እንዳለኝ ጠይቀውኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ስለቢዝነስ ፕላን የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ለማዘጋጀትም አልሞከርኩም፡፡ ይህ ትልቅ ድክመቴ ነው፡፡ የሚጀምር ሰው ቢያዘጋጅ መልካም ነው፡፡

9.       ‹‹ይህን ስራ ስትሰራ ዓላማህ ምንድነው? በትክክል ጥርት ያለ ዓላማ ሊኖርህ ይገባል!›› ያለኝ ሰው ነበር፡፡ ያንንም ጥርት አድርጌ አለማወቄን እንደ ድክመት አየዋለሁ፡፡ ዓላማችንን ካላወቅን ተስፋ መቁረጥ ሊከተልና ስራውም አደጋ ላይ ሊወድቅ ስለሚችል ከመጀመራችን በፊት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ማድረግ እንደማልፈልግ፣ በነጻ ማስነበብን፣ በቅናሽ ዋጋ ማከራየትንና መሸጥን ያካተተ ስራ እንደምሰራ አውቀው ነበር፡፡ አሁንም በዚያ እንደገፋሁበት ነኝ፡፡ አሁን ላይ ሆኜም ሳስበው ከኪራይ ቤት ብቆይ እመርጣለሁ፡፡ ቤት የመስራትን ጣጣ አልፈልገውም፡፡ የቤት ኪራይ ከከበደ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ገንዘብ የማመነጭበትን መንገድ እፈልጋሁ፡፡

10.   መጽሐፍ ስለማከራየት መግለጽ ያለብኝ ነገር ቢኖር በመታወቂያ ማከራየት አክሳሪ መሆኑን ነው፡፡ በቤተመጻሕፍታችን ከ200 በላይ ያልተመለሱ መጻሕፍት አሉ፡፡ በመሆኑም ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ ገንዘብ በማስያዝ እንዲከራዩ አድርገናል፡፡ ይህ አሰራር በእርግጥ ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች እንዳይከራዩ ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሚያስከትለው ችግር አንጻር ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ መከራየት የማይችል ሰው ቤተመጻሕፍቱ ባቀረበለት በነጻ የማንበብ ዕድል ይጠቀማል፡፡

11.   ‹‹ስራው አትራፊ ነው ወይ?›› ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ‹‹አንባቢ ባለበት ከተማ ሊያተርፍ ይችላል›› የሚል መልስ እሰጣለሁ፡፡ ወይም ከአትራፊ ቢዝነስ ጋር በጥምረት ሊሰራ ይችላል፡፡ ስራው የንባብ ጉዳይ ለሚስበውና ቤተመጻሕፍት ኖሮት ለማየት ለሚፈልግ ሰው ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያና ህብረተሰብን ማገልገያ መንገድ ነው፡፡

12.   ለተጨማሪ መረጃ ቢጠይቁኝ ለማገዝ ዝግጁ ነኝ፡፡ ምናልባት ስለ ቤተመጻሕፍቱ መረጃ ለሌላችሁ ሰዎች ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ይባላል፡፡ መገኛው ደብረ ብርሃን ነው፡፡ መጋቢት 2008 ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ ንብረትነቱም የግል ሲሆን፤ በቤተመጻሕፍቱ በነጻ ማንበብ፣ በቀን 1 ብር በመክፈል መከራየትና እንዲሁም መግዛት ይቻላል፡፡

ማክሰኞ 12 ጃንዋሪ 2021

ንባብ ተኮር የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ለሁላችሁም

ከመዘምር ግርማ (mezemirgirma@gmail.com)

ዛሬ ላስተዋውቃችሁ የፈለኩት ጉዳይ ማናቸውም ሰው መጽሐፍ ሻጭ እንዲሆን ለማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ነው፡፡ ማንም ሰው ከቤቱ፣ ከመስሪያ ቤቱ ወይም ከተመቸው ቦታ ሁሉ ሊሰራው የሚችለው ይህ ሥራ ብዙ መነሻ ገንዘብ የማይጠይቅና የጊዜ ነጻነትም ያለው ነው፡፡ መጻሕፍትን ከደራስያን፣ ከአሳታሚዎች፣ ከሻጮችና አንብበወው ከሚሸጡ ግለሰቦች በመውሰድ ለተጠቃሚዎች ማድረስ ይቻላል፡፡ ይህን ሥራ በሚገባ ለመስራት አዳዲስና ያገለገሉ መጻሕፍት የሚገኙባቸውን ቦታዎች ማጥናት፣ ተፈላጊ መጻሕፍትን ማወቅና አንባቢ መሆን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የመጻሕፍትን መገኛ ካወቅንና መጻሕፍቱንም ካነበብናቸው ዳሰሳ መጻፍ፣ ተናግረን ማሳመንና መሸጥ እንችላለን፡፡  ይህ ብቻ ሳይሆን በደንብ ባለመተዋወቃቸው ምክንያት ያልተሸጡ መጻሕፍትን አንብቦ ጥሩ ይዘታቸውን ለማስተዋወቅ ለአንባቢ ማድረስ ይቻላል፡፡  የዚህኛው ዓይነት ሥራ ጠቀሜታው ብዙ ቁጥር ያለውን መጽሐፍ በአንድ ጊዜ ለማግኘትና ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት መቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘአልኬሚስት የተባለው የፓውሎ ኮሊዮ መጽሐፍ በስድስት ወራት ሁለት ኮፒዎች ብቻ ተሸጦ ከብዙ ጊዜያት በኋላ በአንድ አጋጣሚ በሚሊዮኖች ቅጂዎች የተሸጠ መሆኑን ማስታወስ ግድ ይላል፡፡

መጻሕፍትን ለማን እሸጣለሁ የሚለው አንድ አሳሳቢ ጉዳይ ሊሆንብዎት ይችላል፡፡ ይህን እርስዎ እንደ አንድ የቤት ስራ ወስደው እነማን ማንበብ ይችላሉ ብለው እንዲያስቡ ያስፈልጋል፡፡ ማንበብ የሚችሉ ሰዎችን ወደ አእምሮዎ ማምጣት ከቻሉ እንዴት ላስነብባቸው የሚለው ይከተላል፡፡ ማንበብ ጀምረው ከሆነ በዚያው እንዲቀጥሉ የፈለጉትን መጻሕፍት ያቅርቡላቸው፡፡ በየመስሪያ ቤቱና በየሰፈሩ የመጻሕፍት ዕቁብ መስርተውም ለመጻሕፍት ዕቁቡ መጽሐፍ ያቅርቡ፡፡ የማንበብ ልምድ የሌላቸው ከሆኑም ልምዱን እንዲያጎለብቱ አድርገው ወደ ንባብ ዓለም ያስገቧቸው፡፡ ሰዎች በሚፈልጉት ነገር ማንበብ ቢጀምሩ ጥሩ ነው፡፡ ከሚፈልጉት ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ኃይማኖት ዝንባሌ ላላቸው ደንበኞችዎ ከአንድ የመጻሕፍት መደብር የኃይማኖት ማጻሕፍት ስብስብ ያሉ መጻሕፍትን ፎቶ አንስተው ያስመርጧቸው፡፡ የመረጡትንም ያቅርቡ፡፡ የሥራ ፈጠራ ዝንባሌ ላላቸው፣ የስነልቦና መጻሕፍት ለሚወዱ፣ የቴክኖሎጂ ለሚያዘወትሩ ወዘተ እያጠኑ ያቅርቡ፡፡ ለስራዎም ሃያ አምስት በመቶና ከዚያ በላይ ኮሚሽን ያገኛሉ፡፡ በቅርብዎ ያሉትን አንባቢያን ካካለሉ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በቢዝነስ ካርድ ወይም በሌላ ሁነኛ መንገድ ስለስራዎት ማስታወቂያ ይስሩ፡፡ ይህም ማስታወቂያ ወደ ክፍለሃገርና ወደ ውጪ ሃገር መጻሕፍትን መላክ ያስችልዎታል፡፡ መጻሕፍት ተቀባዮች ያምኑዎት ዘንድ ግድ ስለሚል እምነትን የሚገነቡ ነገሮችን ይመርምሩ፡፡

ሌላው ወሳኝ ነገር የእርስዎ አንባቢት በመሆኑ እርስዎ በቤትዎ የመጻሕፍት ስብስብ ይኑርዎ፡፡ ያንን ስብስብ ለማንበብም ሆነ ድንገት ሲታዘዙ ለመሸጥ ይጠቀሙበት፡፡ በሃገራችን ንባብ ገና ያልተነካና የማደግ እድሉ ሰፊ የሆነ ዘርፍ በመሆኑ ለብዙ ሺ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በትንሹ አዟሪዎችንና አነስተኛ ሱቅ ያላቸውን ወገኖች ይመልከቱ፡፡ ለውጣቸው በየቀኑ የሚታይ ነው፡፡ ከማናቸውም ስራ ጋር የሚያስኬዱትና ትውልድን በማነጽ ላይ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችልዎትን ይህን ዘርፍ ቢቀላቀሉ እንኳን ደህና መጡ ብለን እጃችንን ዘርግተን እንቀበልዎታለን፡፡ ከምረቃ በኋላ ሥራ አጥ ሆነው ቀን በቀን ገንዘባቸውን በመከስከስ ላይ ያሉ ወጣቶች የማንበብ ችሎታ እያላቸው ያንን ኢንቬስትመንት ለምን እንደማይጠቀሙት አይገባኝም! እነዚህ ወጣቶች ዕድሜያቸውን ያሳለፉት በመማር ስለሆነ ያንን ትምህርት ቢያንስ የአንባቢያንን ፍላጎት የሚያረካ መጽሐፍ በመምረጥ መጠቀምና መጽሐፉን ሸጠው ኮሚሽን ማግኘት ይቻላቸዋል፡፡

የኦንላይን ገበያ ወደሃገራችን እየገባ ስለሆነ በቅርብ ጊዜ መጻሕፍትን ማናቸውም ሰው መሸጥ እንደሚችል ከሌሎች ሃገራት ልምድ ማየት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ አሁኑኑ መጀመር ለወደፊቱ ልምድ እንዲኖርዎ ያስችላል፡፡

ጥያቄ ካላችሁ በአስተያየት መስጫው ላይ ብቻ ጻፉልኝ፡፡ ይህም የጥያቄዎችን መደጋገም ለማስቀረትና ምልልሱን ሁሉም አባል እንዲያየው ማለት ነው፡፡

መልካም ስራ!


ሐሙስ 24 ዲሴምበር 2020

ለታዳጊ ሃገራት የተመረጡ የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች

 


አሰናጅ - መዘምር ግርማ

 

መግቢያ

በታዳጊ አገር እንደመገኘታችን ያለንበት ሁለንተናዊ ሁኔታ ከሌላው ዓለም የተለየ ነው፡፡ አዳዲስ ነገር የምንሞክር ሰዎች ለአካባቢያችን ተመራጭ የሆነ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያስፈልገን ይሆናል፡፡ ስለሆነም ላለንበት ዘመንና አካባቢያዊ ሁኔታ የሚስማሙ የሥራ ፈጠራ ሃሳቦችን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ በዚህም መሠረት ከድረገጽ ያገኘነውን ጽሑፍ በአጭሩ ወደ አማርኛ መልሰነዋል፡፡ በየሥራ ዘርፉ ያለውን ዕድልና ዝርዝር ሁኔታ ለማወቅ ድረገጹን እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡ ምናልባትም እንግሊዝኛ ቋንቋ የሚቸግራችሁ አንባቢያን ከድረገጹ ጽሑፉን ገልብጠችሁ በመውሰድ በጉግል ትራንስሌት ተርጉማችሁ በአማርኛ ማንበብ የምትችሉ መሆኑን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

 

ዝርዝር የሥራ ዓይቶቹን እነሆ፡-

1.     ደረቅ ቆሻሻ መሰብሰብ

2.     የሕጻናት ማዋያ

3.     ግብርና

4.     የቁጠባ ቤቶች አቅርቦት

5.     የውበት ሳሎን

6.     በድረገጽ ሙያን መሸጥ

7.     ብሎግ መጀመር

8.     የፀሐይ ኃይል ላይ የተመሰረተ ሥራ

9.     የስማርት ስልክ ሽያጭ

10.  ማስጠኛ ማዕከል

11.  ጭማቂ ቤት

12.  ልብስ ስፌት

13.  ሥዕልና ቅርጻቅርጽ

14.  አፕሊኬሽንና የኦንላይን ስራዎች

15.  ዘመናዊ የክፍያ መንገዶች

16.  አነስተኛ ብድርና ቁጠባ

17.  የጉዞ ወኪል

18.  የሞባይል ካርድ መሸጥ

19.  የዩቱብ ቻነል መጀመር

20.  ዕደ ጥበብ ማስተማር

21.  የሙዚቃ መምህርነት

22.  የስፖርት አሰልጣኝነት

23.  አስጎብኚነት

24.  የበይነመረብ የምግብ አሰራር ትምህርት

25.  ቁርስ ቤት

26.  አማራጭ የኃይል ምንጭ

27.  ነዳጅ ቆጣቢ ፈጠራ

28.  አስመጪና ላኪ

29.  ያገለገሉ ዕቃዎች ሱቅ

30.  ሥጋ ቤት

31.  ጥበቃና ደህንነት

32.  የሰራተኛ አገናኝ

33.  የኤሌክትሮኒክ ንግድ

34.  የዳሰሳ ጥናትና መረጃ ስብሰባ

35.  አማራጭ የኃይል ምንጭ

36.  የዕቃ ግዢ አገልግሎት

37.  የማጓጓዝ ሥራ

38.  የኮምፒውር ነክ መረጃ ጥበቃ

39.  የትምህርት ማማከር

40.  የእጥበት አገልግሎት

41.  ጥገና

42.  የጤና አገልግሎት

43.  የኮምፒውተር አገልግሎት ማዕከል

44.  የሂሳብ ሥራ

45.  የቢዝነስ ዕቅድ ሥራ

46.  የመኪና እጥበት

47.  የኮምፒውተር አሰልጣኝነት

48.  የግል የአካልብቃት አሰልጣኝነት

49.  የትርጉም አገልግሎት

50.  ቤት ለሚለቁ ዕቃ ማጓጓዝ

ማጠቃለያ

እስኪ ከእነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት የምርትና አገልግሎት ዓይነቶች የትኞቹን ለመሞከር አሰቡ? የትኞቹስ በአካባቢዎ ተጀምረዋል? የትኞቹስ አዳዲስ ናቸው? ለመጀመር የሚያስፈልጉዎትን ነገሮች ያስቡባቸው፡፡ መሬት ወይም ቦታ፣ ገንዘብ፣ ሥልጠና፣ የሠለጠነ ሠራተኛ ወይስ ሌላ? ለእነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች የሚመጡልዎትን መልሶች በመጻፍ ያቅዱ፡፡ ሌላ የማንክደው ነገር ከላይ የተገለጹት የሥራ ዘርፎች ላይ አልፎ አልፎ ተመሳሳይነትና ብዥታ ሊኖር ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ልዩ ባህርያት አሏቸው፡፡ ከኛ አገር ሁኔታም ጋር አጣጥሞ በማሻሻል በግልም ሆነ በቡድን መስራት ይቻላል፡፡ በቀጣይ ተከታታይ ዕትሞቻችን ሥራ ፈጠራን አስመልክቶ ተከታታይ ጽሑፎችን እንደምናወጣ እየገለጽን ለማናከውም ጥያቄዎ እንዲጽፉልን እንጋብዛለን፡፡

      በሸዋጸሐይ ዝግጅት ክፍል አድራሻ ወይም በ mezemirgirma@gmail.com    

ውድ አንባቢያችን፡- እርስዎም በጉዳዩ ላይ በደንብ አስበውበት በኛ ሁኔታ ሊሰሩ የሚችሉ አስር የሥራ ፈጠራ ሃሳቦችን ከላኩልን ጥሩ የምንላቸውን በቀጣይ ዕትሞች የምናወጣ ይሆናል፡፡

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...