2021 ጃንዋሪ 12, ማክሰኞ

ንባብ ተኮር የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ለሁላችሁም

ከመዘምር ግርማ (mezemirgirma@gmail.com)

ዛሬ ላስተዋውቃችሁ የፈለኩት ጉዳይ ማናቸውም ሰው መጽሐፍ ሻጭ እንዲሆን ለማድረግ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ነው፡፡ ማንም ሰው ከቤቱ፣ ከመስሪያ ቤቱ ወይም ከተመቸው ቦታ ሁሉ ሊሰራው የሚችለው ይህ ሥራ ብዙ መነሻ ገንዘብ የማይጠይቅና የጊዜ ነጻነትም ያለው ነው፡፡ መጻሕፍትን ከደራስያን፣ ከአሳታሚዎች፣ ከሻጮችና አንብበወው ከሚሸጡ ግለሰቦች በመውሰድ ለተጠቃሚዎች ማድረስ ይቻላል፡፡ ይህን ሥራ በሚገባ ለመስራት አዳዲስና ያገለገሉ መጻሕፍት የሚገኙባቸውን ቦታዎች ማጥናት፣ ተፈላጊ መጻሕፍትን ማወቅና አንባቢ መሆን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የመጻሕፍትን መገኛ ካወቅንና መጻሕፍቱንም ካነበብናቸው ዳሰሳ መጻፍ፣ ተናግረን ማሳመንና መሸጥ እንችላለን፡፡  ይህ ብቻ ሳይሆን በደንብ ባለመተዋወቃቸው ምክንያት ያልተሸጡ መጻሕፍትን አንብቦ ጥሩ ይዘታቸውን ለማስተዋወቅ ለአንባቢ ማድረስ ይቻላል፡፡  የዚህኛው ዓይነት ሥራ ጠቀሜታው ብዙ ቁጥር ያለውን መጽሐፍ በአንድ ጊዜ ለማግኘትና ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት መቻሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ዘአልኬሚስት የተባለው የፓውሎ ኮሊዮ መጽሐፍ በስድስት ወራት ሁለት ኮፒዎች ብቻ ተሸጦ ከብዙ ጊዜያት በኋላ በአንድ አጋጣሚ በሚሊዮኖች ቅጂዎች የተሸጠ መሆኑን ማስታወስ ግድ ይላል፡፡

መጻሕፍትን ለማን እሸጣለሁ የሚለው አንድ አሳሳቢ ጉዳይ ሊሆንብዎት ይችላል፡፡ ይህን እርስዎ እንደ አንድ የቤት ስራ ወስደው እነማን ማንበብ ይችላሉ ብለው እንዲያስቡ ያስፈልጋል፡፡ ማንበብ የሚችሉ ሰዎችን ወደ አእምሮዎ ማምጣት ከቻሉ እንዴት ላስነብባቸው የሚለው ይከተላል፡፡ ማንበብ ጀምረው ከሆነ በዚያው እንዲቀጥሉ የፈለጉትን መጻሕፍት ያቅርቡላቸው፡፡ በየመስሪያ ቤቱና በየሰፈሩ የመጻሕፍት ዕቁብ መስርተውም ለመጻሕፍት ዕቁቡ መጽሐፍ ያቅርቡ፡፡ የማንበብ ልምድ የሌላቸው ከሆኑም ልምዱን እንዲያጎለብቱ አድርገው ወደ ንባብ ዓለም ያስገቧቸው፡፡ ሰዎች በሚፈልጉት ነገር ማንበብ ቢጀምሩ ጥሩ ነው፡፡ ከሚፈልጉት ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል፡፡ ወደ ኃይማኖት ዝንባሌ ላላቸው ደንበኞችዎ ከአንድ የመጻሕፍት መደብር የኃይማኖት ማጻሕፍት ስብስብ ያሉ መጻሕፍትን ፎቶ አንስተው ያስመርጧቸው፡፡ የመረጡትንም ያቅርቡ፡፡ የሥራ ፈጠራ ዝንባሌ ላላቸው፣ የስነልቦና መጻሕፍት ለሚወዱ፣ የቴክኖሎጂ ለሚያዘወትሩ ወዘተ እያጠኑ ያቅርቡ፡፡ ለስራዎም ሃያ አምስት በመቶና ከዚያ በላይ ኮሚሽን ያገኛሉ፡፡ በቅርብዎ ያሉትን አንባቢያን ካካለሉ በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በቢዝነስ ካርድ ወይም በሌላ ሁነኛ መንገድ ስለስራዎት ማስታወቂያ ይስሩ፡፡ ይህም ማስታወቂያ ወደ ክፍለሃገርና ወደ ውጪ ሃገር መጻሕፍትን መላክ ያስችልዎታል፡፡ መጻሕፍት ተቀባዮች ያምኑዎት ዘንድ ግድ ስለሚል እምነትን የሚገነቡ ነገሮችን ይመርምሩ፡፡

ሌላው ወሳኝ ነገር የእርስዎ አንባቢት በመሆኑ እርስዎ በቤትዎ የመጻሕፍት ስብስብ ይኑርዎ፡፡ ያንን ስብስብ ለማንበብም ሆነ ድንገት ሲታዘዙ ለመሸጥ ይጠቀሙበት፡፡ በሃገራችን ንባብ ገና ያልተነካና የማደግ እድሉ ሰፊ የሆነ ዘርፍ በመሆኑ ለብዙ ሺ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በትንሹ አዟሪዎችንና አነስተኛ ሱቅ ያላቸውን ወገኖች ይመልከቱ፡፡ ለውጣቸው በየቀኑ የሚታይ ነው፡፡ ከማናቸውም ስራ ጋር የሚያስኬዱትና ትውልድን በማነጽ ላይ ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ የሚያስችልዎትን ይህን ዘርፍ ቢቀላቀሉ እንኳን ደህና መጡ ብለን እጃችንን ዘርግተን እንቀበልዎታለን፡፡ ከምረቃ በኋላ ሥራ አጥ ሆነው ቀን በቀን ገንዘባቸውን በመከስከስ ላይ ያሉ ወጣቶች የማንበብ ችሎታ እያላቸው ያንን ኢንቬስትመንት ለምን እንደማይጠቀሙት አይገባኝም! እነዚህ ወጣቶች ዕድሜያቸውን ያሳለፉት በመማር ስለሆነ ያንን ትምህርት ቢያንስ የአንባቢያንን ፍላጎት የሚያረካ መጽሐፍ በመምረጥ መጠቀምና መጽሐፉን ሸጠው ኮሚሽን ማግኘት ይቻላቸዋል፡፡

የኦንላይን ገበያ ወደሃገራችን እየገባ ስለሆነ በቅርብ ጊዜ መጻሕፍትን ማናቸውም ሰው መሸጥ እንደሚችል ከሌሎች ሃገራት ልምድ ማየት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ አሁኑኑ መጀመር ለወደፊቱ ልምድ እንዲኖርዎ ያስችላል፡፡

ጥያቄ ካላችሁ በአስተያየት መስጫው ላይ ብቻ ጻፉልኝ፡፡ ይህም የጥያቄዎችን መደጋገም ለማስቀረትና ምልልሱን ሁሉም አባል እንዲያየው ማለት ነው፡፡

መልካም ስራ!


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school.

  Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school. The Shenes said they wanted to aven...