(ፍላጎቱ ያላቸው እንዲጀምሩት በማሰብ የተጻፈ)
1.
መጻሕፍት በሽያጭ የማገኝባቸውን
ቦታዎች አወቅሁ፡፡ እነዚህ ቦታዎች በአዲስ አበባ ያሉ የመጻሕፍት ማከፋፈያ መደብሮች ናቸው፡፡ መጀመሪያ ላይ ያገለገሉ መጻሕፍትንም
እገዛ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሻጩ ከየት አምጥቶ እንደሚሸጥልኝ ስለማላውቅ ትቻለሁ፡፡ ግለሰቦች ሲለግሱም እቀበላለሁ፡፡
2.
ሰፋ ያለ ቤት ተከራየሁ፡፡
ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ መደርደሪያና መጻሕፍት አሟላሁ፡፡
3.
ሰራተኛ ቀጠርኩ፡፡ እኔም
እሰራለሁ፡፡
4.
ንግድ ፈቃድ ‹‹የጽሕፈት
መሳሪያና መጻሕፍት ችርቻሮ ንግድ›› በሚል ዘርፍ አወጣሁ፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በንግድ ሕጉ ቤተመጻሕፍት የሚል ስለሌለ ይህን
ዘርፍ መምረጥ ግድ ይላል፡፡ ግብር የሚተምኑ ሰዎች ሲመጡ የምሰራውን ስራ አይተው ግብር መተመን እንጂ ሌላ ይህን አትስራ የሚሉት
ነገር የለም፡፡
5.
ስለቤተመጻሕፍት አሰራር ለማንበብ
ሞከርኩ፡፡ በአማርኛ በዚህ ዘርፍ የተጻፈ ነገር ያለው ኮድ ኢትዮጵያ ያዘጋጀው ያልታተመ ሞጁል ነው፡፡
6.
ለቤተመጻሕፍቱ መጀመሪያ ሥራ
ማስኬጃ የተወሰኑ አስርት ሺዎች ብር ተጠቅሜያለሁ፡፡
7.
የተለያዩ የቤተመጻሕፍት መርሃግብሮችን
ጀምሬያለሁ፡፡ ለምሳሌ የውይይትና ሥነጽሑፍ ምሽት፣ የጉዞ መርሐግብር፣ ሥልጠና ወዘተ፡፡
8.
ሥራውን ልጀምር አካባቢ የጠየኳቸው
ሰዎች ቢዝነስ ፕላን እንዳለኝ ጠይቀውኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ስለቢዝነስ ፕላን የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ለማዘጋጀትም አልሞከርኩም፡፡
ይህ ትልቅ ድክመቴ ነው፡፡ የሚጀምር ሰው ቢያዘጋጅ መልካም ነው፡፡
9.
‹‹ይህን ስራ ስትሰራ ዓላማህ
ምንድነው? በትክክል ጥርት ያለ ዓላማ ሊኖርህ ይገባል!›› ያለኝ ሰው ነበር፡፡ ያንንም ጥርት አድርጌ አለማወቄን እንደ ድክመት
አየዋለሁ፡፡ ዓላማችንን ካላወቅን ተስፋ መቁረጥ ሊከተልና ስራውም አደጋ ላይ ሊወድቅ ስለሚችል ከመጀመራችን በፊት ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
በእርግጥ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ማድረግ እንደማልፈልግ፣ በነጻ ማስነበብን፣ በቅናሽ ዋጋ ማከራየትንና መሸጥን ያካተተ ስራ እንደምሰራ
አውቀው ነበር፡፡ አሁንም በዚያ እንደገፋሁበት ነኝ፡፡ አሁን ላይ ሆኜም ሳስበው ከኪራይ ቤት ብቆይ እመርጣለሁ፡፡ ቤት የመስራትን
ጣጣ አልፈልገውም፡፡ የቤት ኪራይ ከከበደ መፍትሔ መፈለግ ነው፡፡ ገንዘብ የማመነጭበትን መንገድ እፈልጋሁ፡፡
10.
መጽሐፍ ስለማከራየት መግለጽ
ያለብኝ ነገር ቢኖር በመታወቂያ ማከራየት አክሳሪ መሆኑን ነው፡፡ በቤተመጻሕፍታችን ከ200 በላይ ያልተመለሱ መጻሕፍት አሉ፡፡ በመሆኑም
ከሁለት ዓመት አገልግሎት በኋላ ገንዘብ በማስያዝ እንዲከራዩ አድርገናል፡፡ ይህ አሰራር በእርግጥ ገንዘብ የሌላቸው ሰዎች እንዳይከራዩ
ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሚያስከትለው ችግር አንጻር ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ መከራየት የማይችል ሰው ቤተመጻሕፍቱ ባቀረበለት
በነጻ የማንበብ ዕድል ይጠቀማል፡፡
11.
‹‹ስራው አትራፊ ነው ወይ?››
ብሎ ለሚጠይቅ ሰው ‹‹አንባቢ ባለበት ከተማ ሊያተርፍ ይችላል›› የሚል መልስ እሰጣለሁ፡፡ ወይም ከአትራፊ ቢዝነስ ጋር በጥምረት
ሊሰራ ይችላል፡፡ ስራው የንባብ ጉዳይ ለሚስበውና ቤተመጻሕፍት ኖሮት ለማየት ለሚፈልግ ሰው ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያና ህብረተሰብን ማገልገያ
መንገድ ነው፡፡
12.
ለተጨማሪ መረጃ ቢጠይቁኝ
ለማገዝ ዝግጁ ነኝ፡፡ ምናልባት ስለ ቤተመጻሕፍቱ መረጃ ለሌላችሁ ሰዎች ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ይባላል፡፡ መገኛው ደብረ
ብርሃን ነው፡፡ መጋቢት 2008 ዓ.ም ተመሰረተ፡፡ ንብረትነቱም የግል ሲሆን፤ በቤተመጻሕፍቱ በነጻ ማንበብ፣ በቀን 1 ብር በመክፈል
መከራየትና እንዲሁም መግዛት ይቻላል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ