ሐሙስ 27 ሜይ 2021

የኢትዮጵያን አንባቢ ለመታደግ የሚታትረው የእንዳለጌታ ውጥን

በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ባህል ማዕከል የጥበብ ምሽት በጣት የምንቆጠር የጥበብ ቤተሰቦችን ለማናገር ከአዲስ አበባ እንደመጣ ተዋወቅሁት። ለባህል ማዕከሉ ዓመታዊ የጥናት ጉባኤ በድጋሚ መጥቶ ቤተመጻሕፍቴን (ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት፣ ደብረብርሃን) ጎበኘልኝ። ሻይ ቡናም አልን። በጣም ትሁትና ተግባቢ ሰው ነው። ዛጎልና በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ስራዎቹ የተባሉትን መጻሕፍቱን ያነበብኩለት በከተማችን ባካሄድናቸው የመጽሐፍ ውይይቶች ምክንያት ነው። ማዕቀብን አንብቤ ዳሰሳም ጽፌያለሁ። የእርሱን ደርዘን መጻሕፍት ገና ማንበብ ይኖርብኛል። ጓደኛው አንዱዓለም አባተን ከሱ ጋር በስም አሳስታቸው ነበር። የደብረብርሃኑን ልጅ ሳገኘው መጻሕፍቱን ባለማንበቤ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶኛል። ንጉሥ ዘርዓያዕቆብንና የሕሊና መንገድን በመጻሕፍት ክበባችን ሰበብ አነበብኩ። ገና ብዙ ይቀረኛል። አስነብባለሁ እንጂ ንባብ ላይ ገና ነኝ፡፡  

 


 ወደዚህ ሰሞኑ ጉዳያችን በዚህ መንደርደሪያ ልግባ። 

እንዳለጌታ ከበደ ዛጎል የመጻሕፍት ባንክ የሚባል ውጥን ጀምሯል። መጻሕፍትን እያሰባሰበ ለአብያተመጻሕፍት የማድረስ ውጥን አለው። ሰሞኑን ደውሎ አዲስ አበባ ዛሬ ሐሙስ 19.09.2013 እንድገኝና በዛጎል ቤተሰብ ፊት መጻሕፍቱን እንድቀበል ጠየቀኝ። በደስታ ተስማማሁ። ጠዋት ከደብረብርሃን ተነስቼ ወደ አዲስ አበባ አቀናሁ። በብሔራዊ ባለመጻሕፍት ቤቶች ወዳጆቼን እየዞርኩ ሰላም አልኩ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መጻሕፍት አውደ ርዕይን ቃኘሁ። መጥፋቴን ብዙ መጻሕፍት ሻጮች ነገሩኝ። በአዲስ ስራ በክረምቱ እንደምመጣ አበሰርኳቸው። ጓደኞቼን አዲሱ ገረመውንና አዲሱ ኃይሉን ይዤ አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ጀርባ ኢክላስ ሕንፃ 8:00 ደረስኩ። እንዳለጌታ ከበደ ከዕለቱ ሰርፕራይዝ ጋር ተሰይሟል። ዓለማየሁ ገላጋይ ነው፡፡ ዓለማየሁ ገላጋይንና ታዳሚያንን ሰላም ብለን ተቀመጥን። 

በእንዳለጌታ የማስተዋወቅ ሂደት ዝግጅቱ ጀመረ። ቡክ ባንኩ በቅርቡ የጀመረ ነው። ለጮቄ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ አዋሽ አርባ በአጠቃላይ ለሰባት አብያተመጻሕፍት እስካሁን መጻሕፍትን መለገሱ ተነገረን። የዛሬዎቹ ደግሞ ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ፣ ልደታ የሚገኘው የወጣት ጥፋተኞች ማረሚያ፣ የደብረብርሃኑ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት፣ አራተኛው የጎዛምኑ መሰለኝ ነን። ለመጀመሪያ ያህል ለእያንዳችን 200 መጻሕፍት ተበረከተልን እንጂ ዕቅዱ ለእያንዳንዱ 981 መጽሐፍ ነው። 

የዛሬው የትስስር መድረክ ሁላችንም እንድንተዋወቅበት የታሰበ ነው። 

ከአዲስ አበባ የመጡት እንግዶች የተለያዩ ውጥኖች ያሏቸውና በበጎ ፈቃድ የሚሳተፉ ናቸው። ከተማ ውስጥ የመቀመጥ ዕድል ከፍ አድርገው እንዲያስቡ እንዳደረጋቸው ገባኝ። ከተምኛ አንድ ብሔር ባይኖረውም የአይሁድ ሕዝብን አስታወሱኝ። በከተመኝነት የነቃ ህዝብ። 

ያላነበበውን የማያስነብበው የዛጎል ስብስብ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተጻፉ መጻሕፍት ቢለገሱ ደስተኛ ነው። መጽሐፍ ለመለገስ ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ የሆኑት የሚለግሳቸው መጻሕፍት እንዲነበቡ፣ ለውይይት እንዲቀርቡና ለትውልድ እንዲበጁ ይሻል። ዘመኑ ያከተመበት መጽሐፍ፣ ትውልዱን የሚያበላሽም ሆነ የማይሆን ነገር እንዳይመጣ ይፈልጋል። 

ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ የመንገደኛ ደራሲ በማስተርስ ምርምራቸው ላይ የተመሰረተ የአማርኛ መጽሐፋቸውን ይዘት አብራሩልን። አስደማሚ ጉዳይ ነው። በውጪ ቋንቋ የቀረበውን በስደት ላይ የሰሩትን ምርምር በአማርኛ አቅርበዋል። በዋቸሞ መጻሕፍት ቤት የመክፈት ፍላጎት አላቸው። በአዲስ አበባ ስላለው ብራና የንባብ ክበብም አውግተውናል። ከሆቴሎች ጋር በመተባበር ዝግጅቶቹን የሚያቀርብ ነው።

 

WETREK የሃይኪንግ ቡድን አባላት እነ ታምራት ስልጣን ተገኝተዋል። ገለጻቸው ውብ ነው። መጽሐፍ ለግሰዋል። በሆስፒታሎች ላሉ የህጻናት ክፍሎች ስዕል ስለዋል። ከብዙ በጥቂቱ።  

የወጣት ጥፋተኞች ማዕከሉም በልደታ የሚገኘውና በኢትዮጵያ ብቸኛው ነው። የሁላችንንም ጉብኝትና ትኩረት ይሻል። 

 

ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲም ተወክሏል፡፡ አብሮ የመስራት ፍላጎት አለው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ዓይነቱ ዝግጅት መሳተፋቸው ካላቸው የሰው ብዛትና የሃብት መጠን አንጻር ማለፊያ ነው፡፡

እኔ በተሰጠኝ ዕድል ስለ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ገለጻ አድርጌያለሁ። ለቤተመጻሕፍቱ መጀመር ምክንያት ስለሆነችው የትርጉም መጽሐፌ ሁቱትሲና በሷ ስለወጣሁ ስለወረድኩት አጋወሁ። በግል የማሳተምና የማከፋፈልን ጣጣም አነሳሳሁ። ከኔ ንግግር እዚህ ቢደገም የምለው መጽሐፍ የሚወደውና ብሩ ያለው የተለያየ ሰው በመሆኑ በዘርፉ ድጋፍ መታጣቱ ነው።  

ዓለማየሁ ገላጋይ በብዙ የሕይወት ገጠመኞቹና ትረካዎቹ አስተምሮናል። አዝናንቶናል። ሐብታም ላይ የሚዘባነንበትን ስነልቦና የፈጠረው ፍካት የተሰኘ የወጣት ደራስያን ማህበር በጀመረ ተግባሩ ነው። የውይይት ክበብ ነበር። ለአባላቱ መጻሕፍትን በእጅ እየገለበጠ ሳይቀር አስነብቧል። ደብረሲና ስላለ የመጻሕፍት ቤትም አውግቶናል። እገዛ ይሻል ብሏል። ወደስፍራው ለደራሲ ዳኛቸው ወርቁ መታሰቢያ ጉዞ ባደረገ ጊዜ ስለታዘበ ነው። 

 

እንዳለጌታም በጨዋታ እየዋዛ ሁላችንንም አስተዋውቋል፡፡ ትስስር ፍጠሩ የተባለው ላይ ወደቤት ቶሎ ለመሄድ በነበረን ጥድፊያ ባንችልም እንዳለ ወደፊት ያስተሳስረናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ደብረብርሃን በሰላም ገብቻለሁ።

መዘምር ግርማ

mezemirgirma@gmail.com

ከበሬሳ ወንዝ አጠገብ

 

 

 

 

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...