ዓርብ 30 ሴፕቴምበር 2016

‹‹ልጅ ቢኖረኝ እዚያ ነበር የማስተምረው›› አያስብልም?



ባለፈው ያቀረብኩት የአስራ አራት ስራ ፈጣሪ መምህራን ተሞክሮ አነጋጋሪ የነበረ ይመስለኛል፡፡ በዚያ ተነሳስተው በሰዓቱ መንገዳቸውን የጀመሩ እንዳሉ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ዛሬ የማቀርበው መምህር እዚህ ደብረ ብርሃን ላይ የእውነት ስራ ፈጣሪ ነው ስላችሁ ከሐቅ ነው፡፡ የሚሰራው ስራ እነሆ፡-
‹‹በየዕለቱ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንደተመለሱ የቤት ስራቸውን ተከታትሎ እንዲሰሩ ማድረግ፣ በየዕለቱ የተማሩትን ሁሉንም ትምህርት ወደሚቀጥለው ቀን ሳይሸጋገር እንዲከልሱና እንዲያጠኑ ማድረግ›› ይላል ማስታወቂያው፡፡
ከአንደኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በአምስት ትምህርቶች ላይ የማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጥበት ይህ ተቋም ኤፈርት ዞን የቱቶሪያል ማዕከል ይባላል፡፡  ልጆች ከጥገኝነት መንፈስ እንዲላቀቁና በራሳቸው እንዲያጠኑ ያደርጋል፡፡ መምህራንም ተማሪዎቹ በተቸገሩባቸው ነጥቦች ላይ መጠነኛ እገዛ ያደርጉላቸዋል፡፡ አብዛኛውን ስራ በራሳቸው እንዲሰሩ የሚደረጉት ወደዚህ ማዕከል የሚመጡት ተማሪዎች በራስ የመተማመን ስሜታቸው እየጎለበተ ይሄዳል፡፡ ታዲያ ለዚህ ስራው 200 ብር ወርሃዊ ክፍያ አንድን ተማሪ ማስከፈል ይበዛበታል?
ታዲያ በአብዱ ጀባር ህንጻ (ደብረ ብርሃን ቀበሌ 03) የማጠናከሪያ ትምህርቱን የመስጠቱ ሃሳብ ከየት ፈለቀ አይሉኝም? አሁን በማዕከሉ የማስጠናቱን ስራ የተያያዙት መምህራን በፊት በፊት በየቤቱ ያስጠኑ ነበር፡፡ ሲያስጠኑ ግን ተማሪው የሚጠብቁትን ያህል መሻሻል ሳያመጣ ይቀራል፡፡ ምክንያቱን ሲመረምሩት ብዙ ጥረት የሚያደርጉት መምህራኑ ራሳቸው እንጂ ተማሪዎች ስላልሆኑና ተማሪዎች የመለማመጃ ዕድላቸው አናሳ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔ ያሉት አሁን የጀመሩት ስራ ነው፡፡ በየትምህርት ዘርፉ ከየትምህርት ቤቱ የተውጣጡትና በስነ-ምግባራቸው የተመሰገኑት መምህራን ከመደበኛ የስራ ሰዓት በኋላ እየተገኙ ተማሪዎችን ያግዛሉ፡፡ ቅዳሜ የመለማመጃ ጥያቄዎችን ያሰራሉ፡፡ እንግሊዝኛን ኦዲዮ ቪዲዮ ጭምር በመጠቀም ሲያስተምሩ አይቻለሁ፡፡ በክረምትም የማጠናከሪያ ትምህርቱ አይቋረጥም፡፡
ነሐሴ 15፣ 2008 ዓ.ም. ማዕከሉ በድምቀት ሲመረቅ በነበረው የሥልጠናና የውይይት መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት ወላጆች፣ ተማሪዎች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የሰጧቸውን ሃሳቦች በመጠቃቀስና እርስዎም ጥያቄና አስተያየትዎን እንዲለግሱ በመጋበዝ እዚህ ጋ ልሰናበት፡፡
-       ወላጆች ላይ ስለ አሰራራችሁ የግንዛቤ ስራ መሰራት አለበት፡፡
-       ለልጆቻችን በቂ ድጋፍ፣ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ለማንችል ሰዎች መልካም ዕድል ነው፡፡
-       ከትምህርት ቤት መልስ በየቤታችን የልጆቻችንን አእምሮን የሚያበላሹ ነገሮች ስላሉ ልጆቹ እዚህ መቆየታቸው መልካም ነው፡
-       ሞባይልና ኢንተርኔት ጤናቸውን ስለጎዳብንና ሱሰኛም ስላደረገብን ቁጥጥር እናድርግባቸው፤ ልጆቹ ላይ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣትም አሰልጥኑልን፡፡ የጊዜ አጠቃቀምና የአጠናን ስልት ስልጠና የሚያስፈልገው ብዙ ልጅ አለ፡፡
-       የፊልም አማራጭ የበዛበትና ቴክኖሎጂን በተሳሳተ መንገድ በሚጠቀሙበት ሁኔታ ይህ ማዕከል ሁነኛ ስፍራ ነው፡፡
-       ከፊልምና ከቴክኖሎጂ ጋር የሚከፈተው ውጊያ አንዱ ግንባር ይህ ቤት ነው፡፡
-       በቀን ከአራት እስከ አምስት ሰዓት በላይ ለፈልም የሚቀመጥ ወላጅ ለልጁ ትምህርት ትኩረት ባይሰጥ አይገርመኝም፡፡ ልጃችን ግን ቢያጠና ምን ይሆናል?
-       ያልነበረ ነገር እንደዚህ ፈጥራችሁ ልጆቹ ላይ ለውጥ አምጡልን፡፡
-       በዚህ አጀማመር ያላሰባችሁት ነገር ሁሉ ሊሳካላችሁ ይችላል፡፡
-       ትምህርታዊ ውድድሮች፣ ፊልሞች፣ የጥያቄና መልስ ውድድሮች ይኖሯችኋል ብዬ አስባለሁ፡፡
-       ወላጆች የልጃችንን ልብሱን ብቻ አይደለም መቀየር ያለብን፤ አእምሮውንም ነው፡፡
-       የዚህ ማዕከል ውጤት የሚታየው ከብዙ ዘመን በኋላ ነው፡፡ እስከዚያ ግን ብዙ መጋር ያሻል፡፡
-       ልጆቻችንን አያባትልብንም ወይ?

ሐሙስ 29 ሴፕቴምበር 2016

የሰሜን ሸዋ ልጅ

‹‹አትንኩኝ ነው እንጂ ከልክ አትለፉ እስኪ ሠሜን ሸዋን ማን ይለዋል ክፉ››  ይለናል አርቲስት ትዛዙ በትሩ፡፡ እስኪ ይመልከቱትና ለወዳጅዎ ያጋሩት!

ሰኞ 5 ሴፕቴምበር 2016

ያነበቡትን ይተገብራሉ?

ስለንባብ ሳማክር የምጠይቃቸውን እነዚህን ጥያቄዎች እርስዎንም ልጠይቅዎትና በሚጽፉት ምላሽ መሠረት እኔም አባላትም አስተያየት እንስጥዎት፡፡
1. ሲያነቡ ግልፅ ግብ/ዓላማ ያስቀምጣሉ?
2. መጥፎ ያነባበብ ልማዶች አሉብዎ?
3. በንባብ ወቅት የአትኩሮትዎ ሁኔታስ?
4. የፀጥታ መከበር ያሳስብዎታል?
5. ንቁ አንባቢነትን ይግለፁ
6. ምን ዓይነት መጻሕፍት ያነባሉ?
7. ንባብዎ የዕውቀት፣ ክህሎት ወይም ያመለካከት ተብሎ ተከፋፍሏል?
8. ያነበቡትን ለማስታወስ ይቸገራሉ?
9. ከአፍ መፍቻዎ ውጪ በሆነ ቋንቋ ሲያነቡ ይቸገራሉ?
10. ያነበቡትን ይተገብራሉ?
ለተጨማሪ ሐሳብ 0970381070

ረቡዕ 27 ጁላይ 2016

ሉላዊነት (ገሎበላይዜሽን)



በቅርቡ ስሉላዊነት (ገሎበላይዜሽን) ባደረግነው ውይይት ላይ ተሳታፊዎች ያነሷቸውና በማስታወሻ ደብተሬ የያዝኳቸው አንዳንድ ነጥቦች
1. የቻይና ዶክተር በቻይንኛ ተምሮ እዚያው ቻይና ይሰራል፡፡
2. ኢትዮጵያ ከሰለጠነች ችግር አለ ብለው የሚያስቡ አገሮች አሉ፡፡
3. የሉላዊነት ጥቅም አስናፊ አይሁንብን፡፡ ሌላው ዓለም ሁሉንም ሰርቶልናል ብለን አንቀመጥ፡፡
4. ዓሳ ይሰጡናል እንጂ አጠማመዱን አንማርም፡፡
5. የማን ዕውቀት፣ ምርትና ፈጠራ ነው ሉላዊ የሚሆነው?
6. ኮርጅ፣ አበልጽግ፣ ለዓለም አከፋፍል የሚለውን ብንከተል ይሻለናል፡፡
7. ጥሩና መጥፎውን የውጪ ነገር ማን ይምረጥ?
8. እውቀታችን ከሌላው ዓለም የማይመጣጠን ከሆነ  ተጋላጭነታችን ይጨምራል፡፡
9. ቴክኖሎጂውን እኛ ስላልፈጠርነው የመቆጣጠር አቅም የለንም፡፡
የትኛውን ወደድከው/ሽው?

ሐሙስ 14 ጁላይ 2016

መምህር፣ ገና አሁን ማስተማር ጀመርክ!


አንድ ጓደኛዬ ‹‹የገንዘብን ከንቱነት የሰበከ›› ይለኝ የነበርኩት መምህር መጋቢት 20፣ 2008 ዓ.ም. በደብረብርሃን ከተማ የሽያጭ፣ የኪራይና በነጻ የማስነበብ አገልግሎት የሚሰጥ የግል መጻሕፍት ቤት ከፍቻለሁ፡፡ በዚህ ቤተመጻሕፍት የተለያዩ ሰዎች ሲያነቡ አይቶ የተደሰተው አንድ ተማሪ ‹‹መምህር፣ ገና አሁን ማስተማር ጀመርክ›› አለኝ፡፡ እርሱ በእርግጥ ሰዎችን በማስነበቤና በንባብ ላይ እያመጣሁ ያለሁትን ለውጥ አይቶ ነው እንዲህ ያለኝ፡፡ እኔ ግን ሌላም ትምህርት እየሰጠሁ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መምህራንም ሆኑ ሌሎች ስራ እንዲፈጥሩ አርአያ እየሆንኩ ነው፡፡
ለመጻሕፍት ቤታችን ከመምህራንም ሆነ ከሌሎች ግለሰቦች የመጻሕፍት ልገሳ ይደረግልናል፡፡ መምህር ኢዮብ ሚልኪያስ የተባሉ የስነትምህርት መምህር ከለገሱን ሦስት መጻሕፍት አንዱ ‹‹በኢንተርፕረነርሺፕ ራስንና ሀገርን ማበልጸግ›› የሚለው የዶክተር ወሮታው በዛብህ መጽሐፍ ነው፡፡ ኢንተርፕረነርሺፕ ወይንም ስራ ፈጠራ ገና ያልተጠቀምንበት ጥበብ መሆኑን መጽሐፉን አንብቤና ከሰዎች ጋር ተነጋግሬበት ተረዳሁ፡፡ በቤተመጻሕፍታችን ዘወትር ሐሙስ ማታ በምናካሂደው የስነጽሑፍና የውይይት ዝግጅትም አንድ ቀን ከሰላሳ በላይ ሆነን ተወያየንበት፡፡ አወያያችንም ዶክተር ወሮታው ራሳቸው ያሰለጠኗቸው መምህር ነበሩ፡፡ በዚያ ውይይት ላይ አንድ የራሳቸውን ስራ የፈጠሩ ተሳታፊ የተናገሩትን ልጥቀስ፡፡ ‹‹እስካሁን ባነሳችሁት ሐሳብ ላይ ‹ኢንተርኔት እንዲህ ይላል፡፡ ሌላ አገር አንዲህ ተደረገ› ብላችኋል፡፡ ጎግልን ሰላሳ ጊዜ የምንጠቅስ ከሆነ የጎግል ተቀጣሪ ሆነናል፡፡ እዚህ ጋ ያለውን ነገር ነው ማየት የሚኖርብን፡፡ ዓይናችንን ገልጠን እዚህ ምን ሳይሰራ ቀረ ብለን አጥንተን ወደ ስራ መግባት ይኖርብናል›› ብለዋል፡፡ አነጋገራቸው ግማሽ በግማሽ እውነትነት አለው፡፡ ዓይናችንን ለመግለጥ የሚረዳን ቅስቀሳ ያስፈልገናል፡፡
የተወሰንን መምህራን እይታችንን የጋረደውን ጉም አስወግደነዋል፤ ሌሎቻችሁስ?
ገንዘብ በማሰሮና በድብኝት ማስቀመጥ ሐገራችን ኢትዮጵያ የስራ ፈጠራ እንዳይስፋፋባትና እንዳታድግ መሰናክል ሆኖባት ኖሯል፡፡ ይህም ያንገበገባቸውና ሥር የሰደደውን ባህል ለመቀየር ይጥሩ የነበሩ ወጣ ያሉ ሰዎች ብዙ ለፍተዋል፡፡ ለምሳሌ ከከያኒያን እነነዋይ ደበበ ‹‹ሁሉም ቢተባበር›› በሚለው ከታች በመጠኑ ግጥሞቹ በተጠቀሱት ዘፈናቸው ማህበረሰቡን ለማነቃቃት ጥረዋል፡፡
‹‹ሁሉም ቀና ቢያስብ ሁሉም ቢተባበር
ማን? ኧረ ማን? ይደርስብን ነበር?
ያም ያም ቢተባበር
ድህነት ባልነበር፡፡
እኛው ብንስማማ እኛው ብንፋቀር
የለፋ ቢወደስ፣ የሰራ ቢከበር
ማን? ኧረ ማን? ይደርስብን ነበር?››
ማህበረሰባችን ስለስራ ፈጠራ ጥበብ ማወቅ፣ መተግበርና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማምጣት እንዳለበት በትክክል ተረድቻለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ በደብረብርሃን ከተማ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው የሚንቀሳቀሱ 13 መምህራንን ስለስራቸው ሁኔታ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ ዓላማዬም የእነዚህን መምህራን ልምድ ለሌሎች በማሳወቅ ሌሎች ስራ እንዲጀምሩ ማነሳሳት ነው፡፡ ስራ ካልጀመሩት መምህራን ሰባት የሚሆኑትን ለማናገርና ከውጭ ሆነው ሲያዩት ስራ ስለመጀመር ምን እንደሚያስቡ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ስራ ለመጀመር ከሚያስፈልጉትን አንዱን ቁልፍ ጉዳይ እነሆ!
ተነሳሽነትን የሚያዳብር የአስተሳሰብ ለውጥ
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር የሆኑና ራሳቸው ገና ተጨማሪ ስራ መስራት ያልጀመሩ አንድ መምህር መምህራን ተጨማሪ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ እንደሚከተለው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹መምህር ገቢው አነስተኛ ስለሆነ ተጨማሪ ስራ መጀመር አለበት፡፡ በቂ ትርፍ ጊዜ አለን፡፡ ተጨማሪ ስራ ይስሩ የምልህ ሙያቸውን እንዲያዳብሩ ሳይሆን በገቢ እንዲደጎሙ ነው፡፡ ከሙያዬ ጋር ተያያዥ የሆኑት የገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ እንድሰማራ መጀመሪያ ተያያዥ ያልሆኑትን መስራት አለብኝ፡፡ እነዚያ ሌሎች ስራዎች የተሻለ ገቢ ያስገኙኛል፡፡››
እንደ እኚህ መምህር ሁሉ ገና ወደ ስራ ያልገቡ ግን ፍላጎቱ ያላቸው አንድ ሌላ ያነጋገርኳቸው ሰው 400 የቢዝነስ ሐሳቦች እንዳሏቸው ቢነግሩኝም ለራሳቸው የፈጠሩትን ስራ አላሳዩኝም፡፡ ማቀድና መተግበር ሊለያዩ ይችላሉና፡፡ የቢዝነስ ሐሳቦቹን የመሸጥ ዝንባሌ ግን አይቼባቸዋለሁ፡፡ ተነሳሽነት የሚባለው ቅመም ያስፈልጋቸዋል እኚህ መምህር፡፡ እርሳቸውን ለማነሳሳት እየጣርኩ ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ውይይት ምሽታችን አንድ ሌላ ተሳታፊ ‹‹ሁላችንም ውስጥ የታመቀ ስራ ስላለ ወደ ተግባር ለመግባት እንነሳ፡፡ ተቀጣሪነት ለጽድቅ መስራት ነው›› ማለታቸውን ሳስታውስ የስራ ፈጠራ አመለካከቱ የተለወጠ ሰው እስካሁን ያቃጠለው ጊዜ ይቆጨዋል ባይ ነኝ፡፡
አንዴ ተነሳሽነቱን ካዳበርን ወደ ስራ መሰማራት ይኖርብናል፡፡ ለዚህም ገበያን አጥንቶ መግባት ያሻል፡፡ ይህም የሚያዋጣ ቢዝነስን ስራዬ ብሎ ፈልጎ እንደሚያዋጣ እርግጠኛ ሆኖ መግባት ማለት ነው፡፡ አጥንቶና አማራጭ ይዞ ወደ ገበያ ከተገባ፣ ጽናት ካለ፣ ቃል ከተጠበቀ፣ ጥራትን እያሻሻሉ ከተሄደ በሁለት እግሩ የሚቆም ስራ ባለቤት መሆን ይቻላል፡፡ 
በስራ ፈጠራ የህብረተሰብን አመለካከት መገንባት
‹‹በወተት የወፈረ በደምወዝ የከበረ የለም!›› ብሎ ከማስተማር ስራው በተጨማሪ ሌላ ስራ የጀመረ መምህር በአካባቢዎ አይተዋል? ካዩ ለሥራ ፈጠራ አርአያ መምህር አለዎት፡፡ ካላዩ ግን የለዎትም፡፡
‹‹ሁለት እጃችንን ለመንግሥት አንሰጥም፤ በአንድ እጃችን መጠባበቂያ ስራ እንሰራለን እንጂ›› ያሉ መምህራን እንዴት እንደተለወጡ ካየን እኛም የለውጥን ጎዳና ለመጀመርና ችግሮችን የሚጋፈጥ ስብዕና ለመገንባት አንተጋለን፡፡ ‹‹ምን ይሄ አልጠግብ ባይ!›› ብለው ልፋቱን ባልተገባ መንገድ የሚረዱ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነሱ ይልቅስ ለዚህ ጽሑፍ በግብዓትነት ሐሳባቸውን የሰጡትን ወደ ተጨማሪ ስራ የገቡ መምህራን ሐሳብ ቢጠቀሙበት ሕይወታቸውን ሊያሻሽሉ ይችላሉ፡፡  
መምህራን ከማህበረሰቡ አንጻራዊ በሆነ የስልጣኔ፣ የእውቀትና የክህሎት ከፍታ ላይ ስለሚገኙ ክፍተቶችን በቀላሉ ሊያዩና ወደ ስራ ሊሰማሩ ይችላሉ፡፡ማህበረሰቡን ከሐቅ በማገልገል ልምድ ስላላቸው በሚፈጥሩት ስራቸውም ታማኝ ሆነው መዝለቅ ይቻላቸዋል፡፡ ያ የጀመሩት ስራም አርአያ ባደረጓቸው ሰዎች ዘንድ እንደችቦ ደምቆ ስለሚታይ መምህራን የስራ ፈጠራን ግብዓት ለማህበረሰቡ ያበረክታሉ፡፡ እኔ ካስተማሩኝ መምህራን ግን ስራ መፍጠራቸው የሚታወሰኝ አንድ ወይንም ሁለት ብቻ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡
መምህራን አለቃ ከሚበዛባቸው ራሳቸው በጀመሩት ስራ ገፍተውበት የመንግስቱን ስራ በመተው የራሳቸው አለቆች ሆነው ሃላፊነትን በመውሰድ ሌሎች የፈሩትን የስራ መስክ የስራ እድል መፍጠሪያ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ በእርግጥ የመምህር መፈናቀል የሚያመጣው ማህበረሰባዊ ጉዳት ይኖራል፡፡
እውነት አንት አስተማሪ አሸቦ ንግድ ሄደሃላ!
በአንድ ወቅት አንዲት እናት ስለታቸው አልሰምር ብሏቸው በአጥቢያቸው የነበረችውን ታቦት ‹‹እውነት አንቺ የኮረብታ ላይ ታቦት አሸቦ ንግድ ሄደሻላ!›› እያሉ ሲያማርሩ ሰምቻቸዋለሁ፡፡ እኝሁ እናት አሁን አስተማሪው ራሱ የፈጠረውን ስራ እየሰራ የማስተማሩን ስራ ዘንግቶት ቢያዩና በዚሁ አስተማሪ ሰበብ ልጃቸው በትምህርቱ ባይሳካለት ‹‹እውነት አንት አስተማሪ አሸቦ ንግድ ሄደሃላ!›› ይሉት ይመስለኛል፡፡ አዎን አስተማሪው ‹አሸቦ ንግድ› ሄዷል፡፡ ‹አሸቦ ንግዱ› ግን ልቡን እንዳይሰውረው ቢጠነቀቅ አይከፋም፡፡  

ለዚህ ጽሁፍ ሲባል አጂፕ በተባለው ሰፈር አካባቢ ከከተማው መምህራን ያልሆኑ ነጋዴዎች ጋር ባደረኩት ቃለምልልስ የሚከተለውን አስተያየት አግኝቻለሁ፡፡ ‹‹መምህራን ወደ ንግድ ቢገቡ ጥሩ ነው፡፡ በተፈጥሯቸው የገንዘብ አያያዝ ስለሚችሉ፤ ጠንካራ ናቸው፤ ሰውን መቅረጽ ይችላሉ፡፡ ክላስ ውስጥ ብዙ በመቆም ጽናት አላቸው፡፡ የትምህርት ጥራትን አስመልክቶ ግን ልባቸው ሌላ ቦታ ስለሚሆን ተማሪን ይበድላሉ፡፡ መምህርነትን ብቻ እሰራለሁ የሚል በስራው ላይ ቢቀር ጥሩ ነው፡፡ ተማሪውን አብቃው እንጂ መጣል የለብህም ይባላል ከታች ተበላሽቶ የመጣውን ተማሪ፡፡ ለመምህሩ ንግዱ እንዳሰበው ላይሆን ይችላል፡፡ በደንብ ከተከታተለና አዋጭነቱን ካየ ግን አይከስርም፡፡ የመንግስት ስራ መስራትና በግል መስራት ርቀቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው፡፡ በተበላበት ሰዓት መጣንና ነው እንጂ ንግድማ ከመንግስት ስራችን ጋር አይነጻጸርም፡፡ ዲፕሎማም ዲግሪያችንም እሳጥን ተቀምጧል፡፡ እሚገዛ ቢኖር እሸጠው ነበር፡፡››
‹‹አንድን ተጨማሪ ስራ የሚሰራ ሰው ይህ ሰው ለራሱና ለሐገር ሁነኛ ፋይዳ ያለው ሥራ ነው የፈጠረው? ወይንስ ገቢውን ብቻ ነው ያሳደገው?›› ትሉት ይሆናል፡፡ በእርግጥ ‹‹ሥራ ፈጣሪ ማነው?›› የሚለው አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ ከማስተማር ስው ጎን ለጎን ሌላ ስራ የሚሰራን ሰው ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስራ ፈጣሪ እንበለው፡፡
በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ስራ ፈጣሪ ቢኖር በዚያ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖረውን ለውጥ መገመት ይቻላል፡፡ ያ አንድ ሰው እንዲኖር ግን ሦስቱ የስኬታማ ሰዎች ችሎታዎች ማለትም የተነሳሽነት፣ የማቀድና የመፈጸም ችሎታዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ማቀድ ሲባል ግልጽ ዓላማ መቅረጽን፣ በቂ መረጃ ማሰባሰብንና ስልታዊ እቅድና ክትትል ማዳበርን ይይዛል፡፡ መፈጸም በበኩሉ የታቀደው መሬት ላይ መውረዱን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ የግል ነጻነትና በራስ መተማመንን ማሳደግ ወደ ስራ የገባው ስራ ፈጣሪ ቀጣይ የቤት ስራዎች ይሆናሉ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ካነጋገርኳቸው መምህራን ስራ ፈጣሪዎች ያገኘሁትን ሃሳብ አስፍሬያለሁ፡፡ ተጠይቀው የነበሩት ጥያቄዎች እንዴት ወደዚህ ስራ ሊገቡ ቻሉ፣ የስራው ጠንካራና ደካማ ጎኖቹ ምንድን ናቸው እና ለሌሎች መምህራን ምን ይመክራሉ የሚሉ ነበሩ፡፡ በጽሁፍም በቃልም መረጃውን የሰጡኝ አሉ፡፡ በነገራችን ላይ ለቃለ-መጠይቅ በተለያየ ምክንያት ያልተባበሩኝ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ልምዳቸው ይጠቅም የነበረ መምህራን እንዳሉ ከመናገር ወደኋላ ማለት የለብኝም፡፡ ስራቸውን ለቀው በንግድ አለም ጭልጥ ብለው የጠፉ ከበርቴ መምህራንንም ተጠቁሜ ሞክሬ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ለምን እንደሆነ ባላውቅም ሊያናግሩኝ አልፈለጉም፡፡ ያነጋገሩኝን ግን እያመሰገንኩ ሃሳባቸውን ተጠቅማችሁ ስራ እንድትፈጥሩ በማሳሰብ ወደንባቡ በአክብሮት እጋብዛችኋለሁ፡፡
1. አቤኔዘር ወንድወሰን
ጠባሴ፣ እቴነሽ ሆቴል ፊትለፊት ያለ ህንጻ ላይ የመዝናኛ አገልግሎት የሚሰጥ
ስሜ አቤኔዘር ወንድወሰን ይባላል፡፡ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት በማገልገል ላይ እገኛሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባለኝ ትርፍ ሰዓት የግሌን ቢዝነስ የምሰራበትን አጋጣሚ ፈጥሬያለሁ፡፡ የተሰማራሁበት የግል ቢዝነስ የመዝናኛ አልግሎቶችን ማለትም የፑል፣ ፕሌይስቴሽን፣ ቴኒስ፣ ቼዝ ወዘተ በህብረተሰቡ መስጠት ነው፡፡
ይህንን የግል ስራ ከጀመርኩ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡ ወደዚህ ስራ እንድገባ የገፋፋኝ ዋነኛ ምክንያት መምህር ሆኖ በመቆየት የራሴን ህይወት በተለይም የኢኮኖሚ ጥያቄዬን መመለስ እንደማልችል ስለገባኝ ነው፡፡ ማህበረሰቡ ለዩኒቨርሲቲ መምህር ያለው ትልቅ አመለካከት እና በተጨባጭ መምህሩ ከመንግስት የሚያገኘው የገቢ መጠን አለመጣጣም ሌላኛው ምክንያቴ ነው፡፡ መምህር በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊውና በፖለቲካው ላይ ያለው ተሳትፎ ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ላይ መሆን አለበት የሚል የራሴ አስተሳሰብ አለኝ፡፡ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት መምህሩ እነዚህን ነገሮች መፍጠር የሚችልበት አጋጣሚ በዩኒቨርሲቲው አመራርም ሆነ በመንግስት ጭምር አልተፈጠረም፡፡ ስለዚህም በራሴ መንገድ እነዚህን ነገሮች ለማምጣት ስል ያደረኩት ውሳኔ ነው፡፡
ሌላኛው ምክንያቴ ዋረን ቡፌት እንደሚለው በአንድ የገቢ ምንጭ ላይ የሙጥኝ ብዬ መቀመጥ ስለማልፈልግ፡፡ በዚህ ረገድ ከልጅነቴ ጀምሮ የራሴ የሆነ የማስተዳድረው ትልቅ ድርጅት ኖሮኝ የኑሮ ደረጃዬን ማሻሻልና ወደ ትልቅ ደረጃ የማድረስ ጉጉት ነበረኝ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምሰራው ስራ አዲስ የስራ ዕድል በመፍጠር ለማህበረሰቡ አስተዋጽኦ ለማድረግ ስለምፈልግ ይሆናል፡፡
እንደ መምህር ይህንን ስራ ስጀምር ብዙ አስቤበትና የአዋጭነት ጥናት አድርጌ ነው፡፡ ነገር ግን ስራውን ስጀምረው ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ አልሆነልኝም ነበር፡፡ ከችግሮቹ መካከል የገንዘብ እጥረት፣ የሰራተኛ ማጣት፣ ስራውን ለመጀመር ተገቢ ቦታ አለማግኘት ወዘተ ነበሩ፡፡ ሁሉንም ነገር ግን ተጋፈጥኩት፤ ፈተናዎች ቢበዙም ሁሉንም ተራ በተራ ተወጥቼዋለሁኝ ለማለት እችላለሁ፡፡
የዚህን የመዝናኛ አገልግሎት ስጀምር ዋነኛ ደንበኛ ይሆናሉ ብዬ ያሰብኳቸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ነበሩ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በደብረብርሃን ከተማ ላይ ለመዝናኛ የሚሆን ብዙም አጋጣሚዎች አለመፈጠራቸው ነው፡፡
ቢዝነሱን ከጀመሩኩ በኋላ ብዙ መልካም አጋጣሚዎች ተፈጥረውልኛል፡፡ ለምሳሌ ከፑል ቤት አጠገብ የተከፈተው ምግብ ቤት በመጠኑም ቢሆን የደንበኛውን ፍሰት ጨምሮታል፡፡
ሌላው እንደመልካም አጋጣሚ የሆነልኝ ነገር ፑል ቤቱ የሚገኝበት ቦታ ነው፡፡ አብዛኛው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ ፑል ቤቱ መከፈቱ ዘላቂነት ያለው ገቢ ለማግኘት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል፡፡
ባጠቃላይ እንደ መምህር፣ ከመንግስት ስራ ሰዓት ውጪ ያለንን ትርፍ ሰዓት ሌላ ገቢ የማግኛ መንገዶችን በማጥናት ጊዜያችንን ብንጠቀመው መልካም ነው እላለሁኝ፡፡
10/10/2008 ፣  አመሰግናለሁ     
2. መምህር ጀማል (jemalchemistry@gmail.com)
ጠባሴ፣ ሐበሻ ቁርጥ ቤት ጎን ያለ ቡቲክ
ስራውን የጀመርኩት ባለቤቴ የተቀጠረችበትን ስራ ለቃ ስለነበር መንፈሷን ለማደስ ከቤት እንድትወጣ በማሰብ ነው፡፡ ከስራ ሰዓት ውጪና ቅዳሜና እሁድ ያለኝን የእረፍት ጊዜ በፑልና በአሉባልታ አሳልፍ ስለነበረ እየተጋገዝን እንድንሰራ ብዬ ነው ቤቱን የከፈትኩት፡፡ ስራው ገንዘብ በሚያስፈልግህ ጊዜ እንዳትቸገር፣ ብትታመም የሰው እጅ እንዳታይና የተሻለ ኑሮ እንድትኖር ያደርግሃል፡፡
ደንበኞችህ የቢዝነስ ሀሳብ ያፈልቁልሃል፤ እንዴት እንደምትሰራ ይነግሩሃል፡፡ አዲስ አበባ ያሉ እቃ የማመጣባቸው ደንበኞቼ የስራን አቅጣጫ ጠቁመውኛል፡፡ ተጠቃሚው ማነው የሚለውን ለይቻለሁ፡፡ በትእዛዝ አመጣለሁ፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ናዝሬት ጨርቅ ተሸክመን ወስደን እናሰፋ ነበር፡፡ አሁን ግን እዚሁ እንዲሰፋ እያደረግን ነው፡፡ የስፌት ሙያውንና አስፈላጊውን ማሽን አግኝተናል፡፡ ስራው ከሰው ጋር ያገናኝሃል፡፡ ግልጽ ሆነህ ስለምትሸጠው ነገር ከነችግሩ ያለውን መረጃ የምትነግር ከሆነ ደንበኛ ይወድሃል፡፡ ደንበኛ ለመያዝ ባመጣህበትም ልትሸጥ ትችላለህ፡፡ ሌላ ንግድ ላላዋጣው ጓደኛዬ የወንዱን ጨርቅ አሳልፌ ሰጠሁትና እኔ በሴቶች ልብስ ላይ ብቻ እሰራ ጀመር፡፡ ጓደኛዬም የስራ ማሻሻያ አደረገ፡፡ ለትርፍ ጊዜ ሰራተኛና ለዘበኛ የስራ እድል ፈጥረናል፡፡ ስራችን የገጠመው ፈተና የገንዘብ እጥረት፣ የብድር አለመመቻቸት፣ የልምድና የስልጠና ችግር፣ የኪራይ መወደድ፣ ለመንግስት የምንከፍለው የበረንዳ ግብርና የዘበኛ ደምወዝ መኖራቸው ናቸው፡፡ ለሌሎች መምህራን የምላቸው ተጨማሪ ገቢ ያስፈልጋችኋል፡፡ የሰው ሃይል ስለሚኖራችሁ ወይንም መቅጠር ስለምትችሉ ብትሰሩ፤ ቢቻል በሙያችሁ ብትሰማሩ ጥሩ ነው ብዬ እመክራለሁ፡፡››
3. መምህር ቴዎድሮስ እሸቴ
ቴዎድሮስ እሸቴ እባላለሁ፡፡ በደብረብህርሃን ዩኒቨርሲቲ መምህር ስሆን በትርፍ ጊዜዬ ደግሞ ዘመናዊ የወንዶች የውበት ሳሎን ከፍቼ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡ የድርጅቱ ስም ዴዝዴሞና የውበት ሳሎን ሲሆን አድራሻው ጠባሴ፣ ይስሃቅ ካፌና ሬስቶራንት ፊትለፊት ነው፡፡ ይህንን ሥራ ለመሥራት ያነሣሣኝ ዋናው ምክንያት
1.      ጠባሴ ላይ ምንም ዓይነት ዘመናዊ የወንዶች የውበት ሳሎን ስለሌለ ተጠቃሚው ህብረተሰብ ከተማ ድረስ የሚሄድበትን ድካም ለመቀነስ
2.     ትርፍ ጊዜዬን በስራ ለማሳለፍና ራሴም የኢኮኖሚ አቅሜን ለማዳበር
3.     የአካባቢው ህብረተሰብ የምንሰጣቸውን ዘመናዊ የውበት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ
የምንሰጣቸው አገልግሎቶች
በተለያየ ዓይነት የፀጉር ስታይል መስራት፣ የፊት ትሪትመንት፣ ለፀጉር በሚስማማ ቅባት ጸጉር መፈረዝ፣ ቀለም መቀባት፣ የፊትና የጸጉር ስቲም፣ የሳሳ ጸጉር ማከምናቸው፡፡ ለጤንነትዎ ዘመናዊ ስትራላይር ዋስትና ነው፡፡

ቦታው ደባቃ ቢሆንም ሰው ይመጣል፡፡ ነገን በማሰብ ተቀምጠን መስራታችን አንድ ጥንካሬያችን ነው፡፡
ደካማ ጎኑ በግልጽ የማይታይ ቦታ መሆኑ ነው፡፡ ህብረተሰቡ ጸጉር መቆረጥ እንጂ ዘመናዊ አገልግሎቶችን አለመልመዱም ሌላው ችግር ነው፡፡ ለሌሎች መምህራን የራሳቸውን የስራ እቅድ ነድፈው ቢቻል በሙያቸው ቢሰሩ ብዬ እመክራለሁ፡፡ ህብረተሰቡን ማገልገል አለብን፡፡ ተግባራዊ ሊደረግ አይችልም ብለን ከመቀመጥ ነገሮችን ለማየት አቅም ስላለን ቢያንስ ሌላ ቦታ ያለውን አስመስለን ብንሰራ፡፡ ከተለያየ ቦታ መምጣታችን አንድ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ከ4ና 5 በላይ ክፍለጊዜ በቀን የሚያስተምር መምህር ስለሌለ ጊዜ አለን፡፡ ይህ እቃ ወይንም አገልግሎት ደብረብርሃን ላይ የለም ከምንል እኛ ብንጀምረው ጥሩ ነው፡፡

4. መምህር ግራኝ ከድር
(ደብረኤባ ንግድ ባንክ ጎን በስተቀኝ ያለው ህንጻ መሬት ላይ ወይም ቃለአብ ወርቅ ቤት ፊት ለፊት ያለ የሞባይል መሸጫ)
እኚህ መምህር ከዚህ በፊት የሶፋ መሸጫ ሱቅ ነበራቸው፡፡
‹‹ካስተማርኩ በኋላ ያለውን ጊዜ አልጠቀምበትም ነበር፡፡ ፑል፣ ቴኒስ፣ ኳስ ቤት ነበር የማሳልፈው፡፡ አሁን መጥፎ ነገር የማስብበትና የማደርግበት ጊዜ የለኝም፡፡ በመስተማር ስራዬ ረገድ መዘጋጀት ያለብኝን እዘጋጃለሁ፤ መስራት ያለብኝን እሰራለሁ፡፡ የስራው ጥንካሬ አሁን አሁን ስራው ገቢ እያመጣልን መሆኑ ነው፡፡ እቁብም እንገባለን፡፡ ድክመቱ ደግሞ ህጋዊ ሆነህ ለመስራት ስትነሳ የገቢዎች አሰራር በጣም አሰልቺ ነው፡፡ ከመክፈቴ በፊ ፈቃድ ላወጣ ስል መታወቂያ፣ ኪራይ ውል እያሉ አስቸገሩኝ፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ ደግሞ ቁጥጥር የሚደረግበት መንገድ ቢኖር መልካም ነበር፡፡ ወይንም ኮንቴነር ቤት ብናገኝ መልካም ነበር፡፡ በአምስት ዓመት ውስጥ የኤሌክትሪክ ሱቅ፣ በረጅም ጊዜ ደግሞ ሙያውም ስላለኝ ሜንቴናንስና ሌላውንም ተያያዥ ነገር የማስተምርበት ኮሌጅ ለማድረግ እሻለሁ፡፡
ለመምህራን ኑ ከኔ ጎን ቁሙ ነው የምላቸው፡፡ እዚህ ካለው ሰው ጎን ቢቆሙ ጥሩ ነው፡፡ ‹‹መንቀሳቀሻ አነሰን›› ይላሉ፤ ዩኒቨርሲቲያችንም ከሌሎች የንግድ አካላት ጋር አገናኝቶን ስራ ብንጀምር ጥሩ ነው፡፡ እኔ ደምወዝ ወጣ አልወጣ አልቸገርም፤ ይህ ስራም ከሙያዬ ጋር ይገናኛል፡፡ ሌሎች መምህራን ኢንተርፕራይዝ ሆነው በማህበር ቢደራጁ ጥሩ ነው፡፡ በሂደት ጥሩ ነገር ይመጣል፡፡ መንግስትም ማማረር ሲቀንስና መምህሩ ካልቸገረው ስለማይነጫነጭ ስለፖለቲካ ስለማያስብ የፖለቲካ ትርፍ ያገኛል፡፡››
5. መምህር አቡበከር ሰይድ
(ደብረኤባ ንግድ ባንክ ጎን በስተቀኝ ያለው ህንጻ መሬት ላይ ወይም ቃለአብ ወርቅ ቤት ፊት ለፊት ያለ የሞባይል መሸጫ)
‹‹ስማር ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ ቤተሰቦቼ ነጋዴዎች ስለነበሩ የመነገድ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ቤት ለመስራት፣ እቃ ለመግዛትና ባጠቃላይ ኑሮን ለማሻሻል በመንግስት ስራ ያልቻልኩትን አሁን ችያለሁ፡፡ አምሮኝ የሚቀር ነገር የለም፡፡ የፊዚክስ ተማሪዎቻችንን ስለሞባይል ሃርድና ሶፍት ዌር ጥገና በነጻ አሰልጥነናል፡፡ ይህ የምንሰራው ተጨማሪ ስራ ፍሬ ነው፡፡ የሚቀጠሩበት ስራ ቢያጡ ይህን ሰርተው እንዲኖሩ አስበን ነው፡፡ ለህብረተሰቡ ኦሪጅናል ነገር እናቀርባለን፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንሸጣለን፤ በታማኝነት እናገለግላለን፡፡ ይህ ደግሞ የትምህርታችን ውጤት ነው፡፡ መምህራን ያልሆኑት ግን ኦሪጅናል ያልሆነ ሃይኮፒ 3000 ብር ይሸጣሉ ከመሸጫው 1000 ብር ጨምረው፡፡ ስራውን ካለማመድነው ደግሞ ሰራተኛ ተቀጥሮ ይስራዋል፡፡ እኛ መስራታችን ግን ተጨማሪ እውቀት እንድንይዝ ያደርገናል፡፡ ጉዳቱ ቨርቲካል የሆነ መንገድ እንዳትሄድ ይገታሃል፣ ለምሳሌ ትምህርትህን እንዳትቀጥል፡፡ ለሌሎች መምህራን የምመክረው ቢኖር ልብስ መልበስ ፈልገን፣ ስጋ መብላት አምሮን ሳናገኘው መቅረት የለብንም፤ ያልተሰሩ ስራዎችን በተጨማሪ ቢሰሩ የፍላጎታቸውን ያሟላሉ፡፡
መንግስትም ቢሆን ነጋዴዎች እንደሚያማርጡ፣ መንግስት ሰራተኞች ግን መሰረታዊ ፍላጎታቸውን እንኳን ማሟላት እንደማይችሉ ያውቃል፡፡ መምህራን ባሉበት ስራ የሚያገኙት ገቢ ለመኖር አይበቃቸውም፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ስራ መፍጠር ግድ ይላቸዋል፡፡››  
6. መምህር ገዙ ፈለቀ
ከመንዲዳ ቅቤ ቤት ጎን ያለው ህንጻ ላይ ምድር ቤት ግራውንድ ቢ2 ያለ ቡቲክ ባለቤት ነው
ስራን ለምን ጀመርከው? - ለባለቤቴ ስራ ለመፍጠር ነው፡፡ አንድ ዓመት ተኩል ሰራሁ፡፡
ጠንካራ ጎኑ ምንድነው? - ከገንዘብ ጋር ያውልሃል፡፡ ገንዘብ አታጣም፡፡ ከሌላ ቢዝነስ የተሻለ ነው፡
ድክመቱስ? - ግብር ዋነኛ እንቅፋት ነው፡፡ ቦታውም አንድ ችግር ነው፡፡
ለሌሎች መምህራን የምትመክረውስ? - ቢገቡ ጥሩ ነው፡፡ የስራ ጊዜያቸውን በማይሻማ መልኩ፡፡ ሰው መቅጠር ከቻሉም ጥሩ ነው፡፡ እኔ ይህን ስራ ስላየሁት ፒኤች ዲ አልሰራም፡፡ በህይወቴ ላይ ልዩነት ስለማያመጣ አልፈልገውም፡፡ ጭማሪዋንም እንደሆነ እዚህ ቁጭ ብዬ አገኛታለሁ፡፡ መማሬ ከአገሬ በላይ እኔን ይጎዳል፡፡ ፕሮጀክት ለማፈላለግ የልምድ እጦት መኖሩ መምህሩን ይጎዳዋል፡፡ ይህ መምህሩን ሌሎች ሊሰሩ ወደሚገባው ስራ ውስጥ ገፋው፡፡ መምህር ወደ ንግድ መግባቱ ሃገራዊ እንቅፋት አለው፡፡ ሙሉ አቅሙን አሟጦ እንዳይመራመር እና እንዳያስተምር ያደርገዋል፡፡›› 
7. መምህር ተስፋዬ ለገሰ
ጠባሴ፣ ሐበሻ ቁርጥ ቤት ጎን ያለ የቤት እቃዎች መሸጫ መደብር
በገንዘብ ራስን ለማጎልበት ጊዜና ገንዘብ ካለህ ትርፍ ስራ ብትጀምር  አይከፋም፡፡ በሙያችን የምንሰራበት ደሞዝ ለማግኘት እንጂ በፍላጎታችን ገብተንበት አይደለም፡፡ አሁን ሰፊ ሙያ አለ - በዚህ ዘመን- እድሉም አለ፡፡ በእኛ ጊዜ ግን አልነበረም፡፡
መነገዱ ያለህን ተሰጥኦና ችሎታ ለማውጣት ይረዳሃል፡፡
ጥንካሬው ለመግባት ከባድ አለመሆኑ ነው፡፡ ደብረብርሃን ደግሞ ለአዲስ አበባ ሩቅ አይደለም ለመንቀሳቀስ፡፡ ባለችህ ክፍት ሰዓት መስራት ትችላለህ፡፡ ሙሉ አቅምህን ለስራው ለማዋል ትችላለህ፡፡
ለሌሎች መምህራን የምመክረው አቅምና ዝንባሌያቸውን መሰረት አድርገው ትርፍ ጊዜያቸውን ቢጠቀሙ ጥሩ ነው፡፡ ተሰጥኦአቸውን ይፈልጉት፡፡ ያላቸውን አቅምና ጊዜ ወደ ገንዘብ መለወጥ ይኖርባቸዋል፡፡
8. መምህርት ኑሪያ ሁሴን -
በናዝሬት ልብስ የሚነግዱ
ለምን ጀመሩት ካልከኝ ኑሮዬን ለመደጎም ነው፡፡ ጠንካራ ጎኑ ዓላማዬን ለማሳካት ጠቅሞኛል፡፡ በፊት ሳልጀምረው ብድር እበደርና እቸገር ነበር፤ የልጆች የትምርት ቤት ለመክፈል እንኳን እቸጋገር ነበር፡፡ ስራው እንደተፈለገው እንዳይሰራ ቤት ለመከራየት ገንዘብ ማስፈለጉ ነው፡፡ የግብር ጫና ሌላ መሰናክል ነው፡፡ የገጠመኝ ችግር በዱቤ የማበድራቸው ገንዘቡን ለመክፈል ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት ማቆየታቸው ነው፡፡ ለሌላ መምህር የምትመክሪው ላልከኝ በደምወዝ መኖር ማለት ከግራም ለቀኝም በገደል የተከበበች ቀጭን መንገድ ይዘህ መሄድ ማለት ነው፤ የጭንቀት ኑሮ ነው፡፡ ንግዱ የትምህርት ስራን አይጎዳም፤ የምንሰራው ግማሽ ቀን በፈረቃ ስለሆነ፡፡ ስለዚህ ወደ ንግድ እንዲገቡ አጥብቄ እመክራለሁ፡፡
9. መምህር መላኩ ንጉስ
(ደብረኤባ ንግድ ባንክ ጎን በስተቀኝ ያለው ህንጻ መሬት ላይ ወይም ቃለአብ ወርቅ ቤት ፊት ለፊት ያለ የኤሌክትሮኒክስ ጥገና)
ችሎታው ስላለኝና ስራው ተግባራዊ እውቀት የሚፈልግ ስለሆነ እውቀቴን ለማስፋፋት ነው የጀመርኩት፡፡ ኤሌክትሮኒክስ የፊዚክስ ተግባራዊው ክፍሉ ነው፡፡ ጥንካሬው ለአዲስ አበባ ያለን ቅርበት እቃዎችን በግማሽ ቀን ማድረስ ማስቻሉ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መስራቴ ለአዳዳስ ሃሳብ ምንጭነት የኢንተርኔቱ  መኖር ይጠቅመኛል፡፡
ከፈተናዎቼ አንዱ ደግሞ የእውቀት ውሱንነት ነው፡፡ ለምሳሌ የሞባይል ሶፍትዌሮች አቅርቦት ችግር ስላለ ክራክ አድርጌ ለማውረድ ኮኔክሽን ደካማ ነው፡፡ ወደፊት ከውጭ አገር የሚያስመጡትን ማነጋገር ይኖርብኛል፡፡
ሌሎች መምህራንን በተመለከተ የተማርኩት ምንድነው ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እኔ በበኩሌ ስማርም የተማርኩትን ትምህርት በደንብ ለማየት እፈልግ ነበር፡፡ ከንድፈ ሃሳብ ወደ ተግባር ለመለወጥ እሻ ነበር፡፡ ተግባራዊ ለመደረግ የማይችል ትምህርት የለም፡፡ እኔ የምፈልገው ገንዘብ ሳይሆን ፈተናውን ነው፡፡ ይህን እንደላቦራቶሪዬ ነው የምቆጥረው፡፡ ወደፊት የሙያተኞች ቡድን ሆነንም ልንሰራ እንችል ይሆናል፡፡
10. መምህራን ማቲዎስ አቢና መለሰ አበበ
(የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብረብርሃን ቅርንጫፍ አጠገብ ጭማቂ ቤት ከፍተው የነበሩ)
‹‹ተቀጥረን ከምናገኘው በላይ ገቢ ልናገኝ ይገባናል ብለን ስላሰብን ስራውን ጀመርነው፡፡ ጥንካሬው በአነስተኛ ካፒታል መጀመር መቻሉ ሲሆን ድፍረትንም አምጥቶልናል፡፡ ተጨማሪ ስራ እየሰራሁ ነው ብሎ ማሰቡ ጥያቄ ይፈጥርብሃል፡፡ ጊዜዬን እየተጠቀምኩ ነው የሚል ስሜት አለ፡፡ በበቂ ሁኔታ የተያዘ ቢዝነስ ነበር፡፡ ተጠቃሚ ነበርን፡፡ የፍራፍሬ አጠቃቀም ደካማ የነበረበት ቦታ ስለነበር ክፍተቱን ሞልተናል፡፡
የስራውን ድክመት በተመለከተ ቦታው መዳረሻ ሳይሆን መሃል ላይ መሆኑ ጎድቶናል፡፡ ሌላው ድክመት ደግሞ የሰው ሃይል ችግር ነው፡፡ ጠዋት በሰዓቱ ለማድረስ አልቻሉም፡፡ ሰራተኞች ሁለት ዙር ቀያይረናል፡፡ መሻሻል አለመኖሩ እንድንዘጋ አደረገን፡፡ የመቆጣጠር ችግር አልነበረብንም፡፡ ሰራተኞቹ ግን እንደጠበቅነው አልሆኑልንም፡፡ ስንጀምር ወቅቱ ክረምትም ስለነበር ለስድስት ወራት ያህል እኛ በንቃት ሰርተናል ፡፡ በኋላ ላይ መቀዛቀዝ መጣና ክፍተቶች ተፈጠሩ፡፡ ኢንተርፕረነርሽፕ ማለት ሙያህን መሸጥ ነው፡፡ ገንዘብ ደግሞ የመኖር አቅም ነው፡፡ ራዕይህን እየሞከርክ ከሆነ ኢንተርፕረነር ነህ፡፡
አስተማሪ መሆናችንን በተመለከተ ክፍተት አይተን መግባታችን ራሱ የኛን ሙያ መጠቀማችንን ያሳያል፡፡ ከኛ በኋላ አሁን ብዙ ጭማቂ ቤት ከተማው ላይ ተከፍቷል፡፡ ህዝቡ ፍራፍሬ ማግኘት እንደቻለና ባህሉ ላይ ለውጥ ማምጣት እንደጀመርን ገብቶናል፡፡ ሃሳቡ ሳይሆን የወደቀው የቦታ፣ የጊዜና የሰራተኛ ችግር ነው፡፡ ሌላ ሰው የተሻለ ሊሰራው ይችላል፡፡ ሳንጀምር ሰርተነው የነበረው ጥናት (SWOT ANALYSIS= STRENGTH, WEAKNESS, OPPORTUNITIES AND THREAT) ላይ ያላሰብነው ችግር አጋጥሞናል፡፡ ፍሬሽ ምርትና መጠጥ በማቅረብና ደንበኛ አያያዝን ለማሻሻል በማሰብ ገብተናል፡፡ ትስስሮች ለመፍጠርና ግብር ባተረፍነው ልክ ለመክፈል አስበን ነበር፡፡ ነጋዴዎች ግብር እንዲቀነስላችሁ አቤቱታ አቅርቡ ሲሉን እኛ አላደረግንም፡፡ መክፈል ያለብንን በደስተኝነት ከፍለናል፡፡  
ለሌላው መምህር የምንመክረው ለስራ እንዳለው ስሜት ይወሰናል፡፡ እኛ ገንዘብን ብቻ ብናስብ ሌላ ቦታ ላይ ታገኘን ነበር፡፡ ከማስተማር ሌላ ጥሩ ክፍያ ያለው ስራ ላይ እንገባ ነበር፡፡ ያንተን ተሳትፎ የሚፈልግ ስራ ከሆነ አያስፈልግም፡፡ ጊዜህን ይወስዳል፡፡ ሁኔታዎች ይወስኑታል፡፡ ስለትርፍ ጊዜ ስራ ፖሊሲ ቢኖርም የስራው ባህሪ ይወስነዋል፡፡ ራስን መቅጠር (የተሻለ ቁጥጥር ለማድረግ ያስችልሃል) ወይስ የሌሎችን ጊዜ መግዛት አለብኝ ብለህ ወደስራው መግባት አለብህ፡፡››  
11. የህጻናት ማቆያ የጀመሩ መምህር
ደህንነቱንና ደረጃውን የጠበቀውንና ህጻናት ሳይሰለቹ እንዲውሉ ማድረግ የሚችለውን የህጻናት መዋያቸውን የጀመሩት አስፈላጊውን ሁሉ አሟልተውና በሌላ አገር ስላለው ሳይንሳዊ አሰራር ከኢንተርኔት በቂ መረጃ አሳባስበው እንደሆነ አጫውተውኛል፡፡ በሶሲዮሎጂ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሲማሩ እንደአስተማሪ በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚያዩዋቸውን ድክመቶች ለማረም የሚጠቅሙ የትምህርት ዓይነቶችን መርጠዋል፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ መወደዱ ፈታኝ ቢሆንም በጀመሩት ስራ አይበሳጩም፤ አይጸጸቱም፡፡
በተመጣጣኝ ዋጋ የጀመሩት የህጻናት ማዋያ ወላጆች የቤት ሰራተኛ እንዲኖራቸው ሳይገደዱ ስራቸውን በነጻነት እንዲሰሩ ያስችላል፡፡ ከመምህርነት ማንነታቸው ጋር የተቀራረበ ስራ ይሰራሉ፡፡
‹‹ቀደም ባለው ጊዜ የግል ስራ መስራት አይበረታታም ነበር፡፡ አሁን ፖሊሲውም ስለሚፈቅድ የመምህራን አቋም እየተቀየረ ነው፡፡ ከፈለገው የማስተማር ስራው ይቅር ባይ ሆኗል፡፡ በመንግስት ስራ ላይ ተደላድሎ የመቀመጥ ችግር ስራ ፈጠራን የሚጎዳ ልማድ ስለሆነ መቀየር አለበት፡፡ የመምህርነት ስብእና ለመነገድ አይሆንም የሚሉ አሉ፡፡ ይህንን መለወጥ ግን ያስፈልጋል፡፡›› የሚሉትን እኚህን መምህር ትክክለኛ የኢንተርፕረነርነት ስብእና አይቼባቸዋለሁ፡፡  
12. መምህር ለማ ሚደቅሳ
መቀሌ ላይ በሽርክና የሚሰሩበት የቋንቋ ትምህርት ቤት ነበራቸው፡፡ ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ ሲሄዱ ዘግተውታል፡፡ ብዙ ሰዎችን እንደቀየሩበት ነግረውኛል፡፡ ሌሎች የቋንቋ መምህራን ከሚያስተምሩበት በተሻለና በተለየ መንገድ ያስተምሩ ነበር፡፡ ተማሪዎች በተለያየ የትምህርት ዘርፎች ወደዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ መምህራን ክብር ያለው ሞት ለመሞትና ጥሩ ኑሮ ለመኖር ከዚህ የቀን ሰራተኛ ደምወዝ ተከፋይነት መውጣት አለባቸው ይላሉ፡፡



13. አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ መምህር
የዩኒቨርሲቲው ማስተማር ስራ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ አልነበረውም፡፡ ስለሆነም ተጨማሪ ገቢ አስፈለገኝ፡፡ ማስተማሩን ያየን እንደሆነ እርካታ የለውም፡፡ በእኔ ውሳኔ ሳይሆን ከላይ በምታዘዘው በኮታ እንዳሳልፍ ስለሚደረግ (ግን አንድም ቀን በትዕዛዝ አሳልፌላቸው አላውቅም ነበር) እና ሕሊናዬ የማይቀበለው በፈተናም ሆነ በአሳይመንት ላይ የተንሰራፋው ኩረጃ ስራዬን እንድለቅ ካደረጉኝ ምክንያቶች የተወሰኑት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የጀመርኩት ስራ ጥሩ የገቢ ምንጭ ሆኖኛል፡፡ የጊዜ ነጻነት ፈጥሮልኛል፡፡ በስራ እድል ረገድም ሦስት ራሴ ያስተማርኳቸውን ተማሪዎች ቀጥሬያለሁ፡፡ ባለስልጣናት ጎቦኞች መሆናቸው አያሰራህም፡፡ ሰራተኞች ክህሎት ያንሳቸዋል፡፡ ብድር እንደፈለግኸው አይፈቀድልህም፡፡ ለሌሎች መምህራንና በተለይም ለትምህርት አመራሮች የማስተላልፈው መልዕክት መጀመሪያ የትምህርት ጥራት ይታሰብበት፡፡ ወደ ተጨማሪ ስራ ግን ግቡ፡፡ በረፍት ጊዜ ቁጭ ብሎ መዋል ጥሩ አይደለም፡፡ እኔ በሚሊየን የሚቆጠርም ገንዘብ እያለኝ ስራዬን ብለቀው ደምወዜ ይቋረጣል እያልኩ እፈራ ነበር፡፡ ይህን ፍርሃት አስወግዱ፡፡

ማጠቃለያ
ከአንድ አገር ውስጥ ሁለት በመቶ ስራ ፈጣሪ ካለ ያች አገር በእድገትና ብልጽግና ትለመልማለች ይባላል፡፡ የአገሪቱ ጉዳይ ትልቅ ምርምርና ዳሰሳ የሚያሻው ቢሆንም በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ያሉትን መምህራን አስመልክቶ ግን በቅርብ ጊዜ ሁለት በመቶ እና ከዚያም በላይ ስራ ፈጣሪዎች እንደሚኖሩን አልጠራጠርም፡፡ የሚፈጠረው ስራ ደግሞ አብዛኛው የማህበረሰቡ ክፍል ሊሰማራበት የማይችልና የኛን ሙያዎች መሰረት ያደረገ ቢሆን በትክክል ሁለንተናዊ ለውጥ እንደምናስመዘግብ አልጠራጠርም፡፡ ሁልጊዜ የምለው ነገር አለ፡፡ የዚህ ዩኒቨርሲቲ ከሺ በላይ ሰራተኛ በየሙያውና ዝንባሌው ሙሉ አቅሙን አውጥቶ የአካባቢውን ችግሮች እያጤነ ቢሰራ ለዚህ አካባቢ ድህነት ታሪክ በሆነለት!



የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...