ሁቱትሲን ላላነበባችሁ ወዳጆቼ ለቅምሻ ያህል እነሆ፤
ሁለተኛው ዕትም እስኪወጣ።
መግቢያ
ኢማኪዩሌ እባላለሁ
ገዳዮቹ ስሜን ሲጠሩ ሰማኋቸው፡፡
እኔ
በግንቡ በአንደኛው በኩል ስሆን እነሱ ደግሞ በሌላኛው አቅጣጫ ናቸው፤ አንድ ጋት የማይሞላ ውፍረት ያለው ጭቃና ዕንጨት ብቻ ይለያየናል፡፡ ንግግራቸው ጭካኔ የሚንጸባረቅበትና ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
‹‹እዚህ ነች… እዚህ የሆነ ስፍራ እንዳለች እናውቃለን፡፡ …. ፈልጓት - ፈልጓት ኢማኪዩሌን፡፡››
አካባቢው በሁካታ ተሞላ፡፡ ብዙ ገዳዮች መጥተዋል፡፡ በአእምሮዬ ይታዩኛል - ሁልጊዜ በፍቅርና በደግነት ሰላምታ ይሰጡኝ የነበሩ የቀድሞ ወዳጆቼና ጎረቤቶቼ በቤቱ ውስጥ ጦርና ገጀራ ይዘው ስሜን እየጠሩ ይዘዋወራሉ፡፡
‹‹399 በረሮዎችን ገድያለሁ›› ይላል አንደኛው ገዳይ፡፡ ‹‹ኢማኪዩሌ 400 ታደርግልኛለች፡፡ ይህን ያህል ከገደልኩ ምን እፈልጋለሁ!››
በትንሿ ምስጢራዊ መታጠቢያ ቤታችን ጥጋት አንድስ እንኳን የሰውነቴን ክፍል ሳላላውስ ተሸሽጌያለሁ፡፡ እንደኔው ሕይወታቸውን ለማትረፍ እንደተደበቁት ሌሎች ሰባት ሴቶች ሁሉ ገዳዮቹ ስተነፍስ እንዳይሰሙኝ ትንፋሼን ውጫለሁ፡፡
ድምጻቸው የሠራ አከላቴን ገማመሰው፡፡ በከሰል ፍም ላይ እንደተኛሁ፣ እሳትም ላይ እንደተጣልኩ ተሰማኝ፡፡ መላ ሰውነቴ የሕመም ውርጅብኝ ወረደበት፡፡ ሺህ የማይታዩ መርፌዎች ተቸከቸኩብኝ፡፡ ፍርሃት እንደዚህ የሚያርበደብድ ስጋዊ ሥቃይ ያስከትላል ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡
ለመዋጥ ሞከርኩ፤ ጉሮሮዬ ግን ተዘግቷል፡፡ ምራቅ አልነበረኝም፤ አፌም እንደ ኩበት ደርቋል፡፡ ዓይኖቼን ጨፈንኳቸው፤ ራሴንም ለመደበቅ ሞከርኩ፤ ንግግራቸው ግን እየጎላ መጣ፡፡ ምንም ዓይነት ምኅረት እንደማያደርጉልኝ አውቃለሁ፤ በአእምሮዬም አንድ ሐሳብ ያስተጋባ ጀመር - ከያዙኝ ይገድሉኛል፡፡ ከያዙኝ ይገድሉኛል፡፡ ከያዙኝ ይገድሉኛል…
ገዳዮቹ በራፉ ላይ አሉ፤ በማንኛዋም አፍታ እንደሚያገኙኝ አውቃለሁ፡፡ ገጀራው ቆዳዬን አልፎ ሲገባና አጥንቴ ድረስ ሲቆራርጠኝ የሚሰማኝ ስሜት ምን እንደሚመስል አሰብኩት፡፡ ወንድሞቼና ወላጆቼም ትዝ አሉኝ፤ ሞተው ወይንም በሕይወት እየኖሩ እንደሆነ፣ በገነት ከአፍታ በኋላ እንገናኝም እንደሆነ አለምኩ፡፡
እጆቼን እርስ በርሳቸው አጣመርኳቸው፤ የአባቴን መቁጠሪያም ጥብቅ አድርጌ ያዝኩ፤ በለሆሳስም መጸለይ ጀመርኩ - እባክህ እግዚአብሔር ሆይ፣ እባክህ እርዳኝ፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንድሞት አታድርገኝ፣ እንደዚህ አይሁን፡፡ እነዚህ ገዳዮች እንዲያገኙኝ አታድርግ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስህ ከጠየቅን እንደሚሰጠን ትነግረናለህ… እንግዲህ ጌታዬ እየጠየኩህ ነው፡፡ ወይ በለኝ፡፡ እባክህን እነዚህን ገዳዮች ወዲያ እንዲሄዱ አድርጋቸው፡፡ ኧረ በዚህ መታጠቢያ ቤት እንድሞት አታድርገኝ፡፡ እባክህ፣ እግዚአብሔር፣ እባክህ፣ እባክህ፣ እባክህ አድነኝ፡፡
ገዳዮቹ ከቤቱ ወጥተው ሄዱ፡፡ እኛም እንደገና መተንፈስ ጀመርን፡፡ ሄደዋል፤ ሆኖም ግን በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ውስጥ ብዙ ጊዜ ይመላለሳሉ፡፡ ሕይወቴን እግዚአብሔር እንዳተረፋት አምናለሁ፤ ሆኖም ቁምሣጥን በምታክል መታጠቢያ ክፍል ውስጥ ከሰባት ሌሎች ሰዎች ጋር በፍርሃት እየተርበደበድኩ ባሳለፍኳቸው 91 ቀናት መትረፍ ከመዳን በጣም የተለየ አንደሆነ እማራለሁ… ይህ ትምህርትም ለዘለቄታው ለውጦኛል፡፡ ይህ ትምህርት በጅምላ ጭፍጨፋ ውስጥ የሚጠሉና የሚያሳድዱኝን እንዴት መውደድ እንዳለብኝ - ቤተሰቤን ያረዱትንም ሁሉ እንዴት እንደምምር ዕውቀት የቀሰምኩበት ነው፡፡
ስሜ
ኢማኪዩሌ ኢሊባጊዛ ነው፡፡ ይህ በታሪክ ብዙ ሕዝብ ካለቀባቸው ጭፍጨፋዎች በአንዱ እግዚአብሔር እንዴት እንደተገለጠልኝ የሚያሳይ ታሪክ ነው፡፡