2015 ኦገስት 29, ቅዳሜ

ቴሌቪዥን ሳሲት እንዴት እንደገባ




1988 .. የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የአማርኛ አስተማሪያችን፣ ሴት ናቸው፣ የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች የሚባሉት ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን የመሳሰሉት ናቸው የሚል ትምህርት ከመጽሐፉ ያስተምሩናል፡፡ ሬድዮንና ጋዜጣን ቀድሞም ስለምናውቃቸው መምህርታችንን ምንድን ናቸው ብለን አልጠየቅናቸውም ነበር፡፡ ስለ መጽሔት ምንነትም አስረዱን፤ ‹‹እንደጋዜጣ ያለ ነው አሉን›› ተረዳነው፡፡ አነስ ያለ መጽሐፍም ሊሆን ይችላል ብለን ጠረጠርን፡፡
ቴሌቭዥንን እንዴት ያስረዱን! ‹‹እንደ ሬድዮ ያለ ሆኖ ከሬድዮ ልዩነቱ ግን በዜናው ላይ የሚወራውን ነገር ልክ በዕውን እንዳለ አድርጎ የሚያሳይና ዜና አንባቢውን ጨምሮ የሚያሳይ ነው›› ተባልን፡፡ አሁንም አልገባንም፡፡ ‹‹መኪና ቢጋጭም ያሳያል፣ ዛፍም ሆነ ወንዝ፣ ቤትም ሆነ ተራራ ያሳያል›› ብለው አስረዱን፡፡ ይሁን ብለን ቅር እያለን አለፍነው፡፡ በትምህርት ዓለም የተረዳሁት ነገር ቢኖር አንድን እንግዳ ነገር ለማያውቀው ሰው በተለይ ለገጠር ተማሪ ማስረዳት አስቸጋሪ እንደሆነ ነው፡፡ በቃ አስተማሪው/ዋም አላወቁትም የማለት አባዜ ተማሪውን ሲጠናወተው ደቂቃም አይወስድበት፡፡ እኔ ራሴ የዚህ ወረርሽኝ ተጠቂ ነበርኩና ነው እንዲህ ማለቴ፡፡

እነ ኑሮ- ዘዴን፣ እነ እርሻን፣ እነ የመሳሰሉትንና አሁን የረሳኋቸውን ትምህርቶች ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥለን አራተኛን አልፈን አምስተኛ ክፍልን በአዲሱ የትምህርት ስርዓት ባዲስ መንፈስ ጀመርን፤ አለፍነውናም ስድስተኛ ገባን፡፡ ስድስተኛ ክፍልም ሳለሁ፣ 1990 .. መሆኑ ነው፣ እንግሊዝኛ መምህራችን ስለቴሌቪዥን መጠነኛ ማብራሪያ ሰጥተውን ነበር- ያው መጽሐፉ በሆነ መልኩ ስለሱ ስላነሳና እንድናውቀው ስላፈለገ፡፡ ‹‹አይ ዎች ቴሌቪዥን›› የሚል መጽሐፉ ላይ ያለ መሰለኝ፡፡ ልፉ ብሏቸው መምህር፣ እኛ ከሁለት አመትም በኋላ ይህ ነገር አላሳመነንም፣ አልተዋጠልንም፣ አልተገለጠልንም፤ ወይም ቀድሞ ነገር ሃሳቡንም አእምሯችን ውስጥ እንዲገባ አልፈቀድንለትም፡፡ አኔ ብዬ ላውራ መሰለኝ የሌላውን ተማሪ ስለማላውቅ፤ ግን ቢገባቸው ኖሮ በወቅቱ ያስረዱኝ ነበር ብዬ ነው፡፡




ፈረንጅ ሲመጣ እንደዚህ ነበር የሚጎበኘው፡፡

አንድ ቀን የከሰዓት ፈረቃ ሆነን ነው መሰለኝ አዲስ ወሬ መጣ፡፡ የምን ወሬ በሉ ብቻ! ‹‹ቴሌቭዥን ሳሲት ገባ!›› ይሉ ወሬ፡፡
ይህንም የሚያወሩት ልጆች ትናንትናውኑ ‹‹ቴሌቪዥኑን ባይናችን በብረቱ አይተናል፣ ወሬውንም ኮምኩመናል›› ባዮች ናቸው፡፡ ‹‹እኔ ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሰራ የት ነበርኩ?›› ብዬ ራሴን ጠየቅሁ፡፡ ‹‹ወይ እረኝነት፣ ወይ የሆነ ቦታ መልዕክት ተልኬ፣ ወይ የሆነ ቦታ ጨዋታዬን ስጫወት ይሆናል›› አልኩ መሰለኝ፡፡ ወሬውን በደንብ ‹‹እንዴት?›› ብዬ ሳላጣራ መምህር ገቡ መሰለኝ አርፌ ትምህርቴን ቀጠልኩ ወይም ቀጠልሁ፤ የቱ ይሆን ትክክሉ? አንድ ያዲሳባ ልጅ ጓደኛዬ ቢኖር ስቆ ያርምልኝ ነበር፣ ወይ ካዲሳባ ልጅ መራቅ፣ዳንኤል! ሰው ካልሄደና ካልሞተ አይመሰገንም ነው የተባለው? ይሄኔ አንተ ብትኖርልኝ የሰው መሳቂያ አልሆንም ነበር፡፡ ምነው አንድ ቀን እንኳን ‹‹ከተዋበች›› ጋር ሆናችሁ ሁለተኛይኸእንዳትል፤ አዲሳባይሄነው የሚባለው ብላችሁኝ፡፡ ለማንኛውም ባገሬ አማርኛ ላውራ፡፡አገሬ አትበል ብላችሁኝ ነበር ‹‹አገርህ ኢትዮጵያ እንጂ ሳሲት አይደለም፣ ሳሲት የትውልድ መንደርህ ነች! አትጥበብ!›› ያላችሁኝን አልረሳሁትም፤ ሆኖም ግን በቀና እዩልኝ፤ ክፋት አስቤ አይደለም፡፡ ሐገሬ አትዮጵያ መሆኗን ዲቪም እየሞላሁ ቢሆን አልረሳውም፤ ከናንተ ይነጥለኝ፡፡ (በነገራችን ላይ ዲቪ ላለመሙላት ለራሴ ቃል ገብቻለሁ - የናንተን አላውቅም፡፡) ወደ ቴሌቪዥኔ ልመለስ፡፡ ግን ግን በነካ እጄ እንዳዲሳበቦች ስለኢትዮጵያ የሚቆረቆርላት ይኖር ይሆን? ምናልባት ግን የተለያየ ህዝብ ተቀራርቦና አብሮ የመኖሩ ነገር፣ የትምህርትና የንቃተ-ህሊና ነገር ይሆናል ምክንያቱ፡፡ አዲሳበቦች አደንቃችኋለሁ፣ የትም ብሄድ አልረሳችሁም፡፡ ሌላውም እኮ ግን አለመማሩና አንድ ሐይማኖትና ቋንቋ ይዞ ተነጥሎ በመኖሩ ይሆናል እንጂ ክፋት አስቦ አይመስለኝም፡፡

ምን አለፋችሁ ወገኖቼ ወደ ወሬዬ ልመለስ፡፡ የአንደኛው ክፍለ ጊዜ ቲቸር ሲወጡ የሌላው ክፍለ ጊዜ ቲቸር ሲገቡ ለወሬው ጊዜ ጠፋ፡፡ ቁርጥራጭ ወሬዎች ይደርሱኝ ቀጥለዋል፡፡ አስተማሪ ከገቡ ማናባቱ ነው ቃል የሚተነፍሰው? ማንም! መምህር ሲገቡ ከመቀማጫህ ትነሳለህ፣ እንደምን ዋላችሁ ተማሪዎች ይላሉ፣ እንደምን ዋሉ መምህር እንላለን፡፡ (ከሰዓት ላይ ማለት ነው፡፡) መምህር ሲገቡ ከወንበር መነሳትን ለመጀመሪያና ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ ‹‹በኔ ጊዜ ሲሆን ተዉት! ምን ይነት ልማድ ነው ደሞ ይሄን ዓይነቱ!?›› ያሉን የስድስተኛ ክፍል የእንግሊዝኛ መምህራችን ሲሆኑ የእንግሊዝ ባህል አጥቅቷቸው ይሁን የኛ መነሳት አሳዝኗቸው የሚያውቁት አንድዬና እርሳቸው ብቻ ናቸው፡፡ ግምት ነው እንጂ እንግሊዞች መምህር ሲገባ ይነሱ አይነሱ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ወደፊት እዚያ ከተማርኩ ዐይቼ እመጣለሁ፡፡ ዛሬ ግን ወዳጄ፣ ታሪክ ተቀይሯል፡፡ ተማሪ ሆዬያው ሁሉም አይደለም፣ አልፎ አልፎ እንጂ፡፡ አንዳንዱ ታዲያ አለ ትሁት፣ ወረቀት ወይም የሆነ ነገር ሲሰጥህ በሁለት እጁ፣ ተንደርድሮ ማጥፊያህን ተቀብሎ ሰሌዳውንሃጫ በል አስመስሎአጥፍቶ፣ (ምን ይሆን ሃጫ በል? ማስታወቂያ ላይ ነው የሰማሁት- የጥርስ ህክምና ማስታወቂያ ላይ፤ ይኸ እንግሊዝኛ የሚሉ  ቋንቋ እኮ ነው አማርኛን ያስረሳኝ፣ ወይ ገብቶ አይገባ፣ ወይ ወጥቶ አይወጣ! እንትን ቋንቋ እኮ ነው! ያገሩ በሽታ ይሉታል አንድ የስነ-ልሳን ምሁር) ብቻ ጎበዙና አክባሪው ተማሪ ይቅናው በየሄደበት! ሰው ያክብረው፣ አስተማሪም የሆነ እንደሆነም ተማሪ ያክብረው! ቁጭ ብድግ ይበልለት፣ ይለሽለሽለት! ሌላውማ ያው   ፡፡ ልብ ይግዛ፡፡ መርካቶ አይጠፋም የሚገዛ ልብ፣ እዚያ ከሰው ነፍስ ሌላ ሁሉም አለ ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እስከዛሬ ያልገዛውን ልብ ግን ዛሬ ቢገዛው ሰዓቱ ያለፈበት ይመስለኛል፤ አይስማማውም፤ ይሰፋበታል፤ እስኪ ደግሞ ተረኛን ያትክን፡፡ ማነህ ባለ ሳምንት? መቼም ከሳምንት በላይ አይቆይ ከሰው ጋር፡፡ በነገራችን ላይ የኩላሊት ጥቁር ገበያ ደርቷል ይላሉ፤ ጠልፈው ሰዉን ኩላሊቱን ያወጣሉ አሉ፤ ተጠንቀቁ ኋላ! እንኳን ለ10 000 ዶላር ለአንድ መቶ ብርም የሰውን ሕይወት ያጠፋሉ፡፡ ኑሯቸውን ለመደጎም አንድ ኩላሊታቸውን የሚሸጡትን አይመለከትም፡፡

በረፍት ሰአት የቴሌቭዥን ወሬ ደራ፡፡ ደሞ እናንተ ደወል ተደውሎ ነው እንዴ ለወሬው መድራት! ለኔ በዚያን ጊዜ ቴሌቪዥን ማለት ቢያንስ ቤት ይችለዋል ተብሎ የማይታሰብ፣ ወደ አውላላ ሜዳ ላይ ሄዶ ትልቅ ድንኩዋን ተጥሎለት የሚታይ መሆን አለበት፡፡ ካልሆነማ ተራራውን፣ ሸንተረሩንን (የፈረደብሽ ሸንተረር፣ ምኑ እንደሚንሸታረር እሱ ይወቅ … ) ዛፉን፣ ወንዙን እንዴት ሊያሳየን ይችላል? ካልሆነማ ራስ ሳይጠና ጉተና ይሆንበታል ለቴሌቪዥን፡፡/ የቴሌቭዥን መጣን ወሬ ያመጡትን ልጆች ታዲያ ከበን እናዳምጣቸዋለን፡፡ ከወሬያቸው አያያዝ ታዲያ ጭራሹንም የቴሌቭዥን መጣ ወሬያቸውም ውሸት ነው ብዬ ደምድሜ ነበር፡፡ ለምን ብትሉ ቴሌቭዥኗ እቤት ውስጥ ገባች መባሉ ነበር ለኔ ውሸቱ፡፡ እንዴት ገባች ብንላቸው፣ ‹‹አንዱ ወዛደር ታቅፎዋት!›› ጉድ በል ሳሲት ቴሌቪዥን መጣ ጓዳ ሊከተት! ‹‹ሬዲዮ መሰለቻችሁ እንዴ!? ቴሌቭዥን እኮ አገር ሙሉ ታሳያለች›› አልኩዋቸው፡፡ ‹‹ሬዲዮ ወይም ቴፕ ይሆናል ያያችሁት›› ብላቸው ምንስ! ‹‹እኛ ያየነው ነን አንተ ያላየኸው ስለቴሌቭዥን የምታውቀው?›› ብለው አፈጠጡብኝ፡፡ በቃ 2 ዓመታት ያህል ሳስባት የነበረችውን ቴሌቭዥንን ናቅኋት፡፡ እንዲህ አድርጌ አወረደኩዋት ነው እምላችሁ፡፡ ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ፡፡ ‹‹ኧረ አይሆንም፤ መጣች የተባለው በትንሿ የህዝብ ላንድ ሮቨር፤ እቤት ገባች ተባለ - ለዚያውም በእቅፍ - ሕጻን ልጅ መሰለቻቸው እንዴ! ቢያንስ ላገር ምድሩ በከበደ መኪና፣ ሲሆን ሲሆንማ በመለኮታዊ ሐይል መጥቶ ካንዱ ተራራ ጎን ጉብ እንዲል ነው እኔ እምፈልገው፡፡ እኔ እምፈልገው ይሄን ነው! ካለዚያማ እንዴት ተራራን ያሳያል? እንዴት ወንዞች ሲፈሱ ያስጎበኛል? እንዴትስ ዛፍ ያሳያል? እሺ ይሁን በላንድ ሮቨሯ ይምጣ፣ ግድ የለኝም፤ ቢያንስ ቢያንስ ከበር መዝጊያ ማነስ አለበት ምንስ ቢሆን?›› ረፍት አልቆ ገባን፣ ተማርን፣ ወደ ቤታችን ሄድን፡፡ ተለቀቅን ነው የሚባለው እኛ አገር፡፡ ይችን አገርን አለቅም ብያለሁ ጥሎብኝ፡፡ ወይም እናት አገራችንንሐገር›፣ ትውልድ ቀያችንንአገር› እንበል መሰለኝ፡፡ የዕለት ተግባሬ የነበረው በነገራችን ላይ የጠዋት ፈረቃ ከሆንኩ የተገኘውን ቀማምሼ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ፤ ተምሬ እመለሳለሁ፣ ምሳዬን ቤት ያፈራውን በልቼ ወደ ስራ፡፡ ከብት ማገድን የመሳሰለው ስራ ማለት ነው፡፡ ልጅ ነኛ! አይ ሳሲት ዱሮ እኮ ስሟ ምሽግ ነበር አሉ - ጣሊያን መሽጎባት ስለነበረ ነው አሉ፡፡ የከተማ ጸባይ ያዘች በኋላ፡፡ ገበሬ ያልሆነና የማያርስ ሳሲት ላይ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ገጠር ነች ከተማ ታዲያ? ‹‹ሳሲት እገጠሩ ነህ? እከተማው?›› ይላል ሰው አንድን የሳሲት ሰው ወደ ደብረ ብርሃን፣ ሸዋሮቢት ወይም አዲሳባ ጉዳዩን ለመተኮስ ሄዶ ሲያገኘው፡፡ እውብኝ እስቲ እንጊዲህ፣ እንዲህ አይነት አነጋገር እያለ እንዴት ሳሲት ከተማ አይደለችም ይባላል? ‹‹ለማንኛውም እገጠሩም ሁን እከተማው ላባባ ስለት ይዘህልኝ ትሄዳለህ›› ሊለው ይችላል ከተሜው ለሳሲቴው፡፡ ስለ አባባ እናወራለን ሌላ ጊዜ፡፡ የፈጣሪ ታናሽ ወንድሙ ናቸው፡፡ …..

እንደገና ወደ ቴሌቪዥን እንመለስ፡፡ ይቅርታ ግን ጊዜዎን ተሻማሁዎ! በሁዋላ ግን ከትምህርት ቤት ስንለቀቅ እያሰብኳት ሄድኩኝ ቴሌቭዥንን፡፡ ‹‹እኔ ምን አገደደኝ ሬዲዮስ ብታክል፡፡ ሄጄ ማየት አለብኝ!›› አልኩ፡፡ እቤቴ ሄጄ ደብተሬን ወርውሬ በቴሌቪዥኑ ቤት ዙሪያ አንዣብብ ጀመር፡፡ የክፍል ጓደኞቼ ካወሩኝ ነገር የረሳሁትን ላውራችሁ፡፡ ‹‹ቴሌቪዥኗ መጣች- ወዛደር ታቅፏት፣ ከዚያ መምህር አዲሱ ተጠሩ (ነፍስ ይማር፣ ጎበዝ የህብረተሰብ መምህር ነበሩ - ያዲሳባ ልጅ- አጣዬ ወርደው ወባ ነው የቀጠፋቸው አሉ- ስንቱ በዚህ ሁኔታ ወላጅ ሳያስታምመው ተቀጥፎ ይሆን? ቤቱ ይቁጠረው- አይይይ የኛ ነገር!)፡፡ ሁለት አጣና መጣ፣ አንዱ ባንዱ ላይ ተቀጠለ፣ ሽቅብ ቆመ፣ አንቴና ተሰቀለበት፣ የአንቴናውን አቅጣጫ የሚያስተካክል ሰው አለ፡፡ ጄኔሬተር የሚሉ ነገር ትንዶቀዶቅ ገባች፤ የኤሌትሪክ ሽቦ ተቀጠለ፣ ሶኬት ተሰካ፣ ጥሩ የተባለው የምስል ጥራት እስኪመጣ ተጠበቀ፡፡ ከዚያም የኦሮሞ ፈረሰኛ ይጨፍር ገባ፡፡›› ቲቪ አለች ወደተባለበት ቤት ሄድኩ፡፡ ገና ስሄድ ከቤቱ በላይ የተሰቀለውን ነገር አየሁ፡፡ ‹‹ደግሞ አንተ ምን ትሆን? አንቴና ነበር ያሉኝ?›› ብዬ በቤቱ አካባቢ ከልጆች ጋር እየተጫወትኩ ቤቱ እስኪከፈት ጠበቅሁ፡፡ ትናንትናውኑ ቴሌቪዥን የታየው የመጀመሪያ ቀን ስለሆነ ለምርቃት ተብሎ በነጻ ነበር የሚል ወሬም ነግረውኛል መሰለኝ ባልንጀሮቼ፡፡ ተከፈተ! ተገባ፡፡ 14 እንች ቴሌቪዥን (ያልተከፈተ) ለመጀመሪያ ጊዜ አየሁ፡፡ የጄኔሬተርና የቴሌቪዥን መክፈት ስነ-ስርዓቱ ሊካሄድ ጊዜው ተቃርቧል፡፡ በጉጉት እጠብቀው የነበረውን ክስተት እዚያ ቤት ያስተናብር የነበረ ልጅ አጨናገፈብኝ፡፡ ማስታወቂያውን ተናገረ፡፡ ‹‹ቴሌቪዥኑን የሚያንቀሳቅሰው ጄኔሬተር የሚሰራው በቤንዚን ስለሆነ ለዛሬ ምሽት ሃምሳ ሳንቲም ትከፍላላችሁ፤ ማቲም ሳይቀር!›› አለ፤ መሰብሰብም ጀመረ፤ እኔም ሳንቲሙን ፍለጋ ወጣሁ፡፡ መጀመሪያ የሄድኩት በአቅራቢያው ያለ ሱቅ ነበር፡፡ ሻጩን ልጠይቀው ፈልጌ ሌሎች ትልልቅ ሰዎች ስላሉ ፈርቼ በቅርብ ርቀት እስኪሄዱልኝ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ አስር ዓመት የቆዩብኝ መሰለኝ፣ ‹‹ክፉዎች! ጉዳይ ኖሯቸው አይደል ተንኮላቸው አንጂ!›› አልኩ በሆዴ፡፡ ከስንት ጊዜ በኋላ ሲሄዱልኝ ሄጄ ጠየቅሁ፡፡ ‹‹ጋሼ፣ በናትህ ቴሌቪዥን ለማያ ሽልንግ አበድረኝ፤ እቤቴ ብር አለኝ ግን አሁን ከሄድኩ ‹የት ነው በዚህ ምሽት የምትሄደው› ተብዬ እንዳልቀር ነው፡፡›› ‹‹ላንተ የሚሻልህ ትምህርትህን ብትማር ነው፤ የቤት ስራም የለብህ እንዴ?›› ብሎ ትርፍ ንግግር ተናገረኝ፡፡ ትልቅ ሰው ስለሆነ ነው ይህን መምከሩ፡፡ በበሩ ቀዳዳ እንዳላይም ሌሎች ልጆች ስለሞሉት በተስፋ መቁረጥ ወደቤቴ ሄድኩ፡፡ ሳላለቅስ እቀራለሁ! ……………………

ይሄ ሁሉ አልፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ቴሌቪዥን ሳይ ግን ምን እንደተከሰተ ረሳሁት - ራሴን ስቼ ይሆን እንዴ? ከእንግዲህ፣ ቆይቶ ሌላ ቀን ካየኋቸው ዝግጅቶች ውስጥ አንዳንዶቹን ላውራ - በዚያችው በፈረዳባት 14 አንች ቲቪ- ዛሬማ 14 አንች ድንቢጥ ልላትም እችላለሁ ውለታዋን ካልረሳሁ፡፡ ከሁለት፣ ከሶስት፣ ከአራት፣ ከአምሰትም ለሚበልጥ ጊዜ ያየሁት 120 ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ ባልሳሳት የስፔንና የናይጀሪያን መሰለኝ የአለም ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያንም አይቻለሁ፡፡ የዋንጫ ጨዋታንማ ማን ያገኛታል? ወይ የመንግስት ሰራተኛ ነው፤ ወይ ልጁ ነው፤ ወይ ባለ ሱቅ ነው፤ ዞሮ ዞሮ የዋንጫ (የመጠጫው) ተጠቃሚው ነው፡፡ የስቅለትን ፕሮግራም ለማየት የገባሁበትን ወሬ በደንብ ስለማስታውሰው ላውራው፡፡ ‹‹ላውራው አትበሉ ልጻፈው ነው ነው የሚባለው፤›› የሚሉ የስነ ጽሑፍ መምህር ነበሩን - አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሐገራቸው አሰናብቷቸዋል፡፡ (ከአበሾቹ መምህራን በዕውቀት እጅግ ስለሚልቁ፤ በተንኮል ተባረሩ አሉ) - ሕንዳዊ ናቸው - ሕንዳዊ ናቸው ማለቴ እንደ ጉራ እንዳይቆጠርብኝ፡፡ ሕንድ አስተምሮኛል አለ ተብዬ እንዳልወቀስ ማለቴ ነው፡፡
አንድ ብሬን ጨክኜ አውጥቼ የስቅለት አርብ ነው መሰለኝ ፊልም ለማየት እቴሌቪዥኑ ቤት መሄድ (ላለማየት ብለው ይሻላል)፡፡ ካንድ ሁልጊዜ ከምላላክለት የመንግስተ ሰራተኛ ጎን ተቀምጬ ቴሌቪዥኔን ማየት፤ ቴሌቪዥናቸውን ብል ይሻላል - የነሱ ልጅ ብሆን ብሎ ያልተመኘና ቴሌቪዥኔ ማለትን ያልናፈቀ የሳሲት ልጅ እውን ይኖር ይሆን? ከኖረ እሱ/ ቴሌቪዥን ለማየት ያልደረሰ/ ህጻን ልጅ ነው/ች፡፡ ወደ 4፡00 ሰዓት ላይ አመጡታ ያንን ውጧቸውን፡፡ ‹‹በቤንዚን ስለሚሰራ ጨምሩ›› ማለት መጣ፡፡ አንድ ብር ከፍለን ገብተን ሌላ አንድ ብር ጨምሩ ማለታቸው አያናድድም? ያበግን ነበር፡፡ ‹‹በል ጋሽ እንትና ደህና እደር ወደቤቴ ልሂድ›› አልኩት አብሬው የተቀመትኩትን ሰው፡፡እንዴ ምነው?›› ሲለኝ ‹‹አይ የምጨምረው ብር የለኝም›› አልኩት፡፡ የኔ ምርቃት ሳይሆን አይቀርም ያበለጸገው አሁን ቢጠሩት አይሰማም፡፡ ‹‹አንተ ጎበዝ ልጅ አይደለህም እንዴ? ታዛዤ አይደለህም እንዴ? በል ቁጭ በልና እይ፤ እኔ እከፍልልሃለሁ›› አለኝ፡፡ ጋሽ ማን እንደሆንክ ታውቀዋለህ፤ አሁንም የሰው መውደድ ይስጥህ፡፡ ያበላ አይረሳ! የዋለ አይረሳ! ለኔ ደጌ ነው፡፡

ሲጠበቅ ሲጠበቅ የአማርኛው ዝግጅት አልፎ የእንግሊዝኛው ሳይሆን አይቀርም ጀመረ፡፡ ሌላም ታላቅ ፊልም ወይም ሌላ ዝግጅት ተጀመረ መሰለኝ፡፡ በቃ የስቅለቱ ፊልም ቀርቷል ተባለ ተበተንን፡፡
ጊዜው ሲሄድማ እኛ ቤት አምፖል ገባ እላችኋለሁ፡፡ ማጥናት ሆነ፣ የቤት ስራ መስራት፡፡ አንዳንድ ቀን ይደክመኝና ነው መሰለኝ የቤት ስራዬንም ሳልሰራ የመብራቱም ማጥፊያው ሰአት 415 ሳይደርስ እተኛለሁ፡፡ በማግስቱ ወዳጄ፣ ተነስ ይባላላ የቤት ስራ ያልሰራ፡፡ አስር አስሬን ጠጥቼ የምገባው ስንት ቀን ነበር፡፡ መብራቱ የሚታዘዘው ከማዕከል መሰለኝ፤ እኛ ቤት ማብሪያ ማጥፊያ ይኑር አይኑር አላስታውስም፤ የነበረ ግን አይመስለኝም፡፡ 15 ብር ሳይሆን አይቀርም ይከፈል የነበረው፡፡ ባለ ፍሎረሰንቶች 25 ብር - በብዛት ንግድ ቤቶች ነበሩ፡፡ ‹‹ጠሐይ ይውጣላቸው፤ ጠሐይ አስመሰሏት አገሪቱን - ባለ ጀለሜተሮቹ›› ይል ነበር ባልቴቱ ሁሉ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፡፡ ይህ ሁሉ 1990 እና ከዚያ በፊት ወሬ ነው፡፡

2001 .. አስተማሪ በሆንኩ በሁለት አመቱ ለሳሲት የመጀመሪያው የሆነውን ሳተላይት ዲሽ አስገባሁ፡፡ የመጀመሪያ ለመሆኑ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ አይደለም የሚል ወንድ ካለ ይሞግተኝ፤ ሴት ልትሆንም ትችላለች ለነገሩ፡፡ ምን ይታወቃል ወደፊት ከሳሲት የመጀመሪያው ወጣት የህዝብ እንደራሴ ሆኜ መልሼ የምወደውን ያዲሳባ ውሃ እጠጣ ይሆናል፡፡ ያዲሳባ ውሃ ልዩ ነው፡፡ ውሃ ካልሄደ አይመሰገንም፡፡ እሽግ ውሃን ያስናቃል ያዲሳባ ውሃ፡፡ እስቲ ደግሞ ልቀኝ፡፡

መስቀል አደባባይ ይሰቀል መስሎኝ
ቴሌቪዥን ጃን ሜዳ ይጎመር መስሎኝ
የሚከመር ነው ስል እንጦጦ ላይ ወጥቶ
የሚጠበው ነው ስል ስቴድየም ገብቶ
የረር ላይ ቁጭ ብሎ አገር ያየው ብዬ
ቀስተ ደመናውን የሚያክል ነው ብዬ
ይታቀፉት ኖሯል እንደነ አቡሽዬ
እንደ ሬዲዮ ያለ፣ ድንጋይ የማይበላ
ኖሯል ይህ ቴሌቪዥን አየሁት በኋላ፡፡
እቤቴ አለኝ አሁን ባለ 21 ኢንቹ
ከነዲሽ ከነምን ከነኮተቶቹ
ወይ ባለካርዱን ዲሽ አስገባ ይሆናል
አይሆንም አልልም የማይሆነው ሆኗል፡፡
እንደራሴ ሆኜ ልገባ እችላለሁ
እቴሌቭዥኑ ውስጥ ሆኜ አያችኋለሁ
ጠብቁኝ ሳሲቶች 2 ሰዓት ዜና
የሸንጎ ተሟጋች ይወጣኛልና፡፡
በየቤቶቻችሁ አወጋለሁና
እናንተም ቴሌቪዥን ገዝታችኋልና፡፡

ትንሽዬ ማስታወሻ፡- በአሁኑ ጊዜ አጠራሯ (2004 .. ጀምሮ) ሣሢት ታዳጊ ከተማ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በሰሜን ሸዋ መስተዳድር ዞን፣ በሞጃና ወደራ ወረዳ ምትገኝ በጣም አነስተኛ ከተማ ነች፡፡ አሁን መብራት ገብቷል፣ የቴሌቪዥኑም ቁጥር በጣም በዝቷል- 20 አይጠቅመውም፡፡ ዲሹም አምስትን ሳይዘል አይቀርም፡፡ ስለ ጊዜ ከተዜሙ አንዱን መርጣችሁ አድምጡልኝ- በምናብ፡፡
አመሰግናለሁ
አክባሪዎ
እርስዎም ስላደጉበት ሁኔታ ቢያወሩ እናነብልዎታለን፤ ጨከን ማለት ነው ዋናው ነገር፣ እኔ እርስዎ ዘንድ የሚደርስ ጽሁፍ እጽፋለሁ ብሎ ያሰበም ያለመም አልነበረም፡፡ ይህን ሁሉ መተየቡ፣ ማርቀቁና ማረሙ 6 ሰዓታት በላይ ፈጅቶብኛል ስላችሁ ካንጀቴ ነው፡፡ አሪፍ ተጨዋች ከሆንኩ አበረታቱኝ፤ ካልሆንኩም ገስጹኝ፤ mezemir@yahoo.com በመጠቀም፡፡ ኢትዮጵያና ወዳጆቿ ለዘላለም ይኑሩ!!!!!!!

ተጉለት ጉራንጉሩ፡ የጉዞ ማስታወሻ




መዘምር ግርማ እንደተረከው (Mezemir@yahoo.com)
ከሰባት አመታት በፊት ሳሲት* ከተማ አቅራቢያ ታሪክ ራሱን ደገመ፡፡ ዛሬ ላይ ሆኖ ሲያስቡት ይደንቃል፡፡ ድርጊቴንና ወኔዬን ከዳኛቸው ወርቁ ልቦለድ ገጸባህሪ ከአደፍርስ እንግዳ ተግባራት ጋር እንዳወዳድር ይዳዳኛል - ከቋንቋ ተማሪነት ወደ አማተር ጂኦሎጂስት ወይም አርኪኦሎጂስትነት ተለውጬ ነበርና፡፡ ሳሲትና አካባቢዋም ከ70 አመታት በኋላ ባለውለታዋን አስታወሰች፡፡ በሳሲትና አካባቢዋ ነዋሪዎችና በዋሻዎች መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ቁርኝት ሊያሳይ የሚችለው ቀላሉ ነገር የተለያዩ ስፍራዎች የተሰየሙበት ከዋሻ ጋር የተያያዘ ስማቸው ይመስላል - ቀለም ዋሻ፣ ጠጠር ዋሻ፣ ጅብ ዋሻ፣ እንግድዋሻ፣ ልሳንዋሻ፣ ምግልዋሻ፣ አምባዋሻ፣ እምብስ ዋሻ፣ ጽድ ዋሻ፣ ንብ ዋሻ፣ ድል ዋሻ፣ ወርቅ ዋሻ፣ ላም ዋሻ፣ ጨለማ ዋሻ፣ ዋርካ ዋሻ፣ ሾላ ዋሻ …

በታሪካዊ ልቦለዱ በአዳባይ ላይ እንደተገለጸው ‹‹በ1931 ዓ.ም. በአንቀላፊኝ የራስ አበበ የጦር አዝማቾች ከምሁራን ባልደረቦቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ‹የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖቸ አርበኞች ማህበርን› አቋቁመው ፈረሙ፡፡›› (ገጽ 166-7)፡፡ አንቀላፊኝ ሜዳ እና ሌሎችም ታሪካዊ ስፍራዎች በትውልድ አካባቢዬ ቢገኙም በቅድሚያ የመጎብኘት ትኩረቴን የሳበው ከሳሲት እስከ ሰላድንጋይ በምድር ውስጥ ያስኬዳል ተብሎ የሚታመንበት ዋሻ ነበር፡፡ 20 ኪሎሜትር ገደማ ‹‹ይረዝማል›› ይባላል፡፡ ዋሻ መሸሸጊያ መሆኑ በታሪክ የታየበት ጊዜ አለ በሞጃ እና ወደራ ወረዳ፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት ልጅ ሆነው ተሸሽገውበት እደነበረ ያጫወቱኝ አቶ ማሞ ገብሬ፣ ካሳዬ ወንዳፈረው የተባለ የአካባቢው ተወላጅ አርበኛ ከጣሊያን ወራሪ ወታደሮች ጋር እየተታኮሰ የአካባቢውን ህዝብና ከብት ይዞ ወደ ዋሻው እንደገባ፣ ከብቱን የፋሽስት ወታደሮች ከዋሻው አውጥተው ሲያርዱና ሲጥሉት ህዝቡ ግን ራሱን ተከላክሎ ወደ ውስጥ ገብቶ እንደዳነና በማግስቱም የአምስት አመት የስደት ጊዜ ለማሳለፍ ወደ ይፋት እንደወረደ ዋሻውም መጨረሻው እንደማይታወቅና ሰላድንጋይ ይደርሳል ሲባል እንደሰሙም ነግረውኛል፡፡ አቶ አስፋውና አቶ ተክለወልድ ደግሞ ከደጋው ህዝቡ ሲያባርረው የመጣን ጅብ ዋሻው ውስጥ ሊገባ ሲል እንደገደሉት አጫውተውኛል፡፡ ከአብዛኛዎቹ ተጠያቂዎቼ እንደሰማሁት ግን በአንድ ወቅት አንዲት ውሻ በዋናው በር ስትገባ ታይታ ሰላድንጋይ ለጉዳያቸው የወጡ ስትገባ ያዩዋት ሰዎች እዚያም ባለው በር ስትወጣ አይተዋታል እየተባለ እንደሚተረት ነው፡፡ እንዲያውም የዋሻው የሰላድንጋዩ መውጫ በሩ ቁሮ ገደል በተባለ ስፍራ እንደሚገኝ ነግረውኛል፡፡ ለተጠያቂዎቼ ግን ‹‹ይህን ያህል ርዝመት እንዳለው አይታችኋል›› ስላቸው ‹‹እሱ ተብሎ ያለቀ ነው›› ይሉ ነበር፡፡ በህዝቡ ዘንድ የሚወራውን ለማረጋገጥ ዘመቻ ግድ ይል ነበር፡፡

ለ15 ቀናት ያህል ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ስለዚሁ ጉዳይ እንመክራን፤ ስለ ዋሻው የሰሙ ሰዎች መጥተው የሚነግሩኝንና ለዝግጅት የሚያስፈልጉትን ቁሳቁስም እጽፋለሁ፡፡ እንደነፍሰጡር ቀናችንን መቁጠሩ የባሰ ጉጉት አሳደረብን፡፡ ከመካከላችን አንዳንዶቹ የሚያነሷቸው ሃሳቦች የሚከተሉትን ይመሳስሉ ነበር - ‹‹ወደ ዋሻው ገብተን ብንጠፋፋና የዋሻው በር ቢጠፋብን የት እናገኘዋለን?››  እና ሌሎች ደግሞ ‹‹ስንሄድ ባህር ወይም ጎድጓዳ ስፍራ ቢገጥመን ተቀርቅረን መቅረታችን አይደለምወይ?›› ይላሉ፡፡ አስጊ ሁኔታ ነበር፡፡
ከአዛውንቶች በሰበሰብኩት መረጃ መሰረት ዋሻው ወደተለያየ አቅጣጫ የሚወስዱ መንገዶች ስላሉት አንዱን ተከትለን ሰው ወደ ጎን እንዳይሄድ እየተቆጣጠርን መሄድ ፣ ሰላድንጋይ ከተማ የሚያደርስ ከሆነ መንገዱ እንደ መሬት ላይ መንገድ ስለማይቀና ስንቅ ቋጥረን የፈጀውን ያህል ጊዜ ይፍጅ እንጂ የዋሻውን መጨረሻ ማየት አለብን አልን፡፡ በጉዟችን ወቅት ድቅድቅ ጨለማውን ለማብራት ችቦ፣ ጧፍ፣ ማሾ፣ ባትሪ እና ሻማ እንያዝ የሚሉ ሃሳቦች መጡ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ችቦ ጭሱ ያፍነናል ባትሪም ዋሻው ውስጥ አይበራም በማለታቸው ማሾ እና ጧፍ ለመያዝ ተስማማን፡፡
መሽቶ ሲነጋ ሁለት ሳምንት ቀኑን ሙሉ ስለዚሁ ዋሻ ስናወራ እንውላለን፡፡ገብተን ሰይጣን ልናገኝ፣ ለደህንነታችን የሚያሰጋ ተአምራዊ ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል የሚሉ ሰዎችን ስጋት ወደኋላ እየተውን ለመግባት የሚያስፈልገውን የቁሳቁስም ሆነ የስነልቦና ዝግጅት ቀጠልን፡፡ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከመሬት በታች መላዕክት እንደሚኖሩ፣ ሰዎች የሚኖሩበት ሌላ ሃገር እንዳለ፣ በዶሮ የሚታረስበት ግዛትም እንደማይጠፋ ስንሰማ አድገናል፡፡ ምናልባት ይህን የምናይበት ሌላ አለም ሊገኝ ይችላል ብዬ እኔም አስብ ሌሎችም በአዕምሯቸው ያወጡና ያወርዱ ነበር፡፡ሰው ባገኘኝ ቁጥር አስረዳለሁ፤ ጥያቄዎቻቸውንም እመልሳለሁ፤ በሰዎቹ ፍላጎት ደስታና እርካታ ይሰማኛል፤ እጓጓለሁ፤ እገረማለሁ፡፡ በአካባቢያችን ሌሎች መሰል ዋሻዎች አሉ ቢባልና እኛም ብናውቅ መጀመሪያ ያደረግንውን ይህን ዋሻ ለመጎብኘት አንድ ቀን ቀረን - ቅዳሜ መስከረም 6 ቀን 1999 ዓ.ም. ፡፡ በትውስት ማሾዎች ጋዝ ሞላን፤ ጧፎቻችንን ገዛን፤ ሻማና ሌሎችንም እንዲሁ አሟላን፡፡ ሰዉ በማቴሪያል፣ በገንዘብ እንዲሁም በጉልበት ከጎናችን ስለነበረ ነው ዓላማችንን በመጠኑ  ለማሳካትና ይህን ለእናንተ ለመንገር የበቃንው፡፡
በማግስቱ በዋሻው አቅራቢያ ያሉና ሊገቡ የተስማሙ ገበሬዎች በጠዋት እንድትመጡ ስላሉን ሕዝቡንም ለመቀስቀስ ከሌሊቱ 11 ሰአት ላይ ከእንቅልፌ ተነሳሁ፡፡ ጓደኞቼን ቀስቅሼ ሌሎችንም እንዲቀሰቅሱ አሳሰብኩ፡፡ ከነጋ በኋላ ወደ 12፡30 ሰአት ላይ ተጠቃለን ጉዟችንን ለማድረግ ከከተማዋ እምብርት ተነሳን፡፡ ያሰብንውን ያህል ባይሆንም ወደ ሃያ አምስት ያህል ሰዎች ተሰባስበናል፡፡ በየቤቱ እየሄድን ስንቀሰቅሳቸው በሰበብ ባስባቡ እንደማይሄዱ አስተዛዝነው ይነግሩናል፡፡ እኛም ‹‹አላስገደድናቸው ከመጀመሪያው ለምን እሺ አሉ? ሰው ሂድ ብሎ ሳያስገድዱት እሄዳለሁ ይላል እንዴ?›› ብለን ታዘብናቸው፡፡ ለማንኛውም እኛው እንበቃለን ብለን ዝግ ባለ አረማመድ ከተማዋን ለቀን ወደ ምዕራብ ስንጓዝ ሰው ሁሉ ያየናል፡፡ ‹‹አረ የነብር ቁርስ እንዳትሆኑ!›› ሳይል አይቀርም ተመልካቹ - ካይኑ ያስታውቅበታል፡፡ ከተማዋን ለቀን ወደገጠሩ ስንገባ ሰዎች ከዚህም ከዚያም እየሮጡ ከከተማዋም ጭምር ተከተሉን፡፡ በርከትከት እያልን መጣን፡፡ በየቤቱ እንዲሰማ አድርገን የምናውቃቸውን ሰዎች ተጣርተን ብዙ ሰዎች ለመሰብሰብም ቻልን::

ወደ ሰሜን ታጥፈን ቁልቁል ከወረድን በኋላ አፋፉ ላይ ስንደርስ መንዝን ካድማስ ወዲያ ማዶ እያየንና የቆላማውንም ስፍራ ልምላሜ እያደነቅን ለደቂቃዎች እንኳን ሳንቆይ፣ አያቴ ‹ያ ማዶው ሰላሌ ነው› የሚለኝን ጨለማ አገር ቃኝተን ሳንጠግብ አትኩሮታችንን ወደ ተጉለቱ ድንቅ ዋሻ መለስን፡፡ የአካባቢው ገበሬም ቀድሞን ዋሻውንና አካባቢውን ወሮታል፡፡ በዙሪያው ከሩቁ የሚታዩትና ነጫጭ የለበሱት እነዚህ ሰዎች የጥንት አርበኞችን ያስታውሷችኋል፡፡ ደምቃ ፍም መስላ ከወጣችው የጠዋት ፀሀይ ግርጌ ከግራና ከቀኝ ትልልቅ ተራሮችን የተሸከመውና በመሃልም ሸለቆ የሚንፈላሰስበት ባለረጅም አፉ ዋሻ በአረንጓዴ ቅጠላ ቅጠል ተከቦ፣ በሸለቆው ውስጥ የሚመጣው ወንዝና በዋሻው መግቢያ ፊት ለፊት የሚወርደው ፏፏቴ አንድ ላይ ሆነው ሌላ ተፈጥሯዊ ገጸ በረከት እነሆ አሉን፡፡ አንዲት አጎንብሳ ጸጉሯን በሳሙና የምታሽና ጸጉሯም በመታጠቢያው ሳፋ ላይ ለሽ ያለን ኮረዳ ያስመስለዋል፡፡  ጸጉሯን በፏፏቴው፣ ከንፈሯን በዋሻው አፍ ፣ ሁለቱን ትከሻዎቿን በተራሮቹ እንዲሁም ሳፋውን  እታች ፏፏቴው በሚያርፍበት ባህር መመሰል ይቻላል፡፡ ይህን ሁሉ በማየቴ ተደነቅሁ፡፡ ከባልንጀሮቼ ጋር ወደዋሻው ተጠጋሁ፡፡ የሀገር ሽማግሌዎች በዋሻው በር ላይ ተቀምጠው ታሪክ ያወራሉ፣ ይመክራሉ፡፡
ዋሻው በጎንና በጎኑ መግቢያ መንገድ ስላለው ሸረር ብለን ገባን፡፡ አቤት የነበረ ጥድፊያ!  አቤት ያን ዋሻ ተጠግቶ ሲያዩት ያለው ግርማ ሞገስ፡፡ ውስጥ ስንገባ አናቱ ደማቅ ጥቁር ፣ መሬቱ ደግሞ ቀይ ደረቅ ለስላሳ አፈር ሲሆን ጣራው የጠቆረው አባቶቻችን በጣሊያን የግፍ ወረራ ጊዜ በችቦ ለብልበውት ነው ተባልን፡፡ ምክንያቱም ማዕድን ሊሆን ስለሚችል በጣሊያኖች አይን እንዳይገባ ተብሎ ነበር፡፡ ሲፈረፍሩት የሚያብረቀርቅ ልዩ አለት እየተፈረፈረ ይወርዳል፡፡ የወንዙ/የፏፏቴው ውሃ በፊታችን ወርዶ መሬት ላይ ሲያርፍ የሚያሰማው ልዩ ድምጽ ልብን ያሸብራል፣ አዕምሮን በአንዳች ፍርሃታዊ ምትሃት ያርዳል፤ ሁለመናን ይቀሰቅስማል፡፡ ሽሽሽ… ቻቻቻ… ይላል፡፡ ይህም በአቅራቢያው ካለው አያልፉሽ ከተባለው የጸበል ቦታ፣ ከአጃና ሚካኤልም በላይ ምጡቅ ነበር፡፡ ባሕታዊነትን ያስመኝማል፡፡ በዋሻው አቅራቢያ ያለው ስነ-ሕይወታዊ መስተጋብር ለዘርፉ ምሁራን ለም የምርምር ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡ አይደርሱ የለ ደረስን፣ አየንው የንን የጓጓን የቋመጥንለትን  ዋሻ! ታዲያ አፉን እንጂ ሆድ እቃውን ለማየት ገና በዝግጅት ላይ ነበርን፡፡ ማሾዎች ተለኮሱ፤ ጧፉንም ያዝንና ታጥቀን ተመራርጠን ተነሳን፡፡ የዋሻውን አፍ ርዝመት ለክተን 105 ሜትር መሆኑን አረጋገጥን፡፡ ከፍታውም በመግቢያው በር አካባቢ ከ3 ሜትር ቢበልጥ እንጅ አያንስም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በጉንብስ አለያም በጣም ዝቅ ሲል በደረት መሄድ ግድ ይላል፡፡
በውስጠኛው የዋሻው ክፍል አለትና ቋጥኝ፣ የጅብ ጽዳጅ፣ የእንስሳት ብሎም የሰው አጽም አግኝተናል፡፡ ዙሪያውን አሰስንው፤ ጎበኘንው፡፡ ሆኖም ግን  በዚያ በሰፊው የዋሻው ክፍል ውስጥ ወደ ውስጥ መፈናፈኛ ጠፋ፡፡ ‹‹በምን ተገብቶ ነው ሰላድንጋይ የሚደረሰው?›› ብዬ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ አብዛኛዎቹ ተጠያቂዎቼ ‹‹በግለሰቦች ተደፍኖ ነው እንጅ በር ነበረው ፤ የቱጋ እንደሆነ ለማግኘት ከቋጥኙ መብዛት የተነሳ አልቻልንም›› አሉኝ፡፡ ቋጥኞቹን አልፎ ሄድ ሲሉ በዋሻው የቀኝ ክፍል ወደ መሬት የሚያሰገባ መንገድ አግኝተው የተወሰኑት ጓደኞቻችን ገቡ፡፡ አንዲት ሽንቁር ማሰሮና ሁለት የሰው የራስ ቅል ይዘውም ተመለሱ፡፡ ደረጀ አስራተ የተባለው ሌላኛው ዘማች ደግሞ በዋሻው መግቢያ ትይዩ ባለው አቅጣጫ ‹‹ጎራዴ ና ባትሪ ብቻ ስጡኝ›› ብሎ በአንዲት ሰው ሁሉ በፈራት ጠባብ ጎሬ አልፎ ሄዶ ቀረብን፡፡ ግማሹ ሰው ፈራ ተባ እያለ ‹‹ወደ ኋላ ልመለስ ወይንስ ልጠብቀው፣ ጅብ በልቶት ይሆን ነብር?›› ሲል፣ ደምሰው ታችበሌ በልበሙሉነት ሲጋራውን ሲያጨስ በመጨረሻ የደረጀ ድምጽ ሲሰማ ህዝቡ እፎይ አለ፡፡ እኔም ደስ አለኝ፡፡ ‹‹ምን አለ›› ስንለው ‹‹የሆነ ወደላይ የሚያስወጣ መንገድ አለ ወጥቼ ልምጣ›› ሲለን እንደገና ደንገጥ አልንና ጠበቅንው፡፡ ‹‹አይይይ ምንም የለ›› ሲል አንድ ሆነ፡፡ 
ወደ አስር የሚሆኑ በዋሻው የግራ አቅጣጫ የሄዱ ሰዎች ደግሞ ትንሽ ሄደው ሰማይ ሲያዩ ‹‹ሌላ አገር የደረስን መሰለን›› ብለው ጮሁ፤ ግን ሌላ የዋሻው መግቢያ በር ነበር፡፡ ስለዚህኛው መግቢያ በር፣ ከዋናው በር ሌላ መሆኑ ነው፣ በዚያኛው ቡድን በኩል ባለመሆኔ ማየት ባልችልም ከሰማሁት ለመናገር ግን እችላለሁ፡፡ እኔ የነበርኩት በበሩ ትይዩ በነበረው አቅጣጫ ነበር፡፡ አቶ ታደሰ ዘነበ እንደነገሩኝ ደግሞ በዚሁ በቀኙ አቅጣጫ ወደታች አይቼ ልምጣ ብለው ገብተው ጓደኞቻቸው ጥለዋቸው/ረስተዋቸው ሄደው መውጫው ጠፍቷቸው ለደቂቃዎች ተቸግረውና ቢጣሩ የሚሰማቸው አጥተው በስንት ፍለጋ የገቡባትን ከሰው ትከሻ የማትሰፋ በር አግኝተው ወጥተዋል፡፡  ‹‹እኔ ተቻኩዬ ተመለስኩ እንጂ ያችማ ያች የተባለችው ከጎተራ አፍ ትጠባለች ያሏት ወደሰላድንጋይ የምታወጣው የጠፋችብን ዋናዋ በር ሳትሆን አትቀርም፤ ስንትና ስንት መንገድ እኮ ሄጃለሁ፤ በደንብማ ቢፈለግ ይህ ዋሻ አንድ ነገር አይጠፋውም ›› ብለዋል በእለቱ ከሰዓት በኋላ ጉዟችንን ስንገመግም፡፡

በሁሉም አቅጣጫዎች የአለቱን ብዛት አንድ መሃንዲስ ቢኖር በቢያጆ ይገምትልን ነበር፡፡ አንድ ትምህርት ቤት ይሰራል፡፡ ወደፊት በዚያ ዋሻ ሄደን ምናልባት ሰዎች ካገኘን ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት መስሪያ ስሚንቶ ብቻ ከገዙ ይበቃቸዋል፡፡ ዋሻችን ከላይ የሚያዥ ነገር እና መሬትም ላይ የዚያው ክምችት (stalactites and stalagmites) ብዙ ቦታዎቹ ላይ አለው፡፡ ወለሉ ጫር ጫር ሲያደርጉት አፈሩ ልስልስና በእጅም ቢዝቁት የሚዛቅ ነው - ልክ አሸዋ በሉት፡፡ አንዳንዴ በቡድን በቡድን ሆነን ስንድህ ልጅነታችንን ያስታውሰናል፡፡ ከዚያ ደግሞ ሄደን የሚያስቆምና የሚያስፎክር ቦታም እናገኛለን፡፡ በእንደዚህ አይነት ጉዞ ታዲያ መደራጀትን የመሸሽ ችግር አይቀረፍምና ‹‹በቃ እንሂድ፤ በቃ አገራችን እንውጣ!›› እያሉ ካስቸገሩትና ባጭሩ ተስፋ ከቆረጡት በላይ አንዳንዶቹ ከዋሻው እየወጡ ወደ ሳሲት ይመለሱ ጀምረው ነበር፡፡ አንድ ሽማግሌ ደግሞ ከዋሻው በር ላይ ካለው ካብ ላይ ትልልቅ ድንጋይ እያነሱ ታች ቆላ ወዳለው ባህር ሲወረውሩ ረበሹኝ፡፡ ‹‹አረ ተው አብዬ ምነው?›› ሲሏቸው መች ይሰማሉ፡፡ ብቻ ይስቃሉ ደስ ብሏቸዋል መሰለኝ ቦታው፡፡ ይህ በዋሻው በር ላይ የተካበው ካብ አርበኞች ምሽግ አድርገው ይጠቀሙበት የነበረ ይመስለኛል፡፡
በጎብኝዎቹ መጣደፍ ምክንየት ብቻ ከሰአታት መጠነኛ አሰሳ በኋላ ወደ ሳሲት ከተማ በዋሻው በር በሌላኛው አቅጣጫ ወጥተን ትንሽ ዳገትም (ልዩ ስሙ ትልቅ አረህ) ፈትኖን የመልስ ጉዟችንን ያልተመለሱ ጥያቄዎች ይዘን ጀመርንው፡፡ የወረድንው በጭጨት ነበር፡፡ ብዙም ተጉዘን እረፍት ተደረገና ወደ ከተማችን ደርሰን አንድ ቤት ገብተን ውይይትና ጨዋታው ቀለጠ፡፡ ከጉዟችን በኋላ ገበሬው ማዕድን አለበት እያለ የዋሻውን አናት ያገልሰው እንደያዘ ሰማን፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት ከተደረገው ቀጥሎ (ከሰባ አመታት በኋላ) ህዝብ ተነሳስቶ የገባበት ትልቁ ዘመቻ በዚህ መልኩ ተጠናቋል፡፡ ሌላ ጉብኝትና ጥናት ለማድረግ ሰባ አመታት እንጠብቅ ይሆን? ስለተነሳሽነቱ ህዝቡን ባያሌው አመሰግናለሁ፡፡ ህዝቡ ያለው ‹‹ዱሮስ እሱን አምነን›› ሳይሆን ‹‹ይህ ዋሻ ቀን ይወጣለታል›› ነው፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዶ/ር ሲቪል መሃንዲስ ሀይለጊዮርጊስ ወርቅነህ የህይወት ታሪክ ላይ እንደተመለከተው ከሶስት መቶ በላይ የአርበኛ ጦር ከነቤተሰቡ በሳሲት አቅራቢያ ባለ አንድ ዋሻ መሽጎ ነበር፡፡ በተጉለት ሌሎች አርበኞችን ፍለጋ የሚዘዋወረው ይህ ጦር ዋሻ ውስጥ እንደመሸገ በአካባቢው ነዋሪዎች ይጠቆምበትና በአንድ ሺህ የጣሊያን ጦር ይከበባል፡፡ አስራ አራት ቀን ሙሉ በረሃብ ተሰቃይተውና ከዋሻው የላይኛው ክፍል የሚያዠውን ውሃ እየመጠጡ፣ ኮርቻ ፈልጠው እያነደዱ የጤፍ ቆሎ እየቆሉ እየበሉ፣ የጣሊያን ጦር እየተኮሰባቸው ከቆዩ በኋላ በአስራ አራተኛው ሌሊት ወንዶቹ ጥሰው ሲወጡ ተጨፈጨፉ፤ አስራ ሁለት አመት ገደማ ያሉ ወንድ ልጆችም ተረሸኑ፤ ሴቶቹና ህጻናት መጀመሪያ ወደ መንዝ ከዚያም ወደ ደብረ ብርሃን እስርቤቶች ተወሰዱ፡፡ ከላይ የተጠቀሱትም ዶ/ር በዚያን ወቅት አስር አመታቸው ሲሆን በኋላ አድገው ተምረው አለምአቀፍ ምርምሮችን አቅርበው ተሸልመዋል፡፡ በሳይንስ መዛግብት ላይ ስማቸውን ያሰፈረላቸው እስከ 150 ኪሎሜትር ርቀት ጠጣር ነገርን የሚያስተላልፈው ቧንቧቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ (አልፈዋል)! ከመጽሀፋቸው የሚከተለውን እንመልከት ፡- ‹‹በዋሻው ውስጥ አባቴ፣ አጎቴ፣ እናቴና ያጎቴ ባለቤት እና ከዘጠኝ የሚበልጡ የቅርብ ዘመዶቻችን፣ እና ሌሎች ቤተሰቦች እንዲሁም ከ300 የሚበልጥ መሳሪያ ያለው ሰው ነበር፡፡ በዚያም ላይ የቀንድና የጋማ ከብቶችና የቤት እንስሳዎችን የመሳሰሉ ሁሉ ከዋሻው ውስጥ ነበሩ፡፡ ለጥቂት ቀናት የሚበቃ ምግብ፣ ውሃና ማገዶም ተይዞ ተገብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ ለ14 ቀናት ያህል በመከበባችን፣ ያ ይዘን የገባንው ምግብና ማገዶ አለቀ፡፡ ዋሻው ፊት ለፊት ከሚፈሰው ውሃ ለመቅዳት እንዳንችል፣ ጠላት ፊት ለፊት መሽጎ ይጠባበቅ ስለነበረ፣ በጣም አስቸጋሪ ሆነ፡፡›› የህይወቴ ታሪክ (10)    
ይህን ታሪክ እኔና ሳሲቶች የገባንበት እንግድዋሻ አለያም በሱው አቅራቢያ የሚገኘው ልሳን ዋሻ ሊጋሩት ይችላሉ፡፡ ልሳን ዋሻ በአንድ ቀን ብቻ ከ600 በላይ ሰው እንደተረሸነ አዛውንቶቹ አጫውተውኛል፡፡ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ግድያ ሊሆንም ይችላል፡፡ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም የታሪክ፣ የጂኦሎጂና የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎቹን አስተባብሮ ይህን ዋሻ፣ ሌሎችን ዋሻዎችና ታሪካዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ስፍራዎችን ቢያስጠና ለአካባቢው ህዝብ ባለውለታ ያደርገዋልና ቢያስብበት እላለሁ፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የፌደራሉ መንግስት፣ የአርበኞች ማህበር እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶችም የተጉለት ቅርሶች ላይ የተቻላቸውን ሁሉ ቢሰሩ በማለትም አሳስባለሁ፡፡
ጣሊያን ቤቱን ሲያቃጥልበት ህዝቡ ዋሻዎች ውስጥ ነበር የኖረው፡፡ አሁንም ዋሻ እንደሚፈለግ ያሳየኝ ክስተት ቢኖር አንድ አዛውንት በ1999 ዓ.ም. ‹‹አንተ ልጅ ጓዳችንን ለምን ለሰው ታሳያለህ?›› ያሉኝ ነው፡፡ የእርሳቸውን ሃሳብ እያከበርኩ አሁን የአለም ሁኔታ እየተቀየረ መሄዱንና ዋሻ ውስጥ እስክንገባ የሚያሳድደን ነገር እንደማይኖር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ዋሻውን ለአገር ጎብኝ እያሳየን የገቢ ምንጭ እንድናደርገው እና እኛም እንጎበኘው ዘንድ የሁላችሁንም ትብብር በሁሉም ዘማቾች ስም እጠይቃለሁ፡፡ በመጨረሻም ለጭቁን ህዝቦች አርዓያና መጽናኛ በሆኑት በኢትዮጵያ በአርበኞች መዝሙር ልሰናበት፡-
ጥንታዊት ኢትዮጵያ እናታችን ሆይ
አርበኛሽ ጽኑ ነው ቆራጥ ተጋዳይ
የደሙ ምልክት ያው በልብሱ ላይ
ጥንታዊት ኢትዮጵያ አትደፈሪቱ
ጠላትሽ ግፈኛ አረመኔ ከንቱ፡፡
ጥንታዊት ኢትዮጵያ የጀግኖች ማህበር
ጠላትሽ ተዋርዶ ስምሽ እንዲከበር
እንሸከማለን የመከራ ቀንበር፡፡

አዳባይ (243)


*ሳሲት ከተማ ከደብረ ብርሃን ከተማ በስተሰሜን 92 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የምትገኝ ተጉለቴ ነች፡፡ ከሞጃና ወደራ ወረዳ መዲናዋ ከሰላድንጋይ ደግሞ 20 ኪ.ሜ ትርቃለች፡፡ ሰላድንጋይን ብዙ ሰው በጻድቃኔ ማርያም ገዳም ያውቃታል፡፡





2015 ኦገስት 18, ማክሰኞ

የሙታን መንገድ


ደራሲ-ችንዋ አቼቤ (1930 - 2013)
መዘምር ግርማ እንደተረጎመው
የሚካኤል ኦቢ ምኞቶች የተሳኩለት አስቦት ከነበረው እጅግ ቀድመው ነበር፡፡ በጥር 1949 ዓ.ም የንዱሜ ማዕከላዊ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆኖ ተሾመ፡፡ ትምህርት ቤቱ ብዙጊዜ ኋላቀር ሆኖ ስለቆየ የሐይማኖታዊ ተልዕኮው ባለስልጣናት ወጣትና ጉልበቱ ያልተነካ ሰው ያስተዳድረው ዘንድ ለመላክ ወሰኑ፡፡ ኦቢም ይህንን ኃላፊነት በደስታ ተቀበለው፡፡ ብዙ አስደማሚ ሃሳቦች ስለነበሩት ይህ ሁነኛ ዕድል በተግባር ይተረጉማቸው ዘንድ የሚጠቅም ነበር፡፡ የተከታተለው ጥሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከሌሎች በሐይማኖታዊው ተልዕኮ ስር ካሉ ርዕሳነ መምህራን አጉልቶ ያወጣው «ወሳኝ መምህር» የሚል ስም በመስሪያ ቤቱ አስገኝቶለት ነበር፡፡ የአሮጌዎችንና በአብዛኛው ብዙም ያልተማሩትን ሰዎች ጠባብ አመለካከቶች ሲያወግዝ አይጣል ነው፡፡
«ልንጠቀምበት ይገባል፤ አይደል?» ሲል ወጣት ሚስቱን አስደሳቹን የዕድገቱን ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሰሙ ጠየቃት፡፡ «የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡» ስትል መለሰች፡፡ « ቆንጆ የአትክልት ስፍራዎች ይኖሩናል፣ እና ደግሞ ሁሉ ነገር ዘመናዊና ማራኪ ይሆናል …» በሁለት አመት የጋብቻ ቆይታችው «ለዘመናዊ አሰራሮች» ባለው ፍቅርና «ለአሮጌና ጊዜ ላለፈባቸው በትምህርት ሙያ ውስጥ ላሉና በኦኒሻ ገበያ ነጋዴ ሆነው ቢቀጠሩ ለሚሻላቸው ሰዎች» ባለው አግባብ ያልሆነ የትችት ፍቅር ሙሉ በሙሉ ተለክፋለች፡፡ ራሷን የወጣቱ ርዕሰ መምህር ተደናቂ ሚስት የትምህርት ቤቱም ንግስት አድርጋ መውሰድ ጀምራለች፡፡ በሷ ቤት የሌሎች አስተማሪዎች ሚስቶች የሷን ቦታ ይመቀኛሉ፡፡ በሁሉ ነገር ቀዳሚ ትሆናለች…
ከዚያም በድንገት ሌሎች ሚስቶች አይኖሩ ይሆናል የሚል ሃሳብ ብልጭ አለላት፡፡ በተስፋና ፍራቻ መሃል እየዋለለች ባለቤቷን በስጋት እያየች ጠየቀችው፡፡
«ሁሉም የስራ ባልደረቦቻችን ወጣትና ላጤ ናቸው፡፡» አላት እሷ በመጀመሪያ ባልተጋራችው የደስታ ስሜት፡፡ «መልካም ነገር ሆነልን ማለት ነው፡፡» ሲልም ቀጠለ፡፡
«ለምን?»
«ለምን? ሙሉ ጊዜና ጉልበታቸውን ለትምህርት ቤቱ ይሰጣሏ፡፡»
ናንሲ አቀረቀረች፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ስለአዲሱ ትምህርት ቤት ጥርጣሬ ገባት፤ ግን ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ትንሿ የግል ዕድለቢስነቷ የባሏን አስደሳች የወደፊት ህልም ልታጨልምበት አይገባም፡፡ በወንበሩ ላይ እንዳቀረቀረ ባሏን አየችው፡፡ ወገበ ጎባጣና የሚሰበር የሚመስል ነበር፡፡ ሆኖም አልፎ አልፎ በድንገት በሚያሳየው አካላዊ ጉልበት ሰዎችን ያስገርማል፡፡ በአሁኑ ተክለ ሰውነቱ ግን አካላዊ ጥንካሬው ሁሉ ገባ ገባ ባሉት አይኖቹ ውስጥ የተቀበረ ይመስላል፤ ለዓይኖቹ ጥልቅ ሰርጎ ገብ ሃይልም ሰጥቷቸዋል፡፡ ሃያ ስድስት አመቱ ቢሆንም ሲያዩት የሚመስለው ግን ሰላሳ ወይም ከዚያ በላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን አስቀያሚ አልነበረም፡፡
«ስለምን እያሰብክ ነው ማይክ?» አለች ናንሲ ከአፍታ በኋላ አንብባው የነበረውን የሴቶች መጽሔት በማስመሰል፡፡
«ትምህርት ቤት እንዴት እንደሚተዳደር ለነዚህ ሰዎች ለማሳየት በስተመጨረሻ እንዴት ያለ ትልቅ ዕድል እንዳገኘን እያሰብኩ ነበር፡፡» አላት፡፡
ስለ እውነት ከሆነ የንዱሜ ትምህርት ቤት ኋላቀር ነበር፡፡ አቶ ኦቢ ሙሉ ሕይወቱን ለስራው አውሎ ነበር፤ ሚስቱም እንዲሁ፡፡ ሁለት አላማዎች ነበሩት፡፡ ጥሩ ደረጃ ያለው ትምህርት ግድ የሚል ሲሆን የትምህርት ቤቱ ቅጽረ ግቢ ደግሞ ወደ ውበት አውድነት መቀየር ነበረበት፡፡ የናንሲ ምኞት የነበሩት የአትክልት ስፍራዎች ዝናቡ በሰዓቱ በመምጣቱ ሳቢያ ህያው ሆኑ፤ አበቡም፡፡የሚያማምሩ ደማቅ ቀይና ቢጫ አበቦች የተተከሉባቸው መደቦች በእንክብካቤ የተያዘውን የትምህርት ቤት ግቢ ከአቅራቢያው መንደር የቁጥቋጦ ጫካ ለይተው አወጡት፡፡
አንድ ምሽት ኦቢ ስራውን እያደነቀ ሳለ አንዲት ሽማግሌ ሴትዮ ከአቅራቢያው መንደር እያዘገሙ በትምሀርት ቤቱ ግቢ የቢጫዎቹንና ቀዮቹን አበቦች መደቦች እየረገጡ አቋርጠው ሲያልፉ በማየቱ የውርደት ስሜት ተሰማው፡፡ ሴትዮዋ ወዳቋረጡበት ስፍራ ሄዶ ቢመለከት ብዙም አገልግሎት የማትሰጥ ከመንደሩ ትምህርት ቤቱን አቋርጣ በሌላው አቅጣጫ ካለው የቁጥቋጦ ጫካ የምትወስድ የእግር መንገድ የጠፉ ምልክቶችን አገኘ፡፡
«መንደርተኞቹ ይህን መንገድ እንዲጠቀሙ መፍቀዳችሁ ይደንቀኛል፡፡ እንዲያው የማይታመን ነገር እኮ ነው በሉ፡፡» አለ ኦቢ በትምህርት ቤቱ ለሶስት አመታት ሲያስተምር ለቆየ አንድ መምህር፡፡ ራሱንም ነቀነቀ፡፡
«መንገዱ» አለ መምህሩ በይቅርታ ድምጽ «ለእነርሱ በጣም አስፈላጊ ይመስላል፡፡ ብዙም ባይጠቀሙበትም የመንደሩን የአምልኮ ስፍራ ከቀብር ቦታቸው ጋር ያገናኛል፡፡»
«እና ያ ታዲያ ከትምህርት ቤቱ ጋር ምን ያገናኘዋል?» ሲል ርዕሰ መምህሩ ጠየቀ፡፡
«አይ እሱን እንኳን አላውቅም» ሲል መምህሩ ትከሻውን በምን ቸገረኝ ስሜት ነቅንቆ መለሰለት፡፡ «ግን ከተወሰነ ጊዜ በፊት መንገዱን ልንዘጋው ሞክረን ትልቅ አለመግባባት መከሰቱን አስታውሳለሁ፡፡»
«ያ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ነው፡፡ አሁን ግን ማንም ሊጠቀምበት አይችልም፡፡» ብሎ ኦቢ ሄደ፡፡ ‹‹የመንግስት ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊውስ በመጪው ሳምንት ትምህርት ቤቱን ለመገምገም ሲመጣ ምን ያስባል? መንደርተኞቹ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በቁጥጥሩ ወቅት መማሪያ ክፍሉንም ለአረማዊ አምልኮ እንጠቀማለን ብለው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡››
መንገዱ ወደ ትምህርት ቤቱ በሚገባና በሚወጣባቸው ቦታዎች ላይ እንጨት ተተከለ፤ ከዚያም በእሾሃም ሽቦ ታጠረ፡፡
ከሶስት ቀናትም በኋላ አኒ የተባሉ የመንደሩ የሃይማኖት አባት ርዕሰ መምህሩን ማነጋገር እፈልጋለሁ ብለው መጡ፡፡ ጎብደድ ብለው የሚሄዱ ሽማግሌ ናቸው፡፡ በውይይታቸው መሃል አንዳች ጥሩ ነጥብ በሰነዘሩ ቁጥር አጽንዖት ለመስጠት መሬቱን መታ መታ የሚያደርጉበትን ወፍራም ምርኩዛቸውን ይዘው ነበር፡፡
‹‹ሰማሁ›› አሉ ከተለመደው የሰላምታ ልውውጥ በኋላ ‹‹ያባቶቻችን መንገድ በቅርቡ መዘጋቱን ሰማሁ…››
‹‹አዎን›› ሲል መለሰ አቶ ኦቢ፤ ‹‹ማንም ትምህርት ቤታችንን መንገድ እንደዲያደርገው አንፈቅድም፡፡››
‹‹እየውልህ ልጄ›› አሉ የሃይማኖት አባቱ ምርኩዛቸውን ወደ መሬት ዝቅ እያደረጉ፤ ‹‹ይህ መንገድ አንተም ሆንክ አባትህ ሳትወለዱ የነበረ ነው፡፡ የመንደሩ ሕይወት በሙሉ የተመሰረተው በሱው ላይ ነው፡፡ የሚሞቱ ዘመዶቻችን በመንገዱ አድርገው ነው የሚሰናበቱን፤ እንዲሁም የሞቱት አያቶቻችን ሳይቀሩ እየመጡ የሚጠይቁን በዚያው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሊወለዱ የሚመጡ ህጻናት የሚመጡበት መንገድ ነው…››
አቶ ኦቢ እርካታ የተሞላበት ፈገግታ በፊቱ ላይ እያሳየ አዳመጠ፡፡
‹‹የትምህርት ቤቱ አጠቃላይ ዓላማ›› አለ በመጨረሻ ‹‹እንደዚያ ያሉትን እምነቶች ማስወገድ ነው፡፡ የሞቱ ሰዎች የእግር መንገድ አያስፈልጋቸውም፡፡ ሃሳቡ በአጠቃላይ የማይሆን ነው፡፡ የኛ ኃላፊነት ልጆቻችሁን በእንደዚህ አይነቶቹ ሃሳቦች ላይ እንዲስቁ ማስተማር ነው፡፡››
‹‹የምትለው ትክክል ሊሆን ይችላል፤›› አሉ አረማዊው ቄስ፡፡ ‹‹እኛ ግን ያባቶቻችንን እምነት ነው የምንከተለው፡፡ መንገዱን ከከፈትክልን የምንጣላበት ምንም ነገር የለንም፡፡ እኔ ሁልጊዜ የምለው ነገር ቢኖር ጭልፊትም ትኑር አሞራም ትኑር ነው፡፡›› ቄሱ ለመሄድ ተነሱ፡፡
‹‹አዝናለሁ›› አለ ወጣቱ ርዕሰ መምህር፡፡ ‹‹ግን ትምህርት ቤቱ መተላለፊያ አይሆንም፡፡ ከሕጋችን ጋር አይሄድም፡፡ ሌላ መንገድ የትምህርት ቤታችንን ግቢ ሳይነካ ብትሰሩ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ መንገዱን ለመስራትም ልጆችም ልንሰጣችሁ እንችላለን፡፡ ለጥንቶቹ አባቶቻችሁ ተቀያሪ መንገዱ ብዙ ያስቸግራቸዋል ብዬ አላስብም፡፡››
‹‹የምለው ሌላ ነገር የለኝም›› አሉ ሽማግሌው ቄስ እውጭ ሆነው፡፡
ከሁለት ቀናት በኋላ በሰፈሩ የነበረች አንዲት ወጣት ሴት በወሊድ ምክንያት ሞተች፡፡ ወዲያውኑም አዋቂ ተጠይቆ በአጥሩ መታጠር የተሰደቡትን የጥንት አባቶች ለማስታገስ ከበድ ያለ መስዋዕት እንደሚያስፈልግ ተናገረ፡፡
በማግስቱ ጠዋት ኦቢ ከመኝታው ሲነሳ የሰራው ነገር ሁሉ ፈራርሶ አገኘው፡፡ የሚያማምሩት የአበባ መደቦች ወድመዋል፤ ይህም ደግሞ በአጨቃጫቂዋ መንገድ አጠገብ ብቻ ሳይሆን በግቢው በአጠቃላይ ነበር፤ አበቦቹ ተረጋግጠው ተበላሽተዋል፤ ከትምህርት ቤቱ ህንጻዎችም አንዱ ፈርሷል… በዚያች ዕለት ነጩ ተቆጣጣሪ ትምህርት ቤቱን ለመገምገም መጥቶ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ሁኔታ ላይ መጥፎ ማስታወሻ ለበላይ አካላት ጻፈ፡፡ በተለይም ‹‹በአብዛኛው ከአዲሱ ርዕሰ መምህር አቅጣጫውን የሳተ ወኔ የሚመነጭ በትምህርት ቤቱና በመንደርተኞቹ መካከል እያቆጠቆጠ ያለ የጎሳ ጦርነት የሚመስል ሁኔታ›› እንዳለ አጽንዖት ሰጥቶ ነበር የጻፈው፡፡
ለአስተያየትዎ: mezemirgirma@gmail.com, mezemir@yahoo.com

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...