2015 ኦገስት 29, ቅዳሜ

ቴሌቪዥን ሳሲት እንዴት እንደገባ




1988 .. የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የአማርኛ አስተማሪያችን፣ ሴት ናቸው፣ የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች የሚባሉት ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን የመሳሰሉት ናቸው የሚል ትምህርት ከመጽሐፉ ያስተምሩናል፡፡ ሬድዮንና ጋዜጣን ቀድሞም ስለምናውቃቸው መምህርታችንን ምንድን ናቸው ብለን አልጠየቅናቸውም ነበር፡፡ ስለ መጽሔት ምንነትም አስረዱን፤ ‹‹እንደጋዜጣ ያለ ነው አሉን›› ተረዳነው፡፡ አነስ ያለ መጽሐፍም ሊሆን ይችላል ብለን ጠረጠርን፡፡
ቴሌቭዥንን እንዴት ያስረዱን! ‹‹እንደ ሬድዮ ያለ ሆኖ ከሬድዮ ልዩነቱ ግን በዜናው ላይ የሚወራውን ነገር ልክ በዕውን እንዳለ አድርጎ የሚያሳይና ዜና አንባቢውን ጨምሮ የሚያሳይ ነው›› ተባልን፡፡ አሁንም አልገባንም፡፡ ‹‹መኪና ቢጋጭም ያሳያል፣ ዛፍም ሆነ ወንዝ፣ ቤትም ሆነ ተራራ ያሳያል›› ብለው አስረዱን፡፡ ይሁን ብለን ቅር እያለን አለፍነው፡፡ በትምህርት ዓለም የተረዳሁት ነገር ቢኖር አንድን እንግዳ ነገር ለማያውቀው ሰው በተለይ ለገጠር ተማሪ ማስረዳት አስቸጋሪ እንደሆነ ነው፡፡ በቃ አስተማሪው/ዋም አላወቁትም የማለት አባዜ ተማሪውን ሲጠናወተው ደቂቃም አይወስድበት፡፡ እኔ ራሴ የዚህ ወረርሽኝ ተጠቂ ነበርኩና ነው እንዲህ ማለቴ፡፡

እነ ኑሮ- ዘዴን፣ እነ እርሻን፣ እነ የመሳሰሉትንና አሁን የረሳኋቸውን ትምህርቶች ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥለን አራተኛን አልፈን አምስተኛ ክፍልን በአዲሱ የትምህርት ስርዓት ባዲስ መንፈስ ጀመርን፤ አለፍነውናም ስድስተኛ ገባን፡፡ ስድስተኛ ክፍልም ሳለሁ፣ 1990 .. መሆኑ ነው፣ እንግሊዝኛ መምህራችን ስለቴሌቪዥን መጠነኛ ማብራሪያ ሰጥተውን ነበር- ያው መጽሐፉ በሆነ መልኩ ስለሱ ስላነሳና እንድናውቀው ስላፈለገ፡፡ ‹‹አይ ዎች ቴሌቪዥን›› የሚል መጽሐፉ ላይ ያለ መሰለኝ፡፡ ልፉ ብሏቸው መምህር፣ እኛ ከሁለት አመትም በኋላ ይህ ነገር አላሳመነንም፣ አልተዋጠልንም፣ አልተገለጠልንም፤ ወይም ቀድሞ ነገር ሃሳቡንም አእምሯችን ውስጥ እንዲገባ አልፈቀድንለትም፡፡ አኔ ብዬ ላውራ መሰለኝ የሌላውን ተማሪ ስለማላውቅ፤ ግን ቢገባቸው ኖሮ በወቅቱ ያስረዱኝ ነበር ብዬ ነው፡፡




ፈረንጅ ሲመጣ እንደዚህ ነበር የሚጎበኘው፡፡

አንድ ቀን የከሰዓት ፈረቃ ሆነን ነው መሰለኝ አዲስ ወሬ መጣ፡፡ የምን ወሬ በሉ ብቻ! ‹‹ቴሌቭዥን ሳሲት ገባ!›› ይሉ ወሬ፡፡
ይህንም የሚያወሩት ልጆች ትናንትናውኑ ‹‹ቴሌቪዥኑን ባይናችን በብረቱ አይተናል፣ ወሬውንም ኮምኩመናል›› ባዮች ናቸው፡፡ ‹‹እኔ ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሰራ የት ነበርኩ?›› ብዬ ራሴን ጠየቅሁ፡፡ ‹‹ወይ እረኝነት፣ ወይ የሆነ ቦታ መልዕክት ተልኬ፣ ወይ የሆነ ቦታ ጨዋታዬን ስጫወት ይሆናል›› አልኩ መሰለኝ፡፡ ወሬውን በደንብ ‹‹እንዴት?›› ብዬ ሳላጣራ መምህር ገቡ መሰለኝ አርፌ ትምህርቴን ቀጠልኩ ወይም ቀጠልሁ፤ የቱ ይሆን ትክክሉ? አንድ ያዲሳባ ልጅ ጓደኛዬ ቢኖር ስቆ ያርምልኝ ነበር፣ ወይ ካዲሳባ ልጅ መራቅ፣ዳንኤል! ሰው ካልሄደና ካልሞተ አይመሰገንም ነው የተባለው? ይሄኔ አንተ ብትኖርልኝ የሰው መሳቂያ አልሆንም ነበር፡፡ ምነው አንድ ቀን እንኳን ‹‹ከተዋበች›› ጋር ሆናችሁ ሁለተኛይኸእንዳትል፤ አዲሳባይሄነው የሚባለው ብላችሁኝ፡፡ ለማንኛውም ባገሬ አማርኛ ላውራ፡፡አገሬ አትበል ብላችሁኝ ነበር ‹‹አገርህ ኢትዮጵያ እንጂ ሳሲት አይደለም፣ ሳሲት የትውልድ መንደርህ ነች! አትጥበብ!›› ያላችሁኝን አልረሳሁትም፤ ሆኖም ግን በቀና እዩልኝ፤ ክፋት አስቤ አይደለም፡፡ ሐገሬ አትዮጵያ መሆኗን ዲቪም እየሞላሁ ቢሆን አልረሳውም፤ ከናንተ ይነጥለኝ፡፡ (በነገራችን ላይ ዲቪ ላለመሙላት ለራሴ ቃል ገብቻለሁ - የናንተን አላውቅም፡፡) ወደ ቴሌቪዥኔ ልመለስ፡፡ ግን ግን በነካ እጄ እንዳዲሳበቦች ስለኢትዮጵያ የሚቆረቆርላት ይኖር ይሆን? ምናልባት ግን የተለያየ ህዝብ ተቀራርቦና አብሮ የመኖሩ ነገር፣ የትምህርትና የንቃተ-ህሊና ነገር ይሆናል ምክንያቱ፡፡ አዲሳበቦች አደንቃችኋለሁ፣ የትም ብሄድ አልረሳችሁም፡፡ ሌላውም እኮ ግን አለመማሩና አንድ ሐይማኖትና ቋንቋ ይዞ ተነጥሎ በመኖሩ ይሆናል እንጂ ክፋት አስቦ አይመስለኝም፡፡

ምን አለፋችሁ ወገኖቼ ወደ ወሬዬ ልመለስ፡፡ የአንደኛው ክፍለ ጊዜ ቲቸር ሲወጡ የሌላው ክፍለ ጊዜ ቲቸር ሲገቡ ለወሬው ጊዜ ጠፋ፡፡ ቁርጥራጭ ወሬዎች ይደርሱኝ ቀጥለዋል፡፡ አስተማሪ ከገቡ ማናባቱ ነው ቃል የሚተነፍሰው? ማንም! መምህር ሲገቡ ከመቀማጫህ ትነሳለህ፣ እንደምን ዋላችሁ ተማሪዎች ይላሉ፣ እንደምን ዋሉ መምህር እንላለን፡፡ (ከሰዓት ላይ ማለት ነው፡፡) መምህር ሲገቡ ከወንበር መነሳትን ለመጀመሪያና ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ ‹‹በኔ ጊዜ ሲሆን ተዉት! ምን ይነት ልማድ ነው ደሞ ይሄን ዓይነቱ!?›› ያሉን የስድስተኛ ክፍል የእንግሊዝኛ መምህራችን ሲሆኑ የእንግሊዝ ባህል አጥቅቷቸው ይሁን የኛ መነሳት አሳዝኗቸው የሚያውቁት አንድዬና እርሳቸው ብቻ ናቸው፡፡ ግምት ነው እንጂ እንግሊዞች መምህር ሲገባ ይነሱ አይነሱ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ወደፊት እዚያ ከተማርኩ ዐይቼ እመጣለሁ፡፡ ዛሬ ግን ወዳጄ፣ ታሪክ ተቀይሯል፡፡ ተማሪ ሆዬያው ሁሉም አይደለም፣ አልፎ አልፎ እንጂ፡፡ አንዳንዱ ታዲያ አለ ትሁት፣ ወረቀት ወይም የሆነ ነገር ሲሰጥህ በሁለት እጁ፣ ተንደርድሮ ማጥፊያህን ተቀብሎ ሰሌዳውንሃጫ በል አስመስሎአጥፍቶ፣ (ምን ይሆን ሃጫ በል? ማስታወቂያ ላይ ነው የሰማሁት- የጥርስ ህክምና ማስታወቂያ ላይ፤ ይኸ እንግሊዝኛ የሚሉ  ቋንቋ እኮ ነው አማርኛን ያስረሳኝ፣ ወይ ገብቶ አይገባ፣ ወይ ወጥቶ አይወጣ! እንትን ቋንቋ እኮ ነው! ያገሩ በሽታ ይሉታል አንድ የስነ-ልሳን ምሁር) ብቻ ጎበዙና አክባሪው ተማሪ ይቅናው በየሄደበት! ሰው ያክብረው፣ አስተማሪም የሆነ እንደሆነም ተማሪ ያክብረው! ቁጭ ብድግ ይበልለት፣ ይለሽለሽለት! ሌላውማ ያው   ፡፡ ልብ ይግዛ፡፡ መርካቶ አይጠፋም የሚገዛ ልብ፣ እዚያ ከሰው ነፍስ ሌላ ሁሉም አለ ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እስከዛሬ ያልገዛውን ልብ ግን ዛሬ ቢገዛው ሰዓቱ ያለፈበት ይመስለኛል፤ አይስማማውም፤ ይሰፋበታል፤ እስኪ ደግሞ ተረኛን ያትክን፡፡ ማነህ ባለ ሳምንት? መቼም ከሳምንት በላይ አይቆይ ከሰው ጋር፡፡ በነገራችን ላይ የኩላሊት ጥቁር ገበያ ደርቷል ይላሉ፤ ጠልፈው ሰዉን ኩላሊቱን ያወጣሉ አሉ፤ ተጠንቀቁ ኋላ! እንኳን ለ10 000 ዶላር ለአንድ መቶ ብርም የሰውን ሕይወት ያጠፋሉ፡፡ ኑሯቸውን ለመደጎም አንድ ኩላሊታቸውን የሚሸጡትን አይመለከትም፡፡

በረፍት ሰአት የቴሌቭዥን ወሬ ደራ፡፡ ደሞ እናንተ ደወል ተደውሎ ነው እንዴ ለወሬው መድራት! ለኔ በዚያን ጊዜ ቴሌቪዥን ማለት ቢያንስ ቤት ይችለዋል ተብሎ የማይታሰብ፣ ወደ አውላላ ሜዳ ላይ ሄዶ ትልቅ ድንኩዋን ተጥሎለት የሚታይ መሆን አለበት፡፡ ካልሆነማ ተራራውን፣ ሸንተረሩንን (የፈረደብሽ ሸንተረር፣ ምኑ እንደሚንሸታረር እሱ ይወቅ … ) ዛፉን፣ ወንዙን እንዴት ሊያሳየን ይችላል? ካልሆነማ ራስ ሳይጠና ጉተና ይሆንበታል ለቴሌቪዥን፡፡/ የቴሌቭዥን መጣን ወሬ ያመጡትን ልጆች ታዲያ ከበን እናዳምጣቸዋለን፡፡ ከወሬያቸው አያያዝ ታዲያ ጭራሹንም የቴሌቭዥን መጣ ወሬያቸውም ውሸት ነው ብዬ ደምድሜ ነበር፡፡ ለምን ብትሉ ቴሌቭዥኗ እቤት ውስጥ ገባች መባሉ ነበር ለኔ ውሸቱ፡፡ እንዴት ገባች ብንላቸው፣ ‹‹አንዱ ወዛደር ታቅፎዋት!›› ጉድ በል ሳሲት ቴሌቪዥን መጣ ጓዳ ሊከተት! ‹‹ሬዲዮ መሰለቻችሁ እንዴ!? ቴሌቭዥን እኮ አገር ሙሉ ታሳያለች›› አልኩዋቸው፡፡ ‹‹ሬዲዮ ወይም ቴፕ ይሆናል ያያችሁት›› ብላቸው ምንስ! ‹‹እኛ ያየነው ነን አንተ ያላየኸው ስለቴሌቭዥን የምታውቀው?›› ብለው አፈጠጡብኝ፡፡ በቃ 2 ዓመታት ያህል ሳስባት የነበረችውን ቴሌቭዥንን ናቅኋት፡፡ እንዲህ አድርጌ አወረደኩዋት ነው እምላችሁ፡፡ ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ፡፡ ‹‹ኧረ አይሆንም፤ መጣች የተባለው በትንሿ የህዝብ ላንድ ሮቨር፤ እቤት ገባች ተባለ - ለዚያውም በእቅፍ - ሕጻን ልጅ መሰለቻቸው እንዴ! ቢያንስ ላገር ምድሩ በከበደ መኪና፣ ሲሆን ሲሆንማ በመለኮታዊ ሐይል መጥቶ ካንዱ ተራራ ጎን ጉብ እንዲል ነው እኔ እምፈልገው፡፡ እኔ እምፈልገው ይሄን ነው! ካለዚያማ እንዴት ተራራን ያሳያል? እንዴት ወንዞች ሲፈሱ ያስጎበኛል? እንዴትስ ዛፍ ያሳያል? እሺ ይሁን በላንድ ሮቨሯ ይምጣ፣ ግድ የለኝም፤ ቢያንስ ቢያንስ ከበር መዝጊያ ማነስ አለበት ምንስ ቢሆን?›› ረፍት አልቆ ገባን፣ ተማርን፣ ወደ ቤታችን ሄድን፡፡ ተለቀቅን ነው የሚባለው እኛ አገር፡፡ ይችን አገርን አለቅም ብያለሁ ጥሎብኝ፡፡ ወይም እናት አገራችንንሐገር›፣ ትውልድ ቀያችንንአገር› እንበል መሰለኝ፡፡ የዕለት ተግባሬ የነበረው በነገራችን ላይ የጠዋት ፈረቃ ከሆንኩ የተገኘውን ቀማምሼ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ፤ ተምሬ እመለሳለሁ፣ ምሳዬን ቤት ያፈራውን በልቼ ወደ ስራ፡፡ ከብት ማገድን የመሳሰለው ስራ ማለት ነው፡፡ ልጅ ነኛ! አይ ሳሲት ዱሮ እኮ ስሟ ምሽግ ነበር አሉ - ጣሊያን መሽጎባት ስለነበረ ነው አሉ፡፡ የከተማ ጸባይ ያዘች በኋላ፡፡ ገበሬ ያልሆነና የማያርስ ሳሲት ላይ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ገጠር ነች ከተማ ታዲያ? ‹‹ሳሲት እገጠሩ ነህ? እከተማው?›› ይላል ሰው አንድን የሳሲት ሰው ወደ ደብረ ብርሃን፣ ሸዋሮቢት ወይም አዲሳባ ጉዳዩን ለመተኮስ ሄዶ ሲያገኘው፡፡ እውብኝ እስቲ እንጊዲህ፣ እንዲህ አይነት አነጋገር እያለ እንዴት ሳሲት ከተማ አይደለችም ይባላል? ‹‹ለማንኛውም እገጠሩም ሁን እከተማው ላባባ ስለት ይዘህልኝ ትሄዳለህ›› ሊለው ይችላል ከተሜው ለሳሲቴው፡፡ ስለ አባባ እናወራለን ሌላ ጊዜ፡፡ የፈጣሪ ታናሽ ወንድሙ ናቸው፡፡ …..

እንደገና ወደ ቴሌቪዥን እንመለስ፡፡ ይቅርታ ግን ጊዜዎን ተሻማሁዎ! በሁዋላ ግን ከትምህርት ቤት ስንለቀቅ እያሰብኳት ሄድኩኝ ቴሌቭዥንን፡፡ ‹‹እኔ ምን አገደደኝ ሬዲዮስ ብታክል፡፡ ሄጄ ማየት አለብኝ!›› አልኩ፡፡ እቤቴ ሄጄ ደብተሬን ወርውሬ በቴሌቪዥኑ ቤት ዙሪያ አንዣብብ ጀመር፡፡ የክፍል ጓደኞቼ ካወሩኝ ነገር የረሳሁትን ላውራችሁ፡፡ ‹‹ቴሌቪዥኗ መጣች- ወዛደር ታቅፏት፣ ከዚያ መምህር አዲሱ ተጠሩ (ነፍስ ይማር፣ ጎበዝ የህብረተሰብ መምህር ነበሩ - ያዲሳባ ልጅ- አጣዬ ወርደው ወባ ነው የቀጠፋቸው አሉ- ስንቱ በዚህ ሁኔታ ወላጅ ሳያስታምመው ተቀጥፎ ይሆን? ቤቱ ይቁጠረው- አይይይ የኛ ነገር!)፡፡ ሁለት አጣና መጣ፣ አንዱ ባንዱ ላይ ተቀጠለ፣ ሽቅብ ቆመ፣ አንቴና ተሰቀለበት፣ የአንቴናውን አቅጣጫ የሚያስተካክል ሰው አለ፡፡ ጄኔሬተር የሚሉ ነገር ትንዶቀዶቅ ገባች፤ የኤሌትሪክ ሽቦ ተቀጠለ፣ ሶኬት ተሰካ፣ ጥሩ የተባለው የምስል ጥራት እስኪመጣ ተጠበቀ፡፡ ከዚያም የኦሮሞ ፈረሰኛ ይጨፍር ገባ፡፡›› ቲቪ አለች ወደተባለበት ቤት ሄድኩ፡፡ ገና ስሄድ ከቤቱ በላይ የተሰቀለውን ነገር አየሁ፡፡ ‹‹ደግሞ አንተ ምን ትሆን? አንቴና ነበር ያሉኝ?›› ብዬ በቤቱ አካባቢ ከልጆች ጋር እየተጫወትኩ ቤቱ እስኪከፈት ጠበቅሁ፡፡ ትናንትናውኑ ቴሌቪዥን የታየው የመጀመሪያ ቀን ስለሆነ ለምርቃት ተብሎ በነጻ ነበር የሚል ወሬም ነግረውኛል መሰለኝ ባልንጀሮቼ፡፡ ተከፈተ! ተገባ፡፡ 14 እንች ቴሌቪዥን (ያልተከፈተ) ለመጀመሪያ ጊዜ አየሁ፡፡ የጄኔሬተርና የቴሌቪዥን መክፈት ስነ-ስርዓቱ ሊካሄድ ጊዜው ተቃርቧል፡፡ በጉጉት እጠብቀው የነበረውን ክስተት እዚያ ቤት ያስተናብር የነበረ ልጅ አጨናገፈብኝ፡፡ ማስታወቂያውን ተናገረ፡፡ ‹‹ቴሌቪዥኑን የሚያንቀሳቅሰው ጄኔሬተር የሚሰራው በቤንዚን ስለሆነ ለዛሬ ምሽት ሃምሳ ሳንቲም ትከፍላላችሁ፤ ማቲም ሳይቀር!›› አለ፤ መሰብሰብም ጀመረ፤ እኔም ሳንቲሙን ፍለጋ ወጣሁ፡፡ መጀመሪያ የሄድኩት በአቅራቢያው ያለ ሱቅ ነበር፡፡ ሻጩን ልጠይቀው ፈልጌ ሌሎች ትልልቅ ሰዎች ስላሉ ፈርቼ በቅርብ ርቀት እስኪሄዱልኝ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ አስር ዓመት የቆዩብኝ መሰለኝ፣ ‹‹ክፉዎች! ጉዳይ ኖሯቸው አይደል ተንኮላቸው አንጂ!›› አልኩ በሆዴ፡፡ ከስንት ጊዜ በኋላ ሲሄዱልኝ ሄጄ ጠየቅሁ፡፡ ‹‹ጋሼ፣ በናትህ ቴሌቪዥን ለማያ ሽልንግ አበድረኝ፤ እቤቴ ብር አለኝ ግን አሁን ከሄድኩ ‹የት ነው በዚህ ምሽት የምትሄደው› ተብዬ እንዳልቀር ነው፡፡›› ‹‹ላንተ የሚሻልህ ትምህርትህን ብትማር ነው፤ የቤት ስራም የለብህ እንዴ?›› ብሎ ትርፍ ንግግር ተናገረኝ፡፡ ትልቅ ሰው ስለሆነ ነው ይህን መምከሩ፡፡ በበሩ ቀዳዳ እንዳላይም ሌሎች ልጆች ስለሞሉት በተስፋ መቁረጥ ወደቤቴ ሄድኩ፡፡ ሳላለቅስ እቀራለሁ! ……………………

ይሄ ሁሉ አልፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ቴሌቪዥን ሳይ ግን ምን እንደተከሰተ ረሳሁት - ራሴን ስቼ ይሆን እንዴ? ከእንግዲህ፣ ቆይቶ ሌላ ቀን ካየኋቸው ዝግጅቶች ውስጥ አንዳንዶቹን ላውራ - በዚያችው በፈረዳባት 14 አንች ቲቪ- ዛሬማ 14 አንች ድንቢጥ ልላትም እችላለሁ ውለታዋን ካልረሳሁ፡፡ ከሁለት፣ ከሶስት፣ ከአራት፣ ከአምሰትም ለሚበልጥ ጊዜ ያየሁት 120 ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ ባልሳሳት የስፔንና የናይጀሪያን መሰለኝ የአለም ዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያንም አይቻለሁ፡፡ የዋንጫ ጨዋታንማ ማን ያገኛታል? ወይ የመንግስት ሰራተኛ ነው፤ ወይ ልጁ ነው፤ ወይ ባለ ሱቅ ነው፤ ዞሮ ዞሮ የዋንጫ (የመጠጫው) ተጠቃሚው ነው፡፡ የስቅለትን ፕሮግራም ለማየት የገባሁበትን ወሬ በደንብ ስለማስታውሰው ላውራው፡፡ ‹‹ላውራው አትበሉ ልጻፈው ነው ነው የሚባለው፤›› የሚሉ የስነ ጽሑፍ መምህር ነበሩን - አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሐገራቸው አሰናብቷቸዋል፡፡ (ከአበሾቹ መምህራን በዕውቀት እጅግ ስለሚልቁ፤ በተንኮል ተባረሩ አሉ) - ሕንዳዊ ናቸው - ሕንዳዊ ናቸው ማለቴ እንደ ጉራ እንዳይቆጠርብኝ፡፡ ሕንድ አስተምሮኛል አለ ተብዬ እንዳልወቀስ ማለቴ ነው፡፡
አንድ ብሬን ጨክኜ አውጥቼ የስቅለት አርብ ነው መሰለኝ ፊልም ለማየት እቴሌቪዥኑ ቤት መሄድ (ላለማየት ብለው ይሻላል)፡፡ ካንድ ሁልጊዜ ከምላላክለት የመንግስተ ሰራተኛ ጎን ተቀምጬ ቴሌቪዥኔን ማየት፤ ቴሌቪዥናቸውን ብል ይሻላል - የነሱ ልጅ ብሆን ብሎ ያልተመኘና ቴሌቪዥኔ ማለትን ያልናፈቀ የሳሲት ልጅ እውን ይኖር ይሆን? ከኖረ እሱ/ ቴሌቪዥን ለማየት ያልደረሰ/ ህጻን ልጅ ነው/ች፡፡ ወደ 4፡00 ሰዓት ላይ አመጡታ ያንን ውጧቸውን፡፡ ‹‹በቤንዚን ስለሚሰራ ጨምሩ›› ማለት መጣ፡፡ አንድ ብር ከፍለን ገብተን ሌላ አንድ ብር ጨምሩ ማለታቸው አያናድድም? ያበግን ነበር፡፡ ‹‹በል ጋሽ እንትና ደህና እደር ወደቤቴ ልሂድ›› አልኩት አብሬው የተቀመትኩትን ሰው፡፡እንዴ ምነው?›› ሲለኝ ‹‹አይ የምጨምረው ብር የለኝም›› አልኩት፡፡ የኔ ምርቃት ሳይሆን አይቀርም ያበለጸገው አሁን ቢጠሩት አይሰማም፡፡ ‹‹አንተ ጎበዝ ልጅ አይደለህም እንዴ? ታዛዤ አይደለህም እንዴ? በል ቁጭ በልና እይ፤ እኔ እከፍልልሃለሁ›› አለኝ፡፡ ጋሽ ማን እንደሆንክ ታውቀዋለህ፤ አሁንም የሰው መውደድ ይስጥህ፡፡ ያበላ አይረሳ! የዋለ አይረሳ! ለኔ ደጌ ነው፡፡

ሲጠበቅ ሲጠበቅ የአማርኛው ዝግጅት አልፎ የእንግሊዝኛው ሳይሆን አይቀርም ጀመረ፡፡ ሌላም ታላቅ ፊልም ወይም ሌላ ዝግጅት ተጀመረ መሰለኝ፡፡ በቃ የስቅለቱ ፊልም ቀርቷል ተባለ ተበተንን፡፡
ጊዜው ሲሄድማ እኛ ቤት አምፖል ገባ እላችኋለሁ፡፡ ማጥናት ሆነ፣ የቤት ስራ መስራት፡፡ አንዳንድ ቀን ይደክመኝና ነው መሰለኝ የቤት ስራዬንም ሳልሰራ የመብራቱም ማጥፊያው ሰአት 415 ሳይደርስ እተኛለሁ፡፡ በማግስቱ ወዳጄ፣ ተነስ ይባላላ የቤት ስራ ያልሰራ፡፡ አስር አስሬን ጠጥቼ የምገባው ስንት ቀን ነበር፡፡ መብራቱ የሚታዘዘው ከማዕከል መሰለኝ፤ እኛ ቤት ማብሪያ ማጥፊያ ይኑር አይኑር አላስታውስም፤ የነበረ ግን አይመስለኝም፡፡ 15 ብር ሳይሆን አይቀርም ይከፈል የነበረው፡፡ ባለ ፍሎረሰንቶች 25 ብር - በብዛት ንግድ ቤቶች ነበሩ፡፡ ‹‹ጠሐይ ይውጣላቸው፤ ጠሐይ አስመሰሏት አገሪቱን - ባለ ጀለሜተሮቹ›› ይል ነበር ባልቴቱ ሁሉ፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ፡፡ ይህ ሁሉ 1990 እና ከዚያ በፊት ወሬ ነው፡፡

2001 .. አስተማሪ በሆንኩ በሁለት አመቱ ለሳሲት የመጀመሪያው የሆነውን ሳተላይት ዲሽ አስገባሁ፡፡ የመጀመሪያ ለመሆኑ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ አይደለም የሚል ወንድ ካለ ይሞግተኝ፤ ሴት ልትሆንም ትችላለች ለነገሩ፡፡ ምን ይታወቃል ወደፊት ከሳሲት የመጀመሪያው ወጣት የህዝብ እንደራሴ ሆኜ መልሼ የምወደውን ያዲሳባ ውሃ እጠጣ ይሆናል፡፡ ያዲሳባ ውሃ ልዩ ነው፡፡ ውሃ ካልሄደ አይመሰገንም፡፡ እሽግ ውሃን ያስናቃል ያዲሳባ ውሃ፡፡ እስቲ ደግሞ ልቀኝ፡፡

መስቀል አደባባይ ይሰቀል መስሎኝ
ቴሌቪዥን ጃን ሜዳ ይጎመር መስሎኝ
የሚከመር ነው ስል እንጦጦ ላይ ወጥቶ
የሚጠበው ነው ስል ስቴድየም ገብቶ
የረር ላይ ቁጭ ብሎ አገር ያየው ብዬ
ቀስተ ደመናውን የሚያክል ነው ብዬ
ይታቀፉት ኖሯል እንደነ አቡሽዬ
እንደ ሬዲዮ ያለ፣ ድንጋይ የማይበላ
ኖሯል ይህ ቴሌቪዥን አየሁት በኋላ፡፡
እቤቴ አለኝ አሁን ባለ 21 ኢንቹ
ከነዲሽ ከነምን ከነኮተቶቹ
ወይ ባለካርዱን ዲሽ አስገባ ይሆናል
አይሆንም አልልም የማይሆነው ሆኗል፡፡
እንደራሴ ሆኜ ልገባ እችላለሁ
እቴሌቭዥኑ ውስጥ ሆኜ አያችኋለሁ
ጠብቁኝ ሳሲቶች 2 ሰዓት ዜና
የሸንጎ ተሟጋች ይወጣኛልና፡፡
በየቤቶቻችሁ አወጋለሁና
እናንተም ቴሌቪዥን ገዝታችኋልና፡፡

ትንሽዬ ማስታወሻ፡- በአሁኑ ጊዜ አጠራሯ (2004 .. ጀምሮ) ሣሢት ታዳጊ ከተማ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በሰሜን ሸዋ መስተዳድር ዞን፣ በሞጃና ወደራ ወረዳ ምትገኝ በጣም አነስተኛ ከተማ ነች፡፡ አሁን መብራት ገብቷል፣ የቴሌቪዥኑም ቁጥር በጣም በዝቷል- 20 አይጠቅመውም፡፡ ዲሹም አምስትን ሳይዘል አይቀርም፡፡ ስለ ጊዜ ከተዜሙ አንዱን መርጣችሁ አድምጡልኝ- በምናብ፡፡
አመሰግናለሁ
አክባሪዎ
እርስዎም ስላደጉበት ሁኔታ ቢያወሩ እናነብልዎታለን፤ ጨከን ማለት ነው ዋናው ነገር፣ እኔ እርስዎ ዘንድ የሚደርስ ጽሁፍ እጽፋለሁ ብሎ ያሰበም ያለመም አልነበረም፡፡ ይህን ሁሉ መተየቡ፣ ማርቀቁና ማረሙ 6 ሰዓታት በላይ ፈጅቶብኛል ስላችሁ ካንጀቴ ነው፡፡ አሪፍ ተጨዋች ከሆንኩ አበረታቱኝ፤ ካልሆንኩም ገስጹኝ፤ mezemir@yahoo.com በመጠቀም፡፡ ኢትዮጵያና ወዳጆቿ ለዘላለም ይኑሩ!!!!!!!

2 አስተያየቶች:

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...