ማክሰኞ 18 ኦገስት 2015

የሙታን መንገድ


ደራሲ-ችንዋ አቼቤ (1930 - 2013)
መዘምር ግርማ እንደተረጎመው
የሚካኤል ኦቢ ምኞቶች የተሳኩለት አስቦት ከነበረው እጅግ ቀድመው ነበር፡፡ በጥር 1949 ዓ.ም የንዱሜ ማዕከላዊ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆኖ ተሾመ፡፡ ትምህርት ቤቱ ብዙጊዜ ኋላቀር ሆኖ ስለቆየ የሐይማኖታዊ ተልዕኮው ባለስልጣናት ወጣትና ጉልበቱ ያልተነካ ሰው ያስተዳድረው ዘንድ ለመላክ ወሰኑ፡፡ ኦቢም ይህንን ኃላፊነት በደስታ ተቀበለው፡፡ ብዙ አስደማሚ ሃሳቦች ስለነበሩት ይህ ሁነኛ ዕድል በተግባር ይተረጉማቸው ዘንድ የሚጠቅም ነበር፡፡ የተከታተለው ጥሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከሌሎች በሐይማኖታዊው ተልዕኮ ስር ካሉ ርዕሳነ መምህራን አጉልቶ ያወጣው «ወሳኝ መምህር» የሚል ስም በመስሪያ ቤቱ አስገኝቶለት ነበር፡፡ የአሮጌዎችንና በአብዛኛው ብዙም ያልተማሩትን ሰዎች ጠባብ አመለካከቶች ሲያወግዝ አይጣል ነው፡፡
«ልንጠቀምበት ይገባል፤ አይደል?» ሲል ወጣት ሚስቱን አስደሳቹን የዕድገቱን ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሰሙ ጠየቃት፡፡ «የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡» ስትል መለሰች፡፡ « ቆንጆ የአትክልት ስፍራዎች ይኖሩናል፣ እና ደግሞ ሁሉ ነገር ዘመናዊና ማራኪ ይሆናል …» በሁለት አመት የጋብቻ ቆይታችው «ለዘመናዊ አሰራሮች» ባለው ፍቅርና «ለአሮጌና ጊዜ ላለፈባቸው በትምህርት ሙያ ውስጥ ላሉና በኦኒሻ ገበያ ነጋዴ ሆነው ቢቀጠሩ ለሚሻላቸው ሰዎች» ባለው አግባብ ያልሆነ የትችት ፍቅር ሙሉ በሙሉ ተለክፋለች፡፡ ራሷን የወጣቱ ርዕሰ መምህር ተደናቂ ሚስት የትምህርት ቤቱም ንግስት አድርጋ መውሰድ ጀምራለች፡፡ በሷ ቤት የሌሎች አስተማሪዎች ሚስቶች የሷን ቦታ ይመቀኛሉ፡፡ በሁሉ ነገር ቀዳሚ ትሆናለች…
ከዚያም በድንገት ሌሎች ሚስቶች አይኖሩ ይሆናል የሚል ሃሳብ ብልጭ አለላት፡፡ በተስፋና ፍራቻ መሃል እየዋለለች ባለቤቷን በስጋት እያየች ጠየቀችው፡፡
«ሁሉም የስራ ባልደረቦቻችን ወጣትና ላጤ ናቸው፡፡» አላት እሷ በመጀመሪያ ባልተጋራችው የደስታ ስሜት፡፡ «መልካም ነገር ሆነልን ማለት ነው፡፡» ሲልም ቀጠለ፡፡
«ለምን?»
«ለምን? ሙሉ ጊዜና ጉልበታቸውን ለትምህርት ቤቱ ይሰጣሏ፡፡»
ናንሲ አቀረቀረች፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ስለአዲሱ ትምህርት ቤት ጥርጣሬ ገባት፤ ግን ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ትንሿ የግል ዕድለቢስነቷ የባሏን አስደሳች የወደፊት ህልም ልታጨልምበት አይገባም፡፡ በወንበሩ ላይ እንዳቀረቀረ ባሏን አየችው፡፡ ወገበ ጎባጣና የሚሰበር የሚመስል ነበር፡፡ ሆኖም አልፎ አልፎ በድንገት በሚያሳየው አካላዊ ጉልበት ሰዎችን ያስገርማል፡፡ በአሁኑ ተክለ ሰውነቱ ግን አካላዊ ጥንካሬው ሁሉ ገባ ገባ ባሉት አይኖቹ ውስጥ የተቀበረ ይመስላል፤ ለዓይኖቹ ጥልቅ ሰርጎ ገብ ሃይልም ሰጥቷቸዋል፡፡ ሃያ ስድስት አመቱ ቢሆንም ሲያዩት የሚመስለው ግን ሰላሳ ወይም ከዚያ በላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን አስቀያሚ አልነበረም፡፡
«ስለምን እያሰብክ ነው ማይክ?» አለች ናንሲ ከአፍታ በኋላ አንብባው የነበረውን የሴቶች መጽሔት በማስመሰል፡፡
«ትምህርት ቤት እንዴት እንደሚተዳደር ለነዚህ ሰዎች ለማሳየት በስተመጨረሻ እንዴት ያለ ትልቅ ዕድል እንዳገኘን እያሰብኩ ነበር፡፡» አላት፡፡
ስለ እውነት ከሆነ የንዱሜ ትምህርት ቤት ኋላቀር ነበር፡፡ አቶ ኦቢ ሙሉ ሕይወቱን ለስራው አውሎ ነበር፤ ሚስቱም እንዲሁ፡፡ ሁለት አላማዎች ነበሩት፡፡ ጥሩ ደረጃ ያለው ትምህርት ግድ የሚል ሲሆን የትምህርት ቤቱ ቅጽረ ግቢ ደግሞ ወደ ውበት አውድነት መቀየር ነበረበት፡፡ የናንሲ ምኞት የነበሩት የአትክልት ስፍራዎች ዝናቡ በሰዓቱ በመምጣቱ ሳቢያ ህያው ሆኑ፤ አበቡም፡፡የሚያማምሩ ደማቅ ቀይና ቢጫ አበቦች የተተከሉባቸው መደቦች በእንክብካቤ የተያዘውን የትምህርት ቤት ግቢ ከአቅራቢያው መንደር የቁጥቋጦ ጫካ ለይተው አወጡት፡፡
አንድ ምሽት ኦቢ ስራውን እያደነቀ ሳለ አንዲት ሽማግሌ ሴትዮ ከአቅራቢያው መንደር እያዘገሙ በትምሀርት ቤቱ ግቢ የቢጫዎቹንና ቀዮቹን አበቦች መደቦች እየረገጡ አቋርጠው ሲያልፉ በማየቱ የውርደት ስሜት ተሰማው፡፡ ሴትዮዋ ወዳቋረጡበት ስፍራ ሄዶ ቢመለከት ብዙም አገልግሎት የማትሰጥ ከመንደሩ ትምህርት ቤቱን አቋርጣ በሌላው አቅጣጫ ካለው የቁጥቋጦ ጫካ የምትወስድ የእግር መንገድ የጠፉ ምልክቶችን አገኘ፡፡
«መንደርተኞቹ ይህን መንገድ እንዲጠቀሙ መፍቀዳችሁ ይደንቀኛል፡፡ እንዲያው የማይታመን ነገር እኮ ነው በሉ፡፡» አለ ኦቢ በትምህርት ቤቱ ለሶስት አመታት ሲያስተምር ለቆየ አንድ መምህር፡፡ ራሱንም ነቀነቀ፡፡
«መንገዱ» አለ መምህሩ በይቅርታ ድምጽ «ለእነርሱ በጣም አስፈላጊ ይመስላል፡፡ ብዙም ባይጠቀሙበትም የመንደሩን የአምልኮ ስፍራ ከቀብር ቦታቸው ጋር ያገናኛል፡፡»
«እና ያ ታዲያ ከትምህርት ቤቱ ጋር ምን ያገናኘዋል?» ሲል ርዕሰ መምህሩ ጠየቀ፡፡
«አይ እሱን እንኳን አላውቅም» ሲል መምህሩ ትከሻውን በምን ቸገረኝ ስሜት ነቅንቆ መለሰለት፡፡ «ግን ከተወሰነ ጊዜ በፊት መንገዱን ልንዘጋው ሞክረን ትልቅ አለመግባባት መከሰቱን አስታውሳለሁ፡፡»
«ያ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ነው፡፡ አሁን ግን ማንም ሊጠቀምበት አይችልም፡፡» ብሎ ኦቢ ሄደ፡፡ ‹‹የመንግስት ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊውስ በመጪው ሳምንት ትምህርት ቤቱን ለመገምገም ሲመጣ ምን ያስባል? መንደርተኞቹ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በቁጥጥሩ ወቅት መማሪያ ክፍሉንም ለአረማዊ አምልኮ እንጠቀማለን ብለው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡››
መንገዱ ወደ ትምህርት ቤቱ በሚገባና በሚወጣባቸው ቦታዎች ላይ እንጨት ተተከለ፤ ከዚያም በእሾሃም ሽቦ ታጠረ፡፡
ከሶስት ቀናትም በኋላ አኒ የተባሉ የመንደሩ የሃይማኖት አባት ርዕሰ መምህሩን ማነጋገር እፈልጋለሁ ብለው መጡ፡፡ ጎብደድ ብለው የሚሄዱ ሽማግሌ ናቸው፡፡ በውይይታቸው መሃል አንዳች ጥሩ ነጥብ በሰነዘሩ ቁጥር አጽንዖት ለመስጠት መሬቱን መታ መታ የሚያደርጉበትን ወፍራም ምርኩዛቸውን ይዘው ነበር፡፡
‹‹ሰማሁ›› አሉ ከተለመደው የሰላምታ ልውውጥ በኋላ ‹‹ያባቶቻችን መንገድ በቅርቡ መዘጋቱን ሰማሁ…››
‹‹አዎን›› ሲል መለሰ አቶ ኦቢ፤ ‹‹ማንም ትምህርት ቤታችንን መንገድ እንደዲያደርገው አንፈቅድም፡፡››
‹‹እየውልህ ልጄ›› አሉ የሃይማኖት አባቱ ምርኩዛቸውን ወደ መሬት ዝቅ እያደረጉ፤ ‹‹ይህ መንገድ አንተም ሆንክ አባትህ ሳትወለዱ የነበረ ነው፡፡ የመንደሩ ሕይወት በሙሉ የተመሰረተው በሱው ላይ ነው፡፡ የሚሞቱ ዘመዶቻችን በመንገዱ አድርገው ነው የሚሰናበቱን፤ እንዲሁም የሞቱት አያቶቻችን ሳይቀሩ እየመጡ የሚጠይቁን በዚያው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ሊወለዱ የሚመጡ ህጻናት የሚመጡበት መንገድ ነው…››
አቶ ኦቢ እርካታ የተሞላበት ፈገግታ በፊቱ ላይ እያሳየ አዳመጠ፡፡
‹‹የትምህርት ቤቱ አጠቃላይ ዓላማ›› አለ በመጨረሻ ‹‹እንደዚያ ያሉትን እምነቶች ማስወገድ ነው፡፡ የሞቱ ሰዎች የእግር መንገድ አያስፈልጋቸውም፡፡ ሃሳቡ በአጠቃላይ የማይሆን ነው፡፡ የኛ ኃላፊነት ልጆቻችሁን በእንደዚህ አይነቶቹ ሃሳቦች ላይ እንዲስቁ ማስተማር ነው፡፡››
‹‹የምትለው ትክክል ሊሆን ይችላል፤›› አሉ አረማዊው ቄስ፡፡ ‹‹እኛ ግን ያባቶቻችንን እምነት ነው የምንከተለው፡፡ መንገዱን ከከፈትክልን የምንጣላበት ምንም ነገር የለንም፡፡ እኔ ሁልጊዜ የምለው ነገር ቢኖር ጭልፊትም ትኑር አሞራም ትኑር ነው፡፡›› ቄሱ ለመሄድ ተነሱ፡፡
‹‹አዝናለሁ›› አለ ወጣቱ ርዕሰ መምህር፡፡ ‹‹ግን ትምህርት ቤቱ መተላለፊያ አይሆንም፡፡ ከሕጋችን ጋር አይሄድም፡፡ ሌላ መንገድ የትምህርት ቤታችንን ግቢ ሳይነካ ብትሰሩ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ መንገዱን ለመስራትም ልጆችም ልንሰጣችሁ እንችላለን፡፡ ለጥንቶቹ አባቶቻችሁ ተቀያሪ መንገዱ ብዙ ያስቸግራቸዋል ብዬ አላስብም፡፡››
‹‹የምለው ሌላ ነገር የለኝም›› አሉ ሽማግሌው ቄስ እውጭ ሆነው፡፡
ከሁለት ቀናት በኋላ በሰፈሩ የነበረች አንዲት ወጣት ሴት በወሊድ ምክንያት ሞተች፡፡ ወዲያውኑም አዋቂ ተጠይቆ በአጥሩ መታጠር የተሰደቡትን የጥንት አባቶች ለማስታገስ ከበድ ያለ መስዋዕት እንደሚያስፈልግ ተናገረ፡፡
በማግስቱ ጠዋት ኦቢ ከመኝታው ሲነሳ የሰራው ነገር ሁሉ ፈራርሶ አገኘው፡፡ የሚያማምሩት የአበባ መደቦች ወድመዋል፤ ይህም ደግሞ በአጨቃጫቂዋ መንገድ አጠገብ ብቻ ሳይሆን በግቢው በአጠቃላይ ነበር፤ አበቦቹ ተረጋግጠው ተበላሽተዋል፤ ከትምህርት ቤቱ ህንጻዎችም አንዱ ፈርሷል… በዚያች ዕለት ነጩ ተቆጣጣሪ ትምህርት ቤቱን ለመገምገም መጥቶ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ሁኔታ ላይ መጥፎ ማስታወሻ ለበላይ አካላት ጻፈ፡፡ በተለይም ‹‹በአብዛኛው ከአዲሱ ርዕሰ መምህር አቅጣጫውን የሳተ ወኔ የሚመነጭ በትምህርት ቤቱና በመንደርተኞቹ መካከል እያቆጠቆጠ ያለ የጎሳ ጦርነት የሚመስል ሁኔታ›› እንዳለ አጽንዖት ሰጥቶ ነበር የጻፈው፡፡
ለአስተያየትዎ: mezemirgirma@gmail.com, mezemir@yahoo.com

2 አስተያየቶች:

  1. ይህን ታሪክ ከወደዳችሁት አስተያየት እንድትሰጡኝና የእንግሊዝኛውንም ቅጂ Dead Men’s Path – Chinua Achebe ብላችሁ ዳውንሎድ በማድረግ እንድታነቡት እጋብዛችኋለሁ፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. በርታ መዜ፡፡ ያንተ ጥረት እየጨመረ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...