2016 ፌብሩዋሪ 23, ማክሰኞ

የሌሎችን ግጥም ለራስ ሃሳብ በሰበዝነት ስለመጠቀም




ቀጥሎ የምታነቧቸው ከበዕውቀቱ ስዩም አዲስ መጽሐፍ፣ ከአሜን ባሻገር፣ ላይ ያገኘኋቸው ግጥሞች ናቸው፡፡ ግጥሞቹ በአብዛኛው የሕዝብ ሲሆኑ አንዳንድ በግለሰብ ገጣሚያን የተደረሱም አሉባቸው፡፡ ለአንባቢ በጥሩ ሁኔታ ሊገቡ የሚችሉት ግን በአውዳቸው ነው፡፡
የሌሎች ሰዎችን ግጥም እንደሃሳብ ማጎልበቻ አድርጎ በመጠቀም በዕውቀቱ ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር ተመሳስሎብኛል፤ ተስፋዬም የማስታወሻዎቹን እያንዳንዷን ምዕራፍ በሌሎች ገጣሚያን ግጥም መጀመሩን ልብ ይሏል፡፡ አስተያየት ካላችሁ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡

አንች ወዲያ ማዶ፤ እኔ ወዲህ ማዶ
አንገናኝም ወይ፤ ተራራው ተንዶ

ልብሴንም ገፈፈው፤ ለበሰው እርዘኛ
በሬዬንም ነድቶ፤ አረደው ነፍጠኛ
ንጉሥ የቀረዎት፤ ጥቂት ዐማርኛ
ምነው ሆድ አይዘርፉ፤ ዐርፌ እንድተኛ

አዲስ አበባ ላይ፤ ወድቄ ብነሳ
የሰራ አካላቴ፤ ወርቅ ይዞ ተነሳ

የራበህም ብላ፤ የጠማህም ጠጣ፤
ከዚህ የተሻለ፤ ምንም ቀን አይመጣ፡፡
ላገኝ ነው በማለት፤ ሞትኩኝ በሰቀቀን፤
ሂዶ ሂዶ አለቀ፤ የምጠብቀው ቀን፡፡

እኔስ ሄጃለሁ፤ ላሊበላ
እንግዲህ ዲያብሎስ ምን ትበላ

እኔስ አላጣም ልክልክስ
እኔስ አላጣም ልክልክስ
ሮብ ለት ማለዳ ማንኪያ የምትልስ

ከደበበ ሰይፉ
የሮሀ መቅደሶች
ዝነኛ ሕንጻዎች፤ ከዐለት ማህጸን፤ ተፈልፍለው የወጡ፤
ነው አሉ በመላእክት፤ ከአርያም ወርደው፤ በሌሊት የመጡ

ከወዴት መጣሽ፣
ከወዴት ከወዴት
ፊትሽ ያበራል በሌት

እዛው ማርልኝ ያንን ግትቻ
ይዤው እንዳልመጣ የለኝ ማንገቻ

እዛው ማርልኝ ያችን እሳት
ይዣት አንዳልመጣ ነገሩ አያደርሳት

አጥንቱን ልልቀመው፤ መቃብር ቆፍሬ
ጎበናን ተሸዋ፤ አሉላን ተትግሬ
አሉላን ለጥይት፤ ጎበናን ለጭሬ
አሉላ ሴት ልጁን፤ ጥይት ሲያስተኩስ
ጎበና ሴት ልጁን፤ ሲያስተምር ፈረስ
አገሬ ተባብራ፤ ካረገጠች ርካብ
ነገራችን ሁሉ፤ የምቧይ ካብ
                የምቧይ ካብ
ትምህርት እንዲስፋፋ፤ ጉልበት እንዲጠና
አራቱ ጉባኤ ይዘርጉልንና
ጎባና ከፈረስህ ጋር ተነሥ እንደገና
                  ተነሥ እንደገና
ቀኝጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ

አመ ሠላሳ ቀን፤ ጎበና ባይጸና፤
ይካፈሉን ነበር፤ እነ ቱፋ ሙና

ይታመሳል አሉ ከፋና ቦረና፤
አማን አይደሉም ወይ እነ ራስ ጎበና፡፡

የሚሰጡት ቢያጡ፤ ከድፍን አበሻ
ለኡራኤል ሰጡት፤ የጎበናን ጋሻ

ወዝውዘው ወዝውዘው ጣሉት እንደ ዝሆን
ያው ወደቀላቸው ይበሉት እንደሆን

የባህታ ሀጎስ አጽም ይመስክር
ያየደገኛው ወንድ የአካለጉዛዩ ነብር
ይመስክር የህላይ ምድር
የነሳንጎኒቲ ጌታ ‹‹ጣሊያን ኀያል›› ናት ብሎ ሲል
የኢትዮጵያን የበላይነት በቡጢ ከንትሮ የሚያስምል
ጸጋዬ ገብረመድህን

አልቢን የያዘ ሰው፤ ይሁነኝ ውሽማ
መውዜር አይገዛም ወይ፤ ባሌ እንዲሆንማ

አመጣለሁ ብሎ፤ የካሳን ፈረስ
ሳያርመው ሞተ፤ የዘራውን ገብስ

ውሃ ለቀደመ
ግዳይ ለፈለመ

እቴጌ ጣይቱ እጅግ ተዋረደች
ሆቴሏን አቁማ እንጀራ ነገደች

ወይ ጉዴ
ላግባሽ አለኝ ነጋዴ

መልበስ አረንጓዴ
ማግባት ነው ነጋዴ

ብቻ አማራ አይደለም ኦሮሞ ቅልቅል
አንጠልጥሎት ሄደ ልቤን እንደቅል

አልተተከለም ወይ ታቦት ባገራችሁ
ቡልቡላ፣ ዱጉማ፣ ነጃራ ስማችሁ

ሁላችሁም ስሙኝ ከስላሙ እስካማራ
ጳጳሱ መነኩሴው ሰሞኛው ደብተራ

ከአውሮፓዎች እንማር በጣም እንበርታ
ታሪክ እንመርምር እናንብብ ጋዜታ
ቋንቋም እንማር እንመልከት ካርታ
እሱ ነው ለህዝቡ ዐይናቸው የፈታ

እንደ ጾመድጓ መልኳ የረቀቀው
እንደየሩሳሌም ወገቧ የረቀቀው

ዘወትር ብመክርም እሁድ እሁድ ለታ
አንድ ሰው አጣሁኝ የሚነቅፈኝ ጌታ
ወይም የሚለኝ እውነት ነው እንዴታ

አስተርጓሚ ሆኖ ሰሃን ሲፈገፍግ
አሁን ማን አገባው ከጨዋታ ከወግ
ታዛባ ሳይለይ ወድቆ ሳያድር ተፍግ
አክብረውህ ነበር ብለውህ ብላታ
በግር ብረት ገባህ ስለሆንህ ወስላታ
… ስትጠርግ ነበረ ስትደፋ ባሬታ
ትሰድብ ጀመረ የብርሃኑን ጌታ

ምላስህ መርዛም ነው ከንፈርህ መግላሊት
ሰባት ጊዜ ክደህ የለህም ሃይማኖት
ለሞኝ ይመስለዋል ገብረእግዚአብሔር ሲሉት
ዶሮውን ሳያርዱ ይገኛል መረቅ
ግጥም ገጠምሁ ይላል ዐማርኛ ሳያውቅ

ቤቴ
ገመና ከታቼ
ገመና መክተቱ ምንድነው ትርጉሙ
ወደ ጓዳ ገብቶ ዱቄትስ ቢቅሙ
አዝማሪት ጣዲቄ

ወግጂልኝ ዜማ፤ ወግጂልኝ ቅኔ
ወንዶች በዋሉበት፤ መዋሌ ነው እኔ

ሴቶ ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሄራ
ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ

እኔስ ደከመኝ፤ ተፋሁ አሞት
አዙር ተገኝ፤ በንጉሡ ሞት

አውድማው ይለቅለቅ፤ በሮችም አይራቁ
ቀድሞም ያልሆነ ነው፤ ውትፍትፍ ነው እርቁ

የኢትዮጵያ ልጅ፤ ቁርበት ደርባ
እንደ ሰሌዳ፤ ማቅ ተከናንባ
በወርቅ ድሪ ሐብል ፋንታ፤ አንገቷ ቀንበር ጠልቆላት
የዘፈን ቤቷ ፈርሶ
አደባባይዋ በለቅሶ
የትካዜ ጭጋግ ለብሶ
በሽቶ ማእዛና በጽጌረዳ ፈሳሽ ፋንታ
በገጽዋ ትቢያ ተነስንሶ

በሰማይ ላይ ሆነህ፤ ስታላግጥ በሰው
እናትህ ነደደች፤ ሐዘኑን ቅመሰው

ከሀበሻ ወዲህ፤ ከሀበሻ ወዲያ
ሰውንም ገረመው፤ እኔንም ገረመኝ
ዮሀንስ እግዜርን፤ ገድሎታል መሰለኝ

ዱብ ዱብ ይላል እንደበረዶ
በልጅነቱ በረሀ ለምዶ

ትመጫለሽ ብዬ ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ
የልጅነት ዐይኔ ሟሟ እንደ በረዶ

አመልክን በጉያህ
ስንቅህን ባህያህ

እንኳን እናቱ የወለደችው
አማቱ ኮራች የተጋባችው

አባትህ ለገዛ፤ አያትህ ለነዳ
አንተ ምን አግብቶህ ትከፍላለህ ዕዳ?

መሬት የእግዚአብሔር ናት ባለቤት የላትም
ኀይለኛ እየሄደ ያስገብራል የትም






2016 ፌብሩዋሪ 6, ቅዳሜ

ውዳሴ ፌስቡክ




ፌስቡክ ፌስቡክ አሉት ስሙን አሳንሰው
መሬትና ሰማይ የሚያተራምሰው
ከያሆ ይበልጣል ለተጠቀመው ሰው
ሃሳብን ናፍቆትን ፈጥኖ የሚያደርሰው
ከጠጅ ከጮማ አንጀት የሚያርሰው፡፡
ሻውል ፌስቡክ ሆዬ ምንኛ ያኮራል
ይህን ሁሉ ፍጥረት አውሎ ያሳድራል፡፡
ምን ብትል አሰብከው ዓለም ማጣመር
የጠፋን ማስገኘት ኮበሌን ማፋቀር፡፡
ለቡና ባትጠራኝ ይቅር ጎረቤቴ
በፌስቡክ ይረካል የወሬ ናፍቆቴ፡፡
ጌም ላይ ተሰክቼ የምውለው ሰውዬ
ቻት ልማዴ ሆኗል ፌስቡክ መጽናኛዬ፡፡
የዙከርበርግ እናት ኩሪ ይገባሻል
ልጅሽ ካጽናፍ አጽናፍ ሲያስወራ ያመሻል፡፡
የፈጠራ አድማሱ ሀብትን ማመንጨቱ
ዙከርበርግን ፌስቡክ ያሰኘዋል አንቱ፡፡
እረኛ ምናለ የሚለው ንጉሡ
እረኛን ፍለጋ ፌስቡክን ማሰሱ
አይቀርም መክፈሉ ለፌስቡክ ፎሊሱ፡፡
የፌስቡክ ደህንነት ስሙን የቀየረው
ጾታውና ፎቶው የሚያጠራጥረው
አዳሜን ሲያናዝዝ ሲያሳስት የሚውለው
ማን ምናለ ብሎ ዳኛን የሚጠራው
ፌስቡክ ባይኖር ኖሮ ምን ነበር እንጀራው?
አንዳንዱ፣ ሚስቱን አስተኝቶ እጮኛውን ትቶ
ቻት ላይ የሚያነጋው ለምን ይሆን ከቶ?
ጊዜዬን አቃጥዬ ስራዬን ዘንግቼ
ባህሌን ሸርሽሬ ቤቴን አናግቼ
በቻት ሱስ ናውዤ
ለፖስት ተቅበዝብዤ
ራሴን አሻሽጬ
ፈረንጅ አስበልጬ
ባህሩን ፌስቡክን ለምን እወቅሰዋለሁ
መዋኘት ድርሻዬ መሆኑን አውቃለሁ፡፡
ደብዳቤ ቢሞት ተተካ ፌስቡክ
የየቤቱን ጉድ የሚያዝረከርክ፡፡
የሚስትም አይደለም የጊዜም ቀማኛ
አገሩ ሚስቱ ነው ይሄ ታምረኛ
ሲጨንቀኝ መድረሻ ሳጣ
ከየጥጉ ዘመድ ስለሚያመጣ
ስለሚያዋኝ ስራዬ ብሎ
ስጦታ ልስጠው በቶሎ
ዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ከሰጠልኝ በጄ
ካልሆነ፣ ትንሽ ገንዘብ አስፈቅጄ
ለዙከርበርግ፣ ትምህርቱን ላቋረጠው ወዳጄ
ዲግሪ የምገዛለት ነኝ አዙዛ ፓሲፊክ ሄጄ፡፡
አበሻ ጉድ አለ ፈረንጅም ደነቀው
ያለ ፌስቡክ ውሎ እንዳያድር አወቀው፡፡
ቢቢሲ፣ ሲሲቲቪ፣ አልጀዚራ
በፌስቡክ ወሬ ሲዘራ
መንግስት፣ ማህበር፣ ነጋዴ
ከፌስቡክ ይጠፋል እንዴ?
ኢንተርኔት ፈረሱ
ኮምፒውተሩ ስልኩ ማስገሪያው ርስቱ
የንግግር ነጻነት ያለበት ደሴቱ
ይብላኝ ላልገባው ሰው፣ የፌስቡክን ነገር ሰው ዋ ስንቱ ዋ ስንቱ!!

2016 ፌብሩዋሪ 2, ማክሰኞ

የታዋቂዎችን የቀብር ስፍራዎች ይጎበኛሉ?




በሰሜን ሸዋ ያሉ መካነ - መቃብራት
በ2006 ዓ.ም. ጓደኞቼና እኔ በደብረሲና በመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የደራሲ ዳኛቸው ወርቁ አጽም ያረፈበትን መቃብር ቤት አይተን ስሜታችን እንዴት እንደተጎዳ! ተራ የገጠር መቃብር ቤት መሳይ እንጂ ለዳኛቸው የሚመጥን አልነበረም፡፡ በዓመቱ ተበራክተንና የባህል ማዕከሉን የጉብኝት ቡድን አባላት ይዘን እንደሄድን ግን መቃብር ቤቱ ታድሶና በተሻለ ሁኔታ ሐውልት ተሰርቶለት አየንና ተደሰትን፡፡ ከነበረው አንጻር ይህ ጥሩ መሻሻል ነው፡፡ በከተማው እምብርት ላይ ባለ ስፍራም የተሰራለትን ሐውልትና የተሰየመለትን አደባባይም አይተናል፡፡ የደራሲ ዳኛቸው ወርቁ ሚሌኒየም መታሰቢያ አደባባይ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ሲከበር የታነጸ ነው፡፡ 
በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ባለ አንድ ክፍል በመስታዎት ሳጥን የተቀመጠውን የአድዋውን ጀግና የፊታራውሪ ገበየሁን አጽም ጎብኝተን እንባ የተናነቀን በ2007 ዓ.ም. የካቲት 16 ቀን ነበር፡፡ ዘንድሮም ሂያጆች ነን፡፡ አስር ኪሎሜትር ገደማ ከመኖሪያ ከተማችን ከደብረ ብርሃን በእግራችን ሄደን ያየነው አጽም የመጣው ከአድዋ ሲሆን ፊታውራሪ ገበየሁ አድዋ ከተሰዉ በኋላ ሊመጣ የቻለው በህይወት እያሉ ‹‹ከጠላት ጋር ግንባር ለግንባር ስፋለም ከወደቅሁ አስከሬኔን ለትውልድ ስፍራዬ አብቁልኝ፤ ፈርቼ ወደ ቤቴ እየሸሸሁ ከኋላዬ ከተመታሁ ግን አስከሬኔን ትታችሁት ኑ›› ብለው በመናዘዛቸው ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን አድዋ ላይ ለኢትዮጵያ ከወደቁት ይልቅ ኢትዮጵያን ሲወጉ ለሞቱት የጣሊያን ግፈኛ ጄኔራሎች የበለጠ እውቅና ተሰጥቷል የሚል ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ ሐውልት መስራት ካሻንም ለእኛው ጀግኖች እንጂ ባህር ተሻግሮ ለመጣ ጠላት መሆን የለበትም፡፡ እስኪ ይቺን ነገር አድዋ ስሄድ አጣራለሁ፡፡ 
የማዕከላችን አባላት የጎበኙት ሌላው ስፍራ በሚዳ ወረሞ ወረዳ መራኛ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የአቡነ መልከጸዴቅ ገዳም ነው፡፡ አቡኑ በተቀበሩበት ስፍራ ገዳም መመስረቱ ስፍራው እንዲጎበኝ አድርጎታል፡፡ የዚህ ገዳም ነገር ሲነሳ ግን አንድ አነጋጋሪ ነገር ይታወሰኛል፡፡ እዚያ ያሉት ሳይፈራርሱ የተቀመጡት አስከሬኖች ያልፈራረሱት እውን ለቦታው በተሰጠው ጸጋ ነው ወይንስ በሆነ ሳይንሳዊ ምክንያት የሚል ክርክር ነበር፡፡ ውጤቱ ከምን እንደደረሰ አልሰማሁም፡፡
የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ስለት ተስሎ ከሰመረለት አጎቴ ጋር የአንድ ቀን የእግር መንገድ ተጉዤ ደብረሊባኖስን በጎበኘሁበት ጊዜ ብዙ መቃብሮችን አይቻለሁ፡፡ ከአንዱ ላይ ይህን ማንበቤን አስታውሳለሁ፡-
አበሻ ጉድ አለ ጣሊያን ወተወተ
አይነ ጥሩ ጀግና ቧያለው አባተ!!
ከሸዋ ውጪ
እንዴ በደብረብርሃን ዙሪያ ስላሉ የዝነኞች የቀብር ስፍራዎች ስትጽፍ የአጼ ዘርዓያዕቆብን ምነው ረሳኸው? ካላችሁኝ የእርሳቸው ዳጋ እስጢፋኖስ ይገኛል እላችኋለሁ፡፡ ይህ በጣና ደሴት ያለ ገዳም የታላላቅ ሰዎች አጽም አርፎበታል፡፡
አክሱም በሀገራችን የቀብር ስፍራዎችን በተሻለ ሁኔታ የያዘችና የምታስጎበኝ ከተማ ሳትሆን አትቀርም፡፡ የንጉሥ ባዜን፣ የንጉሥ ረምሃይ (ትልቁን የአክሱም ሐውልት ያሰሩት)፣ የአጼ ካሌብና ገብረመስቀል፣ ብሎም የንግስተ ሳባ ቤተመንግስትና መቃብር እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡ እስካሁን አክሱም ያልሄድን ሰዎች እነዚህን ስፍራዎች ለመጎብኘት ያብቃን፡፡ አንዴ እዚያ እንድረስ እንጂ በአምስት ብር ያንን ሁሉ ስልጣኔ መጎብኘት ይቻላል ብለውኛል፡፡ የአክሱሞቹ ጠንካራ ክርስቲያኖች በከተማዋ ላይ መንግስት ብዙም ጣልቃ የማይገባበት አስተዳደር ዘርግተዋል የሚሉ ነገር ሰምቻለሁና ብዙም ታሪክ እዚያ አለና አክሱምን ሳልጎበኝ ባልሞትኩ!
አዲስ አበባ (ሃንዱራ ኢትዮጵያ)
ንግድ ተባለ ትምህርት፣ አስተዳደር ተባለ ቤተክህነት፣ ያችው አዲስ አበባ ነች እናቷም አባቷም ለዚች አገር፡፡ ስለሆነም ይህ ጨዋታችን ያለእርሷ የትም የሚደርስልን አልመሰለኝም፡፡ ሸገር ላይ ያለውን ስርዓት አስመልክቼ የጠየቅኋቸው አንድ ለቤተክርስቲያን የቀረቡ ሰው እንደሚከተለው ምላሽ ሰጥተውኛል፡- ‹‹ሥላሴ ካቴድራል ለቤተመንግስትና ለጎብኚ ቅርብ በመሆኑ ይመስለኛል ታላላቅ ሰዎች የሚቀበሩበት፡፡ የሰዉ ልዩነት መፍጠር እንጂ ቤተክርስቲያን አንድ ነች፡፡ ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ ስለሚል በሰው ዘንድና ለሀገር አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎች በታላላቅ ካቴድራሎች ይቀበራሉ፡፡›› ለነገሩ ሥላሴ ካቴድራልም፣ አቡነ ዮሴፍም፣ ደብረ ሊባኖስም፣ ነይ ገደል በዓታም እኩል ናቸው፡፡
በሥላሴ ካቴድራል የታዋቂዎች ሥርዓተ-ቀብር ተፈጽሟል - የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን፣ የክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የሲልቪያ ፓንከርስት፣ የአጼ ኃይለሥላሴ (መጀመሪያ ተቀብረው ከነበረበት ወጥቶ) ለአብነት፡፡ ጸጋዬና ጥላሁን ከስራዎቻቸው የተወሰዱ ጥቅሶች በሐውልቶቻቸው ላይ ይገኛሉ፡፡ አይቻለሁ ይህን ስፍራ፡፡    



ስለ ቅዱስ ዮሴፍም ሰምቻለሁ፤ እኔ ሄጄ ባላየውም፡፡ በዚህ ስፍራ ከኦርቶዶክስ ተከታዮችም ሌላ እንደሚቀበር ሰምቻለሁ፡፡
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱና ንግስተ-ነገሥታት ዘውዲቱ የተቀበሩት በበዓታ ቤተክርስቲያን እንደሆነ ሰማሁ፡፡ አስተዳዳሪዎቹ ለማስጎብኘት እምብዛም ፈቃደኞች እንዳልሆኑ ሰምቻለሁ፡፡ ምን አልባት አጽሙ ይወሰድብናል የሚል ፍራቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ሚሊዮን ብር ይሸጣል አሉ አጽም፡፡ የዚያች የሉሲ እንዴት በእንክብካቤ ይያዝ እንደነበር!
ውጪ አገር
በጎብኚ ብዛትና ታዋቂነት የጂም ሞሪሰን፣ የማይክል ጃክሰንና የዊሊያም ሼክስፒር የቀብር ስፍራዎች ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ቦታ ይይዛሉ፡፡ የዊሊያም ሼክስፒር ሐውልት ላይ ከራሱ ስራ የተወሰደች ግጥም ተጽፋለች፡-
‹‹ወዳጄ ሆይ በኢየሱስ ይዤሃለሁ
ይቺን ቀብሬንስ አትንካብኝ
ሐውልቴን ካኖርክ መርቄሃለሁ
አጽሜን ብታፈልስ የእጅህን አግኝ››
የማይቀረው ዕዳ
በሕይወት ሳለን እንደ አገልጋይም ሆነ እንደ ልዑል ብንኖር ሞታችን እንደሆነ እርግጥ ነው፡፡
ስንቶች ካጠገባችን በሞት ተለዩን? አስታመን የቀበርናቸው፣ በአደጋ ያጣናቸው፣ የት እንደገቡም ሳንሰማ ጠፍተው የቀሩብንስ ስንት ይሆኑ? የስንቶችንስ ሞት በመሪር ሐዘን አስተናገድን? ከእናት ሞት፣ ከአባት ሞት፣ ከትዳር አጋር ሞት፣ ከልጅ ሞት፣ ከወንድም ወይም ከእህት ሞት … ከዚህ ሁሉስ የትኛው ያይላል? የሞተስ አረፈ፤ ይብላኝለት ለቋሚ!
አንዳንዱ ከውሃ ቀደታ እስከ እንጨት ሰበራ ወይም ከማድቤት እልፍኝ (ዓለም ማለት ያደገበት ቀዬ ብቻ መስላው)፣ ሌላው ከቶኪዮ ኒውዮርክ፣ እንደ አርምስትሮንግ አይነቱ ደግሞ ከጨረቃ መሬት ተመላልሶ ያልፋል፡፡ አስራሁለት ወልዶ ልጆቹ አልቅሰውለት የሚቀበር፣ ታሪክ ሰርቶ ወይም ታሪክ ተሰርቶበት የሚያልፍ፣ በዘረኞች ተገድሎ ዉሻ በልቶት ወይም በጅምላ መቃብር የሚጣልም አለ፡፡ ዱባይ ላይ ሰው የሚበላቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ ሌሎች በህይወት ይኖሩ ዘንድ ስለ ኩላሊታቸው የታረዱ ብሎም ያልፍልናል ብለው ሲሰደዱ የአሳነባሪ ሲሳይ የሆኑ ስንትና ስንት አሉ፡፡ በበኩሌ ጣር ሳያበዛብኝ በተፈጥሮ ሞት እልም ብል ይሻለኛል፡፡ አሟሟቴን አሳምረው ግን ጥሩ ጸሎት ይመስለኛል!




ከሕልፈተ-ሕይወት በኋላ ያለው ስርዓት በብዙ ማህበረሰቦች ዘንድ የተለያየ ነው፡፡ ሙታን እቃዎቻቸው አብረዋቸው የሚቀበሩበት፣ አንጀታቸው ተቆርጦ ከወጣ በኋላ የሚቀበሩበት፣ የሙታኑ መንፈስ እየተመላለሰ ይጠይቀናል ተብሎ የሚታንበት ሁሉ ባህል አለ፡፡ ተማሪዎቼን ጠይቄ አንዳንድ ነገር ነገሩኝ፤ ‹‹ወደ ሀረር መቃብር ላይ ገበሬ ከሆነ በሬ፣ ወታደር ከሆነ ጠመንጃ ይሳላል፡፡ በአንዳንድ ባህል ከቤት በላይ ሰው ይቀበራል፡፡ ግንዛት እንደሟቹ እድሜና ሁኔታ ይለያያል፡፡ የካህናትና የሚስቶቻቸው አስከሬን ቤተመቅደስ ገብቶ ይወጣል›› በማለት፡፡
ቤተክርስቲያናችን
ለእኔ በምትቀርበኝ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቀብር ስፍራዎች በአብዛኛው በአብያተክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ይገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ስለሙታንም ስለሕያዋንም ስለምትጸልይ አጽሙ ዘወትር ጸሎት በሚደረግበት ስፍራ፣ ማለትም በቤተክርስቲያን አቅራቢያ፣ ያርፋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ግን ቀብር አይፈጸምም፡፡
የቀብር ቤት ከተሰራ ለጸሎት የሚመጡ እንዲሁም መምህራንና ተማሪዎች ያርፉበታል፡፡ የእኔ አጥቢያ በሆነችው የማምየለኝ ማርያም ቤተክርስቲያን ጓሮ ሄዳችሁ ብታዩ አንዳንዱ አቅም ያለው ሐውልት አሰርቷል፤ ሌላው ደግሞ አፈር ነውና ካፈር ተመልሷል (ያው በሰሌን ተጠቅልሎ አፈር ተቆልሎበታል)፡፡ በቤተክርስቲያኗ ዙሪያ ባሉ ቀብር ቤቶች ውስጥ ያረፉም አሉ፡፡ ቀብር ቤቶቹ ውስጥ ሐውልት የለም፡፡ ኮረብታ ላይ ያለችው ቤተክርስቲያናችን ዙሪያዋ በቀብር ስለተሞላ እኔ የት እንደምቀበር አላውቅም፡፡ በአማራው አገር እንዴት ቦታ እንደጠበበ ልነግራችሁ የሚያስችለኝ አማርኛ የለኝም፡፡ ምንም ቢሆን ግን ከገረገራ ውጪ አልቀበርም፡፡ ከገረገራ ውጪ ማለት ቤተክርስቲያኗ ለቀብር ካዘጋጀችው ስፍራ ውጪ መሆኑ ነው፡፡ ዝም ብዬ ግን ሳስበው ገረገራ ኦሮምኛ ይመስለኛል - ገረ (ወደ) - ገራ (ሆድ)- ወደ መሬት ሆድ ነው ሁላችሁም የምትገቡት ለማለት፡፡
እዚህ ቤተክርስቲያን፣ ደብር ወይንም ገዳም ቅበሩኝ ካሉ በጠየቁት ስፍራ ኑዛዜያቸው ተጠብቆላቸው የሚቀበሩ አሉ፡፡ ራስ መስፍን ደብረ ሊባኖስ ላይ ያሳነጹትን ሐውልት እንዲጎበኙላቸው ጃንሆይን ሲጋብዟቸው ‹‹አይ መስፍን ሰራኸው እንጂ የት እንደምትቀበር ታውቀዋለህ ወይ?›› እንዳሏቸው ይነገራል፡፡ በስተመጨረሻ ግን ራስ መስፍን ከሰው ክብር ዝቅ ተደርገው እንደተቀበሩ ታሪክ ሲያስታውሰን ይኖራል፡፡ ስድሳዎቹ በቡልዶዘር ተምሶ አፈር ሲደፋባቸው አንድ ሆነ - የፈረንጆች ጥንስስ ነች አይደል ይቺ? የሸዋን ልሂቃን ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት የተቃጣች! እነዚያስ ዘመዶቼ ስላቸው የከረምኩት ሞጃዎች የት ይሆን የተቀበሩት? ፈረንጅ ልኳቸው ነው አሉ የጃንሆይን መንበር ያነቃነቁት፡፡ በቃ አፍሪካና ኢትዮጵያ እንዲህ ወጣው? የፈረንጅ እጁ ረጅም ነው፤ የእያንዳንዳችን ጎጆ ውስጥ ያለው ችግር የነሱ ነገር አለበት፡፡ አንድ ጓደኛዬ እንደሚለው ‹‹ይቺ አጠገቤ ያለችው ብርጭቆ ውሃ ብትፈስ የፈረንጅ እጅ አለበት›› ልል ምንም አልቀረኝ፡፡ ይህ ዘረኝነት ሳይሆን ራስን መከላከል ነው! ፍርድ ቤት አልሞት ባይ … ይል የለ፡፡   
ከእህት ቤተክርስቲያናችን
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ልምድ ቅዱሳን ሲሞቱ መቃብራቸው መንበረ ታቦት ይሆናል፡፡ ክብሩ ተካ መጎብኘት የምትፈልጋቸው የታዋቂ ሰዎች የቀብር ስፍራዎች የትኞቹ ናቸው? ብዬ ጠይቄው የአሲዚውን ቅዱስ የፍራንሲስኮስን (ኢጣሊያ)፣ የቅዱስ አንቶኒዮስን (ፈረንሳይ)፣ እንዲሁም የቅዱስ ጴጥሮስን (ቫቲካን) ብሎኛል፡፡ እኔ በበኩሌ የልዑል ዓለማየሁን የቀብር ስፍራ ብጎበኝ ደስተኛ ነኝ፡፡ አጽሙ እንግሊዝ በተከበረበት ይቀመጥ፤ እባካችሁ ይምጣ አትበሉ፡፡
የቀብር ቦታዎች ቅጥ ይያዙልን
ሰንበቴ ያለው ሰንበቴው ባለበት ቤተክርስቲያን በማህበር ህንጻ ይሰራል፡፡ ህንጻው ለቤተክርስቲያን ገቢ ማስገኛ ይሆንና ምድሩ ለማህበረተኞቹ መቀበሪያ ይሆናል፡፡ አንዲት ፉካም በአንድ ሰው መቅበሪያነት ሰባት ዓመት ታገለግልና ከዚያ በኋላ ያ አጽም ተለቅሞ ሌላ ሰው ይቀበርባታል፡፡ አንዲት እናት እዚህ ከጋራ መኖሪያ ቤቱ ማዶ ቤተክርስቲያኑ ካሰራው ህንጻ ጥግ ጥግ ላይ ያሉትን ፉካዎች አይተው ወደ መኖሪያችን ዘወር ብለው የሚከተለውን ተቀኙ አሉ፡- ‹‹በኮንዶሚኒየም ይኖራሉ፤ በኮንዶሚኒየም ይቀበራሉ፡፡››
የዩኒቨርሲቲ መምህርስ?  
እኔ እስከማውቀው ድረስ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሲሞቱ ነው ከመስሪያ ቤት የሚቀሩት፡፡ ቀን ማስተማር፤ ማታ ማስተማር፤ እሁድ ቅዳሜ ማስተማር፤ ክረምት ማስተማር፤ በጋ ማስተማር፡፡ ምን ማስተማር ብቻ? ማማከር፤ ማረም፤ መመራመር፤ ገቢ ማመንጨት፤ የህዝቡን የዕውቀት አድማስ ማስፋት፡፡ የቀብራቸውንና የቀብር ስፍራቸውን ነገር ምርምር ቢያደርጉበት ወይም ቢያስደርጉበት አይከፋም፡፡ በመቃብር ላይ ጽሑፍ ላይ በዚህ ወሰነ ትምህርት የሚመራመሩ ተማሪዎች አሉን እዚህ ጠባሴ፡፡ የአስተማሪውን እየመረጣችሁ ስሩ ብለን ባቅማችን ሙስና እንስራ ትሉኛላችሁ?     

የተዝናኝና የጎብኚ መስህቦች
የዝነኞች የቀብር ቦታ እኮ ከመቃብርነቱም በላይ ቅርስ ነው፡፡ ለዝነኞቻችን - ለአገር መሪዎች፣ ለስፖርተኞች፣ ለከያኒያን፣ ለጦር ሜዳ ጀግኖች፣ ለበጎ አድራጊዎችና ለሌሎችም የተለየና አድናቂዎቻቸው ሄደው ሊጎበኙት የሚገባ መቃብር መኖር አለበት፡፡ ያ የቀብር ስፍራ ለመዝናኛና ለመቀጣጠሪያ የሚሆን ቢሆን እንዴት ያስደስታል፡፡ በካርታ ላይ የማን መቃብር የት እንደሚገኝ የሚጠቁም ስራ ቢሰራ፣ ሌሎች ምርምሮችም ቢካሄዱና ፍሬያቸው ቢታይ ታሪካችንን እንድናውቅም ሆነ የጉብኝት ባህል እንዲያድግ ይጠቅማል፡፡ ከኛ በፊት ያለፉት የሰሩትን ስራ በክብር ይዘን ማቆየት አለብን፡፡ ለባለውለታቿ ክብር የማትሰጥ መባል የለባትም አገራችን፡፡ መቃብር እንደ ቆሻሻ መጣያ መታየት የለበትም፡፡
መውጫ
የኦርኬስትራ ኢትዮጵያው መስራች ተስፋዬ ለማ ባለፈው ዓመት ባለፈበት በአሜሪካን አገር ሞቶ ሳለ አልተቀበረም - በኑዛዜው መሰረት አስከሬኑ እንዲቃጠል ተደረገ እንጂ፡፡ ይቺ ትንሽ ትከብዳለች አይደል? ሲሞቱ የሰውነታቸው ክፍል እንዲለገስ የሚናዘዙ አሉ - ይቺስ አትከብድም? አይ የሰው ፍጡር! ግማሹ ሰው ይገድላል ግማሹ አካሉን እየቆረሰ ለተቸገረ ያድላል፡፡ በልጅነታችሁ ወደ ቀብር ቦታ በቀትር አትሂዱ መንፈስ ይመታችኋል አልተባላችሁም? ይህስ የቀብር ቦታዎችን አስፈሪ አድርጋችሁ እንድትስሏቸው አላደረጋችሁም? ጎብኙ ስላችሁስ ልታስቀስፈን ነው እንዴ አላላችሁኝም?


በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...