2016 ፌብሩዋሪ 6, ቅዳሜ

ውዳሴ ፌስቡክ




ፌስቡክ ፌስቡክ አሉት ስሙን አሳንሰው
መሬትና ሰማይ የሚያተራምሰው
ከያሆ ይበልጣል ለተጠቀመው ሰው
ሃሳብን ናፍቆትን ፈጥኖ የሚያደርሰው
ከጠጅ ከጮማ አንጀት የሚያርሰው፡፡
ሻውል ፌስቡክ ሆዬ ምንኛ ያኮራል
ይህን ሁሉ ፍጥረት አውሎ ያሳድራል፡፡
ምን ብትል አሰብከው ዓለም ማጣመር
የጠፋን ማስገኘት ኮበሌን ማፋቀር፡፡
ለቡና ባትጠራኝ ይቅር ጎረቤቴ
በፌስቡክ ይረካል የወሬ ናፍቆቴ፡፡
ጌም ላይ ተሰክቼ የምውለው ሰውዬ
ቻት ልማዴ ሆኗል ፌስቡክ መጽናኛዬ፡፡
የዙከርበርግ እናት ኩሪ ይገባሻል
ልጅሽ ካጽናፍ አጽናፍ ሲያስወራ ያመሻል፡፡
የፈጠራ አድማሱ ሀብትን ማመንጨቱ
ዙከርበርግን ፌስቡክ ያሰኘዋል አንቱ፡፡
እረኛ ምናለ የሚለው ንጉሡ
እረኛን ፍለጋ ፌስቡክን ማሰሱ
አይቀርም መክፈሉ ለፌስቡክ ፎሊሱ፡፡
የፌስቡክ ደህንነት ስሙን የቀየረው
ጾታውና ፎቶው የሚያጠራጥረው
አዳሜን ሲያናዝዝ ሲያሳስት የሚውለው
ማን ምናለ ብሎ ዳኛን የሚጠራው
ፌስቡክ ባይኖር ኖሮ ምን ነበር እንጀራው?
አንዳንዱ፣ ሚስቱን አስተኝቶ እጮኛውን ትቶ
ቻት ላይ የሚያነጋው ለምን ይሆን ከቶ?
ጊዜዬን አቃጥዬ ስራዬን ዘንግቼ
ባህሌን ሸርሽሬ ቤቴን አናግቼ
በቻት ሱስ ናውዤ
ለፖስት ተቅበዝብዤ
ራሴን አሻሽጬ
ፈረንጅ አስበልጬ
ባህሩን ፌስቡክን ለምን እወቅሰዋለሁ
መዋኘት ድርሻዬ መሆኑን አውቃለሁ፡፡
ደብዳቤ ቢሞት ተተካ ፌስቡክ
የየቤቱን ጉድ የሚያዝረከርክ፡፡
የሚስትም አይደለም የጊዜም ቀማኛ
አገሩ ሚስቱ ነው ይሄ ታምረኛ
ሲጨንቀኝ መድረሻ ሳጣ
ከየጥጉ ዘመድ ስለሚያመጣ
ስለሚያዋኝ ስራዬ ብሎ
ስጦታ ልስጠው በቶሎ
ዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ከሰጠልኝ በጄ
ካልሆነ፣ ትንሽ ገንዘብ አስፈቅጄ
ለዙከርበርግ፣ ትምህርቱን ላቋረጠው ወዳጄ
ዲግሪ የምገዛለት ነኝ አዙዛ ፓሲፊክ ሄጄ፡፡
አበሻ ጉድ አለ ፈረንጅም ደነቀው
ያለ ፌስቡክ ውሎ እንዳያድር አወቀው፡፡
ቢቢሲ፣ ሲሲቲቪ፣ አልጀዚራ
በፌስቡክ ወሬ ሲዘራ
መንግስት፣ ማህበር፣ ነጋዴ
ከፌስቡክ ይጠፋል እንዴ?
ኢንተርኔት ፈረሱ
ኮምፒውተሩ ስልኩ ማስገሪያው ርስቱ
የንግግር ነጻነት ያለበት ደሴቱ
ይብላኝ ላልገባው ሰው፣ የፌስቡክን ነገር ሰው ዋ ስንቱ ዋ ስንቱ!!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...