2016 ፌብሩዋሪ 23, ማክሰኞ

የሌሎችን ግጥም ለራስ ሃሳብ በሰበዝነት ስለመጠቀም




ቀጥሎ የምታነቧቸው ከበዕውቀቱ ስዩም አዲስ መጽሐፍ፣ ከአሜን ባሻገር፣ ላይ ያገኘኋቸው ግጥሞች ናቸው፡፡ ግጥሞቹ በአብዛኛው የሕዝብ ሲሆኑ አንዳንድ በግለሰብ ገጣሚያን የተደረሱም አሉባቸው፡፡ ለአንባቢ በጥሩ ሁኔታ ሊገቡ የሚችሉት ግን በአውዳቸው ነው፡፡
የሌሎች ሰዎችን ግጥም እንደሃሳብ ማጎልበቻ አድርጎ በመጠቀም በዕውቀቱ ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር ተመሳስሎብኛል፤ ተስፋዬም የማስታወሻዎቹን እያንዳንዷን ምዕራፍ በሌሎች ገጣሚያን ግጥም መጀመሩን ልብ ይሏል፡፡ አስተያየት ካላችሁ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡

አንች ወዲያ ማዶ፤ እኔ ወዲህ ማዶ
አንገናኝም ወይ፤ ተራራው ተንዶ

ልብሴንም ገፈፈው፤ ለበሰው እርዘኛ
በሬዬንም ነድቶ፤ አረደው ነፍጠኛ
ንጉሥ የቀረዎት፤ ጥቂት ዐማርኛ
ምነው ሆድ አይዘርፉ፤ ዐርፌ እንድተኛ

አዲስ አበባ ላይ፤ ወድቄ ብነሳ
የሰራ አካላቴ፤ ወርቅ ይዞ ተነሳ

የራበህም ብላ፤ የጠማህም ጠጣ፤
ከዚህ የተሻለ፤ ምንም ቀን አይመጣ፡፡
ላገኝ ነው በማለት፤ ሞትኩኝ በሰቀቀን፤
ሂዶ ሂዶ አለቀ፤ የምጠብቀው ቀን፡፡

እኔስ ሄጃለሁ፤ ላሊበላ
እንግዲህ ዲያብሎስ ምን ትበላ

እኔስ አላጣም ልክልክስ
እኔስ አላጣም ልክልክስ
ሮብ ለት ማለዳ ማንኪያ የምትልስ

ከደበበ ሰይፉ
የሮሀ መቅደሶች
ዝነኛ ሕንጻዎች፤ ከዐለት ማህጸን፤ ተፈልፍለው የወጡ፤
ነው አሉ በመላእክት፤ ከአርያም ወርደው፤ በሌሊት የመጡ

ከወዴት መጣሽ፣
ከወዴት ከወዴት
ፊትሽ ያበራል በሌት

እዛው ማርልኝ ያንን ግትቻ
ይዤው እንዳልመጣ የለኝ ማንገቻ

እዛው ማርልኝ ያችን እሳት
ይዣት አንዳልመጣ ነገሩ አያደርሳት

አጥንቱን ልልቀመው፤ መቃብር ቆፍሬ
ጎበናን ተሸዋ፤ አሉላን ተትግሬ
አሉላን ለጥይት፤ ጎበናን ለጭሬ
አሉላ ሴት ልጁን፤ ጥይት ሲያስተኩስ
ጎበና ሴት ልጁን፤ ሲያስተምር ፈረስ
አገሬ ተባብራ፤ ካረገጠች ርካብ
ነገራችን ሁሉ፤ የምቧይ ካብ
                የምቧይ ካብ
ትምህርት እንዲስፋፋ፤ ጉልበት እንዲጠና
አራቱ ጉባኤ ይዘርጉልንና
ጎባና ከፈረስህ ጋር ተነሥ እንደገና
                  ተነሥ እንደገና
ቀኝጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ

አመ ሠላሳ ቀን፤ ጎበና ባይጸና፤
ይካፈሉን ነበር፤ እነ ቱፋ ሙና

ይታመሳል አሉ ከፋና ቦረና፤
አማን አይደሉም ወይ እነ ራስ ጎበና፡፡

የሚሰጡት ቢያጡ፤ ከድፍን አበሻ
ለኡራኤል ሰጡት፤ የጎበናን ጋሻ

ወዝውዘው ወዝውዘው ጣሉት እንደ ዝሆን
ያው ወደቀላቸው ይበሉት እንደሆን

የባህታ ሀጎስ አጽም ይመስክር
ያየደገኛው ወንድ የአካለጉዛዩ ነብር
ይመስክር የህላይ ምድር
የነሳንጎኒቲ ጌታ ‹‹ጣሊያን ኀያል›› ናት ብሎ ሲል
የኢትዮጵያን የበላይነት በቡጢ ከንትሮ የሚያስምል
ጸጋዬ ገብረመድህን

አልቢን የያዘ ሰው፤ ይሁነኝ ውሽማ
መውዜር አይገዛም ወይ፤ ባሌ እንዲሆንማ

አመጣለሁ ብሎ፤ የካሳን ፈረስ
ሳያርመው ሞተ፤ የዘራውን ገብስ

ውሃ ለቀደመ
ግዳይ ለፈለመ

እቴጌ ጣይቱ እጅግ ተዋረደች
ሆቴሏን አቁማ እንጀራ ነገደች

ወይ ጉዴ
ላግባሽ አለኝ ነጋዴ

መልበስ አረንጓዴ
ማግባት ነው ነጋዴ

ብቻ አማራ አይደለም ኦሮሞ ቅልቅል
አንጠልጥሎት ሄደ ልቤን እንደቅል

አልተተከለም ወይ ታቦት ባገራችሁ
ቡልቡላ፣ ዱጉማ፣ ነጃራ ስማችሁ

ሁላችሁም ስሙኝ ከስላሙ እስካማራ
ጳጳሱ መነኩሴው ሰሞኛው ደብተራ

ከአውሮፓዎች እንማር በጣም እንበርታ
ታሪክ እንመርምር እናንብብ ጋዜታ
ቋንቋም እንማር እንመልከት ካርታ
እሱ ነው ለህዝቡ ዐይናቸው የፈታ

እንደ ጾመድጓ መልኳ የረቀቀው
እንደየሩሳሌም ወገቧ የረቀቀው

ዘወትር ብመክርም እሁድ እሁድ ለታ
አንድ ሰው አጣሁኝ የሚነቅፈኝ ጌታ
ወይም የሚለኝ እውነት ነው እንዴታ

አስተርጓሚ ሆኖ ሰሃን ሲፈገፍግ
አሁን ማን አገባው ከጨዋታ ከወግ
ታዛባ ሳይለይ ወድቆ ሳያድር ተፍግ
አክብረውህ ነበር ብለውህ ብላታ
በግር ብረት ገባህ ስለሆንህ ወስላታ
… ስትጠርግ ነበረ ስትደፋ ባሬታ
ትሰድብ ጀመረ የብርሃኑን ጌታ

ምላስህ መርዛም ነው ከንፈርህ መግላሊት
ሰባት ጊዜ ክደህ የለህም ሃይማኖት
ለሞኝ ይመስለዋል ገብረእግዚአብሔር ሲሉት
ዶሮውን ሳያርዱ ይገኛል መረቅ
ግጥም ገጠምሁ ይላል ዐማርኛ ሳያውቅ

ቤቴ
ገመና ከታቼ
ገመና መክተቱ ምንድነው ትርጉሙ
ወደ ጓዳ ገብቶ ዱቄትስ ቢቅሙ
አዝማሪት ጣዲቄ

ወግጂልኝ ዜማ፤ ወግጂልኝ ቅኔ
ወንዶች በዋሉበት፤ መዋሌ ነው እኔ

ሴቶ ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሄራ
ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ

እኔስ ደከመኝ፤ ተፋሁ አሞት
አዙር ተገኝ፤ በንጉሡ ሞት

አውድማው ይለቅለቅ፤ በሮችም አይራቁ
ቀድሞም ያልሆነ ነው፤ ውትፍትፍ ነው እርቁ

የኢትዮጵያ ልጅ፤ ቁርበት ደርባ
እንደ ሰሌዳ፤ ማቅ ተከናንባ
በወርቅ ድሪ ሐብል ፋንታ፤ አንገቷ ቀንበር ጠልቆላት
የዘፈን ቤቷ ፈርሶ
አደባባይዋ በለቅሶ
የትካዜ ጭጋግ ለብሶ
በሽቶ ማእዛና በጽጌረዳ ፈሳሽ ፋንታ
በገጽዋ ትቢያ ተነስንሶ

በሰማይ ላይ ሆነህ፤ ስታላግጥ በሰው
እናትህ ነደደች፤ ሐዘኑን ቅመሰው

ከሀበሻ ወዲህ፤ ከሀበሻ ወዲያ
ሰውንም ገረመው፤ እኔንም ገረመኝ
ዮሀንስ እግዜርን፤ ገድሎታል መሰለኝ

ዱብ ዱብ ይላል እንደበረዶ
በልጅነቱ በረሀ ለምዶ

ትመጫለሽ ብዬ ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ
የልጅነት ዐይኔ ሟሟ እንደ በረዶ

አመልክን በጉያህ
ስንቅህን ባህያህ

እንኳን እናቱ የወለደችው
አማቱ ኮራች የተጋባችው

አባትህ ለገዛ፤ አያትህ ለነዳ
አንተ ምን አግብቶህ ትከፍላለህ ዕዳ?

መሬት የእግዚአብሔር ናት ባለቤት የላትም
ኀይለኛ እየሄደ ያስገብራል የትም






ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...