የጉዞ፣ የንባብ፣ የቤተመጻሕፍት ፣ የሕትመትና ስርጭት ወዘተ ጽሑፎችን ያገኙበታል። I share my views and reports of my activities in this blog.
ሐሙስ 14 ሜይ 2015
ጥቁር እንዴት አገሬ ብሎ ይዋጋል?
አርብ ሚያዝያ 30፣ 2007 ዓ.ም. በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ እጅግ ድንቅ ትምህርት ከወሰድኩባቸው መድረኮች አንዱ የነበረው በታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ፊትአውራሪነት የተዘጋጀው ትምህርታዊ መድረክ የተካሄደበት ነበር፡፡ ሰዉ ሁሉ ‹‹እንዲህ ነው ምሁራን ማለት!›› ብሎ ያደነቃቸውና እንኳን መመራመርና ማወቅ ለሚፈልግ ቀርቶ ስለ ዕውቀትና ምርምር መስማት እና ማድነቅ ለሚፈልግ ሰው አርዓያ የሆኑ ተመራማሪዎች ጥልቅ ትምህርት የሰጡበት ቀን ነበር፡፡ የዚህ መድረክ ስያሜ ‹‹የአርበኞች ቀን መታሰቢያ አውደ ጥናት›› ሲሆን ሶስት ጥናቶች ቀርበውበታል፡፡ በጥናቱ የተገኙት 90 በመቶ የሚሆኑት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ሲሆኑ የተቀሩት ከባህል ጽ/ቤቶች የመጡ እንግዶች፣ የሰሜን ሸዋ አርበኞች ተወካዮች እና የዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሰራተኞች ነበሩ፡፡ በየማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ የማስተዋወቅ ስራ ቢሰራም ይህ በየትምህርታዊ መድረኩ የሰው መታጣት ችግር ሊለቀን እንዳልቻለ ግልጽ ነው፡፡ መፍትሔ ማፈላለግ ግድ ይለናል፡፡
የመጀመሪያው አቅራቢ የነበሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ሲሆኑ የእርሳቸው ገለጻም ለጥቀው ለሚያቀርቡት ለኢያን ካምቤል ጥሩ ዳራ አስቀምጦላቸዋል፡፡ Mapping Collaboration and Resistance in Africa Orientale Italiana 1935-1941 የሚለውን ወረቀት ፕሮፌሰሩ ከማቅረባቸው በፊት ለአካዳሚክ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከህዝቡም ጋር ለመነጋገር ዕድል የሚከፍት በመሆኑ ደስ እንዳላቸው በመናገር ነበር የጀመሩት፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ከአውደ ጥናቱ የወሰድኩትን ማስታሻ በቅድሚያም የፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለን በአጭሩ አቀርባለሁ፡፡
አርበኝነትን ያለ ባንድነት ወይንም ለጣሊያን ከተደረገው መተባበር ውጭ ሙሉ ለሙሉ ልንረዳው አንችልም ያሉት ምሁሩ በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ከኢትዮጵያ እጅግ ያየለ ዝግጅት እንዳደረገችና ኢትዮጵያም በነበራት አቅም ወረራውን እንዴት ለመቋቋም እንደቻለች በማስረዳት የወረራውን መልክ አሳይተዋል፡፡ ከ300 000 በላይ ጦር ወደ አፍሪካ ከጣሊያን ጊዜ ወዲህ ተልኮ የማያውቅ ሲሆን ጣሊያንም ይህንን ሁሉ ወታደር የላከችው አንድም የአድዋው ሽንፈት እንዳይደገም በመፍራትና ሁለትም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ዘመናዊነትና ዝና በመገንዘብ ነበር፡፡ እንደተገመተው የኢትዮጵያም ጦር በቀላሉ አልተሸነፈም፤ ጦርነቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ አላለቀ፡፡ 400 ታንክና 300 የጦር ጀቶች የዘመናዊው የጣሊያን ትጥቅ ማሳያዎች ነበሩ፡፡በሰሜን ለመሸነፍ ሰባት ወር፣ በምስራቅ ስምንት ወር ሲፈጅብን፣ በነገሌ ደግሞ አመት ከስድስት ወር ሳንሸነፍ ቆይተናል፡፡ ጣሊያን ደብረብርሃን ሚያዝያ 25፣ ቱሎፋ በተባለች ኮረማሽ አጠገብ ባለች ስፍራ ደግሞ በ26 ገብቶ ሚያዚያ 27 በ10 ሰዓት አዲስ አበባን ይቆጣጠራል፡፡ ይህም በጦርነቱ ተፈጥሮ ላይ የራሱ ተጽዕኖ ነበረው፡፡ የጣሊያን መንግስት በኢትዮጵያ ተብሎ መታወጁ የብዙውን ሞራል ሰብሯል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ ከደብረሲና እስከ አዲስ አበባ ባለው መንገድ ላይ መንገዱን የማወክ የአርበኝነት ተግባር ተጀመረ፤ ከዋና ከተማዋ ወደ አዋሽ የሚሄደውን የባቡር መስመርና የፍቼንም መንገድ የመዝጋት ስራ ተጧጧፈ፡፡ በመልሱም መስመሮቹን የማስከፈትና አርበኛውን የማባረር ስራ በጣሊያኖች ተጀመረ፡፡
አርበኝነቱ ቤተክርስቲያን የነበረችበትና ሰፊ መሰረት የነበረው ነበር፡፡ እንደማሳያም አቡነ ጴጥሮስ የነበራቸው አስተዋጽኦ ይገለጻል፡፡ እኝህ መንፈሳዊ ሰው ከደብረ ሊባኖስ ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ነበሩ፤ እዚያም ይኖሩ ነበር፡፡ አዲስ አበባን ለመቆጣጠር የተጠራውንም ስብሰባ በገዳሙ መርተው ነበር፡፡ በ1928 ሃምሌ ላይ አርበኞቹ አዲስ አበባን ነጻ ለማውጣት ሞከረው የነበረ ሲሆን አቡነ ጴጥሮስም ይህ ሙከራ ከሽፎ ይገደላሉ፡፡
ምዕራብ ኢትዮጵያ ላይ የራስ እምሩ የጎሬው መንግስታቸው ፍልሚያውን ሲያካሂድ ቆይቶ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ራሳቸው ራስ እምሩ ተማርከው ወደ ጣሊያን ይወሰዳሉ፡፡ የጣሊያን ጦር ዋነኛ ተግባራትም የሸዋን መስመሮች ማስለቀቅ፣ የራስ ደስታን ጦር ማጥፋትና የጣሊያንን መንግስት የሚደግፉትን ማፈላለግና ግንኙነት መፍጠር ይሆናል፡፡ የራስ እምሩና የጥቁር አንበሶች መያዝ አንድ ጉልህ ሂደት ነው፡፡ በየካቲትም ወር ግራትሲያኒ መስመሮቹን ስላስለቀቀ አሸንፈናል የሚል ስሜት መጣበት፡፡
ለወራሪው የነጭ ጦር የሚደረገው ትብብር ሁለት መልክ ነበረው፡፡ ይኸውም አንድም ግለሰቦች እንደራስ ሃይሉ ራሳቸው የሚያደርጉት ትብብር ሲሆን ሌላውና ብዙ ሰዎችን የሚካትተው ግለሰቦች ማህበረሰባቸውን ይዘው የሚገቡበት ሂደት ነበር፡፡ በሁለተኛው መንገድ የሚገቡት ባላባቶች በአፋርና በሰሜን ነበሩ፡፡ ለወራሪዎቹ መተባበሩ በነዚህ ስፍራዎች ብቻ ሳይወሰን ድፍን ሸዋ፣ ጎንደር፣ ላስታ፣ ጎጃም ባንዳ ነበር አሉ፡፡ ለአገሩ የሚዋጋ በየስፍራው መኖሩ ግን መዘንጋት የለበትም፡፡
ሰፊ የማግባባት ስራ ከተሰራ በኋላ የወላይታ፣ ጅማ፣ ከምባታ እና ሃድያ ባላባቶች ለጣሊያን ሊተባበሩ ቻሉ፡፡ ለዚህም ትብብር የዳረጋቸው የጣሊያን ፖሊሲና ውትወታ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ማለት አማራ የሚገዛት የአማራ አገር ናት›› እያሉ ጣሊያኖቹ ከወለጋ፣ ከኢሊባቡር እና ከፋ ደጋፊዎችን ማግኘት ችለው ነበር፡፡ ኦርቶዶክስ ነው የሚገዛችሁ በማለትም ይህንን ያገኙትን ድጋፍ አጠናክረውታል፡፡ ከሸዋ ውጭ የነበረውን አማራ ደግሞ ሸዋ ነው የሚገዛችሁ እያሉ ለመከፋፈል ቢሞክሩም አልተቻላቸውም፡፡ የሆነው ሆኖ ከየካቲት 1929 እስከ 1933 ጣሊያኖች በአንጻራዊነት በሰላም የሚያስተዳድሩባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡
ለኘጮቹ የተደረገውን ተብብር ስናይ ባንዳዎች የራሳቸውን ታሪክ ስላልጻፉና ባንዳነታቸውንም ከነጭራሹ ደብቀው ስለተቀመጡ የእነርሱ ታሪክ ያልተሟላ ነው፡፡ በጣሊያኖች በኩል ለተባበሯቸው ኢትዮጵያውያን በሮማ ያደረጓቸውን አቀባበሎችና በቤተመንግስት ያደረጓቸውን መስተንግዶዎች ጨምሮ በርካታ ፎቶዎችን እና ካርታዎችን ከአርኪ ገለጻ ጋር ያቀረቡት ፕሮፌሰሩ ያለምንም የጽሑፍ ማስታወሻ ንባብ የሚሰጡት ማብራሪያ አብዛኛውን እስካሁን የማውቀውን ምሁር የሚያስከነዳ ነበር፡፡ በሞሶሎኒ ቤተመንግሰት ፊት ለፊት ለጅማው ገዥ ለሱልጣን አባ ጆቢር ክብር የተደረገውን ደማቅ ሰልፍ አሳይተውናል፡፡ የአፋርና የቆላው ኢትዮጵያ ሰዎች የተደረገላቸውን አቀባበል በክብር ልብስ ሆነው በፊተኛው ረድፍ ቆመው ሲታደሙ አይተናል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ዮሐንስም ተባባሪ ሆነው ሄደው ነበር፡፡ እንደምገምተው አቅራቢው ምሁር ያላቸው የጣሊያንኛ፣ የአረብኛና የግዕዝ ችሎታ ከተለያዩ መዛግብት ያልተዳሰሱትን እውነታዎች ለመፈልፈል ረድቷቸዋል፡፡
የአርበኝነትን እንቅስቃሴ በተመለከተ ግራትሲያኒ አጠፋዋለሁ ሲል አልሆነለትም፡፡ በውጭው ዓለም ጥቁርና ኋላ ቀር ህዝብ እንዴት ለአገሩ ይዋጋል የሚል አስተሳሰብ ነበር፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ የሚለው ግንዛቤ ግን ለብዙ ዘመን ለሺዎች አመታት የቆየ ሲሆን ንጉስ ኢዛና ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለውን በደብደቤው ውስጥ የተጠቀመው፡፡ መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግዕዝ ሲተረጎምም ኢትዮጵያ የሚል ቃል ተጠቅመዋል፡፡ ከአረብኛ ወደ ግዕዝ የተተረጎመ ገድል ላይም ኢትዮጵያ አለች፡፡ ከዚያ ዘመን ወዲህም በ13ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ይህንኑ ቃል ተጠቅመውት እናገኘዋለን፡፡ በአረብኛ አበሻ የሚለውን ወደ ግዕዝ ሲተረጉሙ ኢትዮጵያ እያሉ ነው፡፡ በግዕዝ ትርጉሙ ላይ አበሻ የሚል የለም፡፡ ስለዚህ ለመንደራቸው፣ ለቀያቸው አለያም ለዘመዶቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሃገራቸው የሚቆሙ አርበኞች መኖራቸው ለወራሪዎች እውነታውን ከጠበቁት በላይ አድርጎባቸዋል፡፡
አርበኞችንም አግባብቶ ወደ ጣሊያን ለማስገባት እልህ አስጨራሽ ጥረቶች ይካሄዱ ነበር፡፡ እንደ ምሳሌም በሞሶሎኒ ጥያቄ አበበ አረጋይ ከኢጣሊያ መንግስት ጋር እደራደራለሁ ይላሉ፤ ይህን የሚያደርጉትም ጊዜ ለመግዛት ነው፡፡ የትምህርት ደረጃቸው ስምንተኛ ክፍል ስለደረሰ የውጭ ቋንቋና ጂኦግራፊም ጭምር ስለሚያውቁ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት መከሰትን ይገምቱ እና ይጠባበቁ ነበር፡፡ ሞሶሎኒም ለእንደራሴዎቹ ወይ ተዋግታችሁ አሸንፉ ወይንም ለቃችሁ ውጡ ይላቸዋል፡፡ ከራስ አበበ ወገን ፊታውራሪ ወንድምነህም ለድርድር መጥተው ፎቷቸው ይታያል ፕሮፌሰሩ ባቀረቡልን ትዕይንት ላይ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ በዓለም ሁኔታም መቀያየርና በነበረውም የሃይል አሰላለፍ መሰረት ሁኔታዎች ሁሉ ለጣሊያኖች ይገለባበጡባቸዋል፤ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ባዳ የነበረውንም ጨምሮ የመቀመጫ መርፌ ይሆኑባቸዋል፡፡ የእንግሊዞች መምጣት አስተዋጽኦ ማድረጉ አይናቅም፡፡ በእንግሊዞች እገዛ ያደረግነው የ1933ቱ ጦርነት የነጻነት ጦርነት ሳይሆን የመጫረሻው ጦርነት መባል አለበት፡፡ ምክንያቱም ከዚያም በፊት በርካታ ጦርነቶች በየጠቅላይ ግዛቱ ስለነበሩ ነው፡፡ ከጥር እስከ ሚያዚያ 1933 ጣሊያን አለቀለት፡፡ ይህም የሆነው ህዝቡና አርበኞች እንደገና ስለተነሱ ነው፡፡ ባላባቱ ሁሉ ወደ አርበኝነት ይገባ ያዘ-- በደቡብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን በሁሉም ቦታ፡፡
ቀጥሎ ምርምራቸውን ያቀረቡት ኢያን ካምቤል ሲሆኑ ምርምራቸውም የሚያጠነጥነው በደብረሊባኖስ ግድያ ላይ ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት ታሪክ እየሰራን ነው ብለው ነበር የጀመሩት፡፡ ይህ የአሁኑ መድረክ የደብረ ሊባኖሱ ታሪክ ለህዝብ ይፋ የሆነበት የመጀመሪያው ነው፡፡ ጣሊያን ግዛት ያስፈልጋታል፤ ኢትዮጵያም መሰልጠን አለባት የሚል ነበር ጣሊያኖች እዚህ ለመግባታቸው ያቀረቡት ምክንያት፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ስለተፈጸመው ትልቁ ግድያ ብዙም የሰማነው ነገር አለመኖሩ የሚገርም ነው፡፡
ግራትሲያኒ የአዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ከሶስት ሳምንት በኋላ የኢትዮጵያ ገዥ ተብሎ ተሾመ፡፡ ግራትሲያኒ በአንደኛው የዓለም ጦርነትና በሊቢያም ተሳትፎ የነበረውና መጥፎ ታሪክ ያለው ሰው ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ስምንት ሰው የሚሰቅሉ ተንቀሳቃሽ የሰው መስቀያዎች ኢትዮጵያን በሚያስተዳድርበት ወቅት በየስፍራው ነበሩት፡፡ ግራዚያኒ ደብረሊባኖስ እና ሌሎች የኦርቶዶክስ አብያተክርስቱያናት የችግሩ ምንጭ እንደሆኑ ያምን ነበር፡፡
ስምኦን አደፍርስ፣ ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ ያቀነባበሩት የግራትሲያኒ የግድያ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቶ ህዝቡን ለማስጨፍጨፍ በቃ፡፡ የሞቱትን ከአዲስ አበባ ለማውጣት በ100 የጭነት መኪናዎች አራት ቀን ወስዶባቸዋል፡፡ ግራዚያኒ የግድያ ሙከራ ከተሞከረበት ጊዜ ትንሽ ቀደም ብሎ በዕለቱ በሚያዘጋጀው ዝግጅት ላይ አቡነ ቄርሎስ ቀርተውበት ሲጠባበቅ የሚያሳይ ፎቶ አይተናል፡፡ እርሳቸውም አሞኛል አልመጣም ብለው ሀኪም ልኮ ጤንነታውን አረጋግጦ በግዴታ አምጥቷቸዋል፡፡ ችግር ሊኖር እንደሚችል ሰው ነግሯቸው ነበር ማለት ነው፡፡
የችግሬ ምንጭ ነው የሚለውን ገዳም የደብረሊባኖስን ለማውደም የሚያዝ ሰነድ አዘጋጅቶ የነበረው ግራትሲያኒ በገዳሙ ያሉትን ካህናትና ምዕመናን ለመግደል ዕቅድ ሲወጣ ከረመ፡፡ ግንቦት 12 ቀንም የአቡነ ተክነሃይማኖት ንግስና የሚካኤልም በዓል ቀን ስለነበር ተመረጠ፡፡ ለንግስ የመጣውንና ሁሉንም ህዝብ ቤተክርስቲያኑ ግቢ ውስጥ አስገብተው ደብቀው ባስቀጧቸው መኪኖች እየጫኑ ወስደው ገደሏቸው፡፡ ግራዚየኒ 452 ሞተ ብሎም ይፋ ቢያደርግ እንኳን ከ1800- 2200 ሰው ተገድሏል፡፡
ከደብረ ሊባኖስ የተረፉትን ወደ ስምንት መቶ የሚጠጉ ሰዎችም ደብረ ብርሃን ያመጧቸዋል፡፡ ከዚያም ወደ አንኮበር መስመር እንግጫ የሚባል ስፍራ ላይ ወስደው በምስጢር ጉድጓድ አስቆፍረው ገድለው እንደቀበሯቸው የሚያስረዱ የአይን ምስክሮችን ጭምር አነጋግረዋል ተመራማሪው፡፡ ከዚያም የተረፉት እዚህ ደብረ ብርሃን ከተማ ጮሌ አካባቢ እንደተገደሉና እንደተቀበሩ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህራን የሆኑት አለባቸው በላይና ቴዎድሮስ ስዩም በዕለቱ ባቀረቡት ምርምራቸው አረጋግጠዋል፡፡ ይህን ቦታም ለመንከባከብ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡
በደብረ ሊባኖስ የሞቱ ሰዎች ዘመዶችና እነዚያን ሰዎች የሚያውቁ ሰዎች ተጠንተው ከሰሜን ሸዋ ተሰብስበው ሶማሊያ ውስጥ ወደሚገኘው ደናኔ እስር ቤት ተወስደው የታሰሩ ሲሆን ብዙዎቹም ሞተዋል፡፡ እነዚህ በሺዎች የሚቆጠሩት ኢትዮጵያውያን የሞቱበትና የታሰሩበት ደናኔ ታሪካዊ ነው፡፡ የደናኔ የማጎሪያ ካምፕ ከ75 ዓመታት በፊት ነበር የተከፈተው እዚያ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፡፡ ግራትሲያኒ የሰራው ግፍና በደል ተደብቆ ቆይቶ አሁን ድረስ ተመራማሪዎችም ሳይገነዘቡት መቆየታቸው ምክንያቱ አንድም እርሱ ራሱ ነገሮቹን ሁሉ እንደዚህ በድብቅ መስራቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ሰዎች ምንድነው እንደዚህ ክፉ የሚያደርጋቸው ከተባለ በማህበረሰብ ያለውን ሁሉንም ነገር ማላመድ ይቻላል፤ ሰውን መግደልንም ማለማመድ ይቻላል፡፡ ጀግናን ማወደስን ተምረንዋል፡፡ ዶሮ እንደመግደል ነው ብሎ ማስተማር፤ ልጆች የአርበኞችን የተቆረጠ ራስ እንዲይዙ ማድረግ መጥፎ ነገር ሰርተው ምንም እንደማመጣባቸውና ተጠያቂነት እንደማይኖር መንገር ነው መላው ብለዋል ኢያን ካምቤል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት ኢትዮጵያ ጣሊያንን ወደ ፍርድ አደባባይ እንዳታወጣ ያደረገው ታሪካዊ ውሳኔ ዘርፈ ብዙ መንስኤዎች ነበሩት፡፡ በመጀመሪያም ሃገሪቱ እንድትወረር እጃቸው ስለነበረበትና በሌሎችም ስሌቶቻቸው ኢጣሊያን ማገዙን ወደውታል፡፡ በእኛ ሀገር በኩል የንጉሰ ነገስቱ መንግስት መጠነኛ እገዛ ቢደረግለትም ያ በቂ አይደለም የሚሉ እየመጡ ነው፡፡
በእንግጫ ሟቾቹን ለማስታወስ ምንም የተደረገ ነገር የለም፡፡ በደብረ ሊባኖስ ግን የሞቱትን ለማሰብ የተጻፈ የጽሑፍ መግለጫ አለ፡፡ የሚታወሱበትን አይነተኛ ነገር መፈለግ ግድ ይለናል፡፡ አሁን በሰሜን ሸዋ አርበኞችና በዩኒቨርሲቲያችን የታሪክ ምሁራን እየተሰራበት ያለው የደብረ ብርሃኑ መታሰቢያ ከዳር ቢደርስ ቀጣይ የሸዋ አርበኞችን ማፍራት እንደሚቻል እምነቴ ነው፡፡
በአውደ ጥናቱ ዕለት ከሸዋ አርበኞች ማህበር የመጡት አራት ሃላፊዎች በመርሃ ግብሩ የታደሙ ሲሆን ገና ወደ አዳራሹ ሲገቡ ተማሪውና ታዳሚው ተነስቶ በጭብጨባ እና በደስታ ነበር የተቀበላቸው፡፡ ባላምባራስ በየነ አደለኝም በወታደራዊ ሰላምታ ህዝቡን አመሰገኑ፡፡ የዚህ ዘመን ወጣቶች ታሪካቸውን ለማጥናት ባላቸው ትጋት እጅግ እንደተደሰቱ ተናግረው በ93 ዓመታቸው ይህን በማየታቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም የታሪክ ትምህርት በየመድረኩ የሚሰጥበት ዕድል ቢመቻች ሁላችንም ስለማንነታችን እንድናውቅና የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ህይወታችንን በተሻለ ሁኔታ እንድንመራ ስለሚያስችለን እንደዚህ ዓይነት መድረኮች ቢጠናከሩ ጥሩ ይሆናል በሚል እርስዎንም ስለሰጡኝ ጊዜ እያመሰገንኩ ልሰናበት፡፡
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?
'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...
-
6 June 2019 Basic Writing Skills (Sophomore English) Lecture 1.1. Phrases and Clauses 1.1.1. Phrases A phrase can ...
-
እሁድ ከደብረብርሃን ካምፕ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱት አማራ ተፈናቃዮች ምን ገጠማቸው? መዘምር ግርማ ደብረብርሃን ረቡዕ፣ የካቲት 13፣ 2016 ዓ.ም. ከብዙ ጭንቀት በኋላ በዕለተ ማክሰኞ ምሽት 4፡1...
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ