የጉዞ ማስታወሻ
በመዘምር ግርማ
mezemir@yahoo.com
ሚያዝያ 27፣ 2007 ዓ.ም. ሁለት መምህራን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሀበር ወደተመሰረተበት ስፍራ ተጉዘን ነበር፡፡ ጉዟችን በመስሪያ ቤታችን በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መኪና ሊሆን ቢታሰብም መኪኖቹ በሌላ ስራ በመያዛቸው በህዝብ ትራንስፖርት እንድንጓዝ ሆነ፡፡
አምና ሰባት ሆነን ወደ ስፍራው ስንጓዝ የገጠመን በየደቂቃው የሚበላሽ መኪና እና ስንመለስም የነበረችው መኪና ውስጥ የምትወልድ ሴት ዓይነት ያልታሰበ ነገር ስላላጋጠመን የዘንድሮው ጉዟችን የተሻለ ነበር፡፡ የጉዟችን ዓላማም በበዓሉ አከባበር ላይ መሳተፍና የስፍራውን ታሪክ መጻፍ ነበር፡፡
ከደብረ ብርሃን እስከ ጣርማበር ባለው 50 ኪሎሜትር አስፋልት ሸለቆውን እየቃኘን ሄድን፡፡ ጣርማበር ከተማ ስንደርስ መኪናችን ውስጥ የምግብና ፍራፍሬ ሻጮች አጥለቀለቁን፡፡ ‹‹ጦስኝ፣ ቆሎ፣ ኩኪስ፣ አገዳ፣ ሙዝ›› ሲሉ ለጆሮ እንደሙዚቃ ይጥማሉ፡፡ ከዚያም 22 ኪሎሜትሩን ፒስታ መንገድ ቁልቁል በስተ ምዕራብ ሰላድንጋይ ድረስ መንገጫገጭ ግድ ይላል:: እዚያች ታሪካዊ ከተማ ሰላድንጋይ ላይ ቆም ብሎ አጼ ምንሊክ የቆረቆሩት የቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን እና የቅድም አያታቸው የልዕልት ዘነበወርቅ ሰገነት በከተማው ዳርቻ ጎን ለጎን ለፍልሚያ የተዘጋጁ አውራ ዶሮዎች መስለው ተረተር ላይ ቆመው ተፋጠው ሲጠባበቁ እያዩ ዘመናዊው ምስራቅ ሆቴል በረንዳ ላይ ሻይ ቡና ማለት የቤተክህነትንና የቤተመንግስትን ተጠባብቆ ኑሮ ያስገነዝባል፡፡
የሞጃና ወደራ ወረዳ ትልቋ ከተማ የሆነችው ሰላድንጋይ ከተማ ከመቼውም በላይ ተውባ ጠበቀችን፡፡ ከመብራት እንጨቶች በአውራ መንገዱ አግድም ከዳር እዳር ረጃጅም የኢትዮጵያ ባንዲራ ሶስት ወይንም አራት ቦታዎች ላይ ተንጣሎ አየን፤ ፎቶም ተነሳን፡፡ ይህ ሁሉ ባንዲራና ድምቀት ግን የአርበኞች በዓልን ለማሰብ መስሏችሁ እንዳትሳሳቱ፡፡ የህዳሴው ግድብ ዋንጫ ወደ ወረዳው በማግስቱ ስለሚመጣ አቀባበል ለማድረግ ነው፡፡ ይህ የግድብ ዋንጫ በሚዞርባቸው ከተሞች ሁሉ ለቦንድ ቃል ይገባል - ይፈጸምማል! ሰላድንጋይ ከተማ ላይ በአንድ ቤት በር ላይ ሳልፍ ስለአርበኞች በሬድዮ ሲወራ ሰማሁ እንጅ ምንም የበዓል አከባበር በከተማዋ አላየሁም፡፡ በነገራችን ላይ እርስዎም ጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም እንዳሉት ‹‹ሰላድንጋይ ምንድነው?›› የሚሉ ከሆነ ግን ከተማዋ ያላትን ታሪክ ብቅ ብለው ይጎብኙ እልዎታለሁ፡፡
ወደ ሳሲት የሚወስድ መኪና በየሰዓቱ ስለማይጠፋ ጠብቆ መሳፈር ይቀጥላል ከዚህ በኋላ፡፡ ይችን የሳሲት 20 ኪሎሜትር መንገድ በእግራችን ስንትና ስንት ጊዜ ፉት እንዳልናት! መኪና ደግሞ ወደ ደብረ ብርሃን ተመላሿ ጠዋት ካመለጠችን ሰላድንጋይ ላይ ማደር ግድ ይል ነበር፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአስር ዓመት በፊት አልነበረም፡፡ ስልክ ደግሞ አንድ የህዝብ ስልክ ቤት ነበረች፡፡ ውሃውም መጠነኛ ነበር፡፡ አሁን ግን እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ከብሄራዊው ኬክ ጠርዝ ሞጃዎች ትንሽ እየላሱ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡ ሞጃዎችን እኮ ጃንሆይ አሳደዋቸዋል፡፡ ልጆቻቸው መንግስቱ እና ግርማሜ ነዋይ ‹አስቀይመዋቸው› ሞጃ የተባለን ሁሉ ከስራ አባረዋል፡፡ ያ አልፏል፤ አሁን ግን ከመንግስት ጋር ታርቀዋል፡፡
ለማናቸውም ሳሲት የሚሄደው መኪና ላይ እኔ፤ ሳለአምላክ ጥላሁን እና እሙዬ አረጋ (ጊፍቲ እኔ እንደምጠራት) (ይቺ ልጅ አምና አብራን ለአርበኞች በዓል ስትሄድ የአባቷን የጋሼ አረጋን ሞት በስልክ አርድተዋት እነዚህም አባቶቼ ናቸው ብላ አርበኞቹን አይታና ለልጆቻቸው ትምህርት ቤት እንዲቀመጥ የገዛችላቸውን የመጻሕፍት ስጦታ ሰጥታ ነበር የመጣችው) ተሳፈርን፡፡
የሳሲትን መንገድ ሳጋምሰው ከሰላድንጋይ ወደ ሳሲት በእግሩ የሚወርድ አንድ ጉብል ተቀኘ ያሏት ግጥም ትዝ አለችኝ፡፡ እነሆ-
ሰላድንጋይ ውዬ ባር ሜዳ መሸብኝ
ላጨርሽው ፍቅር ምነው ጀመርሽብኝ!
ከሰላድንጋይ ወደ ሳሲት ስንሄድ ያገኘሁት የወረዳው ሰራተኛና የትውልድ ስፍራው አንዲት ግራርን አልፎ ጋውና ላይ የሆነው አቶ ሶሎሞን አበበ ‹‹ይህ በዓል አርበኞች አገሪቷን ከጠላት ወረራ ለመከላከል ያደረጉትን ተጋድሎ ለማስታወስ ሲባል የሚከበር በዓል ነው፡፡ ሰራተኛው እንጅ ተማሪው እና አርሶ አደሩ የምን በዓል እንደሆነ አያውቁትም - ሚዲያ ስለማይከታተሉ፡፡ መድረክ በየቀበሌው እና በየወረዳው ቢዘጋጅ ብዙ ሰው ያውቀዋል፡፡ በአርበኞቻችን ኩራት ይሰማኛል፡፡ ስለበዓሉ ግን በትምህርት ቤት ምንም የተማርኩት ነገር አልነበረም፡፡›› በመኪናችን ውስጥ ለቀስተኞች ተቀምጠዋል፡፡ የየራሱን መንገድ የሚሄደውን ያደርሳል ሹፌሩም፡፡
ሳሲት ደርሰን በደጓ በወይዘሮ ዘነበች አስፋው ቤት ስንጋበዝ ይህችን ተዘውታሪ ግጥም አስታወስኩ -
ኧረ ሳሲት ሳሲት ትንሿ ከተማ
የሚበላው ስንዴ ጉዝጓዙ ቄጠማ !
ከዚች ከተማችን ወደ መዳረሻችን የሚወስደን መኪና እስኪገኝ ቡና መጠጣትና ምሳ መብላት ያዝን ያውም ሁለት ቤት ገብተን፡፡ ‹‹በእግራችን አስር ኪሎሜትሩን እንሂድ›› ስል አብራን ያለችው ልጅ ‹‹አልችልም›› አለችና ቀረን፡፡ የአርበኞች መታሰቢያ የሆነው የግራር አምባ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አሰፋ አስታጥቄ ናቸው የዘንድሮ መርሃ ግብር አዘጋጅ፡፡ መሪነቱ ወደ ትምህርት ቤቱ መተላለፉ በዓሉ የወላጆች፣ የመምህራንና የተማሪዎች ስለሚሆን ቀጣይነቱን ያረጋግጣል፡፡ ከእርሳቸው ጋር ስልክ እየተደዋወልን እየመጣን እንደሆነ ነገርናቸው፡፡ ሌሊቱን ሙሉ መብራት ጠፍቶ አድሮ የኔም ስልክ ዘግቶ ስለነበር በጓደኞቼ ስልክ ነበር የደወልኩላቸው፡፡ ከቤታችን ስንነሳና እርስ በእርስ ስንቀሳቀስም በአካል ሄደን ነበር እንጅ የስልክ ነገር ልይቶለት ነበር፡፡
ወደ ግራሯ ለመሄድ መኪና ስንፈልግም ኮንትራት 600 ብር ክፈሉ ተባልን፡፡ በዚህም ወቅት ከዘነበች ቤት ተሰናብተን ሄደን በታላቅ ወንድሜ ቤት ቡና እያስፈላን ስለነበረ መኪና ካልተገኘ እዚሁ ሰብሰብ ብለን እናክብር የሚል ሃሳብ ሰነዘርኩ፡፡ ከሳሲት ወደ አንዲት ግራር የሚወርዱ አምስት የሳሲት ነዋሪዎችም ስለነበሩ ነው እዚሁ እናክብረው ማለቴ፡፡ ህዝቡ መጀመሪያ የወላጆችን በዓል በግራር አምባ ትምህርት ቤት አክብሮ ወደ ግራሯ መጥቶ እየጠበቀን እንደሆነ በመስማታችን ከህዝቡ ጋር ለማክበር ወደ ግራሯ ለመሄድ ጓጉተን ነበር፡፡ ግራር አምባ ትምህርት ቤት የወላጆች በዓል ሚያዝያ 27 መከበሩ አያኮራዎትም? እውነትም የአርበኞች መታሰቢያ ትምህርት ቤት! በመሆኑም አንድ የወረዳው የስራ ሃላፊ በስልክ ደውለው መኪና አስመጥተውልን ፒክ አፕዋ ላይ ከውስጥም ከላይም ሆነን ወደ ስፍራው አመራን፡፡ የእለቱ ልዩ እንግዳና ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ስፍራውን ያየው የበላይ ዘለቀ ያገር ልጅ መምህር ሳለአምላክ ጥላሁን በሳሲት የቤቶቹ መጠጋጋትና የህዝቡ መጎሳቆል አሳዝኖታል፤ አስገርሞትማል፡፡ እኔ ግን እዚያው ተወልጄ ስላደግሁ ምንም አልመሰለኝም ነበር፡፡
ወደ አንዲት ግራር በሚወስደው መንገድ ስንሄድ የገጠር ቤቶችንና የእርሻ ማሳዎችን እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚታዩ የግራር ዛፎችን እያየን ነበር፡፡ የአማራ ክልል ኤፍ ኤም ባለፈው ዓመት በአንዲት ግራር ተገኝቶ የዘገበውን ዘገባ ዘንድሮ በድጋሚ እያቀረበው ኖሮ በመኪናው በተከፈተው ራድዮ ስናደምጠው ወረድን፡፡ ድንቅ ዝግጅት ነበር፡፡ በዚህ ዓመት አቶ ሕላዌ ዮሴፍና አቶ አዲሱ ለገሰም ግራሯን እንደጎበኙ ሹፌራችን ኤርሚያስ በጨዋታ መሃል ነግሮኛል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ባለውቃቢ ወፋ ነገሰን ለመጠየቅ ከሃገራችን የተለያዩ ክፍለ ሃገራት የሚመጡት ባለጉዳዮች በእግራቸው ወደ እርሳቸው መንደር ለመሄድ መንገዱን ሲጠይቁ የሳሲት ነዋሪ ‹‹ዝም ብላችሁ መኪና መንገዱን ተከትላችሁ ስትሄዱ አንድ ትልቅ ግራር ሜዳው ላይ ታገኛላችሁ፡፡ ከዚያ ወደ ቀኝ ታጥፋችሁ ትንሽ ሄዳችሁ እርሳቸው ቤት ትደርሳላችሁ፡፡›› የሚሏቸው ትዝ አለኝ፡፡ በእርግጥ ገንዘብ ለሚከፍል ተጓዥ መንገድ የሚያሳዩና ሻንጣ የሚሸከሙ ወጣቶች ሳሲት አይጠፉም ነበር፡፡ ይህ የሚሆነው የመሬሬው ጥቁር ጭቃ መኪና በማያስገባበት በክረምት ወቅት እንጅ በበጋማ በጭነት መኪና ተጭኖ የሚሄደው ሰው በአንድ ጊዜ ወደ መቶ ይጠጋ ነበር፡፡ አሁን ሳስበው የሚያናድደኝ አንድ ከተሜ በልጅነቴ አይቻለሁ፡፡ ተስተናግዶ ሲጨርስ ወፋ ነገሰ ቤት አቅራቢያ ያሉ አርሶ አደሮችን ‹‹ታምሜያለሁና በቃሬዛ ተሸክማችሁ ሳሲት ድረስ አውጡኝ ፤ ባይሆን ገንዘብ እከፍላችኋለሁ›› ብሎ ተሸክመው ይዘውት መጥተው ገንዘቡን ከፍሎ እየሳቀ ከተሸከሙበት አልጋ ሲወርድ አይቻለሁ፡፡ ቅኝ ገዥዎች የአፍሪካ ህዝብ ላይ እንዳደረጉት ያለ ለህዝቡ ያለውን ንቀት የሚያሳይ ድርጊት ነው፡፡ አሁን ወደ አርበኞች በዓላችን እንመለስ፡፡
ጥላሁን ጣሰው የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ውስጥ የተመሰረተው ዲሞክራሲያዊ ማሕበር የሆነው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የተቋቋመበት አንዱ ምክንያት ለአርበኛው ድርጅት ማስፈለጉ ግልጽ በመሆኑ ነበር ይሉናል፡፡ የማህበር ማቋቋሙ ሂደት ግን ፈተናዎች እንደነበሩበት ታሪክ ያወሳል፡፡ ከእነርሱም ውስጥ በአርበኞች መካከል አለመስማማት፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ማለት እና ወደ ጠላት መክዳት ይጠቀሳሉ፡፡
‹‹የነጻነታችን መሰረት አንዲት ግራር›› በሚል ርዕስ የሞጃና ወደራ ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ያዘጋጀው ግንቦት 2007 የተዘጋጀ ያልታተመ ጽሑፍ እንደሚያትተው ‹‹የሚንቀሳቀሰውን የወራሪ ጦር መደምሰስ የሚያስችል ሌላ የጦር ስልት ለመንደፍ በባላምባራስ በሻህ ኃይሌ አመራር ሰጭነት በየዱር ገደሉ የነበሩት አርበኞች ያስከተሉትን ጦር በመያዝ ጥር 1፣ 1931 በእንግድ ዋሻ ቀበሌ፣ አንቀላፊኝ ሜዳ፣ አንዲት ግራር ስር እንዲሰበሰቡ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡ በትዕዛዙ መሰረት ሁሉም የጦር አለቆች ያስከተሉትን ጦር በመያዝ በተባለው ቦታ እንዲገኙ ተደረገ፡፡ ወደ ስፍራው ከመጡት መካከል ዋና ዋናዎቹና ይመሩት የነበረው የጦር ሃይል ብዛት
ራስ አበበ አረጋይ - 1600 ጦር
ልጅ ግዛቸው ኃይሌ - 800 ጦር
ባላምባራስ በሻህ ኃይሌ - 600 ጦር
ደጃዝማች ተሰማ እርገጤ - 600 ጦር
ፊታውራሪ ታደሰ በላይነህ - 600 ጦር
ልጅ ከፈለው ወልደጻድቅ - 500 ጦር
አቶ ፀሐይ እንቁ ሥላሴ - 750 ጦር
ራስ መስፍን ስለሺ 1600 - ጦር ›› (3) ነበር፡፡
ሰነዱ ሲቀጥልም ‹‹እነዚህን የነጻነት አባት አርበኞችን ሊዘክር የሚችል ሃውልት በቦታው ተሰርቶ ጥር 1፣ 2002 ዓ.ም. በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ ተመርቋል፡፡›› (4) ይለናል፡፡
አርበኞች የተሰባሰቡባት የሰፊው ሜዳ ጌጥ የነበረችውን አንዲት ግራር ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት በ1990 የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ሲሆን አጥር የነበራትም ይመስለኛል ያኔ ሳያት፡፡ አድባር ነበር የመሰለችኝ፡፡ ታሪኳን አሁን ነው እየተረዳሁት የመጣሁት፡፡ አሁን ግን ነሐሴ 6 በጣለው መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ምክንያት መብረቅ መትቷት ወድቃለች፤ ህዝቡም እንደሰው ቁርባን እንዳቆረበላት እና ውለታዋን እንዳልዘነጋ ይታያል፡፡ ግራሯ ወዴት ወገን ወደቀች፤ እንዴት ወደቀች እየተባለ የራሱ የሆነ ትንታኔ በአካባቢው ነዋሪዎች ተሰጥቷል፡፡ አንድ ትልቅ ሰውም ይወድቃል የሚል ስጋት ጥሎባቸው ነበር፡፡ የቀድሞው የሰሜን ሸዋ አርበኞች ሊቀመንበር ባላምባራስ በየነ ይህ ስፍራ አርበኞች ማህበር በመመስረት ትግሉን ያጠናከሩበት የቃል ኪዳን ቦታ ነው ይሉናል፡፡ አርበኞች ከአራት ኪሎው ዋና ጽ/ቤታቸው ለመታሰቢያ በአቅራቢያው የተመሰረተውን የግራር አምባ ትምህርት ቤትንም ያግዛሉ፡፡ አዲሱ ሊቀመንበራቸው ልጅ ዳንኤል መስፍን ስለሺም ትምህርት ቤቱ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች በራሳቸው ወጭ በከፊል አሟልተዋል፡፡
እንግዲህ በዚህ ስፍራ የምናስባቸውን አርበኞች ተግባር ምንነት ለመረዳት አንድ ስማቸውን ለመጥቀስ ያልፈለጉ መምህርን አርበኛ ማለት ምን ማለት ነው? ብዬ ጠይቄያቸው ‹‹አርበኛ ማለት ትልቅ ጥልቅ የሃገር እና የወገን ፍቅር ያለው፣ የሃገሩን እና የወገኑን ጉዳት ማየት የማይሻ እና ለዚህም ማሳያ የሚሆን ውድ የሆነውን የህይወት መስዋዕትነት እስከመስጠት ድረስ ወደኋላ የማይል ነው፡፡›› ብለውኛል፡፡ ለእርስዎስ አርበኛ ምንድነው?
የአርበኞች ቀንን እንዴት ያከብሩታል ብዬ ላቀረብኩት ጥያቄ እኝሁ መምህር ሲመልሱልኝ ‹‹በውስጤ ነው የማከብረው፤ አከባበራችን ይለያያል፡፡ የማስበው ያን ያክል መስዋዕትነት ለማድረግ የነበራቸው የህዝብና የሃገር ፍቅር ስሜት ምናልባትም አሁን ካለው ትውልድ ጋር በማወዳደደር ዛሬስ ያለው ትውልድ ይሄን ትልቅ የህዝብ እና የሃገር ፍቅር ስሜት ይኖረዋል ወይስ ጠፍቷል የሚል አከባበር ነው፤ ስለሚያሳስበኝ ነው፡፡›› እኝህ መምህር ወደ ስፍራው ሳንሄድ ከሰጡኝ ከዚህ ምላሽ እንደምንረዳው በህሊናው አርበኞችን የሚያስብ እንዳለ ነው፡፡ በዓሉን በመሰባሰብ የሚያከብሩት ሰዎችስ እንዴት ያከብራሉ የሚለውን እስኪ እንይ!
ግራሯ በስፍራው ወድቃ ማንም ሳይነካት እንዳለች ይሄው አምስተኛ አመቷን ልጽደፍን ነው፡፡ ግራሯ ወድቃ ባችበት ስፍራ ስንደርስ ህዝቡ ተሰባስቦ ይፎክርና ይሸልል ነበር፡፡ በስፍራ የተገኙት ተማሪዎች፣ ወላጆች እና ተጋባዥ የአካባቢው ነዋሪዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ እኔና ጓደኛዬ መምህር ሳለአምላክም የተሰማንን ስሜትና ህዝቡ ስላዘጋጀው ዝግጅት ያለንን አክብሮት ገለጽን፡፡ አንዲት ሰላድንጋይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የምትማር ወጣት የላከችው ግጥም በመምህር ሻውል ማሞ ሲነበብ ስሰማ የወጣቱን ተሳትፎና ፍላጎት አደነቅሁ፡፡ ከግጥሟ ሁለት መስመር ብንወስድ
‹‹ኑ ታምሯን እዩ የሸዋን አፈር
አብቅላለችና አንዲቷን ግራር፡፡›› ይላል፡፡ ድንቅ እይታ!
ለግራር አምባ ትምህርት ቤት በስጦታነት ይዤ የሄድኩትን አጀንዳ መያዣ መዝገብ በስነ ስርዓቱ ላይ ሳበረክት አንድ ሽማግሌ የሚከተለውን መልዕክት ጽፈው ሰጡኝ፡፡ ‹‹ለመምህር መዘምር ግርማ፣ በረከቱ በአርበኛው ሰብሳቢ በኩል ለተረካቢው ቢሰጥ›› ይል ነበር፡፡ ለአርበኞና ለማህበራቸው ስጦታ ይዤ ባለመሄዴ ተጸጸትኩ፡፡ በሌላ ቀንም ለመውሰድ ቃል ገባሁ፡፡ በወረዳው 602 አባላት ያሉት የአርበኞች ማህበር ነው ያለው፡፡ ከስጦታ ወሬ ሳንወጣ ባለፈው ዓመት ለግራር አምባ ትምህርት ቤት ያሰባሰብንውን መጽሃፍ ስንለግስ የሌሎቹ ትምህርት ቤቶች ወላጆች ‹‹ሁሉንም ለግራር አምባ መስጠታችሁ ምነው?›› ብለውኝ ስለነበር መጽሐፍ ለሌሎቹም ወደፊት የማሰባሰብ የቤት ስራ አለብኝ፡፡ ሌላ የደረሰኝ ማስታወሻ የሚከተለው ነው፡፡ ‹‹ማሳሰቢያ ሰጭ አቶ አወቀ አክሊሉ ስሆን በዚች አንዲት ግራር እንድትተካ አንድ እግር ወርካ ተክዬ እየተንከባከብኩ ስገኝ አጽድቄ እያለሁ ሰዎች ነቅለውብኝ ሞራኔ ከስሮ እገኛለሁ፡፡›› ይላል፡፡ ባለፈው ዓመት አሁን ወድቃ በምትገኘው ግራር ምትክ እንዲተክሉ የቤት ስራ የወሰዱት አባት ነበሩ ይህን መልዕክት የላኩልኝ፡፡ ጥረታቸው አለመሳካቱ ያሳዝናል፡፡ አርበኞቹ የሚታወሱበት እንደ ህዝቡ ጥያቄ አንድ ሐኪም ቤት ወይንም ሌላ ለሕዝቡ የሚጠቅም ተቋም ቢቋቋም ግን ከዛፍ የበለጠ ማስታወሻ ይሆናል እለላሁ፡፡
አርበኞች በስፍራው በ1931 ዓ.ም. በጦርነት ወቅት ሆነው መደራጀታቸውን ሁሌም አደንቃለሁ፡፡ ያልተደራጀ ሕዝብ ምንም የረባ ነገር ላይሰራ ይችላል ብዬ ስለማስብ፡፡ አባቶች በበዓሉ እለት ስለአርበኞች ማህበር አመሰራረት የሚያውቁትን ነግረውናል፡፡ ሰነዳቸውን ካጸደቁ በኋላ 200 ዓመት ያህል ዕድሜ ባላትና ሰዎች ሲጣሉ በሚታረቁባት በዚህች ታሪካዊ ግራር ላይ ያረዷቸውን በጎች ስጋ ሰቅለው እየቆረጡ እየበሉ ተማማሉ ይሉናል፡፡ የአርበቻችን የትግል ህይወት ምን ይመስል እንደነበርና በስፍራው ተሰባስበው በሚመክሩበት ሰሞን ዋና ዋናዎቹ አርበኞች እነማን ቤት እንዳረፉ ጭምር ተነግሮናል፡፡
ቄስ ለማ ገብረመስቀል ባቀረቡት ግጥምና መልዕክት ማጠቃለያ ላይ የሚከተለውን ብለው ነበር፡፡ ‹‹ክቡራን እንግዶች፣ ትውልድ ያልፋል፤ ስም ግን ከመቃብር በላይ ስለሚቆይ ጊዜውን ጠብቆ በኢትዮጵያ ላይ ፈተና የሚገጥም በመሆኑ ወደፊትም በትጋትና በወኔ መቋቋም እንዲቻል የአርበኞቹን ተተኪዎች ልጆች እንድታስቡን አሳስባችኋለሁ፡፡›› የተዘጋጀውን ዳቦና ጠላ ከተጋበዝን በኋላ እና እየፈረሰች ባለችው ሐውልት አጠገብ ፎቶ ከተነሳን በኋላ ቸኩለን ስለነበር እና ዝናብም ስለጀመረ ወደ ሳሲት የመልስ ጉዞ ጀመርን፡፡ በዚህን ጊዜ አንድ አባት አርበኛ እየሮጡ መኪናችንን ሲከተሉ አይተን አቁመን አሳፍረናቸው ይዘናቸው ስንሄድ የሃምሳ አለቃ በላቸው እንደሚባሉና የሞጃ አርበኞች ሊቀመንበር አንደሆኑ ነገሩን፡፡ ለበዓሉ ሲሉ ይህን ሁሉ መንገድ በእግራቸው ሳይሆን አይቀርም የወረዱት! በበዓሉ ላይ ብዙ የማይረሳ ትዝታ ቢኖረኝም አሁን ስለበዓሉ ያናገርኳቸው ሰዎች ወደሰጡኝ ምላሽ እንሄዳለን፡፡
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት አቶ አክሊሉ ይርጉ ‹‹አንዲት ግራርን ካሁን በፊትም አውቃታለሁ፡፡ ስፍራው ጀግኖች አርበኞቻችን ማህበራቸውን ያቋቋሙበት እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ የሰሜን ሸዋው የአርበኞች ማህበርም ለማስተዋወቅ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ማስተዋወቁ ደግሞ ታሪኩ ለወደፊቱ ትውልድ እንዲተዋወቅና እንዲቀጥል እንዲሁም ስለስፍራው ዕውቀት እንዲኖረን ያግዛል፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያንን በመዋጋት አባት አርበኞቻችን ያደረጉትን ተጋድሎ በተገቢው መንገድ ለመዘከር ያስችለናል፡፡ ቦታውን የቱሪስት መስህብ ለማድረግና ለማስተዋወቅ ኮሌጃችንም ሆነ ዩኒቨርሲቲያችን የጋራ ሃላፊነት አለባቸው፡፡››
እሙዬ አረጋ (ጊፍቲ) ስለ በዓሉ አከባበር በሰጠችኝ አስተያየት ‹‹የአምናው አከባበር አሪፍ ነበር - አስበውበት ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን የአርበኞች ሽለላ እንኳን አነስተኛ ነው፡፡ የዘንድሮው ምንም አልታሰበበትም፡፡ ወይ ከምርጫው ወይ ከዋንጫው ሊሆን ይችላል፡፡ አምና በዛ ብለን ነበር የመጣንው፡፡ በእርግጥ ዘንድሮም ትምህርት ቤት አዘጋጅተው ሊሆን ይችላል እኛ ቸኩለን ዝናብም ሆኖ ነው እንጅ፡፡ አምና የልጁ መወለድ ነው ያስመሸን፡፡ የቀይት ጤና ጣቢያን አለፍ ብለን ሲወለድ ደብረ ብርሃን ከምንሄድ ተብሎ ነው የተመለስንው እና ልጁን ሃኪሞች መኪና አዋለዱ፡፡ የልጁ ስም ግን ማን ሆኖ ይሆን? አምና አብረውን በዓሉን ግራሯ ጋ ያከበሩት አራት አባቶች መሞታቸው አሳዝኖኛል፡፡ እኛ ፎካሪው ሰውዬ ሞተው እንዳይሆን …›› ብላኛለች፡፡ እኝህ ፎካሪ ባለፈው ዓመት
‹‹ራያው ከፌ
አዳባይ ገባ እንደ ወለፌ
ቦንብ አይሮፕላን ቲጥል በተራ
መትረየስ ቲጮህ መድፍ ቲያጓራ
የጎበራ ልጅ ይደባለቃል ተነጭ ጋራ!›› ብለው ጎራዴ ይዘው ሲፎክሩ የገባኝን ያህል ተረድቼ ግማሹ አማርኛቸው ስለከበደኝ ራሴን ከባህሌና ቋንቋዬ ምን ያህል እንደራቅሁ እንድታዘብ የረዱኝ ናቸው፡፡ እኝህ የኋላሸት የተባሉ ሽማግሌ አሁንም በህይወት እንዳሉ ከመርሃ ግብሩ መጠናቀቅ በኋላ በሌላ ቀን ሰው ጠይቄ አረጋግጫለሁ፡፡
የፖለቲካል ሳይንስና የፍልስፍና መምህሩን ለማ ሚዴቅሳንም በጉዳዩ ላይ አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ ለእርሳቸው ‹‹ጥቂት የፖለቲካ ልሂቃን የእነርሱ የሆነ አንድ ገናና አስተሳሰብ ብቻ ሃገሪቱ የምትመራበት ይሁን ብሎ ማሰብ በጣም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ምንጫቸው ከምንም ይሁን ከምን የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማስተናገድ የሚችል፣ የሚጠይቅ፣ በህግ የተሰጠውንም ነጻ አስተሳሰቦችን የመሰንዘር መብቱን የሚጠቀም ትውልድ ሊፈጠር ይገባል፡፡ የራስን ቁሳዊ፣ መንፈሳዊና ታሪካዊ እሴቶች የማያከብር፣ የማይንከባከብ እና የማያሳድግ ትውልድ ብዙም አያድግም፡፡
‹‹ይሄ ታሪክ የመላው ኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት የጋራ በሆኑ ታሪካዊ ቅርሶቻችን ላይ ሁላችንም ልንሰራ ይገባል፡፡ ያከባበር ስራዓቱ ሰፋ ባለና በደመቀ ሁኔታ ቢከበር ወጣቱ ኢትዮጵያዊነቱን እንዲያስብ እና ሃላፊነቱን እንዲወጣ ያግዝ ነበር፡፡ ነገር ግን ያ አለመሆኑ ነገሮች የበለጠ የከፉ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለን አዲስ ፌደራል ስርዓት ነው፡፡ ሰዎች በፊት ሲሰማቸው የነበረው ብሔራዊ ስሜት እየተሸረሸረ ክልላዊነት እያየለ መጥቷል፡፡ እና ይህን ባላንስ ያደርግ (ያመጣጥን) ነበር፡፡ ምን ያህል የሚያምር ታሪክ እንደነበረን፣ ከኛም አልፎ ለጥቁሮች አርዓያ የሆነ ታሪክ እንደነበረን ያስታውስ ነበር፤ ሊሰራበት ይገባ ነበር፡፡
‹‹ትውልድ ያልፋል ሃገር ግን ቋሚ ነው፤ ጠንካራና ያደገች አገር ለመመስረት የአንድነት ጠንካራ መሰረት ሊኖር ይገባል፡፡ አሁን ያለው አገር ያለመስዋዕትነት ያገኘነው አይደለም፡፡ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ ወደፊትም ቢሆን አንድ ሃገር ከውስጥም ሆነ ከውጭ አደጋ አይገጥማትም ማለት አይደለም፡፡ ይችን አገር በነበረችበት የጥንካሬ መሰረት ላይ ለማስቀመጥና እየጠነከረች እንድትሄድ ለማድረግ እንዲህ አይነት በዓላት ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ፖለቲካዊ ይዘት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ይዘትም አላቸው፡፡ በተጨማሪም ብዙ ፋይዳ አላቸው፡፡ የታሪካ አጋጣሚ ሆኖ በወቅቱ የነበሩት የፖለቲካ ልሂቃን ከሰሜን ሸዋ የወጡ ስለነበሩ ይህ የታሪክ መታሰቢያ እዚህ መደረጉ የሚከፋ አይደለም፡፡ ነገር ግን በሌሎች ቦታዎችም ያሉ ወጣቶችም የጋራ የሚያደርጋቸው በዓል ስለሆነ በዓሉ ሁሉም ቦታ ላይ ሊከበር ይገባዋል፡፡››
የአርበኞች መሪዎች በአሁኑ ወቅት የአሁኑ ትውልድ ድህነትን መዋጋት ነው ያለበት ሌላ ወራሪ የለብንም በሚሉት ላይ ለጠየቅኋቸው ጥያቄ ሲመልሱ መምህር ለማ የሚከተለውን ብለዋል፡፡
‹‹ለአንድ ሃገር ጠላቱ ድህነት ብቻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ችግሩ ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ሁሉንም ችግሮች በጋራ ለመቋቋም የሚያስችለን ስነ ልቦና መፍጠር አለብን፡፡ እንደዚህ ዓይነት ታሪካዊ ክስተቶችን ማውሳት ደግሞ ለዚያ አንዱ መንገድ ነው፡፡ ››
ሌላው ወደስፍራው አብሮኝ የተጓዘው መምህር ሳለአምላክ ደግሞ
‹‹በቦታው የተገኘነው የአርበኞች አባቶቻችንን በዓል ለማክበር ነው፡፡ አርበኞች አባቶቻችን አገራችንን ባህሏን፣ እምነቷን ሃብቷን ጠብቀውልናል፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ግን ያነበራቸውን ብዙ ነገር አጥተዋል፡፡ የነርሱን ውለታ መክፈል የምንችለው በዓሉን በየዓመቱ በማክበር ነው፡፡ በበዓሉ ላይ ተማሪዎችም አባቶችም ነበሩ፤ የመንግስት ተወካዮች ግን አልነበሩም፤ በዚህ ትንሽ ቅር ተሰኝቻለሁ፡፡ ለበዓሉ ትኩረት እንዳላደረጉ ነው፡፡ እንዲያውም ታስታውስ እንደሆነ ሰላድንጋይ እንደደረስን ከተማዋ በጣም አሸብርቃ ነበር በባንዲራ፡፡ እና እኛ ያሰብነው ምንድነው በዓሉ እየተከበረ ነው በሚል ነበር፡፡ ነገር ግን በኋላ የተረዳነው ነገር የአባይን ዋንጫ ለመቀበል እየተዘጋጁ መሆኑንና ስለበዓሉ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ጠይቀናቸው ስለበዓሉ ምንም ዓይነት ነገር አልሰጡንም፡፡ በቦታውም ስንደርስ የመንግስት ተወካይ አልነበረም፡፡ ይህ የሚሳየው በመንግስት ትኩረት እንዳልተሰጠው ነው፡፡ ለወደፊቱ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይሄ በዓል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ተምሳሌት ስለሆነ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አካባቢው የመሰረተ ልማት ችግር አለበት፡፡ ትምህርት ቤት ይከፈት ብዬ ስጠይቅ አርበኞች ምንድነው ያሉ ሆስፒታል ቢሆንልን ነው፡፡ እና የጤናም ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡ እንደሚታወቀው እድሜህ በገፋ ቁጥር በሽተኛ ትሆናለህ፡፡ እንክብካቤ ያስፈልግሃል፤ ርቀት ሄደህ መታከም አትችልም፡፡ ገቢም ላይኖርህ ይችላል፡፡ እና በዚያ አካባቢ ለአርበኞች ሆስፒታል እንዲቋቋምላቸው ለመጠየቅ እንደተዘጋጀን አስታውሳለሁ፡፡ ሳሲትን ከጠበቅኋት በታች ነው ያገኘኋት፡፡ ምን አልባትም የኪስ ከተማ ስለሆነች ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡ መንገዱ አስፋልት አልሆነም ከዋናው መንገድ ገባ ስትል፡፡ ምንም እንኳን ምቹ ቢሆንም አስፋልት ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ በክረምት ግን ጭቃ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ እና በጣም ግሎባላይዜሽን (ሉላዊነት) የገባባት ከተማ አትመስልም፤ በጣም ትንሽዬ ከተማ ናት፤ ደህና ካፌ እንኳን የለባትም፤ ገብተን ቡና ልንጠጣ ሻይ አዝዤ ቡና ብቻ ነው ያለው አለችኝ፡፡ ህዝቡም ቢሆን ምን ያህል በድህነት አረንቋ ውስጥ ያለ ህዝብ መሆኑ ያስታውቃል፡፡ እኔ ስፍራው ላይ ተገኝቼ በዓሉን በማበሬ ኩራት ተሰምቶኛል፡፡ ለወደፊቱም ሌሎችንም አሳምነን መንግስትም ያመነበት አይመስልም መንግስትም ህብረተሰቡን ቀስቅሶ እንድናከብር እመኛለሁ፡፡ ይህ በዓል እንደሚታቀው ትልቅ በዓል ነው፡፡ እዚያ ግራር አለች አባቶቻችን ጣሊያንን ለመዋጋት መጀመሪያ የተደራጁባት፤ ይሄ ነው የምትለው እንኳን ሐውልት አልቆመለትም፤ ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ይሄ የውጭ ወራሪን ያሸነፍንበት በዓል ነው፡፡ እና በግሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ወደፊትም ህጻናቱ እንዳቀረቡልን ስነጽሑፍ አዘጋጅተን ሰዎችንም ይዘን ተደራጅተን እናከብረዋለን ብዬ አስባለሁ፡፡ ››
መንግስት ለአርበኞች ማህበር መጠናከሪያ ገንዘብ እና ሌላም ድጋፍ በማድረግ እንደሚያግዛቸው ሁሉ ይህን በዓል በድምቀት በማክበር፣ የቀድሞው የመቶ ብር ኖት ላይ የነበረውን የአርበኛ ምስል መልሶ በማተም እና በሌሎችም አርበኞችን በሚያስታውሱ ተግባራት እንዲሳተፍ አሳስባለሁ፡፡ አስተያየትዎንም ይጻፉልኝ፡፡ እስኪ በነዚህ ፉካሮዎች እንሰናበት፡፡ ግን ለመጭው ዓመት ክብረ በዓል እንዳትቀሩ! አደራ በምድር አደራ በሰማይ!!!
እንበለውና ጉልበት ጉልበቱን
እያነከሰ ጨካኙ ጣሊያን ይውጣ ዳገቱን፡፡
የኢትዮጵያ ጀግኖች እኛው መጡ
አይናቸው ይመስላል መዳኒት የጠጡ
እንደ ሰደድ እሳት እየገላመጡ
ለጎጃም ንገሩ ለወሎ ንገሩ
ያ ጨካኙ ጣሊያን ተመልሶ ሄደ በመጣበት እግሩ፡፡
ራያ ከፈለው አይምጣ ይቅር
ጣሊያንን ገደለው አቤት አቤት ሲል፡፡
ዋቢ ጽሑፎች እና ቃለ ምልልሶች
‹‹ሪፖርተር›› Adwa victory by gallant Ethiopian warriors. 05/03/2014
Robert Wren’s article on www.adefris.info (this site is currentlu suspended)
ተድላ ዘዮሐንስ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ - ኢጣሊያ በኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ ማንኩሳ አሳታሚ፣ 2004 ዓ.ም.
‹‹አውራምባ ታይምስ››፣ 3ኛ አመት ቁ 113፣ ሚያዝያ 23/2002
ጥላሁን ጣሰው፣ አዳባይ፣ አዲስ አበባ፣ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት፣ 1975 ዓ.ም.
ከባላምባራስ በየነ አደለኝ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ፣ ሚያዝያ 10፣ 2006 ዓ.ም
መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ሐይሉ ወልደታሪክ፣ መንግስቱ ለማ፣ አ.አ.ዩ. ፕሬስ፣ 2003 ዓ.ም. ፣ አ.አ - ኢትዮጵያ
ከመምህራኑ ለማ ሚደቅሳ፣ ሳለአምላክ ጥላሁን፣ አክሊሉ ይርጉ እና ከወይዘሮ እሙዬ አረጋ ጋር በግንቦት 2007 የተደረጉ ቃለ ምልልሶች፡፡
የጉዞ፣ የንባብ፣ የቤተመጻሕፍት ፣ የሕትመትና ስርጭት ወዘተ ጽሑፎችን ያገኙበታል። I share my views and reports of my activities in this blog.
ዓርብ 3 ጁላይ 2015
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?
'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...
-
6 June 2019 Basic Writing Skills (Sophomore English) Lecture 1.1. Phrases and Clauses 1.1.1. Phrases A phrase can ...
-
እሁድ ከደብረብርሃን ካምፕ ወደ ኦሮሚያ የተመለሱት አማራ ተፈናቃዮች ምን ገጠማቸው? መዘምር ግርማ ደብረብርሃን ረቡዕ፣ የካቲት 13፣ 2016 ዓ.ም. ከብዙ ጭንቀት በኋላ በዕለተ ማክሰኞ ምሽት 4፡1...
የ2009 ጉዞ አስደሳችና የማይረሳ ነበር፡፡ ዘንድሮ 2010 የምናደርገውንም ጉዞም በጉጉት እየጠበቅን ነው፡፡ አጠር ያለ ማስታወሻ በዚህኛውም ጉዟችን አይቀርም፡፡ የአሁኑን ለየት የሚያርገው አስተባባሪው አዲስ አበባ የሚገኘው ማህደረ ሸዋ የወጣቶች በጎ አድራጎት ማህበር ዝግጅቱን ማስተባበሩ ነው፡፡ ስለምታነቡልኝ አመሰግናለሁ፡፡
ምላሽ ይስጡሰርዝ