ቅዳሜ 29 ኦገስት 2015

የንጉሱን እትብት ፍለጋ




የጉዞ ማስታወሻ  በመዘም ግርማ
ወደ ቤቴ ስሸሽ ብመታና ብሞት አስከሬኔን እዚያው ተውት፤ ከጠላት ጋር ግንባር ለግንባር ስፋለም ከሞትኩ ግን አጽሜ ወደ ትውልድ ስፍራዬ ይምጣ - ፊታውራሪ ገበየሁ
በደብረብርሃን ከተማ ጅሩ መንገድ የተገናኘንው አራት የዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ባዶ እጃችንና ቁርስ ሳናደርግ በእግር የኮረኮንቹን ጉዞ ተያያዝንው - ሰኞ የካቲት 16፣ 2007 በጠዋት፡፡ የጉዟችን መዳረሻ አጼ ምንሊክ የተወለዱበትና የአድዋው ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁ አጽም ያረፈበት አንጎለላ ኪዳነምህረት ነው፡፡ በእግራችን አንድ ሰዓት ገደማ የፈጀብን 10 ኪሎሜትር የሚሆነው መንገድ አስፋልት ቢሆን አይጠላም፡፡
በስፍራው እንደደረስን ሶስት ነጫጭ ፈረሶች አውድማ ላይ ገለባ ሲበሉ አይቼ ከጓደኞቼ ተለይቼ ሄጄ ፎቶ እያነሳሁ ከባለፈረሶቹ ጋር አወራለሁ፡፡ ‹‹ይህን ጽድ ማን ተከለው?›› አልኳቸው በመንገድ ዳር ዳር የተተከለ ጽድ አይቼ፡፡ መንገዱ ወደ አጼ ምንልክ መታሰቢያ ክሊኒክ እንደሚወስድና ጽዱም ክሊኒኩ ሲሰራ እንደተተከለ ነገሩኝ፡፡ ጓደኞቼን ካረፉበት ጠርቼ ክሊኒኩንና ሐውልቱን ጎበኘን፡፡ ክሊኒኩም ተከፍቶ የሚያውቅ አይመስልም - የሸረሪት ድር አድርቶበታል፡፡
ከዚህ ስፍራም ወደ  ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ሄድን፤ እናም በዚያ የነበረውን የንግስ ስነስርዓት ታደምን፡፡ አንድ ሰው ሰራሽ ጥንታዊ የዋሻ ምሽግን፣ አጼ ምንሊክ የተከሉትን ሾላ እና የመብረቅ መከላከያ ዛፍ ጎበኘን፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አንጀታችሁን የሚበላው ወደቤቴ ስሸሽ ብመታና ብሞት አስከሬኔን እዚያው ተውት፤ ከጠላት ጋር ግንባር ለግንባር ስፋለም ከሞትኩ ግን አጽሜ ወደ ትውልድ ስፍራዬ ይምጣ  ያለውን የፊታውራሪ ገበየሁን አጽም በአንድ የቤተክርስቲያኑ ግቢ ያለ ክፍል ውስጥ ስታዩ ነው፡፡ ከተቀበረና ከአድዋ ድል ከሰባት አመት በኋላ አጽሙ እንደመጣ የተነገረን ጎራው ገበየሁ ከድሉ በኋላ በጃንሜዳ የጦር አበጋዞች በፈረስ ሲያልፉ የእርሱ ፈረስ ብቻውን ከፊት ሲያልፍ ያዩት አጼ ምንሊክ ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱለት ይነገራል፡፡
በቤተክርስቲያኑ ያገኘናቸው እና እዚያው የሚኖሩት መነኩሴ ከጃንሆይ ጋር ለኬኔዲ ቀብር ዲሲ የሄዱ፣ ኮርያና ኮንጎ ለዘመተው ሻለቃ ጦር የነፍስ አባት ሆነው አብረው ተጉዘው የነበሩ፣ በደርግ የታሰሩና የተደበደቡ መሆናቸውን ሲነግሩን ያልጠበቅንውን ነገር በመስማታችን ተገርመናል፡፡ በ1916 ዓ.ም. ነው የተወለድኩት ብለውናል፡፡
ሕዝቡ አጼ ምኒልክ በተወለዱበት ስፍራና በቤተክርስቲያን እንግዶችን ደግሶ ያበላል፤ ለንጉሱና ለጎራው ገበየሁ ያለው ፍቅርም የትዬለሌ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ቤተክርስቲያን ግቢ ውስጥ ነዋሪው አንዱ ሰፈር ጠላ፣ ሌላኛው ዳቦ፣ ግማሹ እንጀራና ወጥ ታዞ አዘጋጅቶ ማየታችን እና መጋበዛችን ነው፡፡
የሕዝቡ አቀባበልና መስተንግዶ እጅግ የሚያስደስት የነበረ መሆኑን የምናሳይባቸው አንዲት ደግ እናት ቤተክርስቲያኑን ለቀን ስንወጣ አገኘን፡፡ እንጀራ እንዳልበላን ስንነግራቸው ወደቤቴ እንሂድ አሉን፡፡ እርምጃቸው ፈጣን ስለነበረ ከእርሳቸው ጋር መጓዝ አድካሚ ነበር፡፡ ሮጥ ሮጥ እያልን አብረናቸው እያወራ ሄድን፡፡ የሚቸኩሉት አጼ ምንሊክ በተወለዱበት ስፍራ ምግብ ማቅረብ ስላለባቸው የእድር ዳኛ እንዳይቀጣቸው እንደሆነ ነገሩን፡፡ በ1974 ዓ.ም. አጼ ምንሊክ በተወለዱበት ስፍራ ላይ በ15 አመት እድሜያቸው ትዳር ይዘው መንግስት ከስፍራው እንዲለቁ ያዛቸዋል፡፡ የእርሳቸው ቤተሰብና ሌሎች ልቀቁ የተባሉ አምስት አባወራዎች ‹‹አንለቅም፤ ሌላ ቦታም ቤት ለመስራት አቅም የለንም›› ሲሉ መንግስት ለእያንዳንዳቸው አርባ ቆርቆሮ እና አምስት እሽግ ምስማር ይሰጣቸዋል፡፡ አሁንም ‹‹አንለቅም አቅም የለንም ቤቱን ለመስራት›› ይላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ቀበሌው ታዝዞ ቤታቸውን ሰርቶ አጥሩን አጥሮ ያስረክባቸዋል፡፡ እነሱም በአዲሱ ቤታቸው ይገባሉ፤ የአጼ  ምንልክ መታሰቢያ ሀውልትና ክሊኒክም ይሰራል፡፡ ‹‹በወቅቱ ልጆቻችንን ሲያምብን ወስደን ገና አንድ መርፌ ሲወጉ ይድኑልን ነበር፤ ስፍራው የአጼ ምንሊክም ስለሆነ በረከትም ነበረው፡፡ አሁን ቁስል የሚጠርጉ ናቸው ያሉት እንደበፊቶቹ ጥሩ ሐኪሞች አይደሉም፣ እኔም ለመንግስት አቤት እንበል እያልኩ ነበር የሰማኝ የለም፡፡ እኔ አሁን በቅርቡ በጠና ታምሜ በየሆስፒታሉ ስዞር ሳይሻለኝ ቀርቶ ዶክተር አያናው ራሱ አክሞኝ ነው የዳንኩት፤ በሃብት ላይ ሐብት ይስጠው›› አሉን፡፡
በእርሳቸው ቤት የነበረው ግብዣ አስደሳች የነበረ ሲሆን ጠዋት ሐውልቱን ያስጎበኘንን ልጅ ገዘሃኝንም ዘመዳቸው ኖሮ እዚያው አገኘንው፡፡ በጥሩ ሁኔታም አስተናገደን፡፡ በሬውንም ፎቶ እንዳነሳውም ጠየቀኝ፡፡ በዚህ ቤት ውስጥም ሆነ በቤተክርስቲያን ውስጥ አማርኛም ሆነ ኦሮምኛ በእኩል ይነገራሉ፡፡ ተናጋዎቹ በአብዛኛው ሁለቱንም ቋንቋዎች አፉን እንደፈታባቸው ሰው ሁሉ እኩል አቀላጥፈው ይናገሯቸዋል፡፡ ዱቢሳ አማኑኤል የሚባል ቤተክርስቲያንም በቅርብ እንዳለ ነገሩን፡፡ የተደባለቀ ህዝብ ነው፡፡ ገዛሃኝ እንደገና ከዚያ ቤት ተሰናብተን ወደ ራሱ ቤት ወስዶ ጋበዘን፡፡ ‹‹ኑ አጎቴ ቤትም ግቡ›› አለን ከዚያ በኋላ፡፡ በጣም ስለጠገብንም ሰላምታ ብቻ ሰጥተናቸው ስንሄድ ቅር እያላቸው ነበር፡፡ ከባልንጀሮቼ አንዱ በኦሮምኛ አንዱን ወጣት አስር ልጅ ውለድ ሲል መክሮታል- እኔ መጀመሪያ አስራሁለት ያልኩትን በማሻሻል፡፡ ሰኞ ኦሮምኛ የምለማማድባት የተባረከች ቀን ነበረች፡፡ ጽሑፉን ከወደዱት እና ከቻሉ አንጎለላን እንደኛ ሄደው ይጎብኟት እልዎታለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...