2015 ኖቬምበር 16, ሰኞ

ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቡና የጋበዘቻቸው መንዜ ልጃገረድ


የአሁኑ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የዳሽን ቢራ ፋብሪካን ሊያስመርቁ ደብረብርሃን ከተማ ይገኛሉ፡፡ እንደሚመጡ ከሁለት ቀን በፊት በራዲዮ ፋና ሰምቼ ነበር፡፡ በሄሊኮፕተር መሆኑን ማን ጠርጥሮ! ግልገልና እናትየዋ ሜዳ ላይ ቆመዋል፡፡ በ2001 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋን የጎበኙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲመጡ ወደ ደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ጠዋት ክፍለጊዜ ስለነበረኝ ስሄድ በትጥቅ አጀብ ሲሄዱ አይቻለሁ፡፡ እርሳቸው ይሆናሉ ብዬ ልጠረጥር አልችልም ነበር፡፡ በዚያ የሚያንገጫግጭ አስቸጋሪ ጎዳና፣ በተለይ ከጣርማበር በኋላ ባለው 130 ኪሎሜትር ኮረኮንቻማ መንገድ በመኪና ለምን ሄዱ እያልኩ አስባለሁ፡፡ የመሃል ሜዳ ሆስፒታልን ያስመረቁት ሚኒስትር እንኳን በሄሊኮፕተር ነበር የሄዱት፡፡ ታጋዮች በእግራቸው መሄዳቸውን አስበው ወይንም አገሩን ቀረብ ብለው ለመቃኘት ፈልገው ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሃል ሜዳ ሲገቡ ህዝቡ አያውቅም ነበር፡፡ ጥበቃዎች ታዳሚዎቹን አብጠርጥረው ፈትሸው አስገቧቸው፡፡ ዛሬ ጠዋት ያገኘኋት ልጅ ቡና አፍዪ ነበረች፡፡ "እርሳቸው ምን እንደተናገሩ ትዝ አይለኝም፡፡ ጋቢ፣ ዝተትና መንዝ ጌራ የሚል ምንጣፍ ሰጧቸው፡፡ አንዲት ሆድዬ የተባሉ እናት ወደ እርሳቸው ለመጠጋት ሲሞክሩ ጠባቂዎቹ አናስጠጋም አሏቸው፡፡ መለስ ግን ይምጡ አሉ፡፡ ቤቴ በባንክ ተወርሶብኛል ብለው እግራቸው ላይ ወደቁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይመለስልዎታል፤ ባይሆን እዳዎትን እከፍላለሁ አሏቸው፡፡ ሴትየዋም ትከሻቸውን ሳሙ፡፡ አሁን ሆድዬ በቀበሌያችን ዋና የመንግሥት ደጋፊ ሆነዋል፡፡ እርሳቸው የሌሉበት ስብሰባ አይደምቅም፡፡ አበባ ያበረከተችው ልጅ አንድ ዓመት ሙሉ ፊቷን ታመመች፡፡ የሰዉ ዓይን! የመሀል ሜዳው ሁለገብ አዳራሽ የመጀመሪያውን የአገር መሪ አስተናገደ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደመጡ ህዝቡ ለመኪናቸው ሳር በማቅረቡ 'እናንተ በጣም የዋሆች ስለሆናችሁና ፈረንጅ መጥቶ ሊጎዳችሁ ስለሚችል መንገድ አናሰራላችሁም' እንዳሏቸው አንድ አዛውንት አጫውተውኛል" ብላኛለች፡፡ መራዊ ከተማ ባህርዳር አቅራቢያ ግን የቀድሞው መሪ ሲያልፉ አስፋልት ላይ ተንበርክከው የለመኑ ቤታቸው የተወረሰባቸውን የደርግ ባለስልጣን መኪናው ገሸሽ ብሎ አልፏቸዋል አሉ፡፡ ጃንሆይ ሲመጡ ነጠላ ካነጠፋችሁ አቤቱታ ይቀበሉ ነበር አሉ፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም ደብረብርሃን እንደመጡስ ታስታውሳላችሁ? ሌላ የመሪዎች ጉብኝት ትዝታ አላችሁ?

1 አስተያየት:

  1. መንግስቱ ኃ/ይለማርያም አዎ ደብረብርሃን መጥተው ነበር፡፡ ምናልባት 1982/83 ዓ.ም፡፡ እንደሚመጡ ተነግሮን ስለነበር የኃይለማርያም ማሞ ተማሪዎች ሰልፍ ይዘን ወደ ያኔው መስቀል አዳባባይ እያመራን እያለን ሼል አካባቢ ስንደርስ እየመጡ ነው መንገድ ልቀቁ ተባልንና በጀርባ በቀበሌ አምስትና ስድስት አድርገን በስላሴ በኩል ልንገባ ስንጣደፍ አጅሬው ስታዲዮም ገቡ በር ተዘጋ መግባት አይቻልም ተብሎ ተከለከልን፡፡ ብዙ ሞክረን እንደማይቻል ስናውቀው ወደ ቤታችን ውስጡ ውስጡን ተመለስንና አስፓልት መሻገር ስለማይቻል ቀበሌ 4 ልጆች ሁላችንም ጸሐይ ላይ ተሰጥተን መዋላችንን በኋላ እርሳቸው ቀበሌ 4 ወደ ነበረው 605ኛ ኮር ሲገቡ ከስድስት ሰዓት በኋላ አስፓልቱን እንድንሻገር ቢፈቀድልንም ፤የእኔና ጓደኞቼ ቤት ደግሞ ከካምፑ ጀርባ ስለነበር አሁንም በመካከል ባለ መንደር ውስጥ እንድንገባ ተደረገ፡፡ በኋላ ግን እርሳቸው ከዚያ ሲወጡ በቅርብ እርቀት ላይ እያየናቸው በሩቅ እጃቸውን ተሳልመን መሄዳቸውን አውቃለሁ፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...