ባለፈው
ያቀረብኩት የአስራ አራት ስራ ፈጣሪ መምህራን ተሞክሮ አነጋጋሪ የነበረ ይመስለኛል፡፡ በዚያ ተነሳስተው በሰዓቱ መንገዳቸውን የጀመሩ
እንዳሉ ተገንዝቤያለሁ፡፡ ዛሬ የማቀርበው መምህር እዚህ ደብረ ብርሃን ላይ የእውነት ስራ ፈጣሪ ነው ስላችሁ ከሐቅ ነው፡፡ የሚሰራው
ስራ እነሆ፡-
‹‹በየዕለቱ
ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንደተመለሱ የቤት ስራቸውን ተከታትሎ እንዲሰሩ ማድረግ፣ በየዕለቱ የተማሩትን ሁሉንም ትምህርት ወደሚቀጥለው
ቀን ሳይሸጋገር እንዲከልሱና እንዲያጠኑ ማድረግ›› ይላል ማስታወቂያው፡፡
ከአንደኛ
እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል በአምስት ትምህርቶች ላይ የማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጥበት ይህ ተቋም ኤፈርት ዞን የቱቶሪያል ማዕከል
ይባላል፡፡ ልጆች ከጥገኝነት መንፈስ እንዲላቀቁና በራሳቸው እንዲያጠኑ
ያደርጋል፡፡ መምህራንም ተማሪዎቹ በተቸገሩባቸው ነጥቦች ላይ መጠነኛ እገዛ ያደርጉላቸዋል፡፡ አብዛኛውን ስራ በራሳቸው እንዲሰሩ
የሚደረጉት ወደዚህ ማዕከል የሚመጡት ተማሪዎች በራስ የመተማመን ስሜታቸው እየጎለበተ ይሄዳል፡፡ ታዲያ ለዚህ ስራው 200 ብር ወርሃዊ
ክፍያ አንድን ተማሪ ማስከፈል ይበዛበታል?
ታዲያ
በአብዱ ጀባር ህንጻ (ደብረ ብርሃን ቀበሌ 03) የማጠናከሪያ ትምህርቱን የመስጠቱ ሃሳብ ከየት ፈለቀ አይሉኝም? አሁን በማዕከሉ
የማስጠናቱን ስራ የተያያዙት መምህራን በፊት በፊት በየቤቱ ያስጠኑ ነበር፡፡ ሲያስጠኑ ግን ተማሪው የሚጠብቁትን ያህል መሻሻል ሳያመጣ
ይቀራል፡፡ ምክንያቱን ሲመረምሩት ብዙ ጥረት የሚያደርጉት መምህራኑ ራሳቸው እንጂ ተማሪዎች ስላልሆኑና ተማሪዎች የመለማመጃ ዕድላቸው
አናሳ በመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔ ያሉት አሁን የጀመሩት ስራ ነው፡፡ በየትምህርት ዘርፉ ከየትምህርት ቤቱ የተውጣጡትና በስነ-ምግባራቸው
የተመሰገኑት መምህራን ከመደበኛ የስራ ሰዓት በኋላ እየተገኙ ተማሪዎችን ያግዛሉ፡፡ ቅዳሜ የመለማመጃ ጥያቄዎችን ያሰራሉ፡፡ እንግሊዝኛን
ኦዲዮ ቪዲዮ ጭምር በመጠቀም ሲያስተምሩ አይቻለሁ፡፡ በክረምትም የማጠናከሪያ ትምህርቱ አይቋረጥም፡፡
ነሐሴ
15፣ 2008 ዓ.ም. ማዕከሉ በድምቀት ሲመረቅ በነበረው የሥልጠናና የውይይት መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት ወላጆች፣ ተማሪዎች፣ ምሁራንና
ባለድርሻ አካላት የሰጧቸውን ሃሳቦች በመጠቃቀስና እርስዎም ጥያቄና አስተያየትዎን እንዲለግሱ በመጋበዝ እዚህ ጋ ልሰናበት፡፡
- ወላጆች ላይ ስለ አሰራራችሁ የግንዛቤ ስራ
መሰራት አለበት፡፡
- ለልጆቻችን በቂ ድጋፍ፣ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ
ለማንችል ሰዎች መልካም ዕድል ነው፡፡
- ከትምህርት ቤት መልስ በየቤታችን የልጆቻችንን
አእምሮን የሚያበላሹ ነገሮች ስላሉ ልጆቹ እዚህ መቆየታቸው መልካም ነው፡
- ሞባይልና ኢንተርኔት ጤናቸውን ስለጎዳብንና
ሱሰኛም ስላደረገብን ቁጥጥር እናድርግባቸው፤ ልጆቹ ላይ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣትም አሰልጥኑልን፡፡ የጊዜ አጠቃቀምና የአጠናን
ስልት ስልጠና የሚያስፈልገው ብዙ ልጅ አለ፡፡
- የፊልም አማራጭ የበዛበትና ቴክኖሎጂን በተሳሳተ
መንገድ በሚጠቀሙበት ሁኔታ ይህ ማዕከል ሁነኛ ስፍራ ነው፡፡
- ከፊልምና ከቴክኖሎጂ ጋር የሚከፈተው ውጊያ
አንዱ ግንባር ይህ ቤት ነው፡፡
- በቀን ከአራት እስከ አምስት ሰዓት በላይ ለፈልም
የሚቀመጥ ወላጅ ለልጁ ትምህርት ትኩረት ባይሰጥ አይገርመኝም፡፡ ልጃችን ግን ቢያጠና ምን ይሆናል?
- ያልነበረ ነገር እንደዚህ ፈጥራችሁ ልጆቹ ላይ
ለውጥ አምጡልን፡፡
- በዚህ አጀማመር ያላሰባችሁት ነገር ሁሉ ሊሳካላችሁ
ይችላል፡፡
- ትምህርታዊ ውድድሮች፣ ፊልሞች፣ የጥያቄና መልስ ውድድሮች ይኖሯችኋል
ብዬ አስባለሁ፡፡
- ወላጆች የልጃችንን ልብሱን ብቻ አይደለም መቀየር ያለብን፤ አእምሮውንም
ነው፡፡
- የዚህ ማዕከል ውጤት የሚታየው ከብዙ ዘመን በኋላ ነው፡፡ እስከዚያ
ግን ብዙ መጋር ያሻል፡፡
- ልጆቻችንን አያባትልብንም ወይ?