2017 ኖቬምበር 17, ዓርብ

ስለበይነ-መረብ አጠቃቀማችን




በይነ-መረብ (Internet) መኖሩን ያወኩት በ1996 ሳይሆን አይቀርም፡፡ በመሰናዶ ትምህርት ቤታችን፣ ኃይለማርያም ማሞ፣ ደብረ ብርሃን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በፊት ሒሳብ መምህራን የነበሩት ናቸው ይህን ትምህርት ያስተምሩ የጀመሩት፡፡ አንድ ጃፓናዊ መምህርም መጥቶ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አንዳንድ ቀን ላብ ውስጥ ያስተምረን ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ኮምፒውተር መኖሩን ሳይቀር ያወኩት ከዚህ ዓመት ብዙም አይቀድምም፡፡ በ1993 በአንዳንድ ቢሮዎች ውስጥ አይቼ ሊሆን ይችላል፡፡ ቴሌቪዥንን የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ያየሁት ሰው ለኮምፒውተር ብዙም አልዘገየሁም ማለት ይቻላል፡፡
በይነመረብን ልተዋወቅ የቻልኩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የኬኔዲ ቤተመጻሕፍት ነው፡፡ የባሌው ልጅ ጓደኛዬ ነው ያስተዋወቀን(ስሙ ባልሳሳት ከማል ይስለኛል - ይህን የምለው ውጤት ስላልሞላለት ትምህርቱን ሳይጨርስ ወደ አገርቤት ስለሄደ ጊዜው ስለረዘመ ነው)፡፡ ቤተመጻሕፍት ውስጥ ከካታሎጉ አጠገብ ብዙ ኮምፒውተሮች ያለምንም ተጠቃሚ ተከፍተዋል፡፡ ይህ ጓደኛዬም ብቻውን ይጠቀማል፡፡ አጠቃቀሙን ስጠይቀው አሳየኝ፡፡ ‹‹የምትፈልገውን ጻፍበት›› ሲለኝም ፍኩበትና ፈልጌ አገኘሁ፡፡ ይህ ቤተመጻሕፍት በቀን እስከ አራት ሰዓት ለሚሞላ ጊዜ ኢንተርኔት እጠቀምበት የነበረ ነው፡፡ አሰራሩ እንደዚህ ነበር፡፡ ጠዋት ከቁርስ በኋላ የኢንተርኔት ወረፋ ለመያዝ መታወቂያችንን ተራ እናስገባለን፡፡ ከዚያም ሰራተኞች ሲገቡ ይከፈትና እንጠቀማለን፡፡ እንዲህ እንዲህ እየተባለ ከትምህርት መልስ ጊዜው በኢንተርኔት ያልፍ ነበር፡፡ ያኔ እንደዛሬው ፌስቡክ የለም፡፡ ግፋ ቢል ፔንፓል ነው ያለው፡፡ አንዳንድ የዲያስፖራ ሚዲያዎን እከፍት እንደነበርና የፖለቲካ ንቃተ-ህሊናዬ ከፍ ብሎ እንደነበር አስታውሳሁ፡፡ ግን ያኔ ፖለቲካን ያልኮመኮመ  ማን ነበር፡፡ ቦታው ለዚህ ክፍት ነበር፡፡ ጋዜጣው፣ ሬዲዮኑ (በቀን ለብዙ ሰዓታት ሬዲዮ አደምጥ ነበር) ምኑ ቅጡ፡፡ ጊዜው ደግሞ 1997 ነበር፡፡ ‹‹ትምህርቱ መቼ ይጠናል?›› ካላችሁ ልክ ናችሁ፡፡ ያው የእንግሊዝኛ ተማሪ ብዙም አያጠናም ነው መልሱ፡፡
አሁን የኢንተርኔት ሱስ ባመነመነኝ በዚህ ሰዓት-  ኢንተርኔትን ካወቅሁ 13 ዓመት በሆነኝ በአሁኑ ጊዜ - ባወራለት ጥሩ መሰለኝ፡፡ አጠቃቀማችን ላይ ላትኩር፡፡
1. ፌስቡክ ብቻ ለምን? የምንጠቀመው ማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ከሆነ ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ ኢንተርኔት ውቅያኖስ ስለሆነ ወጣ ብለን ማየት አለብን፡፡
2. ጉግል በአማርኛ - ጉግልን እንደ መረጃ መፈለጊያ መጠቀም ትልቅ ብልህነት ነው፡፡ በእርግጥ ለኛ የቋንቋ ገደብ አለብን፡፡ እንግሊዝኛን በምቾት አንጠቀመውም፡፡ ለዚህ አንድ መፍትሔ አለው፡፡ ይኸውም የምንፈልገውን ነገር በአማርኛ ጽፈን ጉግል ላይ መፈለግ፡፡ ብዙ መረጃዎች ስላሉ ፈልጉ፡፡ አንዳንዴ በእንግሊዝኛ ከማገኘው የተሻለ በቋንቋዬ አገኛለሁ፡፡
3. ማንበብ ብቻ ሳይሆን መጻፍም - ማንበብ ብቻ ሳይሆን መጻፍም እንደምንችል የማናውቅ እንኖራለን፡፡ ዳውንሎድ ብቻ ሳይሆን አፕሎድም ማድረግ እንችላለን፡፡ ለዚህም በነጻ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እኔ የምጠቀምባቸውን ነገሮች ለአብነት እነሆ - http://mezemirethiopia.blogspot.com/
https://authenticethiopia.wordpress.com/
4. ጉግል - ጉግል ብዙ ነገር አለው፡፡ እኛ የምውቀው ጉግል ዌብ ብቻ፣ ምናልባት ምስል ከሆነ ገና ይቀረናል፡፡ ለምሁራን ምሁራዊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት ጉግል ስኮላርን እንጠቀም፡፡ ጉግል ኧርዝም አለ፡፡
5. ዩቱብ - ዩቱብ ላይ የተለያዩ ቪዲዮዎች አሉ፡፡ ታዋቂ የዓለማችን ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀሩ የሚያስተምሩትን ትምህርት ቪዲዮ ይለቃሉ፡፡ የኮርሳችንን ወይንም የምዕራፋችንን ስም ጽፈን መሞከር ነው፡፡
6. ኦንላይን መማር - ኦንላይን መማር እንደሚቻል የምናውቅ ስንቶቻችን እንሆን፡፡ በራስ ተነሳሽነት ቋንቋ፣ ኮምፒውተር፣ ሙዚቃ ወዘተ መማር ይቻላል፡፡ በነጻ የሚሰጡ ትምህርቶችን ተከታትለን ኮርሶችን ማጠቃለልም ይቻለናል፡፡ ለመማር open courseware አንዱ ቦታ ነው፡፡
7. ስማርት ፎን ላለው ሰው ደግሞ ሁሉ ነገር ቀና ነው፡፡ በተለይ ዋይፋይ ካለማ ምን ችግር አለ፡፡ እንግሊዝኛ መማሪያ ፖድካስቶችን ማለትም የድምጽ ፋይሎችን አውርዶ ማድመጥ አንዱ ነው፡፡ አፕሊኬሽኖችም እጅግ ጠቃሚ ናቸው፡፡
ተጨማሪ የምታጋሩት ካለ ኢንተርኔትን ብዙም ለማያውቅ ሰው ስለሚጠቅም መድረኩን እነሆ ብያለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...