የአንድ ገጽ የመጽሐፍ ማጠቃለያዎቼ
መዘምር ግርማ
የመጽሐፉ ርዕስ - የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት(1923 – 1948 ዓ.ም)፤
ደራሲ - አምባሳደር ዘውዴ ረታ፤ አሳታሚ - ሻማ ቡክስ፤ በድጋሚ
የታተመበት ዘመን - 2005፤ የገጽ ብዛት - 809፤ ዋጋ - 400 ብር፤
ማሳሰቢያ፡- ይህን መጽሐፍ ለማንበብ ለሚነሣ ሰው የማሳስበው ነገር ቢኖር
ከዚህ መጽሐፍ በፊት ያለውን ታሪክ የያዘውን በእኚሁ ደራሲ የተጻፈውን ‹‹ተፈሪ መኮንን ረጅሙ የስልጣን ጉዞ›› የተባለውን መጽሐፍ
እንዲያነብ ነው፡፡
በቀደመው መጽሐፍ የተነሡትን የተፈሪ መኮንንን በሥልጣን የመደላደል ጥረት
ወደጎን ትተን (ማጠቃለያውን ስለጻፍኩ ሊያነቡትም ይችላሉ) ጥቅምት 23፣ 1923 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተብለው የነገሱትን መሪ
የመጀመሪያዎቹን 25 ዓመታት የንግሥና ጉዞ የሚያሳየውን ይህን መጽሐፍ እንመልከት፡፡
ኢትዮጵያን ከዓለም መንግስታት ማህበር ለማስገባትና አገሪቱም በአጼ ምኒልክ
ዘመን የጀመረችውን የዘመናዊነት ጉዞ ለማጠናከር ቆርጠው የተነሱት ንጉሠ ነገሥቱ መሳፍንቱ ቢቃወሟቸውም ከፍጹም ፋውዳላዊ ወደ ሕጋዊ
አስተዳደር አገሪቱን የሚያራምደውን ሕገመንግሰታቸውን ለማጽደቅና አንዳንድ ሌሎች ለውጦችን ለማስተዋወቅ በቅተዋል፡፡ በአጠቃላይ ከአልጋ
ወራሽነታቸው ጀምሮ አገሪቱን ለ58 ዓመታት የመሩት ኃይለሥላሴ ለስራቸው የሚያግዟቸውን ሰዎች ለማስተማር ጥረታቸው በከፈቷቸው ትምህርት
ቤቶች ህልውና ብቻ ሳይሆን ለትምህርት ጉዳይ በሚያደርጉትም የቅርብ ክትትል ይስተዋላል፡፡ ከታናናሾች፣ ማለትም ከደሆችና የባላባት
ዘር ካልሆኑት ወገን፣ የሚያስተምሯቸው ልጆች ከሚማሩበት አንዱ የነበረው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ያፈራቸው ልጆች አድገው የሚያመጡት
ዓይነተኛ ለውጥ በታሪካችን ይታወሳል፡፡
‹‹ከመንደር ወሮበላነት›› እንዴት ወደ ኢጣሊያ ገዥነት እንደደረሰ ታሪኩ
በዝርዝር የቀረበው ቤኒቶ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ለህልውናዋ የሚያሰጋት መሆኑ ከአድዋ ታሪክም ጋር ስለሚያያዝ የአንባቢን ፍላጎት የሚይዝ
ነው፡፡ ኃይለሥላሴ ኢጣሊያን እንደጎበኙ ያስተናገዳቸው ሙሶሊኒ ለኢትዮያ የደገሰላትን ነገር በግልጽ አላሳየም ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ያጠላውን ‹‹ጥቁር ዳመና›› ለመቆስቆስ የተነሣው የወልወል
ግጭት ‹‹አያ ጅቦ ሳታመሃኝ ብላኝ›› ዓይነት ነው፡፡ ይህች ዙሪያዋን በሦስት ቅኘ ገዥዎች የተከበበችው አገራችን ራሷን ለመከላከል
የጦር መሳሪያ እንኳን እንዳታስገባ ተደርጋ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ላይ በተፈጸመው ወረራ ጉዳይ በቫቲካን አቋም ላይ በቀረበው ጥልቅ
ምርምር እንደተመለከተው መንበረ ጴጥሮስ የፋሽስት ወረራ ተቃዋሚ እንደነበረችና ሊቀ ጳጳሱ ፓፓ ፒዮስም ኢትዮጵያን የሚወዱና ነጻነቷን
የሚፈልጉ መሆናቸው ተገልጧል፡፡ እንዲያውም ተቃውሞ ሲያሰሙ ሙሶሊኒ ማስጠንቀቂያ አድርሷቸዋል፡፡ የተወሰኑት ጳጳሳት ግን ለፋሺስት
ጦር ባደረጉት ድጋፍ ታሪክ ይወቅሳቸዋል፡፡ ቫቲካን ኢትዮጵያን ይቅርታ ትጠይቅ የሚባለውም ይህን አስመልክቶ ሳይሆን አይቀርም፡፡
መሪዎቻቸውንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን በየጊዜው የሚለዋውጡት የፈረንሳይና
የእንግሊዝ መንግስታት ለኢትዮጵያም ነጻነት በተደረጉት ንግግሮችና ውይይቶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የፖለቲካ ጥቅማቸውንና አቋማቸውን
በሚጠቅም መልኩ ሲያዩት ቆይተዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በኢጣሊያ በ1928 በተወረረችበት ጊዜ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ (የመንግሥታቱ ማህበር)
ተጠቂዋ አገር ባቀረበቻቸው አቤቱታዎች ተንጸባርቋል፡፡ ፈረንጆቹ አገራችንን መስዋዕት አድርገው ማቅረባቸው ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥ
ሶስቱ መንግስታት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ቀድሞ የተፈራረሙትን የምስጢር ውል እስከዚህ ጊዜ ድረስ እንደሚጠቀሙት ይታወቃል፡፡ የማህበሩ
አባል አገራት በማዕቀብ ሊያስፈራሩት የሞከሩትን ሞሶሊኒን አንዳንዶቹ አገሮች በምስጢር ሲደግፉት ቆይተው በመጨረሻም ኢትዮጵያን መያዙ
ግድ ሆነ፡፡ በዚህ በደቡብ፣ በደቡብ ምሥራቅና በሰሜን ግንባሮች በነበረው ውጊያ የኢትዮጵያ ጦር የድርጅት፣ የአመራርና የመሳሪያ
ማዕቀብ ችግር ቢኖርበትም፤ በተቻለው አቅም ለመከላከል ሞክሮ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ፋሺስቶች የተጠቀሙት በዓለም የተከለከለው የመርዝ
ጋዝ የኢትዮያን ጦር ወደ መፈታት፣ ንጉሠ ነገሥቱን ወደ ስደት፣ የአርበኞንም እንቅስቃሴ ወደ መጀመር አደረሰው፡፡
የተፈራው ደርሶ ሙሶሊኒ ፊቱን ወደ ሂትለር በማዞር ወዳጅነቱን አጥብቆ
እንግሊዝና ፈረንሳይን በማጥቃቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊጀመር ቻለ፡፡ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ለመርዳትና ፋሺስትን ከአገሪቱ ለማስወጣት
በመወሰናቸው ከስደት ተመላሹ ንጉሠ ነገሥትና አርበኞችም በተሳተፉበት ዘመቻ ጣሊያን ከአገሪቱ ተባረረች፡፡ እንግሊዞችም ጣሊያንን
ካስወጡ በኋላ የቅኝ አገዛዝ ዓይነት አስተዳደር ለመመስረት አስበው አስቸገሩ፡፡ ከብዙ ዲፕሎማሲያዊ ትግል በኋላም ከኦጋዴን በስተቀር
ያሉትን ክፍሎች ለቀቁ፡፡ ‹‹የኤርትራን ጉዳይ›› የሚለው የዘውዴ ረታ ሌላኛው መጽሐፍ በኤርትራ በኩል ያለውን ሁኔታ ስለሚያትት
በሱም ላይ የጻፍኩትን ማጠቃለያ ያንብቡ፡፡ የኢትዮጵያንና የእንግሊዝን ግንኙነት ለማስተካከል የቻሉት የአሜሪካ መሪዎች የአገራችን
አዲሶቹ ደጋፊዎችና አጋሮች ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡
ቀጣዩን የመጽሐፉን ሰፊ ክፍል ይዞ የምናገኘው የአቶ መኮንን ሀብተወልድና
የጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ የስልጣን ዘመን ነው፡፡ ሁለቱም የመንዝና የቡልጋ ዝርያ ያላቸው ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸው ህልም
አይተውላቸው ወደ ቤተመንግስት እንዲጠጉ ያደረጓቸውና ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል የመጡ ነበሩ፡፡ ሁለቱም የቅርብ ጓደኝነት ያላቸውና
ከአንድም በላይ ድርብ ሚኒስትርነት የተሰጣቸው ሰዎች በተራማጅነታቸው በንጉሳውያን ቤተሰብና በመሳፍንቱ ሊወደዱ አልቻሉም፡፡ ጸሐፌ
ትዕዛዙ የንጉሡን ሥልጣን ሳይቀር እያሰጉ
ሲመጡ ሲሻሩ፤ ሦስቱ የሀብተወልድ ወንድማማቾች በስልጣን ኮርቻ ላይ ቆይተዋል ማለት ይቻላል፡፡ የመኮንንና የወልደጊዮርጊስ መቃቃርም
ተዳሷል፡፡ መኮንን ሀብተወልድ የሀገር ፍቅር ማህበርን የመሰረቱ ትጉህ ሰው ሲሆኑ ዓረብ ቤት የሚባለውን ዓረቦች በሃገሪቱ የተንሰራፉበትን
የሱቅ ዘርፍ ለጉራጌ ተወላጆች ያስተላለፉ አገር ወዳድም ናቸው፡፡ ከምንም በላይ መኮንንን የሚያሳስባቸውና ለሃገር ፍቅር ቲአትር
ታዳሚያን ይናገሩት የነበረው የሃገራችን አንድነት እንዳይናጋ ነበር፡፡
ጸሐፌ ትዕዛዝ ወልደጊዮርጊስና የአቶ መኮንን ሀብተወልድ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስትን የማዘመን ስራቸውን ለማጠናከር እንዲረዳቸው በማሰብ
ከባላባቶች አንጻር በጀመሩት ስራ ምስለኔዎችንና ጭቃሹሞችን ሰብስበው ሲናገሩ የገለጹት ነጥብ ለአሁንም ስሜት ስለሚሰጥ አነሆ፡-
‹‹ኢትዮጵያ በአሥራ ሁለት ጠቅላይ ግዛቶች አንድትከፈል የተደረገው፤ ዘመናዊውን አስተዳደር ለመከተል የሚያመች እንዲሆን በማሰብ
ስለሆነ፤ በዚህ አሠራር ሕዝቡ በጎሳና በዘር ልዩነት ተጠንቶ የተደረገ መስሎ እንዳይታየው በሚገባ ማስረዳት›› (611) እንዳለባቸው
አሳስበዋቸዋል፡፡ አገራችን በጎሳ እንዳትከፋፈል፣ የግዛት አንድነቷ እንዳይነካና ዘመናዊነት እንዲገባ የሚጥሩት መኮንን ሀብተወልድ
ከክቡር ቢትወደድ መኮንን እንዳልካቸው ጋር እንዳይሳሳቱብን ያስፈልጋል፡፡ ምክንየቱም እርሳቸውም በነሱ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ስለነበሩ
ነው፡፡
በጣሊያን አገር ሰላሳ ዓመት የኖሩት ዘውዴ ረታ በንጉሠ ነገሥቱ መንግስት ወቅት የቤተመንግሥት ጋዜጠኛ ስለነበሩ፤
ያዩት የነበረውን የከፍተኛ ባለስልጣኖችንና የሃገሪቱን ፖለቲካ ሁኔታ የመመርመር ፍላጎት ስላደረባቸው በአውሮፓና በአሜሪካ እየተዘዋወሩ
በልዩ ልዩ ቋንቋዎች የተጻፉትን ብርቅዬ ሰነዶች አንብበዋል፤ መርምረዋል፡፡ ከዚህም በላይ የታሪኩን ዋነኛ ተሳታፊዎች ወዳጆቻቸውን
ቃለ መጠይቅ በማድረግ ብዙ መረጃ ሰብስበዋል፡፡ ይህን መጽሐፍም ልዩና ጠለቅ ያለ ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው፡፡
የዚህን መጽሐፍ ቀጣይ ክፍል፣ ማለትም ከ1948 እስከ 1967 የነበረውን የንጉሠ ነገሥቱን ታሪክ ደራሲው እያጻፉ
ባለበት ሁኔታ ሕይወታቸው በማለፉ እስካሁን ባለን መረጃ ስለመጽሐፉ መውጣት ምንም የተሰማ ነገር ስለሌለ በልባዊ ሐዘን ለአምባሰደር
ዘውዴ ምስጋናችንን ልናቀርብ ይገባናል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ