ማክሰኞ 5 ኖቬምበር 2019

ቻይናን በኢትዮጵያዊው እይታ



26. 2. 2012

ዶክተር ሃይለሚካኤል ለማ ይባላል፡፡ ዛሬ ጠዋት በስራ ቦታው በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ መዝናኛ ክበብ አግኝቼ በቅርቡ በሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና ስላደረገው አጭር ቆይታ አነጋግሬዋለሁ፡፡ ከጉብኝቱ እድንማርና እንድንወያይበት በመጋበዝ ቀጥታ ወደ ቃለመጠይቁ እንግባ፡፡  

1.    የሄዳችሁበት ዓላማ ምን ነበር?
ዝግጅት አላደረግንም፡፡ በአስቸኳይ ነው የተነሳነው፡፡ አካሄዳችን በዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ላይ ስልጠና ለመውሰድ ነው፡፡ ለሃያ ቀን ቆይተናል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሴት የዩኒቨርሲቲ አመራሮች አሉ፡፡ ምክትሎች ማለት ነው፡፡ የሴት ዋና ፕሬዚዳንት ስለሌለ፡፡ ወንድ አምስት ነን፡፡ ከአማራ ክልል ብቻ ነው ወንዶች የሄድነው፡፡
መጀመሪያ ግዋንዡ ከተማ ነበር የወረድነው፡፡ ከዚያ በሃገር ውስጥ በረራ ዢንዋ ወደሚባል ከተማ ሄድን፡፡ የህዝቡን የእንግዳ አቀባበልና ክብር አየን፡፡ ሰውን በቀና የሚያዩና የሚያከብሩ ናቸው፡፡ የሃገሩ ሁኔታ የተደመምኩበት ነገር ሙሉ በሙሉ ለምለምና አረንጓዴ ነው፡፡ ወጣ ገባ የሆነ አቀማመጥ ቢኖረውም  እንኳን ተራራውን እየበሱ መንገዶችን መሬት ለመሬት ሜዳ አድርገዋል፡፡ ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ያየሁት ቻይና ነው - በመንገድና በአረንጓዴ በማልበስ፡፡
2.    የሌላ አገር ዜጎች አገኛችሁ? ከኛ ያላቸውስ ልዩነት ምን ይመስላል፡፡

ከአፍሪካና ከላቲን የሄዱ ነበሩ፡፡ የኛ በአብዛኛው ዝምተኛና ጨዋ ማህበረሰብ ሲሆን እነዚያ በአንጻሩ ተጫዋች ናቸው፡፡ የወሬያቸውን ፍሬ ሐሳብ ለመያዝ እንኳን ከባድ ነው፡፡ ከአፍሪካ የጋና፣ የናይጀሪያ፣ የሴራሊዮን የመሳሰሉት አሉ፡፡ የቻይና መንግስት የንግድ ሚኒስቴር ነው ወጪውን የሸፈነው፡፡ የሰለጠንነው ስለ አመራር ሳይሆን ቻይና ከአሜሪካ ስላላት ልዩነት ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ስላላቸው ልዩነት አስገንዘበውናል፡፡  
3.    ያስገረመህ ነገርስ?
ያስደመኝ ነገር ቢኖር የከተሞቻቸው ንጽሕና ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የጽዳት ሰራተኛ ነው፡፡ የተጠቀምከውን መጣያ ቅርጫት በየቦታው አለ፡፡ መንገዳቸው በሁለት በኩል ሆኖ ከግራም ከቀኝም ከአራት እስከ ስድስት መኪና የሚያስኬድ አለው፡፡ ሌላ ያስደሰተኝ ድልድዮቻቸውና ህንጻዎቻቸው በጣም ዘመናዊ መሆናቸው ነው፡፡ ሙዚየምም አስጎብኝተውናል፡፡ 3 ቴክኖሎጂ አሳይተውናል፡፡ አብዛኛው ስራቸው በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑም ይመስላል በመንገዶቻቸው ላይ እንደ ህዝብ ብዛታቸው ሰው አይታይም፡፡
4.    ያሳዘነህስ?
የኛና የነሱ ልዩነት ነው ያሳዘነኝ፡፡ መቶ ዓመትም የሚበቃን አይመስለኝም በዚህ ባህላችን፡፡ የመጀመሪያው እንለወጥ ብለን ካሰብን የሚያስፈልገን የአመለካከት ለውጥ ነው፡፡ እነሱ ለሃገራቸው ያላቸው ክብር፣ ቁርጠኝነት፣ ፍቅርና የሥራ ታታሪነት ልነግርህ አልችልም፡፡ እያንዳንዱ የገጽታ ግንባታ ነው፡፡ የመሪያቸውን ንግግር ያለበትን ትልቅ መጽሐፍ ሰጡን፡፡ የስልጠናው ርዕስ ሊባል የሚችለው የገጽታ ግንባታ ነው፡፡ አንዳንዶቹ መሪያቸውን እንደ መልዓክ ያዩታል፡፡ እያንዳንዱን ስራቸውን በተለይ ከአሜሪካና አልፎ አልፎም ከእንግሊዝ ጋር ነው የሚያነጻጽሩት፡፡ በጉብኝቴ ወቅት ለማኝና ሊስትሮ አላየሁም፡፡ ትራፊክ ፖሊስም ያየሁት አንድ ቦታ ብቻ ነው፡፡ አቧራ የሚባል ስለሌለ ይመስለኛል ሊስትሮ የሌለው፡፡ በአንድ ሆቴል ጫማ የሚያጸዳ ማሽን አይቻለሁ፡፡
5.    ከእነሱ ምን እንማር?
የአመለካከት ለውጥ ማምጣትን እንማር እላለሁ፡፡ እርስ በርስ መባላት ሳይሆን ወደ ስራ ማተኮር ግድ ይለናል፡፡ ጠዋት ማታ ሞባይል ስንከፍት ፖለቲካ  ሆነ የምናየው፡፡ ሰው እየታረደ ሌላ ገንቢ ነገር ማየትም መስማትም አልተቻለም፡፡
6.    አሰለጣጠናቸውስ?
የሚገርመው ተማሪ ተኮር ምናምን የሚባል የለም፡፡ መምህር ተኮር ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ሻይ ረፍትም የላቸውም አሉ፡፡ በኛ ጫና ነው የተፈቀደው፡፡ እነሱ የፈለጉትን ብቻ ነው የሚያስተምሩት፡፡ ያሰለቻል፡፡ ትልልቆቹ ፕሮፌሰሮች በአስተርጓሚ ነው የሚያቀርቡት፡፡ ስልጠናው እምበዛም አልተመቸኝም፡፡ ከስልጠናው ይልቅ የተመቸኝ የመስክ ጉብኝቱ ነው፡፡
7.    እኛ ኢትዮጵያውያን ውጪ ሄደን የመኮረጅ አቅማችን ምን ይመስላል?
ብዙም ስላልቆየን ልንኮርጅ አንችልም፡፡ በእርግጥ ለጠቢብ ሰው አንዲት ቃል ትበቃዋለች ይባላል፡፡ ወደዚያ ለመግባት የምናስብ አገር አይደለንም፤ ‹‹ይህ የኔ፣ ያ ያንተ›› እየተባባልን፡፡ ዝንተ ዓለም ብጥብጥ ውስጥ ነን፡፡ ሃምሳ ዓመት ሞላን፡፡ እንደየግለሰቡና እንደየቆይታውም ይለያያል መኮረጅ መቻሉ፡፡  ቻይኖች ብዙም ምስጢር የሚያሳዩ አልመሰለኝም፡፡ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ሆነን ቤተሙከራና ትምህርት አሰጣጣቸውን አላስጎበኙንም፡፡ የተግባር ክንውናቸውን አላሳዩንም፡፡ ፍላጎታቸው እንድናደንቅ ይመስላል፡፡ አሜሪካንን አጣጥፈው ለመሄድ አምስት ዓመት የሚፈጅባቸው አይመስለኝም፡፡ ቴክኖሎጂ በእጃቸው ነው፡፡ የሕዝብ ቁጥር፣ የወታደር ቁጥር ወዘተ፡፡
የእንግሊዝኛ ጋዜጣ የለም፤ ማህበራዊ ሚዲያ ዝግ ነው፡፡ ጋዜጣው በቻይንኛ ነው፡፡ የምናድርበት ውስጥ ያለው የቻይንኛ መጽሐፍ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስሙ የተጻፈው በቻይንኛ ነው፡፡ እያንዳንዷ ወንዝ በጥንቃቄ ተሰርታ መናፈሻ ነች፡፡ አንዲት ውሃ ጠብ አትልም፡፡ ወንዞችና ሃይቆች በአብዛኛው ሰው ሰራሽ ናቸው፡፡ የከተማውን ውሃ ያጣሩታል፡፡
8.    የአሁኑን ጉዞህን ከኬንያ ጉዞህ ጋር እስኪ አነጻጽርልኝ እስኪ፡፡
ኬኒያ ምንም አላየሁም፡፡ ቻይና ቆይታዬ ሆን ብለው ስለወሰዱን ብዙና አጥጋቢ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ምናምን መኮረጅ እንጂ ማስኮረጅ አይፈልጉም፡፡
አሰልጣኛችን ‹‹አሜሪካ በአንድ ዓመት 47 ቢሊየን ዶላር በስኮላርሽፕ አግኝታለች፡፡ ከእዚህ ውስጥ ብዙው የቻይና ነው፡፡ ስለዚህ ራሳችን ማስተማር አለብን፡፡›› አለ፡፡ እኔም ‹‹ከአሜሪካ ምን ተማራችሁ›› ስለው፡፡ ‹‹እነሱ መች ይታወቃሉ!›› አለ፡፡ ‹‹አሜሪካ ለተማረ ዜጋችን ቅድሚያ ከምንሰጥ ለራሳችን ነው መሆን አለበት፡፡›› ብሎኛል፡፡
ማታ ማታ ከህጻን እስከ ሽማግሌ ውጭ ላይ በቻይና መሳሪያ የተቀነባበረ ሙዚቃ እየተዝናኑ ስፖርት ይሰራሉ፡፡ በእግር ሽርሽር ያደርጋሉ - በተለይ ሴቶቹ፡፡
ባህላቸውን እንደሚወዱ ያየሁት በቋንቋቸው በመጠቀማቸውና በሞራላቸው ቢሆንም ሃይማኖት ግን የላቸውም፡፡ በአንጻሩ ክርስትና እየገባ ነው፡፡ በራሪ ወረቀት የሚሰጡ አይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ቻይኖቹ ምዕራባውያን እንዳይገቡ ሁሉንም ነገር ዘጋግተዋል፡፡  

9.    ምግብና መጠጣቸው እንዴት ነው?
በየቦታው ሙቅ ውሃ ስላለ እየቀዱ መጠጣት ነው፡፡ ጁስ፣ ቀዝቃዛ ውሃ፣ ቡና፣ ሻይ፣ ወተት እንደልብ ነው፡፡
ምግቡም ብዙ ዓይነት አለ፡፡ ቁርስ ላይ በጣም ብዙ አማራጭ አለ፡፡ ብዙ የዩኒቨርሲቲም ሰራተኛ ይበላል፡፡ ምሳና ራት ላይ ለኛ ብቻ ስለሚቀርብ ዓይነቱ ይቀንሳል፡፡
10. ከኢትዮጵያ አንጻርስ?
አንድ ቀን እንኳን ስለ ኢትዮጵያ አያወሩም፡፡ ስለመኖራችንም አያውቁም፡፡ የእንግሊዝኛ ጣቢያቸው ሲጂቲቪ ስለ ኢትዮጵያ አንድ ቀን ብቻ ነው ያቀረበው፡፡ አሜሪካ ሸቀጣሸቀጥ እንዳይገባ ያደረገችውን ነገር ላይ በብዛት ያወራል፡፡
11. አመሰግናለሁ
እኔም ይህን ዕድል ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ፡፡

ቅዳሜ 2 ኖቬምበር 2019

አንድ ሰሞን በአክራ፣ ጋና



(An Account of My trip to Accra, Ghana, in Amharic)
የጉዞ ማስታወሻ
በመዘምር ግርማ
ጥቅምት 21 2012

‹‹ወደ ምስራቅም ወደ ምዕራብም አናንጋጥጥም፤ ወደ ፊታችን እናያለን እንጂ›› ዶክተር ክዋሜ ንክሩማ




ለጉዞ ዝግጅት የጀመርኩት ክረምት ላይ ነበር፡፡
ፓስፖርቴ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ስለነበር እሱን ለማሳደስ ከአርብ እስከ ሰኞ አዲስ አበባ ጠብቄ፣ አርብንም ሰኞንም ተሰልፌ ነበር ከሳምንት በኋላ መውሰድ እንደምችል የተረዳሁት፡፡አስቸኳይለተባለው ለዚህ ተግባር 2186 ብር መክፈል ግድ ነበር፡፡ በዋናው ፖስታቤት አዲሱን ፓስፖርት ከሳምንት በኋላ ስወስድ የተከፈለችም 45 ብር አለች፡፡
ከአዲስ አበባው የጋና ኢምባሲ ቪዛ ለማግኘት ድረገጽ ላይ ስልክ ቁጥራቸውን ፈልጌ ደወልኩ፡፡ የሚያስፈልገው ነገር ብዙ ነበር፡፡ የሚከተሉትን ነገሮች እያንዳንዳቸውን ሦስት ያቅርቡ ተባለ፡፡ ፎቶ፣ መታወቂያ፣ ማመልከቻ፣ የፓስፖርት ኮፒ፣ የግብዣ ደብዳቤ፣ ሆቴል የያዙበት፣ የአየር ቲኬት እና የመስሪያ ቤት የትብብር ደብዳቤ፡፡ በሦስት ቀን ውስጥ ቪዛ መተው ሰጡኝ፡፡
ወደ ጋና የምሄደው ረቡዕ 13.2.2012 ሌሊት 930 ቢሆንም ማክሰኞ ጠዋት ከደብረ ብርሃን ተነስቼ ወደ አዲስ አበባ መንገድ ጀመርኩ፡፡ ለዚህም ምክንያቴ የነበረው ወቅታዊው የመንገድ መዘጋጋት ስጋት ነበር፡፡ ቢዘጋጋ እንኳን ቀደም ብዬ ልሂድ ብዬ ነው፡፡ አዲስ አበባ እንደደረስኩ ወደ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ባምቢስ ሄጄ ለደብረ ብርሃን ቅርንጫፋቸው ባቀረብኩት ማመልከቻ መሰረት 500 ዶላር ወሰድኩ፡፡ ለዚህም ትብብራቸው አመሰግናለሁ፡፡
በዚህ ጉዞ የያዝኩት አንድ በጀርባ የምትታዘል ሻንጣ ስትሆን የያዝኩባትም በብዛት ልብስ ነበር፡፡ ምክንያቱን ልብስ ካልያዙ በውጭ ሃገር መቆየት እንዴት እንደሚከብድ ከአሁን በፊት ስለተማርኩ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ወደ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት በመሄድ ዋና ኃላፊውን ለማግኘት ቻልኩ፡፡ እየሰራን ስላለነው ስራ መልካም ውይይት አድርገን አመስግኜ ተለያየን፡፡ በዕለቱ በተረፈኝ ጊዜ ደራሲ ጥላሁን ጣሰውን አግኝቼ እንደተለመደው ተጋብዤ ተለያየን፡፡ ደራሲ አጥናፍሰገድ ይልማ ስደውል መኪና እየነዱ ነው ብለው ሌላ ሰው አነጋገሩኝ፡፡ ሌላ ቀን አገኛቸዋለሁ ብዬ ማስታወሻ ያዝኩ፡፡
የማክሰኞ ምሽት አንዳንድ ወጣ ያሉ ነገሮች ነበሩበት፡፡ በመጀመሪያ እስካሁን የበጎ አድራጊ ድርጅት ገንዘብ እንድጠቀም በሚፈቀድልኝ ጊዜ በአነስተኛ ዋጋ አልጋ እየያዝኩ በሙዚቃ ስረበሽና ቻርጀርና መታጠቢያ እንኳን በሌላው ሁኔታ ስቸገር ስለማድር በአሁኑ ጉዞ ይህን ለማስተካከል ወስኛለሁ፡፡ ራት የበላሁት በአይቤክስ ሬስቶራንት ነው፡፡ ማምሸ ላይ ከዚያው ላዳ ለመያዝ አስቤ ሃሳቤን ቀየርኩ፡፡ ጊዜው ከአንድ ሠዓት አልፎ ስለነበርና ድርጅቱም ይከፍልልኝ ስለነበር ትልቅ ስህተት መስራቴ አሁን ነው የገባኝ፡፡ በሃይገር መገናኛ ሄድኩ፡፡ ከመገናኛ ወደ ላምበረት ለመሄድ በደረጃዎቹ ለመውጣት ስሄድ የሰው መጨናነቅ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ የቅሚያ ሙከራ ያደረገብኝ አንድ ሰው ነበር፡፡ ከዚህ የተረዳሁት ሌሎችም ጓደኞች እንደሚኖሩት ስለነበር የፖሊስን እገዛ መጠየቅ ነበረብኝ፡፡ በተዓምር ይህን ችግር አለፍኩት፡፡ ማንራሲዋ ሆቴል ደርሼ 600 ብር ቁርስ የሌለው አልጋ ያዝኩ፡፡ ጥሩ መኝታ ቤት አላቸው፡፡
በዚህ ቀንና ማታ ላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ እንደ ቦሌ አራብሳ ያሉ አካባዎች ላይ በአማርኛ የተጻፉ ማስታወቂያዎችን ማንሳት መጀመሩንና ሰዎችም ላይ ጥቃት እየተፈጸመ እንደሆነ በፌስቡክ አይቼ ነበር፡፡ እኩለ ሌሊት አካባቢ ይመስለኛል በማህበራዊ የትስስር ገጾች የጃዋር መሐመድንየተከበብኩጥሪ አየሁ፡፡ ጠባቂዬ ከኮማንደር ጋር ሲነጋገር ቀረጽኩ ያለውንም አዳመጥኩ፡፡ የሱን መጨረሻ ለማየት ጓጉቼ ስከታተል አደርኩ፡፡ ሌሊቱን ብዙም አልተኛሁም ነበር፡፡ ባለኝ ግንዛቤና ንባብ ሌሊት ላይ ህዝቡ በተኛበት ብዙ አስጊ ነገሮች ስለሚጠነሰሱ የሁኔታውን አካሄድ ማጥናት ነበረብኝ፡፡   
በዕለተ ረቡዕ መጠያየቅ የነበረብኝን ሰዎች ስጠያይቅ ቆየሁ፡፡ በዚህ ዕለት ወደ አዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች ሁሉ ዝግ ነበሩ፡፡ የዘጉትም በጃዋር መሐመድ ላይ ተደረገ የተባለውን የጠባቂዎች ማንሳት ሂደት ተቃወሙ የተባሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ በከተማውና በአካባቢ አስጊ ሁኔታ ነበር፡፡ ሌሊትና ጠዋት አካባቢ ድረስ እውነትም ጠባቂዎቹ ሊነሱበት ተደርጎ ይሆናል የሚል ግምት ነበረ፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን ነገሩ ሌላ መልክ እንዳለው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ረቡዕ አመሻሽ ላይ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ ሄድኩ፡፡ በዋዜማው ምሽት ላይ የደረሰብኝ የቅሚያ ሙከራ በዚያ ቀን እንድጠነቀቅ አድርጎኛል፡፡ የረብሻ ስጋትም አለ፡፡ ይሁን እንጂ 1200 እስከ ሌሊት 930 መጠበቅ እንዴት አሰልቺ እንደሆነ ልትገነዘቡልት ትችላላችሁ፡፡
ረጅሙን ታሪክ ለማሳጠር ሌሊት 930 በኬኒያ ኤርዌይስ አውሮፕላን ተሳፍሬ ወደ ናይሮቢ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ከአዲስ አበባ ናይሮቢ ሁለት ሰዓት የሚፈጅ አልመሰለኝም ነበር፡፡ ግን ፈጀ፡፡ ኬኒያም ትራንዚት ሳደርግ የኬኒያ ሻይ በወተት ጠጣሁ፡፡ ውኃም ያዝኩ፡፡ የአውሮፕላን ውስጥ መስተንግዶውና ድግሱ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ አልነበረም፡፡
በኬኒያ የሄድኩት የምሄድበት ስብሰባ አስተባባሪዎች በቆረጡልኝ ትኬት መሰረት ነው፡፡ ባይሆን ኖሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጥታ አክራ ድረስ በረራ ስላለው በሱ መጓዝ እችል ነበር፡፡ ከሁለት ሰዓታት ረፍት በኋላ ወደ አክራ በሌላ የኬኒያ አውሮፕላን ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ማክሰኞ ሌሊት በደንብ አለመተኛቴ፣ ረቡዕ ሌሊትም አየር ማረፊያ ግቢ ሳልተኛ ማደሬ የራሱ የሆነ ጫና አለው፡፡ አሁን የምሄድበት አክራ ደግሞ ከኛ ሦስት ሰዓት ስለሚቀድም ቀን እየሆነ ነው የሚሄደው፡፡ ጀት ላግ የሚባለው ነገር ገጥሞኛል፡፡ ከናይሮቢ አክራ ለመድረስ አምስት ሰዓት ተኩል ወስዶብናል፡፡ አክራ ኮቶካ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ መሰራቱ ነው፡፡ በዩቱብ አይቼው ስለነበር አዲስ አልሆነብኝም፡፡ የተለመደችው የኢሚግሬሽን ባለስልጣኖች የጉቦ ጥያቄ ነበረች፡፡ በልምምጥና በዘዴ አልፌያታለሁ፡፡ በአየር ማረፊያው የሆቴሉ ታክሲ ይጠብቀኝ ስለነበር አግኝቸው ይዞኝ ወደ ሆቴሉ ሄደ፡፡ ከተማዋን እየቃኘሁ ኢራታ ሆቴል ገባሁና ቦታዬን ያዝኩ፡፡ የሆቴሉ ብዙዎቹ ነገሮች የአዲስ አበባውን ማንራሲዋ ሆቴል ስለሚመስልና ካሁን በፊትም ካየኋቸው ሆቴሎች ጋር ስለሚቀራረብ አላስቸገረኝም፡፡ ለነገሩ አስተናጋጇ በደንብ አሳይታኛለች፡፡
በዚሁ ዕለት የፕሮጀክታችን አስተባባሪ ጋናዊው ስታንሊ ሆቴል መጥቶ አግኝቶኛል፡፡ የማላዊ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት ኃላፊ የሆነው ግሬይ ኒያሊንም በእራት ሰዓት አግኝቸዋለሁ፡፡ የሆቴሉ ምቾት ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በማግስቱ ጠዋት ምን እንደምንሰራ በማሰብ ላይ ሳለሁ ለአስተባባሪዎች ስብሰባ የመጣውን ስታንሊን አግኝቼ ጠየቅሁት፡፡ የሆቴሉን ሰዎች አነጋግሮ እነሱ የሚያውቁት የታክሲ ሾፌር አስመጣልን፡፡ እኔና ግሬይ በጋራ 45 ዶላር እንደምንከፍል ተነጋግረን ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ የዕለቱ ሽርሽር በመንገድ መዘጋጋት ትንሽ የዘገየ ቢሆንም ደህና ጀምሯል፡፡ በመንገዳችን ላይ ቤተመንግሥታቸውን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱንና የጋና መስራች የሚባሉትን የአሻንቲ ህዝቦች ሰፈርን አየን፡፡ መንገድ መንገዱን ፎቶ ሳነሳና የህዝቡን አኗኗር እያየሁ ከሹፌሩና ከግሬይ ጋር ሳወጋ ነበር፡፡   

የውቅያኖስ ዳርቻ
የባሪያ ንግድ 1673 ነበር አሉ የጀመረው፡፡ ከዚህ ጋር የሚያያዝ ቦታ ልናይ ነው፡፡ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ ዳርቻ አቀናን፡፡ በስፍራው አንድ ወጣት አግኝተን የማስገብኘት ስራውን ጀመረልን፡፡ ይህ የውቅያኖስ ዳርቻ ጀምስ ታውን ይባላል፡፡ እዚያ አንዲት ቀይ የተቀባች በግምት አስር ሜትር የምትረዝም ማማ አለች፡፡ የብርሃን ቤት ትባላለች፡፡ እሷን ከውጭ ጎበኘን፡፡ እንዳንገባ እድሳት ላይ ስለሆነች ነው፡፡ 1871 የተሰራች ስለሆነች እድሳቱ ግድ የሚላት ይመስላል፡፡ 1930 ባትታደስማ ወድቃ ነበር፡፡ መርከቦች ከሩቅ ሲመጡ ብርሃን እንዲያዩባት የምትደረግ ክፍል ነች፡፡ ከእርሷ ጎን የጋና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ለአንድ ዓመት የታሰሩበት ታሪካዊ ቤት አለ፡፡ በዚህ አክራ እድሜጠገብ ክፍል ዓሳ ማጥመድ ዋነኛ የስራ ዘርፍ ነው፡፡ ልጆች በዘጠኝ ዓመታቸው ሳይቀር ዓሳ ያጠምዳሉ ተብለናል፡፡ በመንግስት የመልሶ ማልማት ስራ ምክንያት በአካባቢው ያለው መንደር ፈርሷል፡፡ ፈርሶ ለአንድ ዓመት ያህል ምንም ስላልተሰራበትም ህዝቡ መልሶ ሸራም ምንም እየጣለ ሰፍሯል፡፡ በወደቡ ድህነት እንዳለ አስጎብኛችን ነገረን፡፡ ዘጠኝ ቤትር የሚረዝሙ አከንድ ወጥ እንጨት በባህላዊ መንገድ የተሰሩ ጀልባዎችን አየን፡፡ ግማሹ ዓሳ ይፍቃል፣ ይበልታል፤ ግማሹ ቀንድ አውጣ ያጥባል፡፡ የውቅያኖሱን ዳርቻ አየን፡፡ መርከብና ጀልባወችንም በውቅያኖሱ ለማየት ችለናል፡፡ ለበርካታ ቀናት ዓሳ ለማስገር ሲወጡ በዚያው ሞተው የሚቀሩም እንዳሉ ተረዳን፡፡ ለአስጎብኛችን 20 የጋና ሴዲ (አራት የአሜሪካን ዶላር) ሰጥተን ተሰናበትን፡፡

የንክሩማህ ሙዞሊየም
ቀጣይ መዳረሻችን የዶክተር ክዋሜ ንክሩማህ ሙዞሊየም ነው፡፡ የመጀመሪያው የነጻይቱ ጋና ፕሬዚዳንት የነበሩትን የክዋሜ ንክሩማህን ሙዞሊየም ስንጎበኝ በህይወት ዘመናቸው የተጠቀሙባቸውን ቁሳቁስ፣ የጻፏቸውን መጻሕፍት፣ ከተለያዩ የዓለም መሪዎች ጋር ተነሷቸውን ፎቶዎችና የመሳሰሉትን አይተናል፡፡ በልጅነቱ ሴት አያቱ የሰጡት ከሴሴ እንጨት የተሰራ ወንበር (ግርምቡድ) አይተናል፡፡ ቤተመንግስት ላይ ይጠቀሙበት የነበረው ጠረጴዛ ከነ ወንበሩም አለ፡፡ ትልቅ ፒያኖም እንዲሁ፡፡
የደረቀ አስከሬናቸው ያለበትን መቃብር ቤት ከሙዞሊየሙ ፊት ለፊት አለ፡፡ እሱንም አይተናል፡፡ ጋናውያን ተማሪዎች በትምህርት ቤት ከመምህራን ጋር ሆነው ስፍራውን እየጎበኙ ገለጻ ሲደረግላቸውም አይተናል፡፡ ቀጣዩን ትውልድ ማነጽ ማለት ይህ ነው፡፡ ህጻናቱም እንግሊዝኛ ይችላሉ፡፡ ከቋንቋቸው በተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡ ከነዚህ ስፍራዎች ፊት ለፊት ያለው የውሃ ገንዳ የሙዚቃ መሳሪያ በሚጫወቱ በርካታ ሀውልቶች አጊጧል፡፡ ከዚያ ፊት ለፊት ያለው ለምለም ሻር ጌፀ ሜዳ አእምሮን ያሸፍታል፡፡  
የንክሩማህን ህይወት ታሪክ ፈልጋችሁ እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ፡፡ አዲስ አበባ ሲመጣ በነጠላ ጫማና በሽርጥ መምጣቱን ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ ማንነቱን አስበልጦ ነው፡፡ ንክሩማይዝም የሚባል እንቅስቃሴ እንዳለ አንብቤያለሁ፡፡ በርካታ መጻሕፍትን እንደደረሰም አይቻለሁ፡፡ ‹‹ወደ ምስራቅም ወደ ምዕራብም አናንጋጥጥም፤ ወደ ፊታችን እንጂ›› የሚለው ዶክተር ክዋሜ ንክሩማ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር የስልጣን ሽኩቻ እንደነበራቸው አንብቤያለሁ፡፡ በመፈንቅለ መንግስት የተገረሰሰው የንክሩማህ መንግስት ሲወድቅ ንክሩማህ የጊኒ አጋር ፕሬዚዳንት ለመሆን ቻለ፡፡ በመጨረሻም በህመም ምክንያት ህይወቱ ስታልፍ በጊኒ 1972 ተቀበረ፡፡
ከዚህ ቦታ ወጥተን የባህል ዕቃዎች ወደሚሸጡበት ስፍራ ሄደን የተለያዩ ልብሶችንና የስጦታ ዕቃዎችን ሸመትን፡፡ ለማሳረጊያም ወደ አንድ የውቅያኖስ ዳርቻ መናፈሻ ዘልቀን ውቅያኖሱን በቅርበት አየን፡፡ ለማስዋሻም ፎቶ ተነሳን፡፡
ወደ ሆቴላችን ተመልሰን ከየሃገሩ የሚመጡትን ተሰብሳቢዎች ስንተዋወቅ አመሸን፡፡
በማግስቱ ቅዳሜም ስብሰባችን ጀመረ፡፡ ስብሰባችን ምን እንደሚመስል ከመግለጼ በፊት ስለ ፕሮጀክቱ አንዳንድ ነገር እንነጋገር፡፡ የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ማህበር ከዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚያካሂዱት ይህ ፕሮጀክት በቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ስፖንሰር የተደረገ ነው፡፡ የአብያተ መጻሕፍትን እይታ መጨመር (Advancing Library Visibility in Africa) ይባላል፡፡ አብያተ መጻሕፍትን በያሉበት እየተገኙ የሚመዘገብበት ሂደት ነው፡፡ በመጀመሪያ ያሉበትን ቦታ፣ የቤተመጻሕፍት ሰራተኛውን አድራሻ መሳሰሉትን ከመዘገብን በኋላ በቀጣይ ዙር ደግሞ የሚሰጡትን አገልግሎት እንደያይነቱ እንመዘግባለን፡፡ የዚህ ሁሉ የድረገጽ ምዝገባ ዓላማ የልማት አጋሮች የሆኑ ድርጅቶች አብያተመጻሕፍትን እንዲያግዙ መንገድ መጥረግና ክፍተቱን ማሳየት ነው፡፡ ሌሎችም ጥቅሞች አሉት፡፡ ዝርዝሩን librarysites.io ብላችሁ በመግባት ታገኙታላችሁ፡፡ በአቅራቢያችሁ ያለውን የህዝብ ቤተመጻሕፍት እንድትመዘግቡ ተጋብዛችኋል፡፡
ስብሰባችን ስራችንን የምንገመግምበትና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የምናስቀምጥበት ነው፡፡ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ፖርቹጋልኛ የምንናገር አፍሪካውያን እንደየቋንቋው በቡድን ሆነን በአንድ አዳራሽ ስንሰበሰብ የማስተርጎሙን ስራ እንዲሰሩ የመጡት ስድስት ባለሙያዎች በአንድ ጥግ በተዘጋጀላቸው ቦታ ሆነው ያስተረጉማሉ፡፡ ተሳታፊው የጆሮ ማዳመጫውን ሰክቶና የሚመቸውን ቋንቋ መርጦ ይሰማል፡፡ ቅዳሜና እሁድ ሪፖርቶቻችንን ስናቀርብ፣ የቡድን ስራ እየሰራን ስንወያይና መድረክም ላይ ስናቀርብ፣ የአዘጋጆቹንም ገለጻዎች ስንከታተል ቆይተን ሰኞ ወደ ሁለት አብያተመጻሕፍት የጉብኝት መርሃግብር ነበረን፡፡ ወደ ጋና መምህራን ኮሌጅ ማህበረሰብ ቤተመጻሕፍትና ወደ ችርስ የግል የህጻናት ቤተመጻሕፍት፡፡ ብዙ የተማርንበት ጉብኝት ነበር፡፡ 
ማክሰኞ ብዙው ሰው ወደ ሃገሩ ሄዶ ወይም ወደ ሌላኛው የብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ሚኒስትሮች ስብሰባ ገብቶ ስለነበር እኔ በሆቴሉ ብቻዬን ማለት በሚቻል ሁኔታ ነበርኩ፡፡ በረራዬ ማታ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ ማታ እንደምሄድ የተረዱ የሆቴል አስተናጋጆች ዛሬ ምሳ አትበላም አሉኝ፡፡ ሞባይልክን ስጠኝ ያለኝም ነበር፡፡ ስቄ አለፍኩት፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ የሌሴቶዋ በጎ ፈቃደኛና ተሰብሳቢ ስትመጣ ምሳችንን በልተን መፈረሚያውን አምጡ ብላ ስታፋጥጣቸው አስፈረሙን፡፡ እኔንም 40 ሴዲስ ትከፍላለህ ብሎ ላቀረበልኝ ምሳ ሳያስከፍለኝ ቀረ፡፡ እግሬ ሆቴሉን ከረገጠባት እስከምወጣባት ጊዜ እንደሚከፈልልኝ እየታወቀ ይህ ውንብድና ከአስተናጋጁ አይጠበቅም ነበር፡፡
ወደ አየር ማረፊያው ስሄድ አብሮኝ የሄደው የኒውዮክ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር ነው፡፡ አድራሻውን ይዣለሁ፡፡ የአፍሪካ ጥናት ማህበርን ያስተባብራል፡፡
 አዲስ አበባ ተመልሼ የጋናውን የአስተርጓሚ ድርጅት ግማሽ ባለቤትና ጋና ያገኘሁት ሰው መንትያ ወንድም የሆነውን ኮፊ ኮራንተንን ደውዬ አገኘሁት፡፡ በራስ ሆቴልም አወጋን፡፡ በአፍሪካ ህብረት እንግሊሊኛና ፈረንሳይኛ በማስተርጎም አስር ዓመት ሰርቷል፡፡ ‹‹ንክሩማህ ይመስገን አገራችን ሰላም ነች፡፡ ሁሉም አሁን ያለን ነገር እሱ የጣለው መሰረት ውጤት ነው፡፡ አእምሮን ለማልማት እንሰራን ፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች የሰው ኃይሉን አገር ውስጥ ለማቆየት ነው አሉ እንግሊዝኛ በጥራት እንዳይማር የሚያደርጉት፡፡ ዓለምአቀፍ ድርጅት ለመግባት፣ እድገትን ለማምጣትና ውጭ ለመማር እንግሊዝኛንና የውጭ ፈተናዎችን አሰራር ለልጆቻችን ማስጠናት አለብን፡፡ ስዋህሊ፣ ትዊና አማርኛ ያለነሱ ያሉባቸውን አገሮች ማሰብ አይቻልም፡፡ ጋና፣ ምስራቅ አፍሪካና ኢትዮጵያ በእነዚህ ቋንቋዎች ስለሆነ ህልውናቸው የተረጋገጠው እንዲበለጽጉ መስራት አለብን፡፡›› የሚሉትንና ሌሎችንም ሃሳቦች ኮፊ አካፍሎኛል፡፡ ወደፊትም እንደምንገናኝ ቃል ገብቶልኛል፡፡
የበፊቱን ሚት ኢቲቪ የአሁኑን ሚት ኢቢሲን አዘጋጅ ተፈራ ገዳሙንም እንዲሁ ብሔራዊ በሚገኘው ቢሮው አግኝቼ ቀድሞ ስለነበረን ቀጠሮ ጉዳይ አነጋግሬዋለሁ፡፡

ምልከታ
የመንገድ ላይ ሻጮች በርካታ ናቸው፡፡ የሚያሳድዳቸውም የለም፡፡ እንዲያውም ይበረታታሉ፡፡ ራሳቸው ላይ የተሸከሙ መነገድ ብቻ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ጋና አጥር የለውም፡፡ ህብረተሰቡም በውስጡ በእግርም ሆነ በመኪና አቋርጦ ያልፋል፡፡ ስለ ጉዳዩ የጠየኩት አንድ ተማሪ ‹‹መልካሙን ስለምንጠብቅ አጥር አያስፈልገውም፡›› ብሎኛል፡፡ እኛ አገር በአንጻሩ ጠቀም ያለ በጀት ለአጥርና ለዋና በር ይያዛል፡፡ እርስዎ የትኛው የሚሻል ይመስልዎታል? ሰዎቹ ከቺንዋ አቸቤ ልብወለድ Dead Men’s Path የተማሩ ይመስላሉ፡፡
ሆቴል መኝታ ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ይቀመጣል፡፡ ስብሰባ በጸሎት የሚጀመርበት ጊዜም እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡
የኢትዮጵያውያን ሴቶችን ውበት የማያነሳ የለም፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሄዱና ቦሌ አየር ማረፊያን ደጋግመው የረገጡ በርካቶችን አግኝቻለሁ - ከጋናውያንም ሆነ ከሌሎቹ አፍሪካውያን!
ሰው ሁሉ ሲያየኝ ኢትዮጵያ ይለኛል፡፡ ይህ በመልክ የመለየት ነገር ግን ለክፉ ቀንም ያሰጋል የሚል ነገር ታይቶኛል፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን እንግሊዝኛ ያስቸግራቸዋል፡፡ አንተ ግን እንዴት ቻልክ?›› ያለችኝ በጎ ፈቃደኛ ነበረች፡፡ በትምህርት ጥራት ማነስ መታወቃችን አሳስቦኛል፡፡
ማላዊያዊው ግሬይ ኒያሊ ደግሞ ኢትዮጵያ ለስብሰባ አምስት ጊዜ እንደመጣ ነግሮኛል፡፡ 9/11 ጊዜ አሜሪካ ነበርኩ ብሏል፡፡ በእንግሊዙ ባኪንግሃም ፓላስም ልዑሉን የማግኘት ዕድል ነበረው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመንግስት ለውጥ ጊዜ እንዳይጎዳ ያሰቡ አርቆ አሳቢ አመራሮቹ በጊዜያዊነት ወደ ሌላ አገር አዛውረውት ነበርም ብሎኛል፡፡ 
ዱንስታኔት በምትባል በጎ ፈቃደኛ የተወከለችው ሴራሊዮን አየር መንገድ የላትም፡፡ ዱንስታኔት የልጆች ቤተመጻሕፍት ሰራተኛ ስትሆን ወደ አክራ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ እንደሄድን ለሞዴል ትምህርት ቤቱ ህጻናት መዝሙር አስጠንታቸዋለች፡፡ ሁለት ምርጥ ቃላት አሉ - አመሰግናለሁና እባክዎን የሚሉ፡፡ የሚል መዝሙር ነው፡፡ ዱንስታኔትን እንግሊዝኛ መምህርነት እናንተ አገር ልሞክር ወይ ስላት በአገሯ ስራ ፈላጊው ብዙ መሆኑን ነገረችኝ፡፡ 
‹‹ሌሴቶ የባህር በር የሌላት በደቡብ አፍሪካ የምትዋሰን ሃገር ነች፡፡›› ከዚያቸች ሃገር የመጣች የቤተመጻሕፍት ሰራተኛ አገሯን የገለጸችበት መንገድ፡፡
ሚኪያስ ካሳዬ ‹‹አትላንቲክ ድረስ ሄደህ ውቅያኖስ ላይ ሳትንቦጫረቅ መምጣት አልነበረብህም!›› ብሎኛል፡፡ ልክ ነው፡፡ ለጉዞው ካደረኩት ዝግጅትና በቦታው ምን ዓይነት መዝናኛ ቦታዎች እንዳሉ ካለማወቅ ነው እንጂ ባደርግ ጥሩ ነበር፡፡ 
ግሬይ በፊት የተመረቀው በግብርና ነበር፡፡ በኋላ የግብርና መረጃዎችን በመከታተል ስም ነው ወደ ቤተመጻሕፍት የገባውና በዚያው የቀረው፡፡
በመንገድ ዳር ምግብ የሸጣል፡፡ ዓሳ፣ ፍራፍሬ ወዘተ፡፡
‹‹ለምን መረጃ ትሸጣለህ›› የደቡብ አፍሪካዋ የቤተመጻሕፍት ሳይንስ መምህርት ለኔ ያለችኝ ነው፡፡ ቤተመጻሕፍታችን መጻሕፍትን እንደሚሸጥ ስነግራት ነው እንዲህ ያለችው፡፡
‹‹ኢምፔሪያሊዝም እንድንማርና ስራ እንድንጠላ ያደርገናል፡፡ ዲግሪ ይዘህ ያለ ስራ ትዞራለህ፡፡ ኢምፔሪያሊዝም የእድሜ ልክ ቅኝ ግዛት ነው፡፡›› የአብያተመጻሕፍት ሰራተኞች ሲያወሩ የሰማሁት ነው፡፡ ትክክለኛ ሃሳብ ይመስላል፡፡
አንቶኔታ የዝንባብዌ ቤተመጻሕፍት ተወካይ ናት፡፡ ከንዴቤሌ ጎሳ የመጣች ናት፡፡ በዘመነ ሙጋቤ ፍጅት የተካሄደባቸውን የንዴቤሌን ህዝቦች ብርቱ ተዋጊዎች ናቸው ትላለች፡፡ ፍጅቱን የፈጸመብን አሁን ስልጣን ላይ ያለው ሰውዬ ነው ብላኛለች፡፡ ስለ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም የምትለው አላት፡፡ ‹‹መንግሥቱ የመጡ ሰሞን አንድ ኢትዮጵያዊ ስዋዚላንድ አየር ማረፊያ አግኝቶኝ ‹እናንተ አምባገነን የደበቃችሁ› አለኝ፡፡ የምን አምባገነን እንደሆነ ስጠይቀው ‹ሳታውቂው ቀርተሽ ነው!› አለኝ፡፡ በንግግሬ እንደለየኝ ሲናገር ነበር፡፡ ይህ ሰው ጭራሽ እንደ ጠላት ነው ያየኝ›› ብላለች፡፡
የስዋዚላንድ በጎፈቃደኛዋ ደግሞ አገሯ ስሟን እንደቀየረች ነግራናለች፡፡ ይህን የቅኝ ግዛት ስም ወደ ኢስዋስቲኒ ቀይረዋል፡፡
የቆዳ ቀለሜ ከቀን ወደ ቀን እየጠቆረ ሲመጣ ‹‹ለካ እነ ስታንሊ ወደው አይደለም የጠቆሩት!›› አልኩ፡፡ እዚያ ያለውን ጋናዊ አስተባባሪያችንን ጥቁረት አይቼ ነው፡፡

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...