ማክሰኞ 14 ዲሴምበር 2021

ብርቱ ጉዳይ - አጭር ልቦለድ - በመዘምር ግርማ

 ብርቱ ጉዳይ

አጭር ልቦለድ

በመዘምር ግርማ

ታህሳስ 5፣ 2014 ዓ.ም.

 

ሰኞ ጠዋት እንደወትሮዬ ማልጄ ነበር ወደ ስራ ቦታ የገባሁት፡፡ መምህራን ላውንጅ አንድ ጥጋት ይዤ ሻይ ቡና እያልኩ እንደልማዴ እጻጽፋለሁ፡፡ የተገኘውን ማለዳው ያፈራውን ጽሑፍ ከመጻፍ ይልቅ በዚህ የጦርነት ወቅት እሁድ ህዳር 12፣ 2014 ዓ.ም. በደብረብርሃን ሰማይ ላይ አርብቦ በነበረው የስጋት፣ የድንጋጤና የሽሽት ሁኔታ ላይ አተኩሬያለሁ፡፡ በወቅቱ በነበረው የአገር ህልውና ስጋት ላይ መውደቅና በየግል ሕይወታችን መቀጠል አለመቀጠል ላይ እርግጠኝነት የማጣት ሁኔታ ላይ ከሰሞኑ ላወጣው እያዘጋጀሁት ያለሁትን ከአስር ገጽ በላይ የሚረዝመውን የእንግሊዝኛ ጽሑፌን በማሽሞንሞን ላይ ነኝ፡፡ ሽሙንሙን ያድርገኝ እቴ! እንግሊዝኛን እንዴት አሽሞነሙናታለሁ፤ አርመጠምጣታለሁ እንጂ!  ታዲያ መምህራንና ሰራተኞች ገና ወደ ላውንጁ ሲገቡ እንደልማዳቸው የሚያውቁትን ፊት ፍለጋ ትልቁን አዳራሽ ያማትራሉ፡፡ የሚያውቁኝ ከሆኑ ወደኔ ጠጋ ማለታቸው ግዴታ ነው፡፡ ማለዳው ያፈራውን ወሬ እናወጋለን፡፡ እናነሳለን እንጥላለን፡፡ በየመሃሉም ፋታ እየወሰድኩ እጽፋለሁ፡፡ አውቀውኝም ወደኔ የማይመጡ አሉ፡፡ ሌላ የሚቀርቡት ጓደኛ ካላቸው አለያም ብቻቸውን መሆን ከፈለጉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጠዋቱ አራት ሰዓት በሆነ ጊዜ አንድ የስልክ መልዕክት ደረሰኝ፡፡

‹‹ሰላም መዘምር፣ እንዴት ነህ? ጌታነህ እባላለሁ፡፡ አንተ አታውቀኝም፡፡ ረስተኸኝ ይሆናል፡፡ መምህር አሰፋ ናቸው ስልክህን የሰጡኝ፡፡ የማልረብሽህ ከሆነ ልደውልልህ፤ ለአንድ ብርቱ ጉዳይ ፈልጌህ ነው›› ይላል፡፡

‹‹እሺ፡፡ ደውልልኝ›› ብዬ በአጭሩ መለስኩለት፡፡ ወዲያውኑም ደወለልኝ፡፡

‹‹ሄሎ መዘምር፡፡››

‹‹ሄሎ፡፡››

‹‹እንዳልኩህ አንተ አታውቀኝም፡፡ እኔ አውቅሃለሁ፡፡ በፊት ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት የምንተዋወቅ መሰለኝ፡፡››

‹‹እሺ፡፡ መምህር አሰፋ ስትል ጠርጥሬያለሁ፡፡ አሰፋ ኬሚስትሪ መምህራችን ናቸው አይደል?››     

‹‹አዎ፣ እኔ ጌታነህ እባላለሁ፡፡ ከዚህ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ፈልጌህ ነበር፡፡ ቁጭ ብለን ብናወራ ምን ይመስልሃል?  ቢበዛ ግማሽ ሰዓት ብወስድብህ ነው፡፡››

‹‹ማለት መቼ?››

‹‹አሁን እዚሁ ነኝ፡፡ ቤተሰብ ጥየቃ መጥቼ ነው፡፡›› 

‹‹ይህ ሰው ማነው? የአንድን የበፊት መምህሬን ስም ጠርቶ ለምን ፈለጎኝ ነው?›› ብዬ አሰብኩ፡፡ ዛሬ ጊዜው በከፋበት ሁኔታ ከማላውቀው ሰው ጋር እንዴት እገናኛለሁ? ካሁን በፊትም ፈልጌህ ነበር ብለው ያልሆነ ነገር ውስጥ ሊያስገቡኝ የፈለጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ አሳይመንት ስራልኝ የሚል አለ፡፡ እከሌን ውጤቴን እንዲያስተካክልልኝ ለምንልኝ የሚል አለ፡፡ ይህኛውን ዳኛ ወይም ባለስልጣን አማልደኝ የሚልም አይጠፋም፡፡ የረባ ነገር ይዘው እንደማይመጡ እጠረጥራለሁ፡፡ ዛሬም ይህንኑ ስሜት አስተናገድኩ፡፡ ዕድለቢስነት አለኝ ከምልባቸው ጉዳዮች አንዱ ሰው ‹‹ለሆነ ጉዳይ ፈልጌህ ነው  ወይም አንድ ነገር ትተባበረኛለህ?›› የሚለኝ በደፈናው የሚቀርብ ሃሳብ ስለሆነ በቻልኩት መጠን አይመቸኝም ብዬ እመልሳለሁ፡፡ የማይሆን ነገር ሲሆን ውስጤ ይነግረኛል፡፡ ቢሆንም ግን ቀልቤ አልወደደልኝም ብዬ አምልኮ በሚመስል መልኩ ሰውየውን መዝጋቱ ከኔ የማይጠበቅ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ለመምህራችንም ይህን ቢነግራቸው የሚሰማቸውን አሰብኩት፡፡ ይህን ሁሉ ሃሳብ በሁለት ወይም ሦስት ሴኮንዶች ውስጥ ማውጣት ማውረዴ በራሱ ገርሞኛል፡፡

‹‹እስኪ ያሉኝን ስራዎች ሁኔታ ልይና … ››

‹‹አሁን ከተመቸህ ድንገት እንዳይሆንብህ እንጂ እኔ እዚሁ አካባቢ ስለሆንኩ፣ መኪናም ስለያዝኩ መጥቼ ልወስድህ እችላለሁ፡፡››

‹‹ይሻላል? እሺ በቃ ዩኒቨርሲቲው በር ጋ እንገናኝ፡፡››

‹‹ከስንት ደቂቃ በኋላ?››

‹‹ከአንድ አስር ደቂቃ በኋላ››

ፋይሎቼን ሴቭ አድርጌ፣ የኮምፒውተሬን ሶኬት መነቃቀል ጀመርኩ፡፡ ኮምፒውተሬንም ዘጋሁና ቦርሳዬ ውስጥ አስቀመጥኩት፡፡ ላውንጅ አብረውኝ የነበሩትን ሁለት መምህራን የቀራቸውን እንዲያወሩ ትቻቸውና ሰው እንደፈለገኝ ነግሬያቸው ወጣሁ፡፡ ቦርሳዬን ቢሮ አስቀምጬ ወጣሁ፡፡ የማርፈጃ ስራዬን የሚያቋርጥ ጉዳይ ቢገጥመኝም ዓይኔም ከኮምፒውተሩ ጨረር አረፍ እንዲል አንድ አጋጣሚ ነው ብዬ ወደ ዉጪ መውጣት ጀመርኩ፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የሚመጡ የደህንነት ሰዎች ሁኔታ ለምን እንደሆነ በማላውቀው መንገድ ትዝ አለኝ፡፡ ያኔ የሆነ አሳማኝ መሳይ ጉዳይ ይዘው መጥተው መምህራንን ያናዝዙ ነበር፡፡ ምናልባት አንድ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበረው ብሔር አባል ከሆነ መምህር ወይም ተማሪ ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው ልኮባቸው ይሆናል፡፡ ለማስፈራራት ያህል ከሆነ አስፈራርተውና አስጠንቅቀው ይልኩታል፡፡ ያንንም ማታ ውስኪ እያወሩ ይሳሳቁበት ይሆናል፡፡  የምር በሆነ ምክንያት ከሆነም ያ ሰው የሚገጥመውን ነገር አእምሮ መሄድ እስከሚችለው ድረስ ማሰብ ነው፡፡ አእምሮ ካልሄደም ሰውዬው ስለሄደ የራሱን ተፈጥሯዊ መንገድ ይሄዳል፡፡ ተፈጥሯዊም ካልሆነ ሰው ሰራሽ መንገዶች ይፈለጉለታል፡፡ ስለዚህ ስላለፈ ታሪክ መጨነቄን ትቼ የዩኒቨርሲቲውን ምድረግቢ ዉበት እንዳዲስ እያደናነቅሁ ወደ ዋናው በር አቀናሁ፡፡ ዋናው በር ጋ ስደርስ ወደጠራው የታህሳስ የበጋ ሰማይ ቀና ስል የዩኒቨርሲቲውን ዋና በር በግርማ ሞገስ ተሰይሞ እንዳዲስ አየሁት፡፡ ጠበብ ባይል ኖሮ ሃሳቡ ድንቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የሸዋን ቤቶች እድሞ አስመስሎ የተሰራ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ በእርግጥ የአንኮበርን ቤተመንግሥትም ይመስላል ይላሉ፡፡ አንድ መግለጫ እስካልተጻፈ ድረስ ከመላምትና ከስሚ ስሚ የዘለለ ሃሳብ ልሰጥ አልችልም፡፡ አሁን እውነት ለመናገር የሚያሳስበኝ ጉዳይ እያለ ስለ በር ምን አስጨነቀኝ? ዋናውን በር እንደወጣሁ በስተግራ ከመንገዱ ዳር አንድ መኪና ቆሟል፡፡ ክላክስ አደረገና ጠራኝ፡፡

በሹፌሩ በኩል ሄጄ ሰላም አልኩት፡፡ የኮሮና ሰላምታ አሰጣጥ በክርኔ ነው የገጨሁት፡፡ ቅርበት ይሁን የሰውነቴን ማነስ አይቶ ወይም መኪና ስላልያዝኩ ዝቅ አድርጎ አላውቅም አንቺ እያለ ያናግረኝ ጀመር፡፡

ዓይንና ፊቱን አይቼ ትንሽ ትንሽ አስታወስኩት እንጂ ፈጽሞ ተቀይሯል ለማለት እችላለሁ፡፡ 

‹‹እንዴት ነሽ?››

‹‹ደህና ነኝ፡፡››

‹‹አስታወስሽኝ?››

‹‹ብቻ በደንብ አልመጣህልኝም››

‹‹ዘጠኝና አስር አንድ ትምህርት ቤት ተምረናል፡፡ እኔ አስራ አንደኛን አባቴ ስራ ስለተቀየረ ደብረሲና ስለተማርኩ ነው፡፡››

‹‹ነው እንዴ? ጊዜውም እረዘመ እኮ፡፡››

‹‹አዎ ስንት ዘመኑ! ለዚያውም አንቺ ብዙም አልተቀየርሽ፡፡ እኔማ ጸጉሬም አለቀ፡፡ ቦርጩም ምኑም፡፡››

‹‹ትንሽ ትንሽ ትዝ ትለኛለህ›› አልኩት ለማስታወስ እየሞከርኩ፡፡ የከተማ ልጅና የመንግሥት ሰራተኛ ልጅ መሆኑን አስታወስኩ፡፡

‹‹እነ አብዱሰላም ክፍል ነበርሽ አይደል?›› ሲለኝ በደንብ አስታወስኩት፡፡ የእነርሱ ጓደኛ በመሆኑ አዋዋላቸውና ለእረፍት የሚሄዱባቸው ቦታዎች ትውስ ትውስ አሉኝ፡፡

ከላውንጅ እስከ መኪናዋ ድረስ የተጨነኩት ጭንቀት ተገቢ አለመሆኑ እየታወሰኝ በጨዋታችን መካከል ራሴን ታዘብኩ፡፡ ‹‹መንግሥትን ምን አስቀይሜ ይሆን? በዚህ ዘመን በፌስቡክ ይህንንም ያንንም ስንሞነጫጭር ጠላትና ወዳጁ አልታወቀ! ለክፉ ይሰጠኝ ይሆን?›› ስል ነበር እሱ ጋ የደረስኩት፡፡ 

‹‹የት ይሻለናል?›› በማለት ምርጫዬን ጠየቀኝ፡፡

‹‹የትኛውም ቦታ ቢሆን ችግር የለውም፡፡ ሩቅ አይሁን እንጂ፡፡››

‹‹ጌትቫ እንሂዳ››

‹‹አይርቅም?››

‹‹እንዴ ቅርብ ነው፡፡ ወዲያው ደግሞ ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት አጠገብ ስለሆነም ከፈለግሽ ጎራ ልንል እንችላለን፡፡ ያው ጊዜ ካለሽ፡፡››

የመስማማት ምልክት ሰጠሁት፡፡ መኪናውን አዙሮ ሲነዳ ሳቄ ሊመጣብኝ ነበር፡፡ ምክንያቱ ግን እሱ አይደለም፡፡ ባለፈው ዓመት አንድ ጓደኛዬ እንደ አሸን ከፈሉት የግል የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤቶች ካንዱ አንድ አራት ቀንም መሄዱን እርግጠኛ አይደለሁም ብቻ መንጀ ፈቃድ ይሰጡታል፡፡ ወዲያው ብዙም ሳይቆይ መኪና ገዛ፡፡ አንድ ሳምንት እንደነዳ ሁሉም ስለሱ መኪና መያዝና መንዳት ያወራል፡፡ ጥንቁቅ ወይም ፈሪ ሹፌር ስለመሆኑ፣ ምን፣ ምን እንደ አተያዩ ሁሉም ይወራል፡፡ ሰዉን ሁሉ እያሳፈረ አዲሲቷን ንብረቱን ያሳያል፡፡ ሲነዳ አይቼውም አላውቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን ከቤት ወደ መስሪያ ቤት እየሄድኩ በሩ ጋ ልደርስ ትንሽ ሲቀረኝ በዚያኛው አቅጣጫ የሚሄድ የቤት መኪና ዞሮ አጠገቤ ይመጣል፡፡ ለስራ ቸኩዬ አዲሲቷን መኪና ለመመረቅ ባልተዘጋጀሁበት ያ ጓደኛዬ ኖሯል፡፡ አዙሮ አጠገቤ ገጭ ሲል ሳቄን ለቀቅሁት፡፡ ዓይን ለዓይን ስንገጣጠም ‹‹ምነው?›› ሲለኝ ‹‹እንኳን ለዚህ አበቃህ›› አልኩት፡፡ ‹‹የሳክበትን ምክንያት ንገረኝ እንጂ!›› ሲለኝ ‹‹አይ! እንደዚህ በአንዴ ስታዞራት ገርሞኝ ነው፡፡ ሳትማር እንዴት ቻልክበት?›› ያልኩት ትዝ ብሎኝ ነው፡፡

ጨዋታን ጨዋታ አንስቶት ያኛው ትዝ አለኝ እንጂ የዚህኛውን ሾፌር ስልጠናና ልምድ አላውቅም፡፡ እምነቴን በሱ ላይ ጥዬ መሄድ ነው ያለኝ አማራጭ፡፡ መኪናው ፒክአፕ ነው - ደብል ጋቢና፡፡ ሌላውን ዝርዝር ስለማላውቀው ይህን ካልኩ ይበቃኛል፡፡ መዝሙር ከፈተ፡፡ የኦርቶዶክስ ነው፡፡ ያው ደብረብርሃን ከሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በፊትም ስንማር ከክፍል የተወሰኑ ሙስሊሞች እና አልፎ አልፎ አንድ ወይም ሁለት ፕሮቴስታንት ተማሪዎች ይኖራሉ እንጂ ሁላችንም ኦርቶዶክስ ነን፡፡

‹‹ከንቱ ነኝ

የከንቱ ከንቱ ነኝ …››

ይላል ዘማሪው፡፡  ግጥም ማስታወስ ላይ እስከዚህም ነኝ፡፡ ከዚህ ያለፈውን አላስታውሰውም፡፡ ጅሩ መስመርን አለፍን፡፡ ግራና ቀኝ ብዙ የንግድ ተቋማትን አለፍን፡፡ ሱቁ፣ ቡቲኩ፣ ስጋ ቤቱ፣ ምግብ ቤቱ፣ ሆቴሉ፡፡ ያው ስጋ ቤትና ሆቴል ቢያጅበኝም ከጠዋት ውጪ ምግብ መብላት ካቆምኩ ሁለት ዓመቴን ሚያዝያ ላይ እደፍናለሁ፡፡ ምኞት አይነካኝም፡፡ በዓይኑ የተመኘ ብያለሁ፡፡ ምግብ ሳያምረኝ መሄድ ብቻ፡፡

‹‹በፊት እኮ ጠባሴ ምንም አልነበረባትም፡፡ አስታወስሽ?››

ከሃሳቤ አነቃኝ፡፡ ‹‹አንቺ እያለኝ ስለሆነ እኩል ለመሆን እኔም አንቺ ልበለው? አንቺ ባልለው የጠላሁት ይመስለው ይሆን?›› እያልኩ እየተጨነቅሁ ሳለ አንድ ሃሳብ መጣልኝ፡፡ ይኸውም ከመንገዳችን በስተቀኝ እየተቃረብነው ያለውን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት እንዲጎበኘው መጋበዝ ነው፡፡ የንግግሩን ምላሽም ወደዚያው ወሰድኩት፡፡

‹‹አዎ ተለውጣለች፡፡ በፊትማ ብዙ ደቂቃ ሄደህ የምታገኘው አንድ በጭራሮ አጥር የተከበበ ቤት ነበር እኮ›› አልኩት፡፡

እየሳቀ ተጨማሪ ወግ ሊያመጣ ሲል ቀደም ብዬ

‹‹እዚያች ጋ ያለችውን ቤተመጻሕፍት ሁለት ደቂቃ ወስደን አይተን እንሂድ?›› በማለት ሃሳብ አቀረብኩለት፡፡ ያው ፕሮግራም መሪው እሱ ቢሆንም ሰበር ፕሮግራም ለማስገባት በማስፈቀድ መልኩ፡፡

‹‹ኦ! እሺ፡፡ በደስታ፡፡ ልልሽ ነበር፡፡ ትክክለኛ ቦታውን ስላላወኩት ነው እኮ፡፡››

‹‹ሰምተሃላ? እዚህ ነው አዎ፡፡››

‹‹ምን ያልሰማሁት አለ! ሰምቻለሁ፤ አይቻለሁ፤ መጽሐፍ መጻፍሽን፤ በቴሌቪዥንም አይቼሻለሁ፡፡ አኩርተሸናል፡፡››

‹‹አመሰግናለሁ›› አልኩና ለምን እንደፈለገኝ ለመገመት ብሞክርም አቃተኝ፡፡

ወደ ቤተመጻሕፍቱ እየተጠጋን ዉጪ ላይ ያለውን የሕጻናት መንሸራተቻ አሳየሁት፡፡ እንደ ቀልድ አድርጎ ለመንሸራተት ቢቃጣውም ሸርታቴው እንደማይችለው ስላሰበ ተወው፡፡ መንሸራተቻውን ይዞ በሃሳብ ጭልጥ አለ፡፡ የልጅነት ትዝታውን እያሰባሰበ መሰለኝ፡፡ የከተማ ልጅ ስለሆነ መቼም እንደኛ እንደገጠሮቹ መዋዕለ-ሕጻናት ሳይገባ ዘው ብሎ አንደኛ ክፍል አይገባም ብዬ ነው፡፡  ዘወር ብሎ አየኝና ‹‹ምን ብታስቢ አገኘሽው አንቺ!›› አለኝ፡፡ ፈገግ ብዬ ወደ ውስጥ ጋበዝኩት፡፡ በአስፋልቱ ዳር ከሚያልፉትና በወቅታዊው የጸጥታ ችግር ምክንያት ገና ትናንት የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳላቸው ባጃጆች ድምጽ ታጅበን ነበር፡፡ ለዛሬው ከወር በላይ ጠፍተው የመጡ በመሆናቸው በድምጻቸው ተደስተናል እንጂ አልተማረርንም፡፡

ነጭ ጋወን የለበሰችውን የቤተመጻሕፍት ሰራተኛ በዓይናችን ሰላም ብለን ስንገባ እሷም ከመቀመጫዋ በመነሳት አጸፋውን መለሰችልን፡፡ ቤቱ በአንባቢያን ተሞልቷል፡፡ እንኳን የጦርነት ወቅት ይመስል በማግስቱ ማትሪክ ያለ ነበር የሚመስው፡፡ እኔም እንግዳ ሲመጣ ቤቱ ሙሉ ሆኖ ሳገኘው እደሰታለሁ፡፡ የሆነ የመንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መንፈስ ሊጠናወተኝ ነው መሰለኝ፡፡ ግን ምንም ቢሆን ለዚያ ዓይነቱ ማስመሰል አልንበረከክም፡፡ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ብንሆን ደጋፊያችን የሆነ የውጪ ድርጅት በመጣ ቁጥር አንባቢ ባይኖር የሚሰማንን የስሜት ክስረት አስቡት፡፡ አሁን ግን ቢያነቡም እሰየው፣ ባያነቡም ሌላ መፍትሔ የምንፈልግለት ችግር አገኘን ማለት ነው እያልን እንጽናናለን፡፡ በእርግጥ እንደኔ ላለው ማህበረሰባዊ ለውጥ አራማጅ ችግር መፍትሔን ይፈጥራል ባይ ነኝ፡፡ በሹክሹክታ ለትምህርት ቤት ጓደኛዬ ለጌች ማስረዳት ያዝኩ፡፡

‹‹ከመግቢያው በር ጀምሮ ያሉትን እያቸው፡፡ ይህኛው መደርደሪያ የልቦለድ መጻሕፍትን ይዟል፡፡ ይህኛው ታሪክን፣ ፖለቲካን፣ ልዩ ልዩ መጻሕፍትንና ግጥምን ይዟል፡፡ ይህኛው ደግሞ ከአንደኛ እስከ አስረኛ ክፍል ያሉ መርጃ መጻሕፍትን አካቷል፡፡ ከታች የትርጉም መጻሕፍት በሁለት መደዳ ይታያሉ፡፡ ይህኛው መደርደሪያ ደግሞ የ11ኛና 12ኛ ክፍል መርጃ መጻሕፍትን ይዟል፡፡ ቀጣዩ ደግሞ የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን ማለትም ከዩነቨርሲቲ ደረጃ ጀምሮ የሚሆኑ የታሪክ፣ የግለታሪክ፣ የስነጽሑፍ፣ የሥነልቦና የመሳሰሉትን ይዟል፡፡ እስካሁን ያየሃቸው መጻሕፍት እዚሁ የሚነበቡ ናቸው፡፡ እዚሁ ሲነበቡ ክፍያ አይከፈልም፡፡ ወደ ቤትም ተውሶ መውሰድ ይቻላል፡፡ ለዚያም በቀን አንድ ብር ያስከፍላል፡፡ ከዚህ ጀምሮ ያሉት ሦስት ትንንሽ መደርደሪያዎች የሽያጭ መጻሕፍትን ይዘዋል፡፡ ክፍሉ እንደምታየው ይነበብበታል፡፡ ጓዳዋ ደግሞ የሕጻናት ማንበቢያ ክፍል ነች›› ብዬ ባጭሩ አስተዋወኩት፡፡

ካስረዳሁትና ክፍሉ ውስጥ ያሉትን ነገሮችና ትዕይንት ካስጎበኘሁት በኋላ የመጠየቅ አዝማሚያ ሲያሳይ አንባብያንን እንዳንረብሽ በማሰብ ወደ ውጪ ወጣን፡፡ አንባብያን ቀና ቀና እያሉ ሲያዩን ብዙዎቹ ስለማውቃቸው በዓይን ሰላምታ ሰጠኋቸው፡፡ አንዳንዴ ምሳ ሰዓት፣ አልፎ አልፎ ምሽት እንዲሁም ዘወትር እሁድ በአስነባቢነት ስለምሰራ ባለቤትና ሥራአስኪያጅ መሆኔን ያውቃሉ፡፡

የትምህርት ቤት ጓደኛዬን እየቀረብኩት ስለመጣሁ በከፊል ነፃነት አወራለት ጀመር፡፡ አሁን ተራው የሱ ስለሆነ የተወሰኑ ጥያቄዎች ካሉት ብዬ በማሰብ ዉጪ ላይ ዕድሉን ሰጠሁት፡፡

‹‹በመጀመሪያ አድናቆቴን ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ የትምህርት ቤታችን ቤተመጻሕፍት እንኳን ይህን ያህል መጽሐፍ ያለው አልመሰለኝም! ነበረው እንዴ?››

‹‹አመሰግናለሁ፡፡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ እረሳሁት፡፡ አንድ ቀን ከ14 ዓመት በኋላ ኃይለማርያም ማሞ ሄጄ ቤተመጻሕፍቱ ተዘጋብኝ፡፡ አሁን አንድ ፎቅ ህንጻ ለቤተመጻሕፍት ስለተሰራ ከዚህ ይበልጣል፡፡››

‹‹እውነት በዪኝ››

‹‹አዎ፡፡ አንድ ቀን እናየዋለን ከተቻለ፡፡››

መለስ ብሎ ቤተመጻሕፍቱንና በውስጡ የሚካሄደውን እያየ ‹‹ቆይ ሳልረሳው ያንቺን መጽሐፎች አምጪልኝ፡፡›› አለኝ፡፡

‹‹በውሰት ወይስ …››

‹‹ኧረ በሽያጭ! ይቻላል ብለሽኛል አይደል ቅድም?››

አዎንታዬን ራሴን በመነቅነቅ ገልጬለት ወደ ውስጥ ገብቼ ሦስቱንም መጻሕፍቴን በሽያጭ መዝገብ ላይ አስመዝግቤ ሰጠሁትና 550 ብር ተቀብዬ ለአስነባቢዋ ሰጥቼ ወጣሁ፡፡ ለቤተመጻሕፍቱ ከሳምንቱ ቀናት ከፍተኛው ዕለታዊ ሽያጭ ሳይሆን ያልቀረ ሽያጭ በማስመዝገቤ የጠዋት ድርብርብ ድሌን እያከበርኩ ነበር ለማለት እችላለሁ፡፡ በቀን ሦስት መጽሐፍ መሸጥ ብርቅ ነው፡፡ ቢሸጥማ የቤት ኪራይ ተከፈለ ማለት ነበር፡፡

‹‹እንዳላቆምህ እየሄድን እናውራ፡፡››

‹‹እሺ ጥሩ፡፡››

መኪናዋ እያስነሳ ወሬ ጀመርን፡፡

‹‹እኔ ከጠበቅሁት በላይ ነው የሆነብኝ፡፡ በጣም ተደስቻለሁ፡፡ ከምን እንደምጀምር አላውቅም፡፡ በቃ ማንበብ ልታስጀምረኝ ነው፡፡ እንዳጋጣሚ ሁለቱንም ቃለመጠይቆችህን አይቻለሁ፡፡ አንዱ የዘርማጥፋት ጉዳይ ነበር አይደል?››

‹‹አዎ፣ ነው፡፡››

‹‹ሌላኛው የፆም ጣዕም፣ አዎ፡፡ ስለ ፆም›› እየሳቀ ያየኝ ጀመር፡፡

‹‹እፆማለሁ እኮ፡፡ ግን ያው ሰውነቴ እንደምታዪው ነው፡፡›› እያለ ሆዱንና ሁለመናውን ያስቃኘኝ ጀመር፡፡

‹‹በደንብ ባትፆም ይሆናል፡፡ እስኪ አንብበውና ይታያል፡፡ በእርግጠኝነት የሸንቃጣነትን ህይወት ትጀምራለህ፡፡››

‹‹በእርግጠኝነት ያልሽው ደስ ብሎኛል፡፡ ቃል እገባለሁ፡፡ ኧረ ግፊትም እየጀማመረኝ ነው፡፡››

‹‹በል ፈጠን ብለህ ጀምር፡፡ መፍትሔው እጅህ ገብቷል፡፡››

‹‹አንቺ ግን ተቆጣጥረሽዋል ውፍረትን፡፡ እንዴት ነው አመጋገብሽ፡፡ በቀን አንዴ የሚል ነበር የሰማሁት፡፡››

‹‹አንተማ በሚገባ እየተከታተልከኝ ነው፡፡ ጥሩ አድማጭ ነህ ማለት ነው፡፡››

‹‹አትቀልጂብኝ!››

‹‹ህክምና ነው እንዴ ያጠናሽው?››

‹‹አይደለም፡፡ ሥነጽሑፍ ነው፡፡››

‹‹እውነት? ገራሚ ነው፡፡››

‹‹በግሌ ፍላጎት ስላደረብኝ አንብቤና ተግብሬው ነው፡፡ አንብበኸው እናወራበታለን፡፡››

‹‹ይህኛውስ በእናትሽ?›› አለኝ ሦስተኛውን እየጠቆመና ከመኪና እንውረድ የሚል ምልክት እያሳየኝ፡፡ ጌትቫ ሆቴል ጎጆ በረንዳ ላይ አረፍ አልን፡፡ እሱ ቡና ከረባት፣ እኔ ደግሞ አንድ ሊትር ዉኃ አዘዝን፡፡ እየጠጣን ወጋችንን ቀጠልን፡፡

 ተቀምጦ ሳየው ቦርጩ ውጥር ብሎ የሸሚዙ አዝራሮች ሊበጠሱ ደርሰዋል፡፡ ፊቱም ላብ ችፍ ብሎበታል፡፡ ከኔ ስርጉድ ያለ ሆድ አንጻር ሲተያይ ለንጽጽር የተቀመጥን ይመስላል፡፡

ስለሱ እንዲነግረኝ ጋብዤው ነርሲንግ አጥንቶ የተወሰኑ ዓመታት በመንግሥት ጤና ጣቢያ መስራቱንና ከዚያም ወደ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ገብቶ መስራቱን አጫወተኝ፡፡ ለዚያ ድርጅት ለተወሰኑ ከሰራ በኋላም በአንድ የዉጪ ድርጅት በተሻለ ደምወዝ ተቀጥሮ መስራቱን በመተረክ ቀጠለ፡፡ በየመሃሉም ስለ ዩኒቨርሲቲ ስራ እየጠየቀኝ ነጋገርኩት፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ግን እርሱ በስራአስኪያጅነት የሚመራውን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መስርቶ እየሰራ መሆኑን ነገረኝ፡፡ የስራ ዕቅድን እያስገቡ ከውጪ ድርጅቶች ገንዘብ እያፈላለጉ መስራት እንዴት የሚለመድና አዋጪ እንደሆነ አስረዳኝ፡፡ ገንዘብ የመዝረፊያ መንገድ መሆኑንም ሊደብቅ አይችልም፡፡ ዓይኑም ሁለመናውም ይናገርበታል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ቤተሰቡን በሂሳብ ሹምነት፣ በሹፌርነት፣ በምክትል ስራ አስኪያጅትና በሌሎችም የስራ መደቦች መቅጠሩንና ገንዘብም ሲያገኝ አብዛኛውን ውስጥ ለውስጥ መጠቀሚያ እንደሚያደርጉት ካሉት ንብረቶች ዝርዝር ለመረዳት ሞከርኩ፡፡ አሁን እኔን የፈለገበትን ብርቱ ጉዳይም ነገረኝ፡፡ የግል ቤተመጻሕፍት እንዳለኝና ዩኒቨርሲቲም እንደምሰራ ስለሰማ ሊያዘጋጅ ባሰበው የስራ ዕቅድ ውስጥ ሊያስገባኝና ቤተመጻሕፍቱንም እንደ አጋር ሊጠቀም ማሰቡን አጫወተኝ፡፡ ሃሳቡ በደፈናው ሲያዩት የሚበረታታና ማለፊያ ይመስላል፡፡  በቅርቡ በተከሰተው ጦርነት ወቅት ስለደብረብርሃን ሁኔታ ወገን እንዳይሰጋ በፌስቡክ በተደጋጋሚ ስጽፍና የምጽፈውንም ሰው ሲያጋራው አይቶ ጌች ይከተለኝ ኖሯል፡፡ በዚያውም አንድ ቀን የለጠፍኩትን ጽሑፍ ያያል፡፡ ያ ጽሑፍ በጦርነቱ የወደሙና የተጎዱ የትምህርት ቤትና የህዝብ አብያተመጻሕፍትን  መልሶ ስለማቋቋምና ስለማገዝ የጻፍኩት ነበር፡፡ ሃሳቤም በጅምር ያለና የተጎዱ አብያተመጻሕፍትን ሁኔታና መገኛ ከነገሩኝ ለአገራችንም ሆነ ለአህጉራችን የአብያተመጻሕፍት ማህበራት መሪዎች እንደማሳውቅ ብቻ ያጻፍኩበት ነው፡፡ ጌችም በቡራዩና በጌዲዮ በተከሰቱት ጥቃቶች ወቅት ያገኘውን የ25 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደ አብነት አንስቶ አብረን እንስራ የሚል ሃሳብ አቀረበልኝ፡፡ አዝማሚያውን ሳየው ግን ሃቀኛ ሰው አልመሰለኝም፡፡ ስለሆነም የስራ ጫና፣ የጊዜ እጥረት፣ አብሮ የመስራት ፍላጎት ማነስን ጠቅሼ አቋሜን በአጭሩ አስረዳሁት፡፡ ሂሳቡን ከፍሎ ወደ ዩኒቨርሲቲ መለሰኝ፡፡ ተሰናብተን ሄደ፡፡

ከተሰናበትንም በኋላ በችግረኛ ስም የሚደረገውን ነገር ከሰማሁት ለማሰላሰል ሞከርኩ፡፡ በቅርቡ እንኳን ከሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ በተፈናቀሉና ደብረብርሃን በስደተኛ ጣቢያዎችና በየዘመድ ቤት በተጠለሉ  ወገኖች ስም የሚሰራውን ታዝቤያለሁ፡፡ ደብረ ብርሃን ከአዲስ አበባ ሁለት ሰዓት የመኪና መንገድ ስለሚወስድ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ሆኑ ልዩ ልዩ ተቋማት በተከሰተው ነገር ልባቸው ስለተነካ የሚመጣው እርዳታ ከፍተኛ መጠንና ጥራት ያለው ነው፡፡ ለድንኳን የሚሆን ደረጃውን የጠበቀና አምስት ሺህ ብር የሚሸጥ ሸራ፣ ልዩ ልዩ ምንጣፎች፣ ፍራሾች፣ የተሟሉና ጥራት ያላቸው የማብሰያ ዕቃዎች፣ የምግብ ጥሬ ዕቃ ባለ ሃያ አምስት ኪሎ ከያይነቱ፣ ዘይት፣ ለተለያዩ ጉዳዮች በስደተኞች ባንክ አካውንት የሚገባ ጥሬ ገንዘብ ወዘተ መጥቷል፡፡ በዚያ ላይ እርዳታው ባናት ባናቱ ከየድርጅቱ ይመጣል፡፡ በከፊል የደረሰው አለ፡፡ ለሕይወት ማቆያ ያገኘ አለ፡፡ ምንም ሳያገኝ ተሰልፎ ውሎ የሚመለስም አለ፡፡ የእርዳታው በትክክል የመድረስ ሁኔታ እንደየካምፑ፣ እንደየአከፋፋዩና እንደየ እረጂው ድርጅት ክትትል ይወሰናል፡፡ በትክክል ቢደርስ ተረጂዎቹ እቤታቸው ተመልሰው ለመቋቋምና ለአንድ ዓመት ያለችግር ለመቆየት ያስችላል የተባለ እርዳታ እንደመጣ ይነገራል፡፡ ከተረጂዎቹም ወገን ወጣትና ለማጭበርበር የቻለው ሁለትና ሦስት ዙር እየተቀበለ የሚሸጥ ስላለ ገበያው ደርቷል፡፡ ከተፈናቃይ ገዝቶ ለዓመታት የሚበቃ ቀለብ ያከማቸ  ግለሰብና ስንጥቅ ለማትረፍ ገዝቶ የከዘነ ነጋዴ በየቀጣናው ሞልቷል፡፡ ይህንና ብዙ ዝርዝር ማወቅ ተስፋ የሚያስቆርጥና የሌብነትን ስር መስደድ የሚያስገነዝብ አንድ ተጨማሪ ምሳሌ ነው፡፡ አሁን ከምግብና የዕለት ደራሽ እርዳታ ስርቆት ፈጻሚዎች ሌላ የተማሩና ከዉጪ ትስስር ያላቸው ረቀቅ ወዳሉ የዝርፊያና ቅሚያ መንገዶች የሚገቡበት ጊዜ ስለሆነ እነሱ በተራቸው እየመጡልን ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡    ይህ የቀማኛነትና የእምነት ማጉደል አባዜ አገራዊ ፈተናችን እየሆነ ነው፡፡ አገር የሚሸጡትም ተመሳሳይ በሽታ የተጠናወታቸው ናቸው፡፡ ስርነቀል ለውጥ ካልመጣ ያልለፉበትን ለማግኘት የሚመኙ ከቀን ወደቀን እየበዙ የሚሄዱ ይመስለኛል፡፡ ለቀጣይ ትውልድም በሽታው ይተላለፋል፡፡ ሌብነት የሚያስከብር ጉዳይ እየሆነ ይሄዳል፡፡

ጥር 2014 ዓ.ም.

ጌች ለገና በዓል ቤተሰብ ጋ መምጣቱን ጠቅሶ ደወለልኝ፡፡ እስከ ጥር ሥላሴ የንግሥ በዓልም ስለሚቆይ ብዙ መጨዋወትና ማቀድ እንደምንችል አስቧል፡፡ ጦስኝ አምባ ሆቴል ተገናኘን፡፡ ቢራ ጋበዘኝ፡፡ ሦስቱንም መጻሕፍቴን ማንበቡን ነገረኝ፡፡ በተለይ ‹‹ብዕረኛው የሞጃ ልጅ›› የተባለውን ግለታሪኬንና የስራፈጠራ ህይወት ጉዞዬን አተኩሮ አወጋን፡፡ የህይወት ፍልስፍናችን የተራራቀ መሆኑን በመጠኑ እየተገነዘበ ነው፡፡ በነጻ ማስነበቤን፣ ለበጎ አድራጎት ያለኝን ፍላጎት፣ የወጣሁና የወረድኩትን ሁሉ አንብቦ ገርሞታል፡፡

በመሃል እንዲመጡ ቀጥሯቸው ኖሮ መምህራችን ጋሽ አሰፋ መጡና ተቀላቀሉን፡፡ ሽበት ወሯቸዋል፡፡ ጎብደድ ብለዋል፡፡ እሱ ሳይንስ ላይ ጎበዝ ስለነበር የተሻለ ይግባባሉ፡፡ እኔንም የቤተመጻሕፍቱና የህዝብ አገልግሎት ስራዬን ስለሚወዱልኝ በሂደት እየግባባን ነው፡፡ በመንገድም ስንገናኝ ሞቅ ያለ ሰላምታ እንለዋወጣለን፡፡

‹‹ለቤተመጻሕፍቱ ሕንጻ ማሰራት አለብህ፡፡ እኛም እናግዛለን፡፡ ጠይቀን የሚደርስብንን›› በማለት ጌች ካቋረጠበት ቀጠለ፡፡

‹‹በእውነቱ ለልግስናህ አመሰግናለሁ፡፡ ብጠይቅ ጓደኛም፣ ዘመድም የከተማውም ሰው አይጨክንብኝም፡፡ እንስራልህም የሚል መጥቶ ነበር፡፡ እኔ የምፈልገው ግን በግል ህንጻ ላይ የሚሰራ የግል ቤተመጻሕፍትን ስራ ማሳየት ነው፡፡ ያ ውጤታማ ከሆነ ወደ ሌላ ከተማና አገርም የሚሄድ ልምድ ተገኘ ማለት ነው፡፡››

ጋሽ አሰፋ ክርክራችንን ያዳምጠሉ፡፡

ጌች ቀጠለ፡፡ ‹‹እንዳነበብኩት ወጪውን አይሸፍንልህም፡፡ መጻሐፎቹም የያዙት ብር አለ፡፡ ቀጣይነቱንስ አስበህበታል?››

‹‹ቀጣይነት መንግስታዊ ላልሆነም ሆነ ማናቸውም ድርጅት ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ለግልም ስራ እንደዚሁ፡፡ እኔ የሕይወቴን ጥሪዎች እየሞካከርኩ ነው፡፡ አንባቢ የሚመጣና የሚጠቀም እስከሆነ ድረስ ደስተኛ ነኝ፡፡ አንባቢ ስልህ መጥቶ አንብቦ የሚወጣው፡፡ እነሱ እስካሉ ድረስ አገልግሎት መስጠቴ ያስደስተኛል፡፡››

‹‹ወደፊት ወጪውስ በምን ይሸፈናል? ሁሉ ነገር እየተወደደ መሄዱን ላንተ አላስረዳህም፡፡››

‹‹ልክ ነህ፡፡ የገቢ ማመንጫ መንገዶችን እፈላልጋለሁ፡፡››

‹‹እኮ፡፡ አብረን እንፈልግ፡፡ ትልቅ ቤተመጻሕፍት እናድርገው፡፡ የኛም ድርጅት ቢያቅፈው ይቻላል፡፡›› አለ ጌች ከወገቡ ለጠጥ እያለና መቀመጫውን እየተደገፈ፡፡ ከቢራው ጎንጨት አለ፡፡

በመካከል ከፊት ለፊታችን በሚታየው ቴሌቪዥን ላይ በትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ስላለው ጦርነትና ስለ ዉጪ መንግስታት ጫና መቀጠል የምሁራን ውይይት ይታየናል፡፡ ቤቱ ጫጫታ ስለበዛበት የሚወያዩት በደንብ አይሰማም፡፡ ከዩኒቨርሲቲያችን አንድ የፖለቲካል ሳይነስ መምህር ስለተጋበዙ ለመከታተል ብጓጓም ስላልቻልኩ በኋላ በዩቱብ ላገኘው እችላለሁ በሚል ተጽናንቼያለሁ፡፡

ቀጠልኩ፡፡ ‹‹አይ ቤተመጻሕፍቱን መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከያዘውማ ዓላማውን ሳተ ማለት ነው፡፡››

‹‹እንዴት?››

‹‹ቅድም ከነገርኩህ ዓላማው አንጻር ነዋ፡፡

‹‹እሱስ ልክ ነህ አዎ፡፡››

መምህራችንም የሁለታችንን ሃሳቦች መራራቅ እየታዘቡ ያዳምጡናል፡፡ ልዩነትን ስለማቀራረብ አስተማሩን፡፡ እኛም ከልምዳቸው ያገኙትን ተጠቅመው የሚነግሩንን እየሰማን ሃሳባችንን ለማቀራረብ ቃል ገባን፡፡

ቀኑ እየጨላለመ ስለሄደ ጌች ሂሳብ ከፍሎና ቀጣይ ስንገናኝ የኔ የግብዣ ተራ መሆኑን ነግሬው እኔን ወደ ቤቴ በመኪና አድርሶ መምህራችንን ይዞ ተሰናበትን፡፡ የመሸኘት ተራ ይደርሰኝ መሆኑን አላውቅም፡፡ አንድ ቀን ለእግር ጉዞ ይዤው ካልወጣሁ በስተቀር፡፡

 

የካቲት 2014 ዓ.ም.

ጌታቸው የፌስቡክ ጓደኝነት ጥያቄ ላከልኝ፡፡ ተቀበልኩት፡፡ በቃል ማውጋት ያልቻልናቸውን የገንዘብን አስፈላጊነት፣ እንደዘመኑ የመሆንን ሁኔታና የመተጣጠፍ ችሎታ አስፈላጊነትን አነሳሳልኝ፡፡ ሰማሁት፡፡ መምህራችን እንዳሉትም ለመቀራረብ ብሞክር አልቻልኩም፡፡ ምናልባት እኔም ግትር ሆኜበት ይሆናል፡፡ ያ ግን ለእኔ ላይገባኝ ይችላል፡፡ ለማናቸውም አንድ ጀርመን ሳለሁ ደጋግሜ እሰማት የነበረችን ጉዳይ አስታወስኩ፡፡ እሷን መሰረት አድርጌም ለጓደኛዬ አቋሜን ላብራራለት ሞከርኩ፡፡ ሃሳቡ schicksalsschlag የሚባል ሲሆን፤ እኛ ምንም ብንፍጨረጨር የተጻፈልንን እንኖራለን፡፡ የሚሆነው ይሆናል፤ የሚከሰተው ይከሰታል፤ የሚያጋጥመው ያጋጥመናል፡፡ እንዲያው እንፍጨረጨራለን እንጂ ሆዳችንን ብናሰፋ የትም አንደርስም፡፡  የምናደርገውን ቢያሳጣንም፣ የሰውን ድርሻ ብንቀማም፣ ብንስገበገብም ከልኩ አያልፍም፡፡ ይህን ሳስብ ለሰው መልካም ስለመሆንና ሕሊናችንን ከሸክም ነፃ ስለማውጣት ብናስብ ደስተኛ እንሆናለን፡፡ የሕይወትስ ትርጉሙ ደስተኝነት አይደል?

 

 

 

 

 

1 አስተያየት:

  1. ዐይን የማታስነቅል ጽሁፍ ናት መዜ፡፡ ከህሊና ወቀሳ ነጻ የመውጣት አስተምህሮ እንዳለው ተረድቻለው፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school.

  Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school. The Shenes said they wanted to aven...