ማለዳ ቤተመጻሕፍት ገብቼ ባለፈው የጀመርኩትን መጽሐፍ ጨረስኩት፡፡ እሱም ‹‹የዘውግ ፖለቲካ ስረ-መሰረቶች›› የሚለው የመስከረም አበራ መጽሐፍ ነው፡፡ ሲጨርሱት የሚሰማው ስሜት ከሰው ሰው ሊለያይ ይችላል፡፡ እኔ ለምን አለቀብኝ ነው ያልኩት፡፡ የዘውግ ፖለቲካ ከአውሮፓ ተነስቶ እንዴት ወደ ታዳጊ አገራት እንደተስፋፋ፣ አፍሪካን ለመከፋፈልና ሌሎችንም የዓለም አገራት ለእልቂትና የአስተዳደር ችግር እንደዳረገ ትገነዘባላችሁ፡፡ የፖለቲካ እይታዎች ልዩልዩ ቢሆኑም በአንድ ነገር ላይ ተንጠልጥለው የሚቋቋሙት ግን ውጤታማ አይሆኑም፡፡ ዘውግ የአንድ ሰው አንድ ነጣላ ማንነቱ መሆኑ ተወስቷል፡፡ ዘውግ ፖለቲካ ሲላበስ የሚያመጣውን ጦስ በብዙ የዘርማጥፋት በተካሄደባቸው አገራትና የችግሩ አስከፊ ውጤቶች መታየት እየጀማመሩ ባሉባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ለማየት ተችሏል፡፡ የዘውግ ፖለቲካን ታሪካዊ መነሻዎች በዓለምም ይሁን በአገራችን በተሻለ ሁኔታ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ እንኳን አገርን ለማስተዳደር ይበቃ ከቤተሰባዊና የባህል ትስስር ማጎልበቻነት በላይ ሊጠቀሙበት የማይገባ እንዴት ያለ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ እኛ አገርማ በሕገመንግስት የተደገፈ ዘውገኝነት ስለሆነ ጦሱ ቶሎ በለቀቀን ያስብላል፡፡ ያው ሁላችንም ዘውገኝነትን መዋጋትን ጉዳዬ ብለን ከያዝነው መገላገላችንና ለአገራችን የሚጠቅም የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱ የማይቀር ነው፡፡
እስኪ የዘውግ ፖለቲካን ያመጡታል ተብለው ከሚታሰቡት
አንዱ የሆነውን ነገር እንመልከት፤ በአብነቶችም ለመረዳት እንሞክር፡፡ ምጣኔሐብታዊ ምክንያት የዘውግ ፖለቲካ መነሻና ማቀጣጠያ ሊሆን
ይችላል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው በአንድ አገር ወይም አካባቢ ያለውን ሐብት ለመቀራመት ሲሉ የዘውጉ ልሂቃን ስለሚጀምሩት ነው፡፡
የዚህ አካባቢ ብቸኛና ህጋዊ ተወካዮች እኛ ነን በማለት፣ ሌላውን መጤ ብለው በማራቅና የምርጫ ውጤቱ ወደነሱ እንዲያጋድል በማድረግ
ዘውግ ተኮር አስተዳደር ይመሰርታሉ፡፡ እነዚህ ልሂቃን ህዝባችን የሚሉትን ለመጥቀም ሳይሆን ራሳቸውን ለመጥቀም ሲሉ የሚጀምሩት በህዝቡ
ዘንድ ስሜታዊነትን የሚያጭር የፖለቲካ አካሄድ የእነሱን ሆድ ከመሙላት በዘለለ ለህዝቡ ጠብ የሚልለት ነገር አይኖርም፡፡ ያለውን
ሐብት በጢብኛ ወይም ለአንድ ልጅ የምትበቃ መዳፍ የምታክል ዳቦ መመሰል ይቻላል፡፡ አንዳንድ ቦታ ሽልጦ የሚሏት ነች፡፡ ያችን ሽልጦ
ለመብላት የሚሯሯጠው ብዙ ነው፡፡ ልሂቁ ተቧጭቆ ይጨርሳታል፡፡ ለዚያም ሲባል ሌሎች በላተኞች እንዲመጡ አይፈለግም፡፡
በአንጻሩ ግን ከጢብኛ ይልቅ ዲፎ ዳቦ አለን
ብሎ ማሰቡ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ይኸውም ያ ዲፎ ዳቦ ለብዙ ሰው እንደሚበቃ ማሰቡ መልካም ነው፡፡ ያንንም ዲፎ ዳቦ የአንድ ዘውግ
አባላት ብቻ ሳይሆኑ መላው የአገሪቱ ህዝብ በፍቅር እንደሚበላው ማሰብ የእድገትና አንድነት መሰረት ነው፡፡ ያ ዲፎ ዳቦም በማናቸውም
የአገሪቱ ክፍል አለ፡፡ ያንን ዲፎ ዳቦ ደግሞ ማንም የአገሪቱ ብቻ ሳይሆን ማንም የዓለም ዜጋ እየጋገረ ይበላዋል፡፡ ዳቦው የሚያልቅና
እንደ ጢቢኛዋ አንድ ሰው የሚጨርሰው ሳይሆን ሁሉም በየፈለገው መልኩ የሚጋግረው ነው፡፡ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂና ካፒታል
በዚህ መልኩ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው ይሸጋገራል፡፡ የዓለም ስልጣኔም የመጣው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ብዙ
ትሩፋቶች አሉት፡፡ የሰራኸው ህንጻ በኔ ቦታ ላይ ስለሆነና የኔ ዘውግ አባል ስላልሆንክ አንሳልኝ የሚባል የዘውግ አስተሳሰብ የሚያመጣው
አሰራር ምን ያህል ዕድገትን የሚገታ መሆኑን በመጽሐፉ አንብቤያለሁ፡፡ ፋብሪካ ማቃጠልና ባለሃብትን መግደልን የመሳሰለው የዘውገኝነት
ትሩፋት በቃ ሊባል ይገባል፡፡
ይህ ዳቦው ትንሽ ነው የሚለው ሃሳብ አገርን፣
ድርጅትን፣ ተቋምንም ሆነ ቤተሰብን የሚከፋፍልና ለግጭት የሚዳርግ ስለሆነ መፍትሔ ሊበጅለት ያሻዋል፡፡ ያለዚያ ሌብነትን የሚያበረታታ፣ ዘውገኝነትን የሚያነግስና የማይሆን ጣጣ ውስጥ የሚከት ይሆናል፡፡ ጦሱም እስከ ቀበሌ
የሚደርስ ወገንተኝነትንና የቤተሰብ አሰራርን ያነግሳል እንጂ አገርን የሚያሳድግ መልካም ውድድርን አይፈጥርም፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ