2021 ዲሴምበር 31, ዓርብ

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መጽደቅና ከኮሚሽኑ የምጠብቀው መልካም ስራ

 



 የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መጽደቅና ከኮሚሽኑ የምጠብቀው መልካም ስራ

ከሰሞኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል፡፡ ሁሉን አካታች የሆነ አገራዊ ምክክርና ውይይት በማካሄድ አገራዊ መግባባትና በአገር ጉዳይ የጋራ አቋም እንዲኖር ታስቧል፡፡ ይህን ስራ የሚሰራ ኮሚሽን ለማቋቋም ስለረቀቀው አዋጅ ዝርዝር ሃሳቦቹን ለማግኘት ባልችልም ከዜና ዘገባዎች ለመረዳት እንደቻልኩት ኮሚሽኑ በተለያዩ ጎራዎች የተሰለፉ ልሂቃንንና ምልዓተህዝቡን በአገር ጉዳይ እንዲግባቡ ያስችላል የተባለለት ነው፡፡ ምክክሩን ተግባራዊ ለማድረግ፣ በገለልተኝነት ለመምራትና ለማስተባበር የሚችል ቅቡልነት ያለው ተቋም ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ ከዓመታት በፊት ሲጠየቅ የነበረውን ይህን ኮሚሽን የማቋቋም ተግባር በመጋቢት 2010 ዓ.ም. የተቋቋመው መንግሥት ለማስፈጸም ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ከዚህ ኮሚሽን ብዙ የምንጠበቅው ነገር ይኖራል፡፡ በኃላፊነትና በገለልተኝነት ከሰራም አገራችንን በሰላም ጎዳና የሚያራምዳት ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስለ እርቅ ሂደቱ ለማሰብ ይረዳን ዘንድ ከዓለም ዙሪየ የተለያዩ ተሞክሮዎች ቢኖሩም ለዛሬው የሩዋንዳን የፍትሕና የእርቅ ሂደት እንመልከትና ቀጥሎ በእኛ አገር ላይ የምጠብቀውን ሁኔታ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

የፍትሕና የእርቅ ሂደት በሩዋንዳ

ሩዋንዳውያንን ለከባድ የአእምሮ ጭንቀት የዳረገ፣ መሰረተልማትን ያፈረሰ፣ 48 ዓይነት በዓለም ታይተው የማይታወቁ የተባሉ የጭካኔ እርምጃዎች በመላ ሃገሪቱ በስፋት የታዩበት እ.ኤ.አ. የ1994ቱ የሩዋንዳ ጭፍጨፋ ሩብ ሚሊዮን ሴቶች የተደፈሩበት፣ አንድ ሚሊዮን ቱትሲዎች የተገደሉበትና ብዙ ውድመት የተከሰተበት ነው፡፡ ሩዋንዳውያን በሰላም አብረው ይኖሩ ዘንድ የሚያስችል የፍትሕና የእርቀ-ሰላም ሂደትም ከዚህ አውዳሚ መንግሥታዊና ህዝባዊ የዘረኝነት እብደት በኋላ ተካሂዳል፡፡  ይህንም ለማካሄድ የተቻለው አዲስ መንግሥት በመቋቋሙ ነው፡፡ አገሮቻችን በዘረኛ ሥርዓቶች መከፋፈላቸው፣ በዜጎች ላይ ዘውግን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች መፈጸማቸውና ከዘረኛ ሥርዓት መወገድ በኋላ አዳዲስ መንግሥታት መቋቋማቸው  በርካታ የሩዋንዳና የኢትዮጵያ ተመሳስሎዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ልንማር የምንችለው ከቀውስ የማገገም ትምህርትም አለ የምንለው ለዚህ ነው፡፡

ምንም እንኳን መላው ህዝብ በሚባል ደረጃ የተሳተፈበት የዘር ጭፍጨፋ ቢሆንም 120 000 የሕግ ታራሚዎች በዓለምአቀፉ የሩዋንዳ ፍርድ ቤት፣ በሩዋንዳ የአገር ውስጥ የፍትሕ ስርዓትና በባህላዊው የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች እንደየወንጀላቸው ክብደት ጉዳያቸው ታይቷል፡፡ በአንዱ የፍርድ ሥርዓት ጉዳያቸው ለመታየት ጊዜ የወሰደባቸው በሌላው እየታየ በዓመታት ውስጥ የፍርድ ሂደቱን ለማስተካከል ተችሏል፡፡ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የሚዲያ ሰዎች በዘርማጥፋት ወንጀል ጉዳያቸው ሲታይ በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ወይም በአስርት ዓመታት ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ ከወንጀለኞቹ የሚጸጸቱና እርቅ የሚፈልጉት ቅጣታቸው ዝቅ የሚደረግበት አሰራር ተመቻችቷል፡፡ የፈጸሙትን ወንጀል የሚናዘዙና ከተጠቂዎችና ከቤተሰቦቻቸው ጋር አብረው ለመኖር የሚያስቡት ደግሞ አብረው እንዲኖሩ ተፈቅዶላቸዋል፡፡ 1.2 ሚሊዮን ፍርደኛ በባህላዊው የጋቻቻ የፍትሕ መድረክ ጉዳዩ ይታይ ነበር፡፡

ከተበዳዮችና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለወንጀለኞቹ ወይም ለታራሚዎቹ የእርቅ ስርዓት ተመቻችቷል፡፡ ሁለቱም ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲታረቁም ለማድረግ ተችሏል፡፡ እርቁ ከረጅሙ የፍርድ ሂደት በኋላ የተካሄደ ሲሆን፤ ሩዋንዳዊ ማንነትን መልሶ ለመገንባት፤ ፍትሕ፣ እውነት፣ ሰላምና ደህንነትን ለማምጣትም አስችሏል፡፡ ሩዋንዳውያን እኩል መብት እንዳላቸው ለማስገንዘብም ተችሏል፡፡ መገለልና ከፋፋይ የዘርማጥፋት ሃሳብ እንዲጠፋ የሚያግዙ ህጎችም ተላልፈዋል፡፡

የብሔራዊ አንድነትና እርቅ ኮሚሽን ከፍርዱ ሂደት በኋላ ብዙ ተግባራትን አካሂዷል፡፡ ከእነዚህም የተወሰኑትን እንመልከት፡፡ የሰላምና የአብሮነት ትምህርት መስጫ ማዕከላትን አቋቁሟል፡፡ በእነዚህም ማዕከላት የሩዋንዳን ታሪክና የክፍፍልን አመጣጥ አስገንዝቧል፡፡ የአገር ወዳድነትን ለማሳደግ የሚጠቅም ስራ ሰርቷል፡፡ የሩዋንዳን እሴቶች ማሳደግና ለልማት የሚተጉ መሪዎችን ማፍራትም ተችሏል፡፡ በሥነልቦና ማማከር፣ በግጭት አፈታትና ቅድመ-ጥንቃቄ ላይ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በፍትሕ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብት፣ ብሔራዊ ደህንነትና አገራዊ ታሪክ ላይ ስብሰባዎችና ምክክር ተካሂዷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የብሔራዊ አንድነትና እርቅ ኮሚሽን የግጭቱን መንስኤና መፍትሔን አስመልክቶ ጥናቶችን አሳትሟል፡፡

 

የፍትሕና የእርቅ ሂደት በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የፖለቲካና የአስተዳደር ሥርዓት ያላት አገር መሆኗ ይነገራል፡፡ በዚህም ዘመን በንጉሣዊ ሥርዓት አገራዊ አንድነትን አስጠብቃ ለመኖር ችላለች፡፡ ከኢጣሊያ መምጣት ወዲህ ግን በአገሪቱ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና በዘውግ የተከፋፈለች አገር ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡ ከዚያም በኋላ በህገመንግሥት ፀድቆ የዘውግ ክፍፍል ነፍስ ዘርቶ ብዙ ውድመት አስከትሏል፡፡ በቅርቡ ለንባብ ከወጣው የመስከረም አበራ መጽሐፍ እንደምንገነዘበው ዘውግን እንደ ነጣላ ማንነት ወስዶ አገርን ለመከፋፈል መስራት ያለውን ጥፋት ከኢትዮጵያ በላይ ማስረጃ አይኖርም፡፡ ከአውዳሚው ዘውግ ክፍፍል ውጪ በርካታ መልካም አገር የምትመራባቸው እሳቤዎች እንዳሉ ልብ ይሏል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ የተለያዩ ኮሚሽኖች ተቋቁመው የነበረ ቢሆንም በደርግ ዘመን ኢትዮጵያን ከፊውዳል ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር የሚያስችላትን ሕገመንግስት መቅረጽ ዓላማው ያደረገ መማክርት ሸንጎ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ኢትዮጵያና አምስቱ ህልመኞች በሚለው የዶክተር ኃይሉ አርአያ መጽሐፍ እንደተገለጠው ይህ ኮሚሽን የታሰበው ነጻነት ሳይኖረው ቀረ እንጂ አገሪቱን አንድ እርምጃ ለማራመድና አካሄዷን ለማስተካከል ጥሩ ጅምር ነበር፡፡ እንደዚህ ካሉ ያለፉ ጅምሮች ተምሮ የአሁኑን ከግብ ለለማድረስ አንዳንድ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሰው የዶክተር ኃይሉ መጽሐፍ አምስት ሕልመኞችንና ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ሕልሞች ከነከሸፉበት ምክንያቶች አስነብቦናል፡፡ በስተመጨረሻ ግን ተስፋው ያለው የበረሃ ሕልመኞች ከተባሉት ውስጥ በወጡት የአሁኖቹ መሪዎች ላይ ነው፡፡ የአሁኖቹም መሪዎችም ልዩ ልዩ ኮሚሽኖችን የማቋቋምና ስራዎችን የማከናወን ተግባር ላይ ይገኛሉ፡፡ የአሁኑም ጅምር የዚያ አካል ሲሆን፤ የለውጥ አካሄዳችንን ለማሳመር ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ይሳካ ዘንድ ምን ያስፈልጋል ስል የሚከተሉትን ሃሳቦች ሰንዝሬያለሁ፡፡

የመጀመሪው ሁሉን አካታችነት ነው፡፡ ዶክተር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት በኢትዮጵያውያን አእምሮ ያሉትን ችግሮች ሁሉ ለመፍታት ሞክረዋል፡፡ ያላናገሩት ስለ ኢትዮጵያ የሚመለከተወው አካል የለም ለማለት ይቻላል፡፡ ምናልባት ችግሮቹ የተፈቱበት መንገድና ውስብስብነታቸው የፓንዶራን ሳጥን መክፈትና ወደ ውስብስብ ችግሮች መግባትን ቢያስከትልም ጅምሩ የሚስመሰግናቸው ነው፡፡ ልክ ያኔ እንዳደረጉት ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚካተቱ የተከበሩ፣ ስለአገራቸው በሚገባ የሚያውቁና ገለልተኛ ታማኝ ሰዎች በኮሚሽኑና ኮሚሽኑ በሚፈጥራቸው መድረኮች መካተት አለባቸው፡፡

ሁለተኛው ፍጹም ነጻነት ነው፡፡ ይህን ለማለት የቻልኩት ኮሚሽኑ ነጻነት ካለውና የአገሪቱን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ሰዎች ከተወከሉበት አሁን ካለው የፖለቲካ ሥርዓት በኋላም ላለው ጊዜ የሚሰራ መፍትሔ ይዞ ስለሚመጣ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠልም ተግባብተውና የጋራ አቋም ይዘው የሚያመጡትን ምክር መቀበልና የአገራችንን ህልውና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን በዘር ከፋፍለው፣ በክፍፍላቸው ላይ እንዲያተኩሩ እንጂ አንድነት ላይና አገራዊ ዘላቂ ብልጽግናና አንድነት ላይ እንዳያተኩሩ የሚያደርጉ የውስጥም ሆኑ የዉጪ ኃይሎችን ምኞች የሚያከሽፍ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ግጭትን፣ መሳደድን፣ ሁለተኛ ዜግነትን፣ መጠራጠርንና አገርን ትቶ ሄዶ ሌላ አገር ማገልገልን የሚያስቀር ጅምር ይሆናል ብለን ተስፋ የምናደርገው የዚህ ኮሚሽን ስራ ሃሳባችንን በነጻነት ከዳር ማድረስ ይኖርበታል፡፡

ከኮሚሽኑ ጎን ለጎን የሚሰሩ ስራዎች ቢታሰብባቸው ጥሩ ነው፡፡ ዶክተር ዐቢይ አሁን ያላቸውን ቅቡልነት ተጠቅመው ሕገመንግስቱን አንድ ሊሉልን ይገባል፡፡ የወደቀውን ስርዓት ነፍስ ዘርቶ የሚያንቀሳቅሰው ይህ ሰነድ ኢትዮጵያዊነትን አፍኖ ያስቀመጠና አላንቀሳቅስ ያለ ነው፡፡ ምናልባትም ኮሚሽኑ ህገመንግስቱ ላይ የሚለው ነገር መኖሩንና ኃላፊነቱም ይፍቀድለት አይፍቀድለት አላውቅም፡፡ ለዚያ ደግሞ የህገመንግስት ማሻሻያ ኮሚሽን ይቋቋም ይሆናል፡፡ ልሂቃንን የሚያሳትፉ የአስተዳደር ተግባራትና ዓለምአቀፍ ገጽታችንን የሚገነቡ የዲፕሎማሲያዊ ስራዎችም ለድህረጦርነቱ ገጽታ መስተካከል ሁነኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡

ሰላምንና አብሮነትን እያሰብን ስራ እንኳን ሳንሰራ ብንኖር ያለውን ጥቅም ለመረዳት ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በአገራችን የተከሰቱት ግጭቶች ያስከተሉትን ውድመት ስናይ ነው፡፡ ያንን መልሶ ለመገንባት የሚወስደውን ጊዜና ሃብት ማሰብ የሰላምንና የአንድነትን ዋጋ ለመረዳት ያስችላል፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ በነበረው ግጭት ወቅት ሰዎ በዘራቸው ምክንያት ሲገደሉ ‹‹የጋሞ ህዝብ በታሪክ አጋጣሚ ያጠፋው ካለ ይቅርታ ይደረግልን›› ያሉ አንድ ሸማኔ ንግግር በልቦናዬ አለ፡፡ በዘውግ ፖለቲካ ምክንያት ሁለተኛ ዜጎች ተደርገው የተወሰዱ ሚሊዮኖች ሁኔታ በአእምሮዬ አለ፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ሆና ልትደርስበት የምትችለው ደረጃ ይታየኛል፡፡ የግጭትን አውዳሚነት ለደቂቃ ማሰብ አልችልም፡፡ ዘረኝነት እንደናዚዝም ህገወጥ የሚሆንበት ጊዜ ይናፍቀኛል፡፡ መጤና ነባር የሚለው ሃሳብ እንደሩዋንዳ ህገወጥ የሚሆንበት ጊዜ ይታየኛል፡፡    

ምናልባትም ለመንግስት፣ ለህዝብ፣ ለአገሪቱ ከመጨረሻዎቹ ዕድሎች አንዱ የሆነውን የኮሚሽኑን መቋቋምና ተግባር በጥንቃቄ እንይዘው ዘንድ አሳስባለሁ፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የሩዋንዳም ሆነ የሌሎች አገራት አብነት ለመለወጥ ያለንን ዕድል ያሳየናል፡፡ ከዓለም ዙሪያም ይሁን ከማህበረሰባችን የሚመነጩ የእርቅና አንድነት ሃሳቦች ሰላማዊ፣ የበለጸገችና ዜጎቿ በአንድነት የሚኖሩባትን አገር ባለቤት ያደርገናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...