ረቡዕ 15 ዲሴምበር 2021

ደብረ ብርሃን - በማደግም ባለማደግም የምትገለጽ ከተማ

 

 


ከቅርብ ዓመታት በተለይም ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ ደብረብርሃን ከተማ አድጋለች የሚል ሰፊ ንግግር  ይሰማል፡፡ ይህም በየሚዲያው፣ በግለሰቦችና በየስብሰባው የሚዘወተር ሆኗል፡፡ አድጋለች የሚባለው እውነት ነው ወይንስ ሌላ ዓላማ ያለው? ከደብረብርሃን ወደ ሌላ አካባቢ ስትሄዱ ከኒውዮርክ ወይም ከሲንጋፖር እንደሄዳችሁ ዓይነት ነው የሰዉ አቀራረብ፡፡ አድጋም ይሁን ሳታድግ አድጋለች መባሉ ለከተማዋ ጥቅምም ጉዳትም ይኖረው ይመስለኛል፡፡  ዕድገቱ ደግሞ ከተማዋ ከነበረችበት ያለፈ ሁኔታ ጋር ሊነጻጸር ይችላል፡፡ ከሌሎች ከተሞችም አንጻር ሊተያይም ይችላል፡፡ አድጋለች ብሎ የሚያወራውም ሰው ማንነት ወሳኝነት አለው፡፡ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ አስር ሰዎችን ጠይቄ  እኔም እንደነዋሪ የራሴንም ግምት ወስጄ ይህን ጽሑፍ አዘጋጅቻለሁ፡፡ ጅምር ጽሑፉም ከዳር እንደሚደርስ በማሰብ እናንተም ሃሳብ ስጡኝ፡፡ የጠየኳቸው ግን ከኔ ጋር ቅርበትና የኑሮ ተመሳሳይነት ያላቸው መሆናቸው ጽሑፉ ላይ ተጽዕኖ እንዳይኖረው ያሰጋል፡፡ እስካሁን ጋዜጠኞችን በዚህ ላይ ጻፉ ወይም ዘገባ ስሩበት ብያቸው ስላልሰሩና በሌሎችም ቁጭቶች ጽሑፉን ላዘጋጅ ችያለሁ፡፡

በተሰጡኝ ሃሰቦች መሰረት መልካም የተባሉትን ለውጦች ስንመለከት

ከአካባቢው ነባር የቤት አሰራር ሁኔታ ሲታይ ደረጃቸውን የጠበቁ ህንጻዎች እየተገነቡ ነው፡፡ የግል ግንባታ ላይ በጥቂት ግለሰቦች ባቤትነት ቢሆንም፣ የሌብነት ጉዳይ ቢነሳም፣ የሃብት በጥቂቶች እጅ መከማቸት ቢያጠያይቅም ይህ እውነታ ይመስላል፡፡ መሰረተ ልማትና ኢንዱስትሪ ተስፋፍቷል የሚሉ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ አስፋልትን ያየን እንደሆነ ወደ ሰሜን የሚያቋርጠው አንድ አስፋልት ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኤሌክትሪክ ለረጅም ዘመን የክልሉ ችግር መሆኑና ከደርግ ዘመን ጀምሮ የማከፋፈያ ጣቢያ ስራ አልተሰራም ቢባልም፡፡ ይህ ከሌሎች ቦታዎች በተቃራኒው ነው፡፡ የነዋሪው ቁጥርም ጨምሯል፡፡  የባንኮች በብዛት መከፈት የንግዱን ዘርፍ ለማነቃቃት ችሏል፡፡  ባንክ እንደመስፋፋቱ ግን ለንግድና ኢንቬስትመንት ዘርፍ ያለመድሎ ብድር የማቅረብ ችግር ይነሳል፡፡ ዘመናዊነት መምጣቱም ይወራል፡፡ ይህም በህዝቡ ዘንድ የከተሜነት ሁኔታ እያደገ በመሄዱና የቢዝነስ አስተሳሰብ በማቆጥቆጡ ነው፡፡ የተቋማት መከፈት የሰራተኛን መቀጠርና ቤትን የማከራየት ዕድልን ጨምሯል፡፡ ወደ ዝርዝሮቹ ስንገባ አሳሳቢ ጥያቄዎች ቢኖሩም፡፡ ከግል ምልከታቸው አንጻር ቅዝቃዜው ተሻሽሏል የሚሉም አሉ፡፡

በአሉታዊ መልኩ የሚነሱትን ደግሞ እንይ፡፡

የአስተዳደር ችግር አለ፡፡ አስተዳደር ቢለዋወጥም ለውጥና ብርሃን አላየንም ያሉኝ አሉ፡፡ የለውጡ ተጠቃሚ ያልሆነ ነባር የከተማው ነዋሪ ብዙ ነው፡፡ የዕለት ጉርሱን ሳይቀር የሚቸገር አለ፡፡ በአስተዳደሩ በኩል የሰለጠነ ባለሙያ አይፈለግም፡፡ እንዲያውም ማባረርም አለ፡፡ የአገር ተወላጅ በከተማዋ ለማገልገል ከሌላ ቦታ ሲመጣ አለመሳብና እንዲያውም ፊት መንሳት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ ሙስናም ትልቁ ችግር ነው፡፡ ይህች እንደ አቦሸማኔ እየተስፈነጠረች የምትባል ከተማ መስፈንጠሯ ያጠራጥረናል፡፡ እሷን ተጠቅመው ዘርፈው የተስፈነጠሩና ዕድገቷን ያቀጨጩ ግን አይተናል፡፡

እድገቱ እንደሚወራው አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ከተማውና በየመስሪያ ቤቱ ያለው አገልግሎት እየሰፋ አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ያገኘሁት የተለየ ዝርዝር መረጃ ስለ ጤና ዘርፍ ነው፡፡ በጤና ዘርፍ ከሆነ እንዲያውም ውድቀት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለሆስፒታሉ ትልቅ ደረጃ መስጠት ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ለሲቲ ስካን ሲባል በሽተኛ ኦክስጂን ተሰክቶለት ወደ አዲስ አበበ የግል ምርመራ ማዕከላት ይሄዳል፡፡

ለጤና ዘርፍ በዓመት ድጎማ ከመንግስት 2.8 ቢሊየን ብር ለደቡብ ክልል ይደረጋል፡፡ 2.4 ቢሊየን ብር ለኦሮሚያ ክልል ሲደረግለት፤ ለአማራ ክልል 800 ሚሊየን ብቻ ይደረግለታል፡፡ ይህም ያለውን መድሎ ያሳያል፡፡ ኤም.አር.አይ. ማሽን በክልሉ ያለው ጎንደር ላይ ብቻ ነው፡፡ የደብረብርሃን ሆስፒታል የአፋር፣ ደብረብርሃንና ሰሜን ሸዋ ህዝብ በሪፈር ሲላክም ሆነ በሌላ ወቅት ይጠቀምበታል፡፡ይህ ሁሉ እያለ ሲቲ ስካን እንኳን የለውም፡፡ በራዲዮሎጂ ደካማ ነው፡፡ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ስፔሻሊስት በወረዳ ሲኖር እዚህ ስፔሸሊስት ብርቅ ነው፡፡ የሐረሚያ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል 900 አልጋ አለው፡፡ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ900 በላይ አለው፡፡ አሀን ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአንድ በጎ አድራጊ የተሰራን ሆስፒታል በልገሳ ተቀብሎ አድሶ የህክምና ትምህርት ቤት ሊያደርግ ነው፡፡ ሐኪም ግዛው የተባለው የማስተማሪያ ሆስፒታል ያለው 81 አልጋ ብቻ ነው፡፡ ይህን ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ማነጻጸር ሰማይና ምድርን የማነጻጸር ያህል እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ 15 ዓመት ቢሆነውም ከሱ በፊት የተገነቡት ብዙ ካምፓስ ሲከፍቱና አካባቢዎቻቸውን በልማት ሲያበለጽጉ ይህኛው ግን ለውጡ አይታይም - እንደሚወራው አቦሸማኔ አይደለም፡፡ ከትምህርት ሚኒስቴር ያለ ተጽዕኖ ይሁን ከዩኒቨርሲቲው ምላሽ ይፈልጋል፡፡  እንደዩኒቨርሲቲውና እንደ ሆስፒታሉ ሁሉ የሌሎችም ተቋማት ሁኔታ ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ ስራቸውን ምን ያህል እየሰሩ ነው? እውነት ደብረብርሃንንና ሰሜን ሸዋን አሳድገዋል ወይስ አድጋለች የሚል ሴራ ተባባሪ ናቸው? የግል ተቋማትስ ማደግና መሄድ ያለባቸውን ያህል ሄደው ህዝቡን ተጠቃሚ እየደረገ ነው? ህብረተሰቡ ከትምህርት፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊና ሁለንተናዊ ዕድገት ተጠቃሚ ነው?

የፋብሪካ ብክለት ተደጋጋሚ ጥያቄ ነው፡፡ ይህም አየሩን፣ መሬቱንና የገጸምድርና የከርሰምድር ውኃው የሚበከልበት ነው፡፡ ፋብሪካዎች በገፍ ከሚጠቀሙት ውኃ አንጻር እንደ ሃረር ውኃ አልባ የመሆን ስጋት አለ፡፡ የፋብሪካና መኖሪያ ህንጻ መስሪያ ቦታ አለመለየቱም አንድ ችግር ነው፡፡ ፋብሪካዎችና የኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚቀጥሩት ከ1000 እስከ 1500 ብር የወር ደመወዝ ነው፡፡ ይህም መንግስት ዝቅተኛ ክፍያ ባለማስቀመጡና የሰራተኛ አያያዝ ህጉ የላላ ስለሆነ ነው፡፡ ተቀጣሪዎቻችንን አሰልጥነንና በተከፈቱት የትምርትና ሥልጠና ተቋማት አብቅተን ትልቅ ደምወዝ ማስቀጠር እንዳለ ሆኖ፡፡ የደብረብርሃን ልጅ በቤተሰቡ ደሳሳ ጎጆ እየኖረና ለሆዱም የእናቱን እጅ እያየ፣ የአባቱን የብርድልበስ ፋብሪካ ጡረታ እየጠበቀ በ1000 ብር ደምወዝ ይፈጋል እንጂ 1000 ብር በዚህ ዘመን እንደማያኖር ይታወቃል፡፡ ይህ ገንዘብ ሁለት ጓደኛሞች በአንድ በከተማው በተከፈተ ሆቴል ምሳ በልተው ሻይ ቡና ለማለትም ላይበቃ ይቸላል፡፡  

ለአዲስ አበባ ካላት ቅርበት የተነሳ ለማደግ፣ ነዋሪዋን ሁኔታ ለማሻሻልና ባለሐብቶችን ለመሳብ የምትችለው ደብረብርሃን ካሁን በፊት የፖለቲካ ጫና ነበረባት፡፡ ወደፊት ይኖርባታል ወይ የሚለውን ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል፡፡ ከበፊቱ የተሻሉ ሁኔታዎችን ያየንባት ከተማ ሁለገብ ልማትና እድገት ሊኖራትና ነዋሪዋም ሊጠቀም ይገባዋል፡፡ ሆቴልና ህንጻ ሲሰራ እያየ ሊገባበት የማይችል የደብረብርሃን ነዋሪ ሲኖር ሊያሳስብ ይገባል፡፡ የኢኮኖሚው ተጠቃሚ መሆን የሚችልበት መርሃግብር መቀረጽ አለበት፡፡ ደብረብርሃን አድጋለችም አላደገችም የሚለው ሃሳብ እንደሚጠየቀው ሰው፣ እንደየዘርፉና ሁኔታው፣ እንደየሰፈሩና አውዱ ይወሰናል፡፡ አድጋለችም አላደገችም የሚሉትን ሃሳቦች ማንሳት እንችላለን፡፡ ጆርጅ ኦርዌል ‹ደብል ቲንክ› እንደሚለው እያወቅን ሁለቱንም እንድናስተናግድ የተገደድን ነዋሪዎች ነን፡፡ አድጋለች የሚለውን የፖለቲካ መዋቅሩ ሲያራግብ ምንም ያላየው ህዝብ ደግሞ አላደገችም በማለት ይጮሃል፡፡ ሁለቱም ሃሳቦች ግን በህዝብ አእምሮ አሉ፡፡ ተቃርኖውን እያወቅንም አንናገረውም፡፡ ብንናገርም ሰው ከጉዳዩ አይጽፈውም፡፡

ሲጠቃለል በቅርቡ በነበረው የወያኔ ወረራ ለመጠቃት ያሳጫት አድጋለች የሚለው ወሬ ይሆን? ሌላስ ጠላት ይገዛላት ይሆን? የእውነት እንድታድግስ ምን ይደረግ?

 



 







3 አስተያየቶች:

  1. "ደብረ ብርሀን በእሾህ መሀል የተከበበች ውብ ፅጌረዳ ናት"
    ርዕስ- አዎ ደብረ ብርሀን አድጋለች!

    (ፕሮፌሰር ተክሌ አበባው)
    (የግል ዕይታ)
    ልጅ ሆነን ታሪክ መምህራችን ቲቸር መብራቴ "ሮም በአንዴ አልተገነባችም" የሚሉንን ርዕስ መጠቀም ሀሳቤን ይገልፅልኛል።
    ደብረ ብርሀን ትላንትና (በ1995 ዓ.ም)

    ዩኒቨርስቲ:ኢንደስትሪዎች:የተማሩ ሰዎች:ባለሀብቶች አልነበሯትም።
    1 ሀይስኩልና 1 ኢለመንተሪ ት/ቤት ብቻ ነበራት።ከአንድ ትንሽ የገጠር ከተማ አሁንም ድሮም እንደነበሩትና እንደቀጠሉት ከተማ ነበረች።

    ደብረ ብርሀን ዛሬ (2014)
    600 ዓመት በላይ ያስቆጠረችው ከተማ በ 20 ዓመት ውስጥ ሮም ካደገችበት ፍጥነት አድጋለች። የማወዳድረው 600 እና 20 ዓመትን ነው።
    1. አንድ የነበረው ብርድልብስ ፋብሪካ 200 ደርሷል።
    2.ት/ቤቶች በየአካባቢው ተከፍተዋል።
    3.የተማሩ ሰዎችና ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውንና ዕውቀታቸውን ይዘው ተሰልፈውባታል።የቀናቸው የሙያ ልምዳቸውንና እያካፈሉና እየበለፀጉ ነው።
    4.ከተማዋ በአማላይ ኢንቨስትመንቶች:ኮከብ ሆቴሎች:አዳሪ ት/ቤቶች ወዘተ እየተገነቡላት ነው።(ሮም በአንድ ቀን....አትርሱ)
    ደብረ ብርሀን ከተስፋም በላይ የሚጨበጥ ጎልድ የሆኑ ነገሮች ይዛለች። ወደኋላ እንዳይመለስ ጠንክሮ ማስጠበቅ ይገባል።
    አንድ አባት የክርስቲያን ልጆች ስለሆነን በእምነትና በተስፋ እናምናለን ደብረ ብርሀንና ጫጫ ይገናኛሉ። 1 ክንድ መሬት ወደፊት ብርቅ ይሆናል ያሉት ትንቢት እየተፈፀመ ይመስለኛል።
    እናም ደብረ ብርሀን አድጋለች። "እድገት ጉዞ ነው"። የዛሬ መቶ አመትም ብትጠይቀኝ አድጋለች ነው። የምልህ መሠረቷን ጥላ በእጇ ጨብጣ ይዛለችና።

    ውቧ ፅጌረዳ እንደ እሾህ አጥረው የያዟት ችግሮች

    ደብረ ብርሀንና ተግዳሮቶቿ
    ወጣቱና ችግሮቹ
    በአብዛኛው ወጣቱ በእውቀት:በንባብ የበለፀገ አለመሆን የመጣለትን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ከመለወጥ በጫት:በሺሻና አሉባልታ ወሬ ተጠምዶ ጊዜውን ማሳለፍ ካገኘው መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ከማለፍ ይልቅ መሪዎችና ጠንክረው የሚሠሩ ሰዎችን እንደ ባልቴት ማብጠልጠል...ደብረ ብርሀን ለተወላጅ አትሆንም ለመጤ ነው የሚል የጅል ተረት እየተረተ አረቄውን በሀይላንድ የሚቀነድለው ወጣት ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ከሁሉም በላይ እኔ ፀሀፊውን የሚያመኝ ሁሉም ተቺ : ሰዎችና መንግስትን ማብጠልጠል መፍትሄ ሀሳብ ይዞ ከመቅረብ የሚሰሩትን ሰዎች ማሸማቀቅ በብዛት ይስተዋላል።

    ሌላው ከተማዋ ውስጥ በመጣው ዕድል እየተጠቀሙ ያሉት ከሌላ አካባቢ ስራና ገንዘብ ጠምቷቸው የመጡ ወጣቶች ናቸው። በጋራዥ ሂድ: በከተማ ታክሲ ሂድ ከዞኑ ወረዳዎች ከመጡት ይልቅ አገር አቋርጠው የመጡ (ናዝሬት:ጎንደር:ጎጃም የሚመጡት ይበልጣሉ። መፅሀፍ አዟሪ እንኳን ከየት እንደሚመጡ ይታወቃል)
    በነገራችን ላይ ከሌላ አካባቢ መጥተው የሚለወጡትን እየተቃወምን አይደለም። እያደነቅን እንጅ ...ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል ነው።

    ፕላን አልባ ከተማ
    የከተማዋ እድገቷን የሚመጥን መስፍፍት ያላት ፕላን ያላት አይመስለኝም። የቢራ ፍብሪኮቿ ከአስፓልት ጋር ፍክክር ይዘው ፊት ለፊት ቢራ የሚሸጡ ይመስላሉ። ነዋሪው ደሞ15km ተጉዞ መኖሪያ ቤት እንዲያገኝ (አታክልት ተልኳል)።
    ፕላን አልባነቷ መገለጫ የባጃጅ ስምሪትና የመንገዶቿ ጥበት ነገ ለእድገቷ ማነቆ መሆናቸው አይቀርም።

    መሪዎቿና ባለሙያዎቿ
    ከተማዋን መምራት ያለበት ከትልቅ ከተማ ወይም ከውጪ ሀገር የመጣ መሪ ቢሆን ብዙ ተሞክሮና ዘመናዊነትን የተላበሰ ልምድ ለከተማው ያካፍል ነበር። አለመታደል ሆኖ መሪዎቿ ከራሷ ከከተማዋ ካነሱ መንደሮች መጥተው የከተማ መሪነትን የሚማሩት እዚህ ነው። መሪ ስል የከተማም የቀበሌ መሪዎቿን ነው። ከተማ ያለ እውቀት አይመራም። አይደለም ከተማ ሰልፍ ላይ እንኳን ከፊት ሆኖ ለመምራት እውቀት ይፈልጋል።
    ባለሙያዎቿም ሁሉም ማለት ባንችልም አንዳንዶች ለከተማዋ ለውጥና ዕድገት ከማሰብ በሙስና ገንዘብ የሚያገኙበት ነው የሚያስጨንቃቸው። አንድ ደንብ አስከባሪ ደንብ አስከብሮ ከሚያገኘው የአዕምሮ ደስታ የሚቀበለው 200 ብር የሚያረካው ነው ያለው። በባለሙያዎች ዘንድ የሚታየው ችግር ሙያን አለማክበር:ለማወቅ አለመጣር:ፍሬሽነት:ምን ቸገረኝነት ጎልተው ይታየሉ።
    መሪነትና ብቃት ያለው ባለሙያ በመንግስት መስሪያ ቤት ያለመኖር ለቅሬታና ለፍትህ መጓደል ይወስዳታል። እንኳን ሰፍታ አሁንም አገልግሎቶቿ ያሳፍራሉ።

    (እንደ መውጫ) በውቧ ፅጌረዳዋ የተመሠለችው ደብረ ብርሀን አድጋለች የማንክደው ሀቅ ነው። በዙሪያዋ ታጥረው ያሉ ተግዳሮቶች(እሾህ) በጥበብ መንቀል ያስፈልጋል። ለውጥ መቼም አልጋ በአልጋ ሆኖ አያውቅም።
    ሮምም በአንዴ አልተገነባችምና

    በቀጣይ ለችግሮቿ የመፍትሄ ሀሳብ:ስለሴራ ፖለቲካና እንዴት ከአይን ማውጣት እንችላለን? በሚሉና ስለ ደብረ ብርሀን በአፈታሪክም በመፅሀፍትም የተነገሩ መልካም ትንቢቶችና ተስፍዎችን እንጨዋወታለን።
    ሻሎም!!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. ይህ ልጥፍ በጸኃፊው አስተዳዳሪው ተወግዷል።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
    ምላሾች
    1. በጥሩ ሁኔታ የተብራራና ስፋት ያለው አስተያየት ነው፡፡ አመሰግናለሁ ፕሮፌሰር፡፡

      ሰርዝ

Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school.

  Z.A. They warn Oromo parents to advise their kids to avoid interacting with Amhara kids at school. The Shenes said they wanted to aven...