2022 ጃንዋሪ 1, ቅዳሜ

‹‹ወንድ ብሆን ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር›› የምትለው ተማሪዬ

 መዘምር ግርማ

mezemirgirma@gmail.com




አንድ ቀን እንግሊዝኛ ሳስተምር መጽሐፉ ስለ ሥርዓተፆታ የሚያነሳበት ክፍል ላይ ደረስን፡፡ በመጽሐፉ ላይ ስለ ሥርዓተፆታ እያነሳሳ አስተሳሰባችንን የሚመረምር ክፍል አለ፡፡ በዚያም ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሴቶች እንዳይመቹ ተደርገው የተቀረጹ ነገሮች መኖራቸውን እንገነዘባለን፡፡ በአስተዳደር ሴቶች ትልቅ ደረጃ እንዳይደርሱ የተጠመዱ ፈንጂዎች አሉ፡፡ ምናልባትም እነዚያን ፈንጂዎች ለማምከን የሚፈቅድ ሥርዓት ስለሌለ በላያቸው ተንደባሎ ህይወትን መስዋዕት ማድረግና ለወደፊቱ ትውልድ መንገድ መጥረግ ያስፈልግ ይሆናል፡፡ በሥርዓት የታጠረን ነገር ለማስተካከል ብዙ ጥረት እንደሚጠይቅ ይታወቃል፡፡ የዉጪ እርዳታና ብድር ለማግኘት ሲባል እንደተሟላ ተደርጎ የሚለፈፍለት የሴቶችና ልጃገረዶች መብት አሁንም ለመሻሻሉ ብዙ ጥርጣሬ አለ፡፡ እንዲያውም ወደ እርግጠኝነት የሚያመዝን ነገር አለመሻሻሉን ማመልከት ይቻላል፡፡ በቤቱ ሴትን ሲበድል የሚኖር ሰው መስሪያ ቤት ላይ እንዴት የሴትን መብት የሚያከብር ይሆናል! መጽሐፉ በተለያዩ ጥያቄዎች ስለ ሴቶች መብት ያለንን ግንዛቤ ይመረምራል፡፡ መጀመሪያ በግላችሁ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ጻፉ ይላል፡፡ መልሶቹ ከተጻፉ በኋላ በጥንድ በጥንድ እየሆናችሁ መልሶቻችሁን አስተያዩ፤ አወያዩም ይላል፡፡ ይህም ከተደረገ በኋላ ክፍሉ በሙሉ በመምህሩ አወያይነት እንዲነጋገርበት ይመክራል፡፡ ይህ ሲደረግ ጊዜ ካለ ወሬ ወሬን እያነሳው ከመጽሐፉ ዉጪ የሆኑ ነገሮችን ማነሳሳት ያለ ነው፡፡ የነገሩ ተንኳሽ ማን መሆኑን ባላውቅም ከተማሪዎች በመጡ ጥያቄዎች ላይ ስንወያይ እኔ አንድ ጥያቄ አነሳሁ፡፡ ይኸውም ‹‹ከሴቶቹ ውስጥ ወንድ ብሆን ኖሮ የየሚል አለ?›› የሚል ነበር፡፡ አንዲት ተማሪም እጇን አውጥታ መልስ ሰጠች፡፡ መልሷም አዎንታ ነበር፡፡  ‹‹ወንድ ብሆን ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር›› ነበር ያለችው፡፡ ልጅቱ ከሁኔታዋ ስመለከት ከገጠር የመጣች ናት፡፡ በተለምዶ ለሴቶች ከባድ የሚባል ትምህርት ክፍል የተመደበች ናት፡፡ ምን ይታወቃል የገጠማት ነገር፡፡ ያለፈችበትን የግል ህይወቷን ማን ያውቃል፡፡ ይህች ልጅ ወንድ ለመሆን መመኘቷ ብቻ ነው በእጄ ላይ ያለው ነገር፡፡ ፈጽሞ የማይቻል የሆነውን ነገር ተመኘች፡፡ ይህን ምኞቷን ለማሳካት የሚኬድባቸውን ነገሮች ስናስብ ፆታ ማስቀየርን ልናስበው እንችላለን፡፡ እሱም በቅርብ ጊዜ የመጣና ምናልባትም በልጅቱ አእምሮ ያልነበረ ነው፡፡ በእርግጥ እንደ ሴት ተፈጥረው እንደ ወንድ የሚኖሩ እንዳሉ ይነገራል፡፡ ይህም በአለባበስ፣ የወንድን ሁኔታ በማስመሰልና ከወንዶች ጋር በመዋልና እነሱ በሚያዘወትሯቸው ቦታዎች በማዘውተር ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ራቅ ያሉ ምሳሌዎች ልናስብ የቻልነው በኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች መብት ይከበር ዘንድ ብዙ ዘመናትን መጠበቅ ያስፈልግ ስለመሰለኝ ነው፡፡ ወንዶች የሚደሰቱበት ብዙ መብት ለሴቶች ተነፍጎ ላየችና የዚያም ሰለባ ለሆነች ልጅ ወንድ ብሆን ብሎ መመኘት ላያስገርም ይችላል፡፡ በምን ትዝ አለኝ ይህ ነገር ብዬ ስጠይቅ አንድ ነገር ነው ያስታወሰኝ፡፡  ከባድ ነገር ነው፡፡ ፆታን እንደመቀየር ከባድ የሆነ ነገር ስለሆነ በቀጣይ አንቀጽ እንየው፡፡

እንደዚህ ነው፡፡ በቅርቡ አንድ ጀርመን አገር የሚኖር አበሻ ስለ ጀርመኖች ይነግረኛል፡፡ በሚናገረውም ነገር ሁሉ የእነርሱን ከችግር የማገገም አቅምና ጽናት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሸጋገር ታሪክ፣ ለአገራቸው ያላቸውን ትጋት ሁሉ ከብዙ አብነቶች ጋር ነገረኝ፡፡ በአጠቃላይ ‹‹አገራቸውን በሚገባ ሰርተዋል›› በሚል ደምድሞታል፡፡ ሁሉ ነገር ስርዓት አለው፡፡ የሃብታምና ደሃን ልዩነት ማጥፋት ችለዋል፡፡ ሰዎች ጂንስ ሱሪና ቲሸርት ይለባሳሉ፡፡ ሃብታምና ደሃውን መለየት አይቻልም፡፡ ሁሉም ሰው ቤት ተመሳሳይ የቤት ዕቃ አለ፡፡ ለህይወት አስፈላጊው ነገር ተሟልቷል፡፡ ይህ ኢኮኖሚውን የማስተካከል ነገር ሰላምንና መረጋጋትን ሰጥቷቸዋል፡፡ ሌላው ጥብቅ የሆነ ህግ አላቸው፡፡ ይኸውም በህግ ስለሚመሩ አንዱ ሌላውን ጫፉን አይነካም፡፡ ለምሳሌ ቤት በሩ ሳይዘጋ መተኛት የተለመደ ነው፡፡ ይህን ያህል መተማመን አለ፡፡ ‹‹ጀርመን ሌባ የለም፡፡ ምን ሊዘርፍ ነው! ቴሌቪዥን? ፍሪጅ? እቤቱ አለው አይደል እንዴ? እንዴትስ ይወስደዋል? ሊያስበውም አይችልም›› ነበር ያለኝ ወዳጄ፡፡ መኪና መንገድ ላይ ሰው ቢገጭ አያልፈውም፡፡ ቆሞ ለፖሊስ ደውሎ ያጠፋውን ጥፋት ይናገራል፡፡ ሌላ መኪናም ገጭቶ ይሆናል፡፡ ያንን አሳውቆ ቅጣቱን ይቀበላል፡፡ ቢቸኩል እንኳን አድራሻውን ትቶ ይሄዳል፡፡ ምንም ሰው ባያየውም ያንን ማድረጉ አይቀርም፡፡ ህሊናው እንዳይወቅሰው ከመስጋት ባለፈ የሆነ ቦታ ሰው ተደብቆ ቢያየው እንደማይደብቅለትና ለህግ ተገዢ በመሆኑ ሊጠቁምበት እንደሚችል በትክክል ያውቃል፡፡

ሌላው ለበዓል ምግብ በጣም ይረክሳል፡፡ የተትረፈረፈ የምግብ አቅርቦት አለ፡፡ ከየትም ከየትም ብለው የምግብ አቅርቦት በሽ በሽ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ መስሪያ ቤቶች ለበዓሉ መዋያ ጠቀም ያለ ቦነስ ይሰጣሉ፡፡ አገራቸውን መስራታቸውን የሚያሳዩ ብዙ አብነቶች ቢኖሩም እነዚህን ከጠቃቀስን ይበቃል፡፡ የመሰረተ ልማቱን፣ የዉኃውን፣ የኤሌክትሪኩን ሁሉ ብንጠቅሰው አያልቅም፡፡ አገራቸውን በመጠበቅ ረገድ የሚታረስ መሬት እንዳይበዛ በማድረግ ከኢትዮጵያ ሦስት እጥፍ ያነሰ መሬት ይዘው ህዝባቸው ግን ከእኛ ተቀራራቢ ነው፡፡ የዉጪ ዜጋን ብዙም የማያቀርብ ፖሊሲ አላቸው፡፡ ዜግነት ለማግኘት ከሚከብድባቸው አገሮች አንዷ ጀርመን ነች፡፡ የዉጪ ዜጋ ቢኖርም ገንዘቡን ይዞ የማይወጣበት መንገድ ተመቻችቷል፡፡ ጀርመኖች ሃብታሞችና ተመችቷቸው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ጀርመናዊነታቸውን እንደሚወዱ አያጠራጥርም፡፡ ሌላም ከቤልጂየም የመጣ ሰው በ130 ዩሮ ወር ሙሉ የፈለገውን ምግብ አብስሎ እንደሚበላ ነግሮኛል፡፡ መታደል ነው መቼስ!

ያው መቼም የሰውን አገር ሁኔታ ስንሰማ የኛስ ማለታችን አይቀርም፡፡ ‹‹ተስፋዬ፣ እኔ እኮ ስጋ የሚበሉትን እንጂ የሚያዩትን አላልኩም›› እንዳለው ኮሜዲያን ተስፋዬ ሕይወትን የምንኖራት እንጂ የምናያት አይደለንም ለማለት ያስደፍራል የኢትዮጵያ ህይወት፡፡ ለጀርመኖች ገነት ተደርጋ የተቀረጸችው ጀርመን ለሌሎች ፈታኝ ህይወትን እንደምታኖር ቢታወቅም የእኛዋ ተቃርኖ ግን ይገርማል፡፡ ምርጥ ምርጡን ለፈረንጅ በሚል ፖሊሲ የምትመራ ይመስላል፡፡ ምርጥ ምርጡ ሁሉ ወደ ዉጪ የሚላክ ነው፡፡ የዳቦ ስሙ ባይሆን ኤክስፖርት ስታንዳርድ ይባላል፡፡ በየቦታው ለፈረንጅ ምርጥ ምርጡ ነው በአገር ቤትም፡፡ በሆቴል፣ በሪዞርት፣ በጉብኝት ቦታ ሁሉ ምርጥ ምርጡ ይቀርብላቸዋል፡፡ ከእነርሱ ቀጥሎ ማናቸውም የዉጪ ዜጋ፣ ከዚያም ዲያስፖራ ይከተላል፡፡ ያው ገንዘቡና የዉጪ ንክኪው ነው ተፈላጊው፡፡

‹‹እንዳትቆይ አልደላሃት

እንዳትሄድ በኔ አሰርካት

ለኔ ደግ አባት ነህ

ለሷ ክፉ ባሏ›› እንዳለችው ዘፋኝ የኢትዮጵያ ገዥዎች ዜጎቻቸውን እንደዚያ ክፉ ባል በጉልበት ይዘዋል፡፡ እንዴት ቢባል በአገር ውስጥ ለመኖር የተመቻቸ ነገር የለም፡፡ አንደኛ በተለያዩ ምክንያቶች መድሎ ይኖራል፡፡ ሰው ይገፋል፤ አይበረታታም፡፡ እሺ ልውጣ ብሎ ቢያስብ እንኳን እንዳይወጣና እዚሁ ባሪያ ሆኖ እንዲቀር የተመቻቸ ሁኔታ ነው አፍጥጦ የሚይዘው፡፡ የሰው ኃይሉ እንዳይሄድባቸው የተቻለቸውን ያደርጋሉ፡፡ ለራሳቸው የሚጠቅም፣ ኢንቬስተር ለሚባል መሬትና ሃብት ለሚሰጠው የዉጪ ዜጋ በቅናሽ ደሞዝ ርካሽ ጉልበት እየተባለ በወር በ700 ብር ደምወዝ እንዲቀጠር ያደርጉታል፡፡ የውጪ ፈተና ተፈትኖ አልፎ እንዳይሄድ እንግሊዝኛ አይችልም፤ ሂሳብ አይችልም፡፡ የዉጪ ነገር ሁሉ ተዘጋግቶበታል፡፡ ዶላር ነክቶ አያውቅም፡፡ መኪና የመግዛት አቅም ቢያጎለብትም ቀረጡ ከፍተኛ ነው፡፡ ፓስፖርትና ቪዛው ትስርስር ያለ ይሆንበታል፡፡ የቻለው ድንበር እያቋረጠ በበረሃና በውቅያኖስ በህገወጥ መንገድ ለመሄድ ይሞክራል፡፡ ከስንት አንዱ በስንት ውጣውረድ ህይወቱን ለአደጋ ጥሎ ካሰበበት ቦታ ይደርሳል፡፡ ለምን ትሄዳለህ ሲባል ከዚህ የማይሻል የለም ይላችኋል፡፡ ድመትና ውሻህን ቤት ዘግተህ ብትገርፋቸው አንተኑ ይበሉሃል እንደሚባለው መሪዎቹን ቢበላም ሌላ መሪ ይፈጠርበታል፡፡ እየተባላም ይራባል፡፡ አመሉ ግን አይለወጥም፡፡ በንግድ ቦታ የቁጥጥር ስርዓት ስለሌለ ሁሉ ነገር ውድ ነው፡፡ ያዋጣኛል ብሎ በቅናሽ ለመሸጥ የሚፈልግ ነጋዴ ቢኖር አይበረታታም፡፡ የስራ ውድድር መንፈስ ስለሌለ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ይዞ መጥቶ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ቢሞክርም ፖሊሲው፣ አሰራሩ፣ ህጉ ስለማያበረታታው ከቻለ ስራፈጠራ ወደሚበራታበት አገር ይሄዳል፡፡ ያለዚያ መሳቂያ ሆኖ እዚሁ ይቀራል፡፡ ብዙ መሰናክል አልፎ በሰው አገር ለስኬት የደረሰና የበለጸገ አበሻ ቢኖር እንኳን መልኩ ያው አበሻ ነው፡፡ ነብር ዥንጉርጉነቱን ኢትዮጵያዊ መልኩን አይለቅም እንደተባለው እዚያ ሄዶ ሁልጊዜ አገርህ የት ነው እየተባለ ነው የሚኖረው፡፡ ስኬቱ እውነተኛ ስኬት አይሆንለትም፡፡ ኢትዮጵያ ተወልዶ መሞት ያለበት ይመስል ዘረኝነትና ባይተዋርነት ወደ አገሩ መልሶ እንዲያይ ያስገድዱታል፡፡ መጥቶም የተሻለ ነገር ላስተዋውቅ ቢል ከስንት አንዱ ነው የሚቀናው፡፡ ወይ የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ ይሆናል፡፡ ሙስናውና ጉቦው ያማርረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ባህርዳር ሲሄድ የአውሮፕላን ቲኬቱ ዋጋ ይገርመዋል፡፡ በኬኒያ ኤርዌይስ ናይሮቢ ደርሶመልስ ስድስት ሺ ብር የማይሞላው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህን ያህል ሲወደድ ለምን ይላል፡፡ ወይንም የዉጪ አየር መንገዶች ገብተው ተፎካክረው ኑሮ እንዲረክስ አይደረግ! ለስልክ በወር በሺዎች ብር ያወጣል፡፡ ከጃፓን አንድ ሺ እጥፍ ክፍያ እንዳለ ያያል፡፡ የዓለምን የስልጠኔና የሳይንስ ትሩፋት ኢትዮጵያውያንን የከለከሏቸው የራሳቸው ልሂቃን፣ ባለስልጣናት፣ የተማሩ የአገራቸው ልጆች፣ ከውጪ ማምጣት ሲኖርባቸው ያላመጡና የደበቁ ዕድሉን ያገኙና አገሪቱ በሌላት ገንዘብ ስታስተምራቸው ሲቀናጡ ኖረው የሞቱ ሰዎች ወዘተ መሆናቸውን ያያል፡፡ መጥፎ ልማድ ያለው ወገንና ዘመድ ይከዳዋል፡፡ አዙሪቱ ይቀጥላል፡፡ የቢሊየን ብሩ ጥያቄ ኢትዮጵያውያን አስተሳሰባችንን የምናሻሽለው መቼ ነው የሚል ነው! ህዝቡ ከጠገበ አይገዛልንም የሚል ሃሳብ መቆም አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ልቶ ይጥገብልኝ በሚል የግብርና አብዮት እንደ ህንድ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ቁልፍ ቦታዎችን የያዙ ሰዎች ይህንና መሰል የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽል ነገር ካልሰሩ ቦታውን መልቀቅ አለባቸው፡፡ ‹‹ያቺ ልጅ ወንድ ብሆን ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር›› ያለችው ኢትዮጵያውያን አስተሳሰባችንን ስላልቀየርንና ስላላሻሻልን ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያን ሲዖል የምናደርጋት በሌላ ሳይሆን በአስተሳሰባችንና በክፋትና ምቀኝነት አባዜያችን ነው፡፡ ይህን ግልጽ አድርገን መነጋገር አለብን፡፡ መልካምነት ቢኖረንም ክፋትና ምቀኝነታችንም የውይይት ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ልጅቱ ያን አለች፡፡ ይህን ችግር ሲያይ ደግሞ ‹‹ዘሬን ልቀይር እንዴ?›› የሚል ኢትዮጵያዊ አይጠፋም፡፡ ግን አይቻልም!  ከማይቻለው ዘርን የመቀየር ተግባር  በመለስ ያሉትን ነገሮች እንድንተገብር መድረኩ ይመቻች፡፡ እባካችሁ!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...