ቅዳሜ 1 ጃንዋሪ 2022

የአፍሪካን ቤተመጻሕፍት እያጠፉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

 

 

በመዘምር ግርማ

mezemirgirma@gmail.com

 






ከአንድ የዳር አገር የገጠር ወረዳ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ከቻሉ ጥቂት ወጣቶች አንዱ የነበረና አሁን የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነ ወዳጄ ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ቤተመጻሕፍትን ጉዳይ የነገረኝ፡፡ ጫካ ሄዶ ዛፍ ስር አንብቦ ነው ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የቻለው፡፡ እዚያ ጫካ ዛፍ ስር ሲያነብ ወፎች ደብተሩንና መጽሐፉን የሚያበላሹበት ጊዜ ነበር፡፡ ራሱም ላይ ሊጥሉበት ይችላሉ፡፡ በዚያ ለህዝቡ እንደ መጸዳጃ በሚያገለግል ጫካ ንጹህ ቦታ ፈልጎ ነበር ሊያነብ የሚችለው፡፡ ታዲያ ይህንን የሚያዩ ሌሎች ተማሪዎች ይስቁበት ነበር፡፡ እነርሱ ሲወድቁ እሱ አልፎ ዲግሪውን ለመያዝ በቃ፡፡ አሁንም በእውቀት ዓለም እንደቀጠለ አለ፡፡ ለሌሎችም የእውቀትን ብርሃን ያበራል፡፡ ይህን የዛፍ ስር ማንበቢያ ስፍራ የመረጠው በጥላው ምክንያት ነው፡፡ ፀሐይ ላይ ካነበበ ደግሞ ወረቀቱ ስለሚያንጸባርቅ ዓይኑን ያመዋል፡፡ ይህን የተመረጠ ስፍራ የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ሲሉ ይጠሩታል፡፡ አፍሪካውያን ቢያንስ ዛፍ ስለሚኖራቸው እሱ ስር የተገኘችውን መጽሐፍ ያነባሉ፡፡ ያቺ መጽሐፍ ለአምስት ተማሪ አንድ ደርሳም ከሆነ በፈረቃ ስለምትነበብ የተመደበችለት ሰዓት ሳያልቅ ያነባል፡፡ ከዚያም ሌላኛው ልጅ የቤት ስራውን መስራት ስላለበት ወይንም ለፈተና ለመዘጋጀት መጥቶ ይወስድበታል፡፡ ከዚያም ደብተሩን ሊያጠና ወይም ሊያሰላስል ይችላል፡፡ ይህች ስፍራ አስነባቢ ባይኖራትም፣ መደርደሪያ ባይከባትም፣ ዘበኛ ባታቆምም፣ መታወቂያ ባትጠይቅም ቤተመጻሕፍት ነች፡፡ ከትውልድ ትውልድ አስነብባለች፡፡ ልክ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቤተመጻሕፍት ሰርኩሌሽን ክፍል በሰዓት በወረፋ ታስነብባለች፡፡ አፍሪካ የድህነት ምሳሌ ስለሆነች ይህችን ባዶ ቦታ የዛፍ ጥግ የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት አሏት፡፡ አፍሪካ ውስጥ ብዙ የእርሷን ዓይነት አሉ፡፡ ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ብዙ ትውልዶችንም አፍርተዋል፡፡ ከአገር መሪ እስከ አትሌት፣ ከፕሮፌሰር እስከ ዘመናዊ አርሶአደር፣ ከመምህር እስከ ወታደር፣ ከሐኪም እስከ ኢማም፣ ከቄስ እስከ መሐንዲስ ብዙዎች አንብበው ለአገራቸው መስጠት ያለባቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡ ሕይወታቸውን አቃንተዋል፡፡ እነርሱ ይርሱት ወይም ያስታውሱት ባይታወቅም ታሪክ ግን መዝግቦ ይዞታል፡፡ አሁን ጫካዎች እየተመናመኑ በመጡበት በዚህ ዘመን የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት አገልግሎት እየተመናመነ ሳይሄድ አይቀርም፡፡ እኔ የግሌን ለማጋራት ያህል ሳሲት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ተጠቃሚ ነበርኩ፡፡ በትምህርት ቤታችን ቤተመጻሕፍት ወይም ላይብረሪ የሚባል የተከፈተው የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከእኔ በፊት ያለው ትውልድ የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ተጠቃሚ ነበር ማለት ነው፡፡ በገጠር እንደሚታወቀው እቤት ማንበብ አይበረታታም፡፡ ቤተሰብ ስራ የፈታችሁ ስለሚመስለው ‹‹ትምህርት ቤት ዋልክበት፤ ደግሞ አሁንም! ሂድ ስራ አትሰራም እንዴ!›› በማለት ይቆጣሉ፡፡ ደብረብርሃን ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መጥቼም ግማሽ ቀን ትምህርት ቤት፣ ግማሽ ቀን የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት አነብ ነበር፡፡ ከከተማው ዳር ካሉ ዛፎች ውስጥ ገብቼ አንብቤ እመጣለሁ፡፡ ጓደኞቼም መሄድ ከፈለጉ እንሄዳለን፡፡ አንድ ቀን ወደዚሁ ቤተመጻሕፍት ሄጄ ስመጣ 12ኛ ክፍል የክፍሌ ልጅ የሆነችን ልጅ አገኘኋት፡፡ ከየት እየመጣሁ እንደሆነ ጠየቀችኝ፡፡ እኔም ጫካ ውስጥ ሳነብ ቆይቼ መምጣቴ እንደሆነ ነገርኳት፡፡ ‹‹አንቺስ ጫካ ውስጥ አታነቢም እንዴ?›› ስል ጠየኳት፡፡ ‹‹ባህላችንን ታውቀው የለ! ቤተሰብ መች ይፈቅድልኛል!›› አለችኝ፡፡ በወቅቱ የመሰለኝ ሴት ልጅ ብዙ የቤት ውስጥ ስራ ስለምትታዘዝ ለጥናት ጊዜ አይሰጣትም የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ቆይቼ ሳስበው ጫካ ውስጥ ለጥቃት ትጋለጣለች በሚል ስጋት ሊሆን እንደሚችል ገባኝ፡፡ ከሁኔታው እንደተረዳሁትና በኋላም እንዳጣራሁት ሴቶች በአፍሪካ ቤተመጻሕፍት አያነቡም፡፡ ለውጤታቸው ዝቅ ማለትም ይህ አለማንበባቸው የራሱ ሚና ይኖረዋል፡፡  



ጋዜጠኞች የአንድን ነገር አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታ ለማሳየት ሲፈልጉ አንድን ሰው ጠይቀው የሱን ህይወት ያሳዩናል፡፡ ያንን ሰውም የሁሉም ወኪል አድርገው ያቀርቡታል፡፡ ያም ሰው እንደ ወካይ ይቆጠራል፡፡ ከላይ የተጠቀሰውና ስለአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ የነገረኝ ወዳጄ ብዙዎችን ይወክላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ጨዋታን ጨዋታ እየነሳው ነገሩን እንዳላብዛዛው ሰብሰብ ላድርገው፡፡  በቀጣዩ አንቀጽ እንገናኝ፡፡



ሳሲት አንድ ዘመድ ነበረችን፡፡ ይህች ዘመዳችን በጣም ተጫዋች ነች፡፡ ለአጎቴ ሰርግ ጥሪ ሲደረግ ከሳሲት ልማድ ወጣ ያለ ዘምአመጣሽ አጠራር ነበር የተደረገው፡፡ ይኸውም በታተመ ወረቀት ነበር፡፡ ለወትሮው ቢሆን ከተማዋ ትንሽ ስለሆነችና ሁሉም ሰው ስለሚተዋወቅ ድግስ እንዳለ ከተሰማ መሄድ ብቻ ነው፡፡ ወቀሳ ካለ ለምን አልመጣህም ተብሎ ነው፡፡ በስህተት ያ ወረቀት ሳይደርሳት የቀረችው ዘመዳችን በወረቀት ነው ጥሪው የሚባል ስትሰማ ቀረች፡፡ ጨክናም አልጨከነች ግን በሦስተኛው ቀን መጣች፡፡ ለጨዋታውና ለጭፈራው ሳይሆን ለወቀሳ፡፡ ‹‹ለምን አልተጠራሁም!›› አለች፡፡ ይህንንም ያለችው አጎቴ በማግባቱ ስለምትደሰትና አኩርፋ መቅረት ስለማትችል ነው፡፡ ላልተጠራሁበት ሰርግ ድግስ አልሄድም፤ ሄጄ ግን መርቄው እመጣለሁ ነው ሃሳቧ፡፡ እና እኔም ጥሪ በሚኖርበት በዛሬው የአብርሆት ቤተመጻሕፍት ምረቃ ለምን አልተጠራሁም ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ቢሆንም እስኪ ባለሁበት ለመመረቅ ስለምሻ በዚህ ጽሑፍ አበርክቻለሁ፡፡

ቅዳሜ ታህሳስ 23፣ 2014 ዓ.ም. የተመረቀው ይህ ቤተመጻሕፍት ስለሚሰጣቸው ዝርዝር አገልግሎቶች፣ ስለ መጠኑና አጠቃላይ ሁኔታው በዋልታ ኢንፎርሜሽን የተለቀቀውን ይህን ዜና እናንብብ፡-

 ‹‹የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ዛሬ ይመረቃል

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ)

በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባው የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ዛሬ ይመረቃል፡፡

በአዲስ አበባ 4 ኪሎ በዘመናዊ መልኩ የተገነባው ቤተ መጽሐፍት የማንበብ ባህልን ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመላክቷል።

ቤተ መጽሐፍቱ በዛሬው እለት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የሚመረቅ ሲሆን በአንድ ጊዜ 2 ሺሕ በላይ ተጠቃሚዎችን ማስተናገድ እንደሚችልና በውስጡ ከማንበቢያ ስፍራ በተጨማሪ 8 የመጽሐፍ መሸጫ ሱቆች፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ካፍቴሪያ፣ የህፃናት ማንበቢያ ስፍራዎችን ተካተዋል።

ከዚህ ባለፈም የተለየ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች የሚያነቡበት የመጽሐፍ ክፍል እንዳለው የቤተ መጽሐፍቱ ፕሮጀክት ማናጀር ታሪኩ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ቤተ መፃህፍቱ የተሟላ የመኪና ማቆሚያ እንዳለውም ተገልጿል፡፡››

 

ይህንን ዜና ቀረብ ብለን ለመመርመር እንሞክር፡፡ ቤተመጻሕፍቱ ስሙ አብርሆት ነው፡፡ 17ኛውና በ18ኛው ክፍለዘመን በአውሮፓ የተነሳውን የአብርሆትን ዘመን የስያሜው መነሻ ያደረገው ቤተመጻሕፍቱ በጥበብ፣ በፍልስፍናና በፖለቲካ አብዮታዊ እድገቶች የተመዘገቡበትን ዘመን ያስታውሰናል፡፡ እንደዚያም ዘመን እውቀት፣ ነጻነትና ደስታንም ለኢትዮጵያውያን ለማድረስ በር ይከፍታል ብለን እናስባለን፡፡

በዜናው በአዲስ አበባ የሚለውም ቁልፍ ቃል ነው፡፡ ይህ ጅምር በአዲስ አበባ በብዙ ቦታዎች፣ በአገራችን በየቦታውም መስፋፋት አለበት፡፡ አዎ ቤተመጻሕፍት ቁልፍ ተቋም ነው፡፡ የማንበብ ባህልን ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚለውንም አስምሩበት፡፡ የማንበብ ባህል በቤተመጻሕፍት መኖርና መብዛት የሚዳብር ነው፡፡ ልዩ ልዩ ዘመናዊ የንባብ መርሐግበሮችም ያስፈልጋሉ፡፡ በምርቃቱ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች መገኘታቸው ለእኔ እንደ አንድ የቤተመጻሕፍት መሪ የሚያስደስተኝ ጉዳይ ነው፡፡ ማንም ዘወር ብሎ አይቶት የማያውቀውን የቤተመጻሕፍት ዘርፍ ባለስልጣናት ሲያዩት ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ መጽሐፍ ይዞ የሚታይ ሚኒስትር ለትውልዱም ሆነ ለሁሉም ዜጋ ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል፡፡ እውቀት ዋጋ እንደሌለው እየታየ ገንዘብ በሚመለክበት አገር ይህ ተግባር አቅጣጫ ቀያሪ ነው፡፡ መጽሐፍ መሸጫ ሱቆች መኖራቸው ሰዎች ስጋ ብቻ ሳይሆን የአእምሮ ምግብም መግዛት እንዳለባቸው በብሔራዊ ቴሌቪዥን ከብሔራዊ ቤተመንግሥት አጠገብ መተላለፉ ድንቅ ነው፡፡ የስብሰባ አዳራሾቹም መጻሕፍትን ለመመረቅ፣ የመጻሕፍት ውይይት ለማድረግና የሃሳብ ፍጭት ለማድረግ ሁነኛ ሃሳብ ነው፡፡ ካፊቴሪያውም እየተነበበ የሚዝናኑበት ይሆናል፡፡ የሕጻናት ማንበቢያ ክፍሎች መኖራቸውም እንዴት ከታች ጀምሮ የንባብን ሃሳብ ለማስረጽ መታሰቡን ያሳያል፡፡ የምርምር ማንበቢያ ክፍሉ ትልቅ ሃሳብ ነው፡፡ መኪና ማቆሚያውም እንዲሁ፡፡ በመኪና ቤተመጻሕፍት መሄድን አስቡት፡፡ ከመዝናኛና ከቅንጡዎች መዋያ አንዱ ቤተመጻሕት ሲሆን፡፡ እስኪ ስንት መኪና ነበር ወመዘክር የሚሄደው? ስድስት ኪሎ ዜሮ አራት ያለውን የተንጣለለ ቤተመንግሥት መሳይ ቤተመጻሕፍት ስንት ባለመኪና ያውቀዋል?

በ1.15 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው ይህ ቤተመጻሕፍት 1.4 ሚሊየን መጻሕፍትን የሚይዝ መደርደሪያ አለው፡፡ ሶፍት ኮፒ መጻሕፍትም አሉት፡፡ ከአፍሪካ አስር ትልልቅ አብያተመጻሕፍት አንዱም ነው፡፡ ዝርዝሩን ሁላችንም በሂደት ማየት ግድ ይለናል፡፡ ማንበብም እንዲሁ!

 

ይህ ቦታ ዘወር ብላችሁ ማየት የማትችሉት የቤተመንግሥት ጥበቃ ነበር፡፡ መኪናችሁ ቢበላሽ ማቆም አትችሉም ነበር፡፡ ቅልብ የአድዋ ስርወመንግሥት ወታደር መጥቶ ይወርድባችሁ ነበር፡፡ ዱላውን ፍራቻ በቸርኬም ቢሆን ትሄዳላችሁ፡፡ እግሬ አውጭኝ ነበር፡፡ ‹‹ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው›› የሚል ጽሑፍ ተጽፏል፡፡ ማስጠንቀቂያው ይከበራል፡፡ አንባቢ ነኝ እያለ የሚያስወራው መለስ ዜናዊ ቤተመጻሕፍትን ዘወር ብሎ አላየም፡፡ ለቤተመጻሕፍት ቀን እንደወጣ ያየሁት ዶክተር ዐቢይ ለብሔራዊ ፈተና የሚዘጋጁ ተማሪዎችን በብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ተገኝተው ሲያበረታቱ ነው፡፡ በፊት ማነው ተማሪ ትዝ የሚለው! ማንም! ተማሪ ጠላቴ ያለ ስርዓት ነበር፡፡ እነሆ ቤተመንግሥቱን አንድነት ፓርክ አድርገው ዜጎች ገብተው እንዲዝናኑበትና እንዲጎበኙት ያደረጉት መሪ አሁን ቤተመጻሕፍት ከፍተውልናል፡፡ በአፍሪካ ቤተመጻሕፍት እዚህ የደረሰ ትውልድ አሁን ዛፍ በሌለበት ዛፍ ስር ሊያነብ አይችልም፡፡ ዛፍ ካለበት ርቆ የሚኖረው ከተሜ ብዙ ነው፡፡ A roof over your head ይላል ፈረንጅ፡፡ ቤት ያስፈልጋል ለማለት ነው፡፡ አንባቢም ከራሱ በላይ ጣራ ያስፈልገዋል፡፡ ከዛፍ ጥላ የተሻለና የተደራጀ ቤተመጻሕፍት ኢትዮጵያውያን ያስፈልገናል፡፡ አሳቢና የነቃ ትውልድ በዚህ መልኩ ማፍራት ይቻላል፡፡ 



እኔ በግሌ በቤተመጻሕፍት ዘርፍ የሰራኋቸውን ስራዎች ‹‹ብዕረኛው የሞጃ ልጅ›› በተባለው ስብስብ ስራዎቼን የያዘ መጽሐፌ አውጥቻለሁ፡፡ አሁንም በተመሳሳይ አብያተመጻሕፍትን በስማርት ስልኮች የሚመዘግበውን የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ፕሮጀክት የኢትዮጵያውን በበጎፈቃደኝነት አስተባብራለሁ፡፡ አብርሆት ቤተመጻሕፍትም እንዲመዘገብ አግዛለሁ፡፡ ያኔ ዓለም ሁሉ የሚያየውና የሚያግዘው ቤተመጻሕፍት ይሆናል፡፡ የአፍሪካን ስቶሪቡክ የኢትዮጵያ ተጠሪም ስለሆንኩ በየቋንቋው የተጻፉ ከስድስት ሺህ በላይ የልጆች መጻሕፍትን በሶፍት ኮፒ መስጠት እችላለሁ፡፡ ይህም ለአብርሆት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነው፡፡ የሚፈልጉ በአድራሻዬ እንዲያገኙኝ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

መቼም በዚህ ጽሑፍ ማሳረጊያ ላይ ማስተላለፍ የሚኖርብኝን መልዕክት ሳላስተላልፍ ብቀር ሰው ይታዘበኛል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በእውቀትና በትምህርት የጎለበተና ለአገሩ እድገት የሚተጋ ዜጋ ለማፍራት ሲታሰብ አብያተመጻሕፍት ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ስለሆነም የህዝብ አብያተመጻሕፍትን የሚያስተዳድር ህጋዊ አካል መቋቋም አለበት፡፡ አለ ከተባለም መጠናከር ይኖርበታል፡፡ ባለቤት የሌለው የሚመስለው ዘርፉ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም ስለሚያስፈልጉ ማሰልጠኛዎች መኖር አለባቸው፡፡ የአብያተመጻሕፍት ትምህርት በዲግሪና ከዚያም በላይ በየቦታው መሰጠት አለበት፡፡ ቢያንስ እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮች የአብያተመጻሕፍት ዳይሬክተሮች ሊሰየሙ ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች አገሮች የአብያተመጻሕፍት መሪዎች የሚኒስትር ደረጃ እንዳላቸው ለአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ማህበር ስብሰባ ጋና ሄጄ አይቻለሁ፡፡ የተከበሩ ምሁራን ናቸው፡፡ ይህ ዘርፍ በባለሙያ ከተመራ፣ የሚከታተለው አካል ከተሰየመ፣ አስፈላጊው በጀት ከተመደበለት፣ አዋጅ ከወጣለት አገራችንን ትልቅ ደረጃ እንደሚያደርሳት አይጠረጠርም፡፡ እግረመንገዱንም መንግሥት የግል ቤተመጻሕፍት ዘርፍን የሚያበረታታበትን አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ከዚያ በፊት በፓርላማ እንዲጸድቅ ቀርቦ ለበርካታ ዓመታት ደጅ የሚጠናው አዋጅ አቧራው ተራግፎ ይታይልን፤ ተወያዩበት እላለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ለሌሎች የአፍሪካ መሪዎች አርአያ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

 

‹‹ይገድሉኝም እንደሁ ይኸው ቆምኩልዎ

ይገርፉኝም እንደሁ ይኸው ቆምኩልዎ

ያለ ለምጣም ምኒልክ ብዬ ሰደብኩዎ››

እንደተባለው ያለ ነገር ነው እንዳነበባችሁት በዛሬው ጽሑፍ ይዤ የቀረብኩት፡፡ የየዘመኑ ጸሐፊና ገጣሚ ለመሪው የሚያበረክተው ቅኔና መልዕክት አይጠፋም፡፡ መልዕክቴም እንደሚደመጥልኝ እተማመናለሁ!


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...