ያገሬ ምንጮች
የሳሲቱን መሐንዲስ ገብረሚካኤልን ዛሬ በጠዋት አግኝቼው ነበር። በጨዋታ ጨዋታ ዛሬ ጥምቀት ስለሆነ እነሱ ደጅ አባመንክር ታቦት እንደሚውል አወሳን። ከዚያም ምንጯን አነሳን። ሜዳ ላይ ያለችና ድፍርስ ምንጭ ነች። ለምን ቆፍረው እንደማያስፋፏት የሚያውቅ የለም። እዚያ ከብት ሲያግዱም ሆነ ሲውሉ አንዳፍታ ጫር ጫር ቢያደርጉ ትልቅ ምንጭ ይሆን ነበር። በቅርቡ የኔ አያቶችም ከዚያ እንደሚቀዱ ማየቴን ነገርኩት። አክስቴ ከዚያ ከአባመንክር ድረስ ዉኃ ተሸክማ ስትመጣ አይቼ "ምንጯስ?" አልኳት። "ውይ የመቼህን! ደረቀች እኮ" ማለቷን አስታወስኩ። ከአያቶቼ ቤት አቅራቢያ መቶ ሜትር በሚሆን እርቀት ላይ የነበረችው ምንጭ የደረቀችው በባህር ዛፍ ምክንያት ነው። ዳገቱ ላይ ከመቶ ሜትር ባነሰ እርቀት የአሸናፊ ዛፍ ስላለ ስሩ ዉኃውን መጦ ጨረሰው። ያው በሽክና ወደ እንስራ ወይም ጀሪካን ሲቀዱ ደፍረስ ሊል የሚችል ቢሆንም ጥሩ ምንጭ ነበረች። በመድረቋ አዘንኩ። ሌላኛዋ ምንጭ ደግሞ የአሸናፊ መቅጃ ነች። በአሸናፊ ወርቅሸት የተሰየመችው እሱ ስለቆፈራት ይሁን ስላገኛት ሳሲት ስወርድ እጠይቀዋለሁ። ሳቂታው አሸናፊም እያዋዛ ይነግረኛል። አባቱን ደጉን ጋሼ ወርቅሸትን ባለፈው ለአክስቴ ለየሺ ድረሴ ለቅሶ ሄጄ ማሜለኝ ማርያም አግኝቼዋለሁ። ምን የመሰለ ቆቅ አዳኝ መሰላችሁ! ቆቅም እንኩቶም አብልቶናል። አሸናፊ መቅጃ ከህብረት ዛፍ ጥግ የምትገኝ ስትሆን ሳሲቶች በተለይም ዥንጎዶተራዎች ያዘወትሯታል። ከ1987 ወዲህ ማለቴ ነው። የቦኖ ዉኃ ከመምጣቱ በፊትማ ሁሉም እዚያው ነበር። ክረምት ከሆነ ግን የዝተት መርገጫዋ ስላለች አሸናፊ መቅጃ አትወርዱም። ውይ ምን ዝተት መርገጫስ አስወረዳችሁ! አባማዶ እያለ።
ገብረሚካኤል በደንብ የሚያውቃት ደግሞ ጎድጓዲትን አለፍ ብሎ ያለችውን ነው። ስሟን ረሳሁት። ኧረ አልረሳሁትም። ትንሽ ደንገጥ በሉ ብዬ ነው። ኩልል ያለ ዉኃ ከአለት ላይ የሚፈልቅባት አይጥ ዉኃ ነች። በአምስት ሊትሯ ጀሪካን ብዙ ቀን ንፁህ ዉኃ አምጥተናል። ወንዶቹ በትከሻችን ነው። ሴቶቹ ያዝሉታል። ከፍ ያለ ጀሪካን ወይም እንስራ ሊያዝሉም ይችላሉ እንደየእድሜያቸው። የሳሲት የቦኖ ዉኃ የሚመጣው ከሩቅ ምንጭ ነው። ሞተለሚን አልፎ። ስሙን ረሳሁት።
ለጥምቀት የሞተለሚን ዉኃም ጠጥተናል። ጥምቀትም ባይሆን ከብት ስናጠጣም ቢሆን አይቀር። ዋና ግን እፈራለሁ። ለጥምቀት ሞተለሚ ላይ የዋኘልን መንገሽ ኪዳኔ ሲሆን፤ የአሰብ ትዝታውን አስታውሶ ሞተለሚን ሲያጥጥላት አስታውሳለሁ። አሁን ታሪክ ስለተቀየረ አሰብ (ምናልባት ከተሳሳትኩ ምፅዋን) ጎብኝቶ መመለስ ይችላል።
ሌላኛው የሳሲት የዉኃ ምንጭ ቧንቧ ዉኃ ይባላል። ችግኝ ጣቢያው ጋ ያለው ጣሊያን ሰራሽ ዓመት ከዓመት የሚፈስ ዉኃ ማለት ነው። ብዙ ትዝታ አላችሁ ብዬ አስባለሁ እዚያም። ከሁሉም የምናውቀው እሱን ነው። አንድ ቀን ዉኃ ቀድቼ ሊታጠብ የወረደው የአንበሳው መኪና ይዞኝ እቤቴ ድረስ መጥቷል። ታዲያ ዉኃ ስትቀዱ አልቅት እንዳትቀዱ ተጠንቀቁ።
አንድ ቀን ግሩም አስናቀና እኔ ራበን። ምሳ የሚሰጠን አልነበረም። ምክንያቱም እናቱ ዘነበች (ነፍስ ይማር) ስላልነበረች ነው። ከዚያ ግሩም ጉድ ጉድ ሲል እንጀራም ወጥም ያገኛል። ያንን በላን። ዘነበች ስትመጣ "ውይ ልጆቼን። እራባችሁ አይደል ወጥ ሳልሰራ ሄጄ" ማለት። ግሩም ቀደም ብሎ "ኧረ ወጥ አግኝተን በልተናል" ሲላት፤ "የፆሙን ነው?" ብላ ጠየቀችን። ሁለታችንም ፍጥጥ። ቅዳሜ አባ ኃይለገብርኤል መጡ። ቤተኛ ቄስ ናቸው። ሁሉም ብድግ ብድግ ብሎ ተሳለመ። የግሩም አያት እትዬ እቱነሽ (ነፍስ ይማር) የኛን ጉድ ለአባ መንገር። አባም ጢማቸውን እያሻሹ "በሉ ለእትዬ እቱነሽ ዉኃ ቅዱ" የሚል ቅጣት ሰጡን። ጀሪካኖቻችንን ይዘን ወደ ምንጭ። በቀረጥ ቁልቁል ወደ ፅጌረዳ ገሰገስን። እዚያም መቅ የተባለ ጥልቅ ምንጭ አለ። ቀድተን ከች!
ዛሬ ለግሩም አልደወልኩለትም። እሱም አይጠብቅም። ካልደወልኩ የሚናደደው ለታህሳስ ገብርኤል ነው። ምክንያቱም መጀንና እምቧይባድ ገብርኤል እንሄድ ስለነበረና ትዝታ ስላለብን ነው።
ይህን ይህን እያወራሁ ገብረሚካኤልን በትዝታ ባህር አሰጠምኩት። ማረሻ ማሽን አሰየሰራ ነው። ወደ አንድ ሚሊዮን ብር የተጠጋ ወጪ እያስወጣ ያለ የምህንድስና ፕሮጀክት ነው። ሰሞኑን ጅሩ ላይ የመውቂያ ማሸን እጥረት እንዳለ ነገርኩት። ያንን ሲሰማ "ቆይ እቃ ተርፎኛል፤ መውቂያም እሰራለሁ" ብሎ ፈገግ አለ። "ወንድሜ አንተ በተግባር ላይ የሚውል ትምህርት ነው የተማርከው!" ብዬው ተለያየን። እሱም ወደ ዩኒቨርስቲ ፕሮጀክቱ፤ እኔም ወደ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት።
ለወደፊቱ እንደ ሊንዳ ሆጋን ያገሬን ትዝታ መጻፌ አይቀርም።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ