ሰኞ 7 ፌብሩዋሪ 2022

በኦሮሚያ ስለሚገደሉትና ስለሚፈናቀሉት አማሮች ምን መፍትሔ አለ?

 


በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ስር በሚኖሩት የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙት ዝርፊያ፣ ከቀዬያቸው ማፈናቀል፣ የአካል ማጉደል፣ ግድያ፣ ጅምላ ጭፍጨፋና ሌሎችም ወንጀሎች ከቀን ወደ ቀን እየተባባሱ ላለፉት ዓመታት ያለማቋረጥ ቀጥለዋል። ችግሩም የሚገባውን ትኩረት እንዳያገኝ ሆነ ተብሎ የሚፈጸሙ የመሸፋፈን ስራዎች ከመኖራቸውም በላይ የድርጊቱን ፈጻሚዎችም ለህግ ለማቅረብ የተደረገ ጥረት ወይም ከነጭራሹ ፍላጎትም ስለመኖሩ ግልጽ ማስረጃ የለም። በአገራችን በየጊዜው እየተከሰቱ ያሉት የሰላምና መረጋጋት ቀውሶችም ለጉዳዩ መረሳት የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። ስለ ችግሩ በባለሙያዎችም ሆነ በሚመለከታቸው ኃላፊዎች የሚወጡ ሪፖርቶችና ዳሰሳዎች ካሉ መመልከትና ለወደፊቱ ማናቸውም ውሳኔ በግብዓትነት መጠቀም የተገባ ነው። ከዚያ በተጨማሪም አደጋው የሚመለከተው ማናቸውም ዜጋ በሃሳብም ሆነ በገንዘብ  መደገፍ ይኖርበታል። አደጋው ለነገ የማይባልና ሰፊ ማህበረሰብን የሚመለከት በመሆኑ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ጥሪያችንን ማቅረብ አለብን። ይህም ሲባል የሚከተለውን ሂደት የተከተለ ወይም ከዚህ የተሻለ አሰራር ሊተገበር ይገባዋል። ከግምት ውስጥ ልናስገባው የሚገባን ጉዳይ ቢኖር ተጠቂዎቹ ተነጥሎ በተለየ ቦታ አለመኖራቸው ለጥበቃና ራስን ለመከላከል አለማመቸቱን ነው።

1. ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚፈልግ መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም መመስረት። መንግስታዊ ያልሆነው ተቋም ከግለሰቦች፣ ከሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከተባበሩት መንግስታት ወይም ሌሎች ድርጅቶች ሊሆን ይችላል። 

2.በቀጥታ የጥቃት ሰለባ የሆኑትንና ለወደፊቱም ጥቃት ይፈጸምባቸዋል በሚል የሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች መለየት፣ ቁጥራቸውንና ዝርዝር ሁኔታቸውን ማጥናት

3. በጣም አስጊ በሆኑት አካባቢዎች ያሉትን ነዋሪዎች ለንብረታቸው ከለላ ሰጥቶ በስቴዲየሞች፣ በትምህርት ተቋማት፣ በጊዜያዊ ካምፖች እንዲጠለሉና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ። ጥበቃና ከለላም ለካምፖቹ ማመቻቸት። ይህ ሃሳብ ጄኔራል ሮሚዎ ደሊየር  አንድ ሚሊዮን ሰዎችን በሃምሳ ካምፖች ወይም ስቴዲየሞች አስፍሬ በተወሰኑ ወታደሮች በማስጠበቅ ህይወታቸውን ማትረፍ እችላለሁ ካሉት ጋር ይመሳሰላል። ከዘገየ ግን ቀስ በቀስ ህዝቡ ማለቁ ነው።

4. በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በአገር ደረጃ ላለው የፖለቲካ አለመስማማት መፍትሔ መፈለግና ስለ ዜጎቹ ዘላቂ ዕጣፈንታ መወሰን ያስፈልጋል። 

እስኪ ሃሳባችሁን ስጡበት። ከየሙያና ልምዳችሁ የተሳሳተውን እንድታርሙና መሆን ያለበትን እንድትጽፉልኝ እጠይቃለሁ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...