2022 ፌብሩዋሪ 2, ረቡዕ

ለደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ቤተመጻሕፍት ንግግር አቀረብኩ


ዛሬ ረቡዕ 25.05.2014 ዓ.ም. ለደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ቤተመጻሕፍት ሰራተኞች ከልምዴ በመነሳት ንግግር አቅርቤያለሁ። በመጀመሪያ ቤተመጻሕፍቱ በተለይም አቶ ይድነቃቸው ፈለገ ይህንን መርሐግብር ስላዘጋጁ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። አዲስ ጅምር ማስለመዳቸውን ሰልጣኞቹም ወደውታል። ቤተመጻሕፍት በአጠቃላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሆኖ ሳለ ሲሰጠው አይስዋልም። መሰል ሥልጠናዎችና ዝግጅቶች ወደፊትም መኖር ይገባቸዋል።
ከእኔ በፊት ሁለት የዩኒቨርሲቲያችን የግብርና ኮሌጅ መምህራን ማለትም ዶክተር ካሳሁንና ዶክተር ተስፋዬ ስለ ጊዜ አጠቃቀምና የስራ ባህል ግሩም እንደየቅደምተከተላቸው ዝግጅቶች አቀረቡ። በስዕላዊ አስረጂ የታጀቡ ልዩ አነቃቂና አስተማሪ ዝግጅቶች ነበሩ። ሁለቱ በቦታው ማቅረባቸው የማላዊውን የቤተመጻሕፍት ዳይሬክተር ግሬይ ኒያሊን አስታወሰኝ። የግብርና መረጃ ፍለጋ ገብቶ ቤተመጻሕፍት ገብቶ መውጣት ያልቻለ ግን በዚህ ምክንያት ዓለምን የዞረ ሰው።
ሮበርት ፍሮስት በግጥሙ ያልተሄደበት መንገድ እንዲል የኔ ያለፉት ስምንት ዓመታት የፈጠራ ጉዞ በድንገት ክፍል ከመግባቴ በፊት የቀሩኝን 15 ደቂቃዎች የት እንደማሳልፍ በወሰንኩት ውሳኔ ላይ የተመካ ነው። በዩኒቨርስቲው የእንግሊዝኛ ማሻሻያ ማዕከል ወደምትገኘው የማንበቢያ ጥጋት መሄድ፣ የሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ላይ መጽሐፍ ማግኘት፣ መተርጎም፣ ማሳተም፣ ማከፋፈል። በዚህ ሳላበቃ በደብረብርሃን ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍትን መክፈት። የግል ቤተመጻሕፍቱም ብዙ ነገር ለመሞከር አስቻለኝ።
ኮቪድ መጣ። ሁቱትሲ እንደገና ታተመች። በአጠቃላይ 23,000 ኮፒ። ወደ ኦሮምኛ ተተረጎመች። የሌሎችንም ፀሐፍት ሥራዎች ለማሳተም ቻልኩ።
ከኮቪድ በኋላም ዩኒቨርስቲው ሲከፈት የሥነምግብ መጽሐፍ ከዚያው ከቋንቋ ማዕከሉ አገኘሁ። ሌሎችንም አነበብኩ። በቀን አንዴ ተመጋቢነቴን ተጠቅሜ ከልምድም በመነሳት ሌላ መጽሐፍ አቀረብኩ - 'የፆም ጣዕም'። የቤተመጻሕፍት፣ የጉዞ፣ ትርጉምና ሌሎች ስራዎቼን አሰባስቤ ሦስተኛ መጽሐፍ አሳተምኩ - ብዕረኛው የሞጃ ልጅ።
ከዚህ ሁሉ ምን አደረሰኝ? በጎ ፈቃደኝነት! በአሜሪካ ሠላም ጓድ በበጎ ፈቃደኝነት ሳገለግል ከአፍሪካን ስቶሪቡክ ጋር ተዋወቅሁ። ለአፍሪካ ልጆች ከመቶ በላይ መጻሕፍትን ለማቅረብና በኢትዮጵያም የድርጅቱን ስራዎች በማስተባበር በጎፈቃደኛ ለመሆን በቃሁ። እሱም ሌላ ነገር ይዞ መጣ - የአፍሪካ ቤተመጻሕፍት ማህበርን ፕሮጀክት። ቀጥሎ ሌላ የአፍሪካ የልጆች ጨዋታዎች ፕሮጀክት። ያስመለከተንን መስራት፣ ያ በሚወስደን ጎዳና መሄድ፣ መጨረሻ ላይ ካላሰብነው ቦታ እራሳችንን ስናገኘው ይህን ሁሉ መች አቀድኩት እንላለን - ያልተሄደበት መንገድ ማለት አይደል! ሌሎች ያልነኩት።
የደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ አብያተመጻሕፍትንና ሌሎች የንባብ ጉዳዮችን በብዕረኛው የሞጃ ልጅ ጽፌያለሁ፤ ከአማላይና የማይገመቱ ጉዞዎች ጋር። የቤተመጻሕፍት ሰራተኞች የጊዜ ነጻነት አላቸው - ያንን ለማንበብና ስራ ለመፍጠር እንዲጠቀሙት እመክራለሁ። አንባቢም ቢሆኑ ሙያቸውን የበለጠ ይወዱታል። በዚህ ተለዋዋጭ ጊዜ ቤተመጻሕፍትን እንዲወደድ ማድረግ የምንችለው እኛው ሰራተኞቹ ነን። በመጻሕፍት የደረጀና በቴክኖሎጂ የበለፀገ ቤተመጻሕፍት አለን። ለዛሬ የሥልጠናችንን ደረጃና የሙያችን ዓይነት ተቀብለን እየሰራን ራሳችንን ለማሻሻል መትጋት አለብን። ፍቅሩ ኪዳኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ቦታ ያገኘው በትምህርቱ ደረጃ ከፍተኛነት አይደለም - በጥረቱና ፍላጎቱን በማግኘቱ እንጂ። ከሰራን ራሳችንንም ሆነ ቤተመጻሕፍታችንን ለመለወጥ አሁንም አልረፈደም!




ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...