2022 ሜይ 23, ሰኞ

ኢትዮጵያ ሆይ! ወደ ምግባር ምህዋርሽ ተመለሺ እየተባልሽ ነው!

 



የመጽሐፍ ዳሰሳ

በመዘምር ግርማ

ግንቦት 15፣ 2014 ዓ.ም.

 

የመጽሐፉ ርዕስ - በዝምታ ውስጥ

ደራሲ - ስንታየሁ ገብረጊዮርጊስ

የታተመበት ዘመን - 2012 ዓ.ም.

የገጽ ብዛት - 171

ዘውግ - አጫጭር ጽሑፎችና ግጥሞች

 

መግቢያ

በእንግሊዝኛና አማርኛ ቋንቋዎች ልዩ ልዩ መጻሕፍትን የጻፉት የደራሲ ስንታየሁ ገብረጊዮርጊስ መጻሕፍት በሰፊው ያልተሰራጩና ይህኛውም መጽሐፍ በአጋጣሚ ካልሆነ የማይገኝ ነው፡፡ ደራሲው ስለ ራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት በአማራ ቴሌቪዥን የተላለፈውን ዝግጅት ባዩ በማግስቱ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን ሊያገኙኝ መጥተው መጽሐፉን ከሌላኛውና ‹‹በረከት›› ከተሰኘው መጽሐፋቸው ጋር ስላበረከቱልኝና ስላገኘሁት ደስተኛነቴ ወደር የለውም፡፡ ከአንድ ዝም ካለና በዕድሜና በትምህርት ከጎለበተ ሰው ጋር ለማውጋት መቻል መታደል መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ወጋችንን እንደመግቢያ በመጠቀም ወደ መጽሐፉ አመራሁ፡፡ መጽሐፉን ማንበቤም ደራሲውን የተሻለ ለማወቅና የሚያነሷቸውን ጭብጦች አገራዊ ጠቀሜታ እንዳሰላስል አስችሎኛል፡፡ እንደ ወትሮዬ ሁሉ በአገራችን ካለው የመጻሕፍት ህትመት፣ ስርጭትና ውይይት ችግር አንጻር ስንት ስራዎችና ደራስያን ተደብቀው ኖረው ይሆን ስል ራሴን ጠየቅሁ፡፡

 

ቋንቋውና አቀራረቡ

የልዑል በዕደማርያም ትምህርት ቤት ተማሪ የነበሩት ደራሲው የአማርኛን ሥነጽሑፍ ከዮሐንስ አድማሱ፣ እንዲሁም እንግሊዝኛን በአንድ ጊዜ ከሦስት መምህራን (ማለትም ሰዋስው፣ ጽሑፍ፣ ንግግር ከሚያስተምሩ) ቀስመዋል፡፡ ከቤተክሕነት ትምህርትም የቀሰሙት ክህሎትና ዕውቀት በቋንቋና የሃሳብ ፍሰታቸው ላይ ይንጸባረቃል፡፡ ይህንን ለማለት የቻልኩት ትክክለኛውን የአማርኛ ፊደል በትክክለኛው ቦታ (ሞክሼ ሆሄያትን አስመልክቶ) በመጠቀማቸው፣ የቋንቋ ፍሰቱን በመጠበቃቸውና የፊደል ግድፈት እንዳይኖር በመጠንቀቃቸው ነው - ከብዙ በጥቂቱ! እኔ በግሌ የአማርኛ ሞክሼ ሆሄያትን በመጠቀም ረገድ የትርጉም ስራዬን ስሰራ ተቸጋግሬ ነበር፡፡ የአምሳሉ አክሊሉን መጽሐፍ ተጠቅሜ ነበር ፊደላቱን ልለቅም የቻልኩት፡፡ አማርኛዬም በእንግሊዝኛ በመበረዙና የንግግር ቃላት ስለሚበዛበት መደበኛ አጻጻፍን ለመከተል የፈጀብኝን ጊዜ አውቀዋለሁ፡፡ ተሳክቶልኝ ከሆነ አንባቢ ይፈርዳል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ጽሑፍ ፊደል አልለቀምኩም፡፡ ደራሲ ስንታየሁ ግን ያለፉበት ጥራት የነበረው ትምህርት ያንን ሳያቀልላቸው አልቀረም፡፡ የሚጠብቅና የሚላላ ፊደል ባለበት ሁሉ በቅንፍ ውስጥ ጠብቆ ወይም ላልቶ መነበቡን በመጽሐፉ ሙሉ አመልክተዋል፡፡ ይህም በተወሰነ መልኩ ሐዲስ ዓለማየሁ የሚጠቀሙበትን የመሰለና ሃሳባቸው በትክክል ለተደራሲው መቅረቡን ለማረጋገጥ የሚጥሩ ጠንቃቃ ፀሐፊ መሆናቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ በሁለት ክፍሎች ማለትም ‹‹ቅይጥ›› እና ‹‹ሃሳብን በስንኝ›› በሚሉ የቀረበ ነው መጽሐፉ፡፡ መጀመሪያው ልዩ ልዩ ምልከታዎቻቸውን የሚያሳዩባቸው ዝርው ጽሑፎችን ሲይዝ፤ ሁለተኛው ደግሞ የግጥሞች ስብስብ ነው፡፡

 

‹‹ቅይጥ›› ውስጥ የተቀየጠው ምንድነው

በመጽሐፉ እንደተገለጸው የአርታኢ ብዕር ያላያቸው ጽሑፎችን በዚህ ክፍል እናገኛለን፡፡ ይሁን እንጂ ከደራሲው እንደወረደ ሃሳባቸውን ማግኘታችን ለአንባብያን ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ለእርሳቸውም የመጻፍ ነጻነትን ይሰጣቸዋል፡፡ ያንን የአስተያየት ፍለጋ ረሃባቸውን ባያስታግስላቸውም ሳነብ ያገኘሁትንና የተሰማኝን አንዳንድ ሃሳብ ልሰንዝር፡፡ በመግቢያው በተነሣው ሃሳብ መሰረት በቅይጥ እንጀራ የተመሰለው ይህ ክፍል እውነትም ብዙ የተቀያየጡ ምልከታዎች አሉበት፡፡  ‹‹ያልጨረስናቸው ውይይቶች›› በሚለው ርዕስ ስር ከተነሱት አንዱ ታሪክ ነው፡፡ ከአንባብያን እስከ ታሪክ ምሁራን ድረስ የሚያከራክረው የታሪክ አጻጻፍና ትንታኔ ጉዳይ ተዳሶበታል፡፡ ጽንፍ የሚይዙና ሚዛናዊነት የጎደላቸውን ጸሐፍትን ጨምሮ የታሪክ ጸሐፊዎችን በአራት የሚከፍለው ይህ ክፍል ለማሳያነትም የዳዊትና የጎልያድን ታሪክ እስራኤላውያን፣ ፍልስጤማውያንና ዘመናዊ የታሪክ ጸሐፍት እንዴት ያዩታል የሚለውን በአብነት አስቀምጧል፡፡ በቅርቡ በዩኒቨርሲቲ አንደኛ ዓመት ኮርስነት ይሰጥ ተብሎ ዕቅድ ተይዞለት ሳይሰጥ የቀረው የታሪክ ትምህርት የተስተጓጎለው ምክንያት በፀሐፍት አለመስማማት መሆኑ ይታወሳል፡፡ ‹‹የታረቀ የታሪክ ፀሐፊ በሌለበት፣ የታረቀ ታሪክና ሕዝብ ሊኖር አይችልም፡፡›› (20) የሚለውና ሌሎችንም ቁምነገሮችን በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የሚያነሣሣልን ይህ መጽሐፍ እውነትም ያልጨረስናቸው ምናልባትም ያልጀመርናቸውን ውይይቶች ይነካካልናል፡፡

በማስከተል የቀረበው ባህል ሲሆን የጽንፍን አላስፈላጊነትና የመካካለኛውን ዓይን ጠቀሜታ ይጠቁማል፡፡ ባህሌ ተዋጠብኝ ከሚል የቅራኔ ምንጭ እስከ ባህል ባህርያትና ተያያዥ ጉዳዮች የቀረበበት ሁኔታ ካለፈው የታሪክ ያላለቀ ውይይትነት ጉዳይ ጋር የሚስማማ ነጥብ ነው፡፡  እንግዲህ ቀጥሎ የመጣው ሌላው የየክርክሮቻችን ጉልህ ነጥብ ጀግንነት ነው፡፡ ‹‹አንድ ሕዝብ የሚኮራባቸውን ጉዳዮች ፈጽሞ በመገኘት›› የጀግንነት ካባን እንደምንደርብ በማስገንዘብ ቃሉ የተሸከመውን ሃሳብ አብራርተዋል፡፡ የጀግንነት ታሪክ አጠቃቀማችን፣ ዓለም ሁሉ ጀግና እንዳለው፣ በየዘርፉ ጀግና እንዳለና የተከፋፈለ ህብረተሰብ ደግሞ የየራሱን ጀግና እንደሚፈልግ ተገልጧል፡፡ የአንድ ብሔራዊ ጀግና ሃሳብ በአሁኑ ወቅትም ሆነ በፊት ሲነሳ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ ደራሲው የጫሩትን ክብሪት ተጠቅመን ይህን አጨቃጫቂ ጉዳይ ወደ ጠቃሚነት ማሸጋጋር ሳይኖርብን አይቀርም፡፡

ቀጥሎ ያልፀዱ አመለካከቶችና ልማዶች ይከተላሉ፡፡ ምን አለበት? ወይም ምን ችግር አለው? የሚለውን ሃሳብ ሳነብ ሕጋዊነትን ወደ ጎን በማድረግ በምን አለበት እሳቤ መጥፎ ስራን የሚያራምዱትን አስታወስኩ፡፡ አጥፍተው የሚሳደቡትንም እንዲሁ፡፡ ጥሩ የሰራንም የሚያንቋሽሹትን ወይም እንደ ደራሲው ዕይታ ‹‹ምን ችግር አለው እያሉ ሕግን የሚያከብሩ ዜጎችን ማቃለል›› ላይ ለማሰብና ለማስታወስም ዕድል አገኘሁ፡፡ ሕግን ማክበርን፣ ሕጋዊ ዳኝነትንና ባህላዊውን ሕግ በተወሰነ መልኩ ለመተዋወቅ ቻልኩ፡፡ እነዚህ ሃሳቦች ሲቀርቡ ሃሳቦቹ ብቻ ሳይሆኑ በደራሲው ሕይወት ገጠመኝ የተከሰቱ አብነቶች እንደ ጌጥ ጣል እየተደረጉ ነው፡፡ ይህም ፈገግ እያስባለ ወይም እያስገረመ የአንባቢን ስሜት ለመያዝ የሚጠቅም ነው፡፡

እንዴት ቢንቀኝ ነው የሚለው ምንባብ ደግሞ አባባሉ በተለይ በአለቆች ዘንድ የተለመደ ነው ይሉናል፡፡ ናቀኝ ወይም አላከበረኝም በሚል የተሳሳተ አተያይ የበላይ አለቃ የበታቹን ይጎዳል፡፡ የበታችም ቢሆን ሲጎዱት ምን ችግር ሊያመጣ እንደሚችል በደልን መሸከም በማይችሉ ሰዎች የቤት ሰራተኞችን ጨምሮ መመልከት ይቻላል፡፡ ቂም በቀልን ተሸክመን የምንኖርና ሌላውን ለመጉዳት የመሞከር አባዜ ያለን ህብረተሰብ መሆናችንን በዩኒቨርሲቲ የቃል ተቋቁሞ ጊዜ በነበረ ጥያቄና መልስ የገጠማቸውን የበቀል ጉዳይ አካተዋል፡፡ ይህች ችግር ያጋጠመችን ሁሉ ምስክሮች ነን፡፡ እስኪ ከባለሥልጣን አንጻር ያለውን የበቀል ዱላ በዚህ ጥያቄያቸው እንለፈው ‹‹እንደሚመስለኝ ኢትዮጵያ ውስጥ፤ የሚፈጽሙትን ሕገ-ወጥ ተግባር ለመሸፈን ሥልጣን ጊዜያዊ ዕድልን ስለሚሰጥ ይሆን?›› (54)፡፡   

ያልሆኑትን ማስመሰል የሚለው ጽሑፍ ይከተላል፡፡ መንስኤው ምን ይመስላችኋል? ለምን ያልሆነውን እናስመስላን? ውሸትን ምን አመጣው? ‹‹ማስመሰል ሰው በራሱ ያጎለበተው ትልቁ ድክመቱ ነው ብዬ ነው የምወስደው›› የሚሉን ፀሐፊው ይህ ጉዳይ በፖለቲካ ጭምር እንደሚገባና ስር የሰደደ እንደሆነ ታዝበዋል፡፡ በስልጣን ማስመሰል፣ በትምህርት ማስመሰል፣ በዕውቀት ማስመሰል የመሳሰሉ የማስመሰል ዓይነቶችን ዳሰው ሲያበቁ ሳይማር ተማርኩ የሚለውን አስመሳይ አስመልክተውም ‹‹መሐይምናን በበዙበት አገር ፊደል የቆጠረም ምሁር ነው፡፡›› ይሉናል፡፡  አዎ፣ እንቧጮ የበዛበት ጫካ ተብዬ! በሃብት ማስመሰል ላይ ሳይኖረው አለኝ የሚል ብቻ ሳይሆን እያለውም አበድረኝ እንዳይሉት የለኝም የሚል አለ፡፡ በሁሉም ረገድ በየምክንያቱ ዓለም የአስመሳዮች ምሽግ ናት፡፡

ምን አገባኝ በሚለው ቀጣይ ጽሑፍ ኃላፊነታቸውን በማይወጡ ሰዎች ላይ ሃሳብ ተሰንዝሯል፡፡ ሌላውም ኃላፊነቱን ሊወጣ ቢሞክር ምን አገባህ የሚል ሃሳብ ይከተላል፡፡ ይህ መሆኑ የሚያስከትለውን ከኃላፊነት መራቅና ደንታቢነት ማሰብ ነው፡፡ የዚያ ድምር ውጤት ደግሞ ሳናውቀው ማጥ ውስጥ ይከተናል፡፡

የጫጫታ ዓለም በሚለው በተከታዩ አስተያየታቸው የፌስቡክና ዩቱብን ጫጫታና ጩኸት ይተቻሉ፡፡ የዚህ ጫጫታ መልክ አለመያዝ ችግርም በፖለቲካ ፓርቲዎች እውነትን የማያውቅ ጫጫታ ይስተዋላል ይላሉ፡፡

የተጠቂነት አስተሳሰብ የሚል ርዕስ ባለው በቀጣዩ ሃሳባቸው እንደሚሉት በዓለም ላይ ነጮች በህብረተሰባቸውና በአገራቸው ላይ የበላይነት ስነልቦናን ለማስረጽ ሲሞክሩ ጥቁሮቸ ግን በተቃራኒው በበደል ላይ ያተኮረ የተጠቂት አስተሳሰብ አዳብረዋል፡፡ በደሉ የለም ለማለት እንዳልሆነ የገለጹት ጸሐፊው በተጠቂነትና በደል ላይ ማተኮር ተበዳዩን ራሱን እየጎዳ እንደሚሄድ ያሳዩናል፡፡ የስነልቦና ሽንፈቱን ወደ አገራችንም ያመጡትና ጥቁር አሜሪካውያን ላይ እንደረበበው የሽንፈት ስነልቦና ሁሉ ኢትዮጵያም ውስጥ ብሔረሰቦች ያንን እንደያዙ ይተቻሉ፡፡ ‹‹እውን የብሔረተኝነት ስሜት ካለተጠቂነት አስተሳሰብ መራድ አይችልም እንዴ?›› ሲሉ ያጠይቃሉ፡፡ ይህን የተጠቂነት ስሜትም ወደ አብንም አንዳይሻገር ይሰጋሉ፡፡

ሌላው በታዳጊ አገሮች ከምግብና ከዲሞክራሲ እየተባለ የሚነሣውን ሃሳብ ‹‹ዳቦና ነፃነት›› በሚል ያዩት ይከተላል፡፡ ክርክሩ ለምንና በማን እንደሚነሣ እንዲሁም አካሄዱ እንዴት እንደሆነ ጽሑፉ መነሻ ይሆናል፡፡ 

ማንነት እና መደመር በሚለው ክፍል የማንነት ፖለቲካን ያስረዳሉ፡፡ በቅርቡ በአገራችን ከመጣው ለውጥ በኋላ የተነሣውን የመደመር ጥያቄንም ይነካኩታል፡፡ መደመር የሚለውን ሃሳብ ከሂሳብ ህጎች አንጻር በማንሳት ዩኒየን፣ ኢንተርሴክሽን፣ የሚደመረው ውስጥ ኔጌቲቭ ነው ፖዘቲቭ መብዛት ያለበት የሚሉትን በማንሳት ሃሳቡን ወደ ፖለቲካ ትንታኔ ይወስዱታል፡፡ ብሔር አገር ማለት ሆኖ ሳለ በአገራችን ውስጥ ላሉ ህብረተሰቦች የብሔር ማዕረግ መስጠቱ ያለውን አንደምታ የተነትኑና ነገሩ ወዴት ሊያመራ ነው ይሉናል፡፡ ብሔረ-ሰብ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ስለሆነ እሱን ይመርጣሉ፡፡ ነገሩን ወደራሳቸው ብሔረሰብ ወስደውም የአማራ ህዝብ ራሱን እንዴት በዘር ማደራጀት እንደሌለበት የነበራቸውን ሃሳብ ያቀርቡልናል፡፡ የፕሮፌሰር አስራትን ሃሰብ በወቅቱ ቢቃወሙም አሁን ግን እንደ አርቆ አሳቢ ያየዋቸዋል፡፡ አማራ ምን ዓይነት አደረጃጀት እንደሚያስፈልገው፣ ምን ዓይነት ኢትዮጵያዊነት እንደሚያስፈልግ፣ ምን ዓይነት መደመር እንደሚያሻ ዳሰው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በሠላም፣ በልማትና አብሮነት የሚኖር አማራን ማየት እንደሚሹ ጽፈዋል፡፡  ‹‹ፖለቲካ በጠቅሉ፣ ጨካኝና ማስተዋል የጎደላቸው ሰዎች የሚሰባሰቡበት መድረክ ይመስለኛል፡፡›› የሚለው ሃሳባቸው የአገራችንን የማንነትና ግራ የገባው ፖለቲካ ያጠቃልል ይመስላል፡፡ ሃሳቡ በተወሰነ መልኩ ‹‹ፖለቲከኛ ሁሉ የሚሮጠው ለሆዱ ነው›› ከሚለው የአንድ ወዳጄ ሃሳብ ጋርም ሊሄድ ይችላል፡፡ የአሁኑ አስተዳደር በምን ዓይነት ሁኔታ ይሂድ ለሚለው መነሻ አቅርበውልናል፡፡

ፓርቲዎችን ከመተቸት አልፈው የፓርቲ ምልክቶች ላይ አንድ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ ያውም ራሱን በቻለ ክፍል፡፡ የአገራችን የፓርቲ ምልክቶች እንስሳት ቢሆኑ በሚል ሰፋ ያለ ምልከታ አቅርበው ይህ አሰራር በውጪ አገራት የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የእንስሶቹን የታወቁ ባህርያት በመውሰድ እንጂ የተሰጣቸውን ባህላዊ ታርጋ በማስቀረት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በዝምታ ውስጥ ማየት በሚለው ክፍል ውስጥ በባህላችን ልብ ሳንላቸው ስለቆየንባቸው ጉዳዮች ያጠይቃሉ፡፡ በአጥር የተቀጠረ ግቢ ውስጥ እንደምንኖር፣ በጋቢና በሹራብ የተሸፈነ ገላ ይዘን እንደምንዞር፣ ለአዲስ ሃሳብና ለለውጥ ዝግ የሆነ የተባ አእምሮ እንዳለን፣ ባህልና ወጎቻችን በአብዛኛው በሆድ የታጠሩ መሆናቸውን እንዲሁም በራሳችን ሲደርስ ብቻ የሰው ጉዳት እንደሚገባን በምሳሌዎችና ምክንያታዊ ሃተታዎች አሳይተውናል፡፡

መጽሐፉን በጥሞና ላነበበው ለጥቅስነት የሚበቁ በርካታ ሃሳቦችም አሏቸው፡ ‹‹ጀግኖቻችን በአብዛኛው ከጦር ሜዳ የተገኙ የሆኑበትና ልማት የሚያለማና የፍትሕ አስከባሪ ጀግና የሌለን …›› ይሉናል፡፡ ራስን መርገም በሚለው ክፍል ለምሳሌ ‹‹አንዳንዶች (አገሮችንና ሕዝቦችን ጨምሮ ማለቴ ነው) ከሌሎች የበለጠ የተረገሙ ላለመሆናቸው እጠራጠራሁ፡፡›› (99) ይሉናል፡፡ እንደ እርሳቸው እይታም ከሁሉ የሚያሳፍር እርግማን ራስን በራስ መርገም ይመስለኛል ይሉናል፡፡ በስሜት በመነዳት የእርሳቸው ትውልድ ራሱን መርገሙን ያነሳሉ፡፡ ለዚህም መድኃኒት ይሆን ዘንድ ራሳችንን እንመርቅ ፣ በሽማግሌዎችም እንመረቅ ይሉናል፡፡

በተቃውሞ የዘለቀ ትውልድ የሚለው የቅይጥ ክፍል የመጨረሻው ነው፡፡ ከ1960ዎቹ እስከ 2010 ድረስ ያለውን ትውልዳቸውን ያልተሳካለት በማለት ይገልጹታል፡፡ አሁን ያሉትን የትውልዳቸውን ሰዎችም በሦስት ይከፍሏቸዋል፡፡ በፖለቲካ ትግል የደከመ፣ በተፈጠረው ለውጥ ውስጥ ድርሻ እንዳለው የሚሰማውና አሁንም የፖለቲካ ሥልጣን የሚሻ እና ከፖለቲካ ዉጪ ስራ የሌለው በፖለቲካ ድርጅቶች ተጠልሎ መኖር የሚሻ በማለት ነው፡፡ ወጣቱም ከነርሱ ትውልድ እንዲማር መክረው በቅራኔና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመፈልፈል የሚዘልቅ ትውልድ አያስፈልግም ይሉናል፡፡ እነዚህ ከላይ በክፍል አንድ ያየናቸው ሃሳቦች ራሳችንን ቆም ብለን ለማየት ልንጠቀማቸው የሚገቡ ሁለገብ ትችቶች ሆነው ታይተውኛል፡፡ ደራሲው ከንባባቸው፣ ከትምህርታቸውና ከሕይወት ምልከታቸው ያጋሩን ሃሳቦች አገራዊ ፍልስፍናችንን እንድናይ፣ ከሌለን በጥሞና አስበንና ተመካረን እንድናዘጋጅ፣ በዕውቀትና በጥሩ እሳቤም እንድንመራ ይጠቅሙናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለዚህም እስካሁን የመጣንበት አስቸጋሪ መንገድ ትምህርት ሰጪ ነው፡፡

 

ሃሳብን በስንኝ

ክፍል ሁለት ‹‹ሃሳብን በስንኝ›› የሚለው የግጥሞቻቸው ክፍል ነው፡፡ ከግጥሞች ጋር ያላቸውን ቁርኝት ጅማሮ በክፍሉ መጀመሪያ ላይ ሲገልጹ የቤተክህነት ትምህርታቸው ያስገኛቸውን ጥቅም አንስተዋል፡፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ደራስያን የቤተክህነት ትምህርት እንዳላቸውና ያም ለሥነጽሑፍ ስራዎቻቸው ስንቅ እንደሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከእርሳቸው ሁኔታ ጋር የሚቀራረብ ታሪክ ያላቸው ባለቅኔው መንግሥቱ ለማ ናቸው፡፡ እርሳቸው የአማርኛ ግጥምን ከሁለት መስመር ግጥምነት አውጥተው ባለ ረጅም መስመሮች ያደረጉ መሆናቸውን በግለታሪካቸው ጽፈዋል፡፡ ለዚህም የቤተክሕነቱ ትምህርት ረድቷቸዋል፡፡ ደራሲና ገጣሚ ስንታየሁ ገብረጊዮርጊስ ሌላኛው መጽሐፋቸው ‹‹በረከት›› ለብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቀዳማዊ መታሰቢያ የተበረከተና መንፈሳዊ ግጥሞችን የያዘ ነው፡፡ አንዳንዶቹም መዝሙሮች ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ከገጣሚነትም በዘለለ ለመዝሙር የሚሆኑ ሃሳቦችን ያቀርባሉ ማለት ነው፡፡

ስለ ግጥሞቹ አጻጻፍ ሂደት ሁኔታም ጽፈዋል፡፡ ዓላማቸውንና ከአንባብያን የሚጠብቁትን ምላሽም እንዲሁ፡፡ ለማንኛውም ለህትመት የበቃ ስራ ስለሆነ ልዩ ልዩ ሃሳቦችን ሊያስተናግድ ይችላል፡፡ ብዛታቸው 49 የሆኑት ግጥሞች በዝርው ከቀረቡት ሃሳቦች ጋር ተቀራራቢ ግን ሰፊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ ገጣሚው በምናባቸው የሄዱበትን አብረን እንድንሄድ ያደርጉናል፡፡ የግጥሞቹን ቅርጽና ዝርዝር ሁኔታ ከዚህ ጽሑፍ ዳራ አንጻር አልገባበትም፡፡

በግጥሞቹም ሆነ በዝርው ጽሑፎቻቸው ያሉትን ዋና ዋና ሃሳቦች ከመጽሐፉ ርዕስ በ‹‹ዝምታ ውስጥ››ም ሆነ ከሽፋን ምስሉ ጋር ስናሰናስላቸው ዝም ያሉና በተመስጦ ያሉ አዋቂ  ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን እንታዘባለን፡፡ በሽፋን ስዕሉ ላይ የተካተተውና ከአሜሪካ ፎቶውን ያነሱት ጥቅሰ የማርቲን ኒሞለር ሲሆን፤ ሌሎች ሲጠቁ ዝም ማለት መጨረሻ ራስንም ለጥቃት ማጋለጥ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ በመጽሐፉ ጀርባ ገጽ የተካተተው ጽሑፍ መልካም ዝምታ ትምህርትን ለማፋፋት እንደሚጠቅም ገልፆ፤ በዝምታ ውስጥ በዕውቀት ለሰው ልጆች መልካምነት የሚሰሩ ምሁራን እንዳሉ ሁሉ በጩኸት ብዛት ለራሳቸው ጥቅም የሚሯሯጡና ካለ ዕውቀት ህዝብንም የሚጎዱ እንዳሉ አንስቷል፡፡ የትኛውን ዓይነት ሰዎች ነን ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያደርገን ሃሳብ ሲሆን ለጥያቄያችንም መልስ መጽሐፉ ውስጥ ያሉት ሃሳቦች መነሻ ይሆኑናል፡፡

ከደራሲው ጋር በግል ስናወጋ ነግረውኝ የነበሩት በጽሑፎቻቸው የሚያተኩሩባቸው ጭብጦች የ1940ዎቹና 1950ዎቹ ሥነጽሑፋችን ከሚያተኩሩባቸው ጋር የተመሳሳሉ መሆናቸውን ታዝቤ ነበር፡፡ መልካምነት፣ የአገር ፍቅር፣ ሐቀኝነትና ታላላቆችን ማክበር የመሳሰሉት ሲሆኑ ትውልዱ በምግባር እንዲታነጽ የሚያግዙ ሃሳቦች ናቸው፡፡ አሁን እነዚህን ጭብጦች ይዞ መጻፍ ትክክለኛ ሰዓቱ ነው ባይ ነኝ፡፡ ለምን ቢባል በየቀኑ ስለአገራችን የምንሰማው ወሬ ሁሉ ከምግባር ምህዋሯ መውጣቷን የሚያሳይ ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹እስኪ ማታ ስትተኛ አስብበት፤ እያደረግህ ያለው ነገር ትክክል አይደለም እኮ!›› ተብሎ በአንድ ሽማግሌ የተመከረ የሞጃ ሰው በመኝታው ላይ ሆኖ አስቦበት ተለውጧል፡፡ እኛም ደራሲው እንደሚሉት አንብበን በዝምታ ውስጥ አስበን ወደ መልካም ሰውነት እንለወጥ በማለት ልሰናበት፡፡ 






ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...