ሐሙስ 5 ሜይ 2022

የጉዞ ማስታወሻ

 


ሚያዝያ 27፣ 2014

በመዘምር ግርማ

 


የዛሬው የጉዞ ማስታወሻ በጎበኘናቸው ስፍራዎች ሳይሆን ከእስከዛሬው ለየት ባሉና የሁላችንንም ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ይሆናል፡፡ የጽሑፉም ሁኔታ እኔ እጀማምረውና ሌሎች ተጓዦች የሚጨምሩበትና እናንተም አንባቢያን የምታስፋፉት ይሆናል፡፡ ከዚያም በተለይ መደረግ ባላባቸው ነገሮች ላይ ተግባራዊ ስራ ብንሰራ ደስተኛ ነኝ፡፡ እናንተም ደስተኛ የምትሆኑ ይመስለኛል፡፡

የመጀመሪያው የጉዞ ሰዓት መዘግየት ነው፡፡ ማለዳ 12፡30 ከአዲስ አበባ ለመነሳት ያሰቡት ተጓዦች 1፡00 መነሳታቸው ደብረ ብርሃን መድረሳቸው በመዳረሻ ቦታችን የነበረው ዝግጅት ከጀመረ በኋላ እንድንደርስ አድርጎናል፡፡ ለወደፊቱ የዝግጅቱ ዝርዝር መርሐግብር ተሰርቶ ሁሉንም ዝግጅቶች በሰዓታቸው ብናደርግ የሚል ዕይታ አለኝ፡፡ በእርግጥ እነ ጋሽ ጥላሁን ጣሰው አዲ አበባ ብሔራዊ ቲያትር ለሚካሄደው ‹ተከፍልናል› ለተባለው የሜላት ዳዊት ዘጋቢ ፊልም ምርቃት ተመልሰው መሄዳቸው፣ እኛ የቤተመጻሕፍቱ ሰዎች ለሳምንታዊው የሐሙስ ምሽት ዝግጅት ደብረብርሃን መድረሳችንና ማህደረ ሸዋዎች አዲስ አበባ ገብተው ማደራቸው የውሎገባ ዝግጅት መሆኑ ድንቅ ነው፡፡ ለወደፊቱ ብዙ ሰው በዚህ መልኩ ሊሳተፍና የፈለገም በዋዜማው ሊሄድ ወይም በማግስቱ ሊመጣ ይችላል፡፡ ጨምሩበት፡፡

በመኪና ውስጥ ያለውን ጊዜ ለማንበብና ለውይይት መጠቀማችንን ወድጄዋለሁ፡፡ ሁሉም ተጓዥ የተመደበለትን ክፍል አንብቦ ለጥንድ ውይይትም ሆነ ለሁሉም ተሳታፉ ማቅረቡ አንድን መጽሐፍ በአጭር ጊዜ ለመወያየት ሁነኛ መንገድ ነበር፡፡ ስንመለስ የተካሄደውንም ጥሩ ውይይት እመለስበታለሁ፡፡

ለበዓሉ ከማህደረሸዋ፣ ከራስ አበበ አረጋይም ሆነ ከወረዳው የተደረገው ዝግጅት ቆንጆ ነበር፡፡ ከራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት እንደ እስከዛሬ አባላትን መዝግበን በርከት ብለን መኪና ተከራይተን አለመምጣታችን አንድ ጉድለት ነው፡፡ ማህደረ ሸዋ ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጋር ተነጋግሮ መኪና ስላስመደበ በዚያ ስምንት ሰዎች ልንሄድ ችለናል፡፡ ከወረዳውም በኩል ሰራተኞችን በሁለት መኪናዎች ማጓጓዛቸውና ማሳተፋቸው፣ የዕለቱን ዝግጅት በባለቤትነት መምራታቸው፣ የምሳ ግብዣ ማድረጋቸው ከብዙ በጥቂቱ የሚያስመሰግን ነው፡፡  ጥቃቅንና ለወደፊቱ ልናሻሸሽላቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የማይክራፎን ጉዳይ፡፡ ሌላ ደግሞ ቦታውን በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሞ ሁሉም ሰው ጥግ ላይ ተቀምጦ፣ አንድ መድረክ አዘጋጅቶ ለቀረጻም አመቺ ስፍራ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡

ከእስካዛሬው ለየት ያለው የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ያሳየው የባለቤትነት ስሜት ነው፡፡ የዚህም አንዱ ማሳያ የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ አባሉ ደራሲ ጥላሁን ጣሰው በራሳቸው መኪና ቤተሰባቸውን ይዘው በዝግጅቱ መሳተፋቸው ነው፡፡ በስፍራውም ስለታሪካችን ትምህርት ከሰጡን በኋላ በስፍራው ማህበሩ ስላሰበው ልማት ገለጻ አድርገዋል፡፡ ለዚህ ለወደፊቱ የኛም አስተዋሽነት አስፈላጊ ነው፡፡ ደራሲ ጥላሁን በአዲስ አበባ መሳተፍ ሲጠበቅባቸው ከእኛ ጋር በአንዲት ግራር ማክበራቸው ማህበሩ ለተመሰረተበት ቦታ ያለውን አክብሮትና ውለታ ያሳያል፡፡ ሌላም የማህበሩ አባል እኛ በነበርንበት መኪና ነበሩ፡፡ ብዙ ታሪክም ነግረውናል፡፡ ስለ ወደፊት ስራዎችም አውግተናል፡፡ ማህበሩ መኪና መመደቡም ትልቅ ውለታና አስተዋሽነት ስለሆነ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ይህም ለሌሎች አርአያ ነው፡፡ ለምሳሌ ከዓመታት በፊት ምኒልክ ዘኢትዮጵያ የጉዞ ማህበር፣ ደብረብርሃን ከቤተመሕፍቱ ለምንሄድ 30 ሰዎች የጉዞ ወጪ ሸፍኖልን ነበር፡፡  

ሌላው በስፍራው በበዓሉ አከባበር ላይ የታየው የፋኖና የአካባቢው ህዝብ ተሳትፎ ያላቸውን የአገር ፍቅር የሚያሳይ ነው፡፡ በዛሬው ዕለት ግማሹ የወረዳው አመራር የአራት ሚሊሻዎችን ቀብር ለማስፈጸም ስለሄደ እንዳልተገኘ ተነግሮናል፡፡ ስለዚህ አሁንም ያልተረጋጋ ሁኔታ እንዳለ ማየትና ከታሪክ አስተዋሽነት በላይ ማሰብ አለብን፡፡ ምናልባት የተጎዱትን ሚሊሻዎች ቤተሰብ እንዲሁም የቆሰሉትንም ለመደገፍ ሃሳብ ያለው ካለ የወረዳውን ኃላፊዎች አድራሻ እሰጣለሁ፡፡

በሰላድንጋይ ከተማ ከተካሄደው ውይይት የያዝናቸው ብዙ ነጥቦች ቢኖሩም በወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቤተመጻሕፍት አገልግሎት እየጀመሩ ስለሆነ መጽሐፍ እንድንለግስ የጠየቁን ነው፡፡ በመልስ ጉዟችን በመኪና ውስጥ

ስንወያይ ተጓዦች ለመለገስ የሚችሉትን መጽሐፍ ቃል ገብተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በየግላቸው ከሚያውቋቸው ሰዎችም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እንዲየሰባስቡ ተነጋግረዋል፡፡ ስለዚህ እኔም ያንኑ ጥሪ ተቀብዬ ከግሌ ሰላሳ መጽሐፍ ለመስጠት ቃል ገብቻለሁ፡፡ ይህም ዛሬ ለትምህርት ቤቶቹ ከሰጠኋቸው ሰላሳ መጻሕፍት በተጨማሪ ነው፡፡ ከዚያ በዘለለ እናንተ አንባብያን እንድትሰጡ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ለዚህም ጉዳይ ብትጠይቁኝ ዝርዝር ሃሳቡን ለማጋራት ዝግጁ ነኝ፡፡

 መዘምር ግርማ

ደብረብርሃን

እንኳን ለድል ቀን አደረሰን!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...