2024 ጁን 11, ማክሰኞ

ጓደኛዬ ከሃያ ዓመታት በኋላ

 ጓደኛዬ ከሃያ ዓመታት በኋላ

አህመድ መሐመድ ሰዒድ የደብረብርሃን ልጅ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሩቅም ነው። ከአርጎባ ሙስሊም አባትና ከተጉለት ክርስቲያን እናት ይወለዳል። በተለይ የማስታውሰው በስድስት ኪሎ የ505 የተማሪዎች መኖሪያ ህንፃ ቲቪ ሩም ዜናና የ1997 የምርጫ ክርክር ስንከታተል ነው። እኔን አንድ ዓመት ይቀድመኛል። በምርጫው ሰሞን ጠፋ። የት ሄደ ብዬ ሰጋሁ። ደብረብርሃን መጥቼ የቤተሰቦቹን ቤት ፈልጌ አገኘሁት። በብርድልብስ ተሸፋፍኖ ተኝቶ አልገለጥም አለኝ። ሕመሙ የአእምሮ ነው አሉ። አዝኜ ተመለስኩ። 1997 እና 1998ን አርጎቦች ዘመዶቹ ጋር ገጠር ሄዶ ቆየ። መድሐኒቱንም ይወስዳል። በዘመድ ሲታገዝና በአማኑኤል ሆስፒታል ሲታከም ቆይቶ ስላገገመ በ2000 ዓ.ም. ሁለተኛ መንፈቀ-ዓመት ተመልሶ ዩኒቨርስቲ ገባ። በ2002 ተመረቀ። ሁለት ዓመት ሥራ ሳይቀጠር ደብረብርሃን ቆየ። በስራአጥ ተደራጅቶም ነበር። አባቱን በሥራ ያግዝ ነበር። በ2005 ዓ.ም. በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ጋቸኔ ተቀጠረ። እስካሁንም በዚያው እየሠራ ነው። በዚህ ዓመት አንድ ቀን አባቱን ደብረብርሃን መንገድ ላይ አገኘኋቸው። ስለደህንነቱም ጠየኳቸው። ለህክምና ቀጠሮ ስለሚመጣ እደውልልሃለሁ አሉኝ። እርሳቸው ሳይደውሉልኝ እኔ ደውዬላቸው አገኘሁት። ተገናኝተን ብዙ አወራን። ስልክ አልያዘም። የለውም። ጓደኞቻችንንም እያነሳሳን ቆየን። እቤታቸውም ሄድኩ። ቤተሰቦቹም ተደሰቱ። ህመሙ ስኪዞፍሪኒያ የሚባል የአእምሮ ህመም መሆኑን ነግሮኛል። በቀንም ሆነ በህልሜ የሚመጣብኝ ድምፅ አለ ይላል። እንደሱ ገለጻ ጆሮው ላይ ይንሽካሾካል። በዓይኑ ይታየዋል። ይሳደባሉ ይላል። ሥራ ቦታው ተስማምቶኛል ባይ ነው። ጋቸኔ ማታ ሲደብረኝ ወጣ ብዬ እዝናናለሁ፣ ቴሌቪዥን አያለሁ፣ ከዚያ ተመልሼ እጽፋለሁ ይላል። ሬዲዮም ያደምጣል። በሬዲዮ ዜና፣ መዝናኛና የሰዎችን ታሪክ እሰማለሁ ይላል። መጻሕፍት ስላሉ የሚያሳትምልኝ ባገኝ የሚል ሐሳብ አንስቶልኛል። በኔ ሃሳብ ግን ቀዳሚውና አንገብጋቢው ጤናው መመለሱ ላይ መሰራት አለበት የሚል ነው። ይህን ጽሑፍ ጽፌ አነበብኩለት። እንድለጥፈውም ፈቅዶልኛል።


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ማዕበሉ የማይወስዳቸው ጥቂቶች

  ማዕበሉ የማይወስዳቸው ጥቂቶች መዘምር ግርማ መስከረም 7፣ 2017 ዓ.ም. ደብረብርሃን   ልመና ዛሬ አንድ አረጋዊ ቤተመጻሕፍት መጥተው በር ላይ ቆሙ፡፡ እኔም እንደተለመደው ‹‹እግዚአብሔር ይስጥል...