የዕለት ውሎዬ፣ የዓመቱ አከራረሜና የትውልዱ ዕጣፈንታ
መዘምር ግርማ
ማክሰኞ ሐምሌ 2፣ 2016 ዓ.ም.
ደብረብርሃን
ዛሬ ከደብረብርሃን ወደ ባቄሎ መስመር ሄጄ ነበር። ልጆች ከደብረብርሃን ወደ ባቄሎ አስር ኪሎሜትር በእግራቸው ሲጓዙ አገኘኋቸው። አንደኛው የቤተመጻሕፍት ወዳጆቼ ያሰፉለትን ዩኒፎርም ለብሶ ወደ ባቄሎ ሲመለስ በርዮ ላይ አገኘሁት። ከሁለት ሌሎች ልጆች ጋር ነው። ወደ ደብረብርሃን የሄዱት ቁራሌ ለመስራት መሆኑን፣ ማለትም የዉኃ መያዣ ላስቲክ ለቅመው ለመሸጥ ቢሆንም ስላላገኙ በእግራቸው እንደሄዱ በእግራቸው እየተመለሱ መሆኑን ነገሩኝ። ተሰናብቻቸው ሲሄዱ ጠርቼ ስኳር ድንች ገዛሁላቸው። ምናልባት መሳፈሪያ ብሰጣቸው ይሻል ነበር። ደብረብርሃን ቶሎ መመለስ ያለብኝ አንድ ወዳጄ የቲያትር መጽሐፍ ፈልጎ ጠርቶኝ ነው። ተመልሼ ቤተመጻሕፍት ገብቼ ሳዋራው ሁለት ተፈናቃዮች ልጆች ገቡ። ሰሌዳውን አጽድተው መጻፍ ጀመሩ። ከግማሽ ሰዓት ገደማ ቆይታ በኋላ ወዳጄ ወደ ቤቱ ሲሄድ አንደኛው ልጅ የሳለውን ስዕል አየሁ። የወንድና ሴት ሥዕል ነው። ምናልባት የቤተሰብን አብሮነት የሚያሳይ ይሆን? እናትዮዋ ጥላ አጥልታ ያሳያል። ምናልባት አባቱ ወለጋ ሰው ሲገደል አይቶ አእምሮውን እየታመመ በመድኃኒት እገዛ ስለሚኖር እናትዮዋ የቤቱ ምሰሶ መሆኗን ለመግለጽ ይሆን? በአራት ዓመቱ እየታዘለ የሚኖረውን የአእምሮ ዕድገት ዝግመት ያለበትን ወንድሙን፣ ያለ ዕድሜዋ የተዳረችውን እህቱን ችግር ተሸክማ የምትኖረውን እናቱን ጥንካሬ ለማሳየት ይሆናል። እሱ ግን ወደ ባቄሎ ካምፕ እምብዛም አይሄድም። ምናልባት በደብረብርሃን የጎዳና ተዳዳሪ የመሆን ዕጣፈንታ ይጠብቀው ይሆናል። በበጋው የቤተመጻሕፍታችን የትምህርትና ምገባ ዝግጅት የትምህርት ጊዜ ሲሆን መምጣትን የሚጠላ፣ ትምህርትንም ጭምር የሚጠላ የሚመስል ልጅ ነው። እኔ ብዙውን ጊዜ ቤተመጻሕፍት ተፈናቃዮች ልጆችን በማስተማር ብቻዬን ከመሥራቴና ከሃምሳ በላይ ልጆችን ከማስተናገዴ አንፃር የተለየ እገዛ ወይም ትኩረት ለሚፈልጉ ልጆች ጊዜና ትኩረት አልሰጥም። ትኩረቴ ብዙኃኑ ላይ ነው። የሚያጠፉትንም እቆጣለሁ። ሲብስም ቤተመጻሕፍቱንም ለቀው እንዲሄዱ አደርጋለሁ። አንድ ቀን አንድ ከዚያን ቀን በፊት አይቼው የማላውቀውን ልጅ ከሌሎች ልጆች ጋር ምግብ በትሪ እንዲመገብ ካንዱ ጠረጴዛ አስቀመጥኩት። አልተስማማውም መሰለኝ አለቀሰ። ወደ ሌላም ቡድን ቀየርኩት። አለቀሰ። በል ካልተስማማህ ውጣ ብዬ ወደ ዉጪ አስወጣሁት። ደግነቱ ሁለት በጎፈቃደኞች (ፅዮንና ታምሬ) ዉጪ ስለነበሩ አባብለው አምጥተው ለብቻው በሳህን ተሰጥቶት በላ። በኋላም ደስ ብሎት ሄደ። ችግሩን አናውቅም። ለመጠየቅም ጊዜ የለንም። ምናልባት ወላጅ አልባ ይሆን? ከቤቱ ዉጪ በልቶ አያውቅ ይሆን? ከዚያ ቡድን የተጣላው ልጅ ይኖር ይሆን?
ወደቀደመው ልጅ ስመለስ ትምህርት ሳትማር ለምሳ ለምሳ የምትመጣ ከሆነ እንዳትመጣ ብዬ ነግሬው ነበር። ሌሎችም እኔም በጎፈቃደኞቹም ተው ያልነው ጥፋቶች አሉበት። ሳልረዳ ወይም እሱ ሳያስረዳኝ ውሳኔ ላይ ደርሼ ይሆናል። በወቅቱ ያን ያልኩት ለሱ በማሰብ ቢሆንም ምናልባት ተሳስቼ ይሆናል። የበጋው ዝግጅት ሊያልቅ አንድ ቀን ሲቀረው በእናቱ ስልክ ደውሎ ቅዳሜ መምጣት ይችል እንደሆነ ጠየቀኝ። ፈቀድኩለት። ልጆች በልተው ከሄዱ በኋላ መጣ። ቀሪ እንጀራ ስለነበረን በላ። ከባቄሎ ስለሚመጣና መኪና ስላላገኘ እንደመሸበት ነገረኝ። ብዙውን ጊዜ መንገድ ላይ ሲዞር ቢያሳልፍም በፊት በፊት እናቱ ደብረብርሃን ካምፕ ሳለች ልጅ ሲጠብቅላት ከቤተመጻሕፍት እንደሚቀር ጓደኞቹ ሳይነግሩኝ አልቀሩም። ምንም ብለው ግን እርግፍ አድርጎ አይቀርም። በዚህ ዓመት ህዳር አካባቢ መጀመሪያ የተዋወቅሁት ተፈናቃይ ልጅ እሱ ነው። የትውውቃችንም ምክንያት በቤተመጻሕፍት ደጅ ሲያልፍ ጠርቼው ነው። በእሱ ምክንያት ብዙዎችን አወቅሁ። ከማወቅ በዘለለም ለማስተማርና ለማስነበብ እየሞከርኩ ነው። ይህ ባለታሪኩ ልጅ የበጋው ትምህርት የመጨረሻ ቀን የመጣ የመጨረሻው ልጅ ስለሆነ ቤተመጻሕፍት ፊትለፊት ካለ ሻይ ቤት ሻይ ጋበዝኩት። ለዉሱን ደቂቃዎች እኔን የማናገር ዕድል ሲያገኝ እናቱ በችግር ውስጥ እንዳለች ነገረኝ። የምትፈልገው ደግሞ ቤተሰቧን የምትመግበው ነገር ለማግኘት የሚያስችል ሥራ መጀመር ነው። መልዕክቱን አደረሰ። የፈለገችውን ገና አላገኘሁላትም። ስልኳን ለአንድ ወዳጄ ሰጥቻለሁ። ልጁ አብሮት የሚዞር ጓደኛም አለው። ጓደኛው ደግሞ መስማት የተሳነው ነው። መስማት የተሳነው ልጅ አባቱ ነቀምት በእስር ላይ ይገኛል። የእስሩ ምክንያት ለምን ሰፈራችሁን ከጥቃት ተከላከላችሁ የሚል እንደሆነ ሰምቻለሁ። ሁለቱም ልጆች ከተማውን ሲዞሩ ይውላሉ እንጂ ትናንት ለጀመርነው የክረምት ትምህርት ፍላጎት አላሳዩም። እያንዳንዱ ልጅ የየራሱ ታሪክ አለው። እኔ በተለያዩ መርሐግብሮች በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩ ልጆችን አይቼ ይህን ካልኩ በየካምፖቹ የሚሰሩት ወገኖች ብዙ ጥልቅ ምልከታ ይኖራቸዋል። ከተፈናቃዮቹ ጋር ለአንድ ዓመት ያህል አብሮ እንደቆየ ሰው በእኔ አረዳድ በወለጋ የሚኖሩ አማሮች በአጠቃላይ ዘላቂ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረው ኑሯቸው ሕይወታቸው እንዲቀጥል ያህል አርሰውና ሰርተው እንዲበሉና እንዲኖሩ እንጂ በቋንቋቸው ተምረው፣ በየመሥሪያ ቤቱ ሰርተው፣ መርጠው፣ ተመርጠው ዕጣፈንታቸውን እንዲወስኑ አይደለም። ተምረው ኮሌጅ የመግባት፣ ስለ ዓለምና አገራቸው ሁኔታ የማንበብና የማሰላሰል ዕድላቸው በጣም የመነመነ ነው። አንድ ማህበረሰብ ደግሞ ከውስጡ የተማረ ከሌለው ዕድሉን የሚያቃና አይሆንም። የመጣ የሄደው ዕድሉን ይወስንለታል። ለምሳሌ ተሳደው ወደ ደብረብርሃን ለመምጣት የቻሉት ዕድላቸው በካምፕ ውስጥ በችግር፣ በረሃብና በአእምሮ ጭንቀት ሕይወታቸውን መግፋት ነው። ወደዚህ ለመምጣት ያልታደሉና አካልና ሕይወታቸውን ያጡትን ቤት ይቁጠራቸው። እዚያ የቀሩትንም ሁኔታ አናውቅም። ደብረብርሃን ከመጡ በኋላ ወደ ወለጋ እንዲመለሱ ከተደረጉትም የብዙዎቹ መጨረሻ እዚያው ባሉ ካምፖች ውስጥ ነው። በወለጋና ኦሮሚያ ተብሎ በተከለለው ቦታ የመጤና ነባር አስተያየትና የባለሃገርነት ንፍገት ሲገጥማቸው እንደቆየ ይሰማል። ይህ ትርክት መታረም ይችል ይሆን? ለመሆኑ የኢትዮጵያና የትውልዱ የወደፊቱ ዕጣፈንታስ ምን ይሆን? ስለ አሜሪካ ሰሞኑን እያነበብኩት ካለሁት የባራክ ኦባማ ግለታሪክ 'A Promised Land' እንዲሁም ከሌሎች መጻሕፍት የተገነዘብኩት ዓይነት አንድ ሰው በማንነቱ ሳይሆን በችሎታውና በሥራው የሚወዳደርና የሚዳኝበት ጊዜስ በኢትዮጵያ ይመጣ ይሆን?
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ