ሐሙስ 29 ኦገስት 2024

ከኮርያውያን ጋዜጠኞች ጋር

ወደዚህ የሚመጡበት ጉዳይ ነበራቸው። አብሯቸው የመጣው ወዳጄ ደብረብርሃን እንዳለሁ ስለተረዳ ሻይ ቡና እንበል አለኝና አገኘኋቸው። ኮሪያውያን ናቸው። ደቡብ ወይስ ሰሜን የሚል ጥያቄ ስጠይቃቸው "ደቡብ" ያሉት በኩራትና ሰሜንን በመጠየፍ ዓይነት ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንግሊዝኛ ዲፓርትመንት አብረውን የተማሩት ወጣቶቹ እነ ኦቾልሚን ግን ይህን ጥያቄ ሲጠየቁ "አንድ ኮሪያ" ይሉ ነበር። እነዚህ ምናልባት አዋቂዎች ስለሆኑ፣ ሥራ ስለያዙ፣ እርስበርሳቸው ስለሚጠራጠሩ ይመስለኛል ሰሜን የሚለውን እንደማይወዱት ለማሳየት ይሞክራሉ። ወይም ያስመስሉ ይሆናል። የክፍል ጓደኞቼን ምላሽ አስታውሼ ምናልባት ወደፊት አንድ አገር ትሆኑ ይሆናል አልኳቸው። አንደኛው እንደማይሆኑ ነገረኝ። 

"ይሁኑ ቢባል እንኳን የሐብት ልዩነቱ እጅግ ተራርቋል" ሲል ሞገተኝ።

"ምስራቅና ምዕራብ ጀርመን አንድ ሆነው የለም!" አልኩት። 

"ከምስራቅ ጀርመን በጣም የራቀ ኋላቀርነት ላይ ናቸው እነዚህ" አለኝ።

ይሁን ብዬ ጨዋታውን ባጭር ቀጨሁት። ብገፋበት ይህን የተስፋፊነት አባዜህን አቁምልኝ የሚለኝ መሰለኝ።

ከኮሪያ ወደ አፍሪካ ብቸኛው አየር መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሆነ ገልፀውልኝ ሞዛምቢክን መጎብኘትን የሚጨምረው ጉዟቸው በአንድ ሰው የደርሶ መልስ ሦስት ሺህ ዶላር እንደከፈሉ ነገሩኝ። ከአዲስ አበባ ወደ ኮሪያ ደርሶመልስ ከአየር መንገዱ ሳጣራ 200,000 ብር ገደማ ይላል። ከኮሪያ ወደ አፍሪካ ካለው እርቀት ጋር ተመሳሳይ እርቀት ወዳለው ወደ አውሮፓ መጓዝ ግን አማራጭ ስላለ በጣም እንደሚቀንስ ነገሩኝ። አማራ ክልል ወይም ደብረብርሃን ላይ የእስያ ሰው ነጋዴና ኢንቬስተር ስለሚመስል ጋዜጠኛ ናቸው ብሎ ማንም አያስብም። ቢያስብም ችግር የለባቸውም። የካሜራና መቅረፀድምፅ ጋጋታ የለባቸውም። አንዲት የፂም መላጫ የምታክል ቪዲዮ ካሜራ ነች የያዙት። የአዲስ አበባዎቹን የዉጪ ሬዲዮ ሪፖርተሮች እንኳን ብታዩ ትልቅ ማይክ ከኮታቸው ኪስ ጎስረው ሲሄዱ ጋዜጠኞች መሆናቸው ያስታውቃል። የዘመኑ ቴክኖሎጂ መራቀቅና የካሜራቸው ማነስ እኔንም ወዳጄንም አስገርሞናል። እነዚህ ሰዎች ለሁለት ለጉዞ እንኳን 6000 ዶላር ከፍለው፣ በዚያ ላይ ለሆቴል፣ ለአበል፣ ለመኪና ኮንትራት ስንት እንደሚከፍሉ አሰብኩት። ከኮሪያ ጋግነም ስታይልን እንደምወደው ነገርኳቸው። 5.2 ቢሊዮን ጊዜ በዩቱብ የታየ ሙዚቃ ሲሆን ዘፋኙ Psy ይባላል። ሌላ ጀንትልሜን የሚል ቪዲዮውን አሳዩኝ። ለጋግነም ስታይል የተሠራውን ሐውልት አሳዩኝ።  ከዚህ ጽሑፍ ጋር አያይዤዋለሁ። ደቡብ ኮሪያውያን የክርስትና እምነትን መቀበላቸውን የሚያሳብቁ ነገሮች አሏቸው። አንደኛውን ከነዚህ ሰዎች አየሁ። ልብሳቸው 'Press' ከሚል የተለመደ የሚዲያ ሰዎች ልብስ ይልቅ 'World Vision' የሚል መሆኑ አስገርሞኛል። ጥያቄ አልጠየኳቸውም። ደብረብርሃን ወደሚገኘው ሰሜን ኮሪያ አረቄ ቤት ወዳጄ በመኪናው ወሰደንና በደጁ አለፍን። ምክንያቱም ደቡብ ኮሪያውያኑ ለመግባት አልፈለጉም። ፍርሃታቸው አይጣል ነው። ሰሜን ኮሪያ እንዴት አስቸጋሪ አገር እንደሆነች አንድ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ወደዚያ ተጉዞ ሪፖርተር ላይ የጻፈው ማስታወሻ ስላለ እዩት። 

ከብዙ በጥቂቱ ይኸው ነው።



ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...